Monthly Archives: August 2012

ሐዘን የሸሸገው ፈገግታ


ሐዘን አጥንት ሲደርስ ደግ አይደለም:: ሰውም እግዜሩም አይወዱትም:: ለአገርም አይጠቅምም ለጠላትም ደስ አይበለው:: እንዲህ አገር ነቅሎ ሙሾውን ሲያስነካው ተዉ እሚል ይጥፋ? ምስኪን ትዝ አለኝጃንሜዳ ጋር ሞቶ እሚቀብረው ሲያጣ አዝኖ ወደቤቱ የተመለሰው ሃሃሃሃ…:: ለማንኛውም ሕገ መንግስቱ እንደሚለው የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲያርፍ ወይም በሞት ሲለይ አንድ ቀን ብሔራዊ ሃዘን ይታወጃል:: እንደ በረከት ስምኦን ቢሮ አሥራ አራት ቀን መሆኑ ነው:: [በየቀኑ የሚጣስን ሕገመንግስት አንስቶ መከራከሩ ፅንፈኛ ያስብለኛል ስለዚህ ይለፈኝ] በዛ ላይ ዋሽንት አለ [ለአንዳንዶች vuvusela ሆኖባቸዋል]:: ስለዚህም እንደ አንድ ሐዘናችንን ለማስረሳት እንደሚጥር ልማታዊ አፅናኝ በለቅሶው አካባቢ ከተሰሙት ንግግሮች ጀምሮ ወሬው እንዳመራን ውል አልባ ጨዋታ ብንጨዋወትስ
ሰሞኑን እንደ ጆሮ ስቃዩን ያየ (ሰደቃውን የበላ) የለምጆሮ ሆይ አድናቂህ ነኝ!
የልማታዊው በረንዳ አዳሪ አስተያየት፣አባታችንን ተማምነን ነው በረንዳ የምናድረውየሚለው አስገራሚ ለቅሶ የልማታዊውን እስረኛ ሰሜ ባላገሩን ቃለ ምልልስ ያስታውሰናል፤በመታሰሬ በጣም ደስተኛ ነኝ መንግስቴንም አመሰግነዋለውነበር ያለው ሰሜ ከእስር ቤት እንደወጣ [ሰሜ ሮሚዎን ሆኖ ትያትር እንደተጫወተ ላስታውስ]፡፡ ሰሜን ተንጠላጥለን ወደ ሁዋላ ስንሄድታንክ ተደግፎ መጽሐፍ ያነብ ነበርያለው የኢትዮፈርስት ዌብሳይት  አዘጋጅ ቤን፣ “HR 2003 ከማፅደቃቸው በፊት የአሜሪካን ሴናተሮች ጉዳዩን መላልሰው እንዲያዩት የመከሩት የብቸና ገበሬዎችየአሜሪካንን ኢምፔርያሊዝም ከተሳሳተ ርዕዮተዓለሙ እንዲታረም ያስጠነቀቁት የቦረና አርብቶ አደሮች” …

ለቅሶው የኪራይ ሰብሳቢዎች መጠቀሚያ እንዳይሆን የመከሩምትን ጨምሮእንግዲህ ዓለም ምን ይዋጣት!” ብለው ስለ አለማችን ያለቀሱም ነበሩ:: ዲሞክራሲውን በተደላደለ መሰረት ላይ ማስቀመጣቸውእንደ ክርስቶስ ስለሰው ልጆች መሰዋታቸውንለዚህ ምስኪን ሕዝብ ሲሉ ፀጉራቸውን ተበጥረው፣ ቀበቶአቸውንም አስረው እንደማያውቁ ነግረው ክፉኛ አስደንግጠውናል:: ስለ ዴሞክራሲና ፍትህእኩልነት፣ምስክሮች ሰምተናል:: ነዋይምየሙሴን በትር የተቀበለሲል አቀነቀነ:: የዋልድባ ገዳም አባቶችምእናንተ ናችሁ መተተኞችተብለው መከራ አዩ ሲባልኢትዮጵያ ቀኑ ጨለመባትየሚልም መዝሙር ሰማንወይ ጆሮ:: ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያምም ከዋልድባአወልያና አበበ ገላው እንዲጠነቀቅ ምክር የለገሱ ብቅ አሉ:: የአባይ ግድብ በስማቸው እንዲሆን ወይንም አዲስ የብር ኖት በእርሳቸው ምስል እንዲታተም፣ ሐሳብ ያቀረቡና ጉዳዩን ሕዝባዊ ለማድረግ የሚሰሩም ታይተዋል:: የለቅሶ አይዶል ሊዘጋጅ እንደሚችልም ጭምጭምታ አለ::
አብዮታዊ ስያሜ ያላቸው ንግድ ቤቶችም ቁጥራቸው ጨምሯል፡፡
እነ “ጀግና አይሞትም ስጋ ቤት“፣ እነየስፎርሜሽን ዕቅዱ ይሳካል ሻይ ቤት“፣ እነ “ውሃ ማቆር ባርቤሪ“፣ እነ “አባይ ይገደባል ምግብ ቤት“፣ እነ “ቢፒ አር ልብስ ስፌት“፣ እነ “ባድሜ የኛ ናት የአልጀርሱ ስምምነት ውሳኔ ግን ተገቢ አይደለም ባልትና“፣ እነ “ሬነሳንስ ልማታዊ ቡና ቤት ለሐዘን ከሚሆን ጥሬና ጥብስ እና ከተከዘ አስተናጋጅ ጋር ተቀላቅሏል:: “ጣት እንቆርጣለንና በሊማሊሞ አቋርጡ ችርቻሮ መደብርሃሃሃሃ….
ስለ ደርግ ብዙ አላውቅም:: ትዝ እሚለኝሾላ እርግፍ እርግፍየሚባለው ጨዋታ ብቻ ነው:: እንግዲህ ዳርዳርታው ምነው አነሰ የሚል ክስ ከመጣ በሚል መሆኑ ነው:: ጎልማሶች እንደሚያወሩት ከሆነ ደርግን የሚስተካከል ያፈጠጡዉሃ የማያነሱና የጽሑፎቹ ቀለም ሳይደርቅ ዋጋ ቢስ የሚሆኑት መፈክሮችን ያህል ውሸት የባህሪው የሆነው ኢሕአዴግ እንኳን መፈብረክ አልቻለም::
ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደምተብሎ አብዮት ልጆችዋን በላችሲደመደምእንዲህም ተብሎ ሲገጠም
የሞተው ወንድምሽ
የገደለው ባልሽ
ሃዘንሽ ቅጥ አጣ
ከቤትሽም አልወጣ
ፖለቲካው ሴሰኛ ሲሆንባብዮት ግዜ የለም ትካዜእየተባለ ሲራገብበመጨረሻም በስሪያ ላይ ተጣበቀው ሰፈሩን የሚያሽኮረምሙትን ውሾች ቀጥቅጦ የሚያላቅ ወንድ ጠፍቶሁሉም ቤቱ መሽጎ!
በመሃልተፈጥሮን በቁጥጥር ስር እናውላለንየሚሉ መፈክሮች እስኪሰለቹ ሲለፈፉወይ ተፈጥሮ!!! ምን መስሎን ይሆን?!

ይህንን ያህል ከተጫወትን ይበቃናል:: ሐዘን ላይ ነሽና/ነህና ቀልደህ ሞተሃል ብንባል እንቀበላለን!

ከመለስ በኋላ!

በአዲስ አበባ ዪኒቨርስቲ የፍልሰፍና መምህር እና ከጥቂት የአደባባይ ምሁራን አንዱ የሆነውን ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋን አነጋግረን  ስለወቅቱ ማሕበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ የተለያዩ  ሐሳቦችን ማቅረባችን ይታወሳል፡፡አሁን ደግሞ የአቶ መለስን ‘ድንገተኛ!?’ ሞት  ተከትሎ በድኀረ-መለስ  አትዮጵያና በሌሎች ተያያዥ ጉዳየች ዙሪያ እንደተለመደው ገዢ ሐሳቦቹን ሰጥቶናል፡፡ መልካም ንባብ

የመርዶው ሕዝባዊ ምላሽ
እንደሚታወቀው ለሀያ አንድ አመታት በሙሉ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥኑን መስኮት አጣበው ይዘውት የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መለስ ዜናዊ ናቸው፡፡እንዲሁም በከፍተኛ ሁኔታ ተክለ ስብዕናቸውና ስራቸውን በሚዲያው ሲገነባላቸው የቆዩት ጠቅላይ ሚኒስተር በድንገት የህይወታቸውን ህልፈት ህዝቡ ሲሰማ  ድንጋጤና ሀዘን ፈጠሮበታል፡፡ይህንንም የህዝብ  ሀዘን በሁለት አቅጣጫ ልናየው እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው አስከሬናቸው ከውጭ ሀገር በገባበት ምሽት ከተጠበቀው በላይ ህዝብ ወጥቶ ብሶቱን እና ሀዘኑን ገልጿል፡፡ ምናልባትም ህዝብ ላሳየው የሐዘን ጎርፍ አንድ ወሳኝ የሆነ ነገር መገንዘብ የምንችለው ህዝቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ፓርቲው ከሚያራምደው የጎሳና የነገድ ፖለቲካ ውጪ እንደአንድ ኢትዮጵያዊና እንደግለሰብ አይቶ እንዳዘነላቸው መረዳት አያስቸግርም፡፡ በተጨማሪም  እሳቸው በህይወት እያሉ ለያይተው ያዩት ህዝብ ሲሞቱ ግን እርስ በርስ ሳይለያይ በህይወት እያሉ ያላያያዙትን ህዝብ በሞታቸው ሊያያይዙት ችለዋል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ እየተመለከትን ያለነው የህዝቡን ስሜት ለፖለቲካ ግብአታቸው ለመጠቀም ስትራቴጂ ነደፈው ፣ በተደራጀ መልኩ እንቅሰቃሴ ውስጥ መግባታቸውን ነው፡፡ ከዚህም አኳያ መንግስት ሊያደርግ የሚፈልገው አቶ መለስ ኖረም አልኖረም ህዝቡ የስርዐቱን መቀጠል እንደፈለገና ተቀባይነትም እንዲኖረው ማድረግ ነው፡፡ ይህንንም ለመተግበር በብሔራዊ የቀብር ስነ ስርዓት አስፈጻሚ ኮሚቴ ስም የህዝቡን ስሜት ወደፈለጉት አቅጣጫ ተቆጣጥሮ ለማዞር የሚያስችል ኮሚቴ ተቋቋሞ በስራ ላይ እያየነው ነው ፡፡ በመሆኑም መልስ አዘል ጥያቄ በማቅረብ ህዝቡ እንዲናገር በማደረግ ፣ በየሰፈሩ ድንኳን በመትከል ፣ በካዴሬዎች አማካኝነት በየመስሪያ ቤቱ መመሪያ በመስጠት ወዘተ… የህዝቡን ስሜት ለፖለቲካ ግብዐት እየተጠቀሙበት ይገኛል፡፡ለማጠቃለልም ብዙ ሀዘንተኞች የተጀመረው ፕሮጀክት ከፍጽሜ  እንዲደርስ በርግጥ ቢጠይቁ የመንግስት ኮሚቴ እንደተመኘው  የኢህአዴግን ስርዓት ቅጥያ ሲጠይቁ አልተደመጡም ፡፡ ምን አልባትም ህዝቡ በፕሮጀክት እና በስርዐት መካከል ያለውን ልዩነት የተረዳ ይመስላል፡፡
የስልጣን ሽግግር
የደህረ መለስ መንግስት ምን አይነት የፖለቲካ መንገድ እንደሚይዝ ከመተንተናችን በፊት  ወደኃላ መለስ ብለን ከቅርብ ታሪካችን እና ከፖለቲካ አንጻር ጥቂት በእንበል፡፡
ሀ. ከታሪክ ማህደር
ዶ/ር ሌቪንን “Wax and Gold” በተሰኘው መጽሐፍ ገጽ 152 ላይ  እንዲህ ይላል፡፡
“Successors to the throne were not determined according to fixed rule like primogeniture. Membership in the Solomonian line was normally a prerequisite……Usually however there were several legitimate candidates for the position and the absence of fixed procedures for choosing among the meant that the death of an emperor was often a time of confusion and political improvisation.” 
“የመንበሩ ወራሾች በተደነገገ ቋሚ መመሪያ አልነበረም የሚወሰኑት፡፡ በሰለሞናዊ ስርወ መንግስት መስመር ውስጥ አባል መሆን በጥቅሉ እንደቅድመ ሁኔታ የተቀመጠ ነው… በተለምዶ፣ ምንም እንኳን ቦታውን የሚመጥኑ ብዙ ሕጋዊ(ሰለሞናዊ) እጩዎች ቢኖሩም፣ አንዱን ለመምረጥ የሚያስችል ውሱን መስፈርት ባለመኖሩ የንጉሠነገሥት ሞት ሁልጊዜም ውዥንብር እና ፖለቲካዊ ፈጠራን/ውሳኔን ይጠይቃል፡፡” (ትርጉም የዞን ዘጠኝ)
በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ሰላማዊና ሕጋዊ የሆነ የስልጣን ሽግግር በአብዛኛው ተካሄዶ አያውቅም፡፡ እንደ ዕውቁ ሶሾሎጂስት አገላለጽ ይህም የሆነበት ምክንያት
 •   አንደኛ የስልጣን ሽግግር ህጉ በደንብ አለመቀመጡ
 •  ሁለተኛ ስልጣን ለመያዝ (ዘውድ ለመጫን)  የሰለሞናዊ ስርወ-መንግስት የግዴታ ተወላጅ  መሆንና
 •   በአንድ ጊዜ  ከሰለሞናዊው ስርወ መንግስት ተወላጅ የሚሆኑ ብዙ ተወዳዳሪዎች ለቦታው ብቁ ሆነው መገኘታቸው፤

በመሆኑም ወደ ኢህአዴግ ዘወር በምንልበት ጊዜ ከላይ የጠቀስናቸው ታሪካዊ ክፍተቶች ዛሬም እንደትላንቱ ኢህአዴግም የዘረጋው ስርዓት አልተሻገራቸውም፡፡ ይህንንም ስንል  በሕገ መንግስቱ ላይ በግልጽ የሰፈረ   ቋሚ የስልጣን ሽግግር ህግ የለም፡፡ በተጨማሪም ትላንት ዘውድ ለመጫን የሰለሞናዊው የዘር ሀረግ አስፈላጊ እንደነበረው አሁን ደግሞ ስልጣን ለመጨበጥ የኢህአዴግ አመራር መሆን የግድ ነው፡፡በመሆኑም ለሰለሞናዊው የሽግግር ጥያቄም ሆነ ለአሁኑ ጊዜ በርካታ ተቀራራቢ ዕጩዎች ወይም ተወዳዳሪዎች መኖራቸው ሽግግሩን ውስብስብ እና አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡
ለ. ከፓለቲካ ዳራ
አሁን ለተነሳው የሽግግር ጥያቄ መልስ ለማግኘት የጠቅላይ  ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ አመራር ምን አይነት  መልክ የያዘ ነበር የሚለውን ማወቅ ይገባናል፤ምክንያቱም በየትኛውም የዓለማችን ክፍል እንደሚታየው የስርዓቱ ዲሞክራሲያዊ ወይንም ኢ-ዲሞክራሲያዊ መሆን  በስልጣን ሽግግሩም ላይ ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡ ምንአልባት ይህንን ዐሳብ የበለጠ ለማብራራት የሀኛያው ክፍለ ዘመን የፓለቲካ ፍልስፍና መምህርት ከነበረችው ሐና አረንት  (Hanna Arendt) ትንሸ እንውሰድ፡፡
እንደ ሐና አረንት አመላካከት የዴሞክራሲያዊ ስርዓት አገዛዝ የ’ስልጣን መርህ’(authority principle) ሲከተል  ኢ-ዲሞክራሲያዊ አገዛዝ በአንጻሩ ደግሞ በ’መሪ መርህ’ (leadership principle) ይተዳደራል፡፡ በ’ስልጣን መርሕ’ የስልጣን ተዋረዱና ክፍፍሉ  በሀገሪቱ ህግ በዝርዘርና በግልጽ ተለይቶ ይቀመጣል፡፡በሌላ በኩል በ’መሪ መርሕ’  የሚታዳደሩ ሀገሮች ግን ይህን በተመለከተ የስልጣን ተዋረድ የላቸውም፡፡ ስልጣኑ ተጠቃሎ በመሪው እጅ ይገኛል፡፡ከመሪው ቀጥሎ ሁለተኛ የሚባል ለይስሙላ ይቀመጣል እንጂ መሪው አንድ ነገር ቢሆን በሁለተኛ ደረጃ የተሰየመው ሰው ይተካዋል ማለት አይደለም ፡፡ ለማጠቃለል የሀና አረንት አቀራረብ የሚያስተምረን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ማለት ከ’መሪ መርህ’ ወደ ‘ስልጣን መርህ’ መሸጋገር  ማለት ነው ፡፡ በኢትዮጵያ ሀገ መንግስታዊ ሰርዓት ሲዘረጋ ይህ ታስቦ ቢሆንም የዲሞክሪያሲያችን ጨቅላነት የመሪዉን ጫንቃ መሸከም ስላቀታት ዴሞክራሲው በአጭሩ ተቀጭቶ በ’መሪ መርህ’ ለመመራት በቅተናል፡፡
ድኅረ መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያ (Post; Capital ‘P’ or Small ‘p’)
የእንግሊዘኛውን ‘post’ የሚለውን ቃል ለሁለት ከፍለን ብንመለከተው ለትንተናችን አመች ይሆናል፡፡  ካፒታል ‘ፒ’ እና ስሞል ‘ፒ’ ብለን እንከፍለዋለን፡፡ ካፒታል ‘ፒ’ ተጠቅመን ድህረ(Post) ስንል consequential  መሰረታዊ የለውጥ ሂደቶችን  የካተተ ማለት ሲሆን ባንጸሩ ስሞል ‘ፒ’  ስንጠቀም ደግሞ መሰረታዊ ያልሆነና ፋይዳ ያለው ለውጥና ሽግግር የማይታይበት ሆኖ እናገኛዋለን፡፡  ለምሳሌ በአረብ ሀገራት በቅርቡ የተነሳው አብዮት  መሰረታዊ የስርዓት ለውጥ ስላስከተለ ካፒታል ‘ፒ’   ነው፡፡በሌላ በኩል  ከአንዋር ሳዳት ወደ  ሙባረክ  የነበረው ሽግግር ግን ምንም የስርዓት ለውጥ ስላልታየበት  ስሞል ‘ፒ’  ነው ፡፡
ከሁሉ አስቀድሞ ከላይ በትንሹ ልንጠቅሰው እንዳሰብነው አሁን አመራር ላይ ያሉት ባለስልጣናት የድህረ መለስን ስርዓት እንዳለ እንዲቀጥል እና ሽግግሩም ስሞል ፒ’  እንዲሆን ይፈልጋሉ፡፡ለዚህም ነው አስቀድመው “የፓርላማ አባላቱን በአስቸኳይ ሰብስበን አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝን ከጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስቴርነት  ወደ ቋሚ ጠቅላይ ሚኒስቴርነት እንለውጣለን” የሚል ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት፡፡
መንግስት እንዳሰበው የስርዓቱ ሕልውና በምንም መልኩ ጥያቄ ውስጥ የገባ እንዳልሆነ በየጊዜው የሚነግረን ቢሆንም ብዙ የአደጋ ቀጠናዎች እንዳሉ ግን እየተገነዘብን ከላይ ወደ አነሳነው  ወደ  አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ መመረጥ ፖለቲካ አንድምታ ላይ እንመለስ፡፡
ከአቶ ኃይለ ማርያም ምርጫ ዙሪያ ሁለት ጥያቄዎች ማንሳት እንችላለን፡፡ አንደኛ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የኢህአዴግ መሪዎች ‘የስልጣናችን ምንጭ (legitimacy) የሚፈልቀው  በትጥቅ ትግሉ ውስጥ በከፈልነው መስዋዕትነትን’  ሲሉ ቆይተው በዚህ ጎዳና ያላለፈ ሰው መምረጣቸው ፤ ሁለተኛ  ደግሞ ሌሎች አንጋፋ ፓርቲዎች እያሉ ኢህአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኃላ የተመሰረተ ፓርቲ አባል መሆናቸው ስለሳቸው ሳይሆን በግንባሩ የፖለቲካ ህይወት  ወሳኝ  ሚናን ስለሚጫወቱት አካሎች የሚነግረን ነገር አለ፡፡
ይህንን ለመረዳት ከሁለት ዓመት በፊት ከኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር መካከል አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ እንዴት የምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴርነትን ሹመት እንዳገኙ ማስታወስ ይገባናል፡፡ በዚህ ወቅት ፓርቲው  በመተካካት ጥያቄ እና በጠቅላይ ሚኒስቴሩ ጤና መቃወስ ምክንያት ተወጥሮ ነበር፡፡በዚህም ጊዜ በጣም የሚያስገርመውና የሚያስደምመው የህወሓት ልሂቃን ሁለት አማራጭ ይዘው ቀረቡ፡፡አንደኛ በአገሪቱ ላይ ዴሞክራሲ እንዳይቀጭጭ ከተፈለገ እና እኛ የምንወክለው የሕዝብ ቁጥር አነስተኛ ስለሆነ የጠቅላይ ሚኒስቴሩን ቦታ  ከብአዴን እና ኦህዴድ ብንመርጥ የግንባራችንን የሀይል ሚዛን ሲለሚያዛባው  በኛ በኩል ተቀባይነት የለውም የሚል ዐሳብ አቀረቡ፡፡ሁለተኛ የጠቅላይ ሚኒስቴሩን ጽ/ቤት ለሶስት ወይንም ለሁለት በመክፈል የስልጣን ክምችቱን( premiership ) ብናሰራጨው የተሻለ ይሆናል አሉ፡፡በመሆኑም የመጀመሪያው ዐሳብ በግንባሩ ተቀባይነት በማግኘቱ ከሁለቱ ብዙኃን ፖርቲ ውጪ የሆነ ሰው በምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴርነት ለመምረጥ በቅተዋል፡፡  ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ ሀገሪቱን ለሌሎች ስጋቶች ስለሚያጋልጣት ተቀባይነት አላገኘም፡፡
አሁን ለጊዜው የሀገሪቱ የፖለቲካ አቅጣጫ ወይም የሽግግር ሁኔታ ካፒታል ‘ፒ’ ወይንም ስሞል ‘ፒ’ ይሆናል ለማለት አስቸጋሪ ቢሆንም በዚህ ጉዳይ ላይ ተጽእኖ የሚፈጥሩ አራት ዐበይት  ወቅታዊ ጉዳዮች አሉ፡፡
 1. የአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የፖለቲካ ደረጃ አጠያያቂነት በራሳቸው አመራር እንዳይሄዱ ሰርዓቱ የማይፈቅድላቸው በመሆኑ
 2. የኦሮሚያ ክልል ፕሬዘዳንት አቶ አለማየሁ አቶምሳ ቦታ በህመም ምክንያት ክፍተት በመፍጠሩ እና ከዚህም ጋር ተያይዞ የሚነሳው ውዝግብ
 3. በኢትዮጵያ ሙስሊሞች እና በመንግስት መካከል የተነሳው ውዝግብ እልባት አለማግኘት
 4. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ህልፈት ተከትሎ ቀጣዩን ፓትርያርክ የመምረጥ ሂደት 
መደምደሚያ
እንደሚታወቀው ኢህአዴግን የሚያዋቅሩት የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉም እኩል  ናቸው ቢባልም በኦርዌሊያን (George Orwell) አነጋገር “ሁሉም ፓርቲዎች እኩል ናቸው አንዳንድ ፓርቲዎች ግን የበለጠ እኩል ናቸው” እንዳለው ልክ ከጠቅላይ ሚኒሰቴር ጽ/ቤት ባለነሰ የህወሓት ሊቀመንበር ቦታ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ህይወት ላይ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው አጠያያቂ አይደለም፡፡ ይሄ ፓርቲ የበላይነት እና የገዢ ስፍራውን ለረጅም ጊዜ ማስቀጠል ይፈልጋል፡፡ ይሄንን ለመተግበር አሁን ለማደረግ እንደተፈለገው  ከሌላ (ማለትም ብዙኃን ቁጥር ከሌለው)ፓርቲ በመሾም አሊያም ከራሱ ፓርቲ ሰው መልምሎ በማቅረብ በምንም መልኩ የስልጣን ባለቤትነቱን ለማረጋገጥ ይፈልጋል፡፡

የሳምቱ ጋዜጣና መጽሔቶች ከሰኞ እስከ ሰኞ – አሥራሁለት

(ከነሐሴ 14 እስክ ነሐሴ 21/2004)
ሳምንቱ በጠ/ሚኒስተር መለስ ዜናዊ ህልፈተ ህይወት ዜና የተሞላ ነበር፡፡ የሞታቸው ዜና በቲቪ ከተረጋገጠበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ምላሾች የተስተናገዱ ሲሆን ጋዜጦች እና ህትመቶችም የዚሁ  አካላት ነበሩ፡፡ የፓትሪያርኩና የጠ/ሚኒስትሩ ህልፈት ዜናዎች እና የሃዘን መግለጫዎች የጋዜጣዎችን ገጾች ያጨናነቁ ነበሩ፡፡
አዲስ ዘመን ጠ/ሚኒስትሩን ሲያስታውስ

በህትመቱ የፓትሪያርኩን ዜና እረፍት ሲያነሳ የነበረው አዲስ ዘመን የጠ/ሚኒስትሩን ሞት በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለም “ኢትዮጵያ ታላቁን መሪ በሞት ተነጠቀች ከትላንትና ጀምሮም ብሔራዊ ሃዘን ታውጇል” ብሏል፡፡ በፊት ገጹ ሙሉውን የጠ/ሚኒስትሩን ምስል የያዘው አዲስ ዘመን በተከታታይ ሳምንታዊ እትሞቹ ሙሉውን (ገጽ 3ትን ጨምሮ) ለመለስ ማስታወሻነት እንዲውል አድርጓል፡፡

የኢትዮጵያ ኮፊ ኤክስፕረስ አሰሴሸን፣ ሙገር ሲሚንቶ ኢንተርፕራይዝ እና ልማት ባንክ ሃዘናቸውን ለመግለጽ ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡ አዲስ ዘመን ሳምንቱን ሙሉ የተለያዩ አካላት የሃዘን መግለጫ ሲያስተናግድ ከርሞአል፡፡ “የህዳሴው መሪ” “ለትውልዱ ልማትን እንጂ ልመናን አናወርስም” የሚሉ የተለያዩ ጽኁፎችን በፎቶ አጅቦ ያስተናገደው አዲስ ዘመን ምርጥ የጠ/ሚኒስትሩ ንግግሮችን አቅርቦአል፡፡የተወሰኑትን እነሆ፡-
 • የግሌም ሆነ የድርጅቴ አቋም ህገ በመንግስቱ ሊሻሻል የሚችል ምንም አንቀጽ የለውም የሚል ነው፡፡ መለስተኛ ጉዳዮች ላይ ማሻሻያ ይደረግ ቢባል ግን የሚያበሳጭ አይደለም፡፡
 • የመበታተን እና የመበጣጠስ አደጋ ጠፍቶ አሁን የፊዴራሊዝም ስርአት ሰፍኖ የብሄር የብሄር ብሄረሰቦች ህዝቦች መብትና እኩልነት መረጋገጡን ሳይ ደስታ ይሰማኛል፡፡በሃገራችን እየታየ ያለው የልማት እንቅስቃሴ እኛ ብቻ ሳይሆን በውጪ የሚገኙት መንግስታት ለስራም ሆነ ለስብሰባ ሲመጡ ከአመት አመት እየታየ ያለውን ለውጥ በማየት ይገርማቸዋል፡፡
 • ኢትዮጲያ ፌደራሊዝም ስርአቱን የጀመረችው ከቅርብ አመታት ወዲህ በመሆኑ የፊደራል ስርአትን አስቀድመው ከጀመሩ የምትማረው ብዙ ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን ኢትዮጲያ በስርአቱ ዙሪያ ለተቀሩት ሃገራት የሚተርፍ መልካም ተሞክሮ ያላት ሃገር ሆናለች፡፡
አዲስ ዘመን ከጠ/ሚኒስትሩ ሞት አንድ ቀን ቀደም ብሎ ባለው እትሙ በገጽ ሶስት እትሙ ማህበራዊ ድህረ ገጽ መረጃዎች ተአማኒነት እና አጠቃቀማቸው በሚል ርእስ የማህበራዊ ድህረ ገጾች መረጃዎች ለአመኔታ እንደማይበቁ የሚዳስስ ጽሁፍም አቅርቦ ነበር፡፡

ፍኖተ ነፃነት በልዩ እትም

አርብ እለት በልዩ እትም የወጣችው ፍኖተ ነጻነት በአብዛኛው ከጠ/ሚኒስተሩ ጋር የተያያዙ ዜናዎችን ይዛ ገበያ ላይ ውላለች፡፡የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን መታሰር በፊት ገጽ ላይ የተዘገበ ሲሆን የአንድነት ፓርቲ የሃዘን መግለጫም ተሳካቷል፡፡ የመለስ ዜናዊ ሁለቱ ገጾች በሚል ሰፊ ፍኖተ ነፃነት አራት የተለያዩ ሰፋፊ ጽሑፎችን አስነብባለች፡፡የሚከተሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
 • መለስ ዜናዊ እና ሕገ መንግስቱ
 • አወዛጋቢው የመለስ ‹‹ጀግንነት››
 • የመለስ ዜናዊ ቅይጥ ትዝታዎች (ከዞን ዘጠኝ ተከታታይ ብሎጎች ለጋዜጣ እንዲመች ሆኖ የተዘጋጀ)
 • ከጠ/ሚኒስተር መለስ ሞት ጋር በተያያዘ የአንድነት አባላት እየታሰሩ ነው
ሪፓርተር በረቡዕ እና በእሁድ እትሞቹ
ሙሉ እረቡ እትሙን በአቶ መለስ ሞት ዙሪያ ያደረገው ሪፓርተር በፊት ገጹ የጠ/ሚኒስትሩ ፎቶ ይዞ የወጣ ሲሆን በቁጥራቸው በዛ ያሉ የሙሉ ገጽ የሃዘን መግለጫዎችን ሪፓርተር አስተናግዷል፡፡ በእሁድ እትሙ ደግሞ ሳያርፍ ያለፈው መለስ በሚለው ሰፋ ያለ ፅሁፍ ሪፖርተር ያልተሰሙ የመለስ ታሪኮች በሚል ርእስ ስር የሚከተለውን አስነብቧል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በሽግግሩ ዘመን በሰጡት አንድ መግለጫ ላይ ባንዲራ ጨርቅ መሆኑን መግለጻቸው ይታወቃል፡፡ በዚህ ንግግራቸውም በርካቶች መለስ የአገር ፍቅር እንደሌላቸውና ባንዲራውን እንዳዋደቁት ቆጥረዋቸው ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ስለዚህ ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ተጠይቀው፣ ይቀርፃቸው የነበረውን ካሜራ አስጠፍተው የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ባንዲራ ጨርቅ ነው፤ ይህ በሁሉም ሰው የሚታወቅ ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን ባንዲራ ጨርቅ ሆኖ ሳለ መለስ ሲለው ጨርቅ አለመሆኑን ተረድቻለሁ፤ብለዋል፡፡  
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ብዙ ጊዜ ሲስቁ ስለማይታዩ፣ ለምን? እንደማይስቁ ተጠይቀውለምን እስቃለሁበማለት ጥያቄውን በጥያቄ መልሰዋል፡፡እኔ ቢሮ ውስጥ ሆኜ በየቀኑ የማነባቸው ደብዳቤዎች በሰቆቃ የተሞሉ ናቸው፡፡ እንደዚህ ዓይነት በደል ደርሶብኛል፣ ፍትሕ አጣሁ፣ ያሰርካቸውን ሰዎች ፍታ፣ የሚሉ በርካታ ይህን መሰል ደብዳቤዎች ይደርሱኛል፡፡ አብዛኞቹም ሁሉን ነገር የማደርገው እኔ እንደሆንኩ የሚገልጹ ደብዳቤዎች ናቸው፡፡ በአገሪቷና በአካባቢው ያሉትን በርካታ ችግሮች ለመፍታት በየጊዜው እታገላለሁ፡፡ ታዲያ ምን የሚያስቅ ነገር ኖሮ ነው የምስቀው፤ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ
ሚኒስትር መለስ በሕይወታቸው አሳዛኝ ስለሚሏቸው ገጠመኝ ተጠይቀው ሦስት ነገሮች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡የመጀመሪያው የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የቀረበለትን የሰላም ሐሳብ አልቀበልም፣ አሻፈረኝ በማለቱ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት የተሰው ዜጐች ሁሌም ያሳዝኑኛል፡፡ ሁለተኛው በምርጫ 97 ጊዜ በተፈጠረው ግርግር ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎች ናቸው፡፡ በወቅቱ እኔ እንደ ግለሰብ ብሞት እንኳን ምንም አይሰማኝም፡፡ ሆኖም እኔ የአገር መሪ እንደመሆኔ መጠን በሰላም ሳይሆን በእንደዚያ ዓይነት ግርግር ሥልጣን ብለቅ አገሪቱ ወደማትወጣው አዘቅት ውስጥ ልትገባ ትችል ነበር፡፡ በመሆኑም ውሳኔ ቢያሳዝነኝም ማንም በእኔ ቦታ ቢሆን የሚያደርገው ነገር ነበር፡፡ ሦስተኛ የሚያሳዝነኝ ጉዳይ የሕክምና ትምህርቴን ስከታተል አውቀው የነበረው አንድ ሻይ ቤት ከሰላሳ ዓመት በኋላ ተመልክቼው ምንም ዓይነት ለውጥ ባለማየቴ በጣም አዝኛለሁ፡፡ አገሪቱን ለመለወጥ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን ተረድቼ የበለጠ ለመሥራት ወስኛለሁ፤ብለዋል፡፡

ሳምንታዊው አዲስ ጉዳይ መጽሔት ቋሚ አምዶቹን በሙሉ በማጠፍ ሙሉውን መጽሄቱን አቶ መለስን የተመለከቱ የተለያዩ ጽሁፎችን አስተናግዷል፡፡ በጥቁር የሽፋን ገጽ አቶ መለስን ፎቶ ይዞ የወጣው አዲስ ጉዳይ በመጨረሻ ገጹ ብቻ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ማናቸው የሚል አንድ ገጽ ጽሑፍ ከማስነበቡ ውጪ ሙሉውን አቶ መለስን በሚዘክሩ ጽሁፎች ነበር እሁድ እለት ገበያ ላይ የዋለው፡፡

ሀተታ ወ መለስ – የአቶ መለስን ታሪክ የዳሰሳ ጽሑፍ
ስለመለስ ከአራቱም ማእዘናት – የአቶ መለስ ሞት እና የአለም አቀፍ ሚዲያዎች ዳሰሳ ጽሁፍ ሲሆን አብዛኛውን ጠንካራ ጎናቸውን ያወሱ ሚዲያዎችን ሪፓርት አካተዋል፡፡
የመለስን ጉዳይ መደበቅ ደግ ነበር ፓርቲውስ ከዚህ በኋላ አመኔታ ያጣበታል – የአቶ መለስን ህመም በተመለከተ ፓርቲው ያሳየውን ድብቅ ባህሪያ በዚህ ጽሑፍ በስሱ ተተችቶአል፡፡ በተጨማሪም፡-
·         የጥምረት መንግስት ቢቋቋም የተሻለ ነው – አቶ ቡልቻ ደመቅሳ
·         አቶ መለስን የማገኛቸው ፓርላማ ውስጥ ነበር – ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ (የአንድነት ለፍትህ እና ለዴሞክራሲ ሊቀመንበር)
·         መልካም አስተዳደር ሊኖር የሚችልባቸው መንዶች ቢመቻቹ ጥሩ ነው – የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ (የመድረክ ፓርቲ የፓርላማ ተወካይ)
·         አትሌቱን በመሸኘት እና በመቀበል ከፍተኛ የማበረታታት ስራ ሰርተዋል – አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ
 

አዲስ አድማስ በፊት ገጹን ሩብ የሚሸፍን የጠ/ሚኒስተሩን ፎቶግራፍ ይዞ ለንባብ የበቃ ሲሆን ለፓትያርኩ ቀብር ከሌሎች የህትመት ውጤቶች በተሻለ ሽፋን ሰጥቷል፡፡

ከሞቱ ዜና ጋር በተያያ

ማሕሌት ፋንታሁን

የዚህ ጽሑፍ ዋና ቅጂ በኢትዮጵያ እንዳይነበብ በታገደው የዞን ዘጠኝ ጦማር ላይ ይገኛል፡፡
የመለስን ሞት ተከትሎ ብዙ እየተባሉ ያሉ ነገሮች አሉ፡፡ ሬድዮና ቴሌቭዥኑ ሙሉ ሰዓቱን ጠ/ሩ በህይወት ዘመናቸው ያከናወኗቸውን ተግባራት እና ያደረጉትን ንግግር  ሃዘን ውስጥ የመክተት ብቃት ካላቸው ክላሲካል ሙዚቃ እና ዋሽንት ጋር በማቀነባበር በማሰማት ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የጠ/ሩን ሞት በተመለከተ በተለያዩ በአገራችን ክልሎች የሚገኙ ነዋሪዎችና ታዋቂ ሰዎች የተሰማቸውን  መሪር ሃዘን እና በምን አይነት ሁኔታ እያዘኑ እንዳሉ እየተከታተሉ ዘገባዎችን ያቀርባሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ስርአተ ቀብሩ እስኪፈፀም ድረስ እንደሚቆይ ቢነገርም ከዛ በኋላም ምናልባት እንዳሁኑ ሙሉ የፕሮግራማቸውን ሰዓት ባይሆንም እስከተወሰነ ጊዜ በተመሳሳይ ሁኔታ ሊቀጥል እንደሚችል ጥርጣሬ አለኝ፡፡ ጋዜጣና መፅሄቶችም ስለመለስ በሚያወሩ ፅሁፎች እንዲሁም ከተለያዩ ግለሰቦች እና ድርጅቶች የተላኩ የሃዘን መግለጫዎችን ከታዋቂ ሰዎች የተሰጠ አስተያየት ጋር ይዘው ወጥተዋል፡፡

ፌስቡክ መንደር ደግሞ ጠ/ሩ የመሞታቸው ዜና በአገር ውስጥ ሚዲያ እስከተነገረበት ሰዓት ድረስ አትሌቶቻችን በለንደን ኦሎምፒክ በተሳተፉበት ወቅት ስለተገኙት ውጤቶች ከተወራባቸው ውስን ቀናት ውጪ ለተከታታይ ስልሳ ቀናት ወሬው ሁሉ በአብዛኛው የመለስ የጤና ሁኔታ ነበር ብል ማጋነን አይሆንብኝም፡፡ የተለያዩ ምንጮችን በመጥቀስ መሞቱን ሲዘግቡ የነበሩ ከኢትዮጵያ ውጪ ያሉ ኢትዮጵያዊ ሚዲያዎች ነበሩ፡፡በጠና መታመሙን እና ከዚህ በኋላ ብዙ ጊዜ እንደማይቆይ የሚያትቱ ወሬዎችን ያስነበቡን የውጪ ደህረ ገፆችም የነበሩ ሲሆን በአንፃሩ ደግሞ በአገር ውስጥ የሚገኙ ጋዜጦች በጣም እስክንገረም ድረስ እርስ በርሱ የሚጣረስ መረጃ ሲያቀርቡ ነበር፡፡ ከኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስቴር የሚሰጡ መግለጫዎችም እንዲሁ ግልፅነት የጎደላቸው እና ሙሉ ምላሽ የሚሰጡን አይነት አልነበሩም፡፡ በስተመጨረሻም አቶ በረከት የመለስ ጤንነት በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ እና ለአዲስ አመት መጥተው እንኳን አደረሳችሁ እንደሚሉን ነግረውን ነበር የቆምነው፡፡

ሞቱ በአገራችን ሚዲያ እስከተነገረበትም እለት ድረስ በፌስቡክ እና በተለያዩ የሶሻል ሚዲያዎች ያሉ ተሳታፊዎች ‹አልሞተም›፣ ‹ሞቷል› እና ‹በጠና ታሟል› ብለው ማሳመኛ የሚሉትን ሃሳቦች እያነሱ በንቃት ሲወያዩ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ከዚህም አልፈው ድህረ መለስ ትንታኔ ሲሰጡ እና የተለያዩ ግምቶቻቸውን ሲያካፍሉም ነበር፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የመለስ ሞት በአገራችን ሚዲያ አብዛኛው ሰው ባልጠበቀበት ሰዓት ሲገለፅ ውይይቱ በመለስ ሞት ማዘንን እና አለማዘንን በመግለፅ ተቀየረ፡፡ ያዘኑት ያላዘኑትን ባለማዘናቸው፤ ያላዘኑቱ ደግሞ ያዘኑትን በማዘናቸው መውቀስና መተቸት ተጀመረ፡፡እስካሁንም ድረስ ይህ መወቃቀስ አላቆመም፡፡ በበኩሌ ‹ማዘን› ወይም ‹አለማዘን› ከውስጥ የሚመነጭ ስሜት እስከሆነ ድረስ ባለመስማማት መለያየት ሲቻል ‹ማዘን ነበረብህ› ወይም ‹ማዘን አልነበረብህም› ብሎ መፍረድ እና ያልተገቡ ቃላትን መወራወር ትክክል አይመስለኝም፡፡ ደግሞም ማዘንም ያለማዘንም የግለሰብ መብት እና ምርጫ ናቸው እንጂ ግዴታ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በፌስቡክ በምናያቸው ውይይቶች ላይ የሚስተዋሉት ወቀሳዎችና ትችቶች ግፋ ቢል ስድብ ቢታከልባቸው ነው፡፡ በርግጥ እኛ ሳናቅ በስውር የተፈፀሙ ወይም የሚፈፀሙ ከስድብ የዘለሉ ነገሮች ተከስተውም ሊሆን ይችላል፡፡ በማረሚያ ቤቶችና በአንዳንድ ቦታዎች ግን ነገሩ አለአግባብ ተካብዶና ትኩረት ተሰጥቶት እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆናቸውን የሚያመላክቱ ነገሮች እየሰማን ነው፡፡

ሰሞኑን ርዕዮትን ለመጠየቅ ማረሚያ ቤት በሄድኩበት ሰዓት የሰማሁት ነገር የሚያስደነግጥ ነው፡፡ የመለስ ሞት ከተነገረ በኋላ ያልተለመዱ ማስፈራሪያዎችና ዛቻዎች እየሰማች እንደሆነ በማዘን ነግራኛለች፡፡ ሌሎቹ እስረኞች ‹እነዚህን ልጆች ከመግደላችን በፊት ውሰዱልን› ብለውናል ተብለው እሷና እማዋይሽ የተባለች ሌላ ፍርደኛ ከነበሩበት ክፍል እንዲወጡ ተደርገው ሁለቱም ወደተለያየ ክፍል እንደተላኩና ከማያቋቸው በቀጠሮ ላይ ያሉ እስረኞች ከሚገኙበት ክፍል እንዲዛወሩም ተደርገዋል፡፡ ከተነገራቸው ማስፈራሪያ እና ወደ አዲሱ ክፍል ተለያይተው በመወሰዳቸው ምክንያት እንቅስቃሴያቸው ሁሉ በከፍተኛ ስጋት የተሞላ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ለወትሮው ፈገግታ በተሞላበት ፊት እና ብሩህ ተስፋዋን በሚያመላክት የራስ መተማመን መንፈስ ጠያቂዎቿን የማዋራት እና የማጫወት ልምድ የነበራት ርዕዮት ሰሞኑን ከደረሰባት ዛቻ እና ማስፈራሪያ በመነሳት ያደረባትን ስጋት ስትናገር እንባዋን መቆጣጠር አልተቻላትም፡፡ ከመለስ ሞት ዜና መነገር ጋር በተያያዘ ሆነም ሌላ ያፈፀመችው ጥፋት እንደሌለና ምናልባትም ግን የመለስ ፎቶ ያለበትን ካኔቴራ በ120 ብር ግዙ ሲባል መግዛት እንደማትፈልግ መናገሯ እንዲሁም ይህን መንግስት በመተቸት የምትታወቅ በመሆኗ ምክንያት   ይህ ሁኔታ እንደተከሰተባት የምትጠረጥር ሲሆን ‹‹ይህን የምነግራችሁ የሞትና የሽረት ጉዳይ ስለሆነ እንድታውቁት ነው እንጂ ከዚህ በፊትም ምንም አልነበረም ማለት አይደለም›› ብላለች፡፡ 

በተያያዘ ዜናም ባለፈው አርብ ፍኖተ ጋዜጣ በልዩ እትሙ በቅሊንጦ ማረሚያ ቤት የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ ፕሬዝዳንት ዘሪሁን ገ/እግዚአብሔር ‹መለስ ሞተ ተብሎ ሲነገር ሌሎቹ ሲያለቅሱ አንተ ስቀሃል› ተብሎ በእሰረኞች ከፍተኛ ድብደባ እንደደረሰበት እና ባለቤቱ ከፖሊሶች ‹ካልመከርሽው እስረኞች ሊገሉት ይችላሉ› የሚል ማስጠንቀቂያ እንደደረሳቸው  እንዲሁም ከጠ/ሚር መለስ ሞት ጋር በተያያዘ የአንድነት አባላት እየታሰሩ መሆኑን አስነብቦናል፡፡ ወዴት እየተኬደ ነው ትላላችሁ? እነዚህ ሰዎች መለስ ይማረን ሊያስብሉን ይሆን ይሆን?
ማሕሌት ፋንታሁን

የዚህ ጽሑፍ ዋና ቅጂ በኢትዮጵያ እንዳይነበብ በታገደው የዞን ዘጠኝ ጦማር ላይ ይገኛል፡፡

የመለስን ሞት ተከትሎ ብዙ እየተባሉ ያሉ ነገሮች አሉ፡፡ ሬድዮና ቴሌቭዥኑ ሙሉ ሰዓቱን ጠ/ሩ በህይወት ዘመናቸው ያከናወኗቸውን ተግባራት እና ያደረጉትን ንግግር  ሃዘን ውስጥ የመክተት ብቃት ካላቸው ክላሲካል ሙዚቃ እና ዋሽንት ጋር በማቀነባበር በማሰማት ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የጠ/ሩን ሞት በተመለከተ በተለያዩ በአገራችን ክልሎች የሚገኙ ነዋሪዎችና ታዋቂ ሰዎች የተሰማቸውን  መሪር ሃዘን እና በምን አይነት ሁኔታ እያዘኑ እንዳሉ እየተከታተሉ ዘገባዎችን ያቀርባሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ስርአተ ቀብሩ እስኪፈፀም ድረስ እንደሚቆይ ቢነገርም ከዛ በኋላም ምናልባት እንዳሁኑ ሙሉ የፕሮግራማቸውን ሰዓት ባይሆንም እስከተወሰነ ጊዜ በተመሳሳይ ሁኔታ ሊቀጥል እንደሚችል ጥርጣሬ አለኝ፡፡ ጋዜጣና መፅሄቶችም ስለመለስ በሚያወሩ ፅሁፎች እንዲሁም ከተለያዩ ግለሰቦች እና ድርጅቶች የተላኩ የሃዘን መግለጫዎችን ከታዋቂ ሰዎች የተሰጠ አስተያየት ጋር ይዘው ወጥተዋል፡፡

ፌስቡክ መንደር ደግሞ ጠ/ሩ የመሞታቸው ዜና በአገር ውስጥ ሚዲያ እስከተነገረበት ሰዓት ድረስ አትሌቶቻችን በለንደን ኦሎምፒክ በተሳተፉበት ወቅት ስለተገኙት ውጤቶች ከተወራባቸው ውስን ቀናት ውጪ ለተከታታይ ስልሳ ቀናት ወሬው ሁሉ በአብዛኛው የመለስ የጤና ሁኔታ ነበር ብል ማጋነን አይሆንብኝም፡፡ የተለያዩ ምንጮችን በመጥቀስ መሞቱን ሲዘግቡ የነበሩ ከኢትዮጵያ ውጪ ያሉ ኢትዮጵያዊ ሚዲያዎች ነበሩ፡፡በጠና መታመሙን እና ከዚህ በኋላ ብዙ ጊዜ እንደማይቆይ የሚያትቱ ወሬዎችን ያስነበቡን የውጪ ደህረ ገፆችም የነበሩ ሲሆን በአንፃሩ ደግሞ በአገር ውስጥ የሚገኙ ጋዜጦች በጣም እስክንገረም ድረስ እርስ በርሱ የሚጣረስ መረጃ ሲያቀርቡ ነበር፡፡ ከኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስቴር የሚሰጡ መግለጫዎችም እንዲሁ ግልፅነት የጎደላቸው እና ሙሉ ምላሽ የሚሰጡን አይነት አልነበሩም፡፡ በስተመጨረሻም አቶ በረከት የመለስ ጤንነት በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ እና ለአዲስ አመት መጥተው እንኳን አደረሳችሁ እንደሚሉን ነግረውን ነበር የቆምነው፡፡

ሞቱ በአገራችን ሚዲያ እስከተነገረበትም እለት ድረስ በፌስቡክ እና በተለያዩ የሶሻል ሚዲያዎች ያሉ ተሳታፊዎች ‹አልሞተም›፣ ‹ሞቷል› እና ‹በጠና ታሟል› ብለው ማሳመኛ የሚሉትን ሃሳቦች እያነሱ በንቃት ሲወያዩ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ከዚህም አልፈው ድህረ መለስ ትንታኔ ሲሰጡ እና የተለያዩ ግምቶቻቸውን ሲያካፍሉም ነበር፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የመለስ ሞት በአገራችን ሚዲያ አብዛኛው ሰው ባልጠበቀበት ሰዓት ሲገለፅ ውይይቱ በመለስ ሞት ማዘንን እና አለማዘንን በመግለፅ ተቀየረ፡፡ ያዘኑት ያላዘኑትን ባለማዘናቸው፤ ያላዘኑቱ ደግሞ ያዘኑትን በማዘናቸው መውቀስና መተቸት ተጀመረ፡፡እስካሁንም ድረስ ይህ መወቃቀስ አላቆመም፡፡ በበኩሌ ‹ማዘን› ወይም ‹አለማዘን› ከውስጥ የሚመነጭ ስሜት እስከሆነ ድረስ ባለመስማማት መለያየት ሲቻል ‹ማዘን ነበረብህ› ወይም ‹ማዘን አልነበረብህም› ብሎ መፍረድ እና ያልተገቡ ቃላትን መወራወር ትክክል አይመስለኝም፡፡ ደግሞም ማዘንም ያለማዘንም የግለሰብ መብት እና ምርጫ ናቸው እንጂ ግዴታ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በፌስቡክ በምናያቸው ውይይቶች ላይ የሚስተዋሉት ወቀሳዎችና ትችቶች ግፋ ቢል ስድብ ቢታከልባቸው ነው፡፡ በርግጥ እኛ ሳናቅ በስውር የተፈፀሙ ወይም የሚፈፀሙ ከስድብ የዘለሉ ነገሮች ተከስተውም ሊሆን ይችላል፡፡ በማረሚያ ቤቶችና በአንዳንድ ቦታዎች ግን ነገሩ አለአግባብ ተካብዶና ትኩረት ተሰጥቶት እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆናቸውን የሚያመላክቱ ነገሮች እየሰማን ነው፡፡

ሰሞኑን ርዕዮትን ለመጠየቅ ማረሚያ ቤት በሄድኩበት ሰዓት የሰማሁት ነገር የሚያስደነግጥ ነው፡፡ የመለስ ሞት ከተነገረ በኋላ ያልተለመዱ ማስፈራሪያዎችና ዛቻዎች እየሰማች እንደሆነ በማዘን ነግራኛለች፡፡ ሌሎቹ እስረኞች ‹እነዚህን ልጆች ከመግደላችን በፊት ውሰዱልን› ብለውናል ተብለው እሷና እማዋይሽ የተባለች ሌላ ፍርደኛ ከነበሩበት ክፍል እንዲወጡ ተደርገው ሁለቱም ወደተለያየ ክፍል እንደተላኩና ከማያቋቸው በቀጠሮ ላይ ያሉ እስረኞች ከሚገኙበት ክፍል እንዲዛወሩም ተደርገዋል፡፡ ከተነገራቸው ማስፈራሪያ እና ወደ አዲሱ ክፍል ተለያይተው በመወሰዳቸው ምክንያት እንቅስቃሴያቸው ሁሉ በከፍተኛ ስጋት የተሞላ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ለወትሮው ፈገግታ በተሞላበት ፊት እና ብሩህ ተስፋዋን በሚያመላክት የራስ መተማመን መንፈስ ጠያቂዎቿን የማዋራት እና የማጫወት ልምድ የነበራት ርዕዮት ሰሞኑን ከደረሰባት ዛቻ እና ማስፈራሪያ በመነሳት ያደረባትን ስጋት ስትናገር እንባዋን መቆጣጠር አልተቻላትም፡፡ ከመለስ ሞት ዜና መነገር ጋር በተያያዘ ሆነም ሌላ ያፈፀመችው ጥፋት እንደሌለና ምናልባትም ግን የመለስ ፎቶ ያለበትን ካኔቴራ በ120 ብር ግዙ ሲባል መግዛት እንደማትፈልግ መናገሯ እንዲሁም ይህን መንግስት በመተቸት የምትታወቅ በመሆኗ ምክንያት   ይህ ሁኔታ እንደተከሰተባት የምትጠረጥር ሲሆን ‹‹ይህን የምነግራችሁ የሞትና የሽረት ጉዳይ ስለሆነ እንድታውቁት ነው እንጂ ከዚህ በፊትም ምንም አልነበረም ማለት አይደለም›› ብላለች፡፡ 

በተያያዘ ዜናም ባለፈው አርብ ፍኖተ ጋዜጣ በልዩ እትሙ በቅሊንጦ ማረሚያ ቤት የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ ፕሬዝዳንት ዘሪሁን ገ/እግዚአብሔር ‹መለስ ሞተ ተብሎ ሲነገር ሌሎቹ ሲያለቅሱ አንተ ስቀሃል› ተብሎ በእሰረኞች ከፍተኛ ድብደባ እንደደረሰበት እና ባለቤቱ ከፖሊሶች ‹ካልመከርሽው እስረኞች ሊገሉት ይችላሉ› የሚል ማስጠንቀቂያ እንደደረሳቸው  እንዲሁም ከጠ/ሚር መለስ ሞት ጋር በተያያዘ የአንድነት አባላት እየታሰሩ መሆኑን አስነብቦናል፡፡ ወዴት እየተኬደ ነው ትላላችሁ? እነዚህ ሰዎች መለስ ይማረን ሊያስብሉን ይሆን ይሆን?

ዳኛቸውና ገዢ ሐሳቦቹ

እንዳልካቸው ኃ/ሚካኤል እና አቤል ዋበላ

ከዶ/ር ዳኛቸው ጽሁች መሀከል ጥቂቶቹ
የቄሳር እና አብዮት መጽሐፍ ዳሰሳ
አንዲት ኢትዮጵያ ሬድዮ
ግልጽ ደብዳቤ ለአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳ
ግልጽ ደብዳቤ ለአዲስ አበባ የኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት  አዲስ ጉዳይ መጽሔት
ሰብል እርሻ በጅብ ማረሻ  ፍትሕ ጋዜጣ
ዳኛቸው ስለ ብርቱካን   አዲስ ነገር ጋዜጣ

ብሔራታ ወልማታ- ሸገር ራዲዮ ጋር ያደረው ቃለ ምልልስ
የአገራችንን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ስፋት እና ጥልቀት ስናስተውል ብዙዎቻችንን በቀቢጸ ተስፋ እንባክናለን፡፡ ይህን ለማሻሻል የተጀመረ ተዋስኦ አለመኖሩ ደግሞ ሀዘናችንን እጅግ ያበረታዋል፡፡ በተማሩትና በሰለጠኑበት የሙያ ዘርፍ ዙሪያ እንኳን ትንፍሽ የማይሉ ነገር ግን ማዕረጋቸው ላጠራር የከበደ ሰዎች በየመስኩ ተደርድረዋል፡፡ብዙዎቹ ልሂቃን ትውልድን በሚገራና አቅጣጫ በሚያሳይ መልኩ አርአያ አለመሆናቸው አገሪቱ  በሐሳብ ክፍተት እንድትዳክር አድርጓታል፡፡ ዞን ዘጠኝም የነገዋ ኢትየጵያ መጻዒ ተስፋ የሚያሳስባቸው ወጣቶች ስብስብ እንደመሆኑ መጠን የራስንም የአቻንም መደናበርን ለመቀነስ ወይም ሐሰሳን ለመደገፍ ስናስብ አገሪቱ ካሏት ጥቂት የአደባባይ ምሁራን አንዱ የሆነው ዶ/ር ዳኛቸው አሠፋ ላይ አይናችን አረፈ፡፡ (በዚህ ጽሑፍ ላይ እኚህን የተከበሩ ምሁር ‹አንቱ› ሳንል የቀረነው፣ ለንባቡ ቅልጥፍና እንዲመች በማሰብ መሆኑን አንባቢዎች እንድታውቁልን፡፡)
ከዚህ በፊት ለአደባባይ የዋሉት ሥራዎቹ እጅግ ቢማርኩንም ወጥ የሆኑ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ይህንን የሐሳብ ኦና (idea vacuum) ለመሙላት ከሚታትር መምህር  የበለጠ ለመቅሰም በአንድ ወዳጃችን እርዳታ አገኘነው፡፡የዳኛቸው ሐሳቦች እጅግ የሚገዙ ለአብዛኛው ሰው ቅርብ የሆኑና በቀላሉ በሚገቡ ናቸው፡፡ ሀገራዊ ስነ ቃሎችና ስነጽሑፎችን በማጣቀስ፣ የሀገራችንን የቅርብና የሩቅ ታሪኮች ከፍልስፍና ንድፈ ሐሳብ ጋር በማጣመር  የመተንተን አቅም አለው፡፡ ይህንን ታላቅ ምሁር ከአዲስ አበባ የኒቨርሲቲ ውጭ ላለው የህብረተሰብ ክፍል በማስተዋወቅ አዲስ ነገር ጋዜጣ ጉልህ ሚና ተጫውታለች፡፡ በወቅቱ በእስር ቤት የነበረችውን የአእምሮ እስረኛ ዘሪ ብርቱካን ሚደቅሳን እስራት ኢፍትሕዊነት አስመልክቶ በጻፋቸው ተከታታይ ሑፎች ወደ አደባባይ ብቅ ያለው ዶ/ር ዳኛቸው በብዙ አካዳሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ዙርያ ገዢ ሐሳቦችን እያካፈለ ይገኛል፡፡እኛም ከነዚህ ብዙ ጉዳዮች ውስጥ የተወሰኑትን  በመምረጥ ትውልድ ሊያተኩርባቸው እና የምር ሊያነባቸው እና ሊያዳምጣቸው የሚገ መሆናውን ለመጠቆም እንዲህ አቅርበነዋል፡፡  
የአደባባይ ተዋስኦ /public discourse/
ዶ/ር ዳኛቸው የዲሞክራሲ ባህል እንዲዳብር ከተፈለገ ጫፍ አልባ ውይይት (endless conversation) ያስፈልጋል ይላል፡፡ በንግግር ተዋስኦ የሚመጣው ችግር በበለጠ ንግግር ማሸነፍ ይገባል ሲልም ይከራከራል፡፡ አንዳንዶች ያለገደብ ውይይትን መፍቀድ  ለብዙ የምግባር ችግሮች (ዘለፋ፣ ስድብ እና ልቅ ወሲብ ቀስቃሽ ምርቶች ለመሳሰሉት..) ይዳርጋል ይላሉ፡፡ እነዚህ ችግሮች መኖራቸው አይካድም፡፡ ይህ ግን እቀባ/ እግድ በመጣል  ሊፈታ አይችልም፡፡ ከነጻ ንግግር የሚመጣን ችግር ለመፍታት የበለጠ ነጻ ንግግር (more free speech) መፍቀድ ይገባል፡፡ ብሔርን ብሔርን ያጋጫል፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት ያላትማል የሚል ሰባራ ሰንጣራ ምክንያት በመት ነጻ ንግግርን/ማሰብን ለማለፍ ወይ ለማገድ መሞከር ተገቢ አይደለም ይላል፡፡ የውይይት ባህል መዳበር እንዳለበት ሲያሰረዳ ደግሞ አውሮጳውያን የዲሞክራሲ ባህል ጉዞን ሲጀምሩ በዘመነ አብርኆት (enlightenment) ወደ አንድ ክፍለ ዘመን ለሚጠጋ ጊዜ የነበውን ወግ እና ባህል ፈትሸዋል፡፡ ሰፋ ያለ የውይይት ዘመንን በማለፍ ከዲሞክራሲ ባህል ጋር ተለማምዋል ከዲሞክራሲ አሰራር ጋር የሚጣረሱ ግባራትን እና ጽንሰ ሳቦችን ሁሉ ለማጥራት ችለዋል ይለናል፡፡

ኢትዮጵያ እና የአደባባይ ተዋስኦ ባህላችን
አውሮጳውያን የአደባባይ ተዋስኦ ባህላው እጅግ የጠነከረ እንደሆነ የሚመሰክረው ዶር ዳኛቸው ለዚህም  በዘመነ አብርኆት የዲሞክራሲ ባህላቸውን እንዳያዳብሩ የሚያግዱ ጽንሰ ሳቦችን በይፋ በውይይት ማስወገድ በመቻቸው እንደሆነ ያስረዳል:: ከነዚህ ጽንሰ ሳቦች ውስጥ ተጠማኒያዊነት ይሰኛል፡፡
ኢትዮጵያ ባህል ተወሰነ መልኩ ማኒያነዊነት (Manichaeism) እንደተጫነው የሚጠረጥረው ዶ/ር ዳኛቸው  ለዚህ እንደማስረጃ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ገድላትን ይጠቅሳል፡፡ ማኒያነዊነት አስተምህሮ መነሻው  በሦስተኛ ክፍለ ዘመን በተነሳ እና ራሱን ከዞራስተር፣ ቡዳህና ክርስቶስ ቀጥሎ የመጣ የመጨረሻው ነብይ አድርጎ በሚቆጥረው በማኒ ነው፡፡ ማኒያዊነት የኖስቲክዝም (Gnosticism) ከፍተኛ ተጽእኖ ቢኖርበትም መሰረታዊ አስተምህሮው መላውን ጠፈር በክፉና ደግ አምላክ ትግል እንደተፈጠረች በመጥቀስ ነገሮችን ሁሉ ቅዱስና ርኩስ ብርሃንና ጨለማ በማለት ምነታዌ አድርጎ ይከፋፍላል፡፡ ይህ አስተሳሰብ በአገራችን መኖሩ የዴሞክራሲ ባህልን እንዳንገነባ እንቅፋት ሆኖብናል፡፡  
ግሪኮች  አንድ  ፓለቲካዊ ፍልሰፍናቸውን የገለጹበት ብሒል አላቸው፡፡ አንተ መንግስትን ማማት አትችልም ምክንያቱም አንተ ራስህ  የመንግስት ነጸብራቅ ነህና ግዛትና ባህሉ (state and culture) ተዋህዶ የሚኖር ነው፡፡ ብዙ ጊዜ አምባገነን መሪዎችን በማየት የኛ ናቸው ለማለት ስንቸገር ይታያል:: እንደ ዶ/ር ዳኛቸው ሐሳብ ግን እነዚህን አምባገነኖች የሰራቸው የኛው ማኅበረሰብ ባህል ነው፡፡ ለዚህ እንደማስረጃ መንግስቱ ኃ/ማርያም፣ መለስ ዜናዊና ኢሳያስ አፈወርቂን እንደምሳሌ ያቀርባል፡፡ በውጭ ትምህርት መልክ ለመደበቅ ቢሞከርም የኢትዮጵያዊ ባህል ማሳያ ናቸው፡፡ ምርጫ 97ን ተከትሎ በሀገራችን የተከሰተው ውዥንብር ማንሳት ይቻላል፡፡ Politics is the art of compromising (ፖለቲካ ማለት የማመቻመች ጥበብ ነው፡፡) በባሕላችን ያለው ማኒያዊነት ግን ይህን እንድንረዳ አልፈቀደልንም፡፡ መንግስት ፍጹማዊ ድል ለመጎናጸፍ  የቅንጅት መሪዎችን በመወንጀል ሰብስቦ አሰረ፡፡ ቅንጅት ደግሞ ህዝቡ ተሰልፎ የሰጠውን መብት ሙሉ በሙሉ አልተሰጠኝም በማለት አልቀበልም የምፈልገው ፍጹማዊ ድልን ነው አለ በማለት ዶ/ር ዳኛቸው ይተነትነዋል፡፡
የዘመን መንፈስ
እንደ ሔግሊያን አመለካከት በአንድ ሀገር መንግስትን የሚበይነው (assign) የሚያደርገው መንፈስ አለው፡፡ ኢትዮጵያዊው ፈላስፋ እጓለ ገብረ ዮሐንስ “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ” በተሰኘ መጽሐፋቸው መግቢያ ላይ አውሮጳ፣ በጀርመን ሀገር ሳሉ ላዩት ለዚያ ዘመን ወጣት መንፈስ መጽሐፋቸውን እንደመታሰቢያ ሲያቀርቡ  “በከፍተኛ መንፈስ ለተነሳው ወጣት እጅ መንሻ  እንዲሆነኝ…”  ማለታቸው  በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት ስለነበረው ለመማር፣ ለማወቅ፣ አገርን ለመለወጥ የሚያስብ መንፈስ እንደነበረ እንረዳለን፡፡ እያንዳንዱ ስርዓት የራሱ መንፈስ አለው፡፡ ከዚህ መንፈስ ውጭ ከዚያ ስርዐት መጠየቅ አስቸጋሪ ነው፡፡
እንደ ዶ/ር ዳኛቸው ትንተና የአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስተ ሦስት የዘመን መንፈሶች ነበሩበት፡፡ የመጀመሪያው ምንሊክ እንደወለላ ትተዋት የሄዷትን አትዮጵያ ማያያዝና አሐዳዊ ስርዓትን መዘርጋት ነበር፡፡ ሁለተኛው ደግም ከቅኝ ገዢዎችና ኢምፔሪያሊሰቶች ትንኮሳ ሉዓላዊት ኢትዮጵያ መጠበቅና  የተከበረ የውሃ በርን በበሰለ ዲፕሎማሲ አንድ ጥይት ሳይተኮስ ማሰገኘት ነበር፡፡ ሶስተኛው ደግሞ  ዘመናዊት ኢትዮጵያን መገንባት ሲሆን ይህም የሞሶሎኒን አማካሪዎች አስደንገጦ “ለተፈሪ አስር አመት ከሰጠኸው ኢትዮጵያን ዘመናዊ ያደርጋታል፤ ቶሎ ብለህ ኢትዮጵያን ውረር፤ ኋላ አልሰለጠነችም ብሎ ለመውጋት አስቸጋሪ ነው” የሚል መልእክት እንዲስተላለፉ አስገድዷቸዋል፡፡ የዘመናቸው መንፈስ ያዘዛቸው ይሄን ነው፡፡  ወታደራዊው መንግስት አገርን ለማያያዝ ካደረገው ጥረት ውጪ የረጋ የተጨበጠ መንፈስ አልነበረውም፡፡ ኢህአዴግም ለወጉ ዴሞክራሲ፣ ፌደራሊዝም፣ ሕገ መንግስት የመሳሰሉ ነገሮችን ቢያወራም መንፈስ ግን ያን አላሸከመውም፡፡ በዲሞክራሲ በኩል፣ በነጻነት በኩል፣ በመብት በኩል መመልከት ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ነው፡፡ አሁን እንደተረዳደሁት ይላል ዶ/ር ዳኛቸው  ዴሞክራሲዊነት እንዲያብ፣ ሕገ መንግስታዊነት እንዲመጣ፣ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ መንፈስ እንዲነሳ ኢህአዴግ መታለፍ (supplant) አለበት፡፡ አሁን ኢሕአዴግም ይህን የተረዳ ይመስላል በሚዲያው ስለልማት፣ ስለዕድገት መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ስለማሰለፍ ብቻ ነው የሚያወራው፡፡
ወንበር በሌለበት ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና!?
ሁለት ዓይነት ፍልስፍናዎች አሉ የመጀመሪያው በእንግሊዘኛው small p የሚጽፉት ፍልስፍና (philosophy) ሲሆን ሁሉም ሰው ይህ ፍልስፍና አለው፡፡ ገንዘብ አወጣጥ፣ ልብስ አስተጣጠብ፣ የምግብ አበሳሰል የመሳሰሉት…  ለነገሮች ያለው አዝማሚያ ማለት ነው፡፡ ‘ብዙ ገንዘብ ለሰው ማበደር አልወድም፤ ይህ ፍልስፍናዬ ነው’ ማለት ይቻላል፡፡ በcapital P የሚጽፉት (Philosophy) ግን የተወሰኑ መመራመሪያ መንገዶችን አበጅተው መሰረታዊ ጥያቄዎችን በማንሳት የሚደረግ እንቅስቃሴ  ነው፡፡ አርስቶትል በሜታፊዚክስ እንዲህ ብሏል “እኛ ብቻ ነን እውነት ላይ  ለመድረስ መፈላሰፍ አለብን ያልን ለሌላ ነገር አይደለም፤ ግብጾችን እዩ ስልጣኔ አላቸው ግና ከኋላ ሌላ ዓላማ አላቸው፣ ፐርሺያንም ተመልከቱ እኛ ብቻ ነን ፍልስፍናን ለፍልስፍና ስንል የተከተልን” ብሏል፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ፍልስፍና ስንመጣ ቤተ ክርስቲያን ለሁለት ሺህ ዓመታት የዘለቀ በሀይማኖታዊ አሻራ የቀለመ የትምህርት ዘይቤ አለ፡፡ ይህ የትምህርት ስርዓት በከፋፈላቸው ውስጥ ፍልስፍና የሚያስተምር የትምህርት ዘርፍ የለም፡፡ ከዋሸራ ጀምሮ ባሉ አድባራት እኔ መምህር እገሌ ፍልስፍና አስተምራለሁ ብሎ ወንበር የተከለ መምህር የለም፡፡ ወንበር ማለት የትምህርትና ስልጠና ተቋም (institution) ማለት ነው፡፡ በቅርቡ የተነሳ የሳይንስ ታሪክ ምሁር በመካከለኛው ዘመን የነበረ የእስልምና ሳይንስ የት ደረሰ ብሎ ይጠይቃል፡፡ በመስቀል ጦርነት ወቅት ምዕራባውያን እና ሙስሊሞች ሲዋጉ ምዕራባውያኑ በወታደሮች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ከርኩስ መንፈስ ጋር በማያያዝ በጠበል እና በጸሎት ለመፈወስ ሲተጉ የሙስሊም ሀኪሞች ግን በተቃራኒው በሰውየው ላይ ደረሰውን የጎራዴው ጋር እና ሌሎች ሁኔታዎች ጋር በማያያዝ ሳይንሳዊ ግምት ለመስጠት ጥረት  ያደርጉ ነበር፡፡ ከላይ ያነሳነው  የታሪክ ምሁር እንዲያ ተስፋ ሰጭ የነበረው የእስልምና ሳይንስ ወዴት ጠፋ ብሎ ይጠይቅና የምዕራብ ክርስትና በመካከለኛው ዘመን ለነበረው እውቀት፣ ፍልስፍናና ወንበርን ስትሰጠው እስልምና ግን ወንበር ባለመስጠቷ የያ ተስፋ ሰጭ (promising) ሳይንስ ሊጠፋ ችሏል፡፡ በኢትዮጵያም እንዲሁ ወንበር ስላልነበረ ፍልስፍና አለ ለማለት አይቻልም ባይ ነው – ዶ/ር ዳኛቸው፡፡
የዘርዓ ያዕቆብን እንደ ብልጭታ (Bleeps) ማንሳት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ይህን ከምዕራባውያን ተማረው ለማለት  አይችልም፡፡ በሌሎች የአፍሪካ ሀገር እንዳደረጉት እንዲሁ ጋልበውት (በባህል፣ በሀይማኖት) እንደሄዱት በኢትዮጵያ ተመሳሳይ ሁኔታ አልገጠማቸውም፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ሲደርሱ የራሳችን የሆነ  ቅዳሴ (Liturgy)፣ ትርጓሜ (hermeneutics) የንባብ ባህልና ስነ ጽሑፍ እንዳለ ሲያዩ እንደደነበሩ (shoked እንደሆኑ፣) ይህም ድንጋጤያቸው እስከ ቅርብ ጊዜ አብሯቸው እንደቆየ እንደሚገምተው ዳኛቸው ሐሳብ  በዘመኑ የነበረው ተጋላጭነት (exposure) ይህን በራሱ እንዲጠየቅ አድርጎታል፡፡ ለዚህ እንደ መነሻ የሚያገለግለው በዘርዓያዕቆብ ዘመን የመንበረ ጳውሎስ ትርጓሜን፣  የእስክንድርያንም፣ የኢትዮጵያውያን ሊቃውንትን ትርጓሜ አጠናው ማለቱን ይጠቅሳል፡፡ ይህንንም ቅዱስ  ላሊበላ  በኢየሩሳሌም የነበረውን ቆይታና  ልዑል ተፈሪ መኮንን በአውሮጳ በፓሪስ ከተማ ለሦስት ወራት ያደረጉት ጉብኝት  የፈጠረባቸውን ተጽእኖ በተወሰነ መልኩ ያስረዳል፡፡ ከዚህ ቀደም እንደ ዘርዓያዕቆብ  ያለ  ሰው ከኢትዮጵያ ሊወጣ አይችልም ብለው የጻፉ  ምሁራን አሉ፡፡ ፕሮፌሰር ሳምነርና መምህር አለማየሁ ሞገስ ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡ ሚዛን የደፋ ሐሳብ እንዳላቀረቡ የሚስማማው ዳኛቸው መኖሪያውን በካናዳ ያደረገው የፍስሐ ታደሠ ክርክር ሳቢ የሆነ አዲስ ሐሳብ ይዞ እንደመጣ ይቀበላል፡፡ እንደፍስሐ ሐሳብ የዘርዓ ያዕቆብ ያነሳቸው ንባብ፣ ሐሰሳ፣ ስለመጠየቅ፣ ስለአእምሮ ሲያነሳ የኢትዮጵያውያንን ሊቃውንት አይመጥነንም፡፡ ስንት ብዙ ውስብስብ (sophisticated ) ጽሑፎች እያሉ እንዲህ ሊባል አይገባም፡፡ የኢትዮጵያ ሊቃውንት ብዙ ጠይቀዋል ከዚህ በላይ ያውቃሉ ባይ ነው፡፡ እድሜ ከሰጠን ወደፊት ፍስሐ ታደሠ ያለበት ተዋስኦ እንደገና እንደሚኖር ዳኛቸው ፍንጭ ይሰጣል፡፡ እሰከዚያው ግን ዘርዓያዕቆብን እንደኢትዮጵያዊ ፈላስፋ ነው የምንወስደው፡፡
                                
ማኅበራዊ ጅማት ወይም ውል /social fabrics or contract/
የአገር አመሰራረትን አስመልክቶ ሁለት ዓይነት እሳቤዎች (schools) አሉ፡፡ የመጀመሪያው አገርን እንደ ተክል፣ እንደሚያድግ አበባ፣ ስር፣ ቅርንጫፍ ያለው ቀስ እያለ እየተከማቸ (sedimented) የሚያድግ  ሲሆን  ማኅበራዊ ጅማት (social fabrics)፣ ጥቅል የጋር ትውስታ  (collective memory)፣ ወግ (norm) የመሳሰሉት ገንዝብ ያደረገ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ አገር እንደጭቃ ተድቦልቡላ እንዲሁ በዘፈቀደ የተፈጠረ ነው ባይ ናቸው፡፡ ለዚህ ትልቋ ምሳሌ ዩኤስ አሜሪካ ናት፡፡ ብዙዎቹ የአፍሪካ አገሮችም በቅኝ ግዢዎች ነው እንዲህ ባለ ሁኔታ የተመሰረቱት፡፡ እንደዳኛቸው ሐሳብ ኢትዮጵያ በጠነከረ ማኅበራዊ ጅማት የተገነባች አገር ነች፡፡ ጉዳዩ በአካል ጨብጠህ የምትይዘው ዓይነት ነገር አይደለም ሜታፊዚካልም ይመስላል፡፡ ኢትዮጵያዊነት መንፈስ እጅግ ጠንካራ ነገር ይናገራል፤ ለዚህ እንደምሳሌ በቦስተን ዩንቨርሲቲ ሳለ የገጠመውን ያነሳል፡፡ በኒው ዮርክ ከተማ ለሦስት ቀናት መብራት ይጠፋል ከዚያ በሀገሪቱ ከፍተኛ የሆነ ዝርፊያና ወንጀል ይከሰታል፡፡ በዚያን ወቅት ከሶቪየት ተባሮ በአገረ አሜሪካ ያለ ሶልኒስተን የሚባል የኖቤል ሽልማት አሸናፊ ነበር፡፡ በዚያ ወቅት በሀርቫርድ የኒቨርስቲ ንግግር እንዲያደርግ የተጋበዘው ሶሊንስተን እንዲህ ሲል አሜሪካኖቹን ልካቸውን ነገራቸው፡፡ ሀገራችሁ ጨቅላ ናት፣ ሦስት ቀን መብራት ቢጠፋ እርስ በርስ አንገት ለአንገት  እነዴት ትያያዛላችሁ፤ ሀገሬ ራሺያ ግን ታላቅ ሀገር ናት፡፡ ነገ ዛሬ አምባገነኖች ቢይዟትም ስርዐቱ ነገ ይወድቃል፡፡  በጠንካራ ማኅበራዊ ጅማት የተገመደች ናት፡፡

አሁን ዛሬ ላይ ሆነን ዶ/ር ዳኛቸው ተነቦ የማያልቅ መጽሐፋችን ነው፡፡ ለብዙ ተዋስኦች ጤናማ ገዢ ሐሳቦች አሉት፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክንም አብጠርጠሮ ያውቀዋል፡፡ ፍልስፍና ለእርሱ ክህሎት ነው፡፡ ልክ እንደ ፈረንሳያዊው ፈላሰፋ ሰ በሀገረኛ የስነጽሑፍ ውጤቶች አጅቦ ታላላቅ የፍልስፍና ቲዎሪዎቹን ለብዙዎች በሚገባና በሚማርክ መልኩ ያቀርባል፡፡ እኛ ከባህሩ በጥቂቱ እንዲህ ተመልክተናል፡፡ የበረታ እንዲዋኝበትም ሲሻው ጠጥቶ እንዲሰክር ፈቅደናል፡፡ ፈረስ ያደርሳል እንጂ አይዋጋም፡፡

ጋዜጦች እና መጽሔቶቻችን ከሰኞ እስከ ሰኞ (አሥራአንድ)

(ከነሐሴ 7 እስከ ነሐሴ 14፤ 2004)
የኛ ፕሬስ ጋዜጣ ሲፒጄ የሙስሊሞች ጉዳይ መጽሄት አዘጋጅ የሱፍ ጌታቸው ይፈታ ማለቱን እና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እና መምህራን የዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች ድንጋይ ይጥረቡ መባሉ እንዳሳዘናቸው ዘግቧል፡፡
ፍኖተ ነፃነት በቃለ መጠይቅ አምዱ (/) ክቡር ገናን ይዞ ወጥቷል፡፡ ስለ ኢትዮጵያ ሲቪክ ማህበራት ተግዳሮቶች እና እንቅስቃሴዎች አወያይቶዋቸዋል፡፡ አቶ ክቡር ገናም ‹አንድ ህዝብ ዝም ብሎ ተኝቶ ሲረገጥ አይውልም፤ ድንገት ይነሳል› ማለታቸውን በፊት ገጹ አስፍሯል፡፡
በዚህ ሳምንት አቶ ክቡር ገና ከሰንደቅ ጋዜጣም ጋር ቆይታ ነበራቸው፡፡ በተመሳሳይ የሲቪል ማህበራት ጉዳዮች ዙሪያ ለሰንደቅ ቃለ መጠይቅ ሰጥተዋል፡፡
የጠ/ መለስ ነገር
ከፓትሪያርኩ ዜና እረፍት በፊት የወጡት ጋዜጦች  ሁሉም በፊት ገጻቸው የጠ/ሚኒስትሩን መጥፋት ሽፋን ሰጥተውታል፡፡
የኛ ፕሬስ በፊት ገጹ የጠ/ሚኒስተር መለስ ጉዳይ እያወዛገበ ነው ሲል የተለያዩ ተቋማት ጉዳዩን አስመልክቶ ያወጡትን ዘገባ አስነብቧል፡፡

መለስ ወደ ስልጣናቸው አይመለሱም ዘጋርዲያን
ከአዲስ አመት በፊት ስራቸውን ይጀምራሉ አቶ በረከት
የጠ/ሚሩ የግል ተተኪ አለመኖር አሳስቦናል የኬንያው /ሚኒስተር
ከታቦ ኢንቤኪ ጋር በጉዳዩ እተማከሩ ነው ፋይናንሺያል ታይምስ
ከአሁኑ ስልጣን ለመያዝ እርስበርስ እየተሻኮቱ ነው ሀይሉ ሻውል

ሰንደቅ በፊት ገጹ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አነጋጋሪነት ቀጥሏል ያለው ሰንደቅ ድንገት መሰወራቸው ግብጾችን አሳስቧል ሲል የአሜሪካንን ዝምታ አሳሳቢነት እና የእንግሊዝ ጋዜጦችን ተደጋጋሚ የዜና ሽፋን በጠ/ሚው የትካዜ ፎቶግራፍ አጅቦ አውጥቶአል፡፡
ፍኖተ ነፃነት በበኩሉ አቶ መለስ ከያራ የማዳበሪያ አምራች ፋውንዴሽን ያገኙት ሽልማት በሙስና የተገኘ ነው መባሉን በፊት ገጹ አስፍሯል፡፡ በተያያዘ ዜና የአቶ መለስ ጉዳይ አለየለትም በማለት የአቶ መለስን አለመኖር አስመልክቶ የተለያ አካላትን ሃሳብ ይዞ ወጥቷል፡፡
የፓትሪያርኩ ህልፈት
አዲስ ጉዳይ እና እንቁ መጽሄቶች በፊት ገጻቸው የፓትሪያርኩን ፎቶግራፍ ይዘው የወጡ ሲሆን አዲስ ጉዳይ በፓትሪያርኩ ሕይወት ላይ ያተኮረ ረዥም ጽሁፍ አስነብቧል፡፡ እንቁ በበኩሉ የሞታቸው ምክንያት ከእግራቸው ህመም ጋር የተያያዘ ነው ሲል አዲስ አድማስ ጋዜጣ ደግሞ የህልፈታቸው ምክንያት ስኳር በሽታ መሆኑን ገልጧል፡፡
ሌላም፣ ሌላም
 • ለምግብ እጥረት የተጋለጡ ተጎጂዎች ቁጥር አሻቀበ ሰንደቅ እና አዲስ አድማስ
 • የኢትዮጵያ መንግስት የትጥቅ ትግል ከሚያደርግ ድርጅት ጋር ዛሬ ይፈራረማል/ተፈራረመ ሰንደቅ እና አዲስ አድማስ
 • ተመስገን ደሳለኝ ፍርድ ቤት ሊቀርብ ነው ፍኖተ ነፃነት
 • የታሰሩ ኮሚቴዎቻቸው እንዲለቀቁ ሙስሊሞች ጠየቁ ፍኖተ ነፃነት
 • ከሚስቱ የተጣላው አትሌት ውሎው ሺሻ ቤት ሆኖዋል፡፡ ፊቱ ላይ ተስፋ መቁረጥ እና ራስን መጥላት ታይቶበታል የኛ ፕሬስ ተባራሪ ወሬ
 • የወረዳው ስራ አስፈጻሚ ስልጣናቸውን ለሚስታቸው አደራ ሰጡ የኛ ፕሬስ ተባራሪ ወሬ
 • ሚኒስትር ጂነዲን ማንን ምይቅርታ አልጠይቅም አሉቆንጆ መጽሄት
ርእሰ አንቀጾች
 • ከአፍንጫ አርቆ ማሰብ የተሳነው አትሌቲክስ ፊዴሬሽን የኛ ፕሬስ
 • በጥቂት አትሌቶች ዋጋ የተሸፈነ አስተዳደር ሊፈርስ ይገባዋል ሰንደቅ
 • ኢህአዴግ ነጻውን ፕሬስ ለማጥፋት የጀመረውን ዘመቻ ባስቸኳይ ያቁም ፍኖተ ነፃነት
 • ሜዳው ላይ እንተያይ!” አትሌት ጥሩዬ አዲስ አድማስ
የሳምንቱ ምርጥ ንግግር
‹‹አስራ አምስት አመት የሚያሳስረኝ ከሆነማ ይህች ሃገር የኔ አይደለችም ማለት ነው፡፡››
(ሳምሶን ማሞ
ለየኛ ፕሬስ ጋዜጣ በክሱ ዙሪያ ከተናገረው)

ተቃዋሚውን ማን ገደለው?

ባለፈው ሳምንት ማነው ተቃዋሚው በሚል ርዕስ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲ መንደር የቆበትን አፋፍ፣ እንዲሁም ለሞት የበቃበትን ጉዞ ለማየት ሞክረናል፡፡ ዛሬ ካለፈው ፅሁፍ የቀጠለውን እና የተቃዋሚው ጎራ አሁን ላለበት የመቃብር ህይወት ያበቁትን ጉዳዮች በወፍ በረር እናያለን፡፡

ተቃዋሚው ሞቷል ወይስ አለሞተም? ተብሎ ክርክር ቢነሳ አልሞተም ብሎ ለማረጋገጥ እና የህያዉን ተቃዋሚ ቋሚ አካል ማሳየት እጅግ ፈታኝ ነው፡፡ በተለይም አሁን ባለንበት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር አንፃር፡፡ ስለዚህም አዎ ነብሱን ይማረውና ተቃዋሚውማ ሞቷል ማለትን መርጫለው፡፡ አልአዛርን ይሆናል አይሆንም በቀጣዮቹ ጊዜያት በሚከሰቱት ክስተቶች እና በድኑ በሚሰጠው ምላሽ ይወሰናል፡፡ እናም ለዛሬ ተቃዋሚውን ማን ገደለው; በማለት እንጠይቃለን፡፡ ዋነኛ ተጠርጣሪዎችንም እንመረምራለን:: የግድያው ተካፋዮችን አንድ ባንድ ለማየት እንሞክር፡፡


የሰው ልጅ ራሳቸውን ከሚያጠፉ እንስሳት አንዱ እና ዋነኛው ነው፡፡ የሰው ልጅ ራሱን ማጥፋቱ ያልተፈታ ከባድ እንቆቅልሽ ነው፡፡ ለምን ሰው ራሱን ይጠላል? ራሱንስ እንዴት ይገድላል? የሚለው ጥያቄ ዘመናትን ተሻግሮ እሰከ አሁን ድረስ  ቁርጥ ያለ ምላሽ ባያገኝም መነሻው ይሄ ነው እየተባለ መገመቱ  ግን አልቀረም፡፡ በዋነኛነትም በዘር የሚወረስ ራስን ማጥፋት (Biological Factors)፣ በስነልቦና ችግር የሚመጣ ራስን ማጥፋት ( Psychological Factors) እንዲሁም በማህበረሰባዊ ችግሮች ምክንያት የሚከሰት ራስን ማጥፋት (Sociological Factors) ይጠቀሳሉ፡፡

ታዲያ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ የሞተው ራሱን አጥፍቶ ይሆን? ካጠፋስ በየትኛው ምክንያት ይሆን ራሱን ያጠፋው? በሶስቱ መነሻዋች እንመልከተው እስኪ፡፡

በዘር የወረሰው ራስን የማጥፋት አባዜ ((Biological Reasons)፣) በኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ ከተጀመረ ግማሽ ምዕተ ዓመት እንኳን ያልሞላው ሲሆን ፓርቲ በመመስረት ወደ ፖለቲካው የገቡት ፖለቲከኞች በቀይ ሽብር- ነጭ ሽብር ተጠምደው አንዱ አንዱን ሲያሳድድ የተሸነፍው ራሱን ደብቆ መኖር ሲከብደው ራሱን ከሀገር በማሰደድ ፖለቲካዊ ራስን ማጥፋት ፈፅሟል፡፡ ይሄ ራስን የማጥፋት አባዜ ዛሬ ላለው ተቃዋሚ ከቀዳሚዎቹ በዘር ውርስ ተላልፎ እራሱን አጥፍቶ ይሆን?

በስነ ልቦና ችግር የሚመጣ ራስን የማጥፋት አባዜ (Psychological Reasons)፡ ሳይኮአናሊስቱ ሲግመንድ ፍሮይድራስን ማጥፋት ዋነኛው መነሻው የበዛ ራስን መጥላት (Self Hate)ነው ይለናል፡፡ ከፍሮይድ ተከትለው የመጡ ሳይኮሎጂስቶችም የፍሮይድን ሀሳብ በማጠናከር ሰው ከራሱ ጋር የሚፈጥረው ፀብ በሞት አሸናፊነት ይጠናቀቃል ይሉናል፡፡ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ምናልባትም ራሱን አጥፍቶ ከሆነ ራስን መጥላት ምክንያት ሊሆን ይችላልን? ‹‹ለዚህ ሁሉ ዓመታት ታግየ ምንም ውጤት ማምጣት ካልቻልኩ መኖሬ ምን ሊረባ? እኔስ ለምን ቆሜ እሄዳለው?›› በማለት ራስን ማጥፋት እንደ ግለ ሂስ ቆጥሮት ይሆን?

በማህበረሰባዊ ችግሮች ምክንያት የሚከሰት ራስን ማጥፋት (Sociological Factors)፡ ፈረንሳዊው የስነ-ህብረተሰብ ሊቅ ኤሚል ዱርክሄም በህብረተሰቡ ውስጥ ተቀባይነት ማጣት እንደሁም የግንኙነት መላለት ሰዎችን ወደ ራስን ማጥፋት ይመራቸዋል በማለት ራስን ማጥፋት ማህበረሰባዊ ምክንያት አለው ይላል፡፡ ታዲያ የኢትዮጵያ ተቃዋሚስ ህብረተሰቡ አልተቀበለኝም ብሎ ራሱን አጥፍቶ ይሆን? ወይስ የአባላት እና የደጋፊዎች ቁጥር ማነስ ህብረተሰቡ ለኔ ያለውን ጥላቻ ያሳያል ብሎ ራሱን አጠፋ ይሆን?

የቤተ መንግስቱ ገዳይ (Cold Blooded Murderer from the Palace)

ራሱን አጥፍቶ ሊሆን ይችላል ከሚለው ጥርጣሬያችን በማስከተል የሚቀርበው ሌላው ተጠርጣሪ ደግሞ መኖሪያውን ከወደ ቤተመንግስት ያደረገ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ይህ ተጠርጣሪ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በስልጣን ላይ የቆየ ሲሆን በህግም የብዝሃ-ፓርቲ አስተዳደርን (Multi Party System) የፈቀደ ተጠርጣሪ ነው፡፡ ነገር ግን ሁለት ሀገር ዓቀፍ ምርጫዋችን ያለምንም ችግር ከ98 በመቶ በላይ ድምፆችን በማምጣት ለማሸነፍ የቻለ ሲሆን ሶስተኛው ላይ ግን ችግር ገጥሞት ነበር፡፡ ‹‹እባካችሁ ተጠናክራችው ግጠሙኝ፣ የሚፎካከረኝ አጣሁ እኮ›› ሲል የነበረው ተጠርጣሪ ሳያስበው ህዝቡ ለተቃዋሚዎች የሰጠው ድምፅ አስበርግጎት አለማቀፍ ተቋማት ሳይቀሩ ‹‹አፍረሀል›› ቢሉትም ‹‹እንደተለመደው በሰፊ ድምፅ ማሸነፍ ባልችልም አሁንም ድሉ የኔ ነው›› በማለት ስልጣኑን አልለቅም አለ፡፡

አይ እኛ ነን አሸናፊዎቹ ያሉትን ተቃዋሚዎችም ክፉኛ አቁስሎ ለአአልጋ ቁራኛ፣ ለደዌ ዳኛ አብቅቷቸዋል፡፡ ይባስ ብሎም በቁስል ላይ እንጨት እየሰደደ አንዳንዴም በርበሬ እየነሰነሰ ስቃያቸውን በማባባስ ስልጣኑን ለማራዘም ሞክሯል፡፡ በመጨረሻም አዳዲስ ህጎችን በማውጣት የተቃዋሚውን ግብዓተ መሬት እየሳቀ ከፈፀመ በኋላ አራተኛውን ሀገራዊ ምርጫ 99.6 % ድምጽ በማምጣት ‹‹አሸንፌአለሁ›› በማለት ‹‹ቧልት›› አሰምቷል፡፡

ለዚህም ማሰረጃ የሚሆኑት ሰነዶች ተጠርጣሪው ሟችን የሚያጥላሉ ፅሁፎችን በተደጋጋሚ በልሳኑ እንዲሁም በመንግስት ሚዲያዎች ሲያሰማ የነበረ መሆኑ፣ ምንጮቻቸው ከሰለጠኑት ሀገራት ነው በማለት የተለያዩ አፋኝ ህጎችን ማውጣቱ፣ በተደደጋጋሚ ሲያደርጋቸው የነበሩት ተግባራት በጥቅሉ ሲታዩ ተቃዋሚውን የገደለው የአራት ኪሎው ተጠርጣሪ ይሆን እንዴ? ያስብለናል፡፡

ቅጥር ነብሰ ገዳይ (Mercenary)

ይሄ ተጠርጣሪ ቅጥረኛ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ከአራት ኪሎ ተጠርጣሪ ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚጠረጠር ነው፡፡ ለመጠርጠሩ ዋነኛ ምክንያት የሆነው ደግሞ ከሟች (ተቃዋሚው) ጋር አብሮ አደግ ከመሆኑም በተጨማሪ አብረው የሚበሉና አብረው የሚጠጡ ጓዶች የነበሩ ሲሆን፡፡ ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ ግን ከቤተመንግስቱ ተጠርጣሪ ጋር በፍቅር ክንፍ ብሏል፡፡ ይሄም በዋነኛነት ሟች ከሞተ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ መሆኑ ጥርጣሬያችን ከፍ እንዲል ያደረገዋል፡፡

ለመሆኑ ይህ ተጠርጣሪ ምን ቢያገኝ ነው ወንድሙን የገደለው? ያልን እንደሆን በዋነኛነት የሚቀመጠው ሆድ አደርነት (Opportunism) ነው፡፡ ይሄን እንድንል ያስቻለን ደግሞ ተጠርጣሪው ሟች ከሞተ በኋላ የተለያዩ ንብረቶችን በግሉ ማፍራት የጀመረ ሲሆን በተለያዩ ጊዜያትም ሟችን የሀገሪቱ ዋነኛ ችግር መነሻ አድርጎ ለማቅረብ ሲሞክር ታይቷል፣ በተጨማሪም ሟች የነበረባቸውን ፓርቲዎች ለማፍረስ ከውስጥ ሌላ ‹‹አንጃ›› በመምራት ሟችን በቀን መርዞ እንደገደለው ይጠረጠራል፡፡

ሌላው እና ቅጥረኛ ገዳዩ የሟች አብሮ አደግ እንደሆነ እድንጠረጥር የሚያደርገን ጉዳይ ሟች ከሞተ በኋላ በሞቱ ደስተኛ የነበረ ሲሆን ከገዳይ ቀጣሪም ጋር አብረው መዋል እና ማደር ጀምረው ነበር፡፡ ይባስ ብሎም ‹‹ሟች መሞቱ ትክክለኛ ነገር ነው›› እያለ መግልጫ ሲሰጥ ነበር፡፡ ለህዝቡም እኔ እውነተኛ መሪህ አለሁልህ እያለ ህዝቡ ሟችን በቅጡ እንዳይቀብረው አድርጓል የሚል ጥርጣሬ አለ፡፡ እውን ተቃዋሚው የተገደለው በአብሮ አደግ ጓዱ ይሆን?

ባህል እንደ ተጠርጣሪ

ተቃዋሚውን ገድለውታል ተብለው ከሚጠረጠሩ አካላት አንዱ የህዝቡ ባህል በአጠቃላይ እንዲሁም የህዝቡ የፖለቲካ ባህል በተለይ ነው፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ ይሄን እንድንል ያስቻለን ህዝቡ ተቃዋሚዎች ስልጣን ቶሎ ይዘው መብቱን እንዲያስከብሩለት ከመመኝት ውጭ አብሮ በመርዳት፣ አይዟችሁ በማለት፣ በአባልነት በመሳተፍ ወ.ዘ.ተ ሲደግፋቸው ብዙም አለመታየቱ ነው፡፡ ይሄም ድርጊት የህዝቡ ባህል ተቃዋሚውን በቸልተኝነት ገድሎታል እንድንል ያደርገናል፡፡ 

ሌላው የህዝቡ ባህል ለሟች መሞት ዋነኛውን ድርሻ አበርክቷል እንድንል የሚያደርገን ጉዳይ ተጠርጣሪው በተረቶቹ እንዲሁም በወጎቹ ለሟች መሞት ምክንያት የሚሆኑ ነገሮችን ሲናገር መኖሩ ነው ለምሳሌ ‹‹ሁሉንም ወይም ምንም›› በማለት የብቸኝነት መንገድን እንደ ብቸኛ አማራጭ በማየት ተቃዋሚውግማሽ እንዳይመኝ እና በጋራ እንዳይሰራ አድርጎታል የሚል ጥርጣሬ አለ፡፡

በተጨማሪም የህዝቡ ባህል ‹‹ተባበሩ ወይም ተሰባበሩ›› በማለት አንድ አይነት አቋም የሌላቸውን ተቃዋሚዎች አንድ ላይ ለማድረግ ሞክሮ እንደገደላቸው ይጠረጠራል ይሄም ተግባር አንዳንዴ እንጨትን ከብረት ጋር ለማቅለጥ እንደ መሞከር ነው፡፡ ስለዚህም እውን ተቃዋሚውን የገደለው ባህሉ ይሆን?

ሌሎች ተጠርጣሪዎች

ከላይ ከተጠቀሱት ተጠርጣሪ ገዳዮች በተጨማሪ ሌሎቻ ተጠርጣሪዎችንም ማንሳት ይቻላል ለምሳሌ ሚዲትራኒያንን አቋርጦ የመጣው ባለ ሰማያዊ አይን ተጠርጣሪ አንዱ ነው ይህ ተጠርጣሪ ቤተመንግስት ካለው ተጠርጣሪ ገዳይ ጋር ‹‹ሽብርተኝነትን መዋጋት›› የሚል ውል ተዋውሎ ለሌሎች ነገሮች ትኩረት ባለመስተጠት እና የቤተመንግስቱን ተጠርጣሪ በገንዘብ በመደገፍ ለተቃዋሚው ሞት ተጠያቂ ሊሆን ይችላል፡፡ እውን ይሄ ባለ ሰማያዊ አይን ተጠርጣሪ ተቃዋሚውን ገድሎታልን?

ሌላው ገዳይ ሊሆን የሚችችለው ተጠርጣሪይ በቀዳሚ ነገስታት ሀገሪቱ ‹‹ጥቁር ውሻ ውለጅ›› የሚል ርግማን መረገሟ ሊሆን ይችላል የሚል ኢ-ሳይሳዊ መላ ምትም ይመታል፡፡ እውን እርማኑ ተቃዋሚውን ገድሎት ይሆን?

በአጠቃላይ ተቃዋሚውን ከላይ ከተዘረዘሩት ሀይላት አንዱ ገድሎታል ወይም ራሱን አጥፍቷል ማለት እንችላለን፡፡ የገዳዩን ማንነት የሚገልፀውን ውሳኔ ለማየት ደግሞ በጉጉት እንናፍቃለን፡፡

የያዘን አባዜ

ያለፈ ታሪክን መመርመርና ማወቅ አሁን ለምንኖርበት ነባራዊ ሁኔታ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው የማይካድ ሐቅ ነው፡፡ ታሪኩ ምንም ሆነ ምን እንዳለና እንደነበረ ለትውልድ መተላለፍ አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ ባለፈች አንዲት ሰከንድ ውስጥ የተፈጠረች ክስተት እንኳን ከታሪክነት ትመደባለች፡፡  ከግለሰብ ጀምሮ  አገራትም ጭምር የራሳቸው የሆነ ታሪክ ይኖራቸዋል፡፡ በተለምዶ ግን ታሪክ ስንል ቶሎ ብሎ ወደ አእምሮአችን የሚመጣው የአገር ታሪክ እንደመሆኑ መጠን እኔም የማወራው ስለ አገር ታሪክ እንደሆነ ይታወቅልኝ፡፡
ግራ ገብቶናል!
በርግጥ ሁሉም ዓይነት ታሪኮች ተያያዥነት አላቸው፡፡ ስለግለሰቦች ሳናወራ ስለአገር እናውራ ማለት አንችልም፡፡ በብዛት የአገር ታሪክን የያዙ ፅሁፎች አገሪቷን ሲያስተዳድሩ በነበሩ መሪዎች የቆይታ ዘመን ተከፋፍለው በጊዜው የነበሩ መሪዎች እና የቤተሰብ ታሪክን ጨምሮ አገሪቷን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚካዊ ሁኔታ በዝርዝር ያካትታሉ፡፡ እስካሁን እንደተመለከትኩት ከሆነ ከሚፅፈው ሰው አኳታሪክን በደጋፊ፣ በተቃዋሚ/ጠላት እና በምሁራን የሚፃፍ ብለን በሦስት ከፍለን ልናየው እንችላለን፡፡ በአሁኑ ሰዓት በደጋፊና በተቃዋሚ ተፅፈው የምናገኛቸው ታሪክ የሚተርኩ መጽሐፍቶች ቁጥራቸው ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ መሄዱ አሳስቦኛል፡፡ በዛው ልክ ግራ የተጋባንበትና የትኛውን ተቀብለን ‹ታሪካችን› አድርገን እንደምንወስድ ያላወቅንበት ሁኔታ ያለና ወደፊትም በዚሁ መቀጠሉ አይቀሬ ይመስለኛል፡፡
በጣም አስፈላጊውና ልናውቀው የሚገባን ታሪክ ምርምር ተደርጎ በዘርፉ ምሁራን የተጻፉትን መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ነገር ግን የዚህ ዓይነት መጽሐፍቶችን በሚፈለገው መጠን ማግኘት ተአምር ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ኃላፊነትን ወስዶና ታሪክን ለትውልድ ለማስተላለፍ የሚሰራ አካልም ያለን አይመስለኝም፡፡ ስለዚህም አሉን የምንላቸው የታሪክ ድርሳናት ዘመኑን ወይም መሪውን በመውደድ ወይም በመጥላት ተመርኩዘው እና በሁለት ጎራ ተከፍለው ፅንፍ በመያዝ የተፃፉ ናቸው ብንል ስህተት የማይሆን ነው፡፡
የንጉስ አገዛዝ በነበረት ጊዜ ብንመለከት ጸሐፍያኖቹ ራሳቸው የንጉሡ ጸሐፊ ወይም ወዳጅ ይሆኑና ስለንጉሱና አገዛዛቸው መልካምነት ከመናገር እና ከመጻፍ ውጪ ሌላ አማራጭ አይኖራቸውም፡፡ በደርግ ዘመን ሳንሱርን በመጠቀም አገዛዙን አስመልክቶ ተችቶ ወይም ተቃውሞ መፃፍ በሕግ የተከለከለ ነበር፡፡ አሁን ባለንበት ዘመን ደግሞ እንደተፈለገ መጻፍ እንደሚቻል በመርህ ደረጃ ይነገርና ተግባር ላይ ግን ተፈፃሚ አይሆንም፡፡ በሁሉም ጊዜያቶች የተጻፉ ታሪኮች ግን ተመሳሳይ የሚያደርጋቸው ነገር አለ፡፡ ሁሉም ማለት ይቻላል ካለፈው ወቅት ጋር ሲነፃፀር የራሳቸውን አገዛዝ የተለየና አዳዲስ ለውጦች የታየበት እንደሆነ ያለፈው ግን ትክክል እንዳልነበረ መናገር እና መፃፍ የዘወትር ተግባራቸው ነው፡፡ ይህ ተግባር ታሪክን ከማጥፋት ባሻገር አንድ ታሪክ ያለውን ሕዝብ በጎራ ከፋፍሎ ከአንድ በላይ ታሪክ በማስተማር ትክክለኛውን ታሪክ መረዳት እንዳይችል ያደርጋል፡፡

‹ነግ በኔ›
ያለፉት አልፈዋል ከመውቀስ በስቀተር ምንም ማድረግ አንችልም፡፡ አሁን ያለው የኢሕአዴግ መንግስት ግን አትኩሮት ሰጥቶ በተቻለ መጠን በገለልተኛ ወገን የአገራችን ታሪክ የሚፃፍበት ሁኔታ ቢጀመር መልካም እንደሆነ ተገንዝቦ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ግራ በመጋባት ያለውን ትውልድ መታደግ አለበት፡፡ እስካሁን እየሰራቸው ያሉ ነገሮች ግን ከዚህ በተቃራኒ ናቸው፡፡ የቀድሞ ታሪካችንን በራሱ እይታ በመመልከትና የራሱ ድምዳሜዎችን የኛም እንዲሆኑ ነው የሚደረገው፡፡ መቼም የቀድሞ መሪዎቻችን በጊዜያቸው ሙሉ መጥፎ ነገር ሲያደርጉ ነበር ማለት የሚያስኬድ ነገር አይደለም፡፡ እንዲያውም ያኔ ፈተናው በበዛበት ወቅት በብዙ ነገር ተፈትነው ለኢትዮጵያ አገራችን ከማንም በላይ መስዋእትነት የከፈሉ፣ ታግለውና ተከራክረው አገራችንን ያቆዩልን መሪዎች ነበሩን፡፡ ነገር ግን ይህን መልካም ሥራቸውን ማውራት አሁን ያለውን መንግስት እንደመቃወም የሚቆጠርበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ እነዚህ ታሪኮች እና ተዋናዮቻቸው የሚዘከሩበትና የሚከበሩበት የድል በዓላት አከባበር ድምቀት ከጊዜ ወደጊዜ ቀንሷል፡፡ በዚሁ ከቀጠለ እንዲያውም ሳይረሳም አይቀርም፡፡
ይህ ታሪክን የመቅበር ወይም የመበረዝ ሥራ በዚህ ወቅት አገር ከሚመራ መንግስት የሚጠበቅ አይደለም፡፡ ‹የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ› የሚለው የቴዲ አፍሮ ዘፈን በትክክል ይገልፀዋል፡፡ የኋላችንን የምንጥል ከሆነ እኛም ያልኖርን ጊዜ ታሪካችን እንደማይኖር መታወቅ አለበት፡፡ ትላንት ጠላት ወይም አሸባሪ ሲባል የነበረው አሁን መሪውን እንደጨበጠው ሁሉ ዛሬ አሸባሪ ወይም ጠላት የሚባለው ነገ መሪውን እንደሚይዝ ሳይዘነጋ የህዝብ የሆነን ታሪክ ለትውልድ እንዲተላለፍ የማድረግ ሥራ ቢሠራ መልካም ነው፡፡
ሙዚየም ወይስ የኢሕአዴግ የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ?
ከመጽሐፍት በተጨማሪም በወቅቱ የነበሩ ሰዎች ምስክርነት፣ ስዕላዊ መግለጫዎች፣ ቪዲዮና ኦዲዮዎች፣ ፎቶግራፎች እና ሌሎች መሰል ነገሮችም ታሪክን እንድናቅ የሚረዱ ነገሮች ሲሆኑ ሙዚየም መጽሐፍትን ጨምሮ ከላይ የተዘረዘሩትን ነገሮች ሁሉንም በአንድነት ልናገኝ የምንችልበት ታሪካዊ ቦታ ነው፡፡ ይህን በማሰብ የዞን ዘጠኝ ኢ-መደበኛ የጦማሪዎች ቡድን በደርግ ዘመን በ‹‹ቀይ ሽብር›› ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎች የተሰራውን መታሰቢያ ሙዚየም ጉብኝት አድርገናል፡፡
ፎቶግራፎች፣ የተለያዩ ደብዳቤዎች፣ መጽሔቶችና የሕትመት ውጤቶች፣ አልባሳቶች፣ ይጠቀሙባቸው የነበሩ መሳሪያዎች እና ሌሎችም በሙዚየሙ የተካተቱ ሲሆን በያንዳንዱ ግርጌ መግለጫ ተፅፎባቸዋል፡፡ መግለጫዎቹን ስናነብ የታዘብነውና ያስገረመን ነገር በአብዛኛዎቹ መግለጫዎች የኢሕአዴግ መንግስት በደርግ ላይ ያለውን አመለካከት እና ትንታኔዎች የሚያሳዩ ጽሑፎች መሆናቸው ነበር፡፡ በኢቲቪ ከሚቀርቡት የደርግን መንግስት የሚያወግዙ ዶክመንተሪዎች ላይ ከምንሰማቸው ንባቦች ጋር ወይም በተመሳሳይ ርዕስ በኢሕአዴግ ከሚዘጋጁ የፎቶግራፍ አውደርዕይ ጋር ልዩነት የለውም፡፡ ኢቲቪን በአንድ ህንፃ ማየቱ ታዲያ ምኑን ሙዚየም ሆነው? ውሳኔውን ለተመልካች ወይም ለአንባቢ ትቶ በወቅቱ የነበረውን ነገር ብቻ መግለፅ ከባድ ነገር ሆኖ ነውን? እንግዲህ ነገ የሚመጣው ደግሞ ይህን ሙዚየም እንዴት እንደሚቀይረው እና ምን ዓይነት መግለጫዎች እንደሚጽፍበት ማሰብ ነው፡፡
ታሪካችን ግን በእንዲህ ያለ ሁኔታ ገዢዎቻችን በተለያዩ ቁጥር መቀያየር እና የነሱን ሐሳብ የሚያንፀባርቅ ሳይሆን ትክክለኛው ታሪክ ተጠንቶ ተመሳሳይ የሆነና ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ እና ውዥንብር የማያስነሳ መሆን ይኖርበታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለማንኛውም በኛ በኩል አንድ እና ትክክለኛ ታሪክ እንዲኖረን ማድረግ የምንችለውን እናድርግ፡፡

ድምጻችን ይሰማ!

ርዕሳችንን የተዋስነው ‹‹ለሙስሊሙ ጉዳይ መፍትሔ አፈላላጊው ኮሚቴ›› ከሚጠቀምበት የፌስቡክ ገጽ ስያሜ ነው፡፡ ‹‹ድምጻችን ይሰማ›› የሚለው ሐረግ የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታ በአግባቡ የሚገልጽ ነፍሰጡር ሐረግ ነው፤ ብዙ ፍቺዎችን ይወልዳል፡፡ ጥያቄ፣ ተማፅኖ እና ትዕዛዝም ሊሆን ይችላል፡፡
ሙስሊሙ ማኅበረሰብ በርካታ ጥያቄዎችን አንስቷል፡፡ ከጥያቄዎቹ መካከል ‹‹መጅሊሱ›› አይወክለንም እና ይቀየር የሚለው አንዱ ነው፡፡ ለዚህ የተገኘው ምላሽ መጅሊሱን የሚተኩ አባላት የመምረጥ መብት ቢሆንም አካሔዱ ሌላ ጥያቄ አጭሯል፤ አባላቱ መመረጥ ያለባቸው በቀበሌ ጽ/ቤቶች በኩል ነው በሚል፡፡ ይህንን ደግሞ አብዛኛው ሙስሊም ሃይማኖታዊ ጉዳይን ከፖለቲካጋ ከመቀላቀል ለይቶ አልተመለከተውም፡፡ ስለዚህ ጥያቄው መልስ እስኪያገኝ ድረስ ተቃውሞውን ለመቀጠል የወሰነ ይመስላል – በሰላማዊ ተቃውሞ፡፡
የሰላማዊውን ተቃውሞ ዑደት (cycle) ብንመለከተው – ይጠይቃሉ፣ መልስ የለም፤ ይማፀናሉ፣ መልስ የለም፤ ያዝዛሉ መልስ የለም፡፡ መጠየቅ ተፈጥሯዊ ግዴታቸው ነው እና አያቆሙም፣ መማፀን ሰብአዊ ልምዳቸው ነውና ይተገብሩታል፣ ማዘዝ ሃይማኖታዊ ነፃነታቸው ከፖለቲካ ተፅዕኖ እንዲወጣ የተሰጣቸው ሕገመንግስታዊ መብታቸው ነውና ያዝዛሉ፡፡ ይህ ደግሞ የሰው ልጅ ባሕሪ ነው፡፡ ዕውቁ ቼካዊ ጸሐፊ ፍራንዝ ካፍካ ይህንን በማስመልከት እንዲህ ብሏል፤ ”Believing means liberating the indestructible element in oneself, or, more accurately, liberating oneself, or, more accurately, being indestructible, or, more accurately, being.”
በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ጥያቄ እና በመንግስት ምላሽ ምሳሌ የምንረዳው ጠቅላላውን የሕዝብና መንግስትን ግንኙነት ነው፡፡
ባለፉት 21 ዓመታት ውስጥ /በተለይም ሕገመንግስቱ ከፀደቀ ወዲህ ባሉት 17 ዓመታት/ ሕዝቦች በድምጻቸው መንግስትን ከመሾምና ከመሻር ጀምሮ ያለው መብት በሙሉ ተሰጥቷቸዋል ይባላል፡፡ እውነት ተሰጥቷቸዋል? እስቲ የኢትዮጵያን የጨዋታ ሕግ እንመለከት፡፡

የምዕራባውያን ሚና እና ድምጻችን
ምዕራባውያን አፍሪካን ወይም ኢትዮጵያን እንደመለስ ዓይነት ባሉ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የመግባባት እና የማሳመን ችሎታ ባላቸው ልሂቃን ዓይን መመልከት እና የአፍሪቃ ቀንድን ከቧታል ከሚሉት አደጋ ይጠብቅልናል ብለው በሚያስቡት መሪ ማስገዛት ይፈልጋሉ፡፡ በመሆኑ ሙስሊም ማኅበረሰብም ሆነ ሌላው በሰላማዊ መንግድ ድምጹን በማሰማት ላይ ያለ ሰው ለትግሉ ምላሽ እርሳቸውን የመሰለ ሰው በማግኘት አለማግኘቱ ላይ የተንጠለጠለ ነው::
ምዕራባውያን በአፍሪካውያን እና በአረብ ላይ ያላቸው አመለካከት በጥቅሉ ጨለምተኛ ነው ማለት ይቻላል፤ አረብን ከእስልምና ጋር በመቀላቀልም ቢሆን ከመታማት አይተርፉም፡፡ ምንም እንኳን በአገራችን ውስጣዊ ጉዳይ ላይ አያገባቸውም ብሎ መዝጋት ቢቻልም፣ በመንገዳችን ላይ የሚጥሉብንን እንቅፋት ግን ከመጋፈጥ አንተርፍም፡፡ ስለዚህ ስለድምጻችን መደመጥ ሲባል እነርሱን የማሳመንም ዕዳ አለብን፡፡
አብዮታዊ ዴሞክራሲ እና የድምጽ ዋጋ
ምርጫ 97 እና ውጤቱ ገዢው ፓርቲ ለዴሞክራሲ እሴቶች የሚሰጠው ዋጋ ግምት ውሰጥ የወደቀበት የመጀመሪያው አጋጣሚ ነው ማለት ቢቻልም፣ ይህንን ጥያቄ ለማንሳት የአብዮታዊ ዴሞክራሲን ብያኔ ማወቅ እና ከአጀማመሩ ጀምሮ ያለውን ሒደት መመርመር ያስፈልጋል፡፡
አብዮታዊ ዴሞክራሲን ይህ ነው የሚል ብያኔ የሚሰጥ ምሁር እስካሁን አልተገኘም፡፡ ምናልባትም ክፍተቱ የተፈጠረው በዘፈቀደ የሚጓዙበት ርዕዮተ-ዓለማዊ መንገድ ከመሆኑ አንጻር ነው ብሎ ለመደምደም ያስችል ይሆናል፡፡ የልማታዊ ጋዜጠኝነት አካዳሚያዊ ፍቺ ተዛብቶ በነባራዊቷ ኢትዮጵያ፣ በመንግስት ይዞታዎች ስር ባሉ ሚዲያዎች ‹‹ይሁንታን ማምረት›› እየሆነ እንደሆነ ከዚህ በፊት በዞን ዘጠኝ ላይ አውርተናል፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲም፣ ኢሕአዴግ በጥቅሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ መራኄ ጥያቄ ዳቦ እንጂ ዴሞክራሲ አይደለም ከሚለው ፈሊጥ’ጋ የተያያዘ እንደሆነ መገመት ወደተሳሳተ ድምዳሜ አያደርስም፡፡ በዚህ ስሌት ዳቦን (ልማትን) ለማምጣት ሲባል ዴሞክራሲና ሰብአዊ መብቶች የሚደፈጠጡበት የሚል አንድምታ ላይ ለመድረስ የመንገደድበት ጊዜ ይኖራል፡፡
ድምጽ በዴሞክራሲያዊ ስርዓቶች ውስጥ ያለው ዋጋ ከፍተኛ ቢሆንም፣ (መለስ እንደሙጋቤ ‹‹አፍሪካ የሚያስፈልጋት የምዕራባውያኑ ዓይነት ዴሞክራሲ አይደለም›› ማለታቸው ይታወቃል፤) ስለዚህ አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ አፍሪካውያንን የሚስማማ ዴሞክራሲ ነው ቢሉን እንኳን ለሕዝባዊ ድምጽ የሚሰጠው ዋጋ እስካሁን ተለይቶ አልታወቀም፡፡
የምርጫ 97ን ውጤት ተከትሎ ‹አሸናፊው እኔ ነኝ፣ እኔ ነኝ› በሚለው የገዢውና ተቃዋሚ ፓርቲዎች እሰጥ አገባ መካከል ‹‹ምርጫው ይደገም›› በሚል ተቃዋሚዎች የጠየቋቸውን ወረዳዎች ባብዛኛው ባለመቀበል፣ ወትሮም ነፃ የመሆኑ ነገር የሚያጠያይቀው የምርጫ ቦርድ – የሕዝቦችን ድምጽ ዋጋ አሳጣው፡፡ ትንሽ ቆይቶ ይህንን ርምጃ እየተቃወሙ አደባባይ የወጡ ተቃዋሚዎችን ድምጽ የሚሰማ ነፃ ወገን ጠፍቶ – ቢያንስ ለ193 ሰዎች ሞት መንስኤ ሆነ፡፡
ይህንን ክፉ ገጠመኝ በወቅቱ ሲዘግቡ የነበሩት አገር በቀል ጋዜጦች በጅምላ ታገዱ፡፡ ይህን ጊዜ ብዙዎች ድምጻቸው በምርጫ ዋጋ እንደሌለው ብቻ ሳይሆን ሌላ ድምጻቸውን የሚያሰሙበት መንገድ እንደሌላቸውም ተስፋ መቁረጥ ደረጃ ላይ ደረሱ፡፡ ከዚህ አጋጣሚ በኋላ በተለይም በተቃዋሚው ጎራ ያሉ ወገኖች በደርግ ዘመን አለ ይባል የነበረው የፍርሃት ማስካቸው ውስጥ ገብተው ተሸሸጉ፡፡ ለምርጫ 2002 የተመዘገቡ ሰዎች ቁጥር ከምርጫ 97ቱ በእጅጉ ማነሱም የሚናገረው ሕዝቦች ‹‹ድምጻችን ላይሰማ ነገር…›› ብለው ተስፋ መቁረጣቸውን ነው፡፡
በየጊዜው የሚያሻቅበው የኑሮ ውድነት፣ መንግስት ልማትን ከሰብአዊ መብት የማስደሙ ውዝግብ፣ የፓርቲ አባልነት በመንግስት ተቋማት የሁለተኛ ዲግሪ የማግኘት ዕድል ከማሰጠት ጀምሮ ላሉ ጉዳዮች እንደዋስትና መታየቱ፣ እጅግ በርካታ መንግስትን የሚነቅፉ ዜጎች ባሉበት አገር በፓርላማው ውስጥ አንድ ብቻ ተቃዋሚ መኖሩ… ወዘተ፣ ወዘተ… እጅግ የሚያስጮሁ ሐቆች ሆነው ሳለ ሕዝቡ ዝምታን መምረጡ ድምጼ ሰሚ የለውም ብሎ ተስፋ ወደመቁረጡ መሆኑን እንረዳለን፡፡ ይህንን ዓይነቱን ለመብት ተቆርቋሪነት መቀዛቀዝ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን Political apathy (‹ፖለቲካዊ ዳተኝነት› እንበለው፣) ይሉታል::
‹ፖለቲካዊ ዳተኝነት› የዜጎች በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማድረግ ፍላጎት አለመኖር ነው፡፡ እንደምሳሌም፣ ሰበቡ ምንም ይሁን ምን ‹ፖለቲካዊ ዳተኝነት› ውስጥ የገቡ ሕዝቦች አለመምረጥ፣ ሕዝባዊ አስተያየት አለመስጠት፣ ዜግነታዊ ግዴታን ለመወጣት አለመሻት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ በርካታ ምሁራን እንደሚስማሙበት ደግሞ እንዲህ ዓይነቱ ‹ፖለቲካዊ ዳተኝነት› የአንድን አገር ዕድገት ባለበት ቆሞ እንዲቀር መንስኤ የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ድምጻችን
ተቃዋሚ ፓርቲዎች የገዢው ፓርቲ አይወክለንም የሚሉ ድምጾችን ማስተጋባት /አሊያም ቢያንስ ድምጾቹ ወይም ጥያቄዎቹ አግባብ መሆን አለመሆናቸው ላይ አስተያየት መስጠት/ እንዳለባቸው በጥቅሉ ይታመናል፡፡ ይሁን እንጂ፣ በዚህ ጽሑፍ እንደምሳሌ (sample case) የያዝነውን የሙስሊሞችን ጉዳይ እንኳን በሚመለከት ያለውን ሁኔታ ብናስተውል ተቃዋሚዎች ያላቸው ድርሻ እጅግ አነስተኛ ሁኖ እናገኘዋለን፡፡ እስካሁን ድረስ ጥቂቶቹ ተቃዋሚዎች ብቻ ጊዜያዊ መግለጫቸው ላይ ‹‹ጣልቃ ገብነቱን›› እንቃወማለን ከማለት ባሻገር፣ መሬት ላይ ወርዶ ሊተገበር የሚችል የመፍትሄ ሐሳቦችን በመጠቆምና የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገር፣ ወይም ድምጹን በማጉላት የሠሩት ሥራ አለ ለማለት የሚያስደፍር ነገር የለም፡፡
አንዳንዶች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ራሳቸው ድምጻቸውን የተቀሙ እንደሆኑ ይከራከራሉ፡፡ የሚሰጡትን የአቋም መግለጫም ቢሆን ገዢው ፓርቲ ከቁብ ቆጥሮ ያዳምጣቸው እንደሆነ እንኳን በጥርጣሪ የሚጠይቁ እልፍ ናቸው፡፡
ከድምጻችን ተቀማ እስከ ድምጻችን ይሰማ?
የሙስሊሞች ጉዳይ መፍትሄ አፈላላጊው ኮሚቴ አባላት በሙሉ እንደታሰሩ ተሰምቷል፣ የገዢው ፓርቲ በርካታ ሙስሊሞችን በየክፍለሃገሩ እያስተባበረ ሰልፍ እያስወጣ ይገኛል፡፡ እነዚህ ሰልፍ የሚወጡ ሰዎች ‹‹ምርጫውማ በቀበሌ ነው መካሄድ ያለበት›› እያሉ ለትዝብት የሚዳርግ ክርክር ሲከራከሩ በኢቴቪ አይተናል፡፡ ኢቴቪ እነዚህን ሰዎች ሰፊ ሽፋን መስጠቱ ራሱ ምን እየተሰራ እንደሆነ ግልጽ ያደርገዋል፡፡ ገዢው ፓርቲ ድምጽ መስማት ስለማይችል ድምጽ መቀማት ጀምሯል ማለት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ ድምጽ የማስመለስ ጥረቱ ደግሞ የሚቀጥለው፡፡
በዚህ ዘመነ-መንግስት ድምጽ የመቀማት ወግ የነበረ፣ ያለ እና ኢሕአዴግም እስካለ የሚቀጥል ይመስላል፡፡ ሰላማዊ ሰልፍ መውጣት ይቻል ነበር ቀርቷል፣ በምርጫ 97 መቶ በመቶ የተቃወመ በምርጫ 2002 መቶ በመቶ ደገፈ የሚል ስላቅ ተሰምቷል፣ በየዕለቱ ሁለት ሦስት ጋዜጦች ይወጡ እንዳልነበር አሁን ከሳምንቱ ሦስት ቀናት (ሰኞ፣ ሐሙስ እና አርብ) ምንም ፖለቲካ ነክ ጋዜጦች ማግኘት አይቻልም፡፡ ሐሳብን የመግለጽ መብት በሕግ ሰፍሯል ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የማይጎበኙ ድረገጾች ቁጥር በየቀኑ ያድጋል:: እነዚህ ሁሉ ድምጽ የመቀማት መንግስታዊ ስልት ውጤቶች ናቸው፡፡
ሰላማዊ ትግል እና ‹‹ድምጻችን ይሰማ››
ከቱኒዚያ እና ከግብጽ የፀደይ አብዮት መማር እንደቻልነው፣ ሰላማዊ አብዮታቸው (የነርሱ) ድኅረ ምርጫ 97 ላይ ከነበረው (ከኛ) የተለየ መልክ አለው፡፡ ምንም እንኳን በእኛ አገር፣ ለሕዝባዊ ተቃውሞዎች የመንግስት ሠራዊት የሚወስዳቸው ርምጃዎች ሕዝቡን የሚያስቆጡና ወደአመፅ የሚመሩ ቢሆኑም፣ ያኔ የነበረው ድንጋይ ውርወራ ላይ ያተኮረ አመፅ ከሰላማዊነት ያፈነገጠ ነበር፡፡ አሁን ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ጥያቄውን የሚያቀርብበት መንገድ ግን አስተያየት ሰጪዎች ‹‹የገዢው ፓርቲ ቅጥሮች›› ናቸው በሚሏቸው ሰዎች ብጥብጥ ለመፍጠር የተሞከረ ቢሆንም በብዙሐኑ ለሰላማዊነት ተገዢነት በተደጋጋሚ ከሽፏል፡፡ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ጥያቄውን ወይም ተቃውሞውን አመፅ አልባ በሆኑ መንገዶች ብቻ ለማድረግ መወሰኑ እና ከስድስት ወራት በላይ በትግሉ በፅናት መቆየቱ የሚያሳየን፣ በሰላማዊ መንገድ ረዥም ጉዞ መጓዝ እንደሚቻል ቢሆንም መልስ ሳያገኙ እስካሁን መቆየታቸው ግን መንግስትን በቸልተኝነት ከመወንጀል አያተርፈውም፡፡
እንዲያውም የኢትዮጵያ መንግስታዊ ተቋማት ለሰላማዊ ትግል እና ለድምጻችን ይሰማ ጥያቄ ከፍተኛ ደንቃራ ሊሆኑ እንደሚችሉ መጠርጠር ይገባል:: በብዙ ታዳጊ አገራት እንደምናስተውለው፣ የኢትዮጵያ መንግስታዊ ተቋማት፣ መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት አንፃር ያላቸው ተወዳዳሪነት አነስተኛ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በአሁኗ ኢትዮጵያ፣ ለምሳሌ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨትም ሆነ ማሰራጨት የመንግስታዊ ተቋም ኃላፊነት ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ወሳኝ የአገሪቷ ተቋማት (ፖሊስ፣ ፍርድቤት እና ዩንቨርስቲዎች) የስርዓቱን ወይም የገዢው ፓርቲን ለማገልገል የቆሙ የመምሰላቸውን ጉዳይ ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡
ሕገመንግስቱም ቢሆን ከተመሳሳይ ችግር ሰለባ ከመሆን አላመለጠም፡፡ ዴሞክራሲያዊ መርሆችን በንቀጾቹ እንዲያካትት ቢደረግም በዕለት ተዕለት የመንግስት ባለስልጣናት ተግባር ግን ሲጣስ ይውላል፡፡ ስለዚህ የሰላማዊ ትግል ሚና ሕገመንግስቱን ማስጠበቅ ነው ማለትም እንችላለን፡፡
የድምጻችን ይሰማ ተስፋ
የፌስቡኩ ‹ድምጻችን ይሰማ› ገጽ ላይ የሚሰፍሩ ጽሁፎችን ለተመለከተ ሁለት ነገሮችን መረዳት ይችላል፡፡ አንደኛ፤ የዜጎች ጋዜጠኝነት (citizens journalism) ምን ያህል እየተተገበረ እንደሆነ እንደሆነ እና የሌላውን ሕዝብ ስሜት ላለመጉዳት ምን ያህል ጥንቃቄዎች እየተደረጉ እንደሆነ በግልጽ ማየት ይቻላል፡፡ የገጹ አስተዳዳሪዎች ከተለያዩ ወገኖች የሚገኙ መረጃዎችን ለመላው ሕዝብ እንዲዳረስ የሚያደርጉበት ፍጥነት አስደናቂ ነው፡፡ በሌላ በኩል በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ የተሰነዘሩ የእርምት አስተያየቶችን በሂደት እያስተካከሉ ሲመጡ በጥብቅ የተከታተላቸው የሚረዳላቸው ጥንካሬያቸው ነው፤ የሰላማዊ ትግል ባሕሪም ይኸው ነው፡፡

በዚህ ዓይነት፣ ሕዝቦች አንድነታቸውን እና ሰላማዊነታቸውን በፅናት እስከጠበቁ ድረስ ብሎም የሚጠይቁትን ነገር ሚዛናዊነት እና ምክንያታዊነት እስካወቁ ድረስ፣ መልስ ማግኘታቸው የማይቀር እውነታ ነው፡፡ እዚህጋ መልስ ለመስጠት የማይፈልጉ ሰዎች ሚና ጥያቄውን በሚያቀርቡት ሰዎች ጥንካሬ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ መብት በገዢዎች ችሮታ የሚሰጥ ነገር ሳይሆን በሕዝቦች ፍላጎትና ፈቃደኝነት ላይ የሚገነባ ጉዳይ ነው፡፡ ሕዝቦች ‹ድምጻችን ይሰማ› ካሉ፣ የግድ ነው – ድምጻቸው ይሰማል፡፡

ጋዜጦች እና መጽሔቶቻችን ከሰኞ እስከ ሰኞ – አሥር

(ከሐምሌ 30 እስከ ነሐሴ 6፣ 2004)
Capitalጋዜጣ “Golden Girls” በሚል ርዕስ በፊት ገጹ ላይ ባስነበበው ዜና ኤድናሞል ላይ በተሰቀለው ስክሪን የዓርብ ዕለቱን ሩጫ ሲመለከቱ የነበሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን መሰረት ደፋር በሚበሩት እግሮቿ የመጨረሻውን መስመር ስትረግጥ በሐሴት እንደተጥለቀለቁ ጽፏል፡፡ Fortune ጋዜጣም በተመሳሳይ ዜና ኢትዮጵያውያን በሙሉ ወርቁ የኢትዮጵያ እንደሆነ በርግጠኝነት ተማምነው፣ ሲጠብቁ የነበሩት ከመሰረት እና ከጥሩነሽ ማን ያመጣዋል በሚል እንደሆነ ዘግቧል፡፡
** ** **
‹‹ዳግም የተወለደችው መሠረት ደፋር›› የሚል ዜና ያስነበበን ደግሞ ሪፖርተር ጋዜጣ ነው፡፡ ‹‹“የአምስት ዓመት ልጄን በስልክ አግኝቻት ነበር፡፡ እርሷም ‹ማሚ እባክሽ የወርቅ ሜዳሊያውያን አሸንፊ› ስትል ጠየቀችኝ፡፡ ቃል ገብቼላት ነበር፤ ቃሏን በመጠበቄ ኮርቻለሁ በቃ፣ ዛሬ እንደገና የተወለድሁ ያህል ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል፤” …››
** ** **
‹‹…አቃቤ ሕግ በተመስገን ደሳለኝ ላይ ሦስት ክሶችን የመሰረተ ሲሆን ፥ ክሶቹም 1ኛ ወጣቶች በአገሪቱ መንግስትና ሕገ መንግሥታዊ ሥርአቱ ላይ እንዲያምጹ የመገፋፋትና ግዙፍ ያልሆነ የማሰናዳት ተግባር፣ 2ኛ የሀገሪቱን መንግስት ስም ማጥፋት እና የሀሰት ውንጀላ እንዲሁም 3ኛ የሀሰት ወሬዎችን በማውራት ሕዝብን በማነሳሳት ወይም አስተሳሰባቸውን ማናወጥ የሚሉ ናቸው። …››

 ** ** **
‹‹…በተለይ የአገሪቱ ትልቁ የንግድ ባንክ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለደንበኞቹ ሌተር ኦፍ ክሬዲት መክፈት ሲያቆም፣ ባንኩ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው የአገሪቱ የሦስት ወራት የውጪ ንግድ ከመቀነሱ ጋር በተያያዘ ነው የሚል መልስ እየሰጠ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ …››
** ** **
አዲስጉዳይ መጽሔት ‹‹ጋዜጠኛ ሳምሶን ማሞ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተፈጽሞብኛል አለ›› የሚል ዜና አስነብቧል፡፡ ‹‹በዜድ ፕሬስ ፕሮሞሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ሥር እየታተመ በየሳምንቱ ለንባብ ይቀርብ የነበረው ኢትዮ ቻናል ጋዜጣ ንግድ ፈቃድ ባለማደስ ምክንያት ላልተወሰነ ጊዜ ከህትመት ውጪ እንደምትሆን የኢትዮቻናል ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ሳምሶን ማሞ ለአዲስጉዳይ ተናግሯል፡፡…››
** ** **
ሌላም፣ ሌላም
ርዕሰ አንቀጾች
የሳምንቱ ጥቅስ

‹‹15 አመት እንደምታሰር እያሰብኩ ጋዜጣ ልሠራ አልችልም›› – ሳምሶን ማሞ (ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ በሰጠው ቃለ ምልልስ)