Category Archives: Uncategorized

‘ሰንደቁ’ ላይ ያለው ‘አላማ’

ወቅቱ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ስልጣን በያዘበት ማግስት ነው፡፡ በጊዜው የነበረው የሀገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለማትን ብቻ ያዘ ነበር (በርግጥ በሕግ የተደነገገ ባይሆንም በአንዳንድ የደርግ ተቋማት ውስጥ ሰማያዊ መደብ ያለው ሰንደቅ ዓላማም ይስተዋል ነበር)፡፡ የወቅቱ ባለስልጣናትም  አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀዩ ሰንደቅ ዓላማ ላይ የብሄሮችን መፈቃቀድ የሚገልፅ አርማ መኖር አለበት፤ አርማውስ ምን አይነት ይሁን? የሚል ሃሳብ ይቀርባሉ፡፡ የታሪክ ፕሮፌሰር የሆኑት ላጲሶ ጌ. ዴሌቦም ሀሳባቸውን እንደሚከተለው ሰነዘሩ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ በጣም ተጨቁኖ የኖረ ሕዝብ ነው፡፡ ስለዚህም በሰንደቅ ዓላማው ላይ የሚቀመጠው አርማ ይሄን ጭቆናውን የሚገልፅ መሆን ይኖርበታል፡፡ ለዚህም ደግሞ ‘ከአህያ ምስል’ የተሻለ አርማ የለም፡፡ ሕዝቡ እንደ አህያ ለዘመናት አምባገነንነት ተጭኖበት በጭቆና ውስጥ ነበርና፡፡››  

ይህ ከሆነ 17 ዓመታት በኋላ ተሻሽሎ የወጣው የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 654/ 2001 በአንቀፅ 4 ላይ እንዳሰፈረው ‹‹ብሄራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በየዓመቱ መስከረም ሁለኛ ሳምንት ሰኞ በድምቀት ይከበራል፡፡›› ከአዋጁ መውጥት አስቀድሞ በሰኔ 2000 ዓ.ም በግለሰቦች አነሳሽነት መከበር የጀመረው የሰንደቅ ዓላማ ቀን ዘንድሮ ለ5ኛ ጊዜ  ሰንደቃላማችንን ከፍ አድርገን  በመለስ ቀያሽነትየተጀመረውን ህዳሴ እናረጋግጣለን!” እንደሚከበር ተገልል፡፡ ነገር ግን የዘንድሮው ክብረ በዓል በአዋጁ ከተደነገገው ቀን አልፎ ጥቅምት 19/2005 ዓ.ም ነው  የሚከበረው፤ ይሄን አስመልክተን በኢትዮጵያ  ሰንደቅ አላማ ዙሪያ ያሉ ሀተታዎችን ለመመልከት ተነሳን፡፡

ሰንደቅ ዓላማ

ከሰንደቅ አላማ ቀለም እና ምልክት ጀርባ ታሪክ፣ ባህል፣ ማንነት እንዲሁም አንዳንዴ አስተሳብን የሚያመለክት መንፈስ አለ፡፡  የካውካሲያን ህዝቦችን (ለምሳሌ የአሜሪካ፣ የእንግሊዝ፣ የፈረንሳይ፣የሩስያ፣ የአውስትራሊያ ወ.ዘ.ተ)  ሰንደቅ አላማዎችን ብንመለከት በአብዛኛው ነጭ፣ ቀይ እና ሰማያዊ ቀለማትን ለሰንደቅ አላማነት ይጠቀማሉ፡፡ የቀለማቱም ምርጫ በተወሰነም መልኩ የህዝቦቹን አንድ አይነት አመለካከት ይገልፃሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የአፍሪካዊያንን ሰንደቅ ዓላማ ስንመለከት አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለማት ከፍ ብለው እና በተለያየ አደራደር ተቀምጠው እናያለን፡፡ ይሄም ተመሳሳይ ምክንያት እንዲሸተን ያደርገናል፡፡

ታሪክ ወ አፈታሪክ  

የሀገራችን የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ በሀገሪቱ ውስጥ አነታራኪ ከሚባሉ ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡ ንትርኩም የሚጀምረው ከታሪካዊ አመጣጡ ጀምሮ ነው፡፡ በዚህም ጉዳይ ታሪክን ከአፈታሪክ (History from Myth) ለመለየት አስቸጋሪ ከመሆኑ አንፃር በዋነኛነት ጎልተው የሚሰሙትን ታሪኮች እና አፈታሪኮችን አዳቅለን ለማየት እንሞክር፡፡

በአሁኑ ወቅት ያለውን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ለምን አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለማት ሊሆን ቻለ? ለሚለው መልስ የተለያ ወገኖች የተለያዩ ምክንያቶችን ያቀርባሉ፡፡ ክርስቲያናዊ ትርጉሙም ገዝፎ ይታያል፡፡ እንደ አንዳንድ ፀሃፍት ‹‹የቀድሞ አባቶቻችን እና እናቶቻችን ወደ ጦር ሜዳ ሲሄዱ የተለያዩ የዛፍ ዝንጣፊዎችን ይዘው ይዘዋወሩ ነበር፡፡ የሚይዙት ዝንጣፊም አረንጓዴ በመሆኑ በተለያዩ ነገሮች አረንጓዴ ነገርን በማዘጋጀት እንደ ቀዳሚው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ሆነ፡፡›› በማለት አጀማመሩን ይገልፃሉ፡፡

አፈታሪኩ ሲያስከትልም ‹‹ኢትዮጵያ ከሕገ ልቦና ወደ ሕገ ኦሪት በንግስተ ሳባ አማካኝነት ስትሸጋገር በእግዚአብሄር ተስፋ ማድረግን ለማመላከት ኢትጵያዊያኑ ቀድመው ይጠቀሙበት የነበረው አረንጓዴ መለያ ላይ ቢጫ ቀለምን በመጨመር አንድ እርምጃ ወደፊት ተሻገ›› በማለት ክልኤቱ ይላል፡፡ ክርስቲያናዊ አፈታሪኩ ሲቀጥልም ‹‹በንጉስ ባዚን ጊዜ ወደ እየሩሳሌም አቅንቶ ወንጌልን አውቆ የተመለሰው ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ክርስትናን ወደ ኢትዮጵያ ይዞ ከመግባቱ ጋር ተያይዞ፤ ኢትዮጵያዊያን እየሱስ ክርስቶስ በደሙ ቤዛ እንደሆናቸው በማመናቸው ቀድመው ይጠቀሙበት የነበረውን አረንጓዴ እና ቢጫ መለያ ላይ ቀይ ቀለም በመጨመር አሁን ያለውን ቀለም እንዲይዝ አድርገውታል›› ይላል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ የሆነው እግዚአብሄር አለምን ዳግም በጥፋት ውሃ ላለመምታት ለኖህ የገባውን ቃልኪዳን የፈፀመው በቀስተዳመና ነው፤ በቀስተ ዳመናውም ውስጥ ገዝፈው የሚወጡት ቀለሞች አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ በመሆናቸው የነሱን አምሳያነት ነው የሚል አፈታሪክ ይደመጣል፡፡ ከዚሁ ከኖህ ጋር ተያይዞ ‹‹የጥፋት ውሃው በጎደለ ጊዜ እንደ ብስራት መግለጫ የታየው የወይራ ቅጠል መጀመሪያ አረንጓዴ፣ ሲቆረጥ ወደ ቢጫ በመቀየር መጨረሻ ላይ ቀይ ቀለምን በመያዝ ይደርቃል እናም ሰንደቅ ዓላማችን የወይራው ተምሳሌት በመሆን መልካም ዜናን ገላጭ ነው›› የሚል አፈታሪክም ይደመጣል፡፡

የቅርብ ጊዜ ታሪኮች ደግሞ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የአሁኑን ቀለም የያዘው ባለፍት 150 ዓመታት በተደረገው ክለሳ ነው፡፡ ከዛ በፊት የነበረው ሰንደቅ ዓላማ ሌሎች የተለያዩ ቀለማትን የያዙ ነበሩ ይሉናል፡፡ ነገር ግን አንዳንዶች በአፄ ቴዎድሮስ ሁለተኛ ጊዜ ነው የአሁኖቹ ቀለማት ጥቅም ላይ የዋሉት ሲሉ፤ ሌሎች ደግሞ የለም የለም በአፄ ዩሃንስ አራተኛ ዘመነ መንግስት ነው ይላሉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ አይ በዳግማዊ ምኒልክ ንግስና ዘመን ነው፤ ይህ የሆነው በማለት ታሪኩን ያወሳስቡታል፡፡ እንግዲህ የቀለማቱ ታሪክ እና ትርጉም ስምምነት ላይ ሳይደረስበት ሲሰረዝ እና ሲደለዝ አሁን የምንጠቀምበትን አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለማት በሰማያዊ አርማ እና በቢጫ ኮከብ የታጀበ ሰንደቅ ዓላማ ላይ ደርሰናል፡፡ ውዝግቡ ግን አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ እስኪ በአሁኑ ወቅት በሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ ላይ የሚነሱትን አንዳንድ የውዝግብ ነጥቦች እያነሳን እንመልከት፡፡

ሰንደቅ ዓላማ ወይስ ሰንደቅ ዓላማዎች?

ከጣሊያን ወረራ በማስከተል በተፈጠረው አጋጣሚ ኢትዮጵያ የቀድሞ የግዛት አካሏን እና ለ50 ዓመታት በጣሊያን ቅኝ ግዛት ምክንያት ተነጥሎ የኖረውን የግዛት ክፍሏ ይመለስላት ዘንድ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት አመለከተች፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ከረጅም እና አታካች ውይይት እና ግምገማ በኋላ በአሜሪካን መንግስት አነሳሽነት ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌደሬሽን እንድትዋሃድ ወሰነ፡፡ ኢትዮጵያም በውሳኔው ለጊዜው ግር ብትሰኝም እንደ አሜሪካን እና ህንድ አይነት ታላላቅ ሀገሮችም በዚሁ የፌደሬሽን ስርዓት እንደሚመሩ መገለፁ ብዥታውን እንዲያለዝበው ሆነ፡፡

ነገር ግን በብዙ ኢትዩጵያውያን እና በኤርትራ የሚገኝው የአንድነት ማህበር (The Unionist Party) ፤ ኤርትራ ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ተለይታ የራሷን ሰንደቅ ዓላማ ማውለብለቧ አልተዋጠላቸውም ነበር፡፡ ይሄም ነገር ይቀለበስ ዘንድ አብዝተው በመጎትጎታቸው ለ10 ዓመታት የቆየው ፌደሬሽንም በንጉሱ ፊርማ ፈረሶ የኤርትራ ሰንደቅ ዓላማም ጉዳይ አከተመ፡፡

የኢህአዴግን ስልጣን መያዝ ተከትሎ የኤርትራ መገንጠል ብዙ ኢትዮጵያዊያንን ያስደነገጠ ጉዳይ ነበር፡፡ በሽግግር መንግስቱ ወቅት ተረቆ የፀደቀው የኢፌደሪ ሕገ መንግስት ፌደራሊዝምን እንደ መንግስታዊ መዋቅር መቀበሉ ደግሞ አንዳንድ ወገኖች በተለይም አጥባቂ ኢትዮጵያዊንን (Ultranationalists) ‹‹ይህች ሀገር ተገነጣጥላ ልታልቅ ነው›› የሚል ሌላ ስጋት ውስጥ ከተታቸው፡፡

ሕገ መንግስቱ የፌደራል ስርዓቱ በክልልሎች እንደሚዋቀርና እያንዳንዱ ክልሎችም የራሳቸው የሆነ ሰንደቅ ዓላማ እና አርማ እንደሚኖራቸው መደንገጉ፤ ለነዚህ ወገኖች የኢህአዴግን ፀረ-ኢትዮጵያዊነት መረጋገጫ ነበር፡፡ ኢህአዴግ በበኩሉ ‹‹ፌደራሊዝሙ እንደዚህ ካልተዋቀረ አብረን መኖራችን ያሰጋናል፤ ክልሎች የራሳቸው ሰንደቅ ዓላማ እና ዓርማ እንዲኖራቸው መፍቀዱ ደግሞ አሜሪካን በሚያክል ትልቅ ሀገር ሳይቀር ተቀባይነት ያለው የራስን በራስ የማስተዳደር አንዱ መገለጫ ነው፡፡ ኢትዮጵያም በተወሰኑ ቀለማት ብቻ አትገለፅም፡፡›› የሚሉ ምላሾችን በመስጠት ለክልሎች የራሳቸውን ሰንደቅ ዓላማዎች እንዲመርጡ አስቻላቸው፡፡

ከዛን ጊዜ ወዲህ የሱማሌ ክልል ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ወደ 11 ርዕሰ መስተዳደሮችን የቀያየረ ሲሆን፤ በሰንደቅ ዓላማ መቀየሩስ ለምን ይቅርብኝ? በሚመስል ምክንያት ሁለት የተለያዩ ሰንደቅ ዓላማዎችን ቀይሯል፤ ይሄም ድርጊት ብዥታን መፍጠሩ አልቀረም፡፡ በሌላ በኩል የትግራይ ክልል ሰንደቅ ዓላማ ህወሃት በትግል ወቅት ይጠቀምበት የነበረው ሰንደቅ ዓላማ  ለትግራይ ክልልም ማበርከቱ ትክክል አይደለም የሚል ሀሳብ መነሳቱ አልቀረም፡፡

እንግዲህ አንድ ሀገራዊ ሰንደቅ ዓላማ? ወይስ ሁሉም ክልሎች ከሀገራዊ ሰንደቅ ዓላማው ጎን ለጎን የሚያውለበልቡት የራሳቸው ሰንደቅ ዓላማዎች? የሚለው ሃሳብ አነታራኪነቱን ይዞ ቀጥሏል፡፡

‹‹ባንዲራ ጨርቅ ነው … አንዳንድ ሀገሮች ከወረቀትም ይሰሩታል››

ባለፉት ዓመታት ሰንደቅ ዓላማ በተነሳ ቁጥር የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ መነሳታቸው አልቀረም፡፡ በአንድ ወቅት ‹‹ባንዲራ ጨርቅ ነው›› ማለታቸው እንደ አንድ ሀገሩን የማይወድ መሪ እንዲቆጠሩ ያደረጋቸው ሲሆን፤ ከብዙ ኣመታት በኋላ ‹‹ባንዲራ ጨርቅ ነው›› ሲሉ ምን ማለታቸው እንደሆነ ሲጠየቁ፤ ‹‹አዎ ባንዲራ ትርጉም ከሌለው እንደወረደ ጨርቅ ነው፤ እንዲያውም አንዳንድ ሀገሮች ከወረቀት ይሰሩታል፡፡ ባንዲራ ትርጉም ይኖረው ዘንድ ዜጎች ሊወዱት እና ትርጉም ሊሰጡት ይገባል፡፡›› በማለት ምክንያታቸውን ለማቅረብ ሞክረዋል፡፡

 ነገር ግን ማሳመኛቸው ያልተዋጠላቸው ሰዎች ‹ምንም ቢሆን እንደ ሀገር መሪ እንደዚህ ማለት አልነበረባቸውም›› በማለት ሀሳባቸውን ያጣጥሉባቸዋል፤ አቶ መለስንም በፀረ-ኢትዮጵያዊነት ይፈርጇቸው ነበር፡፡ መለስ ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንደ ሰንደቅ ዓላማ ቀን ባሉ በዓላት ላይ በመገኝት  ስማቸውን ለማደስ መጣራቸው አልቀረም ነበር፡፡

The Magic Emblem

ሌላው በአሁኑ ወቅት በሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ ላይ ጎልቶ የሚነሳው ክርክር፤ በአሁኑ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ላይ ያለው አርማ ምንነት እና ትርጉም ነው፡፡ ለዛም ይመስላል ጉራማይሌ የሆነ የሰንደቅ ዓላማ አይነት በየቦታው የምንመለከተው፡፡ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሰት በአንቀፅ 3 ንዑስ አንቀፅ 2 ላይ እንዲሁም ተሻሽሎ የወጣው የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ 654/2001 በአንቀፅ 8 ላይ እንዳስቀመጡት በሰንደቅ ዓላማው ላይ ያለው ዓርማ ሰላምን፣ እኩልነትን አንድነትን እና ተስፋን ገላጭ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
ይህ ትርጉም  ያልተዋጠላቸው ወገኖች ምልክቱን በብዙ መልኩ በመተርጎም በህገ መንግስቱም ሆነ በአዋጁ የተጠቀሱት የአርማው ምክንያት ውሸት ነው ይልቅስ ‹‹የአንድ ብሄርን የምግብ አይነት አመላካች ነው›› ፣ አይ ‹‹ምልክቱ የኢህአዴግ አመራሮች ከሶሻሊዝም ምንጭ እየጠጡ (From Socialism Background) የጎለመሱ በመሆናቸው የሶሻሊዝሟን ኮከብ በአቋራጭ ሰንደቅ አላማዋ ላይ ማስቀመጣቸው ነው፡፡›› ይላሉ፡፡ ይባስ ብሎም አንዳንዶች ‹‹የጥንቆላ ምልክት ነው፤ እንጅማ የኮከብ ምስል ከኢትዮጵያ ጋር ምን አገናኝው?››› ይላሉ፡፡

የሆነ ሆኖ የሰንደቅ ዓላማ አዋጁ በሕገመንግስቱ ከተቀመጠው ዓርማ ውጭ የተሰራ ሰንደቅ ዓላማን መጠቀም እስከ አንድ አመት በሚደርስ ፅኑ እስራት የሚያስቀጣ መሆኑን የሚደነግግ ሲሆን፤ የኮከቡን አርማ ከያዘው ሰንደቅ አላማ ውጭ ያሉ ታሪካዊ ሰንደቅ ዓላማዎች በቤተ መዘክር እንደሚቀመጡ እና በአረጁ ጊዜም እንደሚቃጠሉ ይገልፃል፡፡

ዳግማዊ ቦሊቪያን መቅደም

በንጉሱ ዘመን የነበረው የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ በአንዳንድ የትርጉም ምክንያቶች ከአረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ወደ ቀይ ቢጫ እና አረንጓዴነት ለመቀየር ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት አመልክታ ይህ አደራደር በደቡባ አሜሪካዊዋ ሀገር ቦሊቪያ የተያዘ መሆኑን ተገልጾ ጥያቄዋ ውድቅ ተደርጎባታል፡፡

እንደ መላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰማያዊ አርማ የሌለበትን ንፁህ አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ሰንደቅ ዓላማ እንደ ትክክለኛው የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ በመቁጠር፤ በፓርቲያቸው ፕሮግራም ውስጥ ያካተቱ ሲሆን ለተባበሩት መንግስታት ድርጅትም የቦሊቪያው ታሪክ እንዳይደገም ይሄን ቀለም የያዘ ሰንደቅ ዓላማ ለሌላ ሀገር እንዳይፈቅድ እስከ መጠየቅ ደርሰዋል፡፡

የሀገራችን ፖለቲካ ፓርቲዎች በሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ ላይ እንኳን ስምምነት ላይ አልደረሱም፡፡ ለየትኛው ሰንደቅ አላማም ክብር (Allegiance) እንደሚሰጡም አልተስማሙም፡፡ ይህ ልዩነት ህብረተሰባችን ውስጥም አለ፡፡ ብቸኛው መፍትሄ ወደ ውይይት ቀርቦ ሀሳብን መሸጥ እና መግዛት ነው፡፡ ያለዚያ የተለያየ ሰንደቅ ዓላማ ይዘን የኢትዮጵያን ጥቅም በጋራ ማስጠበቅ እንዴት ይቻለናል?

መፅሃፍ፤ ከወዴት አለህ?

ባለፈው ሳምንት ፅሁፋችን አንባቢ ኢትዮጵያዊን ፍለጋ በሚል ርዕስ፤ ያለውን የንብብ ባህል ከመጽሃፍ ገበያው ጋር እንዲሁም ለምን ይህ ሆነ ብለን ጠይቀናል፡፡ በዛሬው ፅሁፋችን ደግሞ ምን ይፃፋል? እንዴትስ ይፃፋል? ለማን ይፃፋል? ብለን እንጠይቃለን፡፡
አንድ ፀሃፊ መፅሃፍ ሲፅፍ ብዙ አይነት አላማዎችን ይዞ ሊነሳ ይችላል፡፡ ሀሳብን ከማስተላለፍ እራስን እስከማሻሻል ድረስ፡፡ ከዓማ ሁሉ ገዝፎ የሚታየውና የመፅሃፉን ዋጋ ከፍ የሚያደርገው ደግሞ መፅሃፉ በህብረተሰቡ ውስጥ ያሳደረው ተፅዕኖ እና የሃሳብ አመንጭነቱ ነው፡፡ አንባቢውም መፅሃፉን ገዝቶ ሲያነብ አንድ ነገር መጠበቁ አይቀርም፡፡  እናም የደራሲው ዋና ሚና የሚጠበቀውን ተፅእኖ በተደራጀ እና በሚዋጥ መልኩ ለሚጠብቀው አንባቢ ማድረስ ነው፡፡
በሀገራችን አሁኑ ወቅት በተለይም በአማርኛ ቋንቋ ለአንባቢው እየቀረቡ ያሉ ፅሁፎች ከዚህ አንፃር እንዴት ይገመገማሉ ነው የፅሁፋችን ዋነኛ አላማ፡፡ ምንስ ችግሮች አሉም እንላለን፡፡ በዚህ ፅሁፍ ለማየት የሞከርኩት ሁሉም አይነት መፅሃፍት ውስጥ ለኔ ገዝፈው የታዩኝን ጉዳዮች ነው፡፡
The Zeitgeist is ‘Self-help’
በሀገራችን ዋና ዋና ከተሞች እግረኛ መንገድ እንዲሁም ብርቅ የሆኑትን የመፅሃፍት መደብሮች ተዘዋውሮ የተመለከተ ሰው፤ በአንድ ነገር ቀልቡ መሳቡ አያጠራጥርም፤ ‘የራስ አገዝ’ (Self-help) ወይም በተለምዶ ‘የስነ ልቦና’ መፅሃፍት የሚባሉት መፅሃፍት በገበያው ውስጥ ባላቸው ድርሻ፡፡ አዎ ገበያው ‘ምክር፣ ምክር’ ይሸታል፡፡ 
‘ሀብታም የመሆኛ ሚስጥሮችን’ ከSecrets Stock Market እስከ Save, Run & Invest ፣ ‘ስኬታማነትን በአጭር ጊዜ ለመቀዳጀት’ ይረዱ ዘንድ ከleadership እስከ Entrepreneurship፣ ‘የወሲብ የፀደይ ወራትን’ ይኖሩበት ዘንድ ከHow to Kiss a Breast እስከ Kamasutra ወ.ዘ.ተ በምክር መልኩ ተዘጋጅተው የመፅሃፉን ዓለም በአምባገነንነት ይዘውታል፡፡ ጥያቄው ግን እነዚህ አብዛኞቹ የትርጉም ስራዎች የሆኑ ራስ አገዝ መፅሃፍት አንደሚታሰበው የዜጎችን ንቃተ ህሊና ከፍ በማድረግ የግራ መጋባቱ መፍትሄ ይሆናሉ? እነዚህ ሲያሻቸው ከምዕራብ አለያም ከምስራቅ ፍልስፍና በትንሹ እየጨለፉ ስለማንኖርበት ህይወት የሚያስጎበኙን መፅሃፍት እውነተኛ ዋጋቸው ስንት ነው?
ይህ ከ1980ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ እያደገ የመጣው የራስ አገዝ መፅሃፍት የገበያ አምባገነንነት ጫፍ (Apex) ላይ ደርሷል ማለት የሚያስችለን አሁን ያለንበት ወቅት ነው፡፡ ‘የራስ አገዝ’ መፅሃፍትን በሽሚያ ተሸጠው ማለቅ ስንመለከት፣ ጊዜው የነሱ ነው እንድንል ያደርገናል እናም የአምባገነንነታቸው መጨረሻ በቅርብ አልመስለን ይላል፡፡
የነጭ ሳሩ አንበሳ መሃል ፒያሳ ኬክ ቤት ውስጥ ምን ያደርጋል?
ደራሲ እና ሀያሲ መስፍን ኃ/ማርያም የአንዳንድ ድርሰቶች አኳኋን አላምር ሲለው ‹‹አንዳንዱ ደራሲ በጣም ያሰገርማል፤ ድርሰቱን አስከተወሰነ ቦታ ይወስደው እና መቋጫ ታሪክ ሲጠፋበት ዋናው ገፀ ባህሪ ’መሃል ፒያሳ ኬክ እየበላ እያለ፤ ከነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክ አምልጦ የመጣ አንበሳ ገደለው’ በማለት ታሪኩን ይቋጨዋል፡፡›› ይለናል፡፡ እንግዲህ የስነፅሁፋችን ሌላው አዝማሚ አይረቤ ታሪክን በደረቀ ቋንቋ አጅሎ ‹‹ይህ እንደ ልቤ የማየውና ለ12 ዓመታት አምጨ የወለድኩት የበኩር ልጄ ነው፡፡ እነሆ ተቋደሱልኝ›› መባላችን ነው፡፡ 
በሀገራችን የተደራጀ የስነፅሁፍ ገምጋሚ አካል ካለመኖሩ ጋር ተያይዞ ‘የደራሲያን’ መበራከት ለግልብ መፅሃፍት መንስኤ ተደርጎ መወሰድ ይችላል፡፡ 
ከሳቴ ብርሃን የአማርኛ መዝገበ ቃላት ‘ድርሰት’ የሚለውን ሀሳብ፡ ሐዲስ ጥበብን ፍልስፍናን […] በጽሕፈት መግለጥ በማለት ድርሰት የጥበብ ሽግግር እንደሆነ ይገልፃል፡፡ አያይዞም  ‘ደራሲ’ የሚባለው ማነው; ለሚለው ጥያቄ መልስ ሲሰጥ ደራሲ ማለት፡ ጥበብን፣ ትምህርትን[ና] የዕውቀት መጻሕፍትን የሚደርስ ነው ይለናል። እንግዲህ አሁን ገበያውን ‘ከራስ አገዝ’ መፅሃፍት ጎን ለጎን እየገነኑበት ያሉት ‘ድርሰቶችስ’ የዕውቀት ሽግግር ላይ እንዴት ናቸው? ቋንቋን ለማሳደግስ ምን አስተዋፅኦ እያደረጉ ነው? ተነበው በልብ ይቀራሉ ወይስ ያቅራሉ? የነዚህ መፅሃፍት ‘ደራሲዎችስ’ እንደ ማእረግ ስያሜያቸው ጥበብን ያውጃሉ? ትምህርት እና ዕውቀትንስ ይሰብካሉን? አንባቢያቸውን ያዝናናሉ ወይስ ያሳዝናሉ? የዚህን ሁሉ ጥያቄ መልስ የአብዛኛውን መፅሃፍት ግማሽ ገፅ እንኳን ሳናገባድድ የምናገኝው ነው፡፡ ታዲያ ዘመኑን ማን እየደረሰው ነው? ብለን ስንጠይቅ ግን ድንጋጤ ሽው ይልብናል፡፡ ታዲያ ይሄን ሁሉ ዘመን ሸዋን የማያውቅ አንበሳ በጠራራ ፀሃይ ማሃል ፒያሳ ሲንጎማለል ላንደነግጥ ኑሯል?
Blurb እንደ ውዳሴ ከንቱ
መፅሃፍት ወደ ገበያው ከመውጣታቸው በፊት ለቅድሚያ ግምገማ ለአንዳንድ ሰዎች ሰጥቶ እርማት ማግኝት ትልቅ ብልህነት ነው፡፡ ነገር ግን የግምገማው አላማ ገበያ ተኮር ሲሆን ነገሩ ወደሌላ አቅጣጫ ይመራናል፡፡ ይህ እንግዲህ በብዙ መፅሃፍት ላይ የሚታይ ‘አዲስ’ ሂደት ነው፡፡ ለብ ለብ የሆነች፣ መናኛ የግጥም መድብል ያሳተመ አንድ ጎረምሳ ከመፅሃፉ ጀርባ አንድ ታዋቂ ‘የስነ ፅሁፍ’ ሰው ‹‹ካይን ያውጣህ አንተ ልጅ፡፡ የቃላት አመራረጥህ የFrost ተፅእኖ እንዳለብህ ያሳያል፣ ከፑሽኪንም ጋር መንትያነትክን መመስከር ሳይኖርብኝ አይቀርም፡፡ ምን አለፋችሁ አሁን የማስተዋውቃችሁ የሸክስፒርን አኩያ ነው፡፡›› ብለው አስተያየት ሰጥተው አንባቢው ተሸምቶ ይገዛና፤ እንዴት ነው ነገሩ? ብሎ ይጠይቃል፡፡
ስለቁንጅና ውድድር ማሰልጠኛ ይሆን ዘንድ አንዲት 30 ገፅ የማትሞላ ፅሁፍ ከጀርባዋ ‹‹እንደ ሀሳቡ ጥልቅ ቋንቋ፣ እንደ ውበት ሰባኪነቷ ባህልን አክባሪነቷ ያሰደምማል፡፡ በሌላ ዳጎስ ያለ ስራሽ ለማየት ቸኩያለሁ›› የሚል የአንድ ጉምቱ ‘ምሁር’ አስተያየት አይታችሁ መፅሃፉን ስታዩት በሆሊውድ ተዋንያን ምስል የተሞላ አልበም ሲሆንባችሁ፤ ምንድነው ከማለት ሌላ ምን ትላላችሁ?
እናም እጠይቃለሁ በመፅሃፍ ላይ የሚሰጥ አስተያየት (Blurb) ለማን ነው? ምንድን ነው? ውዳሴ ከንቱውስ የት ያደርሰን ይሆን?
‹‹ዘመን አይሽሬ (Classic) መፅሃፍ ቁጠር ብለው፣ ዴርቶጋዳ አንድ አለ››
በሃገራችን የስነፅሁፍ ታሪክ አጭር ነው ማለት ሁላችንም የሚያሰማማ ሀሳብ ነው፡፡ ስነ ፅሁፉ አድጓል ወይስ አላደገም የሚለው ጥያቄ ግን እንደ ቀዳሚው ቀላል ካለመሆኑም በተጨማሪ አከራካሪም ነው፡፡ ከ1950ዋቹ መገባደጃ እስከ 1970ዎቹ መጀመሪያ ያሉትን 15 ዓመታት የኢትዮጵያ የአማርኛ ስነ ፅሁፍ የፍካት ጊዜ ነበር የሚለው  በብዙሃኑ ተሰሚነት አለው፡፡ በዚህ ወቅት ነበር እነፍቅር እስከ መቃብር፣ ሌቱም አይነጋልኝ፣ አደፍርስ፣ ከአድማስ ባሻገር፣ አልወለድም የመሳሰሉት ብሉይ (Classic) የአማርኛ ድርሰቶች  የታተሙት፡፡ እስከ አሁንም የአማርኛ ድርሰት መለኪያ ሆነው ይቀርባሉ፡፡
እንግዲህ ከዚህ የፍካት ዘመን ወደፊት 40 ዓመታትን ስንቆጥር አሁን ያለንበት ወቅት ላይ እንደርሳለን፡፡ እናም ዛሬስ ምን ይፃፋል? ብለን ለመተየቅ እንወዳለን? አዎ ‘ዴርቶጋዳ’ ተፅፏል፡፡ ግን ግን ልካችን ዴርቶጋዳ ነውን? ዴርቶጋዳን ለማጠልሸት ሳይሆን፤ በእውነት ስነፅሁፋችን ለመታዘብ ያክል ነው ይሄን ያልኩት፡፡ ዴርቶጋዳ የዘመኑ ብሉይ (Classic ) ስራ ነው ካልን የነ ‘አደፍርስ’ ምትኮች ከወዴት አሉ?  ስለ ምንኖረው ህይወት የሚፅፍልን ደራሲስ ከወዴት ነው?

አንባቢውን ኢትዮጵያዊ ፍለጋ

ዓለምን እንዲሁ ልናውቃት አንችልም፡፡ ዓለሚቱን ለመገንዘብ ብዙ ግብዓቶች ያስፈልጉናል፡፡ እንደዛም ሆኖ ግን ዓለምን ሙሉ ለመሉ አናውቃትም፡፡ ስለ ዓለም ጥሩ የሆነ ግንዛቤ ያለው ሰው፤ ስለምድሪቱ ከሌሎች የተሻለ መረጃ አለው ማለት ነው፡፡ መረጃን ማግኛ መንገዶች ደግሞ ከሰው ሰው፣ ከቦታ ቦታ፣ ከጊዜ ገዜ ይለያያሉ፡፡ ፅሁፍ  ከሰው ልጅ ቀደምት የመረጃ ማግኛ ዘዴዎች አንዱና ዋነኛው ነበር/ነው፡፡ ፅሁፍ በአንድ ላይ ተጠርዞ ለአንባቢው ሲቀርብ ደግሞ መፅኃፍ የሚል ስያሜን ያገኛል፡፡

እንግሊዛዊው ባለቅኔ ጆን ሚልተን (1608 – 1674) እንዲህ ይላል ‹‹Who kills a man kills a reasonable creature, God’s image; but he who destroys a […] book, kills reason itself, kills the image of God, as it were in the eye.›› መፅኃፍ ማለት ምክንያት ማለት ነው እንደ ማለት፡፡ ያለምክንያት  ህይወት እንዴት ይሆናል?
መፅኃፍ መረጃን መስጠት አንዱ አላማው ቢሆንም ከዚህ ጋር ተያይዞ ማዝናናት እና ማበልፀግን እንደ ግብ አድርጎ መመልከትም ይቻላል፡፡

አለማቀፉ የመፅኃፍት እና የአንባቢ ግንኙነት

አል አረቢያ ቴሌቪዥን ባለፈው ሃምሌ ወር ሮይተርስን በመጥቀስ ያዎጣው ዜና የአረቡ አለም በንባብ ባህል በኩል በጣም ደካማ እንደሆነና ከምዕራብ ሀገሮች ጋርም ሲነፃፀር በጣም ያነሰ መሆኑን የገለፀ ሲሆን፤ ይሄም በአረቡ አለም ዘንድ አስገራሚ ተብሎ ነበር፡፡ በተጠቀሰው የምርምር ስራ መሰረት አንድ አረብ በዓመት ስድስት ገፅ ብቻ የሚያነብ ሲሆን በአንፃሩ ደግሞ አንድ አሜሪካዊ በዓመት አስራ አንድ መፅኃፍት እንዲሁም አንድ እንግሊዛዊ በዓመት ሰባት መፅሃፍት ያነባል በማለት ፡፡ ‹‹እኛ የአረቡ አለም ነዋሪዎች ልጆቻችን በዓመት ስድስት ደቂቃ ብቻ ለልጆቻችን የንባብ ጊዜ ስናበረክት፤ በአንፃሩ ምዕራባዊያን ቤተሰቦች ደግሞ በዓመት አስራ ሁለት ሽህ ደቂቃዎችን ለልጆቻቸው የንባብ ጊዜነት ያውሉታል›› ይላል፡፡

ይህ የሚያሳየው የንባብ ባህል መኖር በእድገት እና በብልፅግና ላይ የሚያደርሱት ተፅእኖ ትልቅ መሆኑን ነው፡፡ አዎ Readers are Leaders.

ኢትዮጵያዊው መፅሃፍ

ወደ ሃገራችን ኢትዮጵያ ስንመለስ፤ ያለውን የንባብ ባህል በምርምር ስራ አስደግፎ ያቀረበ ምርምር ስራ የዚህ ፅሁፍ ፀሃፊ ሊያገኝ አልቻለም ወይም ያሉትም የአንድ በጣም የተወሰነ ሁኔታን ብቻ የሚገልፁ ናቸው፡፡ ነገር ግን ተያያዥ ሁኔታዎችን አብረን በማየት ያለውን የንባብ ባህል እና የመፅኃፍ ስርጭት የሚያመለክት ስዕል ማስቀመጥ እንችላለን፡፡

ጊዜያዊ ወታደራዊ ደርግ ስልጣን በያዘ ማግስት አላማው ማርክሲስት-ሌኒኒስት ሕብረተሰብን ለመገንባት በማሰብ የመሰረተ ትምህርት ዘመቻ ካወጀ በኋላ፤ ማሀይምነትን ለማጥፋት በሚል ግብ በተደረገው ጥረት በኢትዮጵያ የሚገኙ መሀይማንን  ቁጥር ወደ ሀያ አራት በመቶ ዝቅ ለማድረግ ተችሎ ነበር፡፡ ለዚህም ስኬት በመላ ሀገሪቱ ከሰባት ሽህ በላይ ቤተ መፅኃፍት ተገንብተው እንደነበር በጊዜው የወጡ ሪፖርቶች ይገልፃሉ፡፡ ይሄም የማንበብ ባህልን ከማሳደግ አኳያ ታላቅ እምርታ እንደሆነ ማየት ይቻላል፡፡

ነገር ግን በወታደራዊ ዘመን የመፅኃፍት ሳንሱር በእጅጉ የበረታ ከመሆኑ የተነሳ መንግስታዊ ርዕዮተ ዓለም ከሆነው ማርክሲዝም- ሌኒኒዝም  ውጭ ሌሎች ሀሳቦችን የሚያንፀባርቁ መፅሃፍት ‘የአድሃሪያን’ ናቸው፣ ‘የኢምፔሪያለዝም ጭምቅ መርዞች’፣ ‘የአቢዮት ቀልባሾች ማንፌስቶ ናቸው’ ወ.ዘ.ተ በሚሉ አልባሌ ምክንያቶች የሚታተሙት መፅኃፍት በእጅጉ በተወሰኑ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ብቻ የሚያጠነጥኑ ነበሩ፤ ይሄም የንባብ ባህሉን እና የሀሳብ እንሽርሽሪቱን (Discourse) እድገት አንቆ ይዞት ነበር፡፡

ኢህአዴግ ስልጣን እንደያዘ የኢትዮጵያ ሰላማዊ እና ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ጉባኤ፤ የኢትዮጵያ የሽግግር ወቅት ቻርተርን አፀደቀ፡፡ ቻርተሩ ከያዛቸው ዋነኛ ነጥቦች መካከል ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ያፀደቀውን እና ኢትዮጵያም ፈራሚ የነበረችበትን ‹‹አለማቀፉን የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ(UDHR) ሙሉ ለሙሉ ተቀብላለች›› የሚለው ሃሳብ ይገኝበታል፡፡  ከነዚህ መብቶች አንዱ ሀሳብን በፈለጉት መንገድ የመግለፅ ነፃነት ነው፡፡ ይሄም በንባብ ባህሉ ላይ በአጠቃላይ፣ በመፅኃፍ ገበያውን ላይ ደግሞ በተለይ በአዎንታዊ መልኩ ተፅዕኖ እንደሚሳርፍበት በወቅቱ ተገል፡፡ ለዛም ይመስላል በኢህአዴግ መጀመሪያ የስልጣን አመታት በደርግ ጊዜ ታፍነው የነበሩ ድምፆች መተንፈስ የጀመሩት፡፡ ነገር ግን ከመፅኃፍት ገበያው ጎን ለጎን የግል ጋዜጦች ወደ ገበያው መግባታቸው አንባቢዎችን ከጠጣር (Hard) ወደ ስስ እና ለብ ለብ (Soft) የንባብ ባህል እንዲነዱ ተፅእኖ ፈጥሮባቸዋል፡፡ ይሄም መፅኃፍ ከጋዜጣ የደረሰበት የመጀመሪያው ጠንካራ ቡጢ ነበር፡፡

እንደዛም ሆኖ በነዚህ ዓመታት የመፅኃፍት ገበያው መልካም በሚባል ሁኔታ ላይ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በሂደት ግን የመፅኃፍት ገበያው እየተቀዛቀዘ መጣ፡፡ በ2001 ዓ.ም አካባቢ በሚዩዚክ ሜይ ዴይ የወጣ አንድ ሪፖርት እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያ ውስጥ የመማሪያ መፅኃፍትን ጨምሮ በቀን በአማካኝ አምስት መፅኃፍት ለህትመት ይበቃሉ፡፡ ይህ የሚያመለክተው በዓመት በመላ ሀገሪቱ በሁሉም ቋንቋዎች፤ በሁሉም ርእሰ ጉዳዮች ላይ የትርጉም ስራዎችን ጨምሮ ወደ 1800 አካባቢ መፅኃፍት ይታተማሉ ማለት ነው፡፡ ይሄን ቁጥር ለምሳሌ በአሜሪካ እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2010ዓ.ም በአሜሪካ ከታተሙት  ሶስት መቶ ሃያ ስምንት ሽህ ሁለት መቶ ሀምሳ ዘጠኝ (328,259) መፅኃፍት ጋር ስናነፃፅረው በሀገራችን የሚታተሙትን መፅሃፍት ቁጥር አናሳነት እንረዳለን፡፡

እንግዲህ ከ80 ሚሊዮን በላ ህዝብ ለሚኖርባት ሀገር ይህ ቁጥር እጅግ ትንሽ ቁጥር ከመሆኑም በላይ፡፡ የአንባቢውን ውስንነት እና የንባብ ባህሉን ውድቀት ያሳያል፡፡ ለመሆኑ መፅኃፍ ለምን ተዘነጋ?

መሀይምነት

ከ84 በመቶ በላይ ህዝብ በገጠር በሚኖርባት ኢትዮጵያ የመሃይሙ መጠንም በዚያው ልክ ብዙ እነደሚሆን መገም አያዳግትም፡፡ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2005 ዓ.ም፤ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (UNESCO) በወጣው ሪፖርት መሰረት 45 በመቶ ኢትዮጵያዊያን ብቻ የተማሩ (Literate) እንደሆኑ ሲገልጽ፤ ቀሪዎቹ 55 በመቶዎቹ ደግሞ ያልተማሩ (Illiterate) ናቸው ይላል፡፡ ይሄም የሚያሳየው ከግምሽ በላይ የሚሆኑት ኢትዮጵያዊያን አያነቡም አይፅፉምም ማለት ነው፡፡ በጣም የሚያስገርመው በመሰረተ ትምህርት ዘመቻ አመካኝነት ማንበብ እና መፃፍ ይችሉ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ዝንጋኤ ውስጥ (Memory loss) ሆነው የተማሩትን መዘንጋታቸው ነው፡፡ እናም የመሃይሙን ቁጥር ከፍ አድርጎታል፡፡

እንግዲህ በሀገሪቱ የመሃይማኑ ቁጥር ከተማረው ይልቅ ማየሉ በንባብ ባህሉ እና በመፅኃፍ ገበያው ላይ የሚያስከትለው ተፅእኖ ከፍተኛ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ይሄን ስንል ግን ተምረው – ያልተማሩትን (Functionally Illiterate) ማለትም ፊደል የቆጠሩ ነገር ግን ስለመፅኃፍ ምንም ሀሳብ የሌላቸውን ዜጎች ሳንጨምር ነው፡፡ 

ዕውቀት ተኮር ህብረተሰብ ወዴት ነው?

የመሃይማኑ ቁጥር ከላ እንደተቀስነው ከተማረው ዜጋ ቁጥር በላይ ቢሆንም፤ በተማረው ህብረተሰብ ዘንድ ያለው የመፅኃፍ ግንዛቤም ሌላው ከንባብ ባህሉ ጋር ተያይዞ መነሳት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ የንባብ ምሽቶች፣  የማንበቢያ ቦታዎች (Reading Buzz) መኖር፣ ህፃናት ለማንበብ ያላቸው ተነሳሽነት እንዲጨምር እየተሰሩ ያሉት ተግባራት ወ.ዘ.ተ ስንመለከት የችግሩ ስር ወዴት ሊሄድ እንደሚችል መገመት ያስችለናል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለንባብ ባህሉ እድገት የሰጡት ትኩረት ምን ያህል ነው? በዩንቨርስቲዎች ውስጥ ያሉት ንባብ ተኮር ዝግጅቶች ምን ያክል ናቸው? ተማሪዎች ‘የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግን’ እንዲመለከቱ ትኩረት ተሰጥቶ በሚሰራበት መጠን፤ ለመፅኃፍ ያላቸው ፍቅር እንዲያድግስ ይደረጋል ሆይ? እያልን ስንጠይቅ፤ መልሱን ለጥያቄዎቹ ከምንሰጠው መልስ ጀርባ እናገኝዋለን፡፡

ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ በሞቱ ወቅት የአሁኑ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስተር  እና የትምህርት ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል በሰጡት ቃለ ምልልስ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በእውቀት የተመሰረተ ህብረተሰብን ገንብተዋል›› ብለዋል፡፡ ይሄ እንዴት ይለካል? ነው ጥያቄው፡፡ ምን ማለትስ ነው?

‘የስክሪን ትውልድ’

ሌላው መፅኃፍን ያስረሳው ጉዳይ አዳዲስ ‘አማራጮች’ መስፋታቸው ነው፡፡ ከነዚህ አዳዲስ ክስተቶች አንዱ እና ዋነኛው የሲኒማው ዓለም ዘመነኝነት እና ተደራሽነት ናቸው፡፡ በአጭር ጊዜ፣ በግሩም ቴክኖሎጂ እና በተለያየ መልኩ የሚቀርቡት ሲኒማዎች ትውልዱ ለመፅኃፍ ጀርባውን እንዲሰጥ አድርጎታል፤ የሚለው መከራከሪያ ደግሞ በአንድ በኩል ይቀርባል፡፡ ግን ሲኒማ መፅኃፍን የማስረሳት አቅም አለው ማለት ይቻላል? አንዳንዶች ዘመነኞቹ መረጃን በቀላልና ክሽን ባለ መልኩ (Cooked) መፈለጋቸው ወደሲኒማው ዓለም እንዲያዘነብሉ አድርጓቸዋል ይላሉ፡፡

ነገር ግን እስኪ ስንቱ ሲኒማ ተመልካች ነው “Twilight” መጀመሪያ መፅኃፍ እንደነበር የሚያውቀው? ማነው “Avatar” አይቶ ከመፅኃፍ ላይ የተወሰደ ታሪክ እንደሆነ የሚያስተውለው? “Harry Potter” ተከታታይ ሰኒማን ተመልክቶ መፅኃፍ፤ በምእራቡ ዓለም እንደ ቅዱስ መፅኃፍ የሚመለክ መሆኑን ልብ ያለ ስንቱ ይሆን?

እንግዲህ ‘የስክሪን ትውልድ’ ተብሎ የተፈረጀው ዘመነኛ አይኑ ቴሌቪዥን ላይ እንደተተከለ መፅኃፍ አንብበው ሲኒማውን የሰሩትን ሰዎች እንዳደነቀ እዛው ሶፋ ላይ ይተኛል፡፡ እንዴት ነው?
የቀበሌው ‘ድራፍት ቤት’

መንግስትም እንደዋነኛ ባለድርሻ የመፅኃፉን ዋጋ ከፍ የሚያደርጉ ስራዎችን ይሰራ ዘንድ ከሚጠበቁ አካላት አንዱ ነው፡፡ በየምንኖርበት አካባቢ ያለውን ‘የድራፍት ቤት’፣ ካለው የቤተ መፅኃፍት ቁጥር ጋር አነፃፅረነው እናውቅ ይሆን? በመንግስት ድጋፍ የሚቋቋሙ ‘የድራፍት ቤቶች’ እንዳሉ ሁሉ፤ ምን ያክል ቤተ መፅሃፍተስ እንዲሁ ይቋቋማሉ? ብለን መጠየቅ መንግስት ለዘርፍ ምን ያህል ትኩረት ሰጥቷል? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ያስችለናል፡፡

‘ድራፍት ቤቶች’ መኖራቸውን ልቃዎም አይደለም፡፡ ነገር ግን በነሱ ትይዩስ ምን እየቀረበ ነው? ነው ጥያቄው፡፡ መንግስት በተለያዩ ፖሊሲዎቹ ትኩረት የሚሰጠው ልማት የአእምሮ ልማትን በቅጡ ያካተተ ነው ወይስ አይደለም? 

ይሄን ፅሁፍ ስንጀምር ከእንግሊዊው ባለቅኔ ጆን ሚልተን ‹‹መፅኃፍ ምክንያት ነው፤ መፅኃፍ ከሌለ ምክንያት የለም ››የሚለውን ሀሳብ ተንተርሰን ነበር፡፡ እናም የእኛ ምክንያታዊነትስ እያደገ ነው ወይስ በተቃራኒው? ብለን በመጠየቅ ሳባችን እንቋጭ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?

የመለስ ሞት ለምክር ቤቱ ምኑ ነው?


የኢፌድሪ ሕገ መንግስት ከፀደቀ የፊታችን ህዳር 29 ዓ.ም 17ኛ ዓመት የልደት በዓሉን ያከብራል፡፡ ይህ ኢትዮጵያ ካየቻቸው ቀዳሚ ሕገ መንግስቶች በተሻለ መጠን ሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን የሚቸረው እና የሀገሪቱ የበላይ ሕግ፤ ከያዛቸው አንቀፆች መካከል የመንግስቱን አይነት የሚደነግገው ክፍል በአንቀፅ 45 ላይ ምክር ቤታዊ ዲሞክራሲ (Parliamentarian Democracy) እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ አያይዞም የተዘረጋው ስርዓት ፌደራላዊ እንደሆነና፤ ይሄም አወቃቀር በ9 ክልሎች እና በአንድ ፌደራል / ማዕከላዊ መንግስት የተደለደለ መሆኑን ያስቀምጣል፡፡
እንዲሁም የፌደራሉ ምክርቤት ሁለት የተለያዩ አካላትን ያቀፈ እንደሆነ ገልፆ፤ እነዚህም አካላት ዋነኛ ተግባሩ ሕግ ማውጣት የሆነውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ዋነኛ ተግባሩ ሕገ መንግስቱን መተርጎም የሆነውን የፌደሬሽን ምክር ቤት ናቸው፡፡
በማስከተልም ከሁለቱ የፈደራሉ ምክር ቤቶች አንዱ የሆነው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ‹‹…የሥራ ጊዜ ከመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ እስከ ሰኔ ሰላሳ ነው›› በማለት የሕገ መንግስቱ አንቀፅ 58 ንዑስ አንቀፅ 2 ይደነግጋል፡፡ በዚህም መሰረት የፊታችን ሰኞ መስከረም 28/2004 ዓ.ም የኢፌድሪ ሕገ መንግስት ከፀደቀ ወዲህ ለ4ኛ ጊዜ የተመረጠው ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመኑን ይጀምራል ማለት ነው፡፡
አሁን ሥራ የሚጀምረው ምክር ቤት ከቀዳሚዎቹ ምክር ቤቶች የሚለየው ባለፉት 4 ምክር ቤቶች አባል የነበሩት እና በምክር ቤቱም ጉልህ ሚና የነበራቸውን  የቀድሞውን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ሳያካትት መከፈቱ ይሆናል፡፡ መለስ ለምክር ቤቱ፣ ምክር ቤቱ ለአቶ መለስ ምን እና ምን ነበሩ?
ምክር ቤቱ ያለ መለስ፤  ምን ሆነ?
በኢፌድሪ ሕገ መንግስት መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካሉበት ዋነኛ ግዴታዎች መካከል ‹‹ስለ ሀገሪቱ ሁኔታ፣ በመንግስት ሰለተከናወኑ ተግባራትና ስለወደፊት ዕቅዶች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየወቅቱ ሪፖርት ማቅረብ›› አንዱ ነው፡፡ አቶ መለስም በ17 ዓመት የጠቅላይ ሚኒስትርነት ዘመናቸው (የኢፌድሪ ሕገ መንግስት ከፀደቀበት ጊዜ ወዲህ) ይሄን ተግባር ሲያከናውኑ ነበር፡፡ ነገር ግን የጤናቸው ሁኔታ ጥሩ አይደለም ተብሎ ከአደባባይ ከጠፉበት ካለፈው ሰኔ አጋማሽ ጀምሮ ህልፈታቸው በመንግስት እስከ ተነገረበት የነሃሴ ወር አጋማሽ ድረስ ከዚህ ተግባራቸው ርቀው ነበር፡፡ 
በዚህም መሰረት በሕገ መንግስቱ የተቀመጠው እና አስገዳጅ የሆነው የምክር ቤቱ የስራ ማጠናቀቂያ  ሰኔ ሰላሳ ሊከበር አልቻለም ነበር (የእንግሊዘኛው የሕገ መንግስቱ ቅጅ አንቀፅ 58 ንዑስ ቁጥር 2 The annual session of the House shall … end on the 30th day of the Ethiopian month of Sene በማለት አስገዳጅ እንደሆነ ይነግረናል)፡፡ ምንም እንኳን ምክር ቤቱ የሥራ ጊዜየን ያራዘምኩት ከእርሳቸው መታመም ጋር በተያያዘ አይደለም ቢልም፡፡ አቶ መለስ የሌሉበት ምክር ቤት የምክር ቤቱን የሥራ ዘመን ማጠናቀቂያ ሕገ መንግስቱ ካስቀመጠው ቀን በላይ በማራዘም፤ የሕገ መንግስት ጥሰት ፈፅሟል ይላሉ የቀድሞው የኢትዩጵያ ፕሬዘደንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፡፡ 
ሌላው ምክር ቤቱ ያለ መለስ ምን የተለየ ነገር አደረገ? ብለን ስንጠይቅ የምናገኝው በምክር ቤቱ የ17 ዓመት ታሪክ ውስጥ የአስቸኳይ ስብሰባ የተጠራው ሁለት ጊዜ ብቻ ሲሆን፤ ሁለቱንም ጊዜ ባሳለፍናቸው ሶስት ወራት ውስጥ ነው ያካሄደው፡፡ የመጀመሪያው የቴሌኮምንኬሽን አዋጁን ለማፅደቅ፣ በሀምሌ ወር 2004 ዓ.ም አጋማሽ ሲሆን፤ ሁለተኛውን ደግሞ መስከረም 11/2005 ዓ.ም የአዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሹመት ለማፅደቅ ነበር፡፡ ይሄም ምክር ቤቱ ከመለስ በኋላ ምነው አስቸኮለው? እንድንል ይጋብዘናል፡፡
Economics 101ን ማን ያስተምራል?
አቶ መለስ ዜናዊ በሞት በመለየታቸው የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ ብቻ ሳይሆን አስረክበው ያለፉት፤ የምክር ቤቱን የመሪነት ሚናም ነው፡፡ መለስ በምክር ቤት ውስጥ በምጣኔ ሀብት ጉዳዮች ላይ አብዝተው ተከራካሪ እና ዝርዝር ማብራሪያዎችን ሰጭ እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ በተለይም በሶስተኛው ሀገር ዓቀፍ ምርጫ የተቃዋሚዎች ቁጥር በእጅጉ ከፍ ማለቱን ተከትሎ፤ መለስም የሚጠየቁት ጥያቄ እና ፈተናቸው በዛው ልክ ከፍ ብሎ ነበር፡፡ 
በሀገሪቱ የኑሮ ውድነት አሳሳቢ እየሆነ ነው፣ የዋጋ ግሽበትም ጣሪያ ነክቷል መንግስትዎ ምን ሊያደርግ አስቧል? ተብለው ሲጠየቁ፡፡ ማብራሪያቸውን የሰዋሰው ግድፈት በማረም ‹‹Fiscal እንጅ Physical አይደለም›› በማለት ይጀምሩ ነበር ኢኮኖሚስቱ መለስ፤ ለትዝብት በሚዳርግ መልኩ፡፡ አስከትለውም አዳም ስሚዝን ምክር ቤት ውስጥ እንደ እማኝ በመጥራት ‹‹የነፃ ገበያ መርሆዎችን አልጣስንም፣ ስሚዝንም አላስከፋንም፣ የኢትዮጵያ ገበሬም ስሚዝን አንብቦ ባያውቀውም በፖሊሲዎቻችን አስተዋውቀነዋል›› እያሉ ማስተማር ከዘወትር የምክር ቤት ተግባሮቻቸው አንዱ ነበር፡፡ 
ስለ ፍላጎት እና አቅርቦት ግንኙነት ትንታኔ በማቅረብ መንግስታቸው በኢኮኖሚው ላይ ለተፈጠረው ችግር ተጠያቂ እንዳልሆነና ተጠያቂዎቹ ‘አለማቀፍ ህብረተሰብ’፣ እንዲሁም ‘የመንግስት ሌቦች’ ናቸው እስከማለትም ይደርሳል የመለስ የምጣኔ ሀብት ምክር ቤታዊ ገለፃቸው፡፡
ስለ ምጣኔ ሀብት በምክር ቤት ቀርበው ማብራሪያ ከማብዛታቸው የተነሳ፤ ማብራሪያቸውን በቴሌዚዥን በቀጥታ የሚመለከተው ህዝብ በቅርቡ በኢኮኖሚክስ ዲፕሎማ ወይም የምስክር ወረቀት ማግኝቱ አይቀርም ተብሎ ይቀለድም ተጀምሮ ነበር፡፡ 
እንግዲህ መለስ ከዚህ በኋላ ኢኮኖሚክስ በምክር ቤት ያስተምሩ ዘንድ የህይወት ህግ አልፈቀደም፡፡ አዲሱ ተመራጭ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የአቶ መለስን ቦታ ተክተዋል፡፡ አቶ ሃይለማርያም የመለስን የምክር ቤት ትምህርት ይቀጥሉበታል (አላማየ የመለስን ውርስ ማስቀጠል ነው ማለታቸውን ልብ ይሏል) ወይስ አይቀጥሉበትም?  የሚለው በጊዜ ሂደት የሚታይ ጉዳይ ነው፡፡
በፓርላማው ብቸኛ ተቆጭ
አቶ መለስ በምክር ቤቱ ተገኙ ማለት ምክር ቤቱ ሞቅ ያለ ድባብ አለው፣ ማለትም ሌላው የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ መለስ በምክር ቤት ሲገኙ ‘ከተቃዋሚ ፓርቲዎች’ እስከ ‘ተራ ወንጀለኞች’፣ ‘ከአለማቀፍ የገንዘብ ድርጅቶች’ እስከ ‘አለማቀፍ የሰብዓዊ ተሟጋች ድርጅቶች’፣ ‘ከኢህአዴግ አባላት’ እስከ ‘መንግስት ሰራተኛው’ ድረስ መለስ የማይወርፉት አካል አልነበረም፡፡ 
‘ቆሻሻ’፣ ‘ያበዱ ውሾች’፣ ‘ኪራይ ሰብሳቢ’፣ ‘የመንግስት ሌባ’፣ ‘እነ ጭር ሲል አልወድሞች’ ወ.ዘ.ተ እያሉ የስድብ መአት የሚያዥጎደጉዱት መለስ፤ ማንንም አካል ከመገላመጥ አይመለሱም ነበር፡፡ ይሄም አንዳንዶች የሰውየውን ስብእና በመጥፎ መልኩ እንዲመለከቷቸው አድርጓቸው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት መድረክ የአመራር አባል እና የቀድሞው የኢትዮጵያ ምክር ቤት አባል የነበሩት ዶ/ር መረራ ጉዲና ‹‹አቶ መለስን እንዴት ያስታውሷቸዋል?›› ተብለው በአውስትራሊያው SBS ራዲዮ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመለስሱ ‹‹አቶ መለስን የማስታውሳቸው በፓርላማው ውስጥ ብቸኛው ተቆጭ እንደነበሩ ነው፡፡›› ብለዋል፡፡ ይህ እንግዲህ የመለስ የምክር ቤት ቆይታ ውርስ ነው፡፡ አቶ ሃይለማርያም በምክር ቤት እንዴት ይሆናሉ? ጊዜ ጌታ ነው መልሱ፡፡
‹‹ሳቃቸው መች ያስተኛል››
መለስን በምክርቤት የዋሉ እለት ምክር ቤቱ ከፍጥጫም ባለፈ ሳቅ እና ተረት ልማዱ ነበር፡፡ ከኤዞፕ እስከ አለቃ ገብረ ሀና ተረቶች በመለስ እያነሱ የምክር ቤት አባላትን ሲያስፈግጉ ነበር የሚውሉት፤ መለስ፡፡ በየመሃሉ የሚጥሏቸውም ቃላት ከማስከፋት አልፈው አንዳንዴ ፈገግም ያሰኛሉ፡፡ ባጭሩ መለስ በምክር ቤት የተገኙ እለት የምክር ቤት አባላት ሳቂታዎች ነበሩ፡፡ 
በምክር ቤቱ እንቅልፋቸውን በመተኛት ታዋቂ የነበሩ አንድ የምክር ቤት አባል ‹‹ምንድነው; ምክርቤት የገቡት ለመተኛት ነው እንዴ›› ተብለው ሲጠየቁ፡፡ ‹‹ኢጭ እንተኛስ ብንል ሳቃቸው መች ያስተኛል›› አሉ ተብሎ እስከ መቀለድም ተደርሷል፡፡ አቶ ሃይለማርያም እኒህን ‘እንቅልፋም’ አባል ከእንቅልፍ እየቀሰቀሱ ያማርሯቸዋል ወይስ ‘በሰላም እንዲተኙ’ ይፈቅዱላቸዋል? ጊዜን ማየት መልካም ይሆናል፡፡

ለውድ የዞን ዘጠኝ አንባቢዎች

የዞን ዘጠኝ ጦማር በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ እንዳይነበብ እየታገደ ለአንባቢዎች ስንል አዳዲስ ጦማሮችን እየፈጠርን ስለቆየን፣ ይህ (የመጀመሪያው) ጦማራችን ላይ የቀድሞዎቹን ጽሑፎች እንጂ አዳዲሶቹን ማግኘት አትችሉም፡፡ አሁን፣ ከመንግስት ጋር ፉክክሩን ስላልቻልነው፣ የምትችሉ ሰዎች አማራጮችን እየተጠቀማችሁ የምትጎበኙት የመጨረሻ ጦማራችንን ሊንክ እዚህ ይኸውላችሁ፡፡

የ2004 ዓ.ም. የጊዜ መስመር (timeline)

ይህን ጽሑፍ ለማዘጋጀት ስናስብ የትኞቹ ጉዳዮች ጉልህ ስፍራ ይኖራቸዋል የሚለውን ለመምረጥ  ብዙ ዐሳብ በህሊናችን ተመላልሷል፡፡ በአጠቃላይ ግን አብዛኛውን ሰው የሚያስማሙ ክስተቶችን ለማካተት የሞከርን ሲሆን በተለመደው ሚዲያ ስርዓት በመንግስትም ሆነ ‘ነጻ’ ሚዲያዎች  ትኩረት የተነፈጋቸውንም ለማካተት ጥረት አድረገናል፡፡እንደአለመታደል ሆኖ አማራጭ ትርክትን የሚያቀርብ የሚዲያ ተቋም በማጣታችን ምክንያት እነዚህ ጉዳዮች በወቅቱ ተቀራራቢ ሽፋን አለማግኘታው ከግምት ውስጥ ይገባልን ዘንድ እንጠይቃለን፡፡
መስከረም

የጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች መታሰር
መስከረም 4 ቀን 2004 ዓ.ም የአንድነት ለፍትህ እና ለዲሞክራሲ ፓርቲ አመራር አባላት የሆኑት አንዱአለም አራጌ እና ናትናኤል መኮንን እንዲሁም በኢትዮጵያ የግል ፕሬስ ከተፈቀደ ጀምሮ የተለያዩ ጋዜጦችን በዋና አዘጋጅነት እና በኋላም በተለያዩ ብሎጎች ላይ ስለ ሰብአዊ መብት መንግስትን በሚሞግቱ ፅሁፎቹ የሚታወቀው እስክንድር ነጋ ከሌሎች ተጨማሪ ተከሳሾች ጋር በአሸባሪነት ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡
አስናቀች ወርቁ ከዚህ አለም በሞት ተለየች
ታዋቂዋ ድምጸዊት እና የመድረክ ሰው አስናቀች ወርቁ በአመቱ መጀመሪያ በሞት ካጣናቸው የጥበብ ሰዎች አንደዋ ነበረች፡፡ አስናቀች ለረዥም ጊዜ በህክምና ስትረዳ ቆይታ መስከረም ወር 2004 አም 76 አመትዋ ከዚህ አለም በሞት ተለይታለች፡፡ አስናቀች እንደእየሩሳሌም በተሰኘው ታዋቂ ዘፈንዋ እንዲሁም በቀድሞ ጊዜ በነበሩ የመድረክ ስራዎችዋ ትታወቃለች፡፡
የትግራይ ፖሊስ ኦርኬስትራ ቡድን አባላት ላይ የመኪና አደጋ ደረሰባቸው
መስከረም 15 ቀን 2004 ዓ.ም ከትግራይ ክልል ተነስተው ወደ ሱዳን ሲገዙ በነበሩት የትግራይ ፖሊስ ኦርኬስትራ ቡድን አባላት ጭኖ ይጓዝ የነበረ አውቶቢስ ላይ የመኪና አደጋ ደረሰ፡፡
የደርግ ባለሥልጣናት በይቅርታ ከዕስር ተፈቱ
መስከረም 23 ቀን 2004 ዓ.ም በፍርድ ቤት የተወሰነባቸው የሞት ፍርድ ግንቦት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ወደ ዕድሜ ልክ እስራት መቀየርን ተከትሎ 16 ያህል የሚሆኑ የደርግ ባለስልጣናት የጠየቁት ይቅርታ በመንግስት ተቀባይነት አግኝቶ ከ20 አመት የእስር ቤት ቆይታ በኃላ በነጻ ተለቀቁ፡፡
ኢትዮጲያ የኤሌክትሪክ ሃይል ወደውጭ መላክ ጀመረች
መስከረም 24 ቀን 2004 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጅቡቲ በመገኘት 35 ሜጋ ዋት ከኢትዮጲያ በኤክስፖርት መልክ ማስተላለፍ የጀመረውን ማስተላለፊያ ጣቢያ መርቀው ስራ አስጀመሩ፡፡ ማተላለፊያ ጣቢያው የተገነባው ኢትዮጲያና ጅቡቲ የኤሌክትሪክ ሃይል ለመገበያየት የ25 አመት ስምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ ነበር፡፡ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የመብራት መቋረጥ ተከስቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ጥቅም


መድረክ ግንባር ሆነ
ጥቅምት 2 ቀን 2004 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክሪያሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ከፓርቲዎች ህብረት ወደ ግንባርነት መሸጋገሩን አስታወቀ፡፡ ወደ ግንባርነት መሸጋገሩ የበለጠ የተጠናከረ ሰላማዊ እና ዴሞክሪያሲያዊ ትግል ለማካሄድ እንደሚረዳው ገልፆ ነበር – ግንባሩ፡፡ በወቅቱ ዶ/ር መራራ ጉዲና ወደ ግንባርነት የተሸጋገርነው ግንባርን በግንባር ለመግጠም ነው የምትል ንግግር ጣል አድርገው ነበር፡፡
ስዊድናውያኑ ጋዜጠኞች ታሰሩ
ጥቅምት 9 ቀን 2004 ዓ.ም መንግስት አሸባሪ ድርጅትን አግዛችኋል እንዲሁም የሀገሬን ድንበር በህገ-ወጥ መንገድ ጥሳችሁ ገብታችኋል በሚል ሁለት የሲዊድን ዜግነት ያላቸው ጋዜጠኞች ላይ የመሰረተው ክስ መታየት ጀመረ፡፡ ሁለቱም ጋዜጠኞች ከአሸባሪ ድርጅት ጋር በተያያዘ የተመሰረተባቸውን ክስ ጥፋተኛ አይደለንም ሲሉ በሁለተኛው የሀሪቱን ድንበር በህገ-ወጥ መንገድ ጥሶ በመግባት የተመሰረተባቸውን ክስ አምነዋል፡፡ ጋዜጠኞቹ በቁጥጥር ስር ሲውሉ ከኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባር ተዋጊዎች ጋር ነበሩም ተብሏል፡፡
የመምህራን ደሞዝ ጭማሪ እና አድማ
መምህራን የተደረገላቸውን የደሞዝ ጭማሪ ከንቀት የሚቆጠር እና የሞያውን ክብር ዝቅ ያደረገ ነው በማለት ተቃውሞ አሰሙ፡፡ መምህራኖቹ የደሞዝ ጭማሪውን ቢቃወሙም መንግስት እና “የመምህራን ማህበሩ” ጭማሪ ሳይሆን የእርከን ማሻሻያ ነው ብለው ያስተባበሉ ሲሆን መምህራኑ በበኩላቸው ከደሞዛቸው ለማህበሩ የሚቆረጠው ገንዘብ እንዲቆምና ማህበሩ እንደማይወክላቸው ተናግረው ነበር፡፡ ጥያቄው እስኪመለስ ድረስ በተለያዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ትምህርት ለተወሰነ ጊዜ ተቁዋርጦ የነበረ ሲሆን የመንግስት አካላት የተለያዩ ድርድሮች በማድረግ ትምህርት እነዲቀጥል ማድረግ ችለዋል፡፡

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች መልስ ሰጡ
በተመሳሳይ ቀን የቀድሞ የኢፌደሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በ2004 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው መስከረም 30 ቀን 2004 ዓ.ም በፕሬዝዳንት ግርማ ቀርቦ የነበረውን የመንግስት አመታዊ መረሃ-ግብር ላይ ከምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች መልስ ሰጡ፡፡ በአሸባሪነት ተጠርጥረው ስለተያዙት የፖለቲካ ፓርቲ አባላት እና ጋዜጠኞች ተጠይቀው – በቂ መረጃ እስኪያገኝ ነው እንጂ በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች በሽብርተኝነት ተግባር ላይ መሰማራታቸውን መንግስት ካወቀ እንደቆየ አሁንም መረጃ እየተሰባሰበባቸው ያሉ በሽብርተኝነት ላይ የተሰማሩ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር አባላት እንዳሉ በመጥቀስ መልሰዋል፡፡ ሁለቱን ስዊድናዊያን በሚመለከትም የሀገሪቱን ድንበር ጥሰው ከሽብርተኛ ቡድን ጋር ታጥቀው እንደተያዙ እና እንደማንኛውም ሽብርተኛ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እንደሚታይ ተናግረው ነበር፡፡ ‹‹የነጭም ደም ቀይ ነው፤ የጥቁርም ደም ቀይ ነው… ጋዜጠኞቹ የአሜሪካንን ድንበር ጥሰው ታጥቀው ቢገኙ ማንም የኔ ናቸው ሳይሆን አላውቃቸውም ነበር የሚለው›› ብለው ነበር፡፡
አቶ ያረጋል አይሸሹም ንብረታቸው ታገደ
ጥቅምት 9 ቀን 2004 ዓ.ም የቤንሻንጉል ጉምዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትን በፕሬዝዳንትነት ያገለገሉት አቶ ያረጋል አይሸሹም በሳቸውና በቤተሰቦቻቸው ስም የተመዘገበ ማንኛውም ንብረት እንዳይንቀሳቀስ ታገደ፡፡ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ትዕዛዙን ያስተላለፈው የስነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና አቃቤ ህግ ግለሰቡን በሙስና ወንጀል በመጠርጠር ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ነበር፡፡
የንግድ ሚኒስትሩ እና ሚኒስትር ዲኤታው ከስልጣናቸው ተነሱ
የንግድ ሚንስቴር ሚኒስትር አቶ አብዱራህማን ሼክ መሐመድ እና ሚኒስትር ዲኤታው አቶ አሕመድ ቱሳ ከስልጣናቸው ተነሱ፡፡ የስልጣን ሽረቱ የተካሄደው የዋጋ ግዥበትን ለመቆጣጠር ለአምስት ወር ቆይቶ ያለምንም ውጤት እንዲነሳ የተደረገው የዋጋ ተመን ውድቀት ጋር በተያያዘ ባሳዩት የብቃት ማነስ መሆኑ ተገልጾ ነበር፡፡
የአወሊያ ተማሪዎች አመጹ
ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይግባ እና ስልጣን ላይ ያለው መጅሊስ አይወክለንም፤ በምርጫ ይተካልን በሚል ሰላማዊ በሆነ መንገድ ጥያቄያቸውን ማሰማት ጀመሩ፡፡በዚህ በአወሊያ ተማሪዎች የታገዱ መምህራኖቻችን ይመለሱ ጥያቄ ተነሳው የሙስሊሞች ጥያቄም በመጠንም ሆነ በይዘት ሰፍቶ ለወራት ዘለቀ፡


ህዳር

የኔሰው ገብሬ ራሱን አቃጠለ
ኢትዮጵያዊው መምህር የኔሰው ገብሬ ፍትህ መልካም አስተዳደር እና ልማት የለም በሚል አርብ ህዳር 1 ቀን 2004 ዓ.ም አቃጠለ፡፡
ዳዊት ከበደ እና አቤ ቶኪቻው ከአገር ተሰደዱ፡፡
ህዳር 5 ቀን 2004 ዓ.ም ታዋቂው የፍትህ ጋዜጣ አምደኛ አቤ ቶኪቻው ህዳር 9 ቀን ደግሞ የአውራምባ ጋዜጣ ባለቤትና ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ከአገር ተሰደዱ፡፡ አበበ ቶላ ለ6 ወራት የደህንነት መስሪያ ቤት መታወቂያ የያዘ ሰው በተለያየ መንገድ ጫና እና ክትትል ሲያደርግበት መቆየቱን የገለጸ ሲሆን የዳዊትን መሰደድ ተከትሎ ደግሞ አውራምባ ታይምስ ጋዜጣም ተዘጋ፡፡
ኢትዮጲያ ወታደሮቿን ዳግም  ወደ ሱማሌ ላከች
ህዳር 15 ቀን 2004 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ በተደረገው የኢጋድ ጉባዔ ኢትዮጲያ ለአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ሃይል እገዛ ሚያደርግ ሃይል ወደ ሶማሊያ እንድትልክ አባል ሃገራት ተስማሙ፡፡ በስምምነቱ መሰረትም የኢትዮጲያ ወታደሮችዋን በድጋሚ ወደ ሶማሊያ ላከች፡፡


ታህሳስ
የሁለት ምርጫዎች ወግ መጸሃፍ ተመረቀ
ታህሳስ 10 ቀን 2004 ዓ.ም የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤትን በበላይነት የሚመሩት አቶ በረከት ስምኦን ‹‹የሁለት ምርጫዎች ወግ›› ሲሉ የሰየሙትን መጽሐፋቸውን ለንባብ አቀረቡ፡፡መጽሐፉ ለሽያጭ የቀረበው በ90.00 ብር  ሲሆን በሸራተን ሆቴል በተካሄደው ምርቃት ስነስርአት ላይ ሼህ አላሙዲን መጻሃፉን ባያነቡትም በጣም ጥሩ እንደሆነ ተናግረው ነበር፡፡፡
በብርጋዴር ጀነራል ከማል ገልቹ የሚመራው ኦነግ የመገንጠል አቅዋሙን እንደቀየረ ገለጸ
በብርጋዴር ጄነራል ከማል ገልቹ የሚመራው ኦነግ የመገንጠል ሃሳቡን ከፕሮግራሙ ላይ ማንሳቱን አሳወቀ፡፡ በሜኒሶታ ከተደረገው ልዩ ስብሰባ በሁዋላ ጄነራሉ እንደተናገሩት የሁሉንም ብሄሮች  መብቶች እና እኩልነትን ያረጋገጠች ኢትዮጲያን መመስረት እነደሚደግፉ ገልጸዋል፡፡በዚሁ መግለጫ ላይ ኦነግ ለኦሮሞ ህዝብ ነጸነት ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጲያውያን ነጸነትም እንደሚታገል አንዲሁ ተገልጹዋል፡፡


ጥር

የኤርታሌ ቱሪስቶች በታጣቂዎች ጥቃት ተፈፀመባቸው
ጥር 9 ቀን 2004 ዓ.ም በአፋር የኤርታሌን አካባቢ ለመጎብኘት በቦታው የነበሩ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች እና ኢትዮጲያዊያን አስጎብኚዋቻቸው ላይ ታጣቂዎች ጥቃት ፈጸሙ፡፡በጥቃቱም 5ቱን ጎብኚዎች ሲገደሉ 2ቱን በከፍተኛ ሁኔታ ቆስለው 2 ኢትዮጵያዊያን እና 2 የውጪ ዜጋ ጎብኚዎች ደግሞ ታፍነው ተወሰዱ፡፡ጥቃቱ የተፈፀመው ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ከሚዋሰኑበት ድንበር 25 ኪ.ሜ አካባቢ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት ለጥቃቱ ሽብርተኞችን እያሰለጠነ ወደ ኢትዮጵያ ይልካል ያለውን የኤርትራ መንግስት ተጠያቂ አድርጎ ነበር፡፡
የአፍሪካ ሕብረት ሕንፃ ተመረቀ
ጥር 18 ቀን 2004 ዓ.ም በቻይና መንግስት እርዳታ የተገነባው አዲሱ የአፍሪካ ህብረት ህንፃ ተመረቀ፡፡ በአዲሱ ህንፃ ቅጥር ጊቢ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ወቅት ምዕራባዊ አፍሪካዊት ሀገር ጋናን ይመሩ የነበሩት የክዋሜ ንክሩማ ማስታወሻ ሀውልት የቆመ ሲሆን በወቅቱ የኢትዮጵያ አቻቸው የቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ ሀውልት አለመሰራት ጥቂት የማይባሉ ኢትዮጵያንን አስከፍቶ ነበር፡፡
አወዛጋቢው የሊዝ አዋጅ ፀደቀ
ጥር 30 ቀን 2004 ዓ.ም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በአመቱ ለሁለተኛ ጊዜ የሕዝብ ተወካች ምክር ቤት ተገኝተው መንግስት ተግባራዊ እንዲሆን ያስፀደቀውን የመሬት ሊዝ አዋጅ በተመለከተ ማብራሪያ ሰጡ፡፡አዋጁ ከጸደቀ በኃላ በሰጡት በዚህ ማብራሪያ ላይ ስለ መንግስት ሌቦች እና የግለሰብ ሌቦች በመሬት ዙሪያ ያለውን ችግር እንዳባባሱት ተናገሩ፡፡


የካቲት

አንዱአለም ተደበደበ
የካቲት 7 ቀን 2004 ዓ.ም. አንዱአለም አራጌ በእስር ቤት ውስጥ ድብደባ ተፈፅሞበታል ሲል አንድነት ፓርቲ አስታውቀ፡፡ አንዱአለም በድብደባው ምክንያት ጭንቅላቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት ተዘግቦ የነበር ሲሆን የአንዱዋለም ጉዳዩን በሚገባ የሚያብራራ ጹሁፍ በፍትህ ጋዜጣ በኩል ለንባብ በቅቶ ነበር፡፡
ደራሲና ጋዜጠኛ ስብሃት ገብረ እግዚአብሔር አረፈ
የካቲት 12 ቀን 2004 ዓ.ም ደራሲ ስብሃት ገብረ እግዚአብሔር በህክምና ሲረዳ ቆይቶ  በተወለደ በ76 አመቱ ከዚህ አመት በሞት ተለየ፡፡ በትኩሳት፣ሌቱም አይነጋልኝ እና በአምስት ስድስት ሰባት መጸሃፍቶቹ የሚታወቀው ጋሽ ስብሃት አድናቂዎቹ እና ባልደረቦቹ በተገኙበት የቀብር ስነስርአቱ በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን ተፈጸመ፡፡
ደራሲና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ አረፉ
የካቲት 23 ቀን 2004 ዓ.ም ደራሲና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ፡፡ የ54 መጻህፍት ደራሲና ተርጓሚ የነበሩት አቶ ማሞ የ82 አመት ባለፀጋ እና የ6 ልጆች አባት ነበሩ፡፡ ቀብራቸውም የካቲት 24 ቀን 2004 ዓ.ም. በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡

የዩኒቲ ኮሌጁ ዶ/ር ፍስሐ ተሰደዱ
የካቲት 29 ቀን 2004 ዓ.ም የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ መስራችና ባለቤት የነበሩት ዶ/ር ፍሰሐ እሸቱ ከሀገር ተሰደዱ፡፡ ዶ/ር ፍስሐ ሀገር ለቀው ለመውጣት የተገደዱት ከአስር በላይ አዋጪ የሚሏቸውን የንግድ ሃሳቦች ወደ ተግባር ለውጦ ለሀገርን ለወገን ጥቅም እንዲሰጡ የነበራቸው ህልም በመንግስት ምክንያት እውን መሆን ስላልቻሉ መሆኑን ተናግረው ነበር፡፡ ሙሉ ሰአታቸውንም የኢትዮጲያ ብሔራዊ የሽሽግግር ጉባዔ Ethiopian National Transition Council (ENTC) ለማቋቋም እንደሚያውሉም ተናግረዋል፡፡


ጋቢት     
       
 የኢትዮጵያ ጦር የኤርትራ መንግሥት ላይ  የማጥቃት እርምጃ ወሰደ
መጋቢት 6 ቀን 2004 የኢትዮጵያ መንግስት የኤርትራ መንግስት እና “የተላላኪዎቹን” የጥፋት  ማዕከላትን ማውደሙን አስታወቀ፡፡በአፋር ክልል በጉብኝት ላይ የነበሩትን ቱሪስቶች ላይ መግደሉንና ማሰቃየቱን የሚል ሰበብን እንደመነሻ ምክንያት በመውሰድ  በሦስት ካምፖች ተሰባስቦ  የነበረውን የኤርትራ መንግስት ሀይል ላይ ወታደራዊ እርምጃን ወስዷል፡፡የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የኢንዶክትሬሽንና የሕዝብ ግንኙነት ማዕከል ኃላፊ ኮሎኔል ገብረ ኪዳን ገብረ ማርያም ለኢዜአ  እንደገለጹት ሠራዊቱ ማለዳ ላይ ባደረሰው ጥቃት በሦስት ካምፖች ተሰባስቦ  የነበረውን ኃይል ለማውደም ተችሏል። ኮሎኔሉ ዝርዝሩ ወደፊት ይፋ ይደረጋል ማለታቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘገባ በወቅቱ ቢያመለክትም ይህ የጊዜ መስመር እስከተዘጋጀበት ሰዓት ድረስ ያገኘነው መረጃ የለም፡፡
የወልድባ ገዳም እና የስኳር ልማት ፕሮጀክት
በዋልድባ ገዳምና በወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት መካከል  አለመግባባት ተፈጠረ፡፡የኢትዮጵያ ስኳር ልማት ኤጀንሲ ከያዛቸው የስኳር ማስፋፊያ  ፕሮጀክቶች አንዱ የሆነው የወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት ግድብ ግማሽ ክፍል የገዳሙ ክልል ውስጥ መገንባቱ ፣ በገዳሙ ያረፉ ቅዱሳን አፅም መነሳቱ  ፣በገዳማውያኑ የሚተዳደሩ ሦስተ አቢያተ ክርስቲያናት መነሳታቸው ክርክሩን ያስነሱ ሲሆን ችግሩን ለመፍታት መነኮሳቱ አዲስ አበባ ድረስ ደርሰው  በጠቅላይ ቤተ ክህነት እና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት የደረሰባቸው  አላግባብ ያለሆነ ማንጓጥና እንግልት ጉዳዩን የበለጠ አባብሶታል ተብሎዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ እና በሌላው አለም በሚገኙ ምእመናን አለም አቀፍ ተቃውሞሞ ደርሶበታል፡፡ መንግስት በአደባባይ ብዙ መግለጫዎችን በመስጠት ውይይቶች  ማካሄዱን ቢገልጹም በድብቅ ደግሞ መነኮሳቱን በማስፈራራት እና በማሰር እየታማ ጉዳዩ በእንጥልል እንደቆመ አለ፡፡
የዝቋላ ገዳም ቃጠሎ
ሊበን ዝቋላ ወረዳ አዱላላ ከተማ የሚገኘው የዝቋላ ደብረ ከዋክብት ጻድቁ አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ገዳም በሚገኝበት ተራራ  ላይ በመጋቢት 8 ቀን 2004 ዓ.ም ቀትር  የተነሣው የእሳት ቃጠሎ ሁለት ጋሻ መሬት የሚሸፍን ደን  አወድሞ በቁጥጥር ስር ዋሎዋል ፡፡ በእሳት አጥፊ አውሮፕላን ወይም ሄሊኮፕተር በሚረጭ ኬሚካል በመንግስት በኩል አለመመደቡ መንግስትን ቢያሳማውም ከአዲስ አበባ እና ሌሎች የአከባቢው ከተሞች የሚገኙ ነዋሪዎችና የፌዴራል ፖሊስ አባላት ባደረጉት ከፍተኛ ርብርብ ቃጠሎው  በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡
የአማራ ተወላጆች ከደቡብ ክልል ጉራ ፈርዳ መፈናቀል
1000 ያህል የአማራ ተወላጅ አባወራዎች ከደቡብ ክልል ቤንች ማጂ ዞን ጉራ ፈርዳ ወረዳ ተፈናቀሉ፡፡ አነዚህ አባወራዎች ከአማራ ክልል በተለያዩ የድርቅ ወቅቶች በሰፈራ ኑሮዋቸውን የመሰረቱ ሲሆኑ ለረጅም አመታት በቦታው መኖራቸውን ይናገራሉ፡፡ እነዚህ አባ ወራዎች መሬታቸውን ተቀምተው የተፈናቀሉ ሲሆን ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በመላው ኢትዮጲያ አንድነት ድርጅት(መኢአድ) ጹ/ቤት ቅጥር ጊቢ ውስጥ ተጠልለው ነበር፡፡ በወቅቱ የአቶ ሽፈራው ሽጉጤ አስተዳደር ዜናውን ከእውነት የራቀ ሲል አስተያየት መስጠቱ ይታወሳል፡፡
የፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ያልተጣራ ዜና እረፍት
የኢ.ፌ.ድ.ሪ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ በልብ ህመም ምክንያት ማረፋቸው የተገለጸው መጋቢት 4 2004 ዓ.ም. ነበር፡፡ መንግስት  እንደተለመደው ማስተባበያው በተገቢው ጊዜ አለማቅረቡ ወሬው እንዲዛመት አስተዋእጾ ያደረገ ሲሆን ብዙዎች የቀብሩ ቀን መች እንደሆነ በሚጠባበቁበት ሰዓት ኢዜአ ፕሬዚዳንቱ ለተለመደ የጤና ምርመራ በሳውዲ አረቢያ እንደሚገኙ በመግለጹ ወሬው ቀስ በቀስ ከሚዲያ ጠፍቷል፡፡


ሚያዝያ

የአለም ደቻሳ ጥቃትና ሞት
በሊባኖስ የኢትዮጲያ ቆንስላ ቢሮ በር ላይ በአሰሪዋ ስትደበደብ የታየችው አለም ደቻሳ ከጥቂት ቀናት በሁዋላ ራስዋን አጠፋች መባሉን ተከትሎ ኢትዮጲያውያንን በአለም አቀፍ ያስቆጣ ክስተት ነበር፡፡የአለምን ሞት ተከትሎ የተለያዩ አካላት አጋርነታቸውን የሚያሳይ የተለያዩ ዝግጅቶች በአለም አቀፍ ደረጃ የተካሄዱ ሲሆን ለቤተሰቦችዋም በገቢ ማስገኛ ፕሮግራሞች ድጋፍ ተደርጎላቸዋል፡፡ የአለም ሞት በወቅቱ ከአልጀዚራ ጀምሮ የተለያዩ ታለላቅ የአለም ሚዲያዎች ከፍተኛ ሽፋን ተሰጥቶት ነበር፡፡
እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ዜና እረፍት
እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ በጨጓራ አልሰር ምክንያት አዲስ አበባ በሚገኘው ካዲስኮ ጠቅላላ ሆስፒታል በህክምና ሲረዱ ቆይተው ሚያዝያ 02/2004 ዓ.ም ምሽት 2 ሰዓት 45 ደቂቃ ላይ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ በሀገራቸውና በአውሮፓ ለረጅም ዓመታት የሥነ ጥበብ ሙያን የተማሩ ሲሆን በሀገራቸውና በዓለም አቀፍ ደረጃም በተለያዩት ጊዜያት በርካታ የስዕል አውደ ርዕዮችን በማቅረብ ትልቅ አድናቆትንና ክብርን ለመጎናጸፍ ችለዋል። ሚያዝያ 6 ቀን 2004 ዓ.ም. የቀብራቸው ሥነ ሥርዓት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እኩለ ቀን ተፈጽሟል፡፡
የቴዲ አፍሮ አራተኛ አልበም ተለቀቀ
ሚያዝያ 6 ቀን 2004 ዓ.ም ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ጥቁር ሰው ሲል የሰየመውን አራተኛ አልበሙን ለቀቀ፡፡ በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ካገኘው ሶስተኛው አልበሙ ቀጥሎ በተፈጠሩ ሁኔታዎች ድምጻዊው ለረጅም ጊዜ አዲስ ስራ አለማቅረቡ በከፍተኛ ጉጉት እንዲጠበቅ አድርገውታል፡፡ አልበሙ በስርጭት ብዛት እና በሽያጭ ገቢ ከፍተኛ ከሚባሉት የሙዚቃ ስራዎች መካከል መመደብ ችሏል፡፡ይሁንና አልበሙ ሙዚቀኛው በፊት ከነበረው የተሻለ ብቃት አለማሳየቱን ብዙዎች ቢገልጹም አልበሙ ተወዳጅነት አልቀነሰውም፡፡

ግንቦት

ጋዜጠኛ አበበ ገላው መለስ ዜናዊን በአደባባይ ነቀፈ
ግንቦት 10 ቀን 2004 ዓ.ም በቡድን ስምንት ሀገራት የመሪዎች ጉባዔ ላይ ጋዜጠኛ አበበ ገላው መለስ ዜናዊን በአደባባይ ነቀፈ ፡፡በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ግብዣ መሰረት በምግብ እህል ራስን መቻል አስመልክቶ የሚደረግ ውይይት ላይ ለመሳተፍ ዋሽንግተን ዲሲ የተገኙት የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ በምግብ እህል እራስን መቻል አስመልክቶ በሚያደርጉት ንግግር  መሐል ላይ በስፍራው በነበረው ጋዜጠኛ አበበ ገላው የተቃውሞ ድምፅ ንግግራቸውን በድንጋጤ አቋረጡ፡፡ ጋዜጠኛ አበበ ገላው ‹‹መለስ ዜናዊ አምባገነን ነው፣ እስክንድር ነጋንና ሌሎችም የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ፣ መለስ ዜናዊ የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈፅመዋል፣ ያለነፃነት ስለምግብ አታውሩ” ብሎ ሲናገር ተደምጧል፡፡ይህም ዜና በሀገር ውስጥ ሚዲያዎች(ከፍትህ ውጪ) ሽፋን ባያገኝም በማኀበራዊ መካነ ድሮች እና ሌሎች የዜና አውታሮች ዜናውን ተቀባብለውታል፡፡በተለይ የኢሳት ቴሌቪዥን ጉዳዩን የበለጠ ትኩረት መስጠት ጋዜጠኛ አበበ ገላውን በማናገር ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሚዲያ ሽፋን መራቅ ጋር በማያያዝ ከፍተኛ የጤና መቃወስና የመንፈስ መረበሽ እንደደረሰባው ለማሳመን ጥረት አድርገዋል፡፡


ሰኔ

የሴቶች ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ አለፈ
የኢትዮጰያ የሴቶች እግር ኳስ ብሄራዊ ቡድንም ቅዳሜ ሰኔ 9/2004 የታንዛኒያ አቻውን 1 ለ 0 አሸንፎ ለአፍሪካ ዋንጫ አለፈ፡፡ይህን ተከትሎ ከተለያዩ አካላት ማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡በኢኳቶሪያል ጊኒ አስተናጋጅነት የሚከናወነው 8ኛው የአፍሪካ ሴቶች እግር ኳስ ዋንጫ ኢትዮጵያ ከካሜሩን፣ አይቮሪኮስትና ናይጄርያ ምድብ ተደለደላለች፡፡
የዶ/ር እሌኒ ገ/መድህን  የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ለቀቁ
ሰኔ 11 ቀን 2004 ዓ.ም የኢትዮጵያ ምርት ገበያ መስራች እና ዋና ስራ አስፈፃሚ የነበሩት ዶ/ር እሌኒ ገ/መድሕን ስራ አስፈፃሚነታቸውን በራሳቸው ፈቃድ እንደሚለቁ አስታወቁ፡፡ ስራቸውን የሚለቁት ምርት ገበያው ሲመሰረት ጀምሮ በታቀደው የመተካካት መርሕ መሰረት ሲሆን ስልጣናቸውን ቀደም ሲል የአቢሲኒያ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ለነበሩት አቶ አንተነህ አሰፋ እንደ ሚያስረክቡ ተናግረዋል፡፡
 እርሳቸው ገበያው ሲመሰረት ጀምሮ በታቀደው መተካካት መሰረት እንደለቀቁ ቢናገሩም በመንግስት በኩል ጫና እንደደረሰባቸውና ለሚዲያ ይፋ ያልሆኑ ከገንዘብ ጋር የተያያዙ ችግሮች መኖራቸውን የተለያዩ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡
የቴሌኮም ማጭበርበር ሕጉ
የቴሌኮም ማጭበርበርን ለመከላከል በሚል ሽፋን መንግስት የተለያዩ የመገናኛ መንገዶችን ከልክለዋል ተብሎ የታማበት የቴሌኮም ማጭበርበር ረቂቅ አዋጅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ፡፡ በዚህ በመረጃ ደህንነት መረብ መስሪያ ቤት የተረቀቀው አዋጅ ዙሪያ ከፍተኛ የአለም አቀፍ የሚዲያዎች የተለያዩ ፕሮግራሞች የሰሩ ሲሆን እነደተለመደው የመንግስት ማስተባበያ በአቶ ሽመልስ ከማል በኩል ዘግይቶ ቀረበ ሲሆን ስካይፕ እና የንግድ ያልሆኑ ግንኙነቶችን ህጉ አይከለክልም ሲሉ አቶ ሽመልስ አብራሩ፡፡ነገር ግን ህጉ ያለምንም ጠንካራ ማሻሻያ በሃምሌ መጀመሪያ በተወካዮች ምክር ቤት በአስቸኩዋይ ጉባዔ ጸደቀ፡፡


ሐምሌ

በአሸባሪነት የተከሰሱት ተፈረደባቸው
ሐምሌ 6 ቀን 2004 ዓ.ም የከፍተኛው ፍርድ ቤት ሶስተኛ ወንጀል ችሎት አንዱአለም አራጌን፣ ዶ/ር ብርሀኑ ነጋን፣ አንዳርጋቸው ፅጌን እና ፋሲል የኔአለምን በእድሜ ልክ ፅኑ እስራት፤ እስክንድር ነጋን፣ ኦባንግ ሜቶን፣ ፀጋስላሴ ዘለቀን፣ ናትናኤል መኮንን እና ክንፈሚካኤል ደበበን በ18 አመት ፅኑ እስራት፣ ጋዜጠኛ አበበ ገላው እና አበበ በለውን በ15 አመት ፅኑ እስራት እንዲሁም የአዲስ ነገር ጋዜጣ መስራች እና ኤዲተር የነበሩት አብይ ተክለማሪያምን እና መስፍን ነጋሽን የ8 አመት ፅኑ እስራት ወስኖባቸዋል፡፡ የቅጣት ፍርዱ የተሰጠው ሰኔ 10 ቀን 2004 ዓ.ም የዋለው ችሎት ተከሳሾችን በተከሰሱበት የሽብርተኝነት እና ሽብርተኝነትን የማገዝ ወንጀል ጥፋተኛ ናቸው ብሎ መወሰኑን ተከትሎ ነው፡፡
መለስ የሌሉበት የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ተካሄደ
ሐምሌ 7-8 ቀን 2004 ዓ.ም የአፍሪካ ህብረት 19ኛው መደበኛ የመሪዎች ጉባዔ በአዲስ አበባ ተካሄደ፡፡ ጉባዔው አዲስ አበባ ላይ እንዲካሄድ የተወሰነው እንድታዘጋጅ የተመረጠችው ማላዊ ጉባዔውን በሌላ ሀገር እንዲካሄድ ከጠየቀች በኃላ ነበር፡፡ በጉባዔው ላይ ኢትዮጵያ የተወከለችው በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ሲሆን ይህም ጠቀላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከሪዮ 2012 የከባቢ አየር ውይይት ላይ ከሌላው ጊዜ ከስተው እና ጤና ያጡ መስለው ለመጨረሻ ጊዜ ከታዩ በኃላ እየጠነከረ የመጣውን ጠ/ሚኒስትሩ በጠና ታመዋል የሚለውን ወሬ ይበልጥ አጋጋለው፡፡ አቶ መለስ ዜናዊ የሽግግር መንግስት ፕሬዚደንት ሆነው ስልጣን ከያዙ አንስቶ የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ ላይ ሳይሳተፉ ሲቀሩ የመጀመሪያ ጊዜያቸው ነበር፡፡
የሙስሊሙ ማህበረሰብ ተወካዮች ታሰሩ
በከፍተኛ ብልጠት ለወራት ሳይቁዋረጥ የቀጠለው የሙስሊሞች ተቃውሞ ተወካዮቻቸው በመታሰራቸው ወደ ሌላ ምእራፍ ተሸጋገረ፡፡ያልተፈቀደ የሰደቃ ስነስርአት ማካሄድ አይቻልም የተባለውን የመመንግስትን ክልከላ ተከትሎ አወልያ ትምህርት ቤት ውስጥ በምሽት  በመንግስት ሃይሎች እና በሙስሊሞች መካከል ግጭት የተፈጠረ ሲሆን በተከታዩቹ ቀናት የሙስሊሙን ህብረተሰብን የሚወክለው ኮሚቴ አባላት ለእስር ተዳረጉ፡፡የኮሚቴው አባላት ክስ የጠመሰረተባቸው በሽብርተኝነት ሲሆን አራዳ ፍ/ቤት ቀርበው የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸዋል፡፡
 ፍትህ ጋዜጣ ከዝውውር ውጪ ሆነች

በተለያዩ ጠንካራ ትችቶችን መንግስት ላይ በማቅረብ የምትታወቀው ፍትህ ጋዜጣ በፍትህ ሚ/ር ትእዛዝ የአንድ ሳምንት ከተቁዋረጠች በሁዋላ ብርሃን እና ሰላም ማተሚያ ቤት አላትምም በማለቱ ፍትህ ጋዜጣ ከዝውውር ውጪ ሆናለች፡፡ዋና አዘጋጅዋ ተመስገን ደሳለኝም ተከሶ ፍርድ ቤት ቀርቦ ለ1 ሳምንተ ያህል ከታሰረ በሁዋላ አቃቢ ህግ ባልታወቀ ምክንየት ተጨማሪ መረጃ ለመሰብሰብ ክሱን አቁዋርጦታል፡፡

ነሐሴ

የለንደን ኦሎምፒክ እና ኢትዮጵያውያን አትሌቶች
ከሐምሌ 20-ነሐሴ 6 ቀን 2004 ዓ.ም 30ኛው የኦሎምፒክ ውድድር በእንግሊዝዋ ዋና ከተማ  ተካሄደ፡፡የአትሌቲክሱ አንድ ዘርፍ በሆነው በሩጫ ብቻ ነበር፡፡ በዚህም 3 የወርቅ 1 የብርና 3 የነሐስ በጠቅላላው 7 ሜዳሌያዎችን ማግኘት ችላለች፡፡ የወርቅ ሜዳሌያዎቹን ያስገኙት በሴቶች በ10 ሺህ ሜትር ጥሩነሽ ዲባባ፣ በሴቶች ማራቶን ቲኪ ገላና እና በሴቶች 5 ሺህ ሜትር መሰረት ደፋር ናቸው፡፡ ብቸኛው የብር ሜዳሊያ ደግሞ በወንዶች 5 ሺህ ሜትር በደጀን ገ/መስቀል የተገኘ ነው፡፡ በወንዶች 10 ሺህ ሜትር ታሪኩ በቀለ፣ በሴቶች 10 ሺህ ሜትር ጥሩነሽ ዲባባ እና በሴቶች 3 ሺህ ሜትር መሰናከል ሶፊያ አሰፋ የነሐስ ሜዳሊያዎቹን ያመጡ አትሌቶች ናቸው፡፡ ከውድድሩ ጋር ተያይዞ የአንዳንድ አትሌቶች ብቃት መውረድ እና ከውድድሩ ተሳታፊዎች በላይ ቁጥር ያላቸው የልዑካን ቡደኑ አባላት ወደ ስፍራው ማምራታቸው ከፍተኛ ክርክርን አስነስተዋል፡፡
ብፁህ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አረፉ

ነሐሴ 9 ቀን 2004 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትሪያርክ የነበሩት አቡነ ጳውሎስ ባደረባቸው ህመም አረፉ፡፡ ስርአተ ቀብራቸውም ነሐሴ 17 ቀን 2004 ዓ.ም በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈፀመ፡፡ ብፁህነታቸው የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ለመምራት ከተመረጡበት 1984 ዓ.ም ጀምሮ ለ20 አመታት በፓትሪያርክነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡

መለስ ዜናዊ አረፉ
ነሐሴ 15 ቀን 2004 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክሪያሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ መለስ ዜናዊ ነሐሴ 14 ቀን 2004 እኩለ ሌሊት 5፡40 ላይ መሞታቸውን የሚኒስትሮች ካቢኔ መግለፁን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ይፋ አደረገ፡፡ የኢፌደሪ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ለአራተኛ የምርጫ ዘመን በማገልገል ላይ የነበሩት አቶ መለስ የሁለተኛ አመት የህክምና ትምህርታቸውን ካቋረጡበት ከ19 አመታቸው ጀምሮ ህይወታቸው በፖለቲካ ትግል እና ስልጣን የተሞላ ነበር፡፡ የአቶ መለስ ዜናዊ ብሔራዊ የቀብር ስነ-ስርዓት ብዛት ያላቸው አፍሪካውያን እና ሌሎች መሪዎች በተገኙበት ነሐሴ 27 ቀን 2004 በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡ አቶ መለስ የሁለት ሴት እና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነበሩ፡፡

ከመለስ በኋላ!

በአዲስ አበባ ዪኒቨርስቲ የፍልሰፍና መምህር እና ከጥቂት የአደባባይ ምሁራን አንዱ የሆነውን ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋን አነጋግረን  ስለወቅቱ ማሕበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ የተለያዩ  ሐሳቦችን ማቅረባችን ይታወሳል፡፡አሁን ደግሞ የአቶ መለስን ‘ድንገተኛ!?’ ሞት  ተከትሎ በድኀረ-መለስ  አትዮጵያና በሌሎች ተያያዥ ጉዳየች ዙሪያ እንደተለመደው ገዢ ሐሳቦቹን ሰጥቶናል፡፡ መልካም ንባብ

የመርዶው ሕዝባዊ ምላሽ
እንደሚታወቀው ለሀያ አንድ አመታት በሙሉ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥኑን መስኮት አጣበው ይዘውት የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መለስ ዜናዊ ናቸው፡፡እንዲሁም በከፍተኛ ሁኔታ ተክለ ስብዕናቸውና ስራቸውን በሚዲያው ሲገነባላቸው የቆዩት ጠቅላይ ሚኒስተር በድንገት የህይወታቸውን ህልፈት ህዝቡ ሲሰማ  ድንጋጤና ሀዘን ፈጠሮበታል፡፡ይህንንም የህዝብ  ሀዘን በሁለት አቅጣጫ ልናየው እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው አስከሬናቸው ከውጭ ሀገር በገባበት ምሽት ከተጠበቀው በላይ ህዝብ ወጥቶ ብሶቱን እና ሀዘኑን ገልጿል፡፡ ምናልባትም ህዝብ ላሳየው የሐዘን ጎርፍ አንድ ወሳኝ የሆነ ነገር መገንዘብ የምንችለው ህዝቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ፓርቲው ከሚያራምደው የጎሳና የነገድ ፖለቲካ ውጪ እንደአንድ ኢትዮጵያዊና እንደግለሰብ አይቶ እንዳዘነላቸው መረዳት አያስቸግርም፡፡ በተጨማሪም  እሳቸው በህይወት እያሉ ለያይተው ያዩት ህዝብ ሲሞቱ ግን እርስ በርስ ሳይለያይ በህይወት እያሉ ያላያያዙትን ህዝብ በሞታቸው ሊያያይዙት ችለዋል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ እየተመለከትን ያለነው የህዝቡን ስሜት ለፖለቲካ ግብአታቸው ለመጠቀም ስትራቴጂ ነደፈው ፣ በተደራጀ መልኩ እንቅሰቃሴ ውስጥ መግባታቸውን ነው፡፡ ከዚህም አኳያ መንግስት ሊያደርግ የሚፈልገው አቶ መለስ ኖረም አልኖረም ህዝቡ የስርዐቱን መቀጠል እንደፈለገና ተቀባይነትም እንዲኖረው ማድረግ ነው፡፡ ይህንንም ለመተግበር በብሔራዊ የቀብር ስነ ስርዓት አስፈጻሚ ኮሚቴ ስም የህዝቡን ስሜት ወደፈለጉት አቅጣጫ ተቆጣጥሮ ለማዞር የሚያስችል ኮሚቴ ተቋቋሞ በስራ ላይ እያየነው ነው ፡፡ በመሆኑም መልስ አዘል ጥያቄ በማቅረብ ህዝቡ እንዲናገር በማደረግ ፣ በየሰፈሩ ድንኳን በመትከል ፣ በካዴሬዎች አማካኝነት በየመስሪያ ቤቱ መመሪያ በመስጠት ወዘተ… የህዝቡን ስሜት ለፖለቲካ ግብዐት እየተጠቀሙበት ይገኛል፡፡ለማጠቃለልም ብዙ ሀዘንተኞች የተጀመረው ፕሮጀክት ከፍጽሜ  እንዲደርስ በርግጥ ቢጠይቁ የመንግስት ኮሚቴ እንደተመኘው  የኢህአዴግን ስርዓት ቅጥያ ሲጠይቁ አልተደመጡም ፡፡ ምን አልባትም ህዝቡ በፕሮጀክት እና በስርዐት መካከል ያለውን ልዩነት የተረዳ ይመስላል፡፡
የስልጣን ሽግግር
የደህረ መለስ መንግስት ምን አይነት የፖለቲካ መንገድ እንደሚይዝ ከመተንተናችን በፊት  ወደኃላ መለስ ብለን ከቅርብ ታሪካችን እና ከፖለቲካ አንጻር ጥቂት በእንበል፡፡
ሀ. ከታሪክ ማህደር
ዶ/ር ሌቪንን “Wax and Gold” በተሰኘው መጽሐፍ ገጽ 152 ላይ  እንዲህ ይላል፡፡
“Successors to the throne were not determined according to fixed rule like primogeniture. Membership in the Solomonian line was normally a prerequisite……Usually however there were several legitimate candidates for the position and the absence of fixed procedures for choosing among the meant that the death of an emperor was often a time of confusion and political improvisation.” 
“የመንበሩ ወራሾች በተደነገገ ቋሚ መመሪያ አልነበረም የሚወሰኑት፡፡ በሰለሞናዊ ስርወ መንግስት መስመር ውስጥ አባል መሆን በጥቅሉ እንደቅድመ ሁኔታ የተቀመጠ ነው… በተለምዶ፣ ምንም እንኳን ቦታውን የሚመጥኑ ብዙ ሕጋዊ(ሰለሞናዊ) እጩዎች ቢኖሩም፣ አንዱን ለመምረጥ የሚያስችል ውሱን መስፈርት ባለመኖሩ የንጉሠነገሥት ሞት ሁልጊዜም ውዥንብር እና ፖለቲካዊ ፈጠራን/ውሳኔን ይጠይቃል፡፡” (ትርጉም የዞን ዘጠኝ)
በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ሰላማዊና ሕጋዊ የሆነ የስልጣን ሽግግር በአብዛኛው ተካሄዶ አያውቅም፡፡ እንደ ዕውቁ ሶሾሎጂስት አገላለጽ ይህም የሆነበት ምክንያት
 •   አንደኛ የስልጣን ሽግግር ህጉ በደንብ አለመቀመጡ
 •  ሁለተኛ ስልጣን ለመያዝ (ዘውድ ለመጫን)  የሰለሞናዊ ስርወ-መንግስት የግዴታ ተወላጅ  መሆንና
 •   በአንድ ጊዜ  ከሰለሞናዊው ስርወ መንግስት ተወላጅ የሚሆኑ ብዙ ተወዳዳሪዎች ለቦታው ብቁ ሆነው መገኘታቸው፤

በመሆኑም ወደ ኢህአዴግ ዘወር በምንልበት ጊዜ ከላይ የጠቀስናቸው ታሪካዊ ክፍተቶች ዛሬም እንደትላንቱ ኢህአዴግም የዘረጋው ስርዓት አልተሻገራቸውም፡፡ ይህንንም ስንል  በሕገ መንግስቱ ላይ በግልጽ የሰፈረ   ቋሚ የስልጣን ሽግግር ህግ የለም፡፡ በተጨማሪም ትላንት ዘውድ ለመጫን የሰለሞናዊው የዘር ሀረግ አስፈላጊ እንደነበረው አሁን ደግሞ ስልጣን ለመጨበጥ የኢህአዴግ አመራር መሆን የግድ ነው፡፡በመሆኑም ለሰለሞናዊው የሽግግር ጥያቄም ሆነ ለአሁኑ ጊዜ በርካታ ተቀራራቢ ዕጩዎች ወይም ተወዳዳሪዎች መኖራቸው ሽግግሩን ውስብስብ እና አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡
ለ. ከፓለቲካ ዳራ
አሁን ለተነሳው የሽግግር ጥያቄ መልስ ለማግኘት የጠቅላይ  ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ አመራር ምን አይነት  መልክ የያዘ ነበር የሚለውን ማወቅ ይገባናል፤ምክንያቱም በየትኛውም የዓለማችን ክፍል እንደሚታየው የስርዓቱ ዲሞክራሲያዊ ወይንም ኢ-ዲሞክራሲያዊ መሆን  በስልጣን ሽግግሩም ላይ ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡ ምንአልባት ይህንን ዐሳብ የበለጠ ለማብራራት የሀኛያው ክፍለ ዘመን የፓለቲካ ፍልስፍና መምህርት ከነበረችው ሐና አረንት  (Hanna Arendt) ትንሸ እንውሰድ፡፡
እንደ ሐና አረንት አመላካከት የዴሞክራሲያዊ ስርዓት አገዛዝ የ’ስልጣን መርህ’(authority principle) ሲከተል  ኢ-ዲሞክራሲያዊ አገዛዝ በአንጻሩ ደግሞ በ’መሪ መርህ’ (leadership principle) ይተዳደራል፡፡ በ’ስልጣን መርሕ’ የስልጣን ተዋረዱና ክፍፍሉ  በሀገሪቱ ህግ በዝርዘርና በግልጽ ተለይቶ ይቀመጣል፡፡በሌላ በኩል በ’መሪ መርሕ’  የሚታዳደሩ ሀገሮች ግን ይህን በተመለከተ የስልጣን ተዋረድ የላቸውም፡፡ ስልጣኑ ተጠቃሎ በመሪው እጅ ይገኛል፡፡ከመሪው ቀጥሎ ሁለተኛ የሚባል ለይስሙላ ይቀመጣል እንጂ መሪው አንድ ነገር ቢሆን በሁለተኛ ደረጃ የተሰየመው ሰው ይተካዋል ማለት አይደለም ፡፡ ለማጠቃለል የሀና አረንት አቀራረብ የሚያስተምረን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ማለት ከ’መሪ መርህ’ ወደ ‘ስልጣን መርህ’ መሸጋገር  ማለት ነው ፡፡ በኢትዮጵያ ሀገ መንግስታዊ ሰርዓት ሲዘረጋ ይህ ታስቦ ቢሆንም የዲሞክሪያሲያችን ጨቅላነት የመሪዉን ጫንቃ መሸከም ስላቀታት ዴሞክራሲው በአጭሩ ተቀጭቶ በ’መሪ መርህ’ ለመመራት በቅተናል፡፡
ድኅረ መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያ (Post; Capital ‘P’ or Small ‘p’)
የእንግሊዘኛውን ‘post’ የሚለውን ቃል ለሁለት ከፍለን ብንመለከተው ለትንተናችን አመች ይሆናል፡፡  ካፒታል ‘ፒ’ እና ስሞል ‘ፒ’ ብለን እንከፍለዋለን፡፡ ካፒታል ‘ፒ’ ተጠቅመን ድህረ(Post) ስንል consequential  መሰረታዊ የለውጥ ሂደቶችን  የካተተ ማለት ሲሆን ባንጸሩ ስሞል ‘ፒ’  ስንጠቀም ደግሞ መሰረታዊ ያልሆነና ፋይዳ ያለው ለውጥና ሽግግር የማይታይበት ሆኖ እናገኛዋለን፡፡  ለምሳሌ በአረብ ሀገራት በቅርቡ የተነሳው አብዮት  መሰረታዊ የስርዓት ለውጥ ስላስከተለ ካፒታል ‘ፒ’   ነው፡፡በሌላ በኩል  ከአንዋር ሳዳት ወደ  ሙባረክ  የነበረው ሽግግር ግን ምንም የስርዓት ለውጥ ስላልታየበት  ስሞል ‘ፒ’  ነው ፡፡
ከሁሉ አስቀድሞ ከላይ በትንሹ ልንጠቅሰው እንዳሰብነው አሁን አመራር ላይ ያሉት ባለስልጣናት የድህረ መለስን ስርዓት እንዳለ እንዲቀጥል እና ሽግግሩም ስሞል ፒ’  እንዲሆን ይፈልጋሉ፡፡ለዚህም ነው አስቀድመው “የፓርላማ አባላቱን በአስቸኳይ ሰብስበን አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝን ከጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስቴርነት  ወደ ቋሚ ጠቅላይ ሚኒስቴርነት እንለውጣለን” የሚል ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት፡፡
መንግስት እንዳሰበው የስርዓቱ ሕልውና በምንም መልኩ ጥያቄ ውስጥ የገባ እንዳልሆነ በየጊዜው የሚነግረን ቢሆንም ብዙ የአደጋ ቀጠናዎች እንዳሉ ግን እየተገነዘብን ከላይ ወደ አነሳነው  ወደ  አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ መመረጥ ፖለቲካ አንድምታ ላይ እንመለስ፡፡
ከአቶ ኃይለ ማርያም ምርጫ ዙሪያ ሁለት ጥያቄዎች ማንሳት እንችላለን፡፡ አንደኛ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የኢህአዴግ መሪዎች ‘የስልጣናችን ምንጭ (legitimacy) የሚፈልቀው  በትጥቅ ትግሉ ውስጥ በከፈልነው መስዋዕትነትን’  ሲሉ ቆይተው በዚህ ጎዳና ያላለፈ ሰው መምረጣቸው ፤ ሁለተኛ  ደግሞ ሌሎች አንጋፋ ፓርቲዎች እያሉ ኢህአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኃላ የተመሰረተ ፓርቲ አባል መሆናቸው ስለሳቸው ሳይሆን በግንባሩ የፖለቲካ ህይወት  ወሳኝ  ሚናን ስለሚጫወቱት አካሎች የሚነግረን ነገር አለ፡፡
ይህንን ለመረዳት ከሁለት ዓመት በፊት ከኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር መካከል አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ እንዴት የምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴርነትን ሹመት እንዳገኙ ማስታወስ ይገባናል፡፡ በዚህ ወቅት ፓርቲው  በመተካካት ጥያቄ እና በጠቅላይ ሚኒስቴሩ ጤና መቃወስ ምክንያት ተወጥሮ ነበር፡፡በዚህም ጊዜ በጣም የሚያስገርመውና የሚያስደምመው የህወሓት ልሂቃን ሁለት አማራጭ ይዘው ቀረቡ፡፡አንደኛ በአገሪቱ ላይ ዴሞክራሲ እንዳይቀጭጭ ከተፈለገ እና እኛ የምንወክለው የሕዝብ ቁጥር አነስተኛ ስለሆነ የጠቅላይ ሚኒስቴሩን ቦታ  ከብአዴን እና ኦህዴድ ብንመርጥ የግንባራችንን የሀይል ሚዛን ሲለሚያዛባው  በኛ በኩል ተቀባይነት የለውም የሚል ዐሳብ አቀረቡ፡፡ሁለተኛ የጠቅላይ ሚኒስቴሩን ጽ/ቤት ለሶስት ወይንም ለሁለት በመክፈል የስልጣን ክምችቱን( premiership ) ብናሰራጨው የተሻለ ይሆናል አሉ፡፡በመሆኑም የመጀመሪያው ዐሳብ በግንባሩ ተቀባይነት በማግኘቱ ከሁለቱ ብዙኃን ፖርቲ ውጪ የሆነ ሰው በምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴርነት ለመምረጥ በቅተዋል፡፡  ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ ሀገሪቱን ለሌሎች ስጋቶች ስለሚያጋልጣት ተቀባይነት አላገኘም፡፡
አሁን ለጊዜው የሀገሪቱ የፖለቲካ አቅጣጫ ወይም የሽግግር ሁኔታ ካፒታል ‘ፒ’ ወይንም ስሞል ‘ፒ’ ይሆናል ለማለት አስቸጋሪ ቢሆንም በዚህ ጉዳይ ላይ ተጽእኖ የሚፈጥሩ አራት ዐበይት  ወቅታዊ ጉዳዮች አሉ፡፡
 1. የአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የፖለቲካ ደረጃ አጠያያቂነት በራሳቸው አመራር እንዳይሄዱ ሰርዓቱ የማይፈቅድላቸው በመሆኑ
 2. የኦሮሚያ ክልል ፕሬዘዳንት አቶ አለማየሁ አቶምሳ ቦታ በህመም ምክንያት ክፍተት በመፍጠሩ እና ከዚህም ጋር ተያይዞ የሚነሳው ውዝግብ
 3. በኢትዮጵያ ሙስሊሞች እና በመንግስት መካከል የተነሳው ውዝግብ እልባት አለማግኘት
 4. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ህልፈት ተከትሎ ቀጣዩን ፓትርያርክ የመምረጥ ሂደት 
መደምደሚያ
እንደሚታወቀው ኢህአዴግን የሚያዋቅሩት የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉም እኩል  ናቸው ቢባልም በኦርዌሊያን (George Orwell) አነጋገር “ሁሉም ፓርቲዎች እኩል ናቸው አንዳንድ ፓርቲዎች ግን የበለጠ እኩል ናቸው” እንዳለው ልክ ከጠቅላይ ሚኒሰቴር ጽ/ቤት ባለነሰ የህወሓት ሊቀመንበር ቦታ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ህይወት ላይ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው አጠያያቂ አይደለም፡፡ ይሄ ፓርቲ የበላይነት እና የገዢ ስፍራውን ለረጅም ጊዜ ማስቀጠል ይፈልጋል፡፡ ይሄንን ለመተግበር አሁን ለማደረግ እንደተፈለገው  ከሌላ (ማለትም ብዙኃን ቁጥር ከሌለው)ፓርቲ በመሾም አሊያም ከራሱ ፓርቲ ሰው መልምሎ በማቅረብ በምንም መልኩ የስልጣን ባለቤትነቱን ለማረጋገጥ ይፈልጋል፡፡

ተቃዋሚውን ማን ገደለው?

ባለፈው ሳምንት ማነው ተቃዋሚው በሚል ርዕስ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲ መንደር የቆበትን አፋፍ፣ እንዲሁም ለሞት የበቃበትን ጉዞ ለማየት ሞክረናል፡፡ ዛሬ ካለፈው ፅሁፍ የቀጠለውን እና የተቃዋሚው ጎራ አሁን ላለበት የመቃብር ህይወት ያበቁትን ጉዳዮች በወፍ በረር እናያለን፡፡

ተቃዋሚው ሞቷል ወይስ አለሞተም? ተብሎ ክርክር ቢነሳ አልሞተም ብሎ ለማረጋገጥ እና የህያዉን ተቃዋሚ ቋሚ አካል ማሳየት እጅግ ፈታኝ ነው፡፡ በተለይም አሁን ባለንበት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር አንፃር፡፡ ስለዚህም አዎ ነብሱን ይማረውና ተቃዋሚውማ ሞቷል ማለትን መርጫለው፡፡ አልአዛርን ይሆናል አይሆንም በቀጣዮቹ ጊዜያት በሚከሰቱት ክስተቶች እና በድኑ በሚሰጠው ምላሽ ይወሰናል፡፡ እናም ለዛሬ ተቃዋሚውን ማን ገደለው; በማለት እንጠይቃለን፡፡ ዋነኛ ተጠርጣሪዎችንም እንመረምራለን:: የግድያው ተካፋዮችን አንድ ባንድ ለማየት እንሞክር፡፡


የሰው ልጅ ራሳቸውን ከሚያጠፉ እንስሳት አንዱ እና ዋነኛው ነው፡፡ የሰው ልጅ ራሱን ማጥፋቱ ያልተፈታ ከባድ እንቆቅልሽ ነው፡፡ ለምን ሰው ራሱን ይጠላል? ራሱንስ እንዴት ይገድላል? የሚለው ጥያቄ ዘመናትን ተሻግሮ እሰከ አሁን ድረስ  ቁርጥ ያለ ምላሽ ባያገኝም መነሻው ይሄ ነው እየተባለ መገመቱ  ግን አልቀረም፡፡ በዋነኛነትም በዘር የሚወረስ ራስን ማጥፋት (Biological Factors)፣ በስነልቦና ችግር የሚመጣ ራስን ማጥፋት ( Psychological Factors) እንዲሁም በማህበረሰባዊ ችግሮች ምክንያት የሚከሰት ራስን ማጥፋት (Sociological Factors) ይጠቀሳሉ፡፡

ታዲያ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ የሞተው ራሱን አጥፍቶ ይሆን? ካጠፋስ በየትኛው ምክንያት ይሆን ራሱን ያጠፋው? በሶስቱ መነሻዋች እንመልከተው እስኪ፡፡

በዘር የወረሰው ራስን የማጥፋት አባዜ ((Biological Reasons)፣) በኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ ከተጀመረ ግማሽ ምዕተ ዓመት እንኳን ያልሞላው ሲሆን ፓርቲ በመመስረት ወደ ፖለቲካው የገቡት ፖለቲከኞች በቀይ ሽብር- ነጭ ሽብር ተጠምደው አንዱ አንዱን ሲያሳድድ የተሸነፍው ራሱን ደብቆ መኖር ሲከብደው ራሱን ከሀገር በማሰደድ ፖለቲካዊ ራስን ማጥፋት ፈፅሟል፡፡ ይሄ ራስን የማጥፋት አባዜ ዛሬ ላለው ተቃዋሚ ከቀዳሚዎቹ በዘር ውርስ ተላልፎ እራሱን አጥፍቶ ይሆን?

በስነ ልቦና ችግር የሚመጣ ራስን የማጥፋት አባዜ (Psychological Reasons)፡ ሳይኮአናሊስቱ ሲግመንድ ፍሮይድራስን ማጥፋት ዋነኛው መነሻው የበዛ ራስን መጥላት (Self Hate)ነው ይለናል፡፡ ከፍሮይድ ተከትለው የመጡ ሳይኮሎጂስቶችም የፍሮይድን ሀሳብ በማጠናከር ሰው ከራሱ ጋር የሚፈጥረው ፀብ በሞት አሸናፊነት ይጠናቀቃል ይሉናል፡፡ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ምናልባትም ራሱን አጥፍቶ ከሆነ ራስን መጥላት ምክንያት ሊሆን ይችላልን? ‹‹ለዚህ ሁሉ ዓመታት ታግየ ምንም ውጤት ማምጣት ካልቻልኩ መኖሬ ምን ሊረባ? እኔስ ለምን ቆሜ እሄዳለው?›› በማለት ራስን ማጥፋት እንደ ግለ ሂስ ቆጥሮት ይሆን?

በማህበረሰባዊ ችግሮች ምክንያት የሚከሰት ራስን ማጥፋት (Sociological Factors)፡ ፈረንሳዊው የስነ-ህብረተሰብ ሊቅ ኤሚል ዱርክሄም በህብረተሰቡ ውስጥ ተቀባይነት ማጣት እንደሁም የግንኙነት መላለት ሰዎችን ወደ ራስን ማጥፋት ይመራቸዋል በማለት ራስን ማጥፋት ማህበረሰባዊ ምክንያት አለው ይላል፡፡ ታዲያ የኢትዮጵያ ተቃዋሚስ ህብረተሰቡ አልተቀበለኝም ብሎ ራሱን አጥፍቶ ይሆን? ወይስ የአባላት እና የደጋፊዎች ቁጥር ማነስ ህብረተሰቡ ለኔ ያለውን ጥላቻ ያሳያል ብሎ ራሱን አጠፋ ይሆን?

የቤተ መንግስቱ ገዳይ (Cold Blooded Murderer from the Palace)

ራሱን አጥፍቶ ሊሆን ይችላል ከሚለው ጥርጣሬያችን በማስከተል የሚቀርበው ሌላው ተጠርጣሪ ደግሞ መኖሪያውን ከወደ ቤተመንግስት ያደረገ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ይህ ተጠርጣሪ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በስልጣን ላይ የቆየ ሲሆን በህግም የብዝሃ-ፓርቲ አስተዳደርን (Multi Party System) የፈቀደ ተጠርጣሪ ነው፡፡ ነገር ግን ሁለት ሀገር ዓቀፍ ምርጫዋችን ያለምንም ችግር ከ98 በመቶ በላይ ድምፆችን በማምጣት ለማሸነፍ የቻለ ሲሆን ሶስተኛው ላይ ግን ችግር ገጥሞት ነበር፡፡ ‹‹እባካችሁ ተጠናክራችው ግጠሙኝ፣ የሚፎካከረኝ አጣሁ እኮ›› ሲል የነበረው ተጠርጣሪ ሳያስበው ህዝቡ ለተቃዋሚዎች የሰጠው ድምፅ አስበርግጎት አለማቀፍ ተቋማት ሳይቀሩ ‹‹አፍረሀል›› ቢሉትም ‹‹እንደተለመደው በሰፊ ድምፅ ማሸነፍ ባልችልም አሁንም ድሉ የኔ ነው›› በማለት ስልጣኑን አልለቅም አለ፡፡

አይ እኛ ነን አሸናፊዎቹ ያሉትን ተቃዋሚዎችም ክፉኛ አቁስሎ ለአአልጋ ቁራኛ፣ ለደዌ ዳኛ አብቅቷቸዋል፡፡ ይባስ ብሎም በቁስል ላይ እንጨት እየሰደደ አንዳንዴም በርበሬ እየነሰነሰ ስቃያቸውን በማባባስ ስልጣኑን ለማራዘም ሞክሯል፡፡ በመጨረሻም አዳዲስ ህጎችን በማውጣት የተቃዋሚውን ግብዓተ መሬት እየሳቀ ከፈፀመ በኋላ አራተኛውን ሀገራዊ ምርጫ 99.6 % ድምጽ በማምጣት ‹‹አሸንፌአለሁ›› በማለት ‹‹ቧልት›› አሰምቷል፡፡

ለዚህም ማሰረጃ የሚሆኑት ሰነዶች ተጠርጣሪው ሟችን የሚያጥላሉ ፅሁፎችን በተደጋጋሚ በልሳኑ እንዲሁም በመንግስት ሚዲያዎች ሲያሰማ የነበረ መሆኑ፣ ምንጮቻቸው ከሰለጠኑት ሀገራት ነው በማለት የተለያዩ አፋኝ ህጎችን ማውጣቱ፣ በተደደጋጋሚ ሲያደርጋቸው የነበሩት ተግባራት በጥቅሉ ሲታዩ ተቃዋሚውን የገደለው የአራት ኪሎው ተጠርጣሪ ይሆን እንዴ? ያስብለናል፡፡

ቅጥር ነብሰ ገዳይ (Mercenary)

ይሄ ተጠርጣሪ ቅጥረኛ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ከአራት ኪሎ ተጠርጣሪ ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚጠረጠር ነው፡፡ ለመጠርጠሩ ዋነኛ ምክንያት የሆነው ደግሞ ከሟች (ተቃዋሚው) ጋር አብሮ አደግ ከመሆኑም በተጨማሪ አብረው የሚበሉና አብረው የሚጠጡ ጓዶች የነበሩ ሲሆን፡፡ ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ ግን ከቤተመንግስቱ ተጠርጣሪ ጋር በፍቅር ክንፍ ብሏል፡፡ ይሄም በዋነኛነት ሟች ከሞተ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ መሆኑ ጥርጣሬያችን ከፍ እንዲል ያደረገዋል፡፡

ለመሆኑ ይህ ተጠርጣሪ ምን ቢያገኝ ነው ወንድሙን የገደለው? ያልን እንደሆን በዋነኛነት የሚቀመጠው ሆድ አደርነት (Opportunism) ነው፡፡ ይሄን እንድንል ያስቻለን ደግሞ ተጠርጣሪው ሟች ከሞተ በኋላ የተለያዩ ንብረቶችን በግሉ ማፍራት የጀመረ ሲሆን በተለያዩ ጊዜያትም ሟችን የሀገሪቱ ዋነኛ ችግር መነሻ አድርጎ ለማቅረብ ሲሞክር ታይቷል፣ በተጨማሪም ሟች የነበረባቸውን ፓርቲዎች ለማፍረስ ከውስጥ ሌላ ‹‹አንጃ›› በመምራት ሟችን በቀን መርዞ እንደገደለው ይጠረጠራል፡፡

ሌላው እና ቅጥረኛ ገዳዩ የሟች አብሮ አደግ እንደሆነ እድንጠረጥር የሚያደርገን ጉዳይ ሟች ከሞተ በኋላ በሞቱ ደስተኛ የነበረ ሲሆን ከገዳይ ቀጣሪም ጋር አብረው መዋል እና ማደር ጀምረው ነበር፡፡ ይባስ ብሎም ‹‹ሟች መሞቱ ትክክለኛ ነገር ነው›› እያለ መግልጫ ሲሰጥ ነበር፡፡ ለህዝቡም እኔ እውነተኛ መሪህ አለሁልህ እያለ ህዝቡ ሟችን በቅጡ እንዳይቀብረው አድርጓል የሚል ጥርጣሬ አለ፡፡ እውን ተቃዋሚው የተገደለው በአብሮ አደግ ጓዱ ይሆን?

ባህል እንደ ተጠርጣሪ

ተቃዋሚውን ገድለውታል ተብለው ከሚጠረጠሩ አካላት አንዱ የህዝቡ ባህል በአጠቃላይ እንዲሁም የህዝቡ የፖለቲካ ባህል በተለይ ነው፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ ይሄን እንድንል ያስቻለን ህዝቡ ተቃዋሚዎች ስልጣን ቶሎ ይዘው መብቱን እንዲያስከብሩለት ከመመኝት ውጭ አብሮ በመርዳት፣ አይዟችሁ በማለት፣ በአባልነት በመሳተፍ ወ.ዘ.ተ ሲደግፋቸው ብዙም አለመታየቱ ነው፡፡ ይሄም ድርጊት የህዝቡ ባህል ተቃዋሚውን በቸልተኝነት ገድሎታል እንድንል ያደርገናል፡፡ 

ሌላው የህዝቡ ባህል ለሟች መሞት ዋነኛውን ድርሻ አበርክቷል እንድንል የሚያደርገን ጉዳይ ተጠርጣሪው በተረቶቹ እንዲሁም በወጎቹ ለሟች መሞት ምክንያት የሚሆኑ ነገሮችን ሲናገር መኖሩ ነው ለምሳሌ ‹‹ሁሉንም ወይም ምንም›› በማለት የብቸኝነት መንገድን እንደ ብቸኛ አማራጭ በማየት ተቃዋሚውግማሽ እንዳይመኝ እና በጋራ እንዳይሰራ አድርጎታል የሚል ጥርጣሬ አለ፡፡

በተጨማሪም የህዝቡ ባህል ‹‹ተባበሩ ወይም ተሰባበሩ›› በማለት አንድ አይነት አቋም የሌላቸውን ተቃዋሚዎች አንድ ላይ ለማድረግ ሞክሮ እንደገደላቸው ይጠረጠራል ይሄም ተግባር አንዳንዴ እንጨትን ከብረት ጋር ለማቅለጥ እንደ መሞከር ነው፡፡ ስለዚህም እውን ተቃዋሚውን የገደለው ባህሉ ይሆን?

ሌሎች ተጠርጣሪዎች

ከላይ ከተጠቀሱት ተጠርጣሪ ገዳዮች በተጨማሪ ሌሎቻ ተጠርጣሪዎችንም ማንሳት ይቻላል ለምሳሌ ሚዲትራኒያንን አቋርጦ የመጣው ባለ ሰማያዊ አይን ተጠርጣሪ አንዱ ነው ይህ ተጠርጣሪ ቤተመንግስት ካለው ተጠርጣሪ ገዳይ ጋር ‹‹ሽብርተኝነትን መዋጋት›› የሚል ውል ተዋውሎ ለሌሎች ነገሮች ትኩረት ባለመስተጠት እና የቤተመንግስቱን ተጠርጣሪ በገንዘብ በመደገፍ ለተቃዋሚው ሞት ተጠያቂ ሊሆን ይችላል፡፡ እውን ይሄ ባለ ሰማያዊ አይን ተጠርጣሪ ተቃዋሚውን ገድሎታልን?

ሌላው ገዳይ ሊሆን የሚችችለው ተጠርጣሪይ በቀዳሚ ነገስታት ሀገሪቱ ‹‹ጥቁር ውሻ ውለጅ›› የሚል ርግማን መረገሟ ሊሆን ይችላል የሚል ኢ-ሳይሳዊ መላ ምትም ይመታል፡፡ እውን እርማኑ ተቃዋሚውን ገድሎት ይሆን?

በአጠቃላይ ተቃዋሚውን ከላይ ከተዘረዘሩት ሀይላት አንዱ ገድሎታል ወይም ራሱን አጥፍቷል ማለት እንችላለን፡፡ የገዳዩን ማንነት የሚገልፀውን ውሳኔ ለማየት ደግሞ በጉጉት እንናፍቃለን፡፡

የቴሌኮም ማጭበርበር ሕጉ አወዛጋቢነት

የቴሌኮም ማጭበርበር ሕጉ አወዛጋቢነት የሚጀምረው ‹‹አዋጁ ፀድቋል፣ አልፀደቀም?›› የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ስንጀምር ነው፡፡ አዲስ አድማስ ጋዜጣ በግንቦት 18፤ 2004 እትሙ ‹‹አዋጁ ፀድቋል›› ብሎ ቢዘግብም ለገዢው ፓርቲ በሚወግኑ ጽሁፎቹ የሚታወቀው ጦማሪ ዳንኤል ብርሃነ ደግሞ ገና ‹‹የመጀመሪያውን የንባብ ደረጃ ማለፉ ነው›› ይላል፡፡ ፍኖተ ነፃነትም በበኩሉ በሰኔ 12፤ 2004 እትሙ ‹‹ፍርሀት የወለደው የቴሌ አፋኝ ረቂቅ ሕግ›› ባሰኘው ጽሁፉ ገና ረቂቁ በፓርላማ እንደቀረበ ነገር ግን ከፓርላማችን ያለፈ ልምድ መረዳት እንደሚቻለው ‹‹የቀናት ጉዳይ ነው እንጂ መጽደቁ እንደማይቀር›› ያትታል፡፡

በአገራችን ረቂቅ ሕጎች የሚመለከተው ሕዝብ’ጋ በግልፅ ሳይደርሱ በጭምጭምታ ይቆዩና ድንገት በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው ሕግ የመሆናቸው ነገር የተለመደ ድራማ በዚህ ረቂቅ አዋጅ ይለወጣል ብሎ መገመት ሞኝነት ነው፡፡ ይሄም ጽሁፍ በጭምጭምታው እውነታነት እና በረቂቅ ሕጉ ዙሪያ መጠነኛ ትንታኔ ይሰጣል፡፡

በቃሉ ኃይሉ (ስሙ ለዚህ ጽሁፍ ሲባል የተቀየረ) በስካይፕ የሚያወራው ከሚናፍቃቸውና ባሕር ማዶ ከሚኖሩ፣ እሱን ለማግኘት ኮምፒዩተር ላይ ቁጭ ብለው ከሚጠብቁት ጓደኞቹ’ጋ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ‹‹እኔ እስከማስታውሰው ድረስ›› አለ ለዞን ዘጠኝ አስተያየቱን ‹‹እኔ እስከማስታውሰው ድረስ፤ ምንም ዓይነት ሕግ ሲወጣ ብወደውም ብጠላውም እታዘዝለት ነበር፡፡ አሁን ግን በስካይፕ ማውራት ሕገ-ወጥ ከሆነ ከጓደኞቼ እና ከሕጉ መምረጥ ሊኖርብኝ ነው፡፡ ጓደኞቼን ከሕጉ የማስበልጥበት ምክንያት እስካሁን አይታየኝም፡፡›› በቃሉ ይህንን የተናገረው አዋጁ ስካይፕ መጠቀምን በወንጀልነት ፈርጆታል የሚለውን ወሬ ከሰማ በኋላ ነው፡፡

‹‹የቴሌኮም ማጭበርበር አዋጁ›› ከስያሜውና ከትርጉም ክፍሉ ውጪ 18 አንቀጾች ብቻ አሉት፡፡ በሕገ-ወጥ መንገድ ስልክ ማስደወልም ሆነ ሌሎች የቴሌኮም አገልግሎቶችን ያለ ኢትዮ ቴሌኮም እውቅና መስጠት የማይቻል መሆኑ ድሮም በሕግ የተደነገገ ቢሆንም አሁን የዚህ አዋጅ መውጣት አስፈላጊ የሆነው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በማሕበራዊ ደረገጾች ላይ እያደገ የመጣውን ፀረ-አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊነት ለመገደብ እንደሆነ ብዙዎች መጠራጠር ጀምረዋል፡፡ የአዋጁ መግቢያ ላይም እንዲህ የሚል ይነበባል፡፡ ‹‹…የቴሌኮም ማጭበርበር ከኤኮኖሚ ኪሳራውም ባሻገር ዋና የደህንነት ስጋት በመሆኑ…›› ህግ አውጪው በረቂቅ አዋጂ ከኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ባለፈ ለሃገር ደህንነት ማሰቡን በግልጽ ይናገራል፡፤(በዚህ ጽሁፍ ውስጥ አዋጁ የተጣቀሰው ከእንግሊዝኛው ቅጂ ሲሆን ትርጉሙ የዞን ዘጠኝ ነው፡፡

ኢሕአዴግ ለአብዮታዊ ዲሞክራሲ የሚያደርገው ቅጥ ያጣ ጥበቃ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ትችቶቹን በሐሳብ ማሸነፍ እንዳቃተው ያሳብቃል፡፡ በጥቅሉ የመረጃ መረብን እና በዋናነት ማሕበራዊ ድረገጾችን ማዕከል አድርገው የሚንቀሳቀሱት የመረጃ ምንጮች እንደ ዶ/ር ዳኛቸው አባባል ‹‹የመረጃ ኦና.›› (Information Vacuum) ለመፍጠርና አውራ ፓርቲው ‹የሕዝብ› መገናኛ ብዙሐንን በመጠቀም የሚያጮኻቸው ወደአንድ አስተሳሰብ ያዘነበሉ መረጃዎች ለሚፈጥሯቸው የገደል ማሚቱ ድምጾች እንቅፋት ሆነዋል፡፡

ከቻይና ምን መማር?
‘ሪፖርተርስ ዊዝ አውት ቦርደርስ’ የተባለ የጋዜጠኞች ድንበር የለሽ ቡድን ቻይናን ‹ከኢንተርኔት ጠላቶች› አንዷ እንደሆነች ያስቀምጣታል፡፡ የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ልኡካን ቡድን ደግሞ በአዲስ አበባ ለሚገኘው አቻው – ኢሕአዴግ በብዙሐን መገናኛ እና ኢንተርኔት አስተዳደር ዙሪያ ያካበተውን ልምድ አካፍሎ ተመለሰው በቅርብ ጊዜ እንደሆነ በገዢው ፓርቲ ድረገጽ ላይ የሰፈረው ዜና ያስረዳል፡፡

ቻይና ‹‹የምዕራቡ ዓለም የመረጃ ነፃነት ባሕል የአገሬን ባሕል ያጠፋል›› በሚል ስም ለበርካታ ብዙሐን መገናኛ በሯን ዘግታለች፡፡ ለቻይና ብቻ ተብሎ የተዘጋጀው ጉግል አንዳንድ የኮሙኒስት ፓርቲን የሚያስቀይሙ ቃላቶችን እንዳይፈልግ ተደርጎ በልኳ ተሰፍቶላታል፡፡ ፌስቡክና ትዊተርም ታግደዋል፡፡

የቻይና የፍቅር ልጅ የሆነችው ሃገራችን ከቻይና በቀሰመችው ልምድና ቴክኖሎጂ የቪኦኤና የዶቼቬሌን ሬዲዮ ጣቢያ ማፈኗን መንግስቷ አምኗል፡፡ በርካታ ድረገጾችም ታግደዋል፡፡ አንድ የዞን ዘጠኝ አባል በግሉ ባደረገው ቅኝት 65 ነፃ ድረአምባዎች፣ 14 የፓርቲ እና ለፓርቲ የሚወግኑ ድረአምባዎች፣ 37 ጦማሮች፣ 7 የበይነመረብ ሬዲዮና ቴሌቪዥኖች እና 37 የፌስቡክ ቡድን ገጾች በኢትዮጵያ እንዳይነበቡ መደረጋቸውን አረጋግጧል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ነው አዲሱ አዋጅ በመረጃ ደህንነት መረብ አርቃቂነት ለፓርላማ የቀረበው፡፡ ‹አዲሱ አዋጅ ምን ዓይነት በቀላሉ ትርጉማቸውን ሊጠመዘዝ የሚችሉ አንቀጾች አሉት? የማሕበራዊ ድረገጽ እንቅስቃሴዎችን እንዴት ያውካቸዋል? ሐሳብን በነፃ ከመግለጽ መብት አንጻርስ አዋጁ እንዴት ይታያል? ስካይፕና ጉግል ቶክን የመሳሰሉት በVoice over Internet Protocol የሚጠቀሙ አገልግሎቶችን ሕገወጥ ያደርጋቸው ይሆን?› የሚሉ ጥያቄዎችን የሚያጭሩ እና ለማብራሪያ ክፍት የሆኑ አንቀጾችን ከዚህ በታች እንጠቃቅሳለን፡፡

አወዛጋቢዎቹ አንቀጾች
በአዋጁ ክፍል አንድ በተለዩ ቃላት ትርጉሞች ላይ የሚከተሉትን ያስቀምጣል፡፡ አንቀጽ 2 ላይ ‹‹የቴሌኮሙኒኬሽን ቁሳቁስ ማለት ለቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት የዋለ ወይም ሊውል የታቀደ ዕቃ፤ መገጣጠሚያ (accessories) እና ሶፍትዌሮችን ጨምሮ ማለት ነው፡፡›› ይላል፡፡ አንቀጽ 1 ላይ ‹የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት› የሚለውን ሲተረጉም በኤሌክትሮኒክ መንገድ የሚቀርቡ ጽሁፎች እና ምስሎች ከአገልግሎቱ እንደሚካተቱ ጠቁሟል፡፡ ሶፍትዌሮችን በዚህ ትርጉም ውስጥ በማካተት የተከታይ አንቀጾችን ትርጉም በዚያ መልኪ እንድናይ ያስገድደናል፡፡

ክፍል ሁለት፣ አንቀጽ 3 ‹‹ሚኒስትሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመምከር የትኞቹ የቴሌኮሙኒኬሽን ቁሳቁሶች፣ አምራቾች፣ ገጣጣሚዎች፣ አስመጪዎች ፈቃድ እንደማይሹ ይገልጻል፤ ደንብ ያበጃል›› ይላል፡፡ ይህም በሚኒስትሩ (ሚኒስትሩ የሚባለው የኢንፎርሜሽን እና ኮምዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ነው፡፡) ያልተዘረዘሩ የመገናኛ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም፣ ተጠቃሚውን በወንጀልነት እስከ 4 ዓመት ፅኑ እስራት እና እስከ 40,000 ብር በሚደርስ ቅጣት፣ አስመጪ እና አከፋፋይ ድርጅቶችን ደግሞ ‹‹..ከ10 እስከ 15 ዓመት የሚደርስ ጽኑ እስራት እና ከ100,000ብር እስከ 150,000 ብር የሚደርስ ቅጣት..›› ሊያስከትልበት እንደሚችል ረቂቁ ይደነግጋል፡፡

የዚህ አንቀጽ ለትርጉም ክፍት መሆን የምንጠቀምባቸው የበይነመረብ ማሰሻዎች (Internet browsers)፣ ሶፍትዌሮች (skype, google talk…)፣ የስልክ ቀፎዎች (blackberry, iPhone, Android ስልኮች፣ ወዘተ…)፣ እና ሌሎችም ዓይነት በሚኒስትሩ ይወሰናሉ፣ ካልተወሰኑ ደግሞ ለመጠቀም ፈቃድ ያስፈልጋል የሚል አንድምታ ይኖረዋል ማለት ነው፡፡(የጆሮ ማዳመጫ የተጠቀመ ሰው ያልተፈቀደ መሳሪያ ገጣጥሞ ተጠቀመ ቢባል ሊስቀጣው ነው ማለት ነው እስከሚል የተለጠጠ ትርጉም ድረስ ሊወስደን ሁሉ ይችላል)

አንቀጽ 6(1) ደግሞ ‹‹ማንም የቴሌኮም መረብን ወይም መሳሪያን በመጠቀም በፀረሽብርተኝነት አዋጅ 652/2001 መሰረት የሽብር መልዕክት ቢያሰራጭ ወይም በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ መሰረት የሚያስጠይቅ አጸያፊ መልዕክት ቢያሰራጭ… ከ3 እስከ 8 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እና ከ30,000 እስከ 80,000 ብር ድረስ ይቀጣል›› ይላል፡፡በዚህ አንቀጽ የተጠቀሰውን ወንጀል መፈጸም በዚህ ህግ ቢካታትም ባይካተትም ማስጠየቁ የማይቀር ሆኖ ሳለ በድጋሚ የተለየ ሽፋን መስጠቱ የህጉን አስፈላጊነት እንድንጠይቅ ያስገድደናል፡፡

አንቀጽ 13 ‹‹የቴሌኮም ማጭበርበርን ለመከላከል፣ ለመመርመርና ለመቆጣጠር ብሔራዊ የቴክኒክ ሥራ ቡድን ከሚመለከታቸው አካላት ተውጣጥቶ ይቋቋማል፡፡››

አንቀጽ 14 ‹‹ፖሊስ የቴሌኮም ማጭበርበር ተከስቷል ወይም ሊከሰት ይችላል ብሎ ባመነ ጊዜ ከፍርድ ቤት የብርበራ ፈቃድ መጠየቅ ይችላል፡፡›› ይህም የአንድ ሰው የስልክ ንግግር፣ አጭር የጽሁፍ መልዕክቶች፣ የኢሜይል መልዕክት ልውውጦች እንደአስፈላጊነታቸው የሚበረበሩበትን የሕግ አግባብ ይሰጣል ማለት ነው፡፡ መንግስት የኢንተርኔት አጠቃቀምን በተመለከተ ለአገሪቱ ደህንነት የሚያሰጉ ነገሮች ካሉ መቆጣጠር አለበት የሚለው ነጥብ ላይ መስማማት ቢቻልም የግለሰቦችን ነፃነት በተራ ፍራቻ ማሳጣት ግን ከሰብአዊ መብት ጥሰት ውስጥ ሊመደብ ይችላል፡፡

ህጉ በአጠቃላይ ካሉበት መሰረታዊ ገደቦች(limitations) መካከል ዋና ዋናዎቹ የግለሰቦችን ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በሃገር ደህንነት ስም መንጠቁ፣ለትርጉም ክፍት የሆኑ ሰፋፊ ሃሳቦችን ማጠቃለሉ እንዲሁም የህጉን አስፈላጊነት በሚገባ ሊያሳምን አለመቻሉ ናቸው፡፡

ከሌሎች የተለመዱ ሕጎች በተለየ የማስረጃ ሁኔታን የዳሰሰው ይህ አዋጅ ለወትሮ ከምንጠቀምባቸው የማስረጃ አይነቶች በተጨማሪ ተቀባይነት ያላቸው ያላቸውን ተጨማሪ የማስረጃ አይነቶች ይጨምራል፡፡ይህ ከመሰረታዊ ሰብአዊ መብት ጥበቃ ጋር እና ከመሰረታዊ የወንጀል ህግ ጋር መታረቁ ያልተገጋገጠ የማስረጃ ስርአት በህጉ ትግበራ ወቅት ታርሞ ይተገበራል ማለት ዘበት ነው፡፡

ወደ ኢንተርኔት ወደ ስልክ መደወልን፣ያልተፈቀዱ ሶፍትዌሮችን መጠቀምን፣ እንዲሁም የጽሁፎችን ይዘትን በብዙ ከሚወቀሰው የጸረ ሽብርተኝነት ህግ ጋር ማቀላቀሉ ህጉን ከተጸፈበት በላይ አላም እንዳለው ሌላ ምስክር ነው፡፡
ወደ ስልክ መደወል እና ማስደወልን የሚከለክለው የህጉ አንቀፅ አስር ከተከለከሉ ሶፍት ዌሮች ጋር ተደምሮ የኢንተርኔት የድምጽ ንግግርን ወደ ወንጀልነት ይቀይረዋል፡፡

VoIP (Skype, Google Talk…) በሚኒስትሩ ይፈቀዱ ይሆን?

የቀድሞዋ አዲስ ነገር መራኄ ኤዲተር መስፍን ነጋሽ በፌስቡክ ገጹ ላይ ‹Promote then criminalize!› በሚል ርዕስ ባሰፈረው አጭር የስዕል ማብራሪያ ላይ (ምስሉን እዚህ ጦማር ላይ መመልከት ይቻላል) ከሁለት ቀን በፊት በሚኒስትሩ ድረገጽ ላይ VoIPን (Voice over Internet Protocolን) የሚያስተዋውቅ ይዘት ያለው መልዕክት ተለጥፎ እንዳገኘ (ያ ገጽ አሁን በሌላ ይዘት ተተክቷል) በምስል አዘጋጅቶ እና የመጀመሪያው መስመር ላይ “ስለ VoIP ሰምታችሁ የማታውቁ ከሆነ የረዥም ርቀት የስልክ ጥሪዎችን የምታደርጉበትን መንገድ ለመቀየር ተዘጋጁ” የሚል ነገር እንዳነበበ ጠቅሶ ጽፎ ነበር፡፡ መስፍን ነጋሽ ይህንን ሁኔታ ከረቂቅ አዋጁ አንፃር በመታዘብ አገልግሎቱን እያስተዋወቁ፣ ተጠቃሚዎቹን ወንጀለኛ ከማድረግ የተቀነባበረ ሴራ ለይቶ እንደማያየው ተናግሯል፡፡

የሚኒስተሩ ድረገጽ በፍጥነት በሌላ ጽሁፍ መተካቱ አዋጁ እውነትም VoIP ኢላማ አድርጎ ተነስቷል ብሎ ለመጠርጠር እንደ አንድ ግብአት ሊቆጠር ይችላል፡፡ በሌላ በኩል እ.ኤ.አ. በ2002 የቴሌሴንተር አገልግሎት ፈቃድን በተመለከተ በወጣው መመሪያ አንቀጽ 13(2) ላይ VoIP (ከኮምፒዩተር ወደ ኮምፒዩተር የሚደረግ የድምጽ ግንኙነት ጨምሮ /ስካይፕን ያካትታል/) የተከለከለ ቢሆንም እስካሁን ድረስ የተለያዩ ኢንተርኔት ካፌዎች ስካይፕን በይፋ ሲጠቀሙ እንጂ በወንጀል ሲከሰሱ የታየበት አንድም መረጃ የለም፡፡ ሌላው ቀርቶ ኢቴቪ የሕዳሴው ግድብን አንደኛ ዓመት አስመልክቶ ለጠቅላይ ሚኒስቴሩ በስካይፕ ጥያቄ ማቅረብ ይቻላል እያለ ሲያስተዋውቅ መክረሙ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡

በመሆኑም መመሪያው እያለ፣ የፀረ-ሽብርተኝነቱም ሆነ የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ እያሉ አዲሱ ‹የቴሌኮም ማጭበርበር አዋጅ› እዚያ የተካተቱትን ሕግጋት ደግሞ መውጣቱ ያስፈለገበት ምክንያት ግልጽ አለመሆን የእነዚህን የቴክኖሎጂ ውጤቶች መስፋፋት ተከትሎ እያደገ የመጣውን ሐሳብን በነፃ የመግለጽ መብት ለማፈን የተወሰደ እርምጃ ነው የሚለውን መላምት ያጠናክረዋል፡፡ ለዚህም እንደዋቢ መጥቀስ የሚቻለው በረቂቁ ላይ ‹‹መንግስት በሕዝቡ አመኔታ እንዲያጣ የሚያደርግ…››፣ ‹‹… አፀያፊ ጽሁፎች›› የሚሉ አሻሚ እና ሰፊ ትርጉም የሚኖራቸውን ሐረጎች መጠቀሙ የአዋጁ ኢላማ በተለይ ማሕበራዊ ድረገጾች ላይ በሚደረጉ የግል ሐሳብን በነፃ የመግለጽ መብት ላይ ስጋት የሚጥሉ ሆነዋል፡፡

ሚኒስትሩ VoIPን ከሚከለከሉ አገልግሎቶች መካከል እንደሚያስቀምጣቸው ለመጠርጠር የሚያበቃ ሌላም ምክንያት አለ – የገዢው ፓርቲ የቅርብ ሚዲያ እና ህግ አውጪው ሬድዮ ፋና፡፡ የዜና መጽሄት በተሰኘው ፕሮግራሙ ሬዲዮ ፋና የረቂቅ አዋጁ መንፈስ ሁሉንም ዓይነት VoIPን የሚጠቀሙ አገልግሎቶችን ለማገድ የወጣ እንደሆነ ፍንጭ ይሰጣል:: በተለይ (በፕሮግራሙ ላይ) አንድ የምክር ቤት አባል የአዋጁን አስፈላጊነት ለማስረዳት ሲናገሩ ኢትዮ ቴሌኮም እንደስካይፕ ያሉ በኢንተርኔት ስልክ የማስደወያ ሶፍትዌሮችን በሕግም ሆነ በቴክኖሎጂ ቁጥጥር ስር ማድረግ እንዳለበት አስረድተዋል:: አዲሱ የቴሌኮም አዋጅ ረቂቅ ደግሞ ለቴሌ ይህን ሕጋዊ ዳራ ይፈጥርለታል::

አዋጁ ከኢትዮ ቴሌኮምም በላይ በድብቅ የኢንተርኔት ማጥለል (Internet filtration) ሥራ በመስራት የሚታማውን የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲን (INSAን) ነፃ ያወጣዋል – የረቂቁ አንቀጽ 13 ‹የቴክኒክ የሥራ ቡድን›መቋቋም የሚለው ከለላ በማስቀመጥ፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት እየተዘዋወርን ያነጋገርናቸው ጥቂት የኢንተርኔት ካፌ አገልግሎት ሰጪዎች ከወዲሁ (አዋጁ ከመጽደቁ እና በነጋሪት ጋዜጣ ከመውጣቱ በፊት) የስካይፕ እና ማንኛውንም የድምጽ (Voice over IP) አገልግሎት መስጠት ማቆማቸውን ለመረዳት ችለናል፡፡

ዳንኤል ብርሃነ ከላይ ባጣቀስነው ጦማሩ ላይ ‹‹ስካይፕ በሕግ እንደማይታገድ የጥብቅና ባርኔጣዬን አስይዤ እወራረዳለሁ›› ሲል ከተከራከረው በተቃራኒ መደምደም እንደሚቻለው፣ አዋጁ አሁን አሁን እያቆጠቆጠ የመጣው በበይነመረብ ላይ ሐሳብን በነፃ የመግጽ ፍላጎት ላይ ክፉ ጥላ መጣሉ ነው፡፡ እንዲያውም አንዳንዶች የአዋጁ ብቸኛ ዓላማም ይኸው ነው ሲሉ ጥርጣሬያቸውን ከወዲሁ እየገለፁ ነው፡፡ ውጤቱን ለማየት ግን አዋጁ ፀድቆ(በፓርላማ ክርክር እና የጋለ ውይይት ጋር) የተግባር እርምጃው እስኪጀመር ጥቂት ወራት ብቻ መታገስ በቂ ይሆናል፡፡

ጋዜጦቻችን ከሰኞ እስከ ሰኞ – አንድ

(የሳምንቱ ጋዜጦች ከግንቦት 27 እስከ ሰኔ 3፤ 2004)

በአጭር ጊዜ ውስጥ ተነባቢነት ያተረፈውና በአንድነት ፓርቲ አሳታሚነት ማክሰኞ ገበያ ላይ የሚውለው ፍኖተ ነፃነት በመላው ሃገሪቱ ሰፊ የመረጃ መረብ ስላለው ሁሌም ዜናዎቹ ትኩስና ያልተሰሙ ናቸው፡፡ በዚህ ሳምንትም ከዜናዎቹ ውስጥ እነዚህ ነበሩበት፡-

‹‹…በጎንደር ፖሊስ የሟቾችን አስከሬን በመኪና መሬት ለመሬት አስጎተተ….

‹‹… የዜና ምንጮቻችን እንደሚሉት ‹አቶ ሽንኩ ከፍያለውና አቶ ዳኛቸው የተባሉ ሁለት ግለሰቦች ከፀጥታ አስከባሪዎች ጋር የተኩስ ልውውጥ አድርገው ከተገደሉ በኋላ አስከሬናቸው መሬት ለመሬት ሲጎተት ውሏል› ብለዋል፡፡….››

‹‹…በቤንች ማጂ ዞን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገደሉ….

‹‹… የፍኖተ ነፃነት ምንጮች ባደረጉት ማጣራት የፌዴራል ፖሊስና የመከላከያ ሰራዊት ከመጠን ያለፈ ኃይል ተጠቅመው [ለአራት ወራት የፀጥታ ችግር የሰፈነበትን] አካባቢውን ለማረጋጋት ሞክረዋል፡፡… በዚህ የኃይል እርምጃ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደተገደሉ [ምንጮች] አስረድተዋል….››

‹‹…የኢትዮጵያ ፕሬስ አሳታሚዎች ማህበር የመተዳደሪያ ደንቡን አፀደቀ….

‹‹… በምስረታ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ፕሬስ አሳታሚዎች ማህበር (ኢፕአማ) ሰኞ ግንቦት 27 ቀን 2004 ባካሄደው ስብሰባ የመተዳደሪያ ደንቡን አፀደቀ….››

‹‹…ግንቦት 20ን ለማክበር 120 ሚሊዮን ብር መውጣቱ ተጠቆመ….

‹‹… [የፍኖተ ነፃነት ምንጮች] እንደሚሉት ‹ሰዎችን ጋብዞ ላመጣ አንድ ሺ ብር፣ ለፎረም አባል 600 ብር፣ ለቀበሌ ቀስቃሽ 300 ብር፣ ለሰልፈኛ መቶ ብር እየተከፈለ የተሰበሰበ ነው፡፡ ለዚሁ ማስፈፀሚያ የሚውል ለኦሮሚያ ብቻ 30 ሚሊዮን ብር መመደቡን› ያስረዳሉ፡፡ ….››

የፈቴሌ እማሬ እና ፍካሬ (ፍኖተ ነፃነት፤ በነብዩ ኃይሉ) ያስነበበን ትንታኔ ደግሞ ስለስልክ መጠለፍ ያወጋናል፡- ‹‹… በአንዳንድ የስልክ ልውውጦች ላይ የራስህን ድምጽ መልሰህ የምትሰማበት፣ ከሌሎች ስልኮች በተለየ በአድ ድምጽ የምትሰማበት፣ የሦስተኛ ወገን ንግግር በጣልቃ የሚሰማበትና የሚቆራረጥበት ሁኔታ ስልክ መጠለፉን የሚያሳዩ ምልክቶች ናቸው፡፡… ባለሙያዎች እንደሚሉት ቴሌ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ እያጋጠሙት ያሉት ችግሮች መካከል በዋነኝነት የሚጠቀሰው የኔትወርክ መጨናነቅ ድርጅቱ ለጠፋ ተግባር የሚጠቀምባቸው በአድ መሳሪያዎች ጠንቅ እንደሆነ ይናገራሉ…››

* * *

የጋዜጠኛ ስንዱ አበበ አስገራሚ ቃለ ምልልስ ከየኛ ፕሬስ ጋዜጣ ጋር፤ ቀንጨብ፣ ቀንጨብ እያረግን እንመልከተው፡-

‹‹ጥንቆላ ለልማት መዋል ቢችል ኢትዮጵያ ፈጣን ለውጥ ታመጣለች›› ይላል ርዕሱ!

‹‹… ብዙ ኢትዮጵያውያን ችሎታ እንዳላቸው ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ግን ችሎታቸውን ለክፋት ነው የሚያውሉት፡፡ ለምን? እኔ አሁን እንዲጠየቅልኝ የምፈልገው ይሄንን ነው፡፡…

‹‹… እኔ እንግዲህ ጋዜጠኛ ነበርኩ፡፡ ነፃ ጋዜጣ ሲመሰረት ጀምሮ ከነበሩት ሰዎች አንደኛዋ ነበርኩ፡፡ አንዱ ጋዜጣ ጥሩ ነገር ሲያወራ ሰምተሃል? አሉባልታ፣ ክፋት፣ የሰው ስም ማጥፋት፡፡ እንድታድግ፣ እንድትቀየር፣ የተሳሳትከውን ነገር እንኳ ሲጽፉ የሚፅፉበት መንገድ በክፋት ተወሳስቧል፡፡ ክፋት በዝቷል፡፡ ለምን ይህን ያህልስ እንከፋፈላለን? ክፋት ምን ያደርጋል? ግን ችሎታህን ለክፋት መጠቀም በጣም መርዛማ መርዛማ አኗኗር ነው፡፡ ቫይብሬሽኑን ራሱ መርዛማ አድርገውታል፡፡ የመጀመሪያው ተጠያቂ ደግሞ ሚዲያው ነው፡፡…

‹‹… በማጂክ የምንኖር መሰለኝ እኮ! ሰርተህ ምንም የለም፡፡ እኔ አሁን ዘጠኝ መጽሃፍ አትሜያለሁ፡፡ ላይፌን ደሞ እየው፡፡ ምንድን ነው ይሄ? ምንም ማለት ነው፡፡ ምን ሆኖ? የት ሄደ? የሰራኹት ገንዘብ የት ሄደ? ያ ሁሉ ስራ ምንድን ነው የሆነው? ብትለኝ ላስረዳህ አልችልም፡፡ ውልብልብ ነው… ሁሉም ሰው ገብቶታል ይሄ፡፡…

‹‹… በመንግስት በኩል ለምሳሌ እንየው ብንል ማተሙን አትከለከልም፡፡ ግን ማከፋፈል ላይ ይይዙሃል፡፡ ሜጋ አይገባም ካሉህ አለቀ፡፡ በስንት ቡክ ሾ ልትሸጥ ነው ሜጋ ካልገባህ፡፡ ስለዚህ ያከስሩሃል፡፡…

‹‹…[ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው ጋዜጠኝነት] መጥፎ የሆነ ህዝብ የሚመራ መድረክ ስለሆነ ህዝቡንም ምን ያህል ክፉ እንዳደረግነው አስብ፡፡ እና በጣም ያሳፍራል፡፡ እና ጋዜጠኛ መባል፣ ቃሉንም መባሉንም አልፈልገውም፡፡ ስለነበርኩም አሁን ላይ ይደብረኛል፡፡…

‹‹… ብዙ ጊዜ ደግሞ ጋዜጦቹ ማተም የሚፈልጉት አሉባልታ ነው እንጂ እውነት የተደከመበት ስራ አይደለም፡፡…

‹‹… ስታየው ያለንበት ሁኔታ ተመሰቃቅሏል፡፡ ሃይማኖቶቹም ተመሰቃቅለዋል፡፡ ፖለቲካውም ተመሰቃቅሏል፡፡ ምንድን ነው ስትል ‹‹ሞስትሊ›› ጥንቆላ የሚባለው ጠልሞስ፣ ዛር፣ ደብተራ… እንግዲህ እነኚህ በአግባቡ ያልፈተሽናቸው ኢትዮጵያውያን እሴቶች ናቸው፡፡ አሁን አሉ? የሉም? መጠናት አለበት፡፡ ግን እኔ አሁንም ባለው ሁኔታ ላይ ጥንቆላ ለልማት መዋል ቢችል ኢትዮጵያ ፈጣን ለውጥ ታመጣለች፡፡…

‹‹… እናድናለን ይላሉ፡፡ ያጎራሉ፤ ከሁሉ ነገር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ስለዚህ ለኔ ኢትዮጵያዊ አዕምሮ – የያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አዕምሮ ከጥንቆላ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሴክተሮች ተጠንተው ለልማት የሚውሉበት መንገድ ካለ መንግስት ይህን ቢመረምር ይሻላል የሚል አቋም አለኝ፡፡…››

‹‹… እኔ የሰራኋቸው መጽሃፎች ወደፊት ገና ትንታኔ ይፈልጋሉ፡፡ በአዋቂ ሰዎች፣ ዩኒቨርስቲዎ ፔፐር ይሰሩባቸዋል፡፡ ይደርሳል፡፡ እንደሚደርስ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ከአምስት ስድስት ዓመተ በኋላ የኔ መጽሃፎች በጣም እንደሚፈለጉ አምናለሁ፡፡ ስለዚህ ይህን ቀን ለማየት ፀጥ ብሎ ራስን አክብሮ መኖር፡፡››

* * *

መሰናዘሪያ  በበኩሉ የዶ/ር ኃይሉ አርአያን ምስል ከሽፋን ገጹ ላይ ይዞ ወጥቷል፡፡ ዶ/ሩ ለጋዜጣው ሲነግሩት እንዲህ ብለዋል፤ ‹‹… የአንድ አምባገነን ግለሰብ መለወጥ ምንም ለውጥ አያመጣም

‹‹… የልማት ማዕከሉ ሰው ነው፡፡ አንድ ነገር አደገ ሲባል የሰውን ህይወት መለወጥ አለበት… የዕለትተዕለት ኑሮውን ካላሻሻለው ዋጋ የለውም፡፡ … ያለነፃነት የተሟላ ልማት ሊኖር አይችልም፡፡ ውሸት ነው ቀጣይ የሆነ ዘላቂ ልማት ሊኖር አይችልም፡፡…››

* * *

ሪፖርተር በረቡዕ እትሙ ‹‹… የኤርትራ ጦር በባድመ አንድ ትምህርት ቤትና አንድ አውቶቡስ አቃጠለ›› የሚል ዜና ይዞ ወጥቷል፡፡

‹‹… ባለፈው እሁድ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት በባድመ ግንባር የሚገኘው የኤርትራ ጦር ኃይል በከባድ መሣርያ (ተወንጫፊ) ባደረሰው ጥቃት፣ ‹‹ባድመ ቀዳማይ ብርኪ ቤት ትምህርቲ›› (ባድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት) ሙሉ ለሙሉ በመቃጠሉ ከጥቅም ውጪ ሆኗል፡፡…››

‹‹መለስ በምስክርነት ፍርድ ቤት ሊቀርቡ ነው›› የሚል ዜና ያስነበበን ደግሞ ኢሕአዴግ ሲቀነስ መለስ ምን ይሆናል? የሚል ጥያቄ ሽፋን ገጹ ላይ ይዞ የወጣው ሰንደቅ ጋዜጣ ነው፡፡ ስለመለስ ፍርድ ቤት መቅረብ ሲዘረዝር፡-

‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ጨምሮ የቀድሞ የህወሓት አመራሮች ለምስክርነት መቐለ ከተማ ፍ/ቤት ሊጠሩ ነው፡፡ አመራሮቹ ለምስክርነት የተጠሩት የህወሓት መስራች ከነበሩት አንዱ አቶ አስገደ ገ/ስላሴ ላይ አቃቤ ሕግ የቀረበባቸውን የስም ማጥፋት ክስ ተከላከሉ በመባላቸው ነው፡፡…››

አቶ አስገደ ‹ጋሃዲሦስት› በተባለው መጽሃፋቸወ ምዕራፍ 29 ላይ የቀድሞ የህወሓት የፀጥታና ደህንነት አባልን ስም አጥፍተዋል በሚል በአቃቤ ሕግ ለቀረበባቸው ክስ ነው… መከላከያ ምስክር የጠሩት፡፡

‹‹… አቶ አስገደ በመከላከያ ምስክርነት ከጠሯቸው የመከላከያ ማስረጃዎች መካከል አቶ መለስ ዜናዊ፣ አምባሳደር ሙሉጌታ አለምሰገድ (ነዋሪነታቸው በጣሊያን) አቶ ስብሃት ነጋ፣ አቶ መኮንን (የአባታቸው ስም ለጊዜው ያልታወቀ)፣ አቶ ወልደስላሴ አብርሃ (በትግራይ የሚገኙ)፣ አቶ ሰለሞን ተስፋዬ፣ አቶ ፍሬው ተስፋሚካኤል (በደቡብ ሱዳን ጁባ የሚገኙ)፣ አቶ ገብሩ አስራት፣ አቶ አባይ ፀሃዬ፣ አቶ ስዬ አብርሃ (በአሜሪካ ሃርቫርድ ዩንቭስቲ የሚገኙ)፣ አቶ ስዩም መስፍን (ቻይና በአምባሳደርነት የሚያገለግሉ)፣ አቶ አርከበ እቁባይ፣ አቶ ኪሮስ አቡዬ፣ አቶ አክሊሉ ኪዳነማርያም (በአድማስ ኮሌጅ አዲስ አበባ የሚገኙ) እና ሦስት የመከላከያ ጄኔራሎች ይገኙበታል…››

ሰንደቅ እንደቀጠለ ነው…

‹‹የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ባለስልጣናት የኢሕአዴግ አቻዎቻቸውን አሰለጠኑ…

‹‹… አምስት አባላት ያሉት የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ዓለም አቀፍ አባላት [በአቶ ሴኮቱሬ ለሚመራው] ለኢሕአዴግ አቻቸው….በብዙኃን መገናኛ አቅም ግንባታ፣ በመገናኛ ብዙኃን ተቋማት አስተዳደርና በኢንተርኔት አስተዳደር [ቻይና] ያላትን ልምድ በስልጠናው ተመርጠው ለተገኙ የኢሕአዴግ ከፍተኛ የአመራር አባላት አካፍለዋል፡፡…

‹‹… ቻይና ፌስቡክን ጨምሮ የኢንተርኔት አገልግሎትን በማፈን (ጃም በማድረግ) በዓለምአቀፍ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች ተቃውሞ የሚቀርብባት ሲሆን በሃገሪቱ የሚዲያ አፈና እና የጋዜጠኞች መብት የማይከበርበት መሆኑ በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወሳል፡፡››

* * *

‹የዋጋ ግሽበቱ እና የ‹‹መለኖሚክስ›› [የመለስ-ኢኮኖሚክስ] ክስረት› በሚል ርዕስ የኢኮኖሚ ምሕዳሩን ቅኝት በፍትሕ ጋዜጣ ላይ ያቀረበው ኃይለመስቀል በሸዋምየለህ ‹‹… በየሦስት አልያም አራት ቀናት ውስጥ አንዱን ምንም ምግብ እቤት ውስጥ የማይኖርበት ጊዜ የተለመደ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግር ሲገጥመኝ ለልጆቼ ምንም የሚበላ ነገር እንደሌለ እነግራቸዋለሁ፡፡ አጋጣሚ ሆኖ የተገኘ ጊዜ ደግሞ አንዷን እንጀራ አራት ቦታ ቆርሼ፣ ትንሽ ሽሮ ፈሰስ አደርግና እንዲቃመሱ አደርጋቸዋለሁ፡፡ አሁን እግዚአብሔር ይመስገን ህፃናቱ ያለውን ችግር እየተረዱ መጥተዋል፡፡ እንደከዚህ ቀደሙ ምግብ አምጪ እያሉ አያስቸግሩኝም፡፡…›› ያሉ የኢኮኖሚው መገለጫ ንግግሮችን ከጥናቶች አሰባስቦ አቅርቧል፡፡

ፍትሕ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝም በበኩሉ ‹የጠፋው ትውልድ እና የታህሪር ናፍቆት› በሚል ርዕስ በጻፈው ጦማሩ ‹‹… የባልቻ አባት ሳፎ እንጂ አባ ነፍሶ አይደለም የሚለው ጉንጭ አልፋ ክርክር ሳይሆን ይህች ሀገር እስከመቼ ድረስ እንዲህ በግለሰቦች የተናጠል ትግል ህልውናዋ ሊጠበቅ ይችላል?…›› በማለት ምሁራኑ እንኳን ፈርተው የሸሹትን ‹‹ብቸኛ ታጋይነቱ››ን አወድሷል፡፡ ተመስገን ስለ ‹ያ ትውልድ›፣ ስለ ‹አምላጭ ትውልድ› ሐተታ ካቀረበ በኋላ ‹ታህሪር ናፋቂ› ስላለው ትውልድ ሳምንት ለመመለስ ቃል ገብቶ ተሰናብቷል፡፡

ባለፈው ሳምንት የ‹‹ቃሊቲው ምስጢሮች›› ላይ የሰላ ትችቱን የሰነዘረው ብርሃኑ ደቦጭ በዚህ ሳምንት ደግሞ ‹‹ባለቀለተ ጉዳይ ፍርድ ቤት ከመከራከር ለሕዝብ ዳኝነት አንድ መጽሐፍ መጻፍ፤ የሲሳይ አጌና መጽሐፍ አንድምታ›› በሚል ርዕስ ለዘብ ትችቱን አቅርቧል – በፍትሕ ጋዜጣ!

ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ የኤፍ.ኤም ፕሮግራሞችን በታዘቡበት የሰላ ትችታቸው ‹‹…የዛሬዎቹ ‹ታዲያስ አዲስ›፣ ‹የፍቅር ክሊኒክ›፣ … የመሳሰሉ የኤፍ.ኤም ፕሮግራሞች በየእለቱ የሚረጩት መርዝ የትውልዱን ስነምግባር ሸርሽሮ ከስሩ ነቅሎ እስከሚጥለው፣ ሀገራችን በእውቀትና በስነምግባር የታነጸ ዜጋ ማጣትዋ በግልጽ እስከሚታይ ስንት ዓመት ይፈጃል?…›› ሲሉ ‹ዘመኑ እኮ የኤፍ.ኤም ነው› በሚል ርዕስ ፍትሕ ጋዜጣ ላይ ባወጡት ጽሁፍ በምሬት ጠይቀዋል፡፡

* * *

አዲስ አድማስ ነፃ አስተያየት በተሰኘው አምዱ ‹‹የመንግስት ወከባ ከፍርሃት የማያላቅቅ የሕልም ሩጫ›› የሚል ሰፊ ሐተታ አስነብቧል፡፡ ‹‹… ዲግሪ ወይም ዲፕሎማ የያዙ ስራአጦች እየበዙ ነው፣ ቁጥራቸው በ5 ዓመት ውስጥ በ3 እጥፍ ይጨምራል፣ የትራንስፎርሜሽኑ እቅዱ 2 ዓመት ሊሞላው ነው፤ ነገር ግን በርካታ እቅዶች በተያዘላቸው ጊዜ አልተሰሩም፣ የስራ ፈላጊ ከተሜዎቹ ቁጥ በ330ሺ ይጨምራል፤ ሩብ ያህሉ ብቻ መደበኛ የስራ እድል ያገኛሉ፡፡ የገጠር ሕዝብ በየዓመቱ በ2ሚ. እየጨመረ ነው፤ የዝናብ እጥረት ሳይኖርም ከ12ሚ. በላይ ሰዎች ተረጂ ናቸው…›› እያለ የመንግስት እቅድንና አፈፃፀምን ይተቻል፡:

‹‹..     ይድረስ

ለወዳጄ፡-

እንደምን ሰንብተሃል እኛ ባለንበት እግዚአብሄር ቸርነት ደህና ነን፤ መቼም ወቅት ፈቅዶ ለብዙ ትውልዶች ያህል ተራርቀን ብንኖርም ያገሬ ታሪክ የጀግኖች ታሪክ መቼም አይዘነጋም ብዬም አልነበር… እናም ይሄውልህ በእናንተው ዘመን ደግሞ ብላቴናው ቴዎድሮስ ካሳሁን ‹‹ጥቁር ሰው›› ብሎ ታሪካችንን ብድግ አደረገዋ!

       እንግዲህ ምን ትላለህ? ከሆነልህማ የፊታችን ማክሰኞ ከአመሻሹ 12 ሰዓት ላይ ከቤተመንግሥታችን ዝቅ ብሎ ከሚገኘው ሂልተን ውቴል ብቅ በልና ጠበል ፀዲቅ ቅመስ፤ ስናወጋ እናመሻለን

       አደራ እንዳትቀር

       ያልመጣህ እንደሆነ ግን ማርያምን እቀየምሃለሁ፡፡

       ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ግንቦት 28/2004 ዓ.ም. ›› – የቴዲ አፍሮ ‹ጥቁር ሰው› ሙዚቃ ቪዲዮን ለማስመረቅ የተዘጋጀው የጥሪ ወረቀት ላይ የተጻፈ ጽሁፍ (አዲስ አድማስ)

* * *

ነጋድራስ ጋዜጣ ‹‹በጽንፈኝነት የተቃኘች ሃገር›› በሚል በደሳለኝ ስዩም ባቀረበው ሰፊ ሐተታ ሃይማኖተኞችን፣ የገዢው ፓርቲንና ወገኖችን፣ ተቃዋሚዎችን፣ ጋዜጦችንና ፕ/ር መስፍንን ሳይቀር በማስረጃ እያስደገፈ ተችቷል፡፡ ከጽሁፉ ጥቂት ለመጨለፍ ያክል፡- ‹‹…በመገናኛ ብዙሃን ኢንዱስትሪ ውስጥ መካከለኛ ማግኘት ከባድ ነው፡፡ ጭልጥ ያሉ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ እና የኢሕአዴግ አቀንቃኝ የሆኑ የመንግስት ብዙሐን መገናኛዎች እና ጭልጥ ብለው ምንነቱ ያልታወቀ የተቃውሞ እንቅስቃሴ የሚደግፉ /ኢሕአዴግን በመጥላት ላይ ብቻ የተመሰረቱ/ ብዙሐን መገናኛዎች በየራሳቸው ጽንፍ ላይ ቆመዋል፡፡…››

የጋዜጦቹ ርዕሰ አንቀጽ

ሌላም፣ ሌላም

 • በአዲስ አበባ በቤተ-ክርስቲያን ይዞታ በተቀሰቀሰ ግጭት የሁለት ሰው ህይወት አለፈ፡፡ – ፍትሕ
 • በጋዜጠኛ ርዕዮት ላይ የይግባኝ አቤቱታ ክርክር ሊጀመር ቀጠሮ ተያዘ – ፍትሕ
 • አቶ አስገደ ‹‹የመከላከያ ምስክሮቼን ለማሰማት ከፍተኛ የገንዘብ ችግር ገጠመኝ›› አሉ – ፍትሕ
 • ‹‹ገመና ድራማ ተተራመሰ፤ ተፈሪ አለሙና መሰረት መብራቴ ጀማነሽ ሰለሞንን ተከትለው ራሳቸውን አገለሉ›› – የኛ ፕሬስ
 • ጋዜጠኛ አበበ ገላው በደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷልአዲስ አድማስ
 • ‹‹ስለ ካሴቱና ስለፕሮግራሙ የምሰጠው አስተያየት ባይኖረኝም ክሊፑ በጣም አሪፍ ነው፤ የሠሩት ልጆች መመስገን አለባቸው፡፡›› – የፊልም ባለሙያ ቴዎድሮስ ተሾመ (አዲስ አድማስ)

ቀልድ

‹‹ማርሻል ቲቶ የዩጎዝላቪያ መሪ በነበሩበት ጊዜ ነው አሉ፡፡ ቲቶ የደህንነት ሚኒስትራቸው ራንኮቪክን አስከትለው በከተማዋ ጉብኝት ያድረጋሉ (የሥራ ልትሉት ትችላላችሁ፡፡) መጀመሪያ ወደ አንድ ወላጅ አልባ ህፃናቱ ያሉበትን ሁኔታ ለማሻሻል በሚል 10ሺ ዲናር ይለግሳሉ – ቲቶ፡፡ በመቀጠል ጋብቻ ሳይመሰርቱ የወለዱ እናቶች መጠላያ ይሄዱና 15ሺ ዲናር ይሰጣሉ – የእናቶቹንና የህፃናቶቻቸውን የአኗኗር ሁኔታ ለማሻሻል በሚል፡፡ የቲቶ ቀጣይ ጉብኝት ወህኒ ቤት ነበር፡፡ እዚያ ደግሞ 80ሺ ዲናር ሰጡ – የእስረኞች አያያዝ እንዲሻሻል በማዘዝ፡፡…. ቲቶ ለወህኒ ቤቱ ባደረጉት የበዛ ልግስና የተገረሙት የደህንነት ሚኒስትራቸው፤ ‹ለምንድን ነው የእስረኞች አያያዝ እንዲሻሻል ያን ሁሉ ገንዘብ የሰጠኸው?› ሲሉ ይጠይቋቸዋል፡፡ ቲቶም ሲመልሱ፤ ‹ክፉ ቀን ቢመጣ እኔና አንተ ማረፊያችን የት ይመስልሃል? የህፃናት ማሳደጊያ ተቋም፣ የእናቶች መጠለያ ወይስ ወህኒ ቤት?››› በማለት የጻፈው በብዕር ስሙ ኤሊያስ የአዲስ አድማስ ፖለቲካ በፈገግታ› አምደኛ ነው፡፡ በጽሁፉ ‹‹…አዲስ አዋጅም በሉት መመሪያ ሲወጣ ከዕለታት አንድ ቀን እኔም ላይ ተፈጻሚ ሊሆን ይችላል ብሎ ማሰብ ቢቀር እንኳን መጠርጠር ክፋት የለውም…›› ብሏል፡፡

በመጨረሻም ስፖርት

‹‹በበርካታ የአፍሪካ ዋንጫ ውድድሮች ባለመሳተፏ የተረሳችው ኢትዮጵያ በዘንድሮው የ2012 የአውሮፓ ዋንጫ ስሟ የሚጠራበት አጋጣሚ ተፈጥሯል፡፡ በመጪው አርብ ሰኔ 1 ቀን 2004 በሚጀመረውና ፖላንድ እና ዩክሬን በሚያስተናግዱት የአውሮፓ ዋንጫ ለቼክ ሪፐብሊክ ብሔራዊ ቡድን ከሚሰለፈው ቴዎዶር ገብረስላሴ ጋር ኢትዮጵያም መጠራቷ አይቀርም፡፡…›› – ሰንደቅ፡፡