Monthly Archives: September 2012

የትችት ባሕላችንን ብንተቸውስ?


ከግሪክ፣ የኤሶጵ ተረቶች አንዱ እንዲህ ይተረካል፡፡ አንድ ሰውዬ እና ልጁ፣ አህያቸውን አስከትለው ወደገበያ ሲሄዱ የተመለከታቸው የአገሩ ሰው፣ ‹‹እናንት ሞኞች፣ አህያው እኮ የተፈጠረው ሊጋለብ ነው›› ይላቸዋል፡፡ አባት ልጁን አህያው ላይ ጭኖ ትንሽ እንደተጓዙ የሆኑ ሰዎች ይመለከቱ እና ‹‹ምን ዓይነት የተረገመ ልጅ ቢሆን ነው አባቱን በእግሩ እያስኬደ እሱ የሚጋልበው?›› አሉ፡፡ አባት ልጁን አስወርዶ ራሱ መጋለብ ቀጠለ፤ ጥቂትም ሳይጓዙ ግን ‹‹ምን ዓይነት ክፉ አባት ነው ልጁን በእግሩ እያስኳተነ እሱ አህያ የሚጋልብ?›› ብለው የሚተቹ ሰዎች አለፉ፡፡ ግራ የተጋባው አባት ልጁን ከኋላው ጭኖ አህያውን ለሁለት ይጋልቡት ጀመር፡፡ ይህንን የተመለከቱ ሰዎች ‹‹ምን ዓይነት ጭካኔ ነው፣ አንድ አህያ ለሁለት የሚያስጋልባችሁ?›› አሏቸው፡፡ ግራ የተጋቡት አባትና ልጅ በመጨረሻ አህያውን ለሁለት ተሸክመውት ገበያ በመግባት የገበያተኛው መሳለቂያ ለመሆን በቅተዋል፡፡
የተረቱ ሞራል፣ ሁሉንም ማስደሰት እንደማይቻል ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሁሉንም የሚያስማማ መፍትሄ ባይገኝም ቅሉ ለትችቱ መፍትሄ ለመስጠት ባደረጉት መፍጨርጨር አባት እና ልጅም በፈረቃ ጋልበዋል፣ አህያውም አርፏል፡፡ የሚቀበሉትን ትችት ማወቅ እና አለማወቅ፣ ብሎም ለትችቱ ሁነኛውን መፍትሄ መፍጠር የተተቺው ድርሻ ቢሆንም ‹ትችት› ግን የማይቀር እና ሊቀር የማይገባው ነው፡፡
አሁን የራሳችንን ትችት ባሕል ወደመተቸት እናልፋለን፤ የትችት ባሕላችንን ከመተቸታችን በፊት ግን ለቃሉ ትርጉም በማበጀት ብንጀምር መልካም ነው፡፡ ‹ትችት› የሚለው ቃል ከመነሻው አሉታዊነት እንዳለበት የሚከራከሩ አሉ፡፡ እነዚህ ተከራካሪዎች ‹ሂስ› የሚለው ቃል የተሻለ አስማሚ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በሁለቱ ቃላት መካከል ያለውን ልዩነት ማስታረቅ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ስላልሆነ – ሳይስማሙ እንዲኖሩ እንተዋቸውና ‹ትችት› በዚህ ጽሑፍ ውስጥ እንዲኖረው ስለሚፈለገው ትርጉም እንነጋገር፡፡
‹ትችት› በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ‹‹በሆነ ርዕሰ ጉዳይ፣ ሐሳብ፣ ፍልስፍና፣ ድርጊት ወይም የሥራ ውጤት ላይ የሚሰነዘር፣ በምክንያት ላይ የተመሰረተ የተቃርኖ ወይም የነቀፌታ አስተያየት ነው፡፡››
በአገራችን ለትችት የተነወሩ (አይነኬ) በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ ከነዚህ ጉዳዮች መካከል ለጠቅላላ የትችት ባሕላችን ጉብጠት ምሳሌ ይሆናሉ በሚል በጥንቃቄ የመረጥኳቸውን ጉዳዮች እያነሳሁ ለማቅናት እደረድራለሁ፡፡ ትችቴ ያልተስማማው የመልስ ምት ቢጽፍ በዞን ዘጠኝ ጦማር ላይ ለማስፈር ከወዲሁ ቃል እገባለሁ፡፡

እምነትን መተቸት
የብዙዎቹ ሃይማኖቶች መሠረት እምነት መሆኑ ይታወቃል፤ እምነት ደግሞ ብዙውን ጊዜ የሚቆመው በማስረጃ ሳይሆን በእምነት በራሱ ነው፡፡ የእምነት እና የሃይማኖትዋጋ ባልሰለጠኑ አገራት ከፍተኛ ነው፤ ይህንን የሚያሳዬ በተለያዩ ጥናቶች ሲኖሩ፥ እንደምሳሌም፣ ኢ-አማኒዎች በአውሮፓ አገራት እስከ 60 በመቶ ቢደርሱም ከሰሃራ በታች በሆኑ የአፍሪካ አገራት ግን ከ1 በመቶ በታች ናቸው፤ በኢትዮጵያም ያለው ሁኔታ ተመሳሳይ ነው፡፡ ይህ የእምነት ዋጋ፣ በትችት ባሕላችን ላይ ያሳደረው አሉታዊ ተጽዕኖ በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡ ቅዱስ መጽሐፍቶችን እና አምልኮተ ስርዓቶችን የማይመረመሩ፣ የማይገመገሙ እና የማይሻሩ ሆነው እንዲቀሩ በማድረጉ ዛሬም ድረስ በድሮ ጋሪ እየተጎተቱ ለመኖር የሚያስገድድ ሁኔታ እንዲፈጠር መንስኤ ሆኗል፡፡ ይህ ከትችት ባሕላችንጋ ምን ያገናኘዋል የሚሉ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን እምነት አጥባቂ የሆኑ አገራት ሕገመንግስታቸው ላይ የሚኖራቸው አመለካከት እና ቅዱስ መጽሐፍታቸው ላይ የሚኖራቸው አቋም እምብዛም እንደማይራራቅ ይሰማኛል፡፡
በኢትዮጵያ ከፍተኛ ድርሻ የያዙት ክርስትና (በተለይም ኦርቶዶክስ ተዋህዶ) እና እስልምናን ብንመለከታቸው ከሌላው ዓለም ትንሽ ለየት ያለ ገጽታ አላቸው፡፡ በአንዳንድ ሁኔታዎችም ከባሕሉ ጋር ተቀላቅለው፣ አንዳንድ ባሕላዊ ወጎች እንደሀይማኖቱ ቀኖና፣ አንዳንድ የሀይማኖት ስርዓቶችም እንደባሕሉ መሰረት ሆነው ቆመዋል፡፡ በውጤቱም ሁለቱንም መንካት የማይቻልበት ድባብ ፈጥሯል፡፡
እንደምሳሌ አንድ ጠቅሰን እንለፍ፡፡ ሕዝብ በሚበዛባቸው የመኖሪያ ስፍራዎች ቤተክርስትያኖች እና መስኪዶች ተመስርተዋል፡፡ ሁለቱም ተቋማት ከፍተኛ የሆነ ድምጽ በሌሊት ያወጣሉ፣የአምልኮ መዝሙር/መንዙማቸውን ካሴት ለማስተዋወቅ ሕዝብ በተሰበሰበበት ስፍራ በከፍተኛ ድምጽ እያስጮሁ ያስተዋውቃሉ… ይህ እውነት በሁሉም ሰው የሚታወቅ ገሀድ ቢሆንም እልባት ይደረግለት በሚል፣ ለመንግስት አቤቱታ የሚቀርብበት ፊርማ የሚያሰባስቡ ወገኖች ቢፈጠሩ ውጤቱ ምን የሚሆን ይመስላችኋል? ተቆርቋሪ ነን የሚሉትና የሚቃወሙት ወገኖች በምክንያት ማስረጃ ለመበላለጥ እና ለማሸነፍ የሚደራደሩ ወይስ ቤተ ሃይማኖቴ ተደፈረብኝ በሚል ጦርነት የሚካፈቱ?
ብሔር ነክ ትችቶች
ብሔር ነክ አስተያየቶችን መሰንዘር በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከነውርም የከፋ ነውርም እየሆነ መጥቷል፡፡ አንዱ በሌላው ላይ በአነጋገር ዘዬው (ሌላው ቀርቶ በአንድ ቋንቋ አሜሪካዊው በእንግሊዛዊው ወይም በተቃራኒው) መቀለድ የተለመደ ነው፡፡ ወደእኛ አገር ሲመጣ ግን ዘረኝነት፣ ጥላቻ እና ጭቆና የሚል ባጅ ይለጠፍበታል፡፡ ቀልድ እንዲህ የሚያስፈርጅ ከሆነ መሠረታዊ የሆነ ትችት ምን ሊያስከትል እንደሚችል ማሰብ አስፈላጊ ይሆናል፡፡
‹‹የሃማሴን እና አጎራባች ነዋሪዎች/ተወላጆች አንበጣ (‹‹ክረምት አግቢ››) ይመገባሉ፤›› ብሎ የሆነውን ሆነ ቢል በማሕበራዊ የስነምግባር ሕግ የሚያስቀስፍ ወንጀል ነው፡፡ ከወዲያኛውም ሆነ ከተናጋሪው ወገን እነዚህን እንስሳት መብላት ምንድን ነው ጥፋቱ? ወይም እነዚህን መብላቱ እንዲህ ዓይነት ችግር ያስከስታል እያሉ ለትችቱ መመከቻም ሆነ ትችቱን ለማቅረቢያ ምክንያት መደርደርን ከግምት ውስጥ የሚያስገባ ማግኘት ዘበት ነው፡፡ ለሚበሉት አለመብላቱ እንደሚያስገርም ሁሉ ለማይበሉት ደግሞ ያስፀይፋል፤ በመጨረሻም የማይበለት በቁጥር ስለሚበዙ ነገሩንም ንግግሩንም የማነወር አቅም ያካብታሉ፡፡በተመሳሳይ የዚህ አይነት የብሔር ነክ ትችቶች እና ተያያዥ ጉዳዬች ማንሳት ጉዳዬን ከሚፈጽሙት በላይ ዘረኛ እና ሃጥያተኛ ያደርጋል፡፡
ቤተ ፖለቲካን መተቸት
ከተቃዋሚ እስከ ገዢው ፓርቲ ድረስ ቤተ ፖለቲካን መተቸት ከመፈረጅ አንስቶ እስከ መፈጀት ድረስ የሚያደርስ ቅጣት ያስከትላል፡፡ የገዢው ፓርቲ በአንድ በኩል ሥራዬ፣ ፖሊሲዬ፣ አመራሮቼ፣ አስተዳደሬ፣አመራሬ ፍፁም ነው የሚመስል ክርክር ሲከራከር፣ ተቃዋሚዎች በእኩል ድምፅ ሥራህ፣ ፖሊሲህ፣ አመራሮችህ፣ አስተዳደርህ፣ አመራርህ ፍፁም የተሳሳተ ነው የሚመስል ምላሸ ያሰማሉ፡፡ የገዢው ፓርቲ ባሕርይ ከጥንት ነገሥታቶቻችን ሲወርድ ሲወራረድ የመጣ ነው፤ ንጉሥ አይሳሳትም፡፡ እንዲያው ገዢው ይሳሳታል ያሉት አምላክን ከተቃወሙት አይተናነሱም እና ቅጣት ይገባቸዋል፡፡ ይህንን የሚያውቅ ገዢውን አይተችም፡፡
ተቃዋሚዎችን ያየን እንደሆነም ተመሳሳይ ድራማ በግልባጭ እናያለን፡፡ ተቃዋሚዎች ለመቃወም ብቻ የተፈጠሩ እስከሚመስል ድረስ(ያሉበት የፖለቲካ ምህዳር ጥያቄ እንዳለ ሆኖ) አንድም የራሳቸውን ፖሊሲ ወይም የረባ የፖሊሲ ትንታኔ ሰርተው ሲያሳን አያስተዋልም፡፡ ነገር ግን በተቃራኒው ‹‹እሺ ገዢው ፓርቲ ከተሳሳተ ምንድን ነበር ማድረግ የነበረበት?›› ተብለው ቢጠየቁ ጠያቂያቸውን ጨዋ ከሆኑ‹‹ተቃዋሚዎችን መተቸት ትግሉን ይጎዳዋል›› በሚል በአብዛኛው ደሞ ‹‹አንተማ ወያኔ ነህ›› የሚል ፍረጃ ሊያከናንቡት ይችላሉ፡፡
ታሪክን መተቸት
ነገሥታቱ ዜጎቻቸውን የኔ የሆኑ እና የኔ ያልሆኑ በማለት ተከፋፍለዋቸው እንደሆነ መረጃ የለኝም፡፡ የዛሬ ኢትዮጵያውያን ግን ነገሥታቱን የኔ የሆኑ እና የኔ ያልሆኑ በማለት ሊከፋፈሏቸው ይሞክራሉ፡፡ በተከፋፈሉት መሠረትም ‹‹አፄ ዮሓንስማ ትክክል ነበሩ፣ ምኒልክ አበላሹት እንጂ… የለም አፄ ቴዎድሮስ ናቸው ያበላሹት፤›› እየተባባሉ የኔ ያሉትን ይቀባሉ፣ የኔ ያላሉትን ደግሞ ያራክሳሉ፡፡ የአገራችን ታሪክ ከነገሥታቱ ጋር የተሳሰረ በመሆኑ የአገሪቱን ታሪክም እንዲሁ በማጥላላትና በማወደስ አጣብቂኝ ውስጥ እንዲወድቅ ያደርጉታል፡፡
ችግሩ ያለው ትችቱ መሠረት ላይ ነው፡፡ የትችቱ መሰረት (አመክንዮ) ሥራ ወይም የሥራ ውጤት ሳይሆን የግል ዝንባሌ (ምርጫ)፣ ወይም የግል ጎሣ ሆኖ ተደጋግሞ ይስተዋላል፡፡ በሌላ በኩል የዘመኑን ሁኔታ እና የዘመኑን ልሂቃን ዕውቀት ከግንዛቤ ውስጥ ባላስገባ (ወይም በዚህ ዘመን መለኪያ) ታሪክን መገምገም የራሱ የሆነ ድክመት ያለበት ሲሆን፣ አንንዶቻችን ታሪካችንን እና ባለታሪኮቻችንን የምንተቸው በተሳሳተ መለኪያ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በታሪክ ረገድ በዚህ ወቅት ያለው ትልቁ ችግር ባብዛኛው በተሳሳተ መንገድ መተቸት ሲሆን፡፡ ለሚዛናዊው አተቻቸትም ቢሆን በምላሹ ለጦርነት የማይዘጋጁ ኢትዮጵያውያን ቁጥር አነስተኛ ነው፡፡
የታሪክ አባቶችን ስንዘክር/ስንወቅስ ግዴታ በፍፅምና መሆን አለበት የሚል መመሪያ የለም፡፡ የታሪክ ፋይዳው ለመማሪያ እንጂ ለመፈራረጂያ አይደለም በሚለው ከተስማማን፣ ለምሳሌ በአንድነት ጉዳይ ሊዘከሩ/ሊወቀሱ የሚገባቸው ካሉን በጉዳዩ ብቻ መዘከር/መውቀስ ብቻ ሲቻል፣ የዛሬ ሰው ለአንድነት በሚሰጠው ዋጋ መዝኖ ‹ያ ንጉሥ› ለአንድነት ስለሠራ/ስላልሠራ በሚል ንጉሡ በሕይወት ዘመኑ ተሳስቶ የማያውቅ/ትክክል ሆኖ የማያውቅ አድርጎ ታሪክን በተሳሳተ መንገድ በመጻፍ ሌላ የታሪክ ተጠያቂ ከመሆን አያድንም፡፡
ግለሰቦችን እና ክስተቶችን መተቸት
በግለሰቦች ጉዳይ የትችት ባሕላችን መጀመሪያ የውዳሴ ብቻ ነው፡፡ ቀጥሎ ደግሞ የርግማን ብቻ የማይሆንበት ዕድል የለም፡፡ ‹‹ቀድሞ ማመስገን ቆይቶ ለማማት አይመችም›› የሚለው አባባልም ያመሰገኑትን ሲያጠፋ መውቀስን ለማነወር የተፈጠረ ቃል ይመስላል፡፡ ፍፁም ሰው በሌለበት ዓለም ወይ ፈፅሞ ማመስገን ወይም ፈፅሞ መውቀስ ብቻ ናቸው አማራጮቹ፡፡
ፍፁም ቅዱስ የማድረግ እና የማርከስ ሥራ ባሕላችን ላይ በሰፊው እንደሚታይ ከላይ የተጠቀሰው አባባል አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በባሕላችን አንድን ግለሰብ በመልካም እና ተወዳጅነት ዘመኑ ስህተቱን የመንገር ልምድ የለም፤ ማወደስ ብቻ የበዛበት ቆይታ ይኖረውና አንድ ትልቅ ስህተት ሲሰራ የተወደደበት እና የተወደሰበት መልካም ሥራ ሁሉ ቀርቶ ርግማኑ ብቻ ይወራል፤ በዚህ ወቅት የሱን መልካም የሚጠቅስ ሰው ቢኖር ከማስረገም በተጨማሪ የእኩይ ስራው ተባባሪ የሆነ ያክል ሁሉ ሊቆጠር ይችላል፡፡
አቶ ልደቱ አያሌውንና ምርጫ 97ትን እንደ ምሳሌ መውሰድ እንችላለን፡፡ በተለይ በምርጫ 97 ተከስቶ የነበረውን የተቃዋሚ ጎራ በመክፈል ትልቁን ሚና እንደተጫወቱ የተነገረላቸው አቶ ልደቱ (በርግጥ በቅስቀሳው ወቅትም ትልቁን ሚና ተጫውተው ነበር፤) ከምርጫው በፊት ከአምልኮ ባልተናነሰ ተወድሰው፣ ከምርጫው በኋላ ደግሞ ከስይጣን ባልተናነሰ ተወግዘዋል፡፡ አትሌቶቻችን ብዙ ጊዜ ይህንን ተጋፍጠውታል፡፡ በአሁኑ ሰአት ቴዲ አፍሮን መተቸትም ቤተ ክርስትያን የማቃጠል ያህል እነደሚሆን አይተናል፡፡ሟች ጠ/ሚር መለስ ዜናዊን በአሁኑ ሰዓት መተቸት የሚያስቀስፍ ሃጥያት ሆኖ የተቆጠረ ሲሆን፣ በተቃዋሚዎች ሰፈር ደግሞ ማወደስ ሊያስነቅፍ ይችላል፡፡
የአመክኗዊ ትችት ዋጋችን (የAppeal to Popularity ጥገኝነት)
በክርክር ባሕላችን ውስጥ የተከራካሪው ብዛት፣ እና የደጋፊው ብዛት እንጂ የመከራከሪያ ነጥቡ ዋጋ አነስተኛ ነው፡፡ ምንም እንኳን ይህ ዓይነቱ ነገር በሌላውም ዓለምም ሊኖር የሚችል ቢሆንም በአገራችን የጎላ ነው ብሎ መሟገት ይቻላል፤ ለዚህ እንደምክንያት የማስቀምጠው የዘመናዊ ትምህርት ተዳራሽነት እና የክርክር ባሕላችን አለመዳበሩን ነው፡፡ የሆነ ሆኖ በአገራችን ትችት አሰጣጥ ልምድ መሰረት መከራከሪያ ነጥቡ (አመክንዮው ወይም the logical reasoning) ቢያመዝንም ብዙ የሐሳቡ ደጋፊ ከሌለ ተከራካሪው ተሸናፊ ነው፡፡ ተሸናፊነት ደግሞ በሐሳቡ ብቻ የሚያበቃ ሳይሆን (ምናልባትም እስከመገለል) የሚያደርስ ማሕበራዊ ቅጣት አለው፡፡
እንደውም አብዛኛውን ጊዜ ‹‹ድፍን የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያምንበትን ነገር ትክዳለህ/ጃለሽ እንዴ?›› የሚል ሙግት ሊገጥማችሁ ይችላል፡፡ ይህንን ዓይነቱን ጥርሰት የፈላስፋ ምሁራን Appeal to Popularity ይሉታል፡፡ ብዙሐኑ በነፈሰበት መንፈስ፡፡
በአገራችን፣ ሰዎች የሐሳብ ልዩነታቸውን እንደጥንካሬ በሚቆጥሩበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን የሆነ እምነት መከተል፣ ወይም የሆነ ሐሳብ መደገፍ ከሕይወት የመቀጠፍ አደጋ ይጋርጣል፡፡ ብዙሐኑ የሚደግፉትን መደገፍ ወይም መቃወም ትቶ የራስን አቋም መያዝ ቢያንስ በጥርጣሬ ዓይን ውስጥ ይጥላል፣ ሲከፋም ‹‹መሃል ሰፋሪ በሁለት ጥይት ይሞታል››… እንዲሉ ያደርጋል፡፡ አንድን ግለሰብ፣ ወይም ክስተት መተቸት የግለሰቡ ጠላት ወይም የክስተቱ ተቃዋሚ እንደሆነ እንጂ ለግለሰቡ መሻሻል ወይም ለክስተቱ ማጠናከሪያ የሚሆን ሐሳብ አዋጪ አድርጎ አያጽፍም፡፡

በጥቅሉ በባሕላችን ተቃራኒ ሐሳቦችን አቻችሎ የማየት እና የመረዳት ቅን ልቦና ይጎድላል፤የሥልጣኔ ዋና መንገዱም ይሄው ብቻ ስለሆነ ግን ትችት ለዘላለም ይኑር!!!

ለውድ የዞን ዘጠኝ አንባቢዎች

የዞን ዘጠኝ ጦማር በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ እንዳይነበብ እየታገደ ለአንባቢዎች ስንል አዳዲስ ጦማሮችን እየፈጠርን ስለቆየን፣ ይህ (የመጀመሪያው) ጦማራችን ላይ የቀድሞዎቹን ጽሑፎች እንጂ አዳዲሶቹን ማግኘት አትችሉም፡፡ አሁን፣ ከመንግስት ጋር ፉክክሩን ስላልቻልነው፣ የምትችሉ ሰዎች አማራጮችን እየተጠቀማችሁ የምትጎበኙት የመጨረሻ ጦማራችንን ሊንክ እዚህ ይኸውላችሁ፡፡

ሰለጠቅላይ ሚንስቴር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፦ ያልተባሉና ያልተነገሩ

በቀድሞ ተማሪያቸው
I.      መግቢያ፡-
የጠቅላይ ሚንስተር አቶ መለስ ዜናዊ ድንገተኛ ሞት ተከትሎ የአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ያልተጠበቀና ያልታሰበ ወደስልጣን መምጣት ብዙዎችን ያስገረመ ጉዳይ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ የዚች ሃገር  ጉዳይ  ያገባኛል ያሉ ብዙ ግለሰቦች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማሀበራት እና ሌሎችም የሳቸው ሹመት ለሃገሪቱ ጥሩ አጋጣሚ ሊሆን እንደሚችልና ምናልባትም ፈጣሪ ለዚች ሃገር ለውጥ ያስቀመጣቸው ሊሆኑ ሁሉ እንደሚችሉ ተስፋ አድርገውባቸዋል፡፡ እኔም ከነዚህ ወገኖች አንዱ ነኝ፡፡

ስለ ጠቅላይ ሚንስተር ኃይለማርያም ደሳለኝ በተለያዩ ድህረገጾችና ጋዜጦች ብዙ የተባሉና የተጻፉ ሲሆን አብዛኞቹ የሳቸውን በጎና ጥሩ ጎኖች የሚዳሰሱ ናቸው፡፡ ከዚህም መካከል ሰውየውን ጥሩ ሃይማኖተኛና፣ ፈርሀ እግዚአብሔር ያላቸው፣ የመልካም ስነምግባር ባለቤት፣ ቅንና ተንኮል የሌለባቸው፣ ጥሩ አስተማሪና አስተዳዳሪ የነበሩ፣ ቤተሰባቸውን የሚወዱና የሚያከብሩ፣ ሰውን የማይጎዱ፣ ምንም አይነት ሱስ የሌለባቸውና ሙስናን የሚጸየፉ ወዘተ… የሚሉ ናቸው፡፡ እኔም ከሞላ ጎደል በነዚህ የሰውየው ባህሪያቶች እና ገለጻዎች እስማማለሁ፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ሰሞኑን በፉርቹን ጋዜጣ እና  በቪኦኤ ራዲዮ ጣቢያ በአርባ ምንጭ  የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት (አሁን አርባ ምንጭ ዩንቨርስቲ) ሁለት የቀድሞ የስራ ባልደረቦቻቸው (መምህራን የነበሩት ዶክተር ዮሴፍና ዶክተር ስለሺ በቀለ) እና አንድ የቀድሞ ተማሪ (አቶ ኤርሚያስ) ስለዚሁ ጉዳይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ እነዚህም አስተያየቶች ስለ አቶ ኃይለማርያም ጠንካራና በጎ ጎኖች የሚያወሱ ሲሆኑ አሁንም የዚህ ፅሑፍ ጸሐፊ ከሞላ ጎደል በተሰጡት አስተያየቶች ይስማማባቸዋል፡፡
እንደማንኛውም ዜጋ እና የርሳቸው የቀድሞ ተማሪ በአቶ ኃይለማርያም ሹመት እኔም በበኩሌ ከመገረምም አልፌ ከተደሰቱና የለውጥ ጭላንጭል ከተያቸው ወገኖች ውስጥ አንዱ ነኝ፡፡ ከባለሙያነታቸውም፣ የአካደሚ ሰው ከመሆናቸው፣ በቅርብም ቢሆን በፖለቲካውና በመንግስት ስልጣን ከነበራቸው ተሳትፎ እና ልምድ እንዲሁም ከዳራቸው /Background/ አንጻር ይቺን ሃገር ሊመሩ፣ ሰላም እና ለውጥ ሊያመጡና ሊያሳድጉ ይችላሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ከዚህም አንጻር ይህንን ጹሑፍ በዚህ ሰዓት መጻፍ አልፈለኩም ነበር፡፡ ነገር ግን በምዕራቡ ዓለምም እንደተለመደው አንድ መሪ ወደስልጣን ሲመጣ ለዚያውም የዘጠና ሚሊዮን ህዝብ መሪ ቀርቶ እያንዳንዱ በጎና ደካማ ጎን ከልጅነት ጀምሮ አስተዳደጉና ገጠመኙ ባህሪና የሥራ ፀባ በአጠቃላይ የህይወት ታሪኩ በደንብ ተደርጎ እንደሚዳሰስና ትንተና እንደሚሰጥበት እናውቃለን፡፡
እኔም የዚህ ጽሑፍ ጻሐፊ አቶ ኃይለማርያምን ከ1985-1989 ዓ.ም ለአምስት አመታት ያህል በተማሪነት የማውቃቸው ስሆን ከላይ ከዘረዘርኳቸው በብዙ ሰዎች ከተባሉት በጎ ጎኖች ውጭ ያሉትን እና በተለያዩ ሚዲየዎች ብዙ ያልተነገሩትነና ያልተባሉትን ለመጻፍ እወዳለሁ፡፡

II.     የአቶ ኃይለማርያም ወደ አካዳሚክ ስልጣን አመጣጥ፡-
አቶ ኃይለማርያም የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በ1984 ዓ.ም ከፊላንድ ታምፒር /Tampere/ ዩኒቨርስቲ በውሃና አካባቢ (ሳኒተሪ) ምህንድስና /Water & Environmental (Sanitary) Engineering/ ይዘው እንደተመለሱ በወቅቱ በአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዲን በነበሩት እና በ1997 ዓ.ም ምርጫ ወቅት ደግሞ የኢዴፓ ሊቀመንበር እና የቅንጅት ፓርቲ ም/ሊቀመንበር በነበሩት በዶክተር አድማሱ ገበየሁ ረዳት ሬጅስትራር ሆነው ተሹመዋል፡፡
በዚያን ጊዜ የኢንስቲትዩቱ ሬጅስትራር የነበሩት የስታስቲክስ ምሩቅ የሆኑት አቶ የማነ ናቸው (አሁን በሕይወት የሉም)፡፡ እንደ አቶ ኃይለማርያም በተመሳሳይ ጊዜ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከእንግሊዝ ሀገር ይዘው የመጡት አቶ አባቡ ተክለማርያም (አሁን ዶክተርና በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ) እና አቶ ስለሺ በቀለ ( አሁን ዶክተርና አፍሪካ ህብረት ውስጥ የሚሰሩ) በምክትል ዲንነት እና በምርምርና ህትመት /Research & Publication/ አስተባባሪነት በቅደም ተከተል ተሹመዋል፡፡  ይህ ሹመት በወቅቱ ረዳት ሬጅስትራር ለነበሩት ለአቶ ኃይለማርያም ስላልተዋጠላቸው ቅሬታን ፈጥሮባቸዋል፡፡ አንድም በትምህርት ደረጃም ሆነ በሥራ ልምዳቸው /Seniority/ ከማይበልጧቸው የሚያንሰ ሹመት ማግኘታቸው ሲሆን ሌላው ደግሞ የብሔር አድልዎ ተደርጎብኛል በሚል ስሜት ነው፡፡ ዶክተር አድማሱ የሚፈልጋቸውንና የራሱን ብሔር ተወላጆች  (አማራ) ሲሾም እኔ ከደቡብ አካባቢ ስለሆኩ ጎደቶኞል በሚል ስሜት መሆኑ ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አቶ ኃይለማርያም ዶክተር አድማሱ ከኢንስቲትዩቱ የሚነሳበትን መላና ዘዴ ይፈልጉ ነበር፡፡ በኋላም በታህሳስ ወር 1985 ዓ.ም በወቅቱ የተ.መ.ድ ዋና ፀሐፊ የነበሩት ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሪ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ተከትሎ በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በተነሳው የተማሪዎች አመጽ ዶክተር አድማሱ አመጹን ደግፈሃል እና አበረታተሃል በሚል ምክንያት ከዲንነቱና ከሃላፊነቱ ተንስቷል፡፡ አመጹን ከማይደግፉ ተማሪዎች ኢንፎርሜሽን በመውሰድና ለደህነንትና ፖሊስ አካላት በማቀበል (ዶክተር አድማሱ ለአንድ ቀን ታስሮ ነበር) ዶ/ሩ ከቦታው እንዲነሳና እንዲባረር ያደረጉት አቶ ኃይለማርያም እና በወቅቱ የኢንስቲትዩቱ አስተዳደርና ፋይናንስ ኃላፊ የነበረ አንድ የህወሀት አባል ናቸው፡፡
በዶክተር አድማሱ ምትክ በወቅቱ ምክትል ዲን የነበሩት አቶ አባቡ ተጠባባቂ ዲን ሆነው  ሲሾሙ አቶ ሃለማርያም ደግሞ ምክትል ዲን ሆኑ፡፡አሁን የአቶ ኃይለማርያም  ዋናው የስልጣን ግልበጣ ሴራ ይጀምራል፡፡ አቶ አባቡ ለትምህርታዊ ወርክሾፕ ወደ እንግሊዝ ሃገር በሄዱበት ጊዜ አቶ ኃይለማርያም  በሰሜን ኦሞ ዞን እና በክልሉ ባለስልጣናትና ቁልፍ  የፖለቲካ ሰዎች በመታገዝ እሳቸው የአካባቢው ብሔር ተወላጅ እያሉ እንዴት የሌላ ብሔር (አማራ) ሰው ስልጣን ይይዛል ብለው ሎቢ /Lobby/ በማስደርግና በተደረገ ማግባባት ወ/ሮ ገነት ዘውዴ (በወቅቱ የትምህርት ሚኒስትር) አቶ አባቡን በማውረድ አቶ ኃይለማርያምን የኢንስቲትዩቱ ዲን ያደርጎቸዋል፡፡ ይህም የሆነው አቶ አባቡ በውጪ ሃገር በነበሩበት ጊዜ ሲሆን ወደ ኢንስቲትዩቱ ግቢም አንደተመለሱ ስብዕናቸውን በሚነካ መልኩ በአንድ ቀን ውስጥ በኃላፊነት ይዘውት የነበረውን መኪና እንዲያስረክቡና የዲኑን መኖሪያ ቤትም ለቀው እንዲወጡ በቀደሞ ምክትላቸው በአቶ ሃይለማርያም ታዘው ነበር፡፡ ይህም አቶ ሃይለማርያም ምን ያህል ሥልጣን እንደሚወዱና ለሥልጣን ጓጉተው እንደነበር ያሳያል፡፡
በነገራችን ላይ አቶ ሃይለማርያም ፖለቲከኛ ለመሆን ያሰቡትም፣ ግኝኙነትም የጀመሩት፣ ወደ ፖለቲካ ውስጥም የገቡት በዚሁ አጋጣሚ ነበር፡፡ ይህም ማለት ማለትም በኢንስቲትዩቱ ውስጥ ያለውን የስልጣን ፍትጊያ ለማሸነፍ እና ዲንም ለመሆን ከነበራቸው ፍላጎትና እሱንም በድል ለመወጣት ከደቡብ ፓርቲ (ደኢህዴን) ድጋፍ ለማግኘት ብለው ነበር፡፡ በተጨማሪም የዞኑና የክልል ፖለቲከኞች አቶ ኃይለማርያም የዲንነቱን ቦታ እንዲያገኙ በወቅቱ እጅግ ከፍተኛ ድጋፍ አድርገውላቸዋል፡፡ ስለዚህ አቶ ኃይለማርያምን ፖለቲካ ውስጥ ያስገባቸው ዋናው ምክንያት እና ዛሬ ለደረሱበትም ትልቅ ቦታ መነሻ የሆነው ያ የኢንስቲትዩቱ ዲን የመሆን ፍላጎታቸው ነበር ማለት ይቻላል፡፡
     
III. የአቶ ኃይለማርያም የአመራር መንፈስ
የኢንስቲትዩቱ ዲን ከሆኑ በኋላ ስልጣናቸውን በደንብ ለማደላደል የሚፈልጓቸውንና የሚቀርቧቸውን ሰዎች በተዋረድ ይሾሙም ነበር፡፡ አቶ ኃይለማርያም የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን አባል የሆኑበት  ቤተክርስቲያን ግን ከዋነኞቹ ወንጌላዊ አብያተክርስቲያናት ለየት ያለና በሦስቱ ስላሴዎች የማያምን የኢትዮጵያ ሃዋርያ (Apostolic) ቤተክርስቲን (በተለምዶ only Jesus የሚባሉት) ነው፡፡ እናም በወቅቱ ስልጣን ሲሰጡ የሃዋርያ ቤተክርስቲያን አማኝ ካለ ቅድሚያ ይሰጡና ያዳሉ ነበር፡፡ እርሳቸውም አብዛኛውን ጊዜ የሚያስተምሩት የ/Water supply & West Engineering /ኮርስ ሲሆን እኔም በእሳቸው ሁለት ኮርስ ተምሬአለሁ፡፡ በጣም ጎበዝና ጥሩ የአካደሚክ  ዕውቀት የነበራቸው ሰው እንደሆኑ ልመሰክርላቸው እወዳለሁ፡፡ ነገር ግን አንድ የማልክደው ሀቅ ቢኖር በአስተዳደጋቸው ይሁን፣ ከአሁን በፊት በደረሰባቸው ነገር ለሰሜን አካባቢ ሰው (በተለይ ለአማራ ብሔር ተወላጆች) ትንሽም ቢሆን ጥላቻ ነበራቸው፡፡ ምዕራባውያን የበታችነት ስሜት(ኢንፌሪየሪቲ ኮምፕሌክስ)  እሚሉት አይነት ነገር ይሰማቸው ነበር፡፡ ይህንንም በተለያየ አጋጣሚ ያንጸባርቁት ነበር፡፡ ንግግር በሚያደርጉበት ጊዜ የቀድሞ ገዢዎች፣ ሰሜነኞች፣ ጨቋኞች እያሉ የጨቆኝና የተጨቋኝ አይነት ክርክር /Argument/ ያበዙ ነበር፡፡ በተጨማሪም በአስተዳደራቸው ጊዜም ቢሆን የተወሰነ አምባገነንነት ይታይባቸው ነበር፡፡ ሌላው ደግሞ በኢንስቲትዩቱ ባህል መሰረት  በየአመቱ ከ1-3ኛ ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ለረዳት አስተማሪነት ይቀጠራሉ፡፡ አቶ ኃይለማርያም ዲን ከሆኑ በኋላ ግን መቀጠር ያለበት እሳቸው ከሚፈልጉት ብሔር ውጪ ከሆነ በተለያየ ዘዴ እንዳይቀጠሩ ያደርጉ ነበር፡፡  በዚህ ሁኔታ ብዙ እዛው ቀርተው ማስተማር የነበረባቸውና ዛሬ ትልቅ ቦታ የደረሱ የቀድሞ ተማሪዎች ምስክር ናቸው፡፡ ይህም ምን ያህል አቶ ሃይለማርያም እርሳቸው ጨቋኝ ነበሩ ከሚሏቸው ብሄሮች ጋር ችግር እንደነበረባቸው ያሳያል፡፡
በተጨማሪም  አቶ ኃይለማርያም ዲን በነበሩበት ወቅት መታየትም የሚፈልጉ ሰው ነበሩ፡፡ በተቻላቸው መጠን ዜና ሊሆን የሚችል ነገር እየሰሩ በተለያየ አጋጣሚ ስማቸውንና አርባምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትን በኢቲቪና በሬዲዮ እንዲታወቅ ያደርጉ ነበር፡፡ ይሄም በደቡብ ፓርቲና በመንግስት ባለሥልጣናት አይን ውስጥ እንዲገቡና ለፓርቲው ከፍተኛ ሃላፊነት እንዲመለመሉ አድርጓቸዋል፡፡ ከዚያም በኋላ ነው የደቡብ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው የተሸሙት እና የፓርቲውም ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑት፡፡
IV. አቶ ኃይለማርያም ያለፉባቸው ፈተናዎችና ያጋጠሟቸው ተግዳራቶች
አቶ ኃይለማርያም በህይወታቸው ፈጽሞ ሊረሱት የማይችሉትና ምናልባትም እግዚአብሔር ረድቷቸው የተወጡት፤ ያን ወቅት በብቃት ባያልፉ ኖሮ ይቅርና የቀድሞ የደቡብ ክልል ፕሬዝዳንት ከዚያም አልፎ የአሁኑ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊሆኑ ቀርቶ ከመምህርነት ሙያቸውና (ነገር ግን ዶክትሬታቸውን ሊይዚ ይችሉ ይሆን እንጂ) ከአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አይወጡም ነበር የሚያስብል አንድ ተግዳሮት ደርሶባቸው ነበር፡፡ እሱም በ1988 ዓ.ም ሁለተኛ ሴሚስተር መጀመሪያ አካባቢ በኢንስቲትዩቱ የተነሳው የተማሪዎች አመጽ ነው፡፡ ይህም አመጽ በዚያን ወቅት በነበረው የአቶ ሃይለማርያም  አስተዳደራዊና የኢንስቲትዩቱ አካዳሚካዊ ችግሮች ላይ ተንተርሶ የተቀሰቀሰ ሲሆን አቶ ኃይለማርያምን፣ ምክትላቸውን እና አስተዳዳርና ፋይናንስ ኃላፊውን ከስልጣን እንዲለቁ የሚጠይቅ ነበር፡፡
በወቅቱ ተማሪዎች በፖሊስ ተንገላተዋል፡፡ ከ20 የማያንሱ በተማሪ የተመረጡ መሪዎች ለ21 ቀን በአርባ ምንጭ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ እስርቤት ታስረዋል፡፡ አቶ ኃይለማርያም የዞኑን አስተዳዳሪና ፖሊስ ሃላፊ እያመጡ የተማሪ መሪዎችን አስፈራርተዋል፡፡ የተማሪዎቹን ህጋዊና አግባብ ያለውን ጥያቄን በማጣመም ተማሪዎቹ ምንም ዓይነት ችግር የለባቸውም፤ ችግራቸው ሌላ ብሔር (ወላይታ) አይገዛንም፤ ዲን አይሆንም ብለው ነው በማለት ተማሪውን ከአካባቢው ህበረተሰብ ጋር ለማጣላትና ለማጋጨት ሞክረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ተማሪው በረብሻው ምክንያት ግቢውን ለቆ ሲወጣ እንኳን የከተማው ህዝብ እንዳይተባብረው አድረገዋል፡፡ ተማሪው ከግቢው ወጥቶ ወደ አካባቢው ከሄደ ከአንድ ሳምንት በኋላ ትምህርት ሚኒስቴር በሚዲያ ጥሪ አድርጎ ተማሪዎቹ ተመልሰው ወደ ግቢ እንዲገቡ ከተደረገ በኋላ፤ ከትምህርት ሚኒስቴር ዶክተር ተክለሃይማኖትን (በዚያን ጊዜ ምክትል ትምህርት ሚኒስትር) መጥተው ተማሪውን አወያይተውና አረጋግተው ትምህርት እንዲጀመር ሲደርግ፣ የተማሪውን ጥያቄ ባልመለሰ መልኩ ምንም አይነት የኢንስቲትዩቱ ባለስልጣን አቶ ሃይለማርያምን ጨምሮ እርምጃ ሳይወሰድባቸው በስልጣን እንዲቆዩና እንዲቀጥሉ ተደርጓል፡፡ ስለዚህ የዛሬው ጠቅላይ ሚኒስትር ታላቅ ባለውለታ ምናልባትም ዶክተር ተክለሃይማኖት ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ወቅቱ ብዙ የዪነቨርስቲ ተማሪዎች ያምጹ የነበረበት ጊዜ ሲሆን ትምህርት ሚኒስቴር ከሞላ ጎደላ የተማሪዎቹን ጥያቄ ለመመለስ የየግቢውን ዲኖችና ፕሬዝዳንቶች ያነሳባት ጊዜ ነበር፡፡ ለምሳሌ ወ/ሮ ገነት ዘውዴ አዳማ ድረስ ሄደው በተማሪዎች ጥያቄ መሰረት የናዝሬት ቴክኒክ ኮሌጅ ዲንን በወቅቱ ከሃላፊነት አንስተዋል፡፡ አቶ ኃይለማርያም ግን ያን ማዕበል በዶክተር ተክለሃይማኖት እገዛና ትብብር አልፈዋል፡፡ ማን ያውቃል ፈጣሪ ይህን ትልቅ ቦታና ስልጣን ስላየላቸው ይሆን?
ከዚህ በተረፈ በተማሪዎች ረበሻ ወቅት አቶ ሃይለማርያም ከስልጣን እንዲወርዱ በጣም ሲጥርና ተማሪዎችን ሲያስተባብር የነበረ አንድ የተማሪዎች መሪ እንደነገረኝ ተማሪው ትምህርቱን ጨርሶ ተመርቆ ከወጣ በኋላ ውጪ አገር የትምህርት እድል ለማግኛት የድጋፍ ደብዳቤ /Recommendation Letter/ እንዲጽፉለት ሲጠይቃቸው ተማሪው ባደረገው ነገር ምንም ቂም ሳይዙና ቅር ሳይላቸው በደስታ ጥሩ የድጋፍ ደብዳቤ ጽፈውለት በዚያም መሰረት በውጪ ሃገር እስኮላር ሽፕ አግኝቶ 2ኛ ድግሪውን ተምሮ እንደመጣ አጫውቶኛል፡፡
V. ማጠቃለያ
ከዚያ በኃላ በነበሩ ጥቂት አመታት አቶ ኃይለማርያም በኢንስቲትዩቱ ውስጥ ያላቸውን የሥልጣን ማዕከል ያደላደሉበትና በመሀልም እሳቸውን ከአካዳሚክ ሀላፊነት ወደ ፖለቲከኛነት የሚወስዳቸውን ሽግግር የፈጸሙበት ወቅት ነበር፡፡ የተማሪዎቹም አመጽ ከተደረግ ከ3 ዓመት በኋላ አቶ ሃይለማርያምን ዛሬ ወደ ደረሱበትን ስልጣን ትልቅ ቦታ አንድ ብለው ወደጀመሩበት የስልጣን ጉዞ ወደ ደቡብ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ቢሮ ተሹመው ሄዱ፡፡ ከሐዋሳው ሹመት በኋላ የቆዩበት ሁኔታና ወደአዲስ አበባ ጠቅላይ ሚንስቴር ቢሮ እንዴት ሊመጡ እንደቻሉ እንደቻሉ ከዚያም አሁን እስከተሾሙበት ቁጥር አንድ የሀገሪቱ የሥልጣን እርከን እንዴት እንደደረሱ በዛም ያለፉባቸውን ሁኔታዎችና አጋጣሚዎች ደግሞ ሌላ እንደ እኔ ለማየትና ለመታዘብ እድሉ የገጠመው ሰው ከዚህ ይቀጥልበት፡፡
እስከዚያው ቸር ይግጠመን፡፡
ጠቅላይ ሚንስቴር ኃይለማርያም ደሳለኝ ኃይለማርያም የቀድሞ ተማሪ

 ጸሐፊውን ለማግኘት በዚህ civil.at.aait@gmail.com አድራሻ ይጠቀሙ፡፡  

ይቅርታ የሚገባው የኢትዮጵያ ሕዝብ!

እነሆ ኢትዮጵያ አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትሯን አግኝታለች፡፡ አንድ መሪ ሲሞት ያለምንም ጦርነት እና ገሀድ የወጣ ሽኩቻ ምክትሉ ሲታካው በአገራችን የታየው ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡ ይህ ግን የሚኩራሩበት ችሮታ ሳይሆን ሊታዘዙለት የሚገባ  ሕገ መንግስታዊ መርሕ ነው፡፡ መጪው መሪ ያለፈውን ዘመን ትንሽዋን ስኬት የማክበጃ ፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ባሕል ቀጭተው ወደ ተግባራዊ ለውጦች በመግባት ለውጡ የእውነት መሆኑን ለማሳየት ጊዜው አሁን ነው፡፡ የሆነ ሆኖ የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ ይህ አይደለም፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር ሕመም እና ሞት ተከትሎ የነበሩትን ዘገባዎች ይመለከታል፡፡
አቶ መለስ ዜናዊ መታመማቸው በወሬ ደረጃ መናፈስ ከጀመረ በኋላ ሚዲያዎቻችን በተቃራኒ ጽንፎች ሲወዘወዙ ከርመዋል፡፡ በመጀመሪያ ላይ ስለጉዳዩ የተጠየቁት የመንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮው አቶ ሽመልስ ከማል፥ ‹‹ወሬው የኢሳት ነው፤›› ብለው አጣጥለውት (ወይም ዋሽተው) ነበር፡፡ እኚህ የመንግስት ተጠሪ “የነበሩ” ሰው፣ ሕዝብ የመንግስት ጉዳዮችን የማወቅ ሕገመንግስታዊ መብቱን በመግፈፍ፣ አውቀው – በማን አለብኝነት፣ አሊያም በስህተት የተናገሩትን ተናግረዋል፤ ነገር ግን በጥቂት ቀናት ውስጥ አለቃቸው አቶ በረከት ስምኦን ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀለል ያለ ሕመም›› እንደገጠማቸው ተናግረዋል፡፡
ስለዚህ አቶ ሽመልስ ከማል ለሰሩት ስህተት (ወይም ለሕዝብ ላደረሱት የተሳሳተ መረጃ) የኢትዮጵያ ሕዝብን ይቅርታ መጠየቅ አለባቸው፡፡
ያንን ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሽግግር ምክር ቤት የአቶ መለስን ሞት አረጋግጫለሁ አለ፤ ቀጥሎም በግለሰብ ደረጃ ክርክሩ ቀጥሎ ከርሞ የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥንም በበኩሉ አቶ መለስ መሞታቸውን ምንጮቼ ነግረውኛል አለ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ የመንግስት ባለስልጣናት በየፊናው አቶ መለስ በመልካም ጤንነት ላይ ናቸው የሚል ምንም ዜና በየፊናው በመርጨት ሕዝቡን በጥርጣሬና ስጋት መስክ ውስጥ እንዲወዛገብ ፈረዱበት፡፡ከዚያም አልፎ ለእያንዳንዱ አሉባልታ ምላሽ አንሰጥም ሲሉም ተደመጡ፡፡
በሌላ በኩል የግል ፕሬስ ናቸው በሚል የመንግስት አፍ የሆኑትን ቴሌቪዥን እና ሬድዮኖችን በአማራጭነት እንዲተኩ ተስፋ የምንጥልባቸው ጋዜጦች የራሳቸውን መረጃ አወጡ፡፡ ‘ውስጥ አዋቂ’ ነኝ የሚለው ፎርቹን ‹‹መለስ ወደከተማ ተመለሱ›› በሚል ተሽሏቸው አዲስ አበባ መግባታቸውን ሲያትት፣ ሌላኛው ውስጥ አዋቂ ሪፖርተርም በበኩሉ፣ ‹‹መለስ ተሽሏቸው›› በሕመም ፈቃዳቸው መዝናናት ላይ መሆናቸውን እና አሜሪካን  አገር እንደሚገኙም ዘገበ፡፡ ትንሽ ቆየት ብሎም፣ አዲስ አድማስ ሁነኛ ባለስልጣን ነገሩኝ ብሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤተመንግስት ያለው መኖሪያቸው ውስጥ ሆነው ከአራት የቅርብ ሰዎች ጋር ስራ መጀመራቸውን – ሁሉም በፊት ገጾቻቸው ላይ አስነበቡ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞተዋል ተብሎ በዳያስፖራዎች በተነገረበት ጊዜ አለመሞታቸውን ማረጋገጫ አልተገኘም፡፡ ነገር ግን አገር ውስጥ ገብተዋል፣ እና ተሸሏቸዋል ሲባል የነበረው በሙሉ ውሸት አሊያም በትህትና ለመናገር የመረጥን እንደሆነ ደግሞ ስህተት እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ጉዳዩ አከራካሪ ቢሆንም አንዳንዶች ከመንግስት አካላት ሆነ ተብሎ የተነዛ የማዘናጊያ የሐሰት ወሬ እንደነበር ለመናገር ሞክረዋል፡፡ ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱን ስህተት እያጣሩ ሕዝብ ዘንድ ማድረስ የመገናኛ ብዙሐኑ ተቀዳሚ ተግባር እንደመሆኑ ላሰራጩት የተሳሳተ ዜና ተጠያቂ ከመሆን አይተርፉም፥ከዚህም በተጨማሪ ይህ አይነቱ ትልቅ ሞያዊ ግድፈት የመገናኛ ብዙሐኑንም ሆነ የጋዜጠኞቹን የወደፊት ተአማኒነት ጥያቄ ምልክት ውስጥ ይጥለዋል፡፡
ስለዚህ ፎርቹን(ምንም እንኳን በዚህ ሳምንት ዕትሙ በጉልህ መግለጽ ሲገባው አድበስብሶ ለማለፍ ቢሞክርም)፣ ሪፖርተር እና አዲስ አድማስ ጋዜጦች የተሳሳተ መረጃ ለሰጡት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያላቸውን አክብሮት በይቅርታ መግለፅ አለባቸው፡፡

የመለስ ሞት በኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ከተረጋገጠ በኋላ ያልተጠበቀ ነገር ተከሰተ፡፡ ሕዝቡ የደረሰበትን የፖለቲካዊ አመለካከት ልዩነት፣ የኢኮኖሚ በደል እና ሌሎችንም ከቁብ ሳይቆጥር እንደ ሰው ሐዘኑን አሳየ፡፡ በመሰረቱ የሕዝቡ ስሜት የሚነግረን አንድ ነገር ቢኖር የኢትዮጵያ ሕዝብ በአመለካከት ልዩነት እና በበደል ውስጥ ሆኖም ቢሆን የመሪዎቹን ክፉ እንደማይመኝ ነው፡፡ የሚያሳዝነው ነገር ግን የሕዝቡን ኢትዮጲያዊ የሐዘን ስሜት ተከትሎ የመንግስት ባለስልጣናትና መገናኛ ብዙሐን ስሜት የፕሮፓጋንዳ መጠቀሚያ ማድረጋቸው ነው፡፡
በዋነኝነት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮዎች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየተንቀሳቀሱ ያልተጨበጡ (አልፎ አልፎም የሟቹን ክብር የሚያዋርዱ ንግግሮችን ከጎዳና ተዳዳሪዎች ሳይቀር) እያተቀበሉ እና እያናፈሱ፣ አቶ መለስን ምንም እንከን የማይገኝላቸው ልዕለሰብዕ፣ ፓርቲያቸውን ደግሞ ሕዝባዊ ቅቡልነት ያለው ብቸኛ ፓርቲ እንደሆነ ለማስመስከር ሲጥሩ ከርመዋል፡፡
የተለያዩ የመንግስት ተቋማት ሰራተኞች እና በተለያዩ የገጠር አውራጃዎች የሚኖሩ ሰዎች በአለቆች እና ቀበሌ ሊቀመንበሮች በተጻፉ ደብዳቤዎች ቅስቀሳ ለቅሶ እየደገሱ እና ለቅሶ እየደረሱ በቴሌቪዥን እንዲተላለፉ ተደረገ፡፡ ይህም ከገዢው ፓርቲ ፕሮፓጋንዳነት ያለፈ ፋይዳ አልነበረውም፤ ከዚያም በላይ ያደረሰው ኢኮኖሚያዊ ብክነት(በቤላ ጽሁፍ በደንብ የሚወራበት ሃሳብ ቢሆንም) አልተሰላም፡፡ ይህ ሁኔታ የሚያስመሰክረው ነገር ቢኖር ባለስልጣናቱ ለአገሪቱ ኃብት አጠቃቀም ዙሪያ ምንም ዓይነት ኃላፊነት እንደማይሰማቸው ሆነው መገኘታቸውን  ነው፡፡
ስለዚህ የመንግስት መገናኛ ብዙሐን፣ ለቅሶ ድረሱ የሚል ደብዳቤ የጻፉ ኃላፊዎች እና ሊቀመንበሮች፣ ከሕግ አግባብ ውጪ የሁለት ሳምንት ብሔራዊ ሐዘን ያወጁ ባለስልጣናት እና ሌሎችም የኢትዮጵያ ሕዝብን በሚዲያ እንደሚደሰኩሩት የሚያከብሩት ከሆነ ንፁሕ ሐዘኑን ለፕሮፓጋንዳቸው ፍጆታ ማዋላቸውን አምነው ይቅርታ ይጠይቁ!!!

ቤተመንግስቱ ኃይለማርያምን የሚያሰራ ይሆን?

ነብዩ ኃይሉ
ላለፉት 21 አመታት የምኒሊክ ቤተመንግስት ለአንድና ለሁለት ቀን ግፋ ሲልም ለአንድ ሳምንት ካልሆነ ጌታውን አጥቷቸው አያውቅም፡፡ አቶ መለስ በግንቦት ወር በቡድን ስምንት ጉባኤ ከተካፈሉ በኋላ ግን ማንንም አምነው የማይርቁትን ቤተመንግስት በህመም ምክንያት ትተው ብራስልስ ከረሙ፡፡ ህመማቸው እና አማልክቱ ጨክነውም ዳግም ወደ ምኒሊክ ቤተ መንግስት በቁማቸው ሳይመለሱ ቀሩ፡፡ እናም ቤተመንግስቱ ላለፉት ሦስት ወራት ኦና ሆኗል፡፡

አገሪቱን ማን የት ተቀምጦ እንደሚመራት ብዙም ግልጽ ባይሆንም፣ ኃለማርያም ደሳለኝ በተጠባባቂነት አገሪቱን እየመሩ እንደሆነ ሲገለፅ ሰንብቷል፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ ባለፈው አርብ መስከረም 4 ተጀምሮ ቅዳሜ መስከረም 5 ቀን 2005 ዓ.ም የተጠናቀቀው የገዢው አብዮታዊ ፓርቲ ምክር ቤት ስብሰባ አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝን በሟቹ ሊቀመንበሩ ምትክ ቢያስቀምጥም፣ ሰውየው እስከወሩ ማገባደጃ ቃለ መሀላ ፈፅመው ወደ ቤተመንግስት አይገቡም፡፡(በዚህ ሳምንት መጨረሻም ይሆናል የሚልም ግምት አለ)  ሁኔታው ኢህአዴግ ኃይለማርያምን ቤተመንግስት ከማስገባቱ በፊት ማጠናቀቅ የፈለገው ስራ እንዳለ አመላካች ነው፡፡
ኢህአዴግ ከ21 ዓመት በኋላ ከህወሓት ውጪ የሆነን ግለሰብ ለፓርቲው ሊቀመንበርነት በመሾሙ በፓርቲው የውስጥ ፖለቲካዊ የኃይል አሰላለፍ ላይ ለውጥ መጥቷል ለማለት ያስችላል? የአቶ ኃይለማርያም ፖለቲካዊ ተክለ ስብዕናስ እንደ መሪ ውሳኔዎችን ለመስጠት የሚያስች ይሆን? ለእነዚህ ጥያቄዎች ቀጣዩ ፅሁፍ ምላሽ ለመስጠት ይሞክራል፡፡
የኢህአዴግ የኃይል አሰላለፍ ለውጥ አሳይቶ ይሆን?
ኢህአዴግ ላለፉት አመታት ከህወሓት ተፅእኖ ስር ተለይቶ አያውቅም፡፡ የአራት ፓርቲዎች ስብስብነቱም አፋዊ ከመሆን ያለፈ አልነበረም፡፡ ህወሓት ያቀደው፣ ህውሓት ያቦካውና የጋገረውን ተቀብሎ ከማስተጋባት ውጪ ህወሓትን የሚገዳደር አንድም አባል ድርጅት ያልነበረው ኢህአዴግ፣ ለህወሓት አንደኛ፣ ለብአዴን ሁለተኛ፣ ለኦህዴድ ሦስተኛ እንዲሁም ለደኢህዴን የአራተኛነት ደረጃ የሰጠ ውስጣዊ የኃይል አሰላለፍ ነበረው ተብሎ ሲታማ ከርሞአል፡፡
የህወሓትም ሆነ የኢህአዴግ ጭንቅላት ተደርገው የሚወሰዱት መለስ ዜናዊ ከሞቱ በኋላ ግን የኢህአዴግ ውስጣዊ የኃይል አሰላለፍ እንዲቀያየር የሚያስገድድ ሁኔታ የተ፡፡ ለፓርቲው ቅርብ የሆኑ ወገኖች እንደሚገልፁት ህወሓት በአቶ መለስ ላይ ከተገቢው በላይ በመተማመመን ተተኪ ሰው ባለማዘጋጀቱ በኢህአዴግ ውስጥ የነበረውን ተፅእኖ በቀላሉ ለማጣት ተገዷል፡፡ በከሰተ ይመስላል፡፡ብአዴን ውስጥ አዳዲስ ፊቶች በፊት እንዲመጡ ባይደረግም ቅሉ ፓርቲው ከአቶ መለስ በኋላ አለቅነቱ ለኔ ይገባኛል የሚል የተሳካ እንቅስቃሴ ማድረጉንም እነዚሁ ወገኖች ያስረዳሉ፡፡ ኦህዴዶች በስልጣን ሽኩቻ ላይ ብዙም አልተሳተፉም፤ ከብአዴን ጋር የነበራቸውን ዘመን ያስቆጠረ የመቀናቀን አዝማሚያ ላለማድረግ የተገደዱ ይመስላል፡፡ አሁን ከሞላ ጐደል ኢህአዴግ ውስጥ ብአዴን ጠንከር ያለ ባይሆንም መግባባት ለመፍጠር የሚያስችል የበላይነት ይዟል፡፡ ኢህአዴግ መንግስት እንዲመሰርት የሚያስችለውን ትልቁን የፓርላማ መቀመጫ የሚያዋጣው ኦህዴድ ሀገሪቱ ያላትን ሁለት ከፍተኛ የስልጣን ማዕረጐች ለማግኘት አለመቻሉ አስገራሚ ባይሆንም በፓርቲው ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመካከለኛ አመራር ላይ እየተጠናከረ ከመጣው በኢህአዴግ ውስጥ ስልጣን ይገባናል የሚል ጥያቄ አንፃር የኦህዴድ አመራሮች ፈተና ውስጥ መግባታቸው አይቀሬ ነው፡፡ ደኢህዴን አቶ ኃይለ ማርያምን ስላስመረጠ ብቻ በኢህአዴግ ውስጥ ያለውን ደረጃ በማሻሻል የበላይነቱን አረጋገጠ ለማለት ባይቻልም ተጠቃሚነቱን አረጋግጧል ለማለት ግን ያስደፍራል፡፡
ይህ በሲቪል አስተዳደር ላይ የተደረገ የአሰላለፍ ለውጥ ሁሉን አቀፍ እንደሆነ ተደርጐ ከተወሰደ እና የህወሓት የበላይነት እንዳበቃለት ከተቆጠረ ግን ስህተት ላይ መጣሉ አይቀርም፡፡ ይህ ስህተት የገዢውን አብዮታዊ ፓርቲ ትክክለኛ ማንነት ካለመረዳት ይመጣል፡፡ በተግባር እንደሚታየው ኢህአዴግ ፍፁማዊ አምባገነንነቱን ለማስጠበቅ የተለያዩ ክንፎችን ዘርግቷል፡፡ አንደኛው የሲቪል አስተዳደር ክንፍ ሲሆን ሁለተኛው ወታደራዊና የደህንነት ክፍል ሲሆን ሦስተኛው የፓርቲውን ኢኮኖሚያዊ የበላይነት የሚያሳየው የንግዱ ክንፍ ነው፡፡ እነዚህ ክንፎች አመጣጥ ነው በሁሉም የበላይነቱን ተቆናጠው የነበሩት ህውሓቶች የመለስን ሞት ተከትሎ ከሌሎቹ ኢህአዴጋውያ በበለጠ ስልጣን በማጣት ስሜት ዙሪያው ቢጨልምባቸውም ኢህአዴግ ግን አሁንም ከቁጥጥራቸው ውጪ አይደለም፡፡ በኢንዶውመንት ስም ባቁዋቋሟቸው የንግድ ድርጅቶች [ህውሓቶች] የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የመዘወር አቅም አላቸው፡፡ የህውሓቶች ዋስትና ይህ ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም በኢህአዴግ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ላይ ከፍተኛ ድርሻ ያለውንና ስርዓቱ እንደ አፈና መሳሪያነት የሚጠቀምበትን ወታደራዊና የደህንነት ኃይል በበላይነት መቆጣጠራቸው ለህወሓቶች በሲቪል አስተዳደሩ ያጡትን የኃይል ሚዛን ያስጠብቅላቸዋል፡፡
በቅርቡ ይፋ የተደረገው ወታደራዊ ሹመት ወትሮም በብሔር ስብጥር ፍትሀዊነት ማጣት የሚታማውን የሀገሪቱ የመከላከያ ሰራዊት የከፍተኛ መኮንንነት ስፍራዎች የህውሓት ሰዎች በበላይነት እንዲቆጣጠሩት ተጨማሪ ሀይል ሰጥቷቸዋል፡፡ ይህ እርምጃ ህውሓቶች ያለብዙ ፍትጊያ ሲቪል አስተዳደሩን እንዲለቁ የተሰጣቸው ማስተማመኛ መሆኑን ለመረዳት አይከብድም፡፡ በብሔር ስብጥሩ ከፍተኛ አለመመጣጠን የታየበት ወታደራዊ ሹመት ኃይለማርያም ቤተመንግስት ከመግባታቸው በፊት በጥድፊያ መደረጉ እና በትግራይ ክልል ብዙሀን መገናኛዎች እየተላለፈ ካለው “ሶስተኛውን የወያኔ እንቅስቃሴ እንጀምራለን” የሚል አንድምታ ካለው መልእክት ጋር ሲዳመር የኢህአዴግ የውስጥ ሽኩቻ ሀገሪቱን ለትርምስ እንዳይዳርጋት ያሰጋል፡፡  
ከዚህ በተጨማሪም አቶ ኃይለማርያም በሚያዋቅሩት ካቢኔ ውስጥም ሆነ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በአማካሪነት ደረጃ ለህውሃቶች ሁነኛ ቦታዎች እንደተዘጋጀላቸው ቃል መገባቱን ከታማኝ ምጮች የተገኙ መረጃዎች አመላክተዋል፡፡ ይህ ደግሞ ህውሓቶች ጠቅላይ ሚኒስትሩን በቅርብ ርቀት ለመቆጣጠር የሚያስችላቸው እንደሚሆን ይገመታል፡፡ እዚህ ጋር ሊነሳ የሚገባው ጥያቄ ኃይለማርያም ምን ያክል በዙሪያቸው ያለውን የኃይል ሚዛን ትግል አልፈው በራሳቸው ውሳኔ ሰጪነት መስራት ይችላሉ? የሚለው ነው፡፡
ኃይለማርያም እና ኢህአዴግ
አቶ ኃይለማርያም በኢህአዴግ ውስጥ የጐላ ደርሻ ካላቸው ግለሰቦች ተርታ የተሰለፉት ከሁለት አመት በፊት የኢህአዴግ ምክትል ሊቀመንበር እንዲሆኑ ሲመረጡ ነበር፡፡ ሰውየው ከአስተዳደር ጋር የተገናኙ ስራዎች ላይ ረጅም አመት የመስራት ልምድ ቢኖራቸውም ከፖለቲካ ተክለ ሰብዕናቸው ይልቅ (technocrat) ገራገር የቴክኒክ ሰውነታቸው ያመዝናል፡፡ ይህንን የሚያረጋግጠውም ከሁለት አመት በፊት በምክትል ጠ/ሚኒስትርነትና ውጪ ጉዳይ ሚኒስትርነት ሲሾሙ “ስራው ላይ ልምድ ስለሌለዎት ለመስራት አይቸገሩም ወይ?” ተብለው ሲጠየቁ የሰጡት ማላሽ “ከቅርብ አለቃዬ[ከአቶ መለስ] ምክር እየጠየኩ እሰራለሁ” ማለታቸው ነው፡፡ የያኔው ገራገር ፖለቲከኛ ኃይለማርያም ደሳለኝ ዛሬም ፖለቲካዊ ብስለት ያገኙ አይመስሉም፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ሞት ተከትሎ በሰጧቸው አስተያየቶች መለስን በምንም አይነት ሁኔታ መተካት እንደማይችሉ ጠቅሰው ሀገሪቱን “በጋራ” ለመምራት እንደሚጥሩ ተናግረዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ለአንድ ፖለቲከኛ አስፈላጊና ወሳኝ የሆነው በራስ የመተማመንና ራስን ተፎካካሪ አድርጐ የማቅረብ ብቃት ጨርሶ እንደሌላቸው ነው፡፡ ፖለቲካ፣ መተጋገዝ፣ መተባበርና መመካከርን የሚጠይቅ የጋራ ስራ ቢሆንም፣ ሁልጊዜም ቆራጥነትና በራስ የመተማመን ግላዊ ጥንካሬን የግድ ይላል፡፡
የኢትዮጵያ ህገመንግስት ስልጣንን ሁሉ አከማችቶ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሰጣል፡፡ በመሆኑም አቶ ኃይለማርያም ህገመንግስቱ ሳይሳሻሻል “በጋራ” አመራር ለመስጠት መዘጋጀታቸው የሚያዛልቅ የብልህ ውሳኔ አይመስልም፡፡ “በጋራ” የሚወስኑትም ከማን ጋር እንደሆነ ብዙም ግልጽ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ ከነበረው የወንጀልና የመብት ጥሰት ታሪክ እና አሁንም ሊወስዳቸው በሚችላቸው አደገኛ እርምጃዎች ፈጠነም ዘገየ በፍትህ ፊት የሚዳኝ ስርአት ከመሆኑ አንፃር አቶ ኃይለማርያም “በጋራ” ውሳኔ ለመስጠት መዘጋጀታቸው የኋላ ኋላ ጦስ ተቀባይ ሊያደርጋቸውም ይችላል፡፡ አምባገነንና ወንጀለኛ ስርዓትን መምራት የሚያስከፍለውን ዋጋ ሳያገናዝቡ “መለስ የጀመሩትን” እንደሚያስቀጥሉ ቃል መግባታቸው ከቀደመው የአቶ መለስ አገዛዝ ያልተሻለ አገዛዝ እንደሚኖራቸው አያጠያይቅም፡፡
የሦስተኛው አለም ፖለቲካ በአብዛኛው በጠንካራ አመራር (Bold leadership) ላይ የመመስረት ታሪክ እንደመያዙ፣ ኢህአዴግ ከጅምሩ በሴራ የታሸ ፖለቲካን ከማዘውተሩ እና የኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካዊ ውጥረት ላይ ያለ ከመሆኑ አንጻር የአቶ ኃይለማርያም ፖለቲካዊ ተክለ ስብዕና ፈተና ውስጥ መግባታቸውን ለመገንዘብ አያስቸግርም፡፡
የኃይለማርያም ፈተናዎች
ኢህአዴግ አቶ ኃይለማርያምን ወደ ፊት ያመጣበት ሂደት በፓርቲው የጋራ መግባባት ላይ የተመሰረተ ቢሆንም የኦህዴድ ተመጣጣኝ ቦታ አለማግኘት እንዲሁም የደህንነትና የወታደራዊ ስልጣኖች ተከማችተው ለህወሓት መሰጠታቸው ጊዜ ጠብቀው እንደሚፈነዱ ቦንቦች የሚቆጠሩ ናቸው፡፡
ኦህዴድ በአቶ ኃይለማርያም ካቢኔ የሚሰጠው ቦታ በአመራሮቹና በፓርቲው መካከለኛ አመራሮች መካከል እየተባባሰ ያለውን አለመግባባት ሊያረግበው የሚችል አይመስልም፡፡ በመሆኑም ኦህዴድ ከስድስት ወር በኋላ በሚደረገው የኢህአዴግ ጠቅላላ ጉባኤ ምን አይነት አቋም እንደሚወስድ ለመገመት አስቸጋሪ ነው፡፡ 
በኢትዮጵያ ህገመንግስት ለጠ/ሚኒስትሩ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥነት ስልጣንን ያጎናፅፋል፡፡ አቶ ኃይለማርያም ከመከላከያ ሰራዊቱ አዛዦች ጋር ቅርበት ያላቸው ያለመሆኑ፣ የህውሓት ከኢህአዴግ ኃላፊነት መራቅን ተከትሎ ፖለቲካዊ ውሳኔዎችን በወታደራዊና በደህንነት መዋቅር የመቃወም አዝማሚያ ሊከሰት የመቻሉ አጋጣሚ አይኖርም የማይቻል ነው፡፡      
አለም አቀፉ ማህበረሰብ የኃይለማርያምን ወደ ማማው መውጣት እንደ በጐ ጅማሮ መቁጠሩ የማይቀር ቢሆንም ሰውየው በቂ ዲፕሎማሲያዊ እውቀትና የዳበረ ልምድ ያላቸው ስላልሆኑ የአቶ መለስን ያክል የፋይናንስ ድጋፍ በማግኘት ስራቸው በመቆም ላይ ያሉትን የአባይ ግድብንና ሌሎች ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ለማስቀጠል መቸገራቸው የማይቀር ነው፡፡
ኢትዮጵያ ያለችበት የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ያልተረጋጋና በርስ በርስ ጦርነቶች እንዲሁም በተጐራባች ሀገሮች መሀከል በቋፍ ላይ ባሉ ግጭቶች የተወጠረ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥም ነፍጥ ያነገቱና በጐረቤት ሀገራት የሚደገፉ ቡድኖች የመኖራቸው ጉዳይ፣ የኢትዮጵያ ጦር ሱማሌ ውስጥ ከመገኘቱና ከኤርትራ ጋር ካለው ወታደራዊ ፍጥጫ ጋር ሲዳበል በየትኛው ወቅት ምን ሊከሰት እንደሚችል ለመተንበይ አስቸጋሪ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለው ከቁጥጥር ውጪ የሆነ የዋጋ ግሽበት እና ከፍተኛ የስራ አጥ ቁጥር፣ በአፈና እና በግድያ ያልበረደው የኢትዮጵያውያን የነፃነትና የመብት ጥያቄ እንዲሁም የኢህአዴግ መንግስት በሃይማኖት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት አባዜ ያስጀመረው የሙስሊሞች የተደራጀ ተቃውሞ ትክክለኛ ምላሽ የማያገኙ ከሆነ ሊያቀጣጥሉ የሚችሉት ስርአቱ በምንም አይነት መንገድ ሊወጣው የማይችለው ህዝባዊ ንቅናቄ ሊፈጥር እንደሚችል ለመገመት ነብይነት ግድ አይልም፡፡
ከላይ ከተብራሩት ተጨባጭ ፈተናዎች አንፃር የምኒሊክ ቤተመንግስት ለአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የምቾት ስፍራ ሊሆንላቸው የሚችል አይመስልም፡፡ 
ጸሐፊውን በዚህ አድራሻ Nebiyuhailu@gmail.com ማግኘት ይችላሉ ፡፡

እኛና ሶማሊያ


ከአምስት መቶ ዓመታት በፊት አሁን ሶማሊያ ተብላ የምትጠራውን ሀገር አብዛኛውን ግዛት ያስተዳድር የነበረው አሕመድ ግራኝ በሰሜን የሚያዋስኑት ባብዛኛው ክርስትያንያዊ ከሆኑ አስተዳደር ግዛቶች ላይ ያካሄደው አስከፊ ወረራ አሁን ኢትዮጵያ ተብላ በምትጠራው አገራችንና በጎረቤት አገር ሶማሊያ መካከል ጊዜ እየጠበቀ ለሚያገረሸው ጦር መማዘዝ እና ቁርሾ የመጀመርያው አድርገው ይወስዱታል አንዳንድ ተንታኞች፡፡ 
ሁለቱ አገሮች ዘመናዊ በሆነ ማዕከላዊ መንግስት መተዳደር ከጀመሩበትና ሶማሊያ ከቀኝ አገዛዝ ነፃ ከወጣችበት ጊዜ አንስቶ ቢያንስ ሁለት ጊዜ በይፋ ጦር ተማዘዋል፡፡ ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃት ጋር አብሮ ሶማሊያ ማዕከላዊ መንግስት ካጣች በኋላ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት ለደህንነቴ ስጋት እየፈጠሩ ነው ያላቸው ታጣቂዎች ላይ በተለያየ ወቅት ጥቃት ሲፈጽም ቆይቷል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የኢትዮጵያ ጦር ጥቃቱን የሚፈፅመው ድንበር አካባቢዎች ላይ ወይንም ድንበር አልፎ ከገባም ጥቃቱን ፈፅሞ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ነበር ለቆ የሚወጣው፡፡ ጥቅሙን የሚያስጠብቁ የጎሳ ሪዎችንም ያስታጥቃል በሚል የኢትዮጵያ መንግስትን ክስ የሚያቀርቡበትም ጥቂት አልነበሩም፡፡
እንደ ኢትዮጵያውያን ዘመን አቆጣጠር በሰኔ ወር 1998 ዓ.ም የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ሕብረት በሚል እራሱን የሚጠራ ቡድን የሶማሊያን ዋና ከተማ ሞቃዲሹንና አብዛኛውን የአገሪቱን ደቡባዊ ግዛቶች ተቆጣጠረ፡፡ እንደ ብዙዎች ዕይታ በዚያድ ባሬ የሚመራው መንግስት ወድቆ አገሪቷ መንግስት አልባ ከሆነች በኋላ ሶማሊያ ለመጀመሪያ ጊዜ አንፃራዊ ሰላም እና ሰፊ ግዛት የሚያስተዳድር መንግስት ያገኘችው ሕብረቱ ሞቃዲሹን በቁጥጥር ስር ሲያውል ነበር፡፡

ሕብረቱ በማዕከላዊ እና ደቡባዊ የሶማሊያ ግዛቶች ያገኘውን የበላይነት በሰሜን የሀገሪቱ ግዛቶች መድገም አልቻለም፡፡ ለዚህም ተጠያቂ ያደረገው በአካባቢው ታጣቂዎችን ትረዳለች ያላትን የኢትዮጵያን መንግስት ነበር፡፡ ይህንንም ተከትሎ ቅዱሳዊ ጦርነት (ጂሃድ) ኢትዮጵያ ላይ ማወጁን ሕብረቱ በይፋ አስታወቀ፡፡

ጦርነት የታወጀባት የኢትዮጵያ መንግስትም ይህ አደጋ ግልጽ እና በጊዜ መፍትሔ ሊሰጠው የሚገባ ነው ሲል ፓርላማውን ሞግቶ ‹‹ማንኛውን አስፈላጊ እርምጃ›› እንዲወስድ የአብላጫ ድምፅ ይሁኝታ አገኘ፡፡ በታህሳስ ወር 1999 ዓ.ም ከሕብረቱ ኃይሎች ጋር በሶማሊያ ግዛት ውስጥ ውጊያ እንደጀመረ የኢትዮጵያ መንግስት ይፋ አደረገ፡፡
ዓመት ከፈጀ ውጊያ በኋላ በኢትዮጵያ ወታደሮች የሚደገፈው የሶማሊያ ሽግግር መንግስት ሞቃዲሹን ተቆጣጠረ፡፡ በወቅቱ የኢፌደሪ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ውጊያው በጦርነት በተሞላው ሕይወታቸው ካዩት ውጊያዎች ሁሉ ከፍተኛ የሆነ አለመመጣጠን የጎላበት እንደነበር ተናግረው ነበር፡፡ ምን ያህል ኢትዮጵያውያን ሕይወታቸውን እንዳጡ ግን ለመናገር ኃላፊነት (ግዴታ) እንደሌለባቸው ለማስረዳትም ሞክረው ነበር፡፡
ጊዜ በገፋ ቁጥር እና የኢትዮጵያ ጦር ወደሶማሊያ ዘልቆ እንዲገባ ምክንያት የነበረው የሕብረቱ ኃይሎች የመጨረሻ ጠንካራ ይዞታ ከነበረው ከኪስማዩ ግዛት ተሸንፈው ከተባረሩ በኋላ ‹የኢትዮጵያ ጦር ሶማሊያን ለቆ የሚወጣው መቼ ነው?› የሚለው ጥያቄ በተደጋጋሚ መሰማት ጀምሮ የነበረ ቢሆንም ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል ግን ዓላማዬን ጨርሻለሁና ለቅቄ ልውጣ የሚል አዝማሚያ አልታየበትም ነበር፡፡ 
የሶማሊያ የሽግግር መንግስት ለሀገሪቱ ሰላም እና መረጋጋት ብቸኛ አማራጭ አድርገው ለሚያዩት ሶማሊያዊያንና ጉዳዩ ያገባናል ለሚሉ የውጭ ኃይሎች የኢትዮጵያ ጦር በሸሪፍ ሼክ አሕመድ የሚመራው የሽግግር መንግስት ሞቃዲሹን እንዲቆጣጠር በማገዙ ደስተኛ እንደነበሩ አያጠራጥርም፡፡ ነገር ግን ጦሩ በሶማሊያ የነበረውን ቆይታ ባራዘመ ቁጥር አብዛኛው ሶማሊያዊያን ቅሬታቸው እየበረታ ሄደ፡፡ እንደውም አንዳንድ አክራሪ (አክራሪ ያሰኛቸው ምን ይሆን? የኢትዮጵያ መንግስት…??) የሚባሉ ታጣቂ ቡድኖች ከሽግግር መንግስቱ ጋር ለመደራደር የኢትዮጵያ ጦር አገሪቱን ለቆ መውጣቱን እንደቅድመ ሁኔታ ማስቀመጥ ጀመሩ፡፡
በዚህ መሀል ነበር ተሸንፎ የተበታተነው ሕብረቱ ኃይል ከመካከለኛው ምስራቅ ጠንከር ያለ ‹የእንርዳህ› ጥሪ የቀረበለት፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በ1990ዎቹ መጀመሪያ የአገሪቷን አለመረጋጋት እና መንግስት አልባነት እንደሽፋን ተጠቅሞ እግሩን ወደ ሶማሊያ ማስገባት የሞከረው አል-ቃይዳ ሶማሊያዊያን ከመካከለኛው ምስራቅ መጤ አክራሪ የእስልምና አስተምህሮት ይልቅ ከባህላቸው ጋር የተዋሀደውን እስልምና በመምረጣቸው ሳይሳካለት ቀርቶ ነበር፡፡ ዓለም አቀፋዊ ጅሃድ ሶማሊያውያን ሕይወታቸውን ለመስጠት የሚፈቅዱለት ጉዳይ ሆኖ አላገኙትም ነበር፡፡ ከዓሥር ዓመት በኋላ ግን አል-ቃይዳ ጥሩ እድል ተፈጠረለት፡፡ ‹ከክርስቲያን አገር› የመጡ ወታደሮች ላይ ለመተባበር ለሶማሊያውያን ጥያቄ ሲያቀርብ እንደቀድሞ ላለመቀበል ምንም ምክንያት አልነበራቸውም – ሶማሊያዊያኑ፡፡
ታድያ የ1999ኙ የሶማሊያ ወረራ ከሁለት ዓመት ተልዕኮ ቆይታ በኋላ ተጠናቆ የኢትዮጵያ ጦር በጥር ወር 2001 ዓ.ም ወደ አገሩ ሲመለስ ሶማሊያ ውስጥ አል-ሸባብ ለሚባል ከአል-ቃይዳ ጋር ግንኙነት ላለው እስላማዊ አክራሪ ቡድን ማንሰራራት ምክንያት ሰጥቶ ነበር፡፡
ሶማሊያውያን ወጣቶችን (ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑ አባላቱ እድሜ ከ20 ዓመት በታች ነው፡፡ ‹አገራችንን ከክርስቲያኖች ወረራ እንከላከል› በሚል ስሱ (sensitive) መመልመያ መቀስቀስ የቻለው አል-ሸባብ የኢትዮጵያ ወታደሮች ሶማሊያን መልቀቃቸውን ተከትሎ ድሮም ቢሆን በቅጡ ያልተደራጀውን የሽግግር መንግስት ጦር በቀላሉ በማባረር በዛ ያሉ የአገሪቱን ግዛቶች በጁ አስገብቷል፡፡
የኢትዮጵያ ጦር ከመውጣቱ በፊት በመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ መሰረት ወደ ሶማሊያ የተሰማራው የአፍሪካ ሕብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል የሰላም ስምምነት አካል ያልሆነውን አል-ሸባብን ለመቆጣጠር አልቻለም ነበር፡፡
የአል-ሸባብን ማንሰራራት እና እያደር መጠናከር ተከትሎ፣ መጀመሪያ የኬንያ ጦር በስተደቡብ በኩል ‹ድንበር ጥሰው ዜጎቼን እያፈኑ› ያስቸገሩ ታጣቂዎችን ፍለጋ በሚል ምክንያት ከዚያም የኢትዮጵያ ጦር ‹የአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ኃይልን እንዲረዳ› ከኢጋድ አባል ሀገራት የቀረበለት ጥያቄን ተቀብሎ በሕዳር ወር 2004 ዓ.ም በይፋ ወደ ሲማሊያ ድጋሚ አመራ፡፡ ይህ ጦር አሁንም እዛው ያለ ሲሆን መቼ እንደሚመለስም በይፋ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡
የሶማሊያ መፍትሔ – ችግሩን በሚገባ መረዳት
ሶማሊያውያን 275 አባላት ያሉት ብሔራዊ ምክር ቤት መርጠዋል፡፡ ምክር ቤቱም ከማዕከላዊ መንግስቱ መውደቅ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ በሶማሊያ ምድር በተደረገ ምርጫ ሀሰን ሼክ መሐሙድን የአገሪቷ ፕሬዝዳንት አድርጎ መርጧል፡፡
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ትልቅ ወጣ ውረድ ያለው ኃላፊነት ነው የተሰጣቸው፡፡ ከሃያ ዓመታት በላይ የተረጋጋ ሰላም አግኝታ የማታውቀው ሶማያን ሰላም መስጠት ከኃላፊነታቸው ሁሉ የላቀው ነው፡፡ ይህንን ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ሁሉንም ሶማሊያውያን የሚያግባባ ሐሳብ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ሁሉንም ሶማሊያውያን ማለት አል-ሸባብንም ይጨምራል፡፡ ሶማሊያ ውሰጥ የተረጋጋ ሰላምን ለማምጣት የአል-ሸባብን መውደቅ እንደ ቅድመ ሁኔታ የሚያዩ ሁሉ ስህተት እየፈፀሙ ነው፡፡ ምን አልባት አል-ሸባብን ወግቶ ማሸነፍ እና ወታደራዊ ድርጅቱን ቅርፅ ማሳጣት ይቻል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ሁለት አደጋዎች ተከትለው የመምጣታቸው ዕድል ሰፊ ነው፡፡
አንደኛ፤ ተደራጅቶ በመዋጋት የተሸነፈው አል-ሸባብ የትግል ቅርፁን ቀይሮ ወደ ሰርጎ ገብ ጥቃት መጣልና ወደ ሰፊ አጥፍቶ ጠፊ ጥቃቶች ፊቱን ሊያዞር ይችላል፡፡ የሶማሊያ የመከላከያና ፖሊስ ኃይል ደግሞ እየተሸሎከሎከ ጥቃት የሚፈፅም ኃይልን ተከታትሎ ሊያድን የሚያስችል በቂ አቅም ስለሌላቸው የሰላም መፍትሔውን በዕጅጉ ሊያርቀው ይችላል፡፡
ሁለተኛ፤ ሶማሊያ ውስጥ እስካሁን እንዳየነው የአንድ ታጣቂ ኃይል መውደቅ በሌላ ታጣቂ ኃይል ይተካል፡፡
ስለዚህም ሶማሊያውያንን ወደ ብሔራዊ መግባባት ለማምጣት በሚደረገው ጥረት አል-ሸባብን ማካተት ምርጫ የሚኖረው ጉዳይ አይመስልም፡፡ ምን አልባት አል-ሸባብ እራሱ ወደ ድርድር አልመጣም ብሎ አሻፈረኝ ሊል እንደሚችል መገመት ከባድ አይሆንም፡፡ ይህንንም ለማሸነፍ ግን አማራጮች አሉ፤
በመጀመርያ የአል-ሸባብ ጠንካራ መመልመያ የሆኑትን የውጭ ኃይሎች በተለይም የኢትዮጵያ ወታደሮችን ወደ አገራቸው በመመለስ (በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ስር ያለው ኃይል ሲቀር) አል-ሸባብን የመመልመያ ምክንያት ማሳጣት ይቻላል፡፡ በዚህም ምክንያት እንደድሮ የመመልመል አቅም የማይኖረው አል-ሸባብ የተለሳለሰ አቋም ሊይዝ ይችላል፡፡
ሁለተኛውና ተያይዞ መሰራት ያለበት ለሶማሊያዊያን ወጣቶች ጠብ-መንጃ አንግቶ ከመዋጋት የተሻለ ምርጫ መስጠት ነው – የሶማሊያን መልሶ ግንባታ ቢያንስ ቢያንስ አንፃራዊ ሰላም ባሉባቸው ቦታዎች በማፋጠን፡፡ ይህ ደግሞ አሁን አደራጅቶ የያዘውን ወጣት ልብ ወደ ቀድሞ ለአል-ቃይዳ አስቸጋሪ ወደነበረው ሶማሊያዊ አስተሳሰብ በመመለስ አል-ሸባብን የኃይል መሰረት በማናጋት ያዳክመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሚና
አሁን ሶማያ ለደረሰችበት ተስፋ ሰጪ ደረጃ ኢትዮጵያውያን ወታደሮች ማንም ሊከፍለው ያልደፈረውን መስዕዋትነት ከፍለዋል፡፡ አሁን ተራው እግራችንን ወደ ሶማሊያ እንድንሰድ ከዳር ሆነው ያበረታቱን ምዕራባዊያን ነው፡፡ ከላይ የተጠቀሱትን መፍትሔዎች ለማስፈፀም ፍላጎቱ እንጂ አቅሙ የለንም (በተለይም መልሶ ግንባታውን በተመለከተ)፡፡

‹‹እስከ አሁን መስዕዋትነት የከፈልንበት የሶማሊያ ሰላም እና መረጋጋት ዋጋ እንዳያጣ እና አሁን የተገኘው ተስፋ በጥዋቱ እናዳይጨልም አጥብቀን እንፈልጋለን፤ ስለዚህም ለመሳርያ መግዣ ለማዋል የማትሰስትን የፈረጠመ የገንዘብ አቅማችሁን ተጠቅማችሁ ለሶማሊያ መልሶ ግንባታ ማዋል የሚገባችሁ ጊዜ አሁን ነው›› የሚል ኮስተር ያለ የውለታ ምላሽ ጥያቄ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትራችን እንጠብቃለን፡፡

የሳምንቱ ጋዜጣና መጽሔቶች ከሰኞ እስከ ሰኞ


ሰንደቅ ጋዜጣ
ሰንደቅ ጋዜጣ በዚህ ሳምንት አትሙ 2004 . ጉልህ ክስተቶች የሚል የፌት ገጽ ይዞ ወጥቶዋል፡፡የአመቱ ዋና ዋና ክስተቶች ናቸው የተባሉት መካከልም የደርግ ባለስልጣናት መፈታት፣ኢትዮጵያ ለአሜሪካ ሰው አልባ ጄቶች ማኮብኮቢያ መፍቀዱዋ፣አወዛጋቢው 70/30 የበጎድራጎት ድርጅቶች ህግ የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ መዘጋት እና የዳቦ ዋጋ ጭማሪ፣የአበራሽ ሃይላይ ጉዳይ እና የግብረሰዶማዊያኑ ስብሰባ በኢትዮጵያ ይገኙበታል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ዲያቆን ዳንኤል ክብረትን በእንግድነት ይዞ የመጣው ሰንደቅ ዳንኤልየሚያስጨንቀኝ ቀጣዩ ፓትሪያርክ ሳይሆን ቀጣይዋ ቤተክርስቲያን ናትማለቱን ጠቅሶዋል፡፡
አዲስጉዳይ መጽሔት
ባለፈው ሳምንት ለገበያ መብቃት ያልቻለችው አዲስ ጉዳይ መጽሔት በበኩልዋ የአመቱን አነጋጋሪ ጉዳይ ሞት በማድረግ በአመቱ በሞት የተለዩ ታላላቅ እና ታዋቂ ሰዎችን ይዛ ወጥታለች፡፡በዋና ዋና አምዶቹም
         የአዲስ ዓመት ገበያ
         ሞት የአመቱ አነጋጋሪ ጉዳይ
         መለስ ዜናዊ የአመቱ አብይ ጉዳይ
         2004 የኢትዮጵያ ፖለቲካ የተጠበቀው የቀረበት ያልተጠበቀው የመጣበት
         2004 ያልተቋጨው የህዝብ ብሶት (ከሊዝ አዋጅ እስከ ኑሮ ውድነት፣የሙስሊሙ ህብረተሰብ የመብት ጥያቄ) ሲሆኑ የተለመዱት ቋሚ አምደኞችም የተለያዩ ጽሁፎቻቸውን ይዘው ወጥዋል፡፡
አዲስ አድማስ
አዲስ አድማስ በቅዳሜ እትሙ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ተቀዛዝዋል በሚል ዜና የፊት ገጽ ዜና ይዞ የወጣ ሲሆን ዶር ነጋሶ ጊዳዳን በፓርቲው ጋዜጣ ፍኖተ ነጻነት መታገድ እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ አናግሮዋቸዋል፡፡አድማስ በተጨማሪም በፊት ገጽ ዜናው እና አህመዲን ጀማል /ቤቱን ይቅርታ ጠየቁ የሚል ዜና ይዞ ወጥቷል፡፡
የሙስሊም ማህበረሰብ ችግር መፍትሔ አፈላላጊ በተሰኘው ኮሚቴ ውስጥ ከሚገኙ 17 አባላት መካከል ስምንቱ በረመዳን ወቅት ከተከሰተው ግጭት ጋር ተያይዞ መታሰራቸውና መከሰሳቸው የሚታወቅ ሲሆን፤ ተከሳሾቹ ለእስልምና ጉዳዮች /ቤት የይቅርታ ደብዳቤ ማስገባታቸውን ምንጮች ጠቆሙ፡፡ የኮሚቴው አባላት ከምክር ቤቱ ጋር በነበራቸው ግጭት፤ የምክር ቤት ምርጫ ለረዥም ጊዜ ተቋርጦ መቆየቱን በመጥቀስ ምርጫ እንዲካሄድ መጠየቃቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ምርጫው እንደሚካሄድ ከተወሰነ በኋላ ምርጫ የት ይካሄድ በሚለው ጥያቄ አለመግባባት መፈጠሩ ይታወቃል፡፡ ውዝግቡ መፍትሄ ሳያገኝ በረመዳን ወቅት ወደ ግጭት እንደተሸጋገረ የሚታወስ ሲሆን፤ ከኮሚቴው አባላት መካከል ስምንቱ ታስረው ክስ እንደቀረበባቸው ታውቋል፡፡ ተከሳሾቹ የሠራነው ስራ ስህተት በመሆኑ እንደገና በመወያየት ወደተሻለና አዲስ አሠራር እንድንመጣ እንፈልጋለን በማለት ለም/ቤቱ ደብዳቤ እንዳስገቡ የገለፁት ምንጮች፤ የተከሰሱበት ክስ ቀርቶ በይቅርታ ሊፈቱ ይችላሉ በማለት ግምታቸውን ገልፀዋል፡፡ የመጽሔት አዘጋጅ የሆነውን አህመዲን ጀማልን ጨምሮ በእስር በሚገኙት ስምንት አባላት ፊርማ ደብዳቤው ለምክር ቤቱ እንደደረሰም ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል በቀረበባቸው ክስ /ቤት ለጥቅምት 2 ቀን 2005 . ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ብሏል አድማስ በዘገባው

አዲስ አድማስ ከዶ/ ነጋሶ ጋር ካደረገው ቃለ መጠይቁ በጥቂቱ
ጋዜጣችሁ አሁንም እንደታገደ ነው?
አዎ እንደታገደ ነው፡፡ ባለፈው አርብ ልዩ እትም ለማሳተም ሰዎች ልከን ክፍያ ለመፈፀም ስንል የብርሃንና ሠላም ማርኬቲንግ ሃላፊው ክፍያውን አልቀበልም አለ፡፡ ምክንያቱን ሲጠየቅ፤ በቁጥር 1 ልዩ እትማችሁ ያሳተማችሁት ነገር ቅሬታ ስላስነሳብንና የዚህን አይነት ጋዜጣ እንዴት ታወጣላችሁ ስለተባልን አናትምም ሲል መለሰ፡፡ ልዩ እትሙ የጠ/ሚኒስትሩን ሞት ተከትሎ የተፃፉ በርካታ ሃሳቦችን የያዘ ነበር፡፡ ከሃሳቦቹ መካከልምለፍርድ ሳይቀርቡ መሞታቸውየሚልና እኔ የፃፍኩትህገመንግስቱና /ሚኒስትሩየመሳሰሉ በርካታ በሳል ጽሑፎች አካትቷል፡፡
ሆኖም ግን ጋዜጣችሁን በተመለከተ በስልክ ቅሬታ ስለቀረበባችሁ፣ ማኔጅመንቱ ተወያይቶበት ጋዜጣው እንዳይታተም ወስነናል መባሉ ተነገረን፡፡ እኛም በማግስቱ ሃላፊ ለማነጋገር ሔድን፡፡ እኔ፣ አቶ ግርማ ሠይፉ እና አቶ አስራት ጣሴ ነበርን፡፡ ማርኬቲንግ ማናጀሩ ለኛም ያንኑ ደገመልን፡፡ ታዲያ ምን ይሻላል ብለን ስንጠይቀው ሃላፊዬን አነጋግሩ አለን፡፡ ዋናዋ ስላልነበረች ምክትሉ ቢሮ ገብተን ስናነጋግረው፣ ጋዜጣችን አይታተምም የተባለው ማርኬቲንግ ሃላፊው እንዳለው ሳይሆን በሌላ ምክንያት መሆኑን ሰማን፡፡እኛ አቅም የለንም ነው ያልነው፤ ለኦሮሚያ ክልል የትምህርት መጽሐፍትን ለማተም ጨረታ አሸንፈናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለብዙ ጊዜ ደንበኞች የሆኑ የተወሰኑ ጋዜጦች ስላሉ የእነሱን ብቻ እናትማለን እንጂ የናንተን ለማተም አቅም የለንም፡፡ ማኔጅመንቱ ተወያይቶ የደረሰበት ውሳኔ ይሄ ነው፤ እናንተ አዲስ ስለሆናችሁ የናንተን ላለማተም ወስነናልአለን፡፡ ይሄኔ በጣም ተናደድኩናበምን መስፈርት ነው የእኛን አናትምም ብላችሁ የሌሎችን የምታትሙት?” ብዬ ጠየቅሁት፡፡እነሱ የቆዩ ደንበኞች ስለሆኑ ነው፤ የፈለጋችሁትን ነገር አድርጉ፤ አናትምምብሎ ድርቅ አለብን፡፡ ሆኖም እኛ በደረሰን መረጃ መሠረት፤ እዚያ ማተምያ ቤት አንድ ሰው አለ፤ ጋዜጣው ሲመጣ ምን አይነት ይዘት እንዳለው ለደህንነቱ ሃላፊዎች ደውሎ የሚጠቁም፡፡ ከዛ ጉዳዩ የመንግስት ኮሙኒኬሽን /ቤት ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት አቶ ሽመልስ ከማል ጋር ይደርሳል፤ አቶ ሽመልስ ደግሞ ለም/ሥራ አስኪያጁ ደውሎ እንዳይታተም ያዛል፡፡ እንደዚያ ነው የሆነው፡፡ ይሄ ማለት ደግሞ ከዚህ በፊት እንደነበረው ዓይነት የአፈናና የዲሞክራሲ መብቶች እረገጣ ነው፡፡ በመንግስት ላይ ተቃዋሚ አስተያየትና ሃሳብ የሚሰነዝሩ ግለሰቦችንና የህትመት ውጤቶችን ልሳን መዝጋት ነው፡:
የጋዜጣችንን ሥርጭት 2500 ኮፒ ጀምረን ነበር 20ሺህ ኮፒ ያደረስነው፡፡ ግን ታገደ፡፡ ብርሃንና ሰላም አላትምም ሲለን እሱን ትተን ወደ ግል ማተምያ ድርጅቶች ሄደን ነበር፡፡ አንዳንዱ አቅም የለንም ይላል፤ ሌላው ደግሞ ለማተም ይቸግረናል ይለናል፡፡ ቦሌ ማተሚያ ሆራይዘን፣ ቅድስት ማርያም ማተምያ ቤቶች ሄደናል፤ ግን ለማሳተም አልቻልንም፡፡
ከጋዜጣውን መዘጋት ጋር ተያይዞ ፓርቲው ሰላማዊ ሠልፍ እንደሚጠራ ገልጿል፡፡ የሠልፍ ፈቃድ ባታገኙም በሌላ መንገድ በመጥራት እናካሂዳለን ብላችኋል፡፡ እንዴት ነው ያሰባችሁት?
በመጀመሪያ የምናደርገው ብርሃንና ሠላም ማተሚያ ድርጅት አላትምም ያለበትን ምክንያት በጽሑፍ እንዲገልጽልን ሲሆን ከዚያ በፊት ግን እንደገና አስቦበት እንዲያትምልን ደብዳቤ ልከናል፡፡ የመንግስትና የህዝብ ተቋም ስለሆነ መንግስትም ሃላፊነት አለበት፡፡ /ጠቅላይ ሚኒስትሩም በጉዳዩ ላይ እርምጃ እንዲወስዱ ደብዳቤ ጽፈናል፡፡ በተጨማሪ እኔ በራሴ የቦርዱ ሊቀመንበር / ብስራት ጋሻው ጠና ጋር ደውዬ ልነግራቸው ሞክሬ ነበር፤ ሆኖም አሁን እሳቸው የብአዴን ሃላፊ ስለሆኑ ባህርዳር ናቸው፡፡ ጉዳዩን አላውቀውም፤ አጣርቼ መልስ እሠጣለሁ ብለውኛል፡፡ ያንን እየጠበቅሁ ነው፡፡ ስለዚህ ዝም ብለን አንቀመጥም፡፡ ከዛ በኋላ ነው ሠላማዊ ሠልፉን የምንጠራው፡፡ የሚያስፈልገውን ሁሉ እርምጃ እንወስዳለን፡፡ የታገደውን ጋዜጣ ለማስጀመር እስከመጨረሻው እንታገላለን፡፡
አዲሱ /ሚኒስትር ቢሆኑ ብለው የሚያስቡት ወይም የሚመርጡት ሰው አለ?
ተመርጫለሁ የሚለው ኢህአዴግ ነው፤ ከዛ አንፃር የአገሪቱን ችግሮች ጠንቅቆ የሚያውቅና የሚፈታ ሰው ቢሾም ነው የሚሻለው፡፡ ለዚህ ደግሞ ብቃት አላቸው ብዬ የማስባቸውና ድሮ ከማውቃቸው መካከል … (ስልጣን ከለቀቅሁ 11 አመታት ሊሆነኝ ነው) አቶ ግርማ ብሩ ቢሆኑ ብዬ 1993 . ሃሳብ አቅርቤ ነበር፡፡ አሁን እድሜም ጨምሯል፤ ሆኖም እሱ ቢሆን ችሎታ አለው ብዬ አምናለሁ፡፡ ከህወሓት ብርሃኔ /ክርስቶስ ቢሆን እላለሁ እድሜው ባይገፋ ኖሮ ስዩም መስፍንም ጐበዝ ነው፡፡ ከብአዴን ደግሞ አቶ አዲሱ ለገሠ፡፡ በእርግጥ እነዚህ ሰዎች አርጅተዋል፤ መተካት አለባቸው፡፡ አዲሶቹን ወጣቶች ሊያደርጓቸው ይችሉ እንደሆነ አላውቅም፡፡ እኔ የምሻው ግን የስርአት ለውጥ መጥቶ ህዝቡ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ይመራኛል የሚለውን ቢመርጥ ነው፡፡
የእግርዎ የጤንነት ሁኔታ እንዴት ነው?
አሁን በጣም ጤነኛ ነኝ፡፡ የእግሬን ጉዳይ በተመለከተየስኳር በሽታ አለብኝ፡፡ በሰውነቴ ውስጥ የተከማቸ ኮሌስትሮል አለ፡፡ ለብዙ አመታት ደግሞ ሲጋራ አጨስ ነበር፤ እነዚህ ነገሮች የእግር የደም ስርን የመዝጋት ሁኔታ ፈጥረው ነበርበሁለት እግሮቼ ላይ፡ እረጅም መንገድ መሄድ አልችልም ነበር፡፡ ስለዚህ ሳልታከም ብቆይ ኖሮ አደገኛ ችግር ማስከተሉ አይቀርም ነበር፡፡ አሁን የተዘጋውን የደም ሥር ከፍተውልኛል፡፡ በሙሉ ጤንነት ላይ ነኝ፡ አንዳንድ ሚዲያዎች አጋነውት ነው እንጂ እግሬ መቆረጥ ደረጃ ላይ አልደረሰም፡፡
ዕንቁ መጽሔት
የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር የአቶ መለስ ዜናዊን ፎቶ በፊት ገጹ ይዞ የወጣው እንቁ መጽሔት እንደሌሎቹ ሁሉ የተለያዩ የአመቱን ክስተቶች እና የእንቁን እትሞችን ማጠቃለያ ይዛ ወጥታለች፡፡ዋና ዋና ጽሁፎቹም
         ሰላም ወይስ ሁከት ምርጫችን
         መለስ የጀመረው ህልም ህያው ይሁንበያሬድ ጥበቡ
         መለስ ዜናዊ እና ያላለቀው የኢትዮጵያ ዘመናዊነት ፕሮጄክት – በፕሮፌሰር መሳይ ከበደ
         የመለስ ሞት እንቆቅልሾች እና ምቹ ጊዜያትበፕሮፌሰር ቴወድሮስ ኪሮስ
አዲሱ ዓመትን አስመልክቶ በእንቁ ለተነሱ ጥያቄዎች የተሰጡ መልሶች
 1. ትዳር ሳይኖር ልጅ አይኖርም ስለዚህ ትዳር መቅደም አለበት እላለሁ / ሃይሉ ሻወል ከእውቀት ከስልጣን ከሃብት ከትዳር እና ከልጅ የቱን ያስቀድማሉ ተብሎ ከእንቁ ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት መልስ
 2. የትራፊክ አደጋ መጨመሩ መጥፎ ነው፡፡ሌላው የክቡር /ሚር መለስ ዜናዊ መሞት በጣም አስከፊ እና አስደንጋጭ ነው፡፡በርካታ መንገዶች ተሰርተዋል ይህ ደግሞ በጣም ጥሩ ነገር ነው፡፡ ዋና ሳጅን አሰፋ መዝገቡ ስለአለፈው ዓመት መጥፎ እና ጥሩ ጉዳዮች ከእንቁ ለተጠየቁት ጥያቄ የሰጡት መልስ
 3. ለአገሬ በአዲሱ ዓመት የምመኘው ያለ አንድ ጥይት ተኩስ ማንኛውም የመንግስት ለውጥ በሰላማዊ መልኩ እንካሄድ እና ዴምክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲከናወን ነው፡፡ ማንኛውም ሽግግር በዴሞክራሲያዊ መልክ የሚከናወን ከሆነ መጪው ትውልድ ቢያንስ ከዚህ የሚወርሰው እዳ አይኖርም፡፡ ደራሲ አያልነህ ሙላት በአዲሱ ዓመት በአገርዎ ምን ቢደረግ መልካም ይሆናል ይላሉ ለሚለው የእንቁ ጥያቄ የሰጡት መልስ
ሌሎችም
         የመጀመሪያዋ የሴት ጄኔራል ተሾሙ ሪፓርተር ጋዜጣ
         በአዲሱ ዓመት ሁላችንም ከባድ የቤት ስራ አለብን / ኤፍሬም ይስሃቅ የሃገር ሽማግሌዎች ህብረት ሊቀመንበር ለአዲስ ጉዳይ መጽሔት
         ከመንግስት ሆደ ሰፊነት ይጠበቃልአቶ ተመስገን ዘውዴ አንድነት ፓርቲ የውጪ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አባል ለአዲስ ጉዳይ መጽሔት
         ሼህ አላሙዲን ተመራቂዎች ተማሪዎች ባገኙት የስራ መስክ አገራቸውን እንዲያገለግሉ መከሩ   ሰንደቅ ጋዜጣ
ርዕሰ አንቀጾች
         በአዲስ ዓመት አዲስ መንግስትዕንቁ መጽሔት
         ፍቅሬ ፍቅሬ አይብዛ አዲስ ጉዳይ መጽሔት
         አዲሱ ዓመት ጉድለቶቻችንን የምንሞላበት ዓመት ይሁንልንሰንደቅ ጋዜጣ
         የሚታመን ውሸት ለመዋሸት ከፈለግህ፤ የማይታመን እውነት አትናገር” – የጃፓኖች አባባልእያንዳንዷ ሩዝ ላይ የሚ በላት ሰው ስም ተፅፏል!” – የህንዶች አባባል አዲስ አድማስ ጋዜጣ
         ጉዞአችን የመቀጠል ብቻ ሳይሆን የመጨመርም ይሁን ሪፓርተር ጋዜጣ

“አራማጅነት” በኢትዮጵያ


ኤዶም ካሣዬ የኢትዮጵያ አካባቢ ጋዜጠኞች ማሕበር አባል የሆነች ለአካባቢ ተቆርቋሪ ጋዜጠኛ (Environment Journalist) ነች፡፡ ምንም እንኳን በአጋጣሚ ያለችበት አካባቢ በቆሻሻ የተበከለ ቢሆንም እንኳን የወረቀት ቁርጥራጭ፣ የማስቲካ ልጣጭ፣ ያገለገለ ሶፍት ጨምሮ ምንም ዓይነት አገልግሎት የሰጠ ቁስ መንገድ ላይ አትጥልም፤ አብረዋት ያሉትንም እንዲጥሉ አትፈቅድም፡፡ በየቦታው የቆሻሻ ማስወገጃ ከረጢት (bin) ወይም ገንዳ በቀላሉ ስለማይገኝ በቦርሳዋ እንዲህ ዓይነቶቹን መወገድ ያለባቸው ኮተቶች ማጨቅ የተለመደ ጉዳይዋ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ የፋቀችውን የተንቀሳቃሽ ስልክ ካርድ እዚያው የገዛችበት ሱቅ ትታ ነው የምትወጣው፡፡ የላስቲክ ማሸጊያ ካላቸው ቁሳቁሶች ይልቅ የወረቀት ማሸጊያ ያላቸውን መግዛት ትመርጣለች፣ በጋዜጠኝነት ሙያዋ በተገኘው አጋጣሚ ስለ አካባቢ ነክ ጉዳዮች ትጽፋለች፣ አባል በሆነችበት የተፈጥሮን አድን ኢትዮጵያ ማኅበር አማካይነት በየዓመቱ ለችግኝ ተከላ ትሳተፋለች፣ የተተከሉት ችግኞች እንዲጸድቁ ከሚንከባከቡ የአካባቢ ሰዎች ጋር ትገናኛለች፡፡
በአካባቢ ጉዳዮች ብቻ ሳይሆን በሌሎችም የሕይወት መስኮች እንደ ኤዶም ጥልቅ ስሜት ያላቸው በርካታ ሰዎችን ከፍ ሲልም ማህበረሰቡንም እዚህ ደረጃ ለማድረስ ከሚያስፈልጉ ማህበረሰባዊ ጉዳዮች መሀከል አራማጅነት(Activism) በዋናነት ይጠቀሳል::
አገራችን፣ 80 በመቶ ሕዝቧ በዝናብ ውሃ ላይ ጥገኛ ከመሆኑ አንፃር የአካባቢ ጉዳይ ዋነኛ አጀንዳዋ ነው፤ ሆኖም በቁጥር የሚዘረዘሩ የአካባቢ ጉዳይ ‹አራማጆች› የሉባትም፣ ኢትዮጵያ ፈርጀ ብዙ የባሕል አብዮት እንደሚያስፈልጋት ብዙዎች አስተያየታቸውን ይሰነዝራሉ፣ ነገር ግን በተግባር እንቅስቃሴ አብዮቱን ለማራመድ የተዘጋጁ ሰዎች አይታዩም፡፡ ኢትዮጵያ እና መንግስቷ ከሰብአዊ መብት በደል ጋር በተደጋጋሚ ስማቸው ይነሳል፣ ነገር ግን ለሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ዓይን የሚገቡ አራማጆች የሉንም፡፡
“አራማጅነት” ምንድን ነው?
Activismን አንዳንዶች አራማጅነት፣ ሌሎች አቀንቃኝነት፣ አንዳንዶችም ተሟጋች እያሉ ይተረጉሙታል፡፡ እኛም በዚህ ጽሑፍ “አራማጅነት” የሚለውን ብንመርጥም ሌሎቹንም እንደየአገባቡ አስፈላጊነት ልንጠቀምበት እንችላለን፡፡ ሌላው አቀንቃኝነት በተለይ advocacyን ይወክላል የሚል ነገር ቢኖርም፣ በሁለቱም (activism and advocacy) ውስጥ ተመሳሳይ ሚናዎች ስለሚኖሩ በጥቅሉ አራማጅነት ያልነውን ተከትለን እንሄዳለን፡፡
አራማጅነት ቀጥተኛ የማሕበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ወይም አካባቢያዊ ለውጥ ለማምጣት የሚደረግ ጥረት ነው ሲል ዊክፔድያ ይበይነዋል፡፡ የዚህ ለውጥ ‹አራማጆችን› (activistsን) ደግሞ ለአንድ ጉዳይ ድጋፉን ወይም ተቃውሞውን በተግባር የሚያሳይ ሰው ነው ይለዋል፡፡ ‹አራማጅነት› በጉዳዩ ላይ ሕዝባዊ ንቃትን (awareness) ማስጨበጥ፣ ደብዳቤዎችን ለፖለቲከኞች እና ለጋዜጦች ከመጻፍ ጀምሮ እስከ ማስተባበር እና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ እስከማድረግ (የተወሰኑ ሸቀጦችን አለመግዛት፣ ሰልፍ መውጣት፣ የጎዳና ተቃውሞ፣ አድማ እና ሌሎችም) ድረስ የሚዘልቁ የተለያዩ መገለጫ ተግባራቶች ሊኖሩት ይችላል፡፡
አራማጆች ለምን?

አራማጆች የሚያስፈልጉባቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ፤ ዋነኛው የትኛውም ጠንካራ መንግስት ማኅበረሰቡ ውስጥ ፈጣን የአመለካከት ለውጥ ማምጣት ስለማይችል ነው፡፡ በአገራችንም ቢሆን የፀረ ኤችአይቪ፣ የትራፊክ ጽ/ቤት፣ የሴቶች ጉዳይ እና ሌሎችም ቢሮዎች ቢኖሩም ችግሮቹን መቆጣጠር ቀርቶ ለመቆጣጠር የቀረበ ሙከራ የተደረገበት ጊዜ አልታየም፡፡ ይህም የሚሆነው መንግስት የአስፈፃሚዎች አቅም ማነሱ፣ የአደረጃጀቱ ዴሞክራሲያዊነት ማነሱ፣ የትምህርት ፖሊሲው በማሕበራዊ ንቃት ዘርፍ ያነሰ ትኩረት መስጠቱ እና ሌሎችም ምክንያት ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ክፍተት የሚሸፍኑ አራማጆች እና አራማጅነት በሰፊው ይፈለጋሉ፤ በተለይም ለታዳጊ አገራት፡፡

ምን አይነት አራማጅነት?

‹‹አራማጅነት›› ማለት መንግስትን/ተቃዋሚዎችን መደገፍ ወይም መቃወምም አይደለም፡፡ ይልቁንም ለማኅበረሰቡ ጤናማ የአእምሮ እና የቁስ ዕድገት እሴት የሚጨምሩ ለውጦች እንዲመጡ፣ ለውጡን ማሕበረሰቡ በእውቀት መር አካሔድ እንዲያመጣው መሥራት ነው፡፡

በአገራችን ብዙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለሕዝቡ ለውጥ ለማምጣት፣ ዴሞክራሲ ለማስፈን፣ መልካም አስተዳደር ለመዘርጋት እና ወዘተ እየሰራን ነው ይላሉ፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች የራሳቸውን ግብ አስቀምጠው መንቀሳቀሳቸው ምንም ችግር ባይኖርበትም አገራዊ ለውጥ የሚመጣው ግን በፓርቲ መስራቾች እና በአባሎቻቸው ብቻ አይደለም፡፡ እውነተኛ ለውጥ የሚመጣው በፖለቲካ ፓርቲዎች መፈራረቅ ብቻ ሳይሆን (በእርግጥ ይህ ከተቻለ ተግባራዊ ትምህርቱ የሚናቅ አይደለም) ነገር ግን በሕዝባዊ አስተሳሰብ ለውጥ ነው፡፡
አራማጅነት በሌሎች አገራት

በሌላው ዓለም፣ በተለይም ያደጉ አገራት ውስጥ አራማጆች በማሕበራዊ ለውጥ አማጪነት ሁነኛ ሚና አላቸው፡፡ አሜሪካዊው ማርቲን ሉተር የጥቁሮች መብት በሀገረ አሜሪካ እንዲከበርዴዝሙን ቱቱ በደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ ላይ፣ ኬንያዊቷ ዋንጋሪ ማታይ የአካባቢ ጥበቃ እና የፖለቲካ መብት ተቆርቋሪ በመሆን ዓለም አቀፍ እውቅናን ለማትረፍ የበቁ እና በጉዳዩ ዙሪያ ሳይጠቀሱ የማይታለፉ ናቸው፡፡
“አራማጆች” እና “አራማጅነት” በኢትዮጵያ፤ ጥቂት ምሳሌዎች
(፩) አንድ ሰሞን፣ ጋሽ አበራ ሞላ በሚለው ስሙ ይበልጥ የሚታወቀው የክራሩ ኤክስፐርት ስለሺ ደምሴ በከተማ ንፅህና እና አረንጓዴነት ዙሪያ ከፍተኛ የአራማጅነት ሚና ተጫውቷል፡፡ በወቅቱ ባደረገው ቅስቀሳ መላውን የአዲስ አበባ ወጣት በማነሳሳት ለአጭር ጊዜም ቢሆን አዲስ አበባን ከቆሻሻ ገንዳነት ወደ አረንጓዴ መዝናኛነት የመለወጥ ተስፋ አሳይቷት ነበር፡፡ የጋሽ አበራ ሞላ ፕሮጀክት አሁንም የቀጠለ ቢሆንም የአራማጅነት ሚናው ግን የሞተ ይመስላል፤ ለዚህም ነው ቀድሞ እናየው የነበረውን ያህል ለውጥ አሁን ማየት ያልተቻለን፡፡
(፪) ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) መወለድ ምክንያት የሆኑት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ፕሮፌሰሩ በሰብአዊ መብቶች ጉዳይ አራማጅነት ከየትኛውም ኢትዮጵያዊ የተሻለ የሰሩ ሰው ናቸው፡፡ ይህ ሚናቸው ግን በምርጫ 97 የፓርቲ አባል ሁነው ከመጡ በኋላ የቀነሰ ሲሆን፣ ከዚያን ጊዜ ወዲህ በግለሰብ ደረጃ በአገር ውስጥ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ሆኖ የሚታይ ግለሰብ እምብዛም የለም፡፡
(፫) እስከመጨረሻው ዘልቆ የሆነ ውጤት ባያመጣም፣ በ1994 በአቶ ልደቱ አያሌው (ፓርቲ ኢዴፓ አስተባባሪነት) ‹‹ኢትዮጵያን የአሰብ ወደብ ባለቤት ለማድረግ›› በየከተማው ፊርማ የማሰባሰብ እና ሕዝባዊ ስብሰባዎችን እያደራጁ ንቃት ለማስጨበጥ ያደረጉት ሙከራ ፖለቲካዊ ተራማጅነት (political activism) ሊባል ይችላል፡፡
(፬) ታማኝ በየነ በሙያው አርቲስት ቢሆንም ኢሕአዴግ በአገዛዝ አፍላ ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በአንድ አቋሙ ይታወቃል፡፡ የዴሞክራሲያዊ እና ሰብአዊ መብቶች አራማጅ ተብሎ ሊጠራም ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ እርሱም ስደተኛ በመሆኑ መረጃ የሚሰጣቸው፣ ወይም የሚያቀነቅንላቸው ሰዎች ባመዛኙ በዴሞክራሲያዊ እና ሰብአዊ መብቶች ዙሪያ ለተሻለ ግንዛቤ የተሻለ ተግባራዊ አማራጭ ያላቸው ብቻ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን በአገር ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ባለመሆናቸው በኢትዮጵያ የሚያመጣው ለውጥ የሚጠበቀውን ያህል የጎላ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡
(፬) ዘውዱ ጌታቸው በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የፀረ ኤችአይቪ/ኤድስ እንቅስቃሴ ማሕበር (ተስፋ ጎህን) የመሰረተ ሰው ነው፡፡ ምንም እንኳን አሁን በጉዳዩ ላይ ለመስራት እንደአሸን የፈሉ በርካታ ማሕበራት ቢኖሩም፣ ዘውዱ ጌታቸው ማሕበሩን በመሰረተበት ሰዓት ማኅበረሳባችን ስለጉዳዩ የነበረው ግንዛቤ ለማውራት እስከመጠየፍ ይደርስ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ዘውዱ ጌታቸው እና ማሕበሩ የሰሩት ሥራ ሁሉንም ሰው ግንዛቤ ከማስጨበጥ ጀምሮ እስከ ተጠቂዎቹን ድጋፍ እና ሟቋቋም ድረስ ዘልቋል፡፡
(፭) ሳጅን አሰፋ መዝገቡ ‹‹በኢትዮጵያ አትንዱ›› የሚል ዓለም አቀፍ ባጅ ያሰጠንን የትራፊክ አደጋ አስከፊነት ግንዛቤ በማስጨበጥ ከመንግስት ተቀጣሪነታቸው ውጪ የሚሰሩት ሥራ እንደአራማጅነት የሚያስቆጥራቸው ነው፡፡
(፮) በግለሰብ ደረጃ ጎልተው የወጡ ግለሰቦች ባይኖሩም፣ በኢትዮጵያ ሴት ጠበቃዎች ማህበርም ሲሰራ የነበረው (ከጥብቅና መቆም በላይ) የማንቃት እንቅስቃሴው፣ ማሕበሩን ከአራማጅነት ተርታ ያሰልፈው ነበር፡፡
ሌሎችም ጥቂት ምሳሌዎች ልንጨምር ብንችልም ለ80 ሚሊዮን ሕዝብ ግን በስንት ጭንቅ ትውስ የሚሉ እና በጣት የሚቆጠሩ የዘርፍ አቀንቃኞች ብቻ አይበቁትም፡፡

የሌሉን
በአገራችን በጣም አስፈላጊ ሆነው ሳሉ ጭራሹኑ የተዘነጉ የሚመስሉም አሉ፡፡ ለምሳሌ፡-
 • የፀረ ሙስና አራማጆች የሉም፣
 • በትምህርት ጥራት ዙሪያ የሚሰሩ አራማጆች የሉም፣
 • በፕሬስ፣ በመደራጀት እና በጥቅሉ በሕገመንግስታዊ መብቶች መከበር ዙሪያ የሚሰሩ አራማጆች የሉም፣
 • ፀረ-እፅ (anti-drug) በተመለከተ፣
 • የፍትሐዊ የንግድ ስርዓት፣
 • የከተማ ንፅህናን በተመለከተ፣
 • የሴቶች መብትን በተመለከተ፣
 • በጎዳና ተዳዳሪነት እና ፀረ-ድህነት ላይ፣
 • የኢንተርኔት ነፃነትን በተመለከተ እና  
 • በሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ በቂ አራማጆች የሉንም፤ ይሁን እንጂ ችግሮቹ ስር የሰደዱ እና በመንግስት አቅም ብቻ የሚፈቱ አይደሉም፡፡
አራማጆች እና ውጤታቸው
በመግቢያችን ላይ የተጠቀሰችው ጋዜጠኛ የአካባቢ ተቆርቋሪነቷን በግለሰብ ደረጃ እየተገበረችው ቢሆንም በዙሪያዋ ያሉ ሰዎችን መጠነኛ ግንዛቤ ከማስጨበጥ የበለጠ ሕዝብ ጋር በመድረስ ለውጥ የምታመጣበትን ሥራ እየሰራች አይደለም፡፡ ስለዚህ እሷን አራማጅነት ደረጃ ላይ ማስቀመጥ ያስቸግራል፡፡ እየዘረዘርነው በመጣነው ማብራሪያ መሰረት እሷ የአካባቢ ጉዳይ አራማጆች ፍሬ ናት፤ በሆነ ጉዳይ አራማጅ/አቀንቃኝ/ተሟጋች የምንላቸው፣ ከራሳቸው አልፈው የማኅበረሰቡን አባላት ልክ እንደ ተጠቀሰችው ጋዜጠኛ ዓይነት በጉዳዩ ዙሪያ ተቆርቋሪነት እንዲያዳብሩ እና ተገቢውን ግንዛቤ እንዲጨብጡ ለማድረግ የሚሰሩትን ነው፡፡
እንዳለመታደል ሆኖ አገራችን እንኳን በዓለም ዙሪያ የሚጠቀሱ ቀርቶ በአገር ውስጥ እንኳን ከአንድ ጉዳይ ጋር አወዳጅተን የምናስታውሳቸው አራማጆችን አላፈራችም፡፡ ለዚህ ተጠያቂ በርካታ ምክንያቶች ይኖራሉ፤ አንደኛው የሲቪክ ማሕበራቱ አዋጅ ነው፡፡
ይህ አዋጅ በአራማጅነት ላይ ትልቅ ቡጢ ያሳርፋል፡፡ ግለሰቦች ለውጦች እንዲመጡ የአራማጅነት ሚናን እንዲወስዱ የፋይናንሻል አቅም ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን፣ የሲቪክ ማሕበራቱ በአገር ውስጥ ድጋፍ ካልተዳደሩ በቀር ይህንን ድጋፍ የማድረግ መብት የላቸውም – በተለይ በመብት ጉዳይ፡፡ ይህም፣ አገር በቀሎቹን የየሰብአዊ መብት ጉባኤን እና የሴት ጠበቃዎች ማሕበር ላይ ያደረሰው ማሸመድመድ ሳይጠቀስ አይታለፍም፡፡ መሰረታዊ ፍላጎቶቹ ያልተሟሉለትን ሕዝብ ሲቪክ ማሕበራትህን ራስህ አስተዳድር ማለት ለችግሩ ተባባሪ ከመሆን የተሻለ እርምጃ አይደለም፡፡
ሌላኛው እና ሳይጠቀስ የማይገባው ምክንያት፣ የግለሰቦች የደህንነት ስጋት ነው፡፡ ግለሰቦች በሚያራምዷቸው አስተሳሰቦች እና አመለካከቶች እየተመለመሉ የሹመኞች ጥርስ ውስጥ የሚገቡበት ስርዓት ውስጥ መሆናችን የማይካድ ነው፡፡ ይህ ድባብ ግለሰቦች ለውጥ ማምጣት በሚፈልጉበት እና በሚችሉበት መስክ ተሟግተው ከመጠመድ ይልቅ በጥላው ተሸፍነው ማለፍን ይመርጣሉ፡፡

ጠቅላላው ነባራዊ እውነታ ይህ ቢሆንም፣ ዕድሉን ለማግኘት እየታገሉ በተለያዩ ምክንያቶች ግባቸውን ያልመቱ በርካታ አራማጆች መኖራቸውን ግን መካድ አይቻልም፡፡ ይህ ጽሑፍ የዞን ዘጠኝ የ2005 የመጀመሪያው ጽሑፍ እንደመሆኑ፣ በዚሁ አጋጣሚ ዓመቱ በርካታ ግለሰቦች እና ተቋማት ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም ፖለቲካዊ ለውጥ ለማምጣት የሚሰሩበት ዓመት እንዲሆን መልካም ምኞታችንን እንገልፃለን፡፡

የ2004 ዓ.ም. የጊዜ መስመር (timeline)

ይህን ጽሑፍ ለማዘጋጀት ስናስብ የትኞቹ ጉዳዮች ጉልህ ስፍራ ይኖራቸዋል የሚለውን ለመምረጥ  ብዙ ዐሳብ በህሊናችን ተመላልሷል፡፡ በአጠቃላይ ግን አብዛኛውን ሰው የሚያስማሙ ክስተቶችን ለማካተት የሞከርን ሲሆን በተለመደው ሚዲያ ስርዓት በመንግስትም ሆነ ‘ነጻ’ ሚዲያዎች  ትኩረት የተነፈጋቸውንም ለማካተት ጥረት አድረገናል፡፡እንደአለመታደል ሆኖ አማራጭ ትርክትን የሚያቀርብ የሚዲያ ተቋም በማጣታችን ምክንያት እነዚህ ጉዳዮች በወቅቱ ተቀራራቢ ሽፋን አለማግኘታው ከግምት ውስጥ ይገባልን ዘንድ እንጠይቃለን፡፡
መስከረም

የጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች መታሰር
መስከረም 4 ቀን 2004 ዓ.ም የአንድነት ለፍትህ እና ለዲሞክራሲ ፓርቲ አመራር አባላት የሆኑት አንዱአለም አራጌ እና ናትናኤል መኮንን እንዲሁም በኢትዮጵያ የግል ፕሬስ ከተፈቀደ ጀምሮ የተለያዩ ጋዜጦችን በዋና አዘጋጅነት እና በኋላም በተለያዩ ብሎጎች ላይ ስለ ሰብአዊ መብት መንግስትን በሚሞግቱ ፅሁፎቹ የሚታወቀው እስክንድር ነጋ ከሌሎች ተጨማሪ ተከሳሾች ጋር በአሸባሪነት ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡
አስናቀች ወርቁ ከዚህ አለም በሞት ተለየች
ታዋቂዋ ድምጸዊት እና የመድረክ ሰው አስናቀች ወርቁ በአመቱ መጀመሪያ በሞት ካጣናቸው የጥበብ ሰዎች አንደዋ ነበረች፡፡ አስናቀች ለረዥም ጊዜ በህክምና ስትረዳ ቆይታ መስከረም ወር 2004 አም 76 አመትዋ ከዚህ አለም በሞት ተለይታለች፡፡ አስናቀች እንደእየሩሳሌም በተሰኘው ታዋቂ ዘፈንዋ እንዲሁም በቀድሞ ጊዜ በነበሩ የመድረክ ስራዎችዋ ትታወቃለች፡፡
የትግራይ ፖሊስ ኦርኬስትራ ቡድን አባላት ላይ የመኪና አደጋ ደረሰባቸው
መስከረም 15 ቀን 2004 ዓ.ም ከትግራይ ክልል ተነስተው ወደ ሱዳን ሲገዙ በነበሩት የትግራይ ፖሊስ ኦርኬስትራ ቡድን አባላት ጭኖ ይጓዝ የነበረ አውቶቢስ ላይ የመኪና አደጋ ደረሰ፡፡
የደርግ ባለሥልጣናት በይቅርታ ከዕስር ተፈቱ
መስከረም 23 ቀን 2004 ዓ.ም በፍርድ ቤት የተወሰነባቸው የሞት ፍርድ ግንቦት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ወደ ዕድሜ ልክ እስራት መቀየርን ተከትሎ 16 ያህል የሚሆኑ የደርግ ባለስልጣናት የጠየቁት ይቅርታ በመንግስት ተቀባይነት አግኝቶ ከ20 አመት የእስር ቤት ቆይታ በኃላ በነጻ ተለቀቁ፡፡
ኢትዮጲያ የኤሌክትሪክ ሃይል ወደውጭ መላክ ጀመረች
መስከረም 24 ቀን 2004 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጅቡቲ በመገኘት 35 ሜጋ ዋት ከኢትዮጲያ በኤክስፖርት መልክ ማስተላለፍ የጀመረውን ማስተላለፊያ ጣቢያ መርቀው ስራ አስጀመሩ፡፡ ማተላለፊያ ጣቢያው የተገነባው ኢትዮጲያና ጅቡቲ የኤሌክትሪክ ሃይል ለመገበያየት የ25 አመት ስምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ ነበር፡፡ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የመብራት መቋረጥ ተከስቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ጥቅም


መድረክ ግንባር ሆነ
ጥቅምት 2 ቀን 2004 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክሪያሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ከፓርቲዎች ህብረት ወደ ግንባርነት መሸጋገሩን አስታወቀ፡፡ ወደ ግንባርነት መሸጋገሩ የበለጠ የተጠናከረ ሰላማዊ እና ዴሞክሪያሲያዊ ትግል ለማካሄድ እንደሚረዳው ገልፆ ነበር – ግንባሩ፡፡ በወቅቱ ዶ/ር መራራ ጉዲና ወደ ግንባርነት የተሸጋገርነው ግንባርን በግንባር ለመግጠም ነው የምትል ንግግር ጣል አድርገው ነበር፡፡
ስዊድናውያኑ ጋዜጠኞች ታሰሩ
ጥቅምት 9 ቀን 2004 ዓ.ም መንግስት አሸባሪ ድርጅትን አግዛችኋል እንዲሁም የሀገሬን ድንበር በህገ-ወጥ መንገድ ጥሳችሁ ገብታችኋል በሚል ሁለት የሲዊድን ዜግነት ያላቸው ጋዜጠኞች ላይ የመሰረተው ክስ መታየት ጀመረ፡፡ ሁለቱም ጋዜጠኞች ከአሸባሪ ድርጅት ጋር በተያያዘ የተመሰረተባቸውን ክስ ጥፋተኛ አይደለንም ሲሉ በሁለተኛው የሀሪቱን ድንበር በህገ-ወጥ መንገድ ጥሶ በመግባት የተመሰረተባቸውን ክስ አምነዋል፡፡ ጋዜጠኞቹ በቁጥጥር ስር ሲውሉ ከኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባር ተዋጊዎች ጋር ነበሩም ተብሏል፡፡
የመምህራን ደሞዝ ጭማሪ እና አድማ
መምህራን የተደረገላቸውን የደሞዝ ጭማሪ ከንቀት የሚቆጠር እና የሞያውን ክብር ዝቅ ያደረገ ነው በማለት ተቃውሞ አሰሙ፡፡ መምህራኖቹ የደሞዝ ጭማሪውን ቢቃወሙም መንግስት እና “የመምህራን ማህበሩ” ጭማሪ ሳይሆን የእርከን ማሻሻያ ነው ብለው ያስተባበሉ ሲሆን መምህራኑ በበኩላቸው ከደሞዛቸው ለማህበሩ የሚቆረጠው ገንዘብ እንዲቆምና ማህበሩ እንደማይወክላቸው ተናግረው ነበር፡፡ ጥያቄው እስኪመለስ ድረስ በተለያዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ትምህርት ለተወሰነ ጊዜ ተቁዋርጦ የነበረ ሲሆን የመንግስት አካላት የተለያዩ ድርድሮች በማድረግ ትምህርት እነዲቀጥል ማድረግ ችለዋል፡፡

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች መልስ ሰጡ
በተመሳሳይ ቀን የቀድሞ የኢፌደሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በ2004 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው መስከረም 30 ቀን 2004 ዓ.ም በፕሬዝዳንት ግርማ ቀርቦ የነበረውን የመንግስት አመታዊ መረሃ-ግብር ላይ ከምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች መልስ ሰጡ፡፡ በአሸባሪነት ተጠርጥረው ስለተያዙት የፖለቲካ ፓርቲ አባላት እና ጋዜጠኞች ተጠይቀው – በቂ መረጃ እስኪያገኝ ነው እንጂ በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች በሽብርተኝነት ተግባር ላይ መሰማራታቸውን መንግስት ካወቀ እንደቆየ አሁንም መረጃ እየተሰባሰበባቸው ያሉ በሽብርተኝነት ላይ የተሰማሩ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር አባላት እንዳሉ በመጥቀስ መልሰዋል፡፡ ሁለቱን ስዊድናዊያን በሚመለከትም የሀገሪቱን ድንበር ጥሰው ከሽብርተኛ ቡድን ጋር ታጥቀው እንደተያዙ እና እንደማንኛውም ሽብርተኛ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እንደሚታይ ተናግረው ነበር፡፡ ‹‹የነጭም ደም ቀይ ነው፤ የጥቁርም ደም ቀይ ነው… ጋዜጠኞቹ የአሜሪካንን ድንበር ጥሰው ታጥቀው ቢገኙ ማንም የኔ ናቸው ሳይሆን አላውቃቸውም ነበር የሚለው›› ብለው ነበር፡፡
አቶ ያረጋል አይሸሹም ንብረታቸው ታገደ
ጥቅምት 9 ቀን 2004 ዓ.ም የቤንሻንጉል ጉምዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትን በፕሬዝዳንትነት ያገለገሉት አቶ ያረጋል አይሸሹም በሳቸውና በቤተሰቦቻቸው ስም የተመዘገበ ማንኛውም ንብረት እንዳይንቀሳቀስ ታገደ፡፡ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ትዕዛዙን ያስተላለፈው የስነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና አቃቤ ህግ ግለሰቡን በሙስና ወንጀል በመጠርጠር ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ነበር፡፡
የንግድ ሚኒስትሩ እና ሚኒስትር ዲኤታው ከስልጣናቸው ተነሱ
የንግድ ሚንስቴር ሚኒስትር አቶ አብዱራህማን ሼክ መሐመድ እና ሚኒስትር ዲኤታው አቶ አሕመድ ቱሳ ከስልጣናቸው ተነሱ፡፡ የስልጣን ሽረቱ የተካሄደው የዋጋ ግዥበትን ለመቆጣጠር ለአምስት ወር ቆይቶ ያለምንም ውጤት እንዲነሳ የተደረገው የዋጋ ተመን ውድቀት ጋር በተያያዘ ባሳዩት የብቃት ማነስ መሆኑ ተገልጾ ነበር፡፡
የአወሊያ ተማሪዎች አመጹ
ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይግባ እና ስልጣን ላይ ያለው መጅሊስ አይወክለንም፤ በምርጫ ይተካልን በሚል ሰላማዊ በሆነ መንገድ ጥያቄያቸውን ማሰማት ጀመሩ፡፡በዚህ በአወሊያ ተማሪዎች የታገዱ መምህራኖቻችን ይመለሱ ጥያቄ ተነሳው የሙስሊሞች ጥያቄም በመጠንም ሆነ በይዘት ሰፍቶ ለወራት ዘለቀ፡


ህዳር

የኔሰው ገብሬ ራሱን አቃጠለ
ኢትዮጵያዊው መምህር የኔሰው ገብሬ ፍትህ መልካም አስተዳደር እና ልማት የለም በሚል አርብ ህዳር 1 ቀን 2004 ዓ.ም አቃጠለ፡፡
ዳዊት ከበደ እና አቤ ቶኪቻው ከአገር ተሰደዱ፡፡
ህዳር 5 ቀን 2004 ዓ.ም ታዋቂው የፍትህ ጋዜጣ አምደኛ አቤ ቶኪቻው ህዳር 9 ቀን ደግሞ የአውራምባ ጋዜጣ ባለቤትና ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ከአገር ተሰደዱ፡፡ አበበ ቶላ ለ6 ወራት የደህንነት መስሪያ ቤት መታወቂያ የያዘ ሰው በተለያየ መንገድ ጫና እና ክትትል ሲያደርግበት መቆየቱን የገለጸ ሲሆን የዳዊትን መሰደድ ተከትሎ ደግሞ አውራምባ ታይምስ ጋዜጣም ተዘጋ፡፡
ኢትዮጲያ ወታደሮቿን ዳግም  ወደ ሱማሌ ላከች
ህዳር 15 ቀን 2004 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ በተደረገው የኢጋድ ጉባዔ ኢትዮጲያ ለአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ሃይል እገዛ ሚያደርግ ሃይል ወደ ሶማሊያ እንድትልክ አባል ሃገራት ተስማሙ፡፡ በስምምነቱ መሰረትም የኢትዮጲያ ወታደሮችዋን በድጋሚ ወደ ሶማሊያ ላከች፡፡


ታህሳስ
የሁለት ምርጫዎች ወግ መጸሃፍ ተመረቀ
ታህሳስ 10 ቀን 2004 ዓ.ም የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤትን በበላይነት የሚመሩት አቶ በረከት ስምኦን ‹‹የሁለት ምርጫዎች ወግ›› ሲሉ የሰየሙትን መጽሐፋቸውን ለንባብ አቀረቡ፡፡መጽሐፉ ለሽያጭ የቀረበው በ90.00 ብር  ሲሆን በሸራተን ሆቴል በተካሄደው ምርቃት ስነስርአት ላይ ሼህ አላሙዲን መጻሃፉን ባያነቡትም በጣም ጥሩ እንደሆነ ተናግረው ነበር፡፡፡
በብርጋዴር ጀነራል ከማል ገልቹ የሚመራው ኦነግ የመገንጠል አቅዋሙን እንደቀየረ ገለጸ
በብርጋዴር ጄነራል ከማል ገልቹ የሚመራው ኦነግ የመገንጠል ሃሳቡን ከፕሮግራሙ ላይ ማንሳቱን አሳወቀ፡፡ በሜኒሶታ ከተደረገው ልዩ ስብሰባ በሁዋላ ጄነራሉ እንደተናገሩት የሁሉንም ብሄሮች  መብቶች እና እኩልነትን ያረጋገጠች ኢትዮጲያን መመስረት እነደሚደግፉ ገልጸዋል፡፡በዚሁ መግለጫ ላይ ኦነግ ለኦሮሞ ህዝብ ነጸነት ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጲያውያን ነጸነትም እንደሚታገል አንዲሁ ተገልጹዋል፡፡


ጥር

የኤርታሌ ቱሪስቶች በታጣቂዎች ጥቃት ተፈፀመባቸው
ጥር 9 ቀን 2004 ዓ.ም በአፋር የኤርታሌን አካባቢ ለመጎብኘት በቦታው የነበሩ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች እና ኢትዮጲያዊያን አስጎብኚዋቻቸው ላይ ታጣቂዎች ጥቃት ፈጸሙ፡፡በጥቃቱም 5ቱን ጎብኚዎች ሲገደሉ 2ቱን በከፍተኛ ሁኔታ ቆስለው 2 ኢትዮጵያዊያን እና 2 የውጪ ዜጋ ጎብኚዎች ደግሞ ታፍነው ተወሰዱ፡፡ጥቃቱ የተፈፀመው ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ከሚዋሰኑበት ድንበር 25 ኪ.ሜ አካባቢ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት ለጥቃቱ ሽብርተኞችን እያሰለጠነ ወደ ኢትዮጵያ ይልካል ያለውን የኤርትራ መንግስት ተጠያቂ አድርጎ ነበር፡፡
የአፍሪካ ሕብረት ሕንፃ ተመረቀ
ጥር 18 ቀን 2004 ዓ.ም በቻይና መንግስት እርዳታ የተገነባው አዲሱ የአፍሪካ ህብረት ህንፃ ተመረቀ፡፡ በአዲሱ ህንፃ ቅጥር ጊቢ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ወቅት ምዕራባዊ አፍሪካዊት ሀገር ጋናን ይመሩ የነበሩት የክዋሜ ንክሩማ ማስታወሻ ሀውልት የቆመ ሲሆን በወቅቱ የኢትዮጵያ አቻቸው የቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ ሀውልት አለመሰራት ጥቂት የማይባሉ ኢትዮጵያንን አስከፍቶ ነበር፡፡
አወዛጋቢው የሊዝ አዋጅ ፀደቀ
ጥር 30 ቀን 2004 ዓ.ም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በአመቱ ለሁለተኛ ጊዜ የሕዝብ ተወካች ምክር ቤት ተገኝተው መንግስት ተግባራዊ እንዲሆን ያስፀደቀውን የመሬት ሊዝ አዋጅ በተመለከተ ማብራሪያ ሰጡ፡፡አዋጁ ከጸደቀ በኃላ በሰጡት በዚህ ማብራሪያ ላይ ስለ መንግስት ሌቦች እና የግለሰብ ሌቦች በመሬት ዙሪያ ያለውን ችግር እንዳባባሱት ተናገሩ፡፡


የካቲት

አንዱአለም ተደበደበ
የካቲት 7 ቀን 2004 ዓ.ም. አንዱአለም አራጌ በእስር ቤት ውስጥ ድብደባ ተፈፅሞበታል ሲል አንድነት ፓርቲ አስታውቀ፡፡ አንዱአለም በድብደባው ምክንያት ጭንቅላቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት ተዘግቦ የነበር ሲሆን የአንዱዋለም ጉዳዩን በሚገባ የሚያብራራ ጹሁፍ በፍትህ ጋዜጣ በኩል ለንባብ በቅቶ ነበር፡፡
ደራሲና ጋዜጠኛ ስብሃት ገብረ እግዚአብሔር አረፈ
የካቲት 12 ቀን 2004 ዓ.ም ደራሲ ስብሃት ገብረ እግዚአብሔር በህክምና ሲረዳ ቆይቶ  በተወለደ በ76 አመቱ ከዚህ አመት በሞት ተለየ፡፡ በትኩሳት፣ሌቱም አይነጋልኝ እና በአምስት ስድስት ሰባት መጸሃፍቶቹ የሚታወቀው ጋሽ ስብሃት አድናቂዎቹ እና ባልደረቦቹ በተገኙበት የቀብር ስነስርአቱ በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን ተፈጸመ፡፡
ደራሲና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ አረፉ
የካቲት 23 ቀን 2004 ዓ.ም ደራሲና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ፡፡ የ54 መጻህፍት ደራሲና ተርጓሚ የነበሩት አቶ ማሞ የ82 አመት ባለፀጋ እና የ6 ልጆች አባት ነበሩ፡፡ ቀብራቸውም የካቲት 24 ቀን 2004 ዓ.ም. በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡

የዩኒቲ ኮሌጁ ዶ/ር ፍስሐ ተሰደዱ
የካቲት 29 ቀን 2004 ዓ.ም የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ መስራችና ባለቤት የነበሩት ዶ/ር ፍሰሐ እሸቱ ከሀገር ተሰደዱ፡፡ ዶ/ር ፍስሐ ሀገር ለቀው ለመውጣት የተገደዱት ከአስር በላይ አዋጪ የሚሏቸውን የንግድ ሃሳቦች ወደ ተግባር ለውጦ ለሀገርን ለወገን ጥቅም እንዲሰጡ የነበራቸው ህልም በመንግስት ምክንያት እውን መሆን ስላልቻሉ መሆኑን ተናግረው ነበር፡፡ ሙሉ ሰአታቸውንም የኢትዮጲያ ብሔራዊ የሽሽግግር ጉባዔ Ethiopian National Transition Council (ENTC) ለማቋቋም እንደሚያውሉም ተናግረዋል፡፡


ጋቢት     
       
 የኢትዮጵያ ጦር የኤርትራ መንግሥት ላይ  የማጥቃት እርምጃ ወሰደ
መጋቢት 6 ቀን 2004 የኢትዮጵያ መንግስት የኤርትራ መንግስት እና “የተላላኪዎቹን” የጥፋት  ማዕከላትን ማውደሙን አስታወቀ፡፡በአፋር ክልል በጉብኝት ላይ የነበሩትን ቱሪስቶች ላይ መግደሉንና ማሰቃየቱን የሚል ሰበብን እንደመነሻ ምክንያት በመውሰድ  በሦስት ካምፖች ተሰባስቦ  የነበረውን የኤርትራ መንግስት ሀይል ላይ ወታደራዊ እርምጃን ወስዷል፡፡የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የኢንዶክትሬሽንና የሕዝብ ግንኙነት ማዕከል ኃላፊ ኮሎኔል ገብረ ኪዳን ገብረ ማርያም ለኢዜአ  እንደገለጹት ሠራዊቱ ማለዳ ላይ ባደረሰው ጥቃት በሦስት ካምፖች ተሰባስቦ  የነበረውን ኃይል ለማውደም ተችሏል። ኮሎኔሉ ዝርዝሩ ወደፊት ይፋ ይደረጋል ማለታቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘገባ በወቅቱ ቢያመለክትም ይህ የጊዜ መስመር እስከተዘጋጀበት ሰዓት ድረስ ያገኘነው መረጃ የለም፡፡
የወልድባ ገዳም እና የስኳር ልማት ፕሮጀክት
በዋልድባ ገዳምና በወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት መካከል  አለመግባባት ተፈጠረ፡፡የኢትዮጵያ ስኳር ልማት ኤጀንሲ ከያዛቸው የስኳር ማስፋፊያ  ፕሮጀክቶች አንዱ የሆነው የወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት ግድብ ግማሽ ክፍል የገዳሙ ክልል ውስጥ መገንባቱ ፣ በገዳሙ ያረፉ ቅዱሳን አፅም መነሳቱ  ፣በገዳማውያኑ የሚተዳደሩ ሦስተ አቢያተ ክርስቲያናት መነሳታቸው ክርክሩን ያስነሱ ሲሆን ችግሩን ለመፍታት መነኮሳቱ አዲስ አበባ ድረስ ደርሰው  በጠቅላይ ቤተ ክህነት እና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት የደረሰባቸው  አላግባብ ያለሆነ ማንጓጥና እንግልት ጉዳዩን የበለጠ አባብሶታል ተብሎዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ እና በሌላው አለም በሚገኙ ምእመናን አለም አቀፍ ተቃውሞሞ ደርሶበታል፡፡ መንግስት በአደባባይ ብዙ መግለጫዎችን በመስጠት ውይይቶች  ማካሄዱን ቢገልጹም በድብቅ ደግሞ መነኮሳቱን በማስፈራራት እና በማሰር እየታማ ጉዳዩ በእንጥልል እንደቆመ አለ፡፡
የዝቋላ ገዳም ቃጠሎ
ሊበን ዝቋላ ወረዳ አዱላላ ከተማ የሚገኘው የዝቋላ ደብረ ከዋክብት ጻድቁ አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ገዳም በሚገኝበት ተራራ  ላይ በመጋቢት 8 ቀን 2004 ዓ.ም ቀትር  የተነሣው የእሳት ቃጠሎ ሁለት ጋሻ መሬት የሚሸፍን ደን  አወድሞ በቁጥጥር ስር ዋሎዋል ፡፡ በእሳት አጥፊ አውሮፕላን ወይም ሄሊኮፕተር በሚረጭ ኬሚካል በመንግስት በኩል አለመመደቡ መንግስትን ቢያሳማውም ከአዲስ አበባ እና ሌሎች የአከባቢው ከተሞች የሚገኙ ነዋሪዎችና የፌዴራል ፖሊስ አባላት ባደረጉት ከፍተኛ ርብርብ ቃጠሎው  በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡
የአማራ ተወላጆች ከደቡብ ክልል ጉራ ፈርዳ መፈናቀል
1000 ያህል የአማራ ተወላጅ አባወራዎች ከደቡብ ክልል ቤንች ማጂ ዞን ጉራ ፈርዳ ወረዳ ተፈናቀሉ፡፡ አነዚህ አባወራዎች ከአማራ ክልል በተለያዩ የድርቅ ወቅቶች በሰፈራ ኑሮዋቸውን የመሰረቱ ሲሆኑ ለረጅም አመታት በቦታው መኖራቸውን ይናገራሉ፡፡ እነዚህ አባ ወራዎች መሬታቸውን ተቀምተው የተፈናቀሉ ሲሆን ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በመላው ኢትዮጲያ አንድነት ድርጅት(መኢአድ) ጹ/ቤት ቅጥር ጊቢ ውስጥ ተጠልለው ነበር፡፡ በወቅቱ የአቶ ሽፈራው ሽጉጤ አስተዳደር ዜናውን ከእውነት የራቀ ሲል አስተያየት መስጠቱ ይታወሳል፡፡
የፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ያልተጣራ ዜና እረፍት
የኢ.ፌ.ድ.ሪ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ በልብ ህመም ምክንያት ማረፋቸው የተገለጸው መጋቢት 4 2004 ዓ.ም. ነበር፡፡ መንግስት  እንደተለመደው ማስተባበያው በተገቢው ጊዜ አለማቅረቡ ወሬው እንዲዛመት አስተዋእጾ ያደረገ ሲሆን ብዙዎች የቀብሩ ቀን መች እንደሆነ በሚጠባበቁበት ሰዓት ኢዜአ ፕሬዚዳንቱ ለተለመደ የጤና ምርመራ በሳውዲ አረቢያ እንደሚገኙ በመግለጹ ወሬው ቀስ በቀስ ከሚዲያ ጠፍቷል፡፡


ሚያዝያ

የአለም ደቻሳ ጥቃትና ሞት
በሊባኖስ የኢትዮጲያ ቆንስላ ቢሮ በር ላይ በአሰሪዋ ስትደበደብ የታየችው አለም ደቻሳ ከጥቂት ቀናት በሁዋላ ራስዋን አጠፋች መባሉን ተከትሎ ኢትዮጲያውያንን በአለም አቀፍ ያስቆጣ ክስተት ነበር፡፡የአለምን ሞት ተከትሎ የተለያዩ አካላት አጋርነታቸውን የሚያሳይ የተለያዩ ዝግጅቶች በአለም አቀፍ ደረጃ የተካሄዱ ሲሆን ለቤተሰቦችዋም በገቢ ማስገኛ ፕሮግራሞች ድጋፍ ተደርጎላቸዋል፡፡ የአለም ሞት በወቅቱ ከአልጀዚራ ጀምሮ የተለያዩ ታለላቅ የአለም ሚዲያዎች ከፍተኛ ሽፋን ተሰጥቶት ነበር፡፡
እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ዜና እረፍት
እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ በጨጓራ አልሰር ምክንያት አዲስ አበባ በሚገኘው ካዲስኮ ጠቅላላ ሆስፒታል በህክምና ሲረዱ ቆይተው ሚያዝያ 02/2004 ዓ.ም ምሽት 2 ሰዓት 45 ደቂቃ ላይ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ በሀገራቸውና በአውሮፓ ለረጅም ዓመታት የሥነ ጥበብ ሙያን የተማሩ ሲሆን በሀገራቸውና በዓለም አቀፍ ደረጃም በተለያዩት ጊዜያት በርካታ የስዕል አውደ ርዕዮችን በማቅረብ ትልቅ አድናቆትንና ክብርን ለመጎናጸፍ ችለዋል። ሚያዝያ 6 ቀን 2004 ዓ.ም. የቀብራቸው ሥነ ሥርዓት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እኩለ ቀን ተፈጽሟል፡፡
የቴዲ አፍሮ አራተኛ አልበም ተለቀቀ
ሚያዝያ 6 ቀን 2004 ዓ.ም ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ጥቁር ሰው ሲል የሰየመውን አራተኛ አልበሙን ለቀቀ፡፡ በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ካገኘው ሶስተኛው አልበሙ ቀጥሎ በተፈጠሩ ሁኔታዎች ድምጻዊው ለረጅም ጊዜ አዲስ ስራ አለማቅረቡ በከፍተኛ ጉጉት እንዲጠበቅ አድርገውታል፡፡ አልበሙ በስርጭት ብዛት እና በሽያጭ ገቢ ከፍተኛ ከሚባሉት የሙዚቃ ስራዎች መካከል መመደብ ችሏል፡፡ይሁንና አልበሙ ሙዚቀኛው በፊት ከነበረው የተሻለ ብቃት አለማሳየቱን ብዙዎች ቢገልጹም አልበሙ ተወዳጅነት አልቀነሰውም፡፡

ግንቦት

ጋዜጠኛ አበበ ገላው መለስ ዜናዊን በአደባባይ ነቀፈ
ግንቦት 10 ቀን 2004 ዓ.ም በቡድን ስምንት ሀገራት የመሪዎች ጉባዔ ላይ ጋዜጠኛ አበበ ገላው መለስ ዜናዊን በአደባባይ ነቀፈ ፡፡በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ግብዣ መሰረት በምግብ እህል ራስን መቻል አስመልክቶ የሚደረግ ውይይት ላይ ለመሳተፍ ዋሽንግተን ዲሲ የተገኙት የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ በምግብ እህል እራስን መቻል አስመልክቶ በሚያደርጉት ንግግር  መሐል ላይ በስፍራው በነበረው ጋዜጠኛ አበበ ገላው የተቃውሞ ድምፅ ንግግራቸውን በድንጋጤ አቋረጡ፡፡ ጋዜጠኛ አበበ ገላው ‹‹መለስ ዜናዊ አምባገነን ነው፣ እስክንድር ነጋንና ሌሎችም የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ፣ መለስ ዜናዊ የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈፅመዋል፣ ያለነፃነት ስለምግብ አታውሩ” ብሎ ሲናገር ተደምጧል፡፡ይህም ዜና በሀገር ውስጥ ሚዲያዎች(ከፍትህ ውጪ) ሽፋን ባያገኝም በማኀበራዊ መካነ ድሮች እና ሌሎች የዜና አውታሮች ዜናውን ተቀባብለውታል፡፡በተለይ የኢሳት ቴሌቪዥን ጉዳዩን የበለጠ ትኩረት መስጠት ጋዜጠኛ አበበ ገላውን በማናገር ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሚዲያ ሽፋን መራቅ ጋር በማያያዝ ከፍተኛ የጤና መቃወስና የመንፈስ መረበሽ እንደደረሰባው ለማሳመን ጥረት አድርገዋል፡፡


ሰኔ

የሴቶች ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ አለፈ
የኢትዮጰያ የሴቶች እግር ኳስ ብሄራዊ ቡድንም ቅዳሜ ሰኔ 9/2004 የታንዛኒያ አቻውን 1 ለ 0 አሸንፎ ለአፍሪካ ዋንጫ አለፈ፡፡ይህን ተከትሎ ከተለያዩ አካላት ማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡በኢኳቶሪያል ጊኒ አስተናጋጅነት የሚከናወነው 8ኛው የአፍሪካ ሴቶች እግር ኳስ ዋንጫ ኢትዮጵያ ከካሜሩን፣ አይቮሪኮስትና ናይጄርያ ምድብ ተደለደላለች፡፡
የዶ/ር እሌኒ ገ/መድህን  የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ለቀቁ
ሰኔ 11 ቀን 2004 ዓ.ም የኢትዮጵያ ምርት ገበያ መስራች እና ዋና ስራ አስፈፃሚ የነበሩት ዶ/ር እሌኒ ገ/መድሕን ስራ አስፈፃሚነታቸውን በራሳቸው ፈቃድ እንደሚለቁ አስታወቁ፡፡ ስራቸውን የሚለቁት ምርት ገበያው ሲመሰረት ጀምሮ በታቀደው የመተካካት መርሕ መሰረት ሲሆን ስልጣናቸውን ቀደም ሲል የአቢሲኒያ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ለነበሩት አቶ አንተነህ አሰፋ እንደ ሚያስረክቡ ተናግረዋል፡፡
 እርሳቸው ገበያው ሲመሰረት ጀምሮ በታቀደው መተካካት መሰረት እንደለቀቁ ቢናገሩም በመንግስት በኩል ጫና እንደደረሰባቸውና ለሚዲያ ይፋ ያልሆኑ ከገንዘብ ጋር የተያያዙ ችግሮች መኖራቸውን የተለያዩ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡
የቴሌኮም ማጭበርበር ሕጉ
የቴሌኮም ማጭበርበርን ለመከላከል በሚል ሽፋን መንግስት የተለያዩ የመገናኛ መንገዶችን ከልክለዋል ተብሎ የታማበት የቴሌኮም ማጭበርበር ረቂቅ አዋጅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ፡፡ በዚህ በመረጃ ደህንነት መረብ መስሪያ ቤት የተረቀቀው አዋጅ ዙሪያ ከፍተኛ የአለም አቀፍ የሚዲያዎች የተለያዩ ፕሮግራሞች የሰሩ ሲሆን እነደተለመደው የመንግስት ማስተባበያ በአቶ ሽመልስ ከማል በኩል ዘግይቶ ቀረበ ሲሆን ስካይፕ እና የንግድ ያልሆኑ ግንኙነቶችን ህጉ አይከለክልም ሲሉ አቶ ሽመልስ አብራሩ፡፡ነገር ግን ህጉ ያለምንም ጠንካራ ማሻሻያ በሃምሌ መጀመሪያ በተወካዮች ምክር ቤት በአስቸኩዋይ ጉባዔ ጸደቀ፡፡


ሐምሌ

በአሸባሪነት የተከሰሱት ተፈረደባቸው
ሐምሌ 6 ቀን 2004 ዓ.ም የከፍተኛው ፍርድ ቤት ሶስተኛ ወንጀል ችሎት አንዱአለም አራጌን፣ ዶ/ር ብርሀኑ ነጋን፣ አንዳርጋቸው ፅጌን እና ፋሲል የኔአለምን በእድሜ ልክ ፅኑ እስራት፤ እስክንድር ነጋን፣ ኦባንግ ሜቶን፣ ፀጋስላሴ ዘለቀን፣ ናትናኤል መኮንን እና ክንፈሚካኤል ደበበን በ18 አመት ፅኑ እስራት፣ ጋዜጠኛ አበበ ገላው እና አበበ በለውን በ15 አመት ፅኑ እስራት እንዲሁም የአዲስ ነገር ጋዜጣ መስራች እና ኤዲተር የነበሩት አብይ ተክለማሪያምን እና መስፍን ነጋሽን የ8 አመት ፅኑ እስራት ወስኖባቸዋል፡፡ የቅጣት ፍርዱ የተሰጠው ሰኔ 10 ቀን 2004 ዓ.ም የዋለው ችሎት ተከሳሾችን በተከሰሱበት የሽብርተኝነት እና ሽብርተኝነትን የማገዝ ወንጀል ጥፋተኛ ናቸው ብሎ መወሰኑን ተከትሎ ነው፡፡
መለስ የሌሉበት የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ተካሄደ
ሐምሌ 7-8 ቀን 2004 ዓ.ም የአፍሪካ ህብረት 19ኛው መደበኛ የመሪዎች ጉባዔ በአዲስ አበባ ተካሄደ፡፡ ጉባዔው አዲስ አበባ ላይ እንዲካሄድ የተወሰነው እንድታዘጋጅ የተመረጠችው ማላዊ ጉባዔውን በሌላ ሀገር እንዲካሄድ ከጠየቀች በኃላ ነበር፡፡ በጉባዔው ላይ ኢትዮጵያ የተወከለችው በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ሲሆን ይህም ጠቀላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከሪዮ 2012 የከባቢ አየር ውይይት ላይ ከሌላው ጊዜ ከስተው እና ጤና ያጡ መስለው ለመጨረሻ ጊዜ ከታዩ በኃላ እየጠነከረ የመጣውን ጠ/ሚኒስትሩ በጠና ታመዋል የሚለውን ወሬ ይበልጥ አጋጋለው፡፡ አቶ መለስ ዜናዊ የሽግግር መንግስት ፕሬዚደንት ሆነው ስልጣን ከያዙ አንስቶ የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ ላይ ሳይሳተፉ ሲቀሩ የመጀመሪያ ጊዜያቸው ነበር፡፡
የሙስሊሙ ማህበረሰብ ተወካዮች ታሰሩ
በከፍተኛ ብልጠት ለወራት ሳይቁዋረጥ የቀጠለው የሙስሊሞች ተቃውሞ ተወካዮቻቸው በመታሰራቸው ወደ ሌላ ምእራፍ ተሸጋገረ፡፡ያልተፈቀደ የሰደቃ ስነስርአት ማካሄድ አይቻልም የተባለውን የመመንግስትን ክልከላ ተከትሎ አወልያ ትምህርት ቤት ውስጥ በምሽት  በመንግስት ሃይሎች እና በሙስሊሞች መካከል ግጭት የተፈጠረ ሲሆን በተከታዩቹ ቀናት የሙስሊሙን ህብረተሰብን የሚወክለው ኮሚቴ አባላት ለእስር ተዳረጉ፡፡የኮሚቴው አባላት ክስ የጠመሰረተባቸው በሽብርተኝነት ሲሆን አራዳ ፍ/ቤት ቀርበው የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸዋል፡፡
 ፍትህ ጋዜጣ ከዝውውር ውጪ ሆነች

በተለያዩ ጠንካራ ትችቶችን መንግስት ላይ በማቅረብ የምትታወቀው ፍትህ ጋዜጣ በፍትህ ሚ/ር ትእዛዝ የአንድ ሳምንት ከተቁዋረጠች በሁዋላ ብርሃን እና ሰላም ማተሚያ ቤት አላትምም በማለቱ ፍትህ ጋዜጣ ከዝውውር ውጪ ሆናለች፡፡ዋና አዘጋጅዋ ተመስገን ደሳለኝም ተከሶ ፍርድ ቤት ቀርቦ ለ1 ሳምንተ ያህል ከታሰረ በሁዋላ አቃቢ ህግ ባልታወቀ ምክንየት ተጨማሪ መረጃ ለመሰብሰብ ክሱን አቁዋርጦታል፡፡

ነሐሴ

የለንደን ኦሎምፒክ እና ኢትዮጵያውያን አትሌቶች
ከሐምሌ 20-ነሐሴ 6 ቀን 2004 ዓ.ም 30ኛው የኦሎምፒክ ውድድር በእንግሊዝዋ ዋና ከተማ  ተካሄደ፡፡የአትሌቲክሱ አንድ ዘርፍ በሆነው በሩጫ ብቻ ነበር፡፡ በዚህም 3 የወርቅ 1 የብርና 3 የነሐስ በጠቅላላው 7 ሜዳሌያዎችን ማግኘት ችላለች፡፡ የወርቅ ሜዳሌያዎቹን ያስገኙት በሴቶች በ10 ሺህ ሜትር ጥሩነሽ ዲባባ፣ በሴቶች ማራቶን ቲኪ ገላና እና በሴቶች 5 ሺህ ሜትር መሰረት ደፋር ናቸው፡፡ ብቸኛው የብር ሜዳሊያ ደግሞ በወንዶች 5 ሺህ ሜትር በደጀን ገ/መስቀል የተገኘ ነው፡፡ በወንዶች 10 ሺህ ሜትር ታሪኩ በቀለ፣ በሴቶች 10 ሺህ ሜትር ጥሩነሽ ዲባባ እና በሴቶች 3 ሺህ ሜትር መሰናከል ሶፊያ አሰፋ የነሐስ ሜዳሊያዎቹን ያመጡ አትሌቶች ናቸው፡፡ ከውድድሩ ጋር ተያይዞ የአንዳንድ አትሌቶች ብቃት መውረድ እና ከውድድሩ ተሳታፊዎች በላይ ቁጥር ያላቸው የልዑካን ቡደኑ አባላት ወደ ስፍራው ማምራታቸው ከፍተኛ ክርክርን አስነስተዋል፡፡
ብፁህ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አረፉ

ነሐሴ 9 ቀን 2004 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትሪያርክ የነበሩት አቡነ ጳውሎስ ባደረባቸው ህመም አረፉ፡፡ ስርአተ ቀብራቸውም ነሐሴ 17 ቀን 2004 ዓ.ም በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈፀመ፡፡ ብፁህነታቸው የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ለመምራት ከተመረጡበት 1984 ዓ.ም ጀምሮ ለ20 አመታት በፓትሪያርክነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡

መለስ ዜናዊ አረፉ
ነሐሴ 15 ቀን 2004 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክሪያሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ መለስ ዜናዊ ነሐሴ 14 ቀን 2004 እኩለ ሌሊት 5፡40 ላይ መሞታቸውን የሚኒስትሮች ካቢኔ መግለፁን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ይፋ አደረገ፡፡ የኢፌደሪ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ለአራተኛ የምርጫ ዘመን በማገልገል ላይ የነበሩት አቶ መለስ የሁለተኛ አመት የህክምና ትምህርታቸውን ካቋረጡበት ከ19 አመታቸው ጀምሮ ህይወታቸው በፖለቲካ ትግል እና ስልጣን የተሞላ ነበር፡፡ የአቶ መለስ ዜናዊ ብሔራዊ የቀብር ስነ-ስርዓት ብዛት ያላቸው አፍሪካውያን እና ሌሎች መሪዎች በተገኙበት ነሐሴ 27 ቀን 2004 በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡ አቶ መለስ የሁለት ሴት እና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነበሩ፡፡

የእኛ ጀግንነት


ጀግንነት እና እኛ ኢትዮጵያውያን ከተያያዝን የማንላቀቅ ለሌሎችም ስንሸልመው የኖርን የጀግንነት ወራጅ ሕዝቦች ነን፡፡ ከጀግንነት ጋር ጥልቅ ፍቅር ውስጥ የወደቅን ሕዝቦች መሆናችንን ለማሳየት የታሪክን ምስክርነት መጠየቅ አያስፈልግም፡፡
በቅርብ ጊዜዎች እንኳን ጀግንነትን ለብዙዎች ስንሸልም ተመልክተናል፡፡ በቅርቡ ደግሞ የልማት ጀግንነት ለገበሬዎች እና ድህነትን ድል ላደረጉ ሁሉ ሲሰጥ የነበረ ስያሜም ሆኖም ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን በዘመናችን ከድፍረት ጋር የተያያዘ ጀግንነትን ስለምናደንቅ እና ስለምናበረታታ ጥንት ጥንት የጦር ሜዳ ጀግነነትን አሁን ደሞ የተለየ ድፍረትን በጀግንነት ምሳሌነት ከመጥቀስ ባሻገር የሚያግባባን የጋራ ትርጉም ያለው አይመስልም፡፡
ሰሞኑ እና ጀግንነት

የቀድሞው /ሚር አቶ መለስ ዜናዊ (ነፍሳቸውን ይማርና) ከሞታቸው ጋር ተያይዞ በሰሞኑን ጀግንነትን የመሾም ታሪካችን ውስጥ ከፍተኛ ስፍራን የያዙ መስለዋል፡፡ በእርግጥ በጥቂት ፖስተሮች እና ህትመቶች ላይ ይታይ የነበረው የአቶ መለስ የጀግና ስፍራ ከሞታቸው በኋላ በእርግጠኝነት እና በስፋት በሁሉም ቦታ እና ሁኔታ እየታየ ነው፡፡ ህልፈታቸው ከተሰማበት ማግስት አንስቶ ስራ የጀመረው የፕሮፖጋንዳ ማሽንም አገራዊ ሃዘኑን ለፖርቲ ስብእና ግንባታ መጠቀም መሆኑ በሚያስታውቅ ሁኔታ የጀግናው ሞት ምን ያህል እንዳሳዘነን ሊያሳየን ሞክሯል፡፡ ይህ የሚዲያው ተግባር እና ተያያዥ ሕዝባዊ ምላሾችን አስመልክቶ ውይይቱ ለሌላ ጊዜ ይቆየንና የአቶ መለስን ጀግና ያስባሉ ጉዳዮችን በትኩረት ብንመለከት ቢያንስ ቢያንስ ጀግና ባሰኛቸው ነገር ላይ መነጋገር የወደፊት ጀግኖቻችንን ሹመት በአትኩሮት ለማየት ይረዳን ይሆናል፡፡
ልማታዊ መሪ (የግድብ እና የመንገድ አባት)
አቶ መለስ ዜናዊ የመንግስትን ስልጣን ከተረከቡ 1983 ጀምሮ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡ መንግስታቸው ከሚታወቅበት ጉዳዮች አንዱ መንገዶች እና ህንፃዎች በብዛት መገንባታቸው ነው፡፡ ይህ የመንግስት ስኬት በተለይ ካለፉት መንግስታት ጋር ሲነጻጸር የሚያስመሰግነው ቢሆንም መንገድ የሰራልን መሪያችን ጀግና ነው የሚያስብል ድምዳሜ ላይ ማድረሱን እጠራጠራለሁ፡፡ ለነገሩ ፓርቲውም ቢሆን ስለስኬቶቹ ሲጠየቅ መጀመሪያ የሚያነሳው መንገድን ስለጥፋቶቹም ሲወቀስ መልሶ የሚያነሳው መከላከያ ያው የመንገድ እና የህንፃዎች ግንባታን ነው፡፡ በቅርብየአባይ መደፈርነገሩን ወደዚያ ወሰደው እንጂ ላለፉት 20 ዓመታት ፓርቲያቸው የመንገድ ግንባታን ግብር የሚሰበስብ መንግስት ኃላፊነት ያልሆነ ይመስል ለተለያየ ፕሮፖጋንዳ ሲጠቀምበት ከርሟል፡፡

ግብር ከፋይ ሕዝብ መንገድ ሲሰራለት እነደችሮታ አንዲቆጥረው ሲደሰኮር መክረሙን ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ የአባይ ፕሮጄክት መጀመርን ሙሉ ዕውቅናን ለጠ/ሚኒስትሩ መስጠት የጥረታቸው የሚገባ ዋጋ ነው:: (ይህ እንግዲህ የመነሻ ዓላማውን፣ የፕጄክቱን ስኬታማት ዕድሎች፣… የመሳሰሉትን ክርክሮች ሳይጨምር ነው፡፡) ይህ የሚገባው ዕውቅና እንዳለ ሆኖ ነገር ግን የመንግስት ኃላፊነቶቹን የሚወጣ መሪን ኃላፊነትህን ስለተወጣህ ጀግና ነህ ብሎ ማወደስ የለመደብን፣ የማጋነን እና በነፈሰበት የመንፈስ ዘይቤ ውጤት ይመስላል፡፡ የአባይን የመገደብ ፕሮጄክት ብቻውን ለሟች /ሚር ተገቢ ዕውቅና ቢሰጣቸውም ሌሎቹን ልማታዊ ቅጥያዎች መንግስታዊ ኃላፊነታቸው/ሥራቸው መሆኑን ባንረሳ ጥሩ ነው፡፡
ልማቱ ከተነሳ አይቀር በልቶ ማደር ብርቅ የሆነባቸው የከተማ ነዋሪዎች፣ የቤት ኪራይ እና የደሞዝ መጠን አንድ የሆነበት ጊዜ፣ ትራንስፓርት ችግር የሚያስለቅስበት ወቅት፣ የኑሮ ውድነቱን መቋቋም ያልተቻለበት ዘመን የእርሳቸው አመራር ውጤት መሆኑንም መዘንጋት አያስፈልገንም፡፡
የኢትዮጵያ/የአፍሪካ ተወካይ
ኢቴቪ፣ መሰሎቹ እና ሐዘንተኞቹ በተደጋጋሚ ያነሱት የነበረው የአቶ መለስ የመጀመሪያ ሰሞን የጀግነት መገለጫ በአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ዙሪያ ያደረጉት ንግግር ነው፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ አቶ መለስ ስለአገራቸው በቅንነት እና እንደመሪ በሚያኮራ መልኩ የተናገሩት ብቸኛ ንግግር ይሄ ነወ ለማለት እደፍራለሁ:: ኢቴቪም ቢሆን የአገር መሪ እንዳጣን ሊያስታውሰን ሲሞክር ደጋግሞ ሲያሳየን የነበረው ይሁንኑ ንግግር ነበር፡፡ ከዚያ ውጪ ያለውን የአቶ መለስን ስብዕና ሰስናስታውስ ደጋግሞ የሚታወሰኝብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦችተያያዥ ጉዳዮች እና ከእሳት የተፈተነ ብሔር መምጣታቸውን በኩራት የተናገሩበት ንግግራቸውም ጭምር ነው፡፡
አፍሪካ ህብረት እና ኢትዮጵያ በአፍሪካ ያላት ቦታ ዛሬ በመለስ ዘመን ያገኘነው አዲስ ቦታ አይደለም፡፡ (አቶ መለስም ቀደም ሲል በገለጽኩት ንግግራቸው ላይ ይህንን ያምናሉ)፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት (በቀድሞ አፍሪካ አንድነት) ውስጥ የነበራትን ቦታ ይዛ እንድትቀጥል ማድረጋቸው እንደ አንድ መሪ የሚያስመሰግናቸው ቢሆንም ጀግና የሚያስብል ማዕረግ ግን የሚያላብስ አልነበረም፡፡ እንደውም እንደአለመታደል ሆኖ ነው እንጂበየስብሰባው የሚዞር መሪያላት አገር ተብሎ ከመታወቅ ይልቅ በፈጣን የዴሞክራሲ ስርአት እና ተያያዥ ፍሬዎቹን የሚያጣጥሙ ሕዝቦች አገር ተብሎ መታወቅ ይበልጥ ያምርብን ነበር፡፡
የአቶ መለስ አለም አቀፍ የተግባቦት ችሎታ የማይካድ ቢሆንም የግል ስብእናቸውን ገንብቶ እኛን ለኢቴቪ ፕሮፖጋንዳ ከመዳረግ ውጪ እንደ አገር ኢትዮጵያን የጨመረላት ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ እንደውም ይህ የተግባቦት ችሎታቸው የሰብአዊ መብት ጥሰቶቸን እና ጭቆናን ለመደበቅ እነደመሳሪያ ሆኖ ማገልገሉን አናንሳ ካልን ነው፡፡ ከአፍሪካ መሪዎች በተሻለ የማሳመን ችሎታቸው የሚታወቁትን አቶ መለስን አፍሪካ ተወካይ አድርጋ ብትመርጥ አይገርምም:: የአፍሪካ መሪዎች ብዙዎቹ አምባገነኖች ናቸው፡፡ ሕዝቦቻቸውን በማማረር በሚታወቁ የአፍሪካ መሪዎች መካከል በሙስና እና በመልካም አስተዳደር እጦት ሕዝቦቻቸውን የሚያሰቃዩ መሪዎችን መወከል የምርጦች ምርጥ መሆን አይደለም፡፡ አቶ መለስ የዴሞክራሲያዊ አገራትና የሚኮራባቸው ስኬታማዎች መሪዎች ተወካይ አልነበሩም፡፡ ኢትዮጵያን እንደ ሃገር በየአመቱ ብዙ ሺህ ሰዎች የሚሰደዱባት፣ በየአገሩየሞቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎችዋን በየቀኑ የምትቀበል አገር መሆንዋን የአቶ መለስ ተወካይነት አላስቀረውም፡፡ ምክንያቱም ይህ በእርሳቸው አስተዳደር ዘመን ኢትዮጵያ ያለችበት እውነታ ነውና!
የዴሞክራሲያ አባት/የአንድነት አባት
ይህንን ወደቀልድነት የሚያደላ የአቶ መለስ ቅጥያ ጀግንነት የሰማሁት ከኢቲቪ እና መሰሎቹ ነበር፡፡ እንደሰማሁት መጀመሪያ የተሰማኝ የነበረውየዴሞክራሲን እና የአንድነትን ትርጉም ለመረዳት ምን ያስፈልገናል ወይስ አይገባቸውም ተብለን ይሄን ያሕል ተንቀን ነውየሚል ጥያቄ ነበር፡፡ አንዳንዴ ሳስበው አቶ መለስን በግል ከየትኛውም ሚዲያ ውጪ ብናጨዋውታቸው ራሳቸው የአንድነት እና የዴሞክራሲ አባት ነኝ የሚሉ አይመስለኝም፡፡ ዴሞክራሲ ሒደት ነው ብለው ይሸፋፍኑት ይሆናል እንጂ፡፡
አቶ መለስ የዴሞክራሲን ማስፈን ፍላጎት እና ተግባራዊነት የተቀላቀለባቸው መሪ ነበሩ፡፡ (ይህንን ለመረዳት ሕገ መንግስቱን እና ተግባራዊውን ሁኔታ ማወዳደር ይበቃል) የፓርቲያቸውም ሆነ የግለሰብ ባህሪያቸው ዴምክራሲን እሴታቸው አድርጎ አይቶ የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡ አለማቀፋዊ ተቀባይነትን ለማግኘት ከሚሞከሩ የጨዋታ ምርጫና ሚዲያ ውጪ የተቃውሞ ድምጾች መገለጫም ሆነ ቁጥር ቀን በቀን እየቀነሰ ሄዶ አሁን ዜጎች መንግስትን የምትተች ትንሽ ንግግር እንኳን ሲያደርጉ አካባቢያቸውን ዞር ዞር ብለው ለማየት እና ድምጻቸውን ለመቀነስ የተገደዱበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ ይህ እንግዲህ የአቶ መለስን 1997ቱን የኢትዮጵያን የሰላማዊ ዴምክሲያዊ ሽግግር ዕድል የገደሉበትን፣ ነፍስ ያስጠፉበትን ተግባራቸውን እንርሳ ካልን ነው፡፡
የአቶ መለስ መንግስት ባለፉት 21 ዓመታት ከፈጠራቸው ታላላቅ ጠንካራ አገራዊ ጥፋቶች መካከል አንዱ እንደአገር ልዮነቶቻችን ላይ አንድናተኩር የመደረጋችን ስትራቴጂ ነው፡፡ ይህ የሃይማኖት እና የብሔር ልዩነትን በዕውቅና እና መብት መስጠት ሽፋን በማስፋፋት የማንነታችን መነሻ ኢትዮጵያዊነት መሆኑን የረሳንበት ደረጃ ላይ አድርሶናል ለማለት እደፍራለሁ፡፡ ይህ በጋራ መሃከል ላይ እስክንመጣ ድረስ የሚቆይ አገራዊ የቤት ሥራ የአቶ መለስ አመራር ውጤት ሆኖ እያለ አቶ መለስን የአንድነት አባት ማለት፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲከኛ እስረኞች ያሉባትን ሃገር፣ የፓለቲካ ስደተኞች የበዙባትን ሃገር፣ ሽምግልና የፓለቲካ እስረኞችን ለማስፈታት መቀለጃ እና መሳሪያ በሆነበት ዘመን፣ አቶ መለስን የዴሞክራሲ አባት አድርጎ መሳል በሕዝቦች ላይ መቀለድ ነው፡፡
አንደበተ ርቱዕ?
የአቶ መለስ አንደበተ ርቱዕነት ሰሞኑን አንዱ የጀግንነታቸው ምክንያት ሆኖ ተገልጧል፤ (ለነገሩ ወደ በኋላ ትንሽ ደበዘዘ እንጂ የድሮም ዝናቸው መሰረት አንደበተርዕቱነት ነበር)፡፡ በእርግጥ አቶ መለስ ሐሳባቸውን በመግለጽ በኩል ጠንካራ ነበሩ፡፡ ሐሳባቸውን የሚገልጹበት መንገድ እና ሁኔታ ቢለያይም (ፓርላማ ላይ ሌላ፣ ከአገር ውስጥ ጋዜጠኞች ጋር ሌላ፣ ከሃገር ውጪ ስብሰባ ላይ ሌላ፤ የአገር ውስጥ ስብበሳ ላይ ሌላ) በራስ መተማመን መንፈስ ሐሳባቸውን ከመግለጽ ተቆጥበው አያውቁም ነበር፡፡ በሃገር ውስጥ በሚደረጉ ውይይቶች ላይ ግን አቶ መለስ የመሪነት ስልጣናቸውን እንደፈለጉ ለመናገር መሳሪያ አድርገው ተጠቅመውበታል የሚል እምነት አለኝ፡፡
አቶ ለመለስ በፓርላማ ይጠየቃሉ እንደፈለጉት ይመልሳሉ፤ እርሳቸው ለመለሱት መልስ ክርክር እና ተጨማሪ ምላሽ የመስጫ ጊዜ ኖሮ ስለማያውቅ ከማሰካካት ባለፈ የክርክራቸውን ቀሽምነትን እና ጥሩነት ከሌሎች ጋር በመከራከር ተፈትኖ አያውቅም፡፡ በዚህ ብዙ ዕድሎች የሰጠን ምርጫ 97 እንኳን እርሳቸውን በአደባባይ ሲከራከሩ ሊያሳየን አልቻለም ነበር፡፡ በተለይ በአገር ውስጥ ጉዳዮች ዙሪያ የአቶ መለስ አንደበት አንድም ቀን ለክርክር ቀርቦ አያውቅም፡፡ እሳቸው ይናገራሉ ሌሎች ያዳምጣሉ፡፡ እንደውም ሞታቸው የሚቆጨው ከአንድም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ጋር ለቀጥታ ክርክር ቀርበው ሳይከራከሩ በመቅረታቸውም ጭምር ነው፡፡ የአቶ መለስ አንደበተ ርቱዕነት በዓለም አቀፍ መድረኮች የሚመሰከርለት ቢሆንም እንደ ኢትዮጵያዊ ምስክር ሆነን እና አፋችንን ሞልተን እናወራለት ዘንድ እሳቸው ብቻ ሲናገሩ መክረማቸው ቀርቶ በአገራዊ ውይይቶች ከሌሎች ጋር ሲያወሩ፣ ሲወያዩ እና ሲከራከሩ የማየት እድሉ ቢኖረን ይህንን የጀግንነታቸው መገለጫ አንደበተ ርቱዕነታቸውን ነው ብለን አፋችንን ሞልተን እናወራ ነበር፡፡
ለእኔ በግሌ አቶ መለስ የምኮራባቸው ጥሩ መሪ አልነበሩም፡፡ እዚህ ቅሬታ ላይ የሰሞኑን ቅጥ ያጣ ፕሮፖጋንዳ ሲጨመርበት ደግሞ እንደ ሰው ያዘንኩትን ሐዘን በኢቴቪ እና በመሰሎቹ እንዳልቀማ ጥረት ሳደርግ ቆይቻለሁ፡፡ ሐዘኑን ፓለቲካ ሲያደርጉብን ከርመው እኛ ፓለቲካዊ ስናደርገው የሚወቅሱን ካሉ ለአቶ መለስ ማዘን እና ፕሮፖጋንዳውን ባለመቀላቀል እንዲረዱኝ ለማስታወስ እወዳለሁ፡፡ አልታደልንም እንጂ ኢቴቪን ወደ አንድ ጽንፍ ሲጎትተን የሚያመጣጥንልን ሌላ ሚዲያ ቢኖረን ኖሮ በዚህ ሐሳብ ዙሪያ ለመነጋገርም አንነሳም ነበር፡፡
አቶ መለስ ታታሪ፣ ለአላማቸው ጽኑ፣ ጠንካራ ሰራተኛ፣ የፓርያቸው ምሰሶ ነበሩ፡፡ የእርሳቸው ዓይነት አንድ ሁለት ሰው አንደተተኪ እንኳን ሳያበቁ ማለፋቸው የአመራራቸውን ድክመት ያሳያል፡፡ እርሳቸው የጥቂት ዓመታት መሪ ቢሆኑ ኖሮ በቂ ጊዜ ሳይኖራቸው ነው ብለን እናስተባብልላቸው ነበር ነገር ግን 30 ዓመት በላይ በመሩት ፓርቲ ውስጥ ለሚተካቸው መጥፋት መልሶ ራሳቸውን ተጠያቂ ያደርጋቸዋል፡፡ በዚሁ አጋጣሚ የሰሞኑን የመንግስት ባለስልጣናት አቶ መለስን ሲያወድሱ የፓርቲያቸውን ባዶ ሜዳ መቅረትም እየነገሩን ነበር፡፡ የአቶ መለስ ታታሪነት አንጂ ተተኪ ያለመኖር ታሪክ የሚኮራበት መሆን አልነበረበትም፡፡
ለታታሪው ኢትዮጵያዊ አቶ መለስ ዜናዊ ነፍስ ይማር፡፡ በፕሮፖጋንዳ ብዛት ራሳቸውን እያጠፉ ላሉት ኢቴቪና ዘመድ አዝማድ ሚዲያዎችም ነፍስ ይማር!