Monthly Archives: July 2012

ፎንቱ ፎኒፍ ሪፈታ ጄናን ኢቲሌን ጂቢቻ ቲ ካቴ ("ስጋ ለስጋ ይደነግጣል ቢባል ጥጃ እንኳ በቁርበት ደነገጠች")

“አገሬ፣ አገራችን ኢትዮጵያ ነች። እንደ ኢትዮጵያዊ እንከራከራለን። ኢትዮጵያ መኖር አለባት። ሁላችንም የኢትዮጵያ አባል መኾን አለብን ብዬ ነው የማስበው።”
“የኢትዮጵያ አንድነት እና ነፃነት፣ እኩልነት ከተጠበቀ፣ በተፈጥሮ ሃብት የተደላደለች፣ በታሪኳ የገነነች፣ ኢትዮጵያ ሳትከፋፈል እና ሳትቆራረስ ለዘላለም እንድትኖር፣ የጎሳ ልዩነት ሳይደረግ በኢትዮጵያ ውስጥ የተወለደ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ኢትዮጵያዊነት ግዴታው እና መብቱም ነው ብዬ አምናለሁ፡፡”
 “I am so humbled and am forever grateful to our ancestors; no matter what mistakes they committed, they resisted all the colonizing powers in a way that made them create a history and logo that branded Ethiopia as the very idea of the decolonizing imagination.”
የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎች [ኢ-መደበኛ] ቡድን አባል መሆኔ በዚህ ዓመት ከተከሰቱልኝ ምርጥ እውነታዎች ውስጥ በጣም ጠቃሚው ነው፡፡ ቡድናችን ‹‹የንባብ ፕሮግራም›› የተሰኘ በአንድ ርዕሰ ጉዳይ፣ አንድ ጽሑፍ ላይ ተመስርቶ በተወሰነ የጊዜ ዝላይ (Time Interval) መወያየት ጀምሯል፡፡
ይህ ጽሑፍ የዚህ ‹‹የንባብ ፕሮግራም›› ትሩፋት ነው፡፡ በእንዳልክ መራጭነት ‹‹Oromo Narratives›› የዶ/ር ዶናልድ ሌቪን ጥናት ላይ ለመወያየት ተጠራርተን ተገናኘን፡፡ ርዕሰ ጉዳዩ የኦሮሞ ብሔረሰብ የፖለቲካ ጥያቄዎችና አማራጭ መልሶች ላይ በጥቅሉ የሚያጠነጥን ነበር፡፡ በጉዳዩ ላይ የጠለቀ እውቀት ለሌለው ለእንደኔ ዓይነቱ ልብን በብርሃን የሚያጥለቀልቅ (enlights) የንባብና የውይይት ፕሮግራም ነበር፡፡ ይህንን ሳያካፍሉ መቅረት ስስት ነውና፣ ባይሆን እየቆነጠርኩ ላካፍላችሁ፡፡

የብሔረሰቦች ጥያቄ ቢያዳፍኑት የማይጠፋ፣ ቢያቀጣጥሉት የሚፋጅ፣ አይነኬ ጉዳይ ይመስለኝ ነበር፡፡ እርግጥ አላዋቂ አራጋቢ ሲያራግበው – ሰደድ እሳትም ቢሆን ማስነሳቱ አይቀርም፡፡ ነገር ግን የማይነካ ጉዳይ አድርጎ ማሰብ የተሳሳተ ነው፡፡
የኦሮሞ ብሔረሰብ ጥያቄዎች ከማንነት እና እሴት እስከ ኤኮኖሚ፣ እስከ አስተዳደራዊ እና አመራር ሚናዎች ድረስ ሁሉንም ያካልላሉ፡፡ እኛም ጨረፍ፣ ጨረፍ እያደረግን እንመለከታቸዋለን፡፡ መጀመሪያ ወደመጀመሪያው!
ከታሪክ በማንኪያ
የገዳ ስርዓት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በዘመናዊነት ተቃኝቶ ሊተገበር የሚችል ብቸኛው አገርበቀል ትውፊታዊ የፖለቲካ ስርዓት ነው፡፡ ስርዓቱ ለአምባገነናዊነት በማይመች መልኩ የገዢዎችን መደብ የስልጣን እና ዘመነ ስልጣን የሚገድብበት ደንብ ያለው፣ የወላጆችና ልጆች ትውልድ ክፍተትን የሚያስታርቅበት እና ትውልዶች በየዕድሜያቸው እርከን የአስተዳደር/አመራር ልምድ የሚያዳብሩበት አካሄድ ያለው፣ ከአምልኮጋ ግንኙነት የሌለውና (it indeed has a religious element, the good thing is that the Geddaa system explicitly differentiates the two and the leadership of ritual and the political spheres) ሲያጠፉ የሚከሰሱበት እኩልነትን ማስፍን የሚችል የሕዝባዊ አስተዳደር ስርዓት ነው፡፡ የገዳ ስርዓት በዘር የሚሾሙ (የዕድሜ ልክ ) እና በምርጫ የሚሾሙ (ቢበዛ የ8 ዓመት) መሪዎች ይኖሩታል፡፡ በቀላሉ ሊሻሻሉ ከሚችሉት ድክመቶቹ (ለምሳሌ፤ ሴቶችን አሳታፊ አለመሆኑና ከዘውዳዊነትጋ የሚመሳሰልበት አካሄድ መኖሩ) በስተቀር ራሱን የቻለ ወጥ የዲሞክራሲያዊ ፖለቲካ ስርዓት ፍልስፍና ነው፡፡ ለዝርዝሩ ይህንን(አውርዳችሁ) ወይም ይህንን (ባለበት) እንድታነቡት እየጋበዝኩ የኦሮሞን ብሔረሰብ ወደመላው ኢትዮጵያ አካባቢዎች የመሰራጨት ታሪክ በአንድ አንቀጽ እወጣዋለሁ፡፡
ከ16ኛው ክፍለዘመን ወዲህ የኦሮሞ ሕዝቦች ወደሰሜን፣ ምስራቅ እና ምዕራብ በመሰራጨት እንደአሁኑ በመላው የአገሪቱ ክልሎች ውስጥ ለመገኘት በቅተዋል፡፡ የኦሮሞ ብሔረሰብ አባላት ባላቸው በቀላሉ የመዋሃድ እና የመወዳጀት ችሎታ ምክንያት በመላው ኢትዮጵያ በሚስፋፉበት ወቅት በሰሜን ኢትዮጵያ ክርስትናን፣ በምዕራብ ኢትዮጵያ እስልምናን ተቀብለዋል፤ በደቡብ ምዕራብ መንግስት ሲያቋቁሙ፣ በሸዋ ደግሞ አርሶአደር ማኅበረሰብ መስርተዋል፡፡
እዮኣስ (የንጉሥ የበካፋ የልጅ ልጅ) ግማሽ የኦሮሞ ብሔረሰብ አባል የሆነ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ንጉሥ ነው፡፡ ሦስት ሺህ የኦሮሞ ተወላጅ ወታደሮችም ነበሩት፡፡ ከዚያ በኋላም በኢትዮጵያ የነገሥታት ታሪኮች ውስጥ የኦሮሞ ደም ያላቸው የጎጃም ንጉሥ ተክለሃይማኖት፣ ዳግማዊ ምኒልክ፣ እቴጌ ጣይቱ ብጡል፣ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ እና እቴጌ መነንን ጨምሮ በርካታ የንጉሣዊ ቤተሰብ አባላት ነበሩ፡፡
የኦሮሞ ብሔረሰብ ጥያቄዎች
የኦሮሞ ሕዝብ ከሁሉም ብሔረሰቦች ቁጥር በላይ ቢበዛም ‹‹የሁለተኛ ደረጃ ዜጋ›› ሁኗል ብለው የሚከራከሩት ብዙሐን ናቸው፡፡ በአመራር ደርሻ ከፍተኛ ሚና የነበራቸው አማሮች እና ትግሬዎች (‹‹አቢሲኒያዎች››) ‹‹የመጀመሪያውን ደረጃ›› ይወስዳሉ ነው ምሬቱ፡፡
ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የምታገኝበት ቡና እና አሁን ገቢው እያደገ የመጣው የወርቅ ማዕድንም የኦሮሚያ ምድር ፍሬዎች ናቸው፡፡ ሆኖም ኦሮሚያ በኢኮኖሚ የሚገባትን ያህል አልተጠቀመችም የሚል ሌላው የኦሮሞ ብሔረሰብ ተወላጆች ዐብይ ጥያቄ ነው፡፡
መፍትሔዎቹስ?
ብዙሐኑ ነጭ በሆነበት አሜሪካ ጥቁር ፕሬዚደንት ሲመረጥ ‹‹ለውጥ መጣ›› ልንል እንችላለን፤ ሌላውን ስርዓቱ ይሰራዋልና፡፡ የኦሮሞ ብሐየረሰብ ተወላጅ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ቢመረጥ ግን እንዲህ በቀላሉ የኦሮሞ ተወላጆች (ወይም በጥቅሉ የብሔረሰቡ) ጥያቄ መልስ አገኘ ብለን መደምደም አንችልም፡፡
ዶ/ር ሌቪን በጠቀስነው ጥናታቸው ውስጥ ሦስት ትርክታዊ አማራጭ መፍትሔዎችን ጠቁመው ነው ጥናታቸውን የሚደመድሙት፡፡
1ኛ. ትውፊታዊው ትርክት
‹‹… sustaining and strengthening whatever can be preserved of the traditional institutions of the Oromo Gadaa system. Toward that end they should maintain a certain distance from the political center of the Ethiopian nation. …›› (…በትውፊታዊው የገዳ ስርዓት ውስጥ አጠናክሮ ማቆየት የሚቻለውን ማስቀጠል፤ በዚያውም ከኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ማዕከል ጋር ያለውን ርቀት ባለበት ማስጓዝ፡፡…)
2ኛ. የቅኝ ተገዢነት ትርክት
‹‹… a “national liberation struggle [that] will continue between Oromia and Ethiopia until the Oromo nation freely decides its political future by uprooting Ethiopian settler colonialism …›› (…የኦሮሞ ብሔረሰብ ተወላጆች ኢትዮጵያዊ ሰፋሪ ቅኝ ገዢዎችን ነቅለው በማስወገድ ስለራሳቸው ዕጣ ፈንታ መወሰን እንዲችሉ/እስኪችሉ ድረስ/ የብሔራዊ ነፃነት ትግል ማድረግ …)
3ኛ. የኢትዮጵያዊነት ትርክት
‹‹… struggling to institutionalize pluralistic democracy and multicultural diversity, Oromo rhetoric and self-understanding should be revised to include appreciation of the many Oromo contributions to building the modern Ethiopian nation, and Oromo customs could be deliberately invoked and adopted to civilize the conduct of members of the national parliament and other deliberative bodies …›› (ብዝሐ ዴሞክራሲያዊነት እና ብዝሐ ባሕላዊነት በኢትዮጵያ እንዲሰፍን መታገል፣ የኦሮሞ ብሔረሰብ ለዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ግንባታ ያለውን እና የነበረውን ሚና ዋጋ ማሰጠት፣ እና የኢትዮጵያ ፓርላማ የኦሮሞን ትውፊታዊ ስርዓትና ወግ ዘመናዊነት በማላበስ ለተግባራዊነት ማብቃት፡፡…)
በግሌ ሦስተኛው የመፍትሔ አማራጭ ውስጥ ራዕይ ይታየኛል፡፡ በመግቢያዬ ላይ ያስቀመጥኳቸው የተቀነጨቡ አባባሎችም የሚያጠናክሩት ‹የኢትዮጵያዊነት ትርክት› መፍትሔዎችን ነው፡፡ ትውፊታዊው የገዳ ስርዓት እጅግ የሚያስደንቁ፣ መቻቻልን የሚያበረታቱ፣ የሕግ የበላይነትን የሚያሰፍኑ፣ እና ሌሎችም በርካታ ጠንካራ ጎኖች አሉት፡፡ በዶናልድ ጽሑፍ ላይ ተወያይተን ስናበቃ እንዲህ አለምኩ፤
‹‹የኦሮሞ ክልላዊ መንግስት የገዳን ስርዓት ዘመነኝነት አላብሶ በክልላዊ አስተዳደሩ ሲተገብረው፣ የፌዴራል መንግስቱ በስኬቱ ቀንቶ (ከስኬቱ ተምሮ) ስርዓቱን ለብሔራዊ ስርዓትነት ሲያውለው – ለገዛ አገራችን ችግር አገራዊ መፍትሄ… ምኑ ቅጡ!››
ሕልሜ እውን እስኪሆን ድረስ ማለሜን አላቆምም!!!

ፖካ ዮኬ፣ IDIOT PROOF; ETHIOPIA


በዚህ በምህንድስናው የትምህርት ዘርፍ ልብን የሚሰቅዝ ህሊናን የሚቆጣጠር ርዕስ ብዙውን ጊዜ አይኖርም፡፡በተለይ እንደኔ መሐል አዲስ አበባ በሚገኙ የድሆች መንደር ተወልዶ ያደገ ሰው ለራሱም ሆነ ለማኀበረሰቡ ችግሮች ከግል ጥረት እና ላቂያ በላይ መወቅራዊ መስተካከል እንደሚያሰፈልግ ሰለሚያምን ካልገባው ወይም ካልተሸወደ በስተቀር በሁለንተናው አይተጋም፡፡ምህንድስና ደግሞ ኮ/ል መንግስቱ ኃ/ማርያም “ተፈጥሮን በቁጥጥራችን ስር እናውላለን፡፡” ካሉት በተቃርኖ ተፈጥሮን ባለበት አኳኃን ከሳይንሳዊ ጥናቶች በመረዳት ለሰው ልጆች ጥቅም  የሚውልበትን መንገድ ማፈላለግ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በአጭር ጊዜ በስሎ የሚበላ ፣ ለብዙዎች ችጋር የወዲያው መፍትሔ የሚሰጥ አይደለም፡፡ የሚያጠግብ ቢኖር እንኳ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን የሚፈታ ሰው ሰው የሚሸት መፍትሔ አይሰጥም፡፡ብዙዎች ስሙን ከሩቅ ቢያከብሩትም ቆዳቸው ሳሳ ያለ ሰዎችን አይመስጥም፡፡አንዳንዴ ግን አልፎ አልፎ ልብን ላፍታ የሚያሸፍት ነገር አይጠፋም፡፡ዛሬ በምኞት መልክ እንድንጫወትበት ያሰብኩት ርዕስም ከነዚህ የአንድ ሰሞን የዐሳብ ግልቢያዎች በረከት የተገኘ  ነው፡፡

የአንድን ማሽነሪ ንደፍ የሚሰራ ሰው ከሚያደርጋቸው ጥንቃቄዎች ውስጥ አንዱ IDIOT PROOF ይሰኛል፡፡ይህም ማሽኑን የሚያመርተውን ፣ የሚገጥመውን፣ የሚያንቀሳቅሰው እና የሚጠግነውን ሰው ክህሎት እና ንቃት በመጠርጠር የሚጀምር ነው፡፡ ምንም እንኳን ሰውየው አስፈላጊው ዕውቀት ቢኖረው ፣ ተገቢውን ስልጠና ቢያገኝ እንኳ ይሳሳታል ተብሎ ይታመናል፡፡ይህም ከሰው ስህተት ከብረት ዝገት አይጠፋም እንደሚለው ሀገርኛ ቢሒል ያለ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት እንዲህ ያለ ስህተት ይከሰታል  ፤ እንዲህ አድርጎ ገልብጦ ይገጥመዋል ፤ የቀኙን ወደግራ የግራውን ወደቀኝ  ይቀያይረዋል ብሎ በመገመት ስህተት ፣ ሰህተቱን በመመንጠር የስራውን ክንውን ህጸጽ አልባ ማደረግ ነው ፡፡በኢቪየሽን እና ወታደራዊ ማሽኖች ላይ ስህተት ቢፈጠር ጉዳቱም የከፋ ስለሚሆን ይህ ደናቁርትን የማጥለል ጥበብ በብዛት ይስተዋላል፡፡  ማረፊያ ጎማው (landing gear) ተገልብጦ በተገጠመለት  አውሮፕላን ቢሳፈሩ ምን እንደሚፈጠር አስቡት? አያድርስ! ነው ብለው ፈጣሪዎን ይጠሩታል ወይስ ለአእዋፍ እንኳ ያልተፈቀደውን ዘላለማዊ በረራን ይመኙለታል? ጉድና ጅራት ከወደኋላ መሆኑን የተረዱት ፈረንጆቹ ግን በአጋጣሚ ይህን ማረፊያ ጎማ የሚገጥም ሰው  ከደናቁርት ወገን ሊሆን ስለሚችል ተስሳቶ እንኳን ገልብጦ እንዳይገጠመው አድርገው ከወዲሁ ያበጁታል፡፡ ጃፓኖች ይህንን ጥበብ ፖካ ዮኬ ይሉታል፡፡ትርጓሜውም  መወድቂያህን አሳምር ወይም በጥንቃቄ ውደቅ (fail-safing) እንደማለት ነው፡፡ለነገሩ  የምህንድስናውን አነሳው እንጅ በሌሎች የትምህርት ዘርፎችም  ይህ ስልት እንደሚተገበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡እስኪ ቅጥ አምባሩ ለጠፋው ቦለቲካችን ለምን  አንሞክረውም?

የኢትዮጵያን ያለፉ 40 ዓመታት የቦለቲካ ጨዋታ ላስተዋለ ሰው ብዙ የዕውር ድንብር ታሪኮች ያጋጥሙታል፡፡በአስራ ዘጠኝ ስልሳዎቹ አለማችን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ እንደገባች ታሪክ ያስረዳናል፡፡በመሆኑም የገበሬዎች አመጽ ወይም የተማሪዎች ሰላማዊ ሰልፍ እንደመነሻ ምክንያት ያገልግሉ እንጂ አብዮት  የማይቀር ነበር፡፡ ነገር ግን አብዮቱ ሲጀመር  በመሀል መኀይማን እንደሚያኮላሹት የተረዳ እና በሩን ለመዝጋት ሙከራ ያደረገ  አልነበረም፡፡ካረጀው እና ካፈጀው ዘውዳዊ ስርዓት መላቀቅ ነበረባት፡፡  ነገር ግን ከዘውዳዊው ስርዓት መኳንንት እና መሳፍንት የባሱ ደናቁርት በወንበሩ ሊቀመጡ እንደሚችሉ  መገንዘብ የተገባ ነበር፡፡በኃላም ማርክሲዝም አለምን ሲያጥለቀልቅ የኢትዮጵያን በር እንደሚያንኳኳ መረዳት ነብይ መሆንን አይጠየቅም፡፡ነገር ግን በወቅቱ ከነበረው የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ከነበሩብን ችግሮች እና መልካም ሁኔታዎች አንጻር ሳይቃኝ እንደወረደ በመተግበሩ የአንድ ትውልድ ወጣት እንዳይሆን እንዳይሆን ሆኖ አልፏል፡፡ ነፍጥ ያነገቡ ሰዎች ከወደ ደደቢት ተነስታው በቃህ እስኪሉትም የቻለውን ያህል ጥፋት እንዳደረሰ በመንገር እንደ ኢተቪ አላደክማችኹም፡፡
በ1983  ዓ.ም. በአዲስ አበባ እናቶች ጸዓዳ ቀሚሳቸውን ገጭ አድርገው ፣ፈንድሻቸውን አፍክተው አስፋልት ላይ እየበተኑ የኢትየጵያ ትንሳኤ እበራፍ ላይ የቆመ መሆኑን ሲያበስሩ ነበር፡፡ብዙም ትሻልን ሰድጄ ትብስን አመጣው ማለት የጀመሩት ግን ልማዳዊው (sentimental) የሀገር ፍቅር የሌላቸው በብሔር ቦለቲካ የተለከፉ ደናቁርት በቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው ኢትዮጵያን ሲያራክሱ ነበር፡፡አንዳንዶች አሁን ሀገሪቷ ያለችበትን ሁኔታ  ከቀድሞ ጋር በማነጻጸር የተሻለ ሁኔታ ውስጥ እንዳለች ይናራሉ፡፡ከድንቁርና እና ደናቁርትን ማጥሊያ(Idiot proofing institutions ) ተቋማት አንጻር ስንገመግመው አላዋቂነት ለብቻው ተቀምጦ እናያለን፡፡ለአብነት ያህል የሀገሪቱን ፓርላማ ፣ምርጫ ቦርድ ፣ የፍትሕ አካላት ፣ የሀይማኖት ተቋማት ፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፣ የሚዲያ ተቋማት መዘርዘር ይቻላል፡፡በቅርቡ በአንድ የህግ ባለሙያ ወዳጄ ጉትጎታ የእነ እስክንድር ነጋ የክስ መዝገብ ወደሚታይበት ወደ ልደታ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጎራ ብዬ ነበር፡፡በኔ ባልተማረ ሰው ምልከታ  ‘በህግ አምላክ ሲሉት ውሃ እንኳን ይቆማል’ የሚባልበት ሀገር ውስጥ ያለ  ፍትሕ ተቋም አይመስልም፡፡ድኀረ መለስ ኢትዮጵያ ከሚጠብቃት ትልልቅ የቤት ስራዎች ውስጥ አንዱ በህግ ፍትሕ ርትዕን አገኛለው የሚልን መተማመን በማኀበረሰቡ ወስጥ ዳግም ማስረጽ ነው፡፡
የዛሬ ስልሳ አመት ገደማ በሀገረ አሜሪካ ‘ጥቁር ሰው ነው’ ፣ ‘ሴት ከወንድ እኩል ነች’ ብለው ለመቀበል የሚቸገሩ ሰዎች ቁጥራቸው የትየለሌ ነበር፡፡  ችግራቸውን እያስወገዱ ድንቁርናን እየከሉ ስለመጡ ዛሬ ሰማየ ሰማያት ደርሰው በጥቁር ፕሬዚዳንት ለመመራት በቁ፡፡እኛ ግን ምንአልባት በአጸደ ስጋ ቢገኙ እንኳን ከሌላው ኡትዮጵያዊ የከፋ ጉዳት ደርሰብን የማይሉ ወገኖቻችንን እየጠቀስን የልዩነትን ግንብ እንገነባለን ፤ የጥላቻን ጉድጓድ እንቆፍራለን ፤ ልዩነትን እንሰብካለን፡፡
ከዘመኑ የቅኝት ስልት ጋር ራስን እያስታከኩ መንጎድ ቀላል ነው ፡፡ተገደን የምንገባበትም ነው፡፡ማርከሲስት መጣ ተቀበልነው ፡፡ማርክሲስት ወደቀ ተውነው፡፡ምዕራባውንን ስንከተል ነበር አሁን ደግሞ ወደቻይና አዘንብለን ያለምንም ማስተዋል እየከነፍን ነው፡፡ዋሽንግተንም ቤጅንግም መሄድ እጅግ ቀላል ነው፡፡ መለስ ዜናዊም ጥሩ ነገር በዚያ አልገጠማቸወም እንጂ በቅርቡ ዲሲ አይተናቸው ነበር፡፡በወንበሩ ተደላድለው መቀመጣቸው ያልየው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝም  በታላቋ ቻይና ቴሌቪዥን ቀርበው የወዳጅ ሀገርን ለጋስነነት ሲያወድሱም ታዘበናል፡፡እንዲህ ቀላል ነው፡፡እኛን የቸገረን አዲስ ማዕበል በመጣ ቁጥር የጠነከረውን ጥፊ መቀበላችን ነው፡፡ እንደ የውሃ ላይ ኩበት እየተገላበጥን መሄዳችን ካለፈ ታሪካችን  ተምረን መጻዒው ጊዜ ስህተት የለሽ ማድረግ አለመቻላችን ነው፡፡  
ግብጾች እና ታህሪር እንዲህ ያለ ትስስር ያላቸው ይመስለኛል፡፡መኀይምነትና ደናቁርት ስጋ ለብሰው  እንዳየሰለጥኑባቸው የሚያደርጉበት መድረክ፡፡አባቶቻቸው ፒራሚድ ሲገነቡ እነርሱ ደግሞ የሰህተትና ድንቁርና ማጥለያ አደባባይ ታህሪርን አበጅተዋል፡፡ በአንዋር ሳዳት እግር ስር የተተካውን ሙባረክን ከነድንቁርናው ያጠለሉት ታህሪርን ይዘው ነው፡፡ወታደራዊውን ፍርድ ቤትንም እንከባበር ያሉት እዚያው ነው፡፡ከሰው መሐል መርጠው ወደ መድረክ ያመጡት ሞሐመድ ሙርሲስ ቢሆን   ከተሰመረለት መስመር ውልፍት ቢል ይለቁታል? እድሜ ከሰጠን አብረን የምናየው ይሆናል፡፡ እንዲህ ስላችኹ በቃ መስቀል አደባባይ እንገናኝ እንዳትሉኝ፡፡ ቀስ! … ቀስ! …ገና ብዙ የቤት ስራ አለብን  ግብጻውያን እኮ ታንክ ተደግፈው ነው እምቢኝ ድንቁርና! ያሉት ፡፡ ይልቅስ እንደአሁኑ ወቅት  ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ እንደማያጣፍጥ በተረዳን ጊዜ ነው ፖካ ዮኬ የሚሰፈልገን  የኛ የነገዋ ኢትዮጵያ ወደኃላ የምትራመድ መሆን አይገባትም፡፡ ካለፈ ስህተቷ ተምራ ማንም ደንቆሮ የማይጠመዝዛት ወደፊት የምትጓዝ…  “Anything that can go wrong, will go wrong” ህልም እና ምኞታችንን ማን ይከለክለናል፡፡

ጋዜጣና መጽሔቶቻችን ከሰኞ እስከ ሰኞ – ስምንት

(ከሐምሌ 16 እስከ ሐምሌ 22፤ 2004)
Capital ጋዜጣ ‹‹Counting 20›› በሚል ርዕስ ባስነበበው የሽፋን ገጽ ታሪክ ላይ አቡነ ጳውሎስ የጵጵስና ‹‹ስልጣን›› የያዙበትን 20ኛ ዓመት አከባበር ይተርካል፡፡ በዓሉ በሸራተን አዲስ ሆቴል ሲከበር የተለያዩ ሃይማኖት አባቶች፣ የቢዝነስ ሰዎች እና የፖለቲካ ሰዎች ተገኝተዋል – ከነርሱም ውስጥ ቴዎድሮስ አድሃኖም እና ኃ/ማርያም ደሳለኝ ይገኙበታል፡፡
** ** **
Fortune  ጋዜጣ “Fineline” በተሰኘው የሚስጥር አምዱ ላይ ሰማሁ ብሎ ካንሾካሾካቸው ምስጢሮቹ ውስጥ መለስ ጁላይ 20 አዲስ አበባ ስለመግባታቸው፣ በርሳቸው ስም ተፈርመው የወጡ ዶክመንቶች ስለመኖራቸው እና እረፍታቸው ለአንድ ሳምንት ያህል የሚቀጥል መሆኑን ተናግሯል፡፡
** ** **
አዲስጉዳይ መጽሔት ቴዎድሮስ ተክለአረጋይ ከፖለቲካ ሳይንስና የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ ይዞ ወጥቷል፡፡ ከቃለምልልሱ ውስጥ የተቀነጨበውን እነሆ፡-

‹‹…በእኔ አስተያየት ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ተቃዋሚ ፓርቲዎች አሉ ብሎ ለመናገር ያስቸግራል፡፡ ድምጻቸው ጠፍቷል፡፡ አይታዩም፡፡ ግን አለን ይላሉ፡፡››
‹‹…እኛን ከሶቪየት ህብረትና ከዩጎዝላቪያ ጋር ማወዳደር ግድ ይሆንብኛል፡፡ በሁለቱም አገሮች የፌዴራል ስርዓቱ የተሳሰረው ከአውራው ፓርቲና ከአንድ ግለሰብ መሪ አውራነት ጋር ነበር፡፡ ሁሉቱም (ፓርቲውም አውራ መሪውም) ከስልጣን ሲወገዱ በሁለቱም አገሮች ፌዴሬሽኑ ፈራረሰ፡፡…››
‹‹…ሙስና ለእኔ ዋናው በሽታ ሳይሆን የበሽታው አንድ ምልክት ነው፡፡ ችግሩ (በሽታው) የዲሞክራሲና መልካም አስተዳደር መምከን፣ ስልጣን በአንድ ፓርቲ መዳፍ ውስጥ መግባት ነው፡፡››
‹‹…ህዝቡ በፍርሃትና በተለያዩ ምክንያቶች ዝም ሲል እንደተስማማ አድርጎ መቁጠር ስህተት ነው፡፡ ከሚጮህ ዝም ያለ ሕዝብ አደገኛ ነው፡፡…››
ሌላም ሌላም
ርዕሰ አንቀጾች
የሳምንቱ ጥቅስ
       ‹‹አጠገቡ ካሉ ሰዎች እንደምሰማው ጤንነቱ በፍጥነት እየተሻሻለ ነው፡፡››
አቦይ ስብሓት ነጋ ለአዲስ አድማስ 
ጋዜጣ ስለመለስ ጤንነት ከተናገሩት!

ባልቻን ፍለጋ

የመድፍ አረር አካባቢውን አጥኖታል፣ ጎራዴ ይብለጨለጫል፣ የደም ወንዝ ይጎርፋል፡፡ አዎ ይህ ጥቁር ጦር ቀላል  እንዳልሆነ እየታየ ነው፡፡ ያ የበጋ ሰማይ ደምን አየ መሰለኝ ክፉኛ ቀልቷል፡፡ በቀላ ሰማይ ስር ጦርን እንደ ብዕር ደምን እንደ ቀለም አድርገው ጀግኖች ታሪክ ይፅፋሉ፡፡ ታሪክን በመክተቡ መሀል ለጥቁሮቹ ጀግኖች አንድ አስደንጋጭ ነገር አጋጠማቸው፡፡ ከመሪዎቻቸው ንዱ የሆኑት ከጠዋቱ 3 ሰዓት ገደማ  ፊትአውራሪ ገበየሁ ተሰው፡፡ ወላድ በድባብ ትሂድ ገበየሁን ያጣ ጦር አልተበተነም ባልቻን የሚያክል መሪ አግኝቷልና፡፡ ደጃዝማች ባልቻም መድፉን እንደ ቀላል ያገላብጠው ጀመር፡፡ ይሄን የታዘበ አዝማሪም፡

 <<ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ፣

መድፍ አገላባጭ፣ ብቻ ለብቻ፡፡>>

ብሎ ተቀ፡፡ ምስጋና ለባልቻ፣ ምስጋና ለገበየሁ ያ ጥቁር ጦር ጠላቱን ድል ነሳ፣ አዲስ ታሪክም ፃፈ፡፡ የካቲት 23/1888 ዓ.ም አድዋ ኢትዮጵያ፡፡
ዛሬ ገበየሁ
አዎ እነ ገበየሁ እነ ባልቻ ታሪክ ከጻፉ ድፍን አንድ ምእተ ዓመት ሊሞላቸው 5 ዓመታት ብቻ ነው የቀረው ወቅቱም 1983 ዓ.ም ውልደቱ በታሪካዊዋ አድዋ የሆነ፣ ራሰ በሀ፣ ቀጭን-አጭር መሪ ነገሰ ኢትዮጵያን ሊያስተዳድር፡፡ የቀድሞው ፕሬዘደንት ያሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፡፡ መለስ እንደ ገበየሁ ከፊት ሆነው ህዝቡን ወደ ድል  ወይስ ወደ ገደል መሩት? ከተለያዩ አቅጣጫዎች የተለያዩ መልሶች ናቸው የሚሰጡት፡፡
ባንድ ወገን ‹‹ነፃነትን ያለገደብ ሰጠ፣  ድንቅ እና ውብ ህገ-መንግስት ለህዝቡ አስረከበ፣ ሀገሪቱን በልማት ጎዳና ትጓዝ ዘንድ አረር በማይሸትበት፣ጎራዴ በማይብለጨለችበት የልማት መንገድ መርተዋታል፣ ማን እንደ እርሳቸው? ማን እንደ መለስ?›› በማለት ‹‹ወዲ ወሊደሙ መለስ በልዩ›› (ልጅ ወልደሽ ስሙን መለስ በይው)  እያለ መለስ ለህዝቡ ከመሪም በላይ ናቸውን ሲሰበክ፣ ‹‹ይቀጥል ሊቁ ሰው ጥበብ የተካነው›› እያለ ንጉስ ሆይ ሽህ ዓመት ይንገሱ፣ ዙፋንዎት ይፅና፣ አመራርዎት ይቅና  ይዘምራል፡፡
በሌላ ወገን ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በማይወዳት መሪ እየተመራች ነው፣ ‘ባንዲራን ጨርቅ’ ያለ የቅርስን ዋጋ ያሳነሰ፣ ‘ኮሮጆ የሚያስገለብጥ’፣ ህግ ደንታ የማይሰጠው ህግ ሰሪ ህግ አፈራሽ በአጠቃላይ ምሉዕ በኩሉሄ የሆነ መሪ ከቶ ለምኔ? እርሱ ወረደ እለት ስለቴን አስገባለሁ፣ እሱ የሞተ እለት ፈጣሪ የህዝቡን እንባ አይቷል ማለት ነው እያለ ይተቻል፡፡
አዎ ! ዛሬ ‘ገበየሁ’ ፈተናቸው ብዙ ነው፡፡ አዎ ! ዛሬ ‘ገበየሁ’ ‘ጠላትን’ ለመዋጋት ጦር ሜዳ መሄድ አላስፈለጋቸውም ያሉበት ቦታ ድረስ ይሰማቸዋል የመድፍ ጩኸት፣አይናቸው ላይ ያብረቀርቃል የጎራዴው ስለት፣ በዓይነ ህሊናቸው ይታያቸዋል ደም የቀደደው ቦይ ፡፡ በርግጥ ‘ገበየሁ’ ዛሬ ግለሰብ ብቻ ሳይሆኑ ስርዓትም ናቸው ቢባል አያሰገርምም፡፡ በርግጥም መድፉን ብቻቸውን አገላብጠውታል፡፡ 
የሆነ ሆኖ በአሁኑ ወቅትም ‘ገበየሁ’ የት እንዳሉ በትክክል ማወቅ አልተቻለም፡፡ ጓዶቻቸው ‹‹ሥራ ጫና ነበረባቸው አሁን እያረፉ ነው›› ሲሉ ህዝቡ ‹‹ድሮስ ብቻቸውን ህዝብን የሚያክል ነገር እያገላበጡ ምነው አይደክሙ?›› ይላል፡፡ እንዲሁም የ አለፉ ዘመናትን ሲያስታውስ፡
ደከመኝ ሰለቸኝ፣ እረፍት የማያውቀው፣

አብዮታዊ መሪ፣ ጓድ መንግስቱ ነው፡፡

ተብሎ  ለመንግስቱ-ኮመኒስቱ የተዘመረውን መዝሙር ይታወሰዋል፡፡
በተቃራኒው ደግሞ ‹‹አይ ‘ገበየሁ’ ለዘላለሙ አሸልበዋል የስልጣን ሽኩቻውም በበታቾቻቸው መካከል ጡፏል›› የሚል መረጃ ይሰማል፡፡
የትኛው መረጃ እንደሚጨበት ማወቅ አልተቻለም፡፡ ለማንኛውም ጨዋታችን እንዲሞቅ እንዲህ እናስብ፡፡ ከእንግዲህ ‘ገበየሁ’ በህወይት ኖሩም አልኖሩም ወደስልጣን አይመለሱም ስለዚህም የገበየሁን ተኪ ‘ባልቻን’ እንፈልግ፡፡
‘ባልቻን’ ፍለጋ  
‘ገበየሁን’ ይተካ ዘንድ ‘ባልቻን’ እንፈልጋለን፡፡ መጀመሪያ ‘ባልቻ’ ሊኖርባቸው የሚችሉትን ቦታዎች እናስስ እስኪ፡፡
1.      – ‘በመስዋዕትነት ከተገኘው ህገ መንግስት’

ከሌሎች ሀገሮች ህገ መንግስቶች በተለየ የኢፌድሪ ህገ-መንግስት ገበየሁ ቢሞት የባልቻ መገኛ የት እንደሆነ በግልፅ አይጠቁምም፡፡ ይልቅስ ህገ መንግስቱ ገበየሁ ‹በማይኖር ጊዜ› በሚል ጥቅል አጠራር ምክትሉ ‘የባልቻን’ ድርሻ ይወርሳል ይላል፡፡ ይህ ህገመንግስታዊ አንቀፅ ለትርጉም ክፍት ነው፡፡ ‘ገበየሁ’ ከስራ ለአጭር ጊዜ ሲርቅ ነው ብቻ ነው ተብሎ ሊተረጎምም ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አይ ‘ገበየሁ’ በሞተም ጊዜ ተክቶ ሊሰራ ይችላል ተብሎ ሊተረጎም ይችላል፡፡ እንግዲህ ‘ባልቻን’ ከህጋዊ መስመር አገኘን የሚሉም ከሁለተኛው ትርጉም የተነሳ መሆን አለባቸው፡፡ አሁን ካለው ድባብ በመነሳት ይህ  የመሆን ዕድሉ ዝቅተኛ ይመስላል፡፡ ቢሆን እንኳን እንደ ‘ገበየሁ’ ህዝቡን ብቻውን ማገላበጡ ያጠራጥራል፡፡  

2.     – ‘ጀኔራል ባልቻ’

እነሆ ‘ባልቻን’ ፍለጋ የጦር ካምፕ ውስጥ ነን ‘ባልቻን’ በግልፅ ለማየት ግን አልተቻለም፡፡ በርግጥም ‘ባልቻን’ ከጦር ካምፕ የምናገኝው ከሆነ ግን ጉዳዩ ያስፈራል፡፡ ቢያስፈራም ግን ‘ባልቻ’ በጦር ካምፕ ውስጥ መሽጎ ሊሆን ይችላል፡፡ የተገኝ እለት ‘ጀኔራል ባልቻ’ ሀገሪቱን በአንድ እግሯ አቆሟት መባሉ የማይቀር ነው፡፡

3.     ‘ባልቻን’ ከቤተ መንግስት
 
ሌላው ጥርጣሬያችን ‘ባልቻን’ እዛው ‘የገበየሁ’ ቤተ-መንግስት ውስጥ ልናገኛቸው እንችላለን የሚለው ነው፡፡ አይሆንም አይባልም፡፡ ሴቱ-ወንዱ የቤተ መንግስት ባለሟል ድንገት ‹‹ባልቻ ነኝ እኮ ስለምን ርቃችሁ ትፈልጉኛላችሁ እዚሁ ቤተመንግስት ነበርኩ እኮ›› ሊል ይችላል፡፡ ‹‹ሹመት በተርታ፣ ስጋ በገበታ››ን እየተረተ ‹‹የሞትንም እኛ ያለንም እኛን›› እያለ ሊያሳውጅ ይችላል ‘ባልቻ’ ከቤተ መንግስት፡፡

4.     ባልቻን’ ከምድረበዳ

በርግጥም ‘ባልቻን’ ከምድረበዳ ያልነው ‘ከተቃዋሚው’ ጎራ ይመጣ ይሆን የሚለውን ግምታችን ነው፡፡ ዲያስፖራ ተቃዋሚው መግለጫ፣ ኮምኒኬ ወ.ዘ.ተ በማውጣት ዱብ ዱብ እያለ እራሱን እያሟሟቀ ይገኛል፡፡ መቸም ‘ባልቻ’ ‘አትላንቲክን’ ወይም ‘ሚድትራኒያንን’ አለዚያም ‘መረብ’ ወንዝን አቋርጦ ሊመጣ ይችላል ማለት ከባድ ነው! ኧረ በጣም ከባድ ነው፡፡ በሌላ ጎኑ ሀገር ውስጥ ያለውን ተቃዋሚ ስናይ አሁን ባለበት ሁኔታ ጀኔራሎቹ፣ ይሆኑ ወይስ ከቤተ መንግስት እያለ ከመገመት ውጭ ያው በምድረበዳ እየተንከራተተ ነው፡፡ እናም አንድ ነገር ላይ እርግጠኛ መሆን እንችላለን አዎ ‘ባልቻን’ በድረ በዳ መፈለግ ከንቱ ልፋት ነው፡፡

የሆነ ሆኖ ‘የገበየሁ’ ዘመን እያለቀ ይመስላል፡፡ ‘የባልቻን’ መምጫ ግን ማወቅ አልተቻለም፡፡ ቢመጣስ እንደ ‘ገበየሁ’ ብቻውን ህዝቡን ያገላብጠዋል የሚለውም ሌላ ጥያቄ ነው፡፡

ባርነት በዘመን ሲዋጅ?

ፍቃዱ አንዳርጌ
በሰባተኛው ክፍለ ዘመን ኋላ ቀሩ የአፍሪካ የባርነት ስርዓት በሁለት አፍሪካዊ ባልሆኑ ነገዶች እንደተጀመረ በጉዳዩ ዙሪያ የተፃፉ ፅሁፎች ያስረዳሉ፡፡ እነዚህ ሁለት የአረብ ሙስሊም እና የአውሮፓ ባሪያ አቅኝዎች በአፍሪካ ዙሪያ አሰፍስፈው በአፍሪካውያን ሰብዓዊነት ላይ ትልቅ ኪሳራ ሲያሳድሩ ከቆዩ በኋላም የአረብ ሙስሊም የባሪያ አቅኝዎች ከመመካከለኛው፣ከምዕራብና ከምስራቅ አፍሪካ የቃረሟቸውን ሰብዓዊ ፍጡሮች እስከ 20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወደ ሰሜን አሜሪካና ኤዥያ በመላክ የሰው ላብ የገቢ ምንጫቸውን በማሳደግ ሃያልነታቸውን ለማስጠበቅ ሲታትሩ ቆይተዋል፡፡ አውሮፓውያኑም ቢሆኑ ከ15ኛው እሰከ 19ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ከምዕራብ፣መካከለኛውና ምስራቅ አፍሪካ በርካሽ የገዟቸውን አፍሪካዊ በትርፍ ወደ አውሮፓ፣ ሰሜን አሜሪካ፣መካከለኛውና ደቡብ አሜሪካ በመሸጥ የሰብዓዊነትን ልዕልና ተጋፍተዋል፡፡እነዚህ በባርነት ስም ከተለያዩ የአፍሪካ ሃገሮች የሚጋዙት ምስኪኖች ትንሽ ከሚባል ስራ ጀምሮ እስከ ከባድ የጉልበት ስራ፣ ለጦርነት ፍጆታ ሲያገለግሉ ዘመናትን አሳልፈዋል፡፡
“የምክንያት ዘመን” እየተባለ የሚጠራው ሰብዓዊነትንና ምክንያትን ያማከለው ዘመን እያቆጠቆጠ በመጣበትና ከጨለማ ወደ ብርሃን ጉዞ በሚደረግበት ዘመን (age of enlightenment) እንዲሁም የኢኮኖሚው ስርዓት ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪው መሸጋገር ተከትሎ በምእራብ አውሮፓ የባሪያ ንግድ አብሮ እያከተመ ታሪክ ወደ መሆን ተቃረበ፡፡ በዚህን ጊዜ የምዕራቡ ዓለም የባሪያ ስርዓት ገበያው እንደ ጦፈ ነበር፡፡ የማታ ማታ ግን ብሪቴን በ1833 በሁሉም ግዛቶቿ የባርያ ስርዓትን ቀሪ ስታደርግ፣ ፈረሳይ በ1848 ቅኝ ለመግዛት በሰለጠነችባው ሃገሮች የስርዓቱን ቀሪነት በህግ ደንግጋለች፤ የተባበሩት አሜረካም ብትሆን በ13ኛው የህገ መንግስት ማሻሻያ አውግዛ ሰብዓዊነት እንዲልቅ አድርጋለች፡፡ ይህንን ተከትሎም በ1888 የአትላንቲክ የባሪያ ንግድ ላይመለስ ጦሱን ይዞ ቀርቷል፡፡ ቢሆንም ግን ይህ ባርነት ህገ ወጥ በሆነ መልኩ እሰከ 1930 ድረስ ሙሉ በሙሉ ሳይጠፋ ሰብዓዊነትን ሲጋፋ እንደቆዬ እሙን ነው፡፡
ይህ የባርነት ዘመን በአፍሪካውያን ላይ ታላቅ የሆነ የስነ ልቦና ኪሳራ ያሳደረ ከማሰብ መብት ጀምሮ እስከ መዘዋወር መብትን የነፈገ፣ የማንነት ቀውስጥ ውስጥ የጣለ፣ የበታችነት ስሜት እንዲዳብር ያደረገ፣ በተፈጥሮ የተሰጠውን ሰብዓዊ መብት የነፈገ “ዘመነ ንፉግ” ሆኖ አልፏል፡፡

የሃገሩን ሰርዶ በሃገሩ በሬ!
“ራሳችንን ለማስተዳደር ዕድሉ ቢሰጠን በፍጥነት ምድራዊ ገነት እንደምንፈጥር አስመስለን አወራን፤ በተቃራኒው ያሰፈነው ግን የፍትህ መጓደልና ብሎም ፈላጭ ቆራጭነት ነው”
(ፕሬዘዳንት ጁሊየስ ኔሬሬ(ታንዛኒያ))
አሁንም አፍሪካውያን የታደልን አይመስልም እንደሚታወቀው በዘመነ ባርነት የነበሩ አፍሪካውያኖች ጉልበታቸውን ገብረዋል፣ማንነታቸውን አጥተው ከባህላቸው፣ ከቋንቋቸው፣ከሃይማኖታቸው ጋር ተፋተው ማቀዋል፡፡ በዘመኑም የነበሩ ባሪያ አሳዳሪዎች የሚፈልጉት ገና ያልተነካውን ትኩስ ጉልበታቸውን ለኢኮኖሚያዊ እድገት ማካበቻ እና ለሃያልነት ማስጠበቂያ ጦርነት ፍጆታ አውለውታል፡፡ ዘመነኞች የሆኑ ገዥዎቻችንም ያገሩን ሰርዶ በሃገሩ በሬ ያሉ ይመስል በሃገሬው ላይ ክንዳቸውን አበረትተው በባርነት በትር መውቃታቸውን ቀጥለዋል፡፡ የማይወቀሱ፣ የማይገሰሱ የሃገሪቱ አርማና ፈላስፋ አድርገው ራሳቸውን የነፃነት ተምሳሌት አድርገው ለገበያ ያቀርባሉ፡፡ በህዝባቸው ላይ ግፍ ይፈፅሙና ትዕዛዛቸውና ማስፈራሪያቸው ሲደርሰው በየአደባባዩና ስታዲዬሙ ነቅሎ በመውጣት “ሙሁሩ፣ፈላስፋው ፣ደፋሪው መሪያችን አንተ ለዘላለም ኑርልን አንተን እና መንበርህን የደፈረ ለዘላለም የአሸባሪነት ካባ ከላዩ ላይ አይውለቅ” የመሳሰሉ መፈክሮችና መዝሙሮች ያስፈክራሉ፣ ያዘምራሉ፣ያስደግማሉ፡፡
ዛሬም በእኛ ዘመን በጥቁር ምድር “ባርነት” በዘመን ተዋጅቶ ከዘመኑ ጋር እንዲሄድ በማር የተለወሰ መርዝ ሆኖ ቀርቧል፡፡ የባርነት ስርዓት ማንነትን፣ ትውልድን እንደሚገድል ሁሉ ዛሬ ማንነት እየሞተ ብኩርና በምስር ወጥ እንዲሸጥ አድርጓል፡፡ ይህ ሁኔታም በእኛ ቅኝ ባልተገዛነው ኢትዮጲያውያን ላይ ቀረልን አይስልም፡፡ በእኛ በኢትዮጵያውያን ላይ የተዘረጋው “ዘመናዊ ባሪያ አሳደሪ” ስርዓት በውዴታ ግዴታ ሰንሰለት አንገታችን ተጠፍሮ ወደ ጎን እንዳንመለከትና ከባርነት ሰልፉ እንዳናመልጥ ተደርጓል፡፡ የድሮ አሳዳሪዎች የባሪያውን ጉልበት ለኢኮኖሚና ፖለቲካ ሃያልነታቸው ማስጠበቂያ እንደተጠቀሙበት ሁሉ ዛሬም በሃበሻ ምድር በዘመኑ ዋጅተውት ትውልድን በማድከም ድክመቱን ተጠቅመው የራሳቸውን የፖለቲካ ሃያልነታቸውን እሩቅ ከፍ አድርግው ሰቅለውታል፡፡ ሰንሰለቱን እረዘም አድርገው ዘርግተው ወደ ውዴታ ግዴታ መስመር በማስገባት አንድ ሰው ስራ ለማግኘትም ሆነ ማህበራዊ አገልግሎት ሆነ ሌላ አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን አንድ በውዴታ የሚፈፀም ግዴታ ይቀመጥለታል፡፡ የተሰጠውን ኢ-ምክንያታዊ ግዴታ ሲፈጽም የጠየቀው ይሰጠዋልም ይደረግለታልም፡፡ ወጥነት ያለው ሃሳብ እንዲኖርህ ብቻ የስርዓቱን ሰልፍ ልትከተል ግድ ይላል፤ ከሰልፉ ካፈነገጥክ አሁንም በዜግነትህ ብቻ ማግኘት ያለብህን ነገር ልታጣ ትችላለህ፡፡ ስለዚህ በውዴታ ግዴታ ሰልፉ ውስጥ ገብተህ ትሰለፋለህ፡፡ ሰልፉ ውስጥ ከገባህ በኋላ ግዴታ እንጅ መብት የለህም፣ አወ ማለት እንጅ ለምን ማለት የለም፣ መጎንበስ እንጅ መቃናት አይቻልም፣ እያዩ ማለፍ እንጅ ማስተካከል የለም፣ ሲርብህ መራብ እንጅ ማዛጋት አይቻልም፣ መቀበል እንጅ መጠየቅ አይኖርም፡፡ የባርነትን ጥልቅ ትርጉም በተረዳነው ይህ ራሱ ጉልበትን ያላካተተ ከባርነት አገዛዝ የማይተናነስ መሆኑን ለማወቅ ነጋሪ አያስልገውም፡፡
አንድ ሰው በሃገሩ እየኖረ በታሪኩ ካልኮራ፣ታሪኩን ጮክ ብሎ ሲያወራ ድምፅ ቀንስ እንዲያውስ ማን አባክ አውራ አለህ፣ ሲርበው እራበኝ ብሎ መጠየቁ አሸባሪ የሚያሰኘው ከሆነ፣ ሃሳቡን በነፃነት ሲገልፅ ለምን ተብሎ ወህኒ የሚጋዝ ከሆነ፣ ተበደልኩ ሲል ፀረ ዲሞክራሲ፣ ለምን ሲል ፀረ ልማት የሚባል ከሆነ፣መሪዎቹን በሚደግፍ ሰልፍ ሳይወጣ ሲቀር የሚወገዝ ከሆነ፣ በዲግሪ ማስትሬት ተመርቆ ስራ ብሎ ሲጠይቅ ከግልምጫ ጋር ስራ አትፈጥርም ተብሎ የሚሳለቅበት ከሆነ፣ እድገት የለም ሲል ፀረ- ልማት ፣ የሃይማኖት መብቴ ሲል አክራሪ እየተባለ በሃገሩ እንደሌላ ዜጋ ተቆጥሮ ምን አገባህ እኔ አውቅልሃለው ከተባለ……. እስኪ ተጠየቁ ከዚህ በላይ ባርነት ከወዴት አለ?
በባርነት መኖር ወይስ ወደ ነፃነት እየሄዱ መመሞት?
እስካሁን ከተለያዩ ሰዎች ጋር በግል ካደረኳቸው ውይይቶች ሆነ ሰዎች ሲወያዩ ከታዘብኳቸው አብዛኛዎቹ በዘመናዊ መልኩ የባሪያ አሳዳሪ ስርዓት ሃገሪቱ ውስጥ ሰፍኖ እንዳለና መልኩን ቀይሮ እንደመጣ የሚስማሙ ናቸው፡፡
ባርነቱ ላይ የተስሙት ብዙዎች ተመችቷቸው እንደሆነ፣ አሁን በሃገሪቱ ተዘርግቶ ስላለው ስርአት ሲጠየቁ ግን ሲጠየቁ እረ “የደላው ሙቅ ያኝካል” አሉ የሚል መልስ ሲሰጡ ይሰማል፡፡ታዲያ ስርዓቱ ላይ ቅሬተ ያለው ሰው ካለ ለምን ጥያቄስ አያቀርብም ያልን እንደሆነ አብዛኛው የሚሰጠው መልስ “እናውቃለን ብንናገር እናልቃለን አይነት ነው፡፡

ይህ የነጻነትን ጣእም በቅጡ ያለመረዳት ችግር የሚቀረፍበትን መንገድ በቀላሉ አግኝተን የምንለውጠውም አይመስልም፡፡የነጻነትን ጣእም ያለመረዳት ችግር ባይሆንም ኖሮ ለዘመናት የባርነትን እና ገዢዎችን እያፈራረቅን አንኖርም ነበር፡፡ ይህ አዙሪት መቼ ይሆን የሚያበቃው?

—–
ፍቃዱ አንዳርጌ ይህንን ጽሁፍ የላኩልን በzone9ners@gmail.com ሲሆን፣ ለዞን ዘጠኝ አንባቢዎች እንዲስማማ መጠነኛ አርትኦት አድርገንበታል፡፡ ጸሐፊውን የሚገኙበት የኢሜይል አድራሻ፡- fekidyiab@gmail.com

ማን ስልጣን ላይ ተወለደና?

በናትናኤል ፈለቀ



Murder at 1600 ዊስሊ ስናይፕስ (Wisely Snipes) የተሰኘ ጥቁር አሜሪካዊ የሚተውንበት ልብ አንጠልጣይ ፊልም መጠሪያ ነው – Murder at 1600፡፡ 1600 (Sixteen hundred) የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች መኖሪያ የሆነው ዋይት ሀውስን በር ይዞ የሚያልፈው መንገድ መጠሪያ ነው፡፡

ፊልሙ የሚያጠነጥነው ስናይፕስ ዋይት ሀውስ ውስጥ ተገድላ የተገኘች ሴትን ነፍሰ ገዳይ እና የአማሟት ሁኔታ ለማጣራት በሚያደርገው ውጣ ውረድ ላይ ነው፡፡ ነፍሰ ገዳዩን ለማግኘት ስናይፕስ በሚያደርገው ክትትል በግድያው የፕሬዝዳንቱ እጅ እንዳለበት የሚጠቁሙ የጥርጣሬ መረጃዎች ያገኛል፤ ይህ ያልተዋጠላቸው የፕሬዝዳንቱ ቺፍ ኦፍ ስታፍ ስናይፕስን ደውለው ያስጠሩትና የዋሽንግተንን ማስታወሻ ሃውልት አሻግሮ የሚያሳየው ፓርክ ውስጥ የጠዋት ስፖርት እየሰሩ ስናይፕስን የክትትሉን ትኩረት ወደ ሌላ ተጠርጣሪዎች እንዲያዞር ወይንም ከነጭራሹ ቢተወው እንደሚሻል ለማስረዳት ይሞክራሉ፡፡ ስናይፕስ ግን የሚመለስ አልሆነም፤ እንደውም መረጃዎች የጠቆሙት ሰው እና ስልጣን ድረስ እንደሚሄድ አስረግጦ ይነግራቸዋል፡፡ ይህን ጊዜ ቺፉ ቆጣ ብለው ‹‹ፕሬዝዳንትነቱ ተቋም ነው (ግለሰብ አይደለም) እዛ እንድትደርስ አልፈቅድልህም›› ይሉታል፡፡

ስልጣን ተቋማዊ (Institutionalized) ሲሆን ምን ማለት ነው?

በታዳጊ ሀገራት ያሉ የመንግስት የአስፈፃሚ ቅርንጫፍ አናት ላይ የሚገኙ ባለስልጣናት ብዙ ጊዜ ሲፈፅሙ/ሊፈፅሙ ሲሞክሩ ከምናያቸው የፖለቲካ ቅሌቶች መካከል ስልጣን ላይ ለተጨማሪ ዓመታት ለመቆየት ሕገመንግስቱን ማሻሻል (ሴኔጋል እና ቬንዙዌላ የቅርብ ምሳሌዎች ናቸው)፣ ምርጫ ማጭርበርበር (ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ዚንባቡዌ)፣ በምርጫ ቢሸነፉም ስልጣን አለቅም ማለት (ኮትዲቩዋር) ይገኙበታል፡፡  እነዚህን የመሰሉ አሳፋሪ ድርጊቶች የሚፈፅሙት ታዲያ ስልጣንን የሚያዩት እንደህዝብን ማገልገያ መሳርያ ሳይሆን እስከ እለተ ሞታቸው የፈለጉትን እየፈለጡና እየቆረጡ የሚኖሩበት የግል ንብረታቸው አድርገው ስለሆነ ነው፡፡ ማቲያስ ባሰዶው እና አሌክሳንደር ስትሮህ የተባሉ የማህበራዊ ሳይንስ ጥናት ባለሙያዎች የፖለቲካፓርቲዎች ተቋማዊነት በታዳጊ ሀገራት በፈተሹበት ጥናት ተቋማዊነትን ሲተረጉሙ ‹ድርጅቶች እሴቶችን የሚመርጡበት እና ቀጣይነትን የሚያረጋግጡበት ሂደት ነው› ሲሉ ይገልፁታል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደማንኛውም ድርጅት ትውልድ ተሻጋሪነታቸውን ለማረጋገጥ ግልፅ የሆነ ስልጣንን (ቢያንስ ፓርቲ ውስጥ) ለተተኪዎች የሚያስተላልፉበት መመሪያ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ይህንንም ሽግግር የሚያበረታታ ስልጣን ህዝብን ማገልገያ መሳሪያ ብቻ እንደሆነ የሚያረጋግጥ የውስጠ ፓርቲ እሴት ያስፈልጋል፡፡ ኃላፊነትን ለመረከብ በጥሩ ሁኔታ የተኮተኮተ ተተኪ ማዘጋጀት እና ተተኪውም ብቁ መሆኑ ሲረጋገጥ ስልጣን (የፓርቲውንም ይሁን የሀገር) ማስረከብን አማራጭ የሌለው ምርጫ የሚያደርግ ባህል መፍጠርን ያካትታል ማለት ነው – ተቋማዊነት፡፡ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱትን ማድረግ ያልቻለ እንደ ትልቅ ውድቀት የሚቆጠርበት በተለይም ስልጣን አልለቅም ብሎ ችክ ማለትን አሳፋሪ የሚያደርግ እሴት መፍጠር ወሳኝ ነው፡፡
አምባገነኖች እና ተቋማዊነት!

“What would I do if I leave the Presidency? Chop Onions?” Hosni Mubarak

ከላይ እንደ ተጠቀሰው አምባገነኖች ስልጣን ላይ ለመቆየት ምንም ከማድረግ ወደኋላ አይሉም፤ ድርጊታቸው ምንም ያክል አሳፋሪ ቢሆንም፡፡ አንባገነኖች እራሳቸውን ብቸኛ ነፃ አውጪ፣ ሰላም አስከባሪ፣ አልሚ …ወ.ዘ.ተ አድርገው ነው የሚቆጥሩት ወይም እንዲቆጠሩ የሚፈልጉት፡፡ ለዚህም ነው መልካም ስራ በመስራት ትንሽም ቢሆን ህዝባዊ ተቀባይነት የሚያገኙ ሰዎችን ከኃላፊነታቸው ዞር ከማድረግ አንስቶ ‹‹በህጋዊ›› እርምጃም ከጨዋታ ውጪ የሚያደርጓቸው፡፡ ሰዎች በአምባገነኑ ጥርስ ውስጥ ለመግባት የሚጠበቅባቸው ጥሩ ስራ ሰርተው በህዝብ ዘንድ ጥሩ ስም እና አመኔታ መገንባት ብቻ ነው፤ የአምባገነኑ ፓርቲ ወይንም ጎሳ አባል፣ አብሮ አደግ፣ ወይንም የተፎካካሪ ፓርቲ አባል መሆን ልዩነት ያለው የሚከተለው ቅጣት ላይ ነው እንጂ ህዝብ እንዲወደውና አመኔታ እንዲጣልበት የሚፈቀደው ለአምባገነኑ ለእራሱ ብቻ ነው፡፡ አምባገነኖች በወዳጅ ሀገሮችም ዘንድ እንደብቸኛ የወዳጅነቱ ጠባቂ ሆነው መቅረብ ነው የሚፈልጉት – እነሱ ከሌሉወ ዳጅነቱ ገደል እንደሚገባ፡፡

ይህን ትንተና ለመደገፍ የቀድሞ የግብፅ ፕሬዝዳንት የነበሩትን ሆስኒ ሙባረክ እና የሊቢያ መሪ የነበሩትን ሙአመር ቃዳፊን ማየት ይበቃል፡፡ ሁለቱ መሪዎች በየሀገራቸው ለረጅም (ከሦስት አሥርት ዓመታት በላይ) በስልጣን የቆዩ ሲሆን ሀገሮቻቸው የሚያስፈልጋቸው ዴሞክራሲ ከምዕራቡ ዓለም ለየት ያለ እንደሆነ ሲሰብኩ የኖሩ ነበሩ፡፡ የአረቡ ዓለም ፀደይን ተከትሎ ሁለቱም ስልጣናቸው አደጋ ላይ ሲወድቅ የተለመደውን የአምባገነኖች ብሔራዊ መዝሙር ነበር የዘመሩት፤ እስከዛሬ እኔ ሆኜ ነው እንጂ ይህች ሀገር በብዙ ችግሮች የተተበተበች ናት፣ ያለ እኔም በቀጥታ የእርስ በእርስ ጦርነት ነው የምትታመሰው፣ በኋላ ሙባረክ/ቃዳፊ ምን በደለን የምትሉበት ቀን ይመጣል የሚል አንድምታ ያለው ንግግር ነበር የሚያቀርቡት – የሚሰማቸው አላገኙም እንጂ፡፡ የሚገርመው ከጥቃቅን የማስዋቢያ ለውጦች በስተቀር የሁሉም አምባገነኖች ክርክር አንድ ነው – የእናት ሆድ ዥንጉርጉር የሚለው አባባል ለአምባገነኖች የሚሰራ አይመስልም፡፡ በስተመጨረሻ መውደቂያቸው ሲቃረብ አምባገነኖች የሀገሪቷን ችግሮች አጋንነው ሲደረድሩ ለሃያና ሠላሳ ዓመት በአመራራቸው ስር ስለነበረች ሀገር ሳይሆን ስለሌላ መልካሙዋን ማንሳት ስለማይፈልጓት ፀበኛ ሀገር የሚያወሩ ነው የሚመስለው፡፡

አምባገነኖች ሁልጊዜም ቢሆን እንደስልጡን መሪ መታየት ይፈልጋሉ፡፡ ጎልማሳ እያሉ ስልጣን እንደያዙ ምንም የማይወጣለት ብሔር ብሔረሰኖችን የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እስከመገንጠል የሚያጎናፅፍ ሕገመንግስት ሲያፀድቁ እና በሀገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያ ሊባል የሚችል ህዝባዊ ምርጫ ሲያካሂዱ የተሰጣቸውን የ‹‹ተራማጅ››ነት ዝና ስልጣን ላይ ከድፍን ሃያ ዓመት በላይ ከቆዩ በኋላ በልማታዊነት እንደገና ዝናዋን መልሰው ሊጎናፀፉ ይፈልጋሉ፡፡ አንድ አሁን በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊ የምጣኔ ሃብት ባለሙያ በመጽሐፋቸው እንዳሰፈሩት አምባገነኖች እራሳቸውን ለማሞኘት የሚሄዱትን ርቀት አሳንሶ መመልከት በርግጠኝነት መሳሳት ነው፡፡

ከአንባገነኖችበኋላስ?

አምባገነኖች የፖለቲካ ስልጣንን የግል ንብረታቸው አድርገው በመመልታቸው ተተኪ ማዘጋጀት ይቅርና ሊተኩ ይችላሉ የሚባሉትን ሰዎች ብቻ አይደለም ሐሳቡንም ጭምር ማጥፋት ከተቻላቸው ይሞክሩታል፡፡ ከላይ ለማሳየት እንደተሞከረው አንባገነኖች እራሳቸውን እና እራሳቸውን ብቻ ለሀገሪቱ አማራጭ የሌለው ምርጫ አድርገው፤ እኔ ከሌለሁ ምንም አይኖርም በሚል ስልታዊ የፍራቻ ድባብ ውስጥ የሚመሩት ሀገር ዜጎች ሁሉ እንዲገቡ በማድረግ የስልጣናቸውን እድሜ ማራዘም ነው ግባቸው፡፡ እንደሳቸው ማነው አቻችሎ የሚገዛን? እሳቸው ባይኖሩ እኮ እስከዛሬም አልቀን ነበር ብለን እንድናስብ ነው የሚፈለገው፤ ስለሆነ ሳይሆን ለዓላማቸው ስለሚረዳቸው ብቻ፡፡

ወደገደለው

አቶ መለስ ዜናዊ ስልጣን ላይ አልተወለዱም፡፡ ፈጣሪም እሳቸውን ብቻ ለቦታው የሚመጥኑ አድርጎ እንዳልሰራቸው ምስክር ከራሳቸው ሌላ የሚያስፈልገን አይመስለኝም፡፡ እንደውም
  • አስፈራርቶ እና በጠብ-መንጃ ተማምኖ ከሚገዛን ልምድ ያለው አምባገነን አንድ ሀገራዊ ራዕይ ፈጥሮ የሚመራን ጀማሪ ይሻለናል፣
  • ተቃዋሚዎችንና ጋዜጠኞችን ሳስር እና ሳንገላታ አያገባችሁም፣ ገንዘባችሁን በሊማሊሞ በኩል ይዛችሁ መሄድ ትችላላችሁ፤ ሃያ አንድ ዓመት ማሸነፍ ያቃተን የምግብ እህል ተረጂዎች ጉዳይ ግን የጋራችን ነው ብሎ ሀገሪቷን ከሚያዋርድ መሪ በግልፅ ቋሚ የውጭ እገዛ የምንፈልግበትን ሀገራዊ ጉዳይ ለይቶ ከሁሉም ወዳጅ ሀገራት ጋር ተስማምቶ የሚሰራ መሪ ይሻለናል፣
  • ስልጣን ላይ ለመቆየት ንፁሀን ዜጎችን ከሚገድል/ከሚያስገድል ይህን ተግባር እፈፅማለሁ፣ ሀገሪቷን ከእህል ተረጂነት አላቅቃለሁ አለበለዚያ ግን ስልጣን የናንተ ነውና እለቃለሁ የሚል፣ ብሎም የሚፈፅም መሪ ይሻለናል፡፡

ምናልባት፣ ምናልባት… ከመለስ በኋላስ?

የመንግስት ኮምንኬሽን ጉዳዮች በነገሩ ላይ አስተያየት ለመስጠት ቢሞክርም የአቶ መለስን “ቀላል ህመም” ከማመን ይልቅ አሁንም ኢትዮጵያ በዚሁ ዜና እውነትነት እና ውሸትነት ዙሪያ እየተናጠች ትገኛለች – የሚያሳምን እና የተረጋገጠ መረጃ የሚሰጥ እስካሁን አልተገኘም እንጂ! ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ታመዋል፣ ኧረ እንዲያውም ሞተዋል፣ አይ… መዳከም ነው እንጂ ደህና ናቸው… ወ.ዘ.ተ›› የሚሉ መላምቶች አሁንም በየፊናው ይሰነዘራሉ፡፡ ይህ ዜና እየተናፈሰ ባለበት በዚህ የውጥረት ሰሞን አንድ የመንግስት ኃላፊ ወጥቶ ትክክለኛ መረጃ ለመስጠት ረዥም ጊዜ መውሰዱ መንግስትን ትዝብት ላይ ቢጥለውም ከአቶ በረከት መግለጫ በኋላ ደግሞ የመረጃው ትክክለኛነት ለማመን እንኳን ሳይሞክሩ፣ ብዙዎች በተከታዩ የድኅረ መለስ ዘመን ላይ እያወሩ ይገኛሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ (እንደ ኮምንኬሽን ሚኒስትሩ ንግግር ቀላሉን ያርግላቸውና) ከዚህ በኋላ  አገሪቱን መምራት የማይችሉበት ሁኔታ ቢፈጠር ቀጥሎ ምን ይከሰት ይሆን?›› የሚለው ልብ አንጠልጣይ ጥያቄም በተለያዩ ሰዎች እና አካላት ዘንድ የመወያያ አጀንዳ እየሆነ ይገኛል፡፡
የአቶ መለስ አለመኖር…
የኅወሓት ‹‹የነፍስ አባት›› አቦይ ስብሃት ነጋ በቅርቡ ከቪኦኤ ጋር በነበራቸው ንግግር የአቶ መለስን በጊዜያዊነትም ሆነ በቋሚነት አለመኖር አቃለው ሃገሪቷ በአመራር ደረጃ የሚያጋጥማት ክፍተት እንደማይኖር ተናግረዋል፡፡ ይህ እንግዲህ ከአንድ የበታች አመራር ካድሬ የተሰጠ ሐሳብ ቢሆን ኖሮ ‹‹የፓርቲውን እና የመንግስትን አሠራር ያልተረዳ፣ የዋህ፣ ልማታዊ›› ብለን እናልፈው ነበር፡፡ ጉዳዩን የተናገሩት ግን የፓርቲው ከፍተኛ ተጽእኖ ፈጣሪ እነደመሆናቸው መጠን የመለስ አለመኖርን ክፍተት ለመረዳት የመረጃ እጥረት አለባቸው ተብሎ አይታሰብም፡፡ በሌላ በኩል ክፍተቱ ቢኖርም እንኳን፣ አቦይ ስብሓት ክፍተት አለ ብለው እንዲሉ መጠበቅ የዋህነት ነው፡፡
 
የአቶ መለስ ስልጣን ለረዥም ዓመታት ተለጥጦ መቆየቱም ብዙም የሚያወያይ እና የሚያከራክር አይደለም፡፡ በተለይ በተለይ በአሁኑ ወቅት በዋናነት የሚታዩትን የመንግስት ዋና ዋና ዕቅዶች (የእድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን እና የግድብ ግንባታውን ጨምሮ) አርቃቂ እና ባለቤት እንደሆኑ ይነገራል፡፡ የዚህ “ከአቅም በላይ የተንጠራራ” ዕቅድ አፈጻጸምን ያለሳቸው ማሰብ ትንሸ አስቸጋሪ ይመስላል፡፡ በተለያዩ ሚኒስትር መስሪያ ቤቶች አሠራር እና አፈጻጸም ላይ ጠንካራ እጃቸው በተደጋጋሚ ይገባል፣ ለውሳኔም ይቃጣሉ ተብለው የሚታሙት አቶ መለስ ከቤሮክራሲው መጥፋታቸው የሚታይ ክፍተት መፍጠሩም የማይቀር ነው፡፡ ለኢኮኖሚያዊ ትንታኔው፣ለመንግስት ስህተቶች መከላከሉ፣ ለልማትና ጥፋቱ ማብራሪያ ባለፉት አሥር ዓመታት በብቸኝነት ብቅ የሚሉት መለስ አለመኖራቸው፣ “የፋጡማን አለመኖር” ያህል ነው ብሎ በቀላሉ ማለፍ ለማንም የፖለቲካ ንቃት ላለው ኢትዮጵያዊ የሚዋጥ አይመስልም፡፡ ሌላው ቀርቶ በሕጋዊው የፍትህ ስርዓት የማይፈቱ የሚመስሉ ጉዳዮችን የመጨረሻ እልባት የመስጠት ድረስ ስልጣን ያላቸው አቶ መለስ መሆናቸው እየታወቀ ይህ ለዓመታት የተገነባን “ሁሉ ያገባኛል”  ስብዕና አለመኖር የሚፈጥረው ክፍተት የሚካድ አይደለም፡፡
ታዲያ ይህንን ሁሉ ጫና ጠቅልለው የያዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ድንገት ሳይዘጋጁ እና ሳያዘጋጁ ከመድረኩ ድንገት ድርግም ማለታቸው ከወደፊቱ የአገሪቷ መጻኢ ጊዜ  ጋር ቢገናኝ ስህተት ነው ማለት አይቻልም፡፡

ሕገ መንግስታዊው መንገድ
አንዳንዶች የኢፌድሪ ሕገመንግስት አንቀጽ 75/1/ለ ‹ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማይኖር ጊዜ ተክቶ ይሠራል፤› የሚለውን እየጠቀሱ  አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርገው ያስባሉ፤ በዚሁ አንቀጽ መሠረት ሕገ መንግስቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሌሉበት ሁኔታ ሁሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተክተው እንደሚሰሩ ያናገራል፡፡ የዚህን አንቀጽ ተፈጻሚነት ደረጃ በግልጽ በሕገ መንግስቱ ባይቀመጥም ጉዳዩን በተመለከተ የተሻለ የሕግ አግባብ ተብሎ ሊጠቀስ የሚችለው የአገሪቱ ሕግም  ይህ ብቻ ነው፡፡ በተቃራኒው ይህንን የሕገ መንግስቱን አንቀጽ በሚነካ እና ክፍተቱን መጠቀም በሚመስል መልኩ የኅወሓት “የነፍስ አባት” አቦይ ስብሓት ነጋ በጉዳዩ ዙሪያ ስልጣኑን ለፓርላማው የሰጠ እና አዲስ ምርጫን ያገናዘበ የ“ተረጋጉ!” መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ አቦይ በዚሁ የአሜሪካ ድምጽ የሬዲዮ ጣቢያ ንግግራቸው የአቶ መለስ መኖር እና አለመኖር የሚያመጣው ችግር እንደሌለ እና ተተኪ መምረጥ የፓርላማው ኃላፊነት መሆኑን ነው አጽንኦት ሰጥተው ነው የተናገሩት፡፡
ጥቂቶች በተጻፈው (የቀረበ) ሕግ መሰረት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን የወደፊቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ ብለው ቢገምቱም ብዙዎች ግን ይህ የገዢው ፓርቲን ብሎም የኅወሓትን ባሕሪ የማያውቁ እና ያልተረዱ የዋሆች ግምት ነው ብለው ይተቹታል፡፡ እንደ ተቺዎቹ አባባል ከሆነ በቀድሞው የኅወሓት ክፍፍል ወቅት ሚናቸው ከደጋፊነት ባልተሻለ ሁኔታ የነበረው አባል ፓርቲዎች አሁን በአጠቃላይ የኅወሓት የበላይነት የሚታይበትን ሁኔታ ተቀይሮ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱ ቦታ ለአቶ ኃይለማርያምም ሆነ ለሌላ አባል ፓርቲ አመራር ይሰጣል ማለት ዘበት ነው፡፡በዚህ ሐሳብ የሚስማሙት ተቺዎች  ተከታይ ቦታውንም ሆነ ውስጣዊ ትግሉን ወደ መገመት ሲመጣ ነገሩን ከውጭ በማየት ብቻ ተከታዩ የመሪ ምርጫ ምን እንደሚመስል ለመገመት  ይቸገራሉ፡፡
የአቦይ ስብሃት መንገድ
በፓርቲው ውስጥ ባላቸው ቦታ እና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለሚዲያ ቅርብ በመሆን የሚታወቁት አባት ስብሃት ነጋ የስልጣን መተካቱን ነገር አስመልክተው የሰጡት ምላሽ የማይሆን፣ የማይባል እና ሌሎች የአጋር  አመራሮችን ገሸሽ ያደረገ የሚመስል አካሄድ ይታይበታል፡፡ አቦይ ከየት እንዳመጡት በማይታወቀው ሕግ ተመስርተው አብላጫ ድምጽ ያለውን ፓርቲ አዲስ እጩ የማቅረብ ስልጣን ሰጥተው ሲያበቁ የተለዩ ሐሳቦች አፍልቆ የማያውቀውን ፓርላማ የአዲሱ ጠ/ሚኒስትር መራጭ ያደርጉታል፡፡ ነገሩ ጠንካራ የሕግ ድጋፍ ያለው ባይመስልም ከእስከዛሬው የኢህአዴግ/ኅወሓት ህጋዊነት ባህሪይ በመነሳት በዚህ መንገድ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊመጣ የማይችልበት ምንም ምክንያት የለም ብሎ መደምደምን አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡
በእርግጥ የአቦይ ስብሃት መንገድ ተግባራዊ ለመሆን የውስጠ ፓርቲ ትግሉ እና የእርሳቸው የኃይል ሚዛን ወሳኝ ጉዳዮች ይሆናሉ፡፡
የኅወሓት ምናልባትም የኢህአዴግ መንገድ
ይህ መንገድ ለመገመት የሚከብደው ጉዳዩ የውስጠ ፓርቲ ትግል ስለሆነ ብቻ ሳይሆን እንደ ከዚህ በፊቶቹ ታውቀው የወጡ ልዩነቶች በፓርቲው በቅርብ ጊዜ ባለመታየቱም ጭምር ነው፡፡ ሁሉም ውሳኔ እና አመራር ከላይ ወደ ታች በሆነበት የኢሕአዲግ አሰራር ግለሰቦች ለአመራር ያላቸውን ፍላጎት እና ዝግጁነት የማሳየት ዕድል አልነበራቸውም፡፡ በተሻለ አፈፃፀም የሚታወቁትም ቢሆኑ “ከአቶ መለስ ጋር መሥራትን መባረክ ነው” እያሉ ወደሰብአዊ አምልኮ በተጠጋ አድንቆት ከማደናነቅ ውጪ ራሳቸውን በተመጣጣኝ ቦታ ያለ ሥራ አስፈጻሚ እና ዕጩ ተተኪ አድርገው ያቀረቡበት ጊዜ የለም፡፡ በዚህ የአመራር ክፍተት ላይ የውስጠ ፓርቲ ቁርሾ እና “ከእኛ በላይ ለአሳር” አስተሳሰብ ተጨምሮበት የሚቀጥለውን ተተኪ መገመቱን አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡

ከቅርብ ሰዎች ተገኙ የተባሉት መረጃዎችም የሚያሳዩት ገና ካሁኑ ለሁለት የተከፈሉ እና ለቦታው ራሳቸውን ያጩ ጎራዎች መኖራቸውን ብቻ ነው፡፡ የተባለው መረጃ እውነት ሆኖ የትኛውም ውስጠ ፓርቲ ቡድን ቢያሸንፍ እንኳን አዲሱ እጩ ወደ ስልጣን የሚመጣበትን መንገድ የፓርቲዎቹ ሕግጋቶች የሚመልሱት ጥያቄ አይመስልም፡፡ የፓርቲ መሪዎቹን የቆይታ ጊዜ የማይገድብ የፓርቲ ሕገ ደንብ እንዲህ ዓይነቱን ሁኔታ የሕጋዊ ሽፋን ለመስጠት ምን ዓይነት ስልቶች እንደሚመጡ መገመት አስቸጋሪ ነው፡፡ ጉዳዩ በተለያየ አተያይ የተወሳሰበ ቢመስልም የትኛውንም ነገር ያስከፍል እንጂ የኅወሓትን የፓርቲ የበላይነት አረጋግጦ የሚጠናቀቅ እንደሚሆን የብዙዎች ግምት ነው፡፡ በእርግጥ ይህ አዲስ መሪ የማምጣት ትግል የውስጠ ፓርቲ መረጋጋት ላይም የራሱን ተጽዕኖ መፍጠሩ የማይቀር ነው፡፡ አቶ መለስ ለዓመታት የገነቡትን እምነት እና በየሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ቢሮ መግለጫ ላይ ሳይቀር የሚከሰት ስብእና ማጣት፣ የአባላትን በራስ መተማመን መጉዳቱ የማይቀር ነው፡፡ በተለይ በተለይ እንደኢሕአዲግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አባላት ባሉበት ፓርቲ ውስጥ የመረጋጋቱ ሁኔታ ጊዜ የሚወስድ ይሆናል፡፡ ይህ የውስጠ ፓርቲ መረጋጋት እና መለስን የሚተካ አዲስ ምሰሶ የማቆም ሥራ ከፓርቲው ውጪ ለሆኑ የፓለቲካ እንቅስቃሴዎች አዲስ ዕድል ይከፍት ይሆናል የሚሉ ግምቶችንም ፈጥሯል፡፡
የተቃዋሚዎች እና የሌሎች የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች መንገድ
በደካማነቱ እና በተስፋ አስቆራጭነቱ የሚታማው የተቃዋሚው ጎራ በዚህ አዲስ ምዕራፍ ውስጥ የሚኖረው ሚና ብዙም ከፍተኛ ላይሆን ይችላል፡፡ በተለይ በተለይ በማኅበረሰብ ደረጃ በምርጫ ዋዜማ ላይ የሚገናኙት (ለዚህ ምክንያቶቹ ብዙ ቢሆኑም) 91 ፓርቲዎች በእንደዚህ ዓይነት የአመራር ክፍተት ወቅት የሚኖራቸው ሚና ላይ ዝግጅት አላደረጉም ብሎ መደምደም ከባድ አይሆንም፡፡ የፓርቲዎች ከሕዝቡ ጋር በቅጡ አለመገናኘት እና አለመተዋወቅ ለስልጣን ሽግግሩ ከሚታሰቡት አካላት መካከል የመጨረሻዎቹ አድርጎዋቸዋል፡፡ የራሳቸውን ህልውና በማቆየት እና ባለማቆየት ላይ የተጠመዱት እነዚህ አካላት የተሻለ የስልጣን ዕድል ያለው አካል የሚመጸውታቸውን የፖለቲካ ምህዳር ከመጠበቅ ውጪ አማራጭ ያላቸው አይመስሉም፡፡

ይህ የአመራር ክፍተት አሉ እየተባሉ የሚጠሩትን አገር ውስጥ ከሚገኙት ፓርቲዎች ውጪ ያሉ የተለያዩ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችም ቢሆን፣ አሁን ባላቸው በግልፅ የማይታይ እና የማይነገር  የፖለቲካ እንቅስቃሴ ላይ ተመርኩዞ ወደ ላይ ብቅ ይላሉ ብሎ ማሰብ ዘበት ነው፡፡ (ክፍተቱ ለተለያዩ እንቅስቃሴዎች የተወሰነ ዕድል መስጠቱ የማይቀር ቢሆንም!)
ድኅረ መለስ
አገሪትዋ አሁን ካለችበት የፓለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና ተያያዥ አጣብቂኝ ሁኔታዎች ላይ የአቶ መለስ መጥፋት ተጨምሮበት ጉዳዩን ከድጡ ወደማጡ እንዳያሸጋገግረው የሰጉ ጥቂቶች አይደሉም፡፡ በቀጣዩ አመራር ወቅት አሁን ትታይ የነበረችውንም የፓለቲካ ምህዳር ጠራርጎ ማጥፋት አዝማሚያ አሁኑኑ እየታየ ነው የሚሉ ክርክሮችም እየበረከቱ ነው፡፡ ቁርጡ ሳይታወቅ ገና፣ ከሰሞኑን በፍትህ ጋዜጣ ላይ የተወሰደው ግራ የሚያጋባ “ሕጋዊ” እርምጃ የድኅረ መለስ ውጤት ተደርጎ መወሰድ ጀምሯል፡፡ በቅርቡ የተወሰደውንም የሙስሊሞችን ጥያቄ በኃይል የመፍታት አዝማሚያ የዚሁ ምሳሌ ሊሆን ይችላል፡፡
ጠቅልሎ ስልጣንን የማስተዳደር ክህሎት የማጣት ችግር የሚመስለው ይህ እርምጃ ለካ ጠቅላይነት ስልጣን ብቻ ሳይሆን ክህሎትም (የአምባገነንት ክህሎት እንበለው እንዴ?) የሚጠይቅ ነው የሚያስብል ሆኗል፡፡ አዲሱ አመራር ቢያንስ ሁሉን አቀፍ ስልጣን መያዙን እስኪያገጋግጥ እና እስኪለማመድ ድረስ እንኳን ቢሆን ተመሳሳይ እርምጃዎች የማይበረክቱበት ምንም ምክንያት የለም፡፡
በአቶ መለስ፣ በቋሚነት ያለመኖር ዋና ተግዳሮቱ ወይም ዕድሉ የሚሆነው መጀመሪያ ለፓርቲው ለራሱ ለኢሕአዴግ ነው፡፡ ፓርቲው የአቶ መለስን አለመኖር እንደ ዕድል በመጠቀም ቢያንስ የሚታማበትን የአንድ ግለሰብ አምባገነንነት እና አመራር ወደ ቡድን አመራር እና እውነተኛ መተካካት ሊቀይረው የሚችልበት እድል አለ፡፡ ይህንን ዕድል በሚገባ ከተጠቀመ ኢሕአዲግ ቀስ በቀስ የቡድን ሐሳቦችን ወደማንሸራሸር እና የሐሳብ ልዩነቶችን ወደሚያስተናግድ ፓርቲነት ሊቀየር ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ በፓርቲው ውስጥ ታፍነው የቆዩ ሐሳቦችን ለንግግር እና ለትግበራ የማምጣት ዕድል ይኖረዋል፡፡
በተቃራኒው ከፓርቲው የቀድሞ ልምዶች በመነሳት የዴሞክራሲ ባህሉ ዝቅተኛ በመሆኑ ጭራሽ ወደባሰ የውስጠ ፓርቲ ችግር ባይገባም እንኳን ባለበት ሁኔታ የመጨረሻ ውጤቱ የጠቅላዩን መቀየር ብቻ ይሆናል የሚሉ ግምቶች አሉ፡፡ ምናልባት የመለስ ግለሰባዊ  ግዙፍነት ከዚህ በባሰ ሁኔታ ተጽዕኖ አሳርፎ ከነበረ ደግሞ ፓርቲውን የተለየ ሐሳብ  እያራመዱ፣ በአቶ መለስ ምሰሶነት ጥላ ስር ብቻ የነበሩ አካላት ከአቶ መለስ አለመኖር ጋር ተያይዞ ራሳቸውን በማግለል የአዲስ ቡድኖች የመፈጠር ዕድልም ሊኖር ይችላል የሚሉ መላምቶች በስሱ ይሰማሉ፡፡ (ምንም እንኳን የዚሀ ሁኔታ መፈጠር ዕድል ጠባብ ቢመስልም፡፡) ኢሕአዲግ የአቶ መለስ ስብዕና ብቻ ከፓርቲው ጋር ያጠጋጋቸው መለስን አትንኩብን ፓርቲውን ግን እንደፈለጋችሁ ብለው መለስ ላይ እምነት ያሳደሩ ከፓርቲ ፓለቲካ ውጪ ያሉ አካላትን ይዞ የመቀጠሉ ጉዳይም ሌላው የድኅረ መለስ ጊዜ ጥያቄ ነው፡፡ ብዙዎቹ እንደሚገምቱት ጉዳዩ በውስጠ ፓርቲ ትግል ጠቅላይን ለጠቅላይ በመተካት ብቻ የኢሕአዲግን ግዙፍነት በመጠበቅ ከተጠናቀቀ የወደፊትዋ ኢትዮጵያ አዝማሚያ ለመሻሻል እድል የሌለው ሊመስል ይችላል፡፡

በዚህ መሀል፣ እንደሕዝብ – የአቶ መለስን የውጪ ተክለ ስብዕና የሚተካ ጠንካራ ሰው ማምጣት የሚጠበቅበት አዲሱ አመራር በዕድሉ ተጠቅሞ የፓርቲውን የዲሞክራሲ ባህል መለወጥ ካልቻለ የአቶ መለስን ዓይነት ሌላ ሰው፣ በዘዴ ሁሉን የመጠቅለል ክህሎት እስኪያዳብር ድረስ ‹‹የአንባገነንት መለማለጃ ልንሆን ይሆን እንዴ?›› የሚል ጥያቄ ከወዲሁ ማንሳቱ አስፈላጊ ነው፡፡

መለስ ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያውያን

ኢትዮጵያ ድፍን የ25 ብር ኖት የላትም፤ ሆኖም ሊዘጋጅላት ነው ብለን እናስብ:: በኢትዮጵያ ታሪክ ከፍተኛ ተጽእኖ ፈጣሪ ናቸው ተብለው የሚታመንባቸው መሪዎች ምስላቸው በዚህ የብር ኖት ላይ ታትሞ እንዲወጣ ቢፈለግ፣ ኢትዮጵያውያንን የሚያስማሙ መሪዎች አሉን? አቶ መለስስ ለዚህ ማዕረግ በስንቱ ኢትዮጵያዊ ይታጩ ይሆን? ብለን ብንጠይቅ:: መልሱ አዳጋች ነው:: እንደበለፀጉት ሀገሮች ነጻ የሆነ የሕዝብ አስተያየት የሚሰበስብ የሚዲያም ሆነ የህዝብ ግንኙነት ድርጅት በሌለበት እንደ ኢትዮጵያ ባለ ሀገር አቶ መለስን አብዛኛው ሕዝብ ‹ይወዳቸዋል› ወይም ‹ይጠላቸዋል› ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይከብዳል:: እንደ አፄ ምንሊክ ወይም እንደ አፄ ኃይለስላሴ የኢትዮጵያዊያንን አስተያየት በተለያየ መስመር እንደማይበታትኑ መናገር ግን አይከብድም:: ከሕዝብ ዕይታ ከተሰወሩ ወዲህ እንኳን፣ ስለጠቅላይ ሚንስትሩ በየማህበራዊ ድረገጾች እና በየጦማሮቹ የሚጻፉት ጽሁፎች የተቃውሞ እና የድጋፍ በማለት ለሁለት መክፈል ይቻላል:: ለመሆኑ አቶ መለስ በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያውያን እንዴት ይታያሉ?
ባልደራባዬ አቤል ጠቅላያችን የማን ናቸው? ብሎ በጠየቀበት ጦማሩ ‹‹ኢትዮጵያውያን እርሳቸውን የኔ ብለው ለመቀበል ይቸገራሉ፤ በግድ አስገድደው ያንተ ነኝ ካላሉት በቀር ሁሉም እርሳቸውን መሪዬ ናቸው ብሎ ለመቀበል አይፈልግም›› ይለናል:: ነገር ግን ባለፉት ሃያ አንድ ዓመታት የኢሕአዲግ የፊት ገጽ ሆነው የቆዩት አቶ መለስን ኢትዮጵያውያን እንዴት ያዩዋቸዋል የሚለውን ለመረዳት የኢሕአዲግን የአስተዳደር ስረዓት በቅጡ መረዳት ያስፈልጋል::
ኢሕአዲግ በቁመናው ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ድርጅት ቢመስልም ሊቀመንበሩ አቶ መለስ ዜናዊ በጠና ታመዋል የሚል ወሬ ሲናፈስ በፓርቲው አባላት መንደር የሚስተዋለው አለመረጋጋት ብሎም የሚወራው የስልጣን ሽኩቻ የኢሕአዴግን ሀገር አቀፍነት ሳይሆን በአቶ መለስ ዜናዊ ሙሉ ቁጥጥር ስር የወደቀ ፓርቲ መሆኑን የተለያዩ ተንታኞች ይናገራሉ:: አቶ መለስ እና ደጋፊዎቻቸው ኢትዮጵያን በአዲስ መንገድ ለመስራት መንገድ ጀምረናል ብለው ቢናገሩም ከተቀናቃኞቻቸው እና ተቃዋሚዎቻቸው ግን ቀድሞ ከነበሩት የኢትዮጵያውያን የአገዛዝ ስርዓቶች ምንም የተለያ ነገር እንዳላመጡ ይባሱንም ሀገሪቱ የነበራትን መልካም እሴቶች እንዲሸረሸሩ ምክንያት ሆነዋል ብለው ይወቅሷቸዋል::

በቅርቡ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ የአቶ መለስን የሃያ አንድ አመት አስተዳደር ስርዓት በማስመልከት በሰማያዊ ፓርቲ ጋባዥነት ባደረጉትን ንግግር ላይ የአቶ መለስን ስርዓት ከበፊት ስርዓቶች ጋር በማነፃፀር ተናግረዋል:: እንደ ዶክተር ዳኛቸው አገላለፅ የዐፄ ኃይለሥላሴ የፈረስ ስም “ጠቅል” ነበር። ስርዓታቸውና የፈረሳቸው ስም የተዋሃደ ነበር። ፈረሱን ተምሳሌታዊ ያደርጋሉ “ጠቅል” ሲሉ ፍፁማዊ ስርዓት (Absolute State) እየፈጠሩ ነበር። የሰሜኑን ባላባቶች ተራ በተራ በፖለቲካ ካሸነፉ በኋላ “ጠቅል” ነው የሆኑት። እንደ ዐፄ ቴዎድሮስ “አገር በእጄ” ነው ያሉት። ዐፄ ኀይለ ሥላሴ ቢያንስ ግልፅ ነበሩ። የአቶ መለስ ስርዓት ግን ለየት ያለ “የጠቅልነት”(“Absolutism”) ባህሪ የሚስተዋልበት መሆኑን አስረድተዋል:: ይህ የአቶ መለስ ስርዓት ለየት ያለ “የጠቅልነት”(“Absolutism”) ባህሪ ያለው ሲሆን ምንም ዐይነት ተቀናቃኝ ኃይል የማያስተናግድ እና የተደራጀውንም ሆነ ያልተደራጀውን የማይታገስ ፍፁማዊ ነው። በተጨማሪም የአቶ መለስን የኢሕአዲግ አገዛዝ የዴሞክራሲ ማዕከላዊነት (Centralized Democracy) የሚተገብር ነው ብለው ገልፀውታል::
የመለስ ፊት ደጋግ ስጦታዎቸ ለኢትዮጵያ
አቶ መለስ ዜናዊ በሰብዓዊ መብት አያያዝ እና በሌሎች በርካታ ጉዳዮች የሰላ ሂስ ቢሰነዘርባቸውም በደጋፊዎቻውም ሆነ በተቃዋሚዎቻቸው ዘንድ የሚመሰገኑበት ደጋግ ተግባራት አሏቸው:: ከነዚህ በቀዳሚነት የሚነሳው ፍትሐዊ አይደለም ቢባልም የኢኮኖሚ እድገቱ ነው:: ከዚህ በተጨማሪ በቀድሞዎቹ የሊቢያው መሪ ሞአመር ጋዳፊ እና በሴኔጋሉ መሪ አብዱላሂ ዋዴ የአፍሪካ ሕብረትን መቀመጫ ከአዲስ አበባ ወደ ሀገራቸው ለመውሰድ የተለያዩ ማባበያዎችን በመጠቀም ቢሞክሩም በአቶ መለስ አንደበተ ርቱዕነት ተሸንፈው የኅብረቱ መቀመጫ ከታሪካዊ ቦታው ሳይነሳ ቀርቷል:: ነገር ግን ዘግይተዋል አልያም ለፖለቲካ ፍጆታ አውለውታል ተብለው ቢታሙም የታላቁ የአባይ ግድብ ስራ ጅማሮም ሌላው አቶ መለስ ሊታወሱበት የሚችሉበት ደግ ተግባራቸው እንደሆነ ብዙዎች ይመሰክሩላቸዋል:: አቶ መለስ በተለያዩ ዓለምአቀፍ ስብሰባዎች የኢትዮጵያን አልፎም የአፍሪካን ጉዳዮች በማስረዳት የአፍሪካ መሪ የሚል ስያሜ እንዳተረፉ ከተለያዩ ጽሁፎች መረዳት ይቻላል::
መለስ ለኢትዮጵያ ንፍገት እና ክፋት
‹‹አንድ ሺኅ አራት መቶ ማይልስ የሚያህል የውኃ ጠረፍ ካስረከብን በኋላ አራት መቶ ኩንታል ድንች ለማያመርት ቦታ ከ50 እስከ 60 ሺሕ ወጣት በጦርነት ገብረናል›› ይላሉ ዶ/ር ዳኛቸው አሠፋ የኤርትራ መገንጠልን ተከትሎ ሀገሪቱ ወደብ አልባ መሆኗን እና ሁለት ዓመት የቆየውን የኢትዮ ኤርትራን ጦርነት ክስረት በአንድ ላይ ለማውሳት:: ይህ እንግዲህ የአቶ መለስን ንፍገት እና ክፋት ለማውሳት ተችዎቻቸው በቀዳሚነት የሚያነሱት ተግባራቸው ነው:: በስምም ቢሆን ሕገ መንግስታዊ ስርዓት አቋቁመው በሕገ መንግስቱ ላይ የተዘረዘሩትን ሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ሸራርፈዋል፤ በሕገ መንግስቱ የተረጋገጡ መብቶችን የሚደፈጥጡ አዋጆችን አውጥተው የዜጎችን መብት ገፈዋል የሚሉ ሂሶችም ከአቶ መለስ ተቃዋሚዎች ተዘውትረው የሚደመጡ ትችቶቻቸው ናቸው::

ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ Diciphering Meles Zenawi’s haterade to Ethiopia በሚለው አንድ በቅርቡ ባሳተሙት ጽሑፋቸው ‹ኢትዮጵያን ሳይወዱ ኢትዮጵያን ያስተዳደሩ ብቸኛ መሪ› በሚል በአቶ መለስ ላይ የሚሰነዘሩ ትችቶችን ባጠናከሩበት ጽሑፋቸው አቶ መለስ ሀገራቸውን የማይወዱበትን ምክንያት የተለያዩ የስነልቦና ኀልዮቶች በማንሳት አስረድተዋል:: በብሔር ብሔረሰቦች መብት መረጋገጥ ስም በርካታ የብሔር ሥራ ፈጣሪዎች (Ethnic entrepreneurs) በየሰፈሩ እንዲፈለፈሉ ምክንያት ሆነዋል የሚል ትችትም ከአቶ መለስ ስም ጋር በተደጋጋሚ የሚነሳ ጉዳይ ነው:: አቶ መለስ አንደበተ ርቱዕ እንደሆኑ በደጋፊዎቻቸው ቢመሰከርላቸውም ሌሎች ግን ‹በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የነበሩ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮችን በማንጓጠጥ እና አግባብ ያልሆኑ ቃላትን በመጠቀም ይናገራሉ፤ ይህም ከአንደበተ ርቱዕነት አቅም ማጣት የሚመነጭ ነው› በማለት በተቃራኒው ይተቿቸዋል:: የኢትዮጵያ ታሪክ ለነገሥታቱ የሚወግን ታሪክ በመባል በሚዛናዊነት በተለያዩ ወገኖች ይወቀሳል፡፡ ቀጣዩ የኢትዮጵያ ታሪክስ፣ ከመቶ ዓመታት በኋላ የአቶ መለስን ታሪክ እንዴት ያስታውሰው ይሆን?

ጋዜጣና መጽሔቶቻችን ከሰኞ እስከ ሰኞ – ሰባት

(ከሐምሌ 9፣ 2004 እስከ ሐምሌ 15፣ 2004)
ሪፖርተር  በረቡዕ ዕትሙ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በመልካም ጤንነት ላይ መሆናቸው ተሰማ›› የሚል ዜና አስነብቦናል፡፡ ‹‹በ21 ዓመታት የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በጤንነት ችግር በ19ኛው የአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ ላይ ያልተሳተፉት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በመልካም ጤንነት ላይ መሆናቸው ተሰማ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጪዎቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ የውጭ ሕክምና ክትትላቸውን ጨርሰው ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለሱም ምንጮች ገልጸዋል፡፡ …››
** ** **
‹‹የሚኒስትር ጁነዲን ሳዶ ባለቤት ከሳዑዲ ዓረቢያ የሃይማኖት አታሼ ቢሮ ገንዘብ ይዘው ሲወጡ ተያዙ›› የሚል ዜና ያስነበበን ሰንደቅ ጋዜጣ ነበር፡፡ ‹‹…[ወ/ሮ ሃቢባ ሐምሌ 10፣ 2004] …ግምቱ ከሃምሳ ሺ እስከ መቶ ሺ ብር የሚገመት የታሰረ ገንዘብ እና በዓረብኛ የተጻፉ መጽሐፍት ይዘው ሲወጡ እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን ምንጮቻችን ገለጹ፡፡…››
** ** **
ፍትህ ጋዜጣ ከጋዜጦች ሁሉ ተለይቶ በዚህ ሳምንት አልወጣም፡፡ የጋዜጣው ከፍተኛ አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝ በፌስቡክ ገጹ ችግሩ ከአሳታሚው አለመሆኑን እንዲህ ሲል ተናግሯል፡፡ ‹‹ዛሬ አርብ ነው፤ ፍትህ ግን አንባቢያን ጋር አልደረሰችም፡፡ በእርግጥ ትላንት የጋዜጣው የሽያጭ ሰራተኛ ብርሃና ሰላም ማተሚያ ቤት ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ተገኝቶ ለ30 ሺህ ኮፒ 80385 (ሰማኒያ ሺህ ሶስት መቶ ሰማኒያ አምስት) ብር ከፍሏል፡፡ የፍትህ ህትመት ክትትልም እኩለ ሌሊት ላይ ማተሚያ ቤት ቢደርስም የህትመት ክፍል ሀላፊው ‹‹ፍትህን እንዳታትሙ ተብለናል›› በሚል ጋዜጣዋ ሳትታተም አደረች፡፡

‹‹በዛሬው ዕለትም የማተሚያ ቤቱን ምክንያት ለማወቅ ወደ ብርሃና ሰላም ከጥቂት ባልደረቦቼ ጋር ሄድኩኝ፡፡ ሆኖም ምክትል ስራ አስኪያጁ ከሌሎች የድርጅቱ ሀላፊዎች ጋር በመሆን ስብሰባ ቢጤ አድርገን እንድንወያይ ጠየቁን፡፡ ተወያየን፡፡ በፊት ገፅ ላይ ያለ አንድ ዜና ማንሳት እንዳለብን ከመጠቆም ባለፈ እዚህ ጋር የማልገልፀውን እጅግ አሰፋሪ የሆነ መደራደሪያ አቀረቡ፡፡ እኛም የሀገሪቱን ህግ ጠቅሰን ተከራከርን፡፡ ያለስምምነት ከሰዓት 8፡30 ላይ ተወያይተው ውሳኒያቸውን ሊያሳውቁን በቀጠሮ ተለያየን፡፡ ቀጠሮውንም ተቀብለን ስንወጣ ከተሰበሰብንበት የም/ስራ አስኪያጁ ትንሿ አዳራሽ በር ላይ የፍትህ ሚንስቴር ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች እና ዓቃቢ ህግ ተቀምጠው አየናቸው፡፡ በር ላይ ደግሞ በመልክ የምናውቃቸው በርከት ያሉ የፀጥታ ሰራተኞች እንደተለመደው አጀቡን፡፡ ይህንን በዕምሮአችን ይዘን ወደቢሮአችን ተመለስን፡፡ ሰዓቱ እስኪደርስ ለምሳ ወጣን፡፡ ምሳ ለመብላትም ካሳንችስ አካባቢ አንድ ምግብ ቤት ገባን፡፡ ተመግበን ስንወጣም አደባባይ ላይ የመኪናዬ ጎማዎች ፈንድተው አገኘን፡፡ ከዛም ከሰዓት በኋላ በቀጠሮአችን ሰአት ም/ስራአስኪያጁ ቢሮ ስንደርስ ‹‹እንዲታተም ተፈቅዷል›› የሚል መልስ ተሰጠን፤ እናም ጋዜጣዋ አሁን እየታተመች ነው፡፡ ነገ ጠዋት ትወጣለች ብለንም እንጠብቃለን፡፡››
ተመስገን እንዲህ ቢልም ፍትህ ጋዜጣ ቅዳሜም ገበያ ላይ አልዋለም፡፡ ይህንንም ተከትሎ ተመስገን ይህንን ጽሁፍና የደብዳቤ ኮፒ አያይዟል፡፡ ‹‹በትላንትናው ዕለት ለስርጭት መብቃት የነበረባት ፍትህ የጠቅላይ ሚንስትሩን መታተም ተከትሎ በተፈጠረው የስልጣን ትግል እያሸነፈ በመጣው አክራሪ ሀይል ተስተጓጉላ የነበረ ቢሆንም በማግስቱ እንድትታተም ተፈቅዷል ተብሎ ታተመች፡፡ ትላንት ከምሽቱ 2 ሰዓት ላይም ሙሉ በሙሉ ታትማም አለቀች፡፡ ነገር ግን አንባቢያን እጅ ልትደርስ አልቻለችም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ (በዛው ኃይል ትዕዛዛ ይመስለኛል) በአቃቢ ህግ ብርሃኑ ወንድምአገኝ ‹‹ለሀገር ደህንንት የሚያሰጋ ዘገባ በጋዜጣው ላይ መታተሙ መረጃ ስለደረሰን እንዲታገድ ወስነናል›› በሚል የተፈረመ የዕግድ ደብዳቤ ማተሚያ ቤቱ እንደደረሰው ገለፀልን፡፡ በዚህም ምክንያት በአሁኑ ሰዓት 30 ሺህ የፍትህ ጋዜጣ እትም በብርሃና ሰላም ማተሚያ ቤት ተቆልፎበት ይገኛል፡፡
…እንዴት ነው ነገሩ? ‹‹ትሻልን ፈትቼ ትብስን አገባሁ›› እየሆነ ነው? ይህ ሁኔታ ወደስልጣን እየመጣ ያለው ሀይል የባሰ እንደሆነ ምልክት እያሳየስ ይሆን? ለማንኛውም መጨረሻውን አይተን የራሳችንን እርምጃ እንወስዳለን፡፡ (ማተሚያ ቤቱ ለጋዜጣው ዝግጅት ክፍል የላከውን ደብዳቤ እዚህ ይመልከቱ)››
— — —
በተያያዘ ዜና፣ ‹አልቁዱስ› የተባለው የሙስሊሞች ጋዜጣ የሚታተምበት ማተሚያ ቤት በመታሸጉ ‹ዘገነርስ› የተባለው የአርብ ስፖርት ጋዜጣም ሳይታተም ቀርቷል፡፡ አርብ ዕለት ይወጣ የነበረው ‹ነጋ ድራስ›ም በዚህ ሳምንት ገበያ ላይ አልዋለም፡፡
** ** **
አዲስ አድማስ ጋዜጣ በፊ ገጹ ‹‹አዲሱ የመንግስት ቤቶች የመሸጫ ዋጋ ይፋ ሆነ›› ይላል፡፡ አነስተኛ ገቢ ያቸው ዜጎች በ26ሺ ብር የቤት ባቤት ይሆናሉ፣ በቀጣዩ ዓመት 10ሺ ቤቶች ይገነባሉ፡፡ ‹‹… በነዚህ ፕሮጀክቶች ውስጥ ለመታቀፍ የቤቱን ሽያጭ ዋጋ 40 በመቶ በመቆጠብ 60 በመቶውን ከባንክ በሚገኝ ብድር የቤት ባለቤት ለመሆን እንደሚቻልም ሚኒስትሩ ተናግረዋል…››
** ** **
‹‹Meles Back in Town›› (መለስ ወደከተማ ተመልሰዋል) የሚል የፊት ገጽ ዜና ያስነበበን Fortune ነው፡፡ በዝርዝሩም፣ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ መግለጫ በተሰጠ ማግስት (አርብ ዕለት) ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደአዲስ አበባ መግባታቸውንና የጤንነታቸውም ሁኔታ በጣም እየተሻሻለ መምጣቱን ምንጮቼ ነገሩኝ ብሎ ዘግቧል፡፡
ሌላም፣ ሌላም
  • ኢትዮጵያን አይዶል ክብሩን ያጣ ፕሮግራም ነው፣ ባለሙያዎቹ ምንም ነገር የማያውቁ ናቸው ተብያለሁ – አቶ ይስሐቅ ጌቱ (የኛ ፕሬስ)
  • የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መራራ የዕድገት ሽሙጦች፤ 140 ሺ ቶን ጫት በየዓመቱ ይቃማል፣ 7 ቢሊዮን ብር ለጫት ፍጆታ ይውላል – መሰናዘሪያ
  • አንድነት በሰላማዊ ትግል ለሚመጣ ችግር ኃላፊነቱን እወስዳለሁ አለ፤ ለጠ/ሚስትሩ መልካም ጤንነት ተመኝቷል፡፡ – አዲስ አድማስ
  • ከኮሌስትሮል ነፃ የሚባለው የፓልም ዘይት ነፍሰገዳይ መሆኑን ያውቃሉ? – ኢትዮ ቻናል
  • ንግድ ባንክ የሚድሮክ የሚድሮክ ኩባንያዎችን በ942 ሚሊዮን ብር ብድር አንበሸበሸሪፖርተር (እሁድ)
ርዕሰ አንቀጾች

የመለስ ዜናዊ ፲ ታላላቅ የአፍ ወለምታዎች

የዞን ዘጠኝ ነዋሪዎች የሆኑት በፈቃዱ ዘ ኃይሉ የመለስ ዜናዊ ‘ሀሁ’ በስልጣን ጎዳና እንዲሁም ዘላለም ክብረት መለስ ወደ ውጭ – መለስ ከውጭ በሚል ርዕስ ሁለት ጦማሮች አስነብበውናል፡፡ ይህም ስለጠቅላያችን የጤና ሁኔታ ከነበረው ውዝግብ መለስ ብለን ሌሎች ሁኔታዎች እንድንቃኝ ዕድል ሰጥቶናል ፡፡ዛሬ ቀኑ ቅዳሜ ነው፤ እሰኪትንሽ ቅዳሜ ቅዳሜ የሚሸት ነገር እያወራን ዘና እንበል በሚል ደግሞ ይችን ጽሑፍ ከዱራሜ ዶት ኮም ያገኘነውን የጠቅላያችንን አስር ታላላቅ የአፍ ወለምታዎች ፣ በዚህ ንግግራቸው የተገረመው አብዛኛው ሰው ወደሚሰማው ቋንቋ እንደወረደ ተርጉመን ለአደባባይ አውለነዋል፡፡
፲. በ1983  ዓ.ም. በለንደኑ ጉባዔ  በኢህአዴግ ታርጋ የተሰባሰቡት ቡድኖች የፓርቲያቸው ህወሓት ተቀጥላ እንደሚሆኑ ለአሜሪካና ብሪታኒያ ባለስልጣናት አረዷቸው፡፡ብሪታኒያውያኑ ይህንን በተቃወሙ ጊዜ ቁጣቸው በግልጽ የሚታየው አቶ መለስ እንዲህ አሉ፡፡
     “አንድ ነገር ግልጽ ላድርግ  ፤ ከጉባዔው በኋላ  ኢህአዴግ የሚባል መንግስት አይኖረንም፡፡”
           
፱.  በ1985/6  ዓ.ም. ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ያላቸውን እይታ በአንድ ቃለ መጠይቅ ማብቂያ ላይ እንዲያካፍሉ ከአንድ ዘጋቢ ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ መለስ እንዲህ ሲሉ መለሱ፡፡
     “የኢትዮጵያ ዕድሜ መቶ አመት ብቻ ነው ፤ከዚህ በቀር ሌላ  የሚያወሩት ራሳቸውን በተረት ተረት እያሞኙ ነው፡፡” 
፰. በ1986/7 ዓ.ም. አስመራ ከተማ ውስጥ  ለአንድ የውጭ ሀገር ጋዜጠኛ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ስለ ኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቅ እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
    “ከኢሳይያስ ጋር አንድ ሰዓት ማሳለፍ፣ 10 መጽሐፍ ከማንበብ በላይ ልበብሩህ፣ አዋቂ እና ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡”
፯. ለአምስት አስርት ዓመታት የኢትዮጵያን ታሪክ ካጠኑት ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን ጋር በ1989 ዓ.ም.  በነበራቸው ወይይት ከምንሊክ ወረራ በፊት ኢትዮጵያ የምትባል አንዲት  አገር እንዳልነበረች ተናገሩ፡፡ይህ የበለጠ አጽንኦት ለመስጠት ሲሞክሩ እንዲህ አሉ፡፡
      “ትግሬዎች የአክሱም  አላቸው ፤ ይህ ለጉራጌ ምኑ ነው? አገዎች ላሊበላ  አላቸው ፤ ይህ ለኦሮሞ ምኑ ነው? ጎንደሬዎች ቤተ መንግስት አላቸው፤ ይህ ለወላይታ ምኑ ነው?”
፮. ለመንግስት ሚዲያዎች በሰጡት አንድ ቃለ መጠይቅ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ከጨርቅነት የዘለለ ምንም እንዳልሆነ ተናገረዋል፡፡
      “ባንዲራ የጨርቅ ቁራጭ ነው”
፭. በ1990 ዓ.ም. ሰማኒያ ሺ የሚደርሱ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ኤርትራውያንን ሀብት ንብረታቸውን ቀምተው  ኢ-ሰብዐዊ በሆነ መልኩ ከሀገር ካስወጡ በኃላ ለፓርላማው እንዲህ አሉ፡፡
      “የአይናቸው ቀለም ካላማረን ፣ ከሀገራችን የማባረር መብት አለን፡፡”
፬. በ1993 ዓ.ም. ልጇ ወደ ኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ዘምቶ አለመመለሱ ያሳሰባት  እናት ልጇ ወዴት እንዳለ መለስ ዜናዊን  አጥብቃ ጠየቀች፡፡በጥያቄዋ ድምጸት የተበሳጩት አቶ መለስ እንዲህ ሲሉ መለሱ፡፡
      “ሴትዮ፣ ልጅሽ በስድስት ወራት  ወደቤቱ ካልተመለሰ ፣ መልሱን ታውቂዋለሽ፡፡”
፫. በ1997 ዓ.ም. ምርጫን ተከትሎ በተካሄደው  ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ  በጠቅላያችን ትዕዛዝ 193 ያልታጠቁ ንጹሐን ዜጎች በአዲስ አበባ እንዲገደሉ ትዕዛዝ  ሲሠጡ የትግራዋይ ተወላጅ ለሆነው ለታማኛቸው ጄኔራል ሳሞራ አማራዎችን ለማለት አህዮች የሚለውን ቃል ተጠቅሟል፡፡
      “እነዚህ አህያ አማራዎች  ትምህርት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ሰላማዊና  ሃይማኖተኛ  የሚሆኑት ክላሽንኮቭ ስትደግንባቸው ብቻ ነው፡፡”
፪. ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ የከሸፈ ፣ ተከተታይ ወረራ   በ1998 ዓ.ም.  በሱማሊያ መሬት ላይ መሬት ያዛ በነበረበት ሰዓት ለ ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ አላማቸው የኢስላማዊ ፍርድ ቤቶች ህብረትን ለማንበርከክ ሳይሆን በዚያ የሌሉትን በሱማሊያ የሚገኙት የኤርትራ ወታደሮች ለማሰደድ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
     “እያጠቃን ያለነው   በሱማሌ ወይዛዝርት ቀሚስ ስር  የተሸሸጉ የኤርትራ ኃይሎችን ብቻ ነው፡፡”
፩. በ2002 ዓ.ም. ከሊቢያው አምባገነን ሙዐመር ጋዳፊ ጋር ስለ ሁለትዮሽ ግንኙነት በሚወያዩበት ጊዜ አቶ መለስ እንዲህ አሉ፡፡
       “እኔ የመናዊ ነኝ ፤ የመናዊ እንደሆንኩኝ አውቃለው ፤ ሁላችንም የመናውያን ነን፡፡ ከነገሥታቱ  ቤተሰብ በቀር ሁላችንም አረብ ነን፡፡”