Category Archives: Sociopolitics

የእነርሱ እና የእኛ ሕዳሴ


የሐዲስ ዓለማየሁን “ጉዱ ካሣ”፣ የበዓሉ ግርማን “አበራ”፣ የዳኛቸው ወርቁን “አደፍርስ” ማን ይዘነጋቸዋል? እንኳን ‘ፍቅር እስከመቃብር’ን፣ ‘ከአድማስ ባሻገር’ን እና ‘አደፍርስ’ን ያነበቡ ቀርቶ ያላነበቡም ያውቋቸዋል፡፡ እነዚህ ገጸ ባሕርያት የሚታወሱት ከዘመናቸው ባፈነገጠ ማኅበራዊ ሃያሲነታቸው ነው፡፡
እነዚህን ገጸ ባሕርያት ወደኋላ ዞር ብለን የፈጠሯቸውን ደራሲያን ስናስብ ደራሲያኑ በየገጸ ባሕሪዎቻቸው አንደበት ማኅበረሰቡን በነገር አለንጋ ይገርፉታል፣ በምክንያት ይሞግቱታል፡፡ ያኔ እነዚህ እና ሌሎቹም ጸሐፍት ይህንን አሉ፤ ዛሬ እና የዛሬዎቹስ?
እዚህች’ጋ ሌላው የዞን ዘጠኝ ጦማሪ ባለፈው ሣምንት የጠየቃትን ጥያቄ መልኳን ቀይሬ ላንሳትና፣ እንደው ለመሆኑ (ከዚሁ ከልቦለድ ዘርፍ ሳንወጣ) በአለፉት አምስት፣ አሥር ወይም ሀያ ዓመታት ውስጥ እጅግ ተወደደ አነጋገረ፣ ልቤ ውስጥ ቀረ የምንለው መጽሐፍ አለ? ከላይ የጠቀስናቸውን ገጸ ባሕርያት ያክል ያመራመረን፣ ያነጋገረን፣ የሚታወሰን ገጸ ባሕሪ አለ? – ለኔ የለም፡፡
ጥያቄውን በልቦለድ ብቻ አነሳሁት እንጂ፣ ከአንድ ወዳጄ’ጋ ከዚህ ቀደም በመሰል ሐሳቦች ዙሪያ ስናወራ፤ እስኪ የ60ዎቹን ዘመን ወጣቶች እና የአሁኖቹን እናወዳድር ብለን በሁሉም ዘርፍ ሞክረን ነበር፡፡ ያኔ የነበሩ ወጣት ደራሲያኖችን እና ገጣሚዎቻችንን ጠቃቀስን እና አሁን ላይ መጣን… ከበውቀቱ ስዩም እና ምናልባትም እንዳለ ጌታ ከበደ በላይ መሻገር አልቻልንም፡፡ እነአፈወርቅ ተክሌ፣ እነእስክንድር ቦጎሲያን እና ወዘተን… ጠቃቀስን እና የነርሱ እኩያ ይሆናሉ ብለን ተስፋ የምንጥልባቸውን ሰዓሊዎች ማፈላለግ ጀመርን፣ ይሄ ነው ልንነው የምንችለው ሰው አልመጣልንም፤ ሌላው ቀርቶ የሙዚቃ ባንድ እና ዘፈን ዘርፍ ውስጥ መጣን፣ የበፊቶቹን ኦርኬስትራ ቡድኖች የሚተካ፣ ወይም ሁሌም ልብ የሚያሸብሩትን ዘፈኖች እና ዘፋኞች ይተካል ብለን የምንጠራው ዘፋኝ አልነበረንም… ምናልባት እጅጋየሁ ሽባባው… ተባባልን፡፡ ከጋዜጠኞችም ለማወዳደር ሞካክረን ነበር፣ እነ ጳውሎስ ኞኞን፣ እነ ታደሰ ሙሉነህን የሚተካ ቀርቶ ተስፋ የሚጣልበት ጋዜጠኛ አለ?
በየጊዜው በናፍቆት የምንጠብቀው የጋዜጣ ወይም የመጽሔት አምድ/አምደኛ፣ የሬዲዮ ወይም የቴሌቪዥን ትዕይንት፣ ልባችን እስኪጠፋ በጋራ የምናደንቀው ወጣት ባለሙያ ወይም ጀግና… ብቻ በጥቅሉ ምንም የለንም፡፡
ችግሩ የኛ አለማወቅ ነው፣ ወይስ አማተሮቹን ከአንጋፋዎቹ ጋር ማወዳደራችን የሚል ጥያቄም ተከስቶብኝ ነበር፤ ይሁን እንጂ እነዚህን የምናደንቃቸውን አንጋፋ ባለሙያዎች የምናደንቅላቸው የወጣትነት ሥራዎቻቸውን እንጂ አሁን በስተርጅና የሠሯቸውን (ያውም ካሉ) አለመሆኑን ሳስብ ችግሩ የእውነት የወቅቱ የፈጠጠ ችግር መሆኑ ታሰበኝ እና እንድንነጋገርበት ይዤው መጣሁ፡፡
ኢትዮጵያ እንዴት ሰለጠነች?
ለውይይታችን ማጠናከሪያ፣ ኢትዮጵያን የማዘመን ሙከራዎች በየመንግሥታቱ መሞካከራቸውን እያስታወስን ከነዚህ ውስጥ ዐብይ ለውጥ ያስከተሉትን ጥንታውያን የዘመናዊነት እንቅስቃሴዎች እና የሀያኛውን ክፈለዘመን እርምጃዎች እያየን ዘንድሮ ላይ እንደርሳለን፡፡

 1. የአክሱም ስልጣኔ
  ከክርስቶስ ልደት በፊት 400 ዓመት አስቀድሞ የተጧጧፈው የአክሱም ስልጣኔ እስከ 10ኛው ክፍለ ዘመን ለመዝለቅ ችሎ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የአክሱም ስልጣኔ ስር መሠረት እና ውርሱ በቅጡ አይታወቅም፡፡ እስካሁንም ድረስ ቆመው ከሚገኙት እና አምልኮተ-መራባትን ያመለክታሉ ከሚባሉት ሀውልቶች በቀር ለትምህርትነት የሚበቃ፣ ወይም ከዚያ ዘመን ሲወርድ ሲወራረድ የመጣ ትውፊታዊ ቁምነገር አለ ለማለት የሚያስደፍር ግኝት የለም፣

 2. የዛግዌ ስልጣኔ
  የአክሱም ስልጣኔ መውደቅን ተከትሎ የኢትዮጵያ የጨለማ ዘመን ለ200 ዓመታት ነገሠ፡፡ ከዚያም በመራ ተክለሃይማኖት አማካይነት የዛግዌ ስልጣኔ ተጀመረ፡፡ የዛግዌ ስልጣኔ ክርስትናን በማስፋፋት ላይ የተመሠረተ ሲሆን ትሩፋቱም የላሊበላ ውቅር ዐብያተ ክርስትያናት እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ትውፊታዊ ትምህርት ናቸው፡፡ የዛግዌ ዘመነ መንግስት ከአክሱም ስልጣኔ በተሻለ ሃይማኖት ቀመስ ቢሆኑም ጽሑፎች ተጽፈው ለቀጣዩ ትውልድ የተላለፉበት የመጀመሪያው ዘመን ነው ማለት ይቻላል፣

 3. ሰሎሞናዊ ስልጣኔ
  ይሄንኛው የስልጣኔ ዘመን የአክሱም ዘመን ቀጣይ እና ሰሎሞናዊ ቤተሰብ ነን በሚሉ ነገሥታቶች የተመራ የስልጣኔ ዘመን ነው፡፡ የዚህ ዘመን መጨረሻ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ነው፡፡ ይህ ዘመን ለቅርስነት ያስመዘገባቸው ነገሮች የሉም ማለት ይቻላል (የዘመነ መሳፍንት ቤተመንግሥታትም ቢሆኑ በዚህ ዘመን መሐል የተፈጠሩ የመከፋፈል ታሪኮች ናቸው፤) ሆኖም የአሁኒቷ ኢትዮጵያ የአሁኑን ቅርጿን የያዘችው በዚህ የስልጣኔ ዘመን ነው፡፡ በዚህ ዘመን አውሮጳውያን አፍሪካን ሲቀራመቱ ኢትዮጵያውያን ግን በእምቢተኝነት ራስ ገዝ አስተዳደር የፈጠሩበት ይህ ዘመን ነው፡፡ በዚህ ዘመን በተለይም ከአድዋ ድል በኋላ የተሠሩት ሥራዎች ኢትዮጵያን ከዘመናዊነት ጋር በማስተዋወቁ ረገድ መንገድ ጠራጊዎች ናቸው ማለት ይቻላል፤ በዚህ ዘመን ባቡር፣ ዘመናዊ ትምህርት፣ የጤና ብሎም የባንክ አገልግሎቶች እና ወዘተ ለመጀመሪያ ጊዜ በአገራችን ተዋውቀዋል፣

 4. የድኅረ ጣሊያን ኃይለሥላሴ ስልጣኔ
  በዘመናዊት ኢትዮጵያ ውስጥ ጉልህ ስፍራ የሚኖራቸው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አብዛኛውን ኢትዮጵያን የማዘመን ሥራ የሠሩት ከጣልያን የአምስት ዓመት ወረራ በኋላ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ሚያዝያ 27/1933 ንጉሡ ከስደት ሲመለሱ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት የ‘አዲስ ዘመን’ እንቅስቃሴያቸውን ጀመሩ፡፡ በወቅቱ ኢትዮጵያን ከሙሉ ፊውዳላዊ አስተዳደር በከፊል አላቀዋታል፣ በብሔር እና ሃይማኖት “መቻቻል” ላይ መጠነኛ ሚዛን እንዲሰጥ በሚል ሕገ መንግሥታቸውንም አሻሻለዋል፣ ፓርላማው ለሕዝቦች በመጠኑ የተከፈተውም በዚሁ ዘመን ነው፣ በተለይም ደግሞ ዘመናዊ ትምህርት ተስፋፋ፡፡ ከዚያም በላይ እስከአሁኑ የአባይ ግድብ፣ የቁጠባ ቤቶች (ኮንዶስ)፣ የአዲስ አበባ ቀለበት መንገድ እና ወዘተ መሠረታቸው የተጣለው በዚህ የስልጣኔ ዘመን ነበር፡፡ በተለይ በዚህ ዘመን የተፈጠረው የትምህርት እና የአንባቢነት ፋሽን በመግቢያችን ላይ የጠቀስናቸውን ዘመን አይሽሬ ጠበብት ለመፍጠር በቅቷል፣

 5. የማርክሲስት ስልጣኔ
  የዚህ ዘመን ስልጣኔ ባለቤቶች የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን ወጣቶች ሲሆኑ፣ ወደማርክሲዝም የመራቸውም በዘመኑ ለነበረው ፊውዳላዊ አስተዳደር የነበራቸው የመረረ ጥላቻ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ለተመሳሳይ ርዕዮተ ዓለም (ማርክሲዝም/ማኅበረሰባዊነት) ነገር ግን በተለያየ ቡድን ተቧድነው ሲቆራቆዙ የነበረበት ዘመን ሲሆን፣ ለሁለት አሥርት ዓመታት በዘለቀው መቆራቆዛቸው ሳቢያ ‘ሰብኣዊ-ዘመናዊነት’ የጎደለው ዘመነ ስልጣኔ፣ ነገር ግን በተለይ መንግሥታት ከሃይማኖታዊ ጥገኝነት የተላቀቁበት ዘመን ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ ዘመን መጀመሪያ ላይ ተስፋ ፈንጥቆ የነበረው መሃይምነትን የመቅረፍ ‹የመሠረተ ትምህርት› ዘመቻም፣ በዘመኑ መጨረሻ ላይ ጠውልጎ ነበር፤ ሕዝቦች ለፖለቲካዊ ተሳትፎ የነበራቸው ጉጉት በፍራቻ መቀመቅ የወረደውም በዚህ ዘመን ነው፣

 6. የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ስልጣኔ
  የማርክሲስትን የስልጣኔ ዘመን (በአገራችን) ተክቶ የመጣው የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ስልጣኔ አጀማመሩ ላይ ለካፒታሊዝም የቀረበ ቅይጥ ኢኮኖሚ መር ስልጣኔ ለመሆን ቢሞክርም፣ የኋላ ኋላ ሶሻሊስታዊ ዴሞክራቲክ ኢኮኖሚ መር የሚመስል የስልጣኔ ዘመን ሆኗል፡፡ ዘመኑን በይፋ ‘የሕዳሴ ዘመን’ ብሎ ለመጥራት በመንግሥት የታወጀ ሲሆን፣ በተለይ ለአንደኛ ደረጃ (አውራ) መንገዶች እና ሕንጻ ግንባታ ትኩረት የሰጠ የስልጣኔ ዘመን ነው፡፡ በዚህ ዘመንም፣ ልክ እንደ ማርክሲስታዊው የስልጣኔ ዘመናችንም ሁሉ የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊው የስልጣኔ ዘመን ለሰብኣዊ ልማት ምንም ትኩረት ያልሰጠ፣ ትምህርት ከጥራት ይልቅ በቁጥር የተመዘነበት እና በአስተዳደሩ ርዕዮተ ዓለም አስፈጻሚነት የተከረከመ ትውልድ ከማፍራት በላይ ያልተጋ ዘመን ነው ለማለት የሚያስደፍር ትውልድ ተፈጥሯል፡፡
በየዘመናቱ የከፋፈልናቸውን የስልጣኔ መስመሮችን ተከትለን ስንመለከት፥ ለሰብኣዊ ሀብት ልማት (ዕድገት) ትኩረት የሰጠው የድኅረ ጣልያን ኃይለሥላሴ ዘመን ብቻ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በተቃራኒው ደግሞ አሁን ያለንበት ዘመን “የሕዳሴው ዘመን” እየተባለ በአስተዳደሩ እየተጠራ ነው፡፡ እውነት ሕዳሴ ማለት የግንብ ብቻ ነው?
የእነርሱ ሕዳሴ
የኢትዮጵያ መንግሥት “ሕዳሴ” የሚለውን ቃል የኮረጀው ከአውሮፓጳውያን “Renaissance” ይመስላል፡፡ ሬኔሳንስ በፍሎረንስ፣ ጣልያን ተጀምሮ በመላው አውሮጳ መስፋፋት የቻለ እና ከ14ኛው እስከ 17ኛው ክፍለዘመን የዘለቀ “የባሕል እንቅስቃሴ” ወይም የባሕል አብዮት ነው፡፡
የእነርሱ ሬኔሳንስ በመካከለኛው ዘመን እና በአሁኑ ዘመን መካከል የስልጣኔ ሽግግር ድልድይ በመሆን አገልግሏል፡፡ የዚህ ሬኔሳንስ ዋነኛው መሠረቱ ሥነ ጽሑፍ፣ ሥነ ፍልስፍና፣ ሥነ ስዕል፣ ሥነ ፖለቲካ እና ሌሎችም ላይ የዘመናዊነት መልክ ለማላበስ የተካሔዱት ክርክሮች የአስተሳሰብ አብዮቶች በማፍለቅ አውሮጳውያንን ግንባር ቀደም የስልጣኔ ቀዳጅ አድርጓቸዋል፡፡
የእኛ “ሕዳሴ” ግን በቀለበት መንገዶች እና በ“ሰማይ ጠቀስ” ሕንጻዎች ላይ የተንጠለጠለ በመሆኑ የቀለበት መንገዱን አጠቃቀም እና የሕንጻዎቹን አጠቃቀም እንኳን በአግባቡ የማያውቅ እና ቢያውቅም የማያከብር ብዙሐን አፍርቷል፡፡ የትምህርት ፖሊሲውም በበኩሉ ብዙሐኑን ተከራክሮ የሚያሳምን የሐሳብ ሊቅ ሊፈጥር ቀርቶ የሥራ ማመልከቻ በተስተካከለ ሰዋሰው መጻፍ የማይችል የዲግሪ ምሩቅ እያፈራ ነው፣ ሚዲያው እንኳን ሊያስተምር እና አርኣያ ሊያኖር ወይም ሊያቀርብ ቀርቶ “ወሮ በሎች” ልላቸው የምፈቅደው ሰዎች መናኸሪያ ሆኗል፡፡

አሁን ያለንበትን ዘመን ስንታዘበው፥ አንድም አያቶቻችን ባኖሩልን የኩሩነት፣ የጨዋነት እና የሥነ ምግባር መመሪያ ሳንታነፅ አሊያም ሉላዊነት (globalization) ዘልቆን ከሰለጠኑት ዓለማት እኩል በሐሳብ ሳንራመድ – እንዲሁ የባከንን ትውልድ ሆነን መቅረታችን ያሳስበኛል፡፡ የዚህ ብክነት መፍትሔው – መማር እና ማንበብ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን እንደ ትውልድ የትምህርት ዕድሉንም ሆነ እውነተኛ ለውጥ አጎናፃፊ ትምህርት ወይም የሚለውጥ ንባብም ሆነ ማንበቢያ በማጣት እየተሰቃየን እንደሆነ ሳስብ ደግሞ ስለራሳችን አዝናለሁ፡፡

ዳያስፖራው ጽንፈኛ ወይስ ተስፈኛ?

ከነበረበት ባሕል፣ ተመሳሳይ ቋንቋ ተናጋሪ ማኅበረሰብ፣ የኑሮ ዘዬ ወይም ባጭሩ ከነበረበት አገር (በማንኛውም መልኩ) ለቆ ወደ ሌላ አገር ለተወሰነም ሆነ ላልተወሰነ ጊዜ እየኖረ ያለ ሰው/ማኅበረሰብ ቀድሞ ለነበረበት አገር ሰዎች ‹ዳያስፖራ› ይባላል (dispersed; disaspora /የፈለሰ፤ ፈላሻ እንደማለት)፡፡ አገርኛ ስናደርገው ደግሞ ከኢትዮጵያ ወጥቶ ከኢትዮጵያ ውጪ ባሉ የዓለም ክፍል ተበትነው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ዳያስፖራ እንላቸዋለን፡፡ ‹‹የዳያስፖራ ፖለቲካ›› ስንል ደግሞ ዳያስፖራ በሆነው ማኅበረሰባችን የሚንፀባረቀውን ፖለቲካዊ አቋም፣ አመለካከት እና እንቅስቃሴን ማለታችን ነው፡፡ በተለይ አሁን አሁን ስለአገራችን ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ‹ዳያስፖራው ምን አለ?› የሚለው ጥያቄ የማይሻር ጉዳይ እየሆነ ነው፡፡ ሆኖም ደግሞ በጉዳዮች ላይ የተሰጡ አስተያየቶችን አይቶ ከኢትዮጵያ ውጪ በሚኖር ሰው የተሰጠ መሆኑን እና አለመሆኑን ለማወቅ ቀላል እየሆነ እንደመጣ የሚከራከሩም አሉ፡፡ እነዚህም፡-

 •  በተለምዶም የአስተያየቱን ጽንፉን ተመልክቶ ‹የዲያስፖራ ፖለቲካ›› የሚባል ስያሜ እየተሰጠው ይገኛል፡፡ የ‹የዳያስፖራ ፖለቲካ› ውስጥ በብዛት ጽንፉ ወዲህ ወይም ወዲያ ይሆን ይሆናል እንጂ ፅንፍ መያዙ አይቀርም የሚለው እምነት የብዙዎች እየሆነ ነው፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ ሁለቱንም ጽንፎች አዳርሰዋል በሚል ሰለሞን ተካልኝ በማስረጃነት ያነሳሉ፡፡
 •  ዳያስፖራው እኛ (በአገር ውስጥ ነዋሪዎች) የማናውቀውን የዴሞክራሲ ጣዕም የሚያውቅ፣ እኛ የሌለን የፖለቲካ ምኅዳር ያለው፣ ገሚሱ ኑሮው ሞልቶለት የወገኑ ጉዳይ ከሩቅ የሚቆረቁረው የለውጥ ተስፈኛ እንጂ ጽንፈኛ ሊባል አይገባውም የሚሉት ደግሞ በሌላ ወገን ይገኛሉ፡፡

በርግጥም ጽንፍ የያዙ እና ማንኛውንም ዓይነት በአገራችን ውስጥ የሚታዩ እንቅስቃዎችን ጥቃቅን ጉድለቶችን እየነቀሱ በማውጣት፣ በማጉላት እና ጠንካራ ትችት ማቅረብ የዳያስፖራ ፖለቲከኞች መለያ እየሆነ ነው እንዲያውም ዋነኛ ዓላማቸው መቃወም እንጂ ለለውጥ መትጋት አይደለም ቢባልም፣ የእውነተኛ ለውጥ መንገድን ለማምጣት ገንዘባቸውን፣ ዕውቀታቸውን እና ጊዜያቸውን እየፈሰሱ ያሉትም ‹‹ከኑግ የተገኘሽ መጭ አብረሽ ተወቀጭ›› በሚል ሰበብ አብረው እየተጨፈለቁ ነው፡፡ ጉዳዩን በኮንትሮባንድ ውስጥ ለውስጥ ከማስኬድ ይልቅ በመወያየት የሚበጀውን አካሔድ በጽንፍ/ተስፋ ቅጥያ ሳንከፋፈል እንድንሄድበት ማድረግ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ነው፡፡  
ምንም እንኳን እነርሱ ከሌሉበት (አስተያየታቸውን ካልሰጡበት) የኢትዮጵያ ፖለቲካ ነፍስ የሌለው በድን ይሆናል የምንላቸው ዳያስፖራዎች ቢኖሩም፣ ይህ ጽሑፍ ግን ባመዛኙ ‹‹ስንዴውን ከገለባ ለመለየት›› ሲባል ሊወቀሱ የሚገባቸውን መውቀስ ላይ ያተኩራል፡፡ ሊወቀሱ የሚገባቸው የምንላቸው እነዚህን ያካትታል፡-
·         ኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተውን የፖለቲካ ምኅዳር መጥበብ የግል መጠቀሚያ (መተዳደሪያ) ከማድረግ ውጪ ፖለቲካ ያለ ለማይመስላቸው፣
·         በተለያዩ አደጋዎች የደረሰባቸውን አደጋ መንግስት እንዳደረሰባቸው በማስመሰል የሐሰት ትዝብት በመፍጠር ላይ ላሉ፣
·         ለምክንያት (causes) ሳይሆን ለጥገኝነት መጠየቂያ ሲባል ብቻ የመሪዎችን መምጣት ተከትሎ የሚደረጉ ሰልፎች መብዛት፣
·         ይህንና ይህን መሰሎች ችግሮች እያሉባቸው ጉዳዩን እንዳይወራ ለማነወር እየጣሩ ያሉ ቀጥተኛ ተጠያቂ ዳያስፖራዎችን ነውሩን ለመጠየቅ ነው፡፡
የአንድ “ተራ” ዳያስፖራ አመለካከት እዚህ አገር ካለ ፖለቲከኛ ይልቅ (ዕድሜ ለቴክኖሎጂ እና ሐሳብን ለመግለጽ ነጻነት) ሕዝቡ ጓዳ የመግባት ዕድል ያለው እየሆነ ነው፤ ስለሆነም የጎበጠ የሚመስለንን ለማቅናት እና የተቃናውን ደግሞ ለመጠናከር መወያያ ጊዜው አሁን ነው፡፡ ለውይይት እንዲያመቸንም አንድ በሚያደርጓቸው ባሕርያት እየከፋፈልን እንመለከታቸዋለን፡-
ጫና ያሳደዳቸው
የአገራችን ፖለቲካና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር የሚጽፉ እና የተበደሉ ሕዝቦችን ድምፅ ባገኙት አጋጣሚ ሲያሰሙ የነበሩ ጋዜጠኞች፣ ጸሐፊዎች እና የሰብዐዊ መብት ተሟጋቾች እዚህ ምድብ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ አገር ውስጥ እያሉ በሠሯቸው ሥራዎች ዕውቅናን ያተረፉና የሕዝብን ጆሮ አግኝተው የነበሩ ብዙ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች የሕዝቦቻቸው ልሳን በመሆናቸው ብቻ በስልክ ከሚደርሳቸው ማስፈራሪያ እና ዛቻ አንስቶ ለአካላዊ ጉዳት የመዳረግ፣ የመንገላታት እና የመታሰር ዕጣ ሊደርስባቸው እንደሚችሉ ጥቁምታዎች ወይም ምልክቶች በሚያገኙበት ጊዜ በተለያየ ምክንያት አገራቸውን ለቀው ለመሰደድ ይወስናሉ፡፡
እነዚህኞቹን በተመለከተ አገር ውስጥም ባሉ ሆነ ቀድሞውንም በተሰደዱ ሰዎች ‹‹መሰደዳቸው አግባብ አይደለም፤ እዚሁ ሆነው እስከ መጨረሻው ድረስ የሚደርስባቸውን ሁሉ ማለትም እስሩንም፣ እንግልቱንም፣ፍትሕ ማጣቱንም ከሕዝባቸው ጋር እንደጀመሩት መጨረስ ነበረባቸው›› የሚል አመለካከት ያላቸው ሰዎች ያሉትን ያክል ‹‹የለም፤ እነዚህ ሰዎች እስር ቤት ገብተው ለራሳቸውም ከሚንገላቱ፣ ወጥተው የቻሉትን ያህል ሕዝባቸውን በአቋራጭ ቢታገሉለት፤ በዚያውም ለዓለም አገር ውስጥ ያለውን ችግር ቢያስረዱ ይሻላል›› የሚሉትም ብዙ ናቸው፡፡
ይሁን እንጂ ከሩቅ ሆነው በላፕቶፕ የሚታገሉት ሰዎች የመጀመሪያውን ሲናገሩ አገር ውስጥ ካሉት ይልቅ የበለጠ ያስከፋል፡፡ ለዚያም ነው ‹‹እነርሱ ሊኖሩት ያልፈቀዱትን ሌሎች እንዲኖሩ ግፊት ያደርጋሉ›› በሚል በጽንፈኝነት የሚከሰሱት፡፡
በተረፈ ግን ብዙዎቹ በዚህ መንገድ ተሰደው የወጡ ጋዜጠኞችን እንደምሳሌ ብንወስዳቸው ባመዛኙ ከጽንፈኝነ የፀዱ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ የአዲስ ነገር ጋዜጠኞች፣ የአውራምባ ታይምሱ ዳዊት ከበደ፣ የፍትሑ አበበ ቶላ፣ እና እንደ አርጋው አሽኔ ያሉ ነጠላ ስደተኞች፣ ከተሰደዱ ወዲህ በተለያዩ አምባዎች እና ማኅበራዊ አውታሮች ከሚያሰፍሯቸው ጽሑፎች ውስጥ መረዳት እንደምንችለው፣ አንደኛ በስደት ሆነውም ብዙዎቹ አገር ውስጥ ሆነው የነበራቸውን አቋም ቀጥለውበታል፤ ሁለተኛ ከተሰደዱ ወዲህ ያሉ ወቅታዊ ጉዳዮችን በመከታተል ራሳቸውን ከአገር ውስጥ መረጃዎች አላራቁም፣ ሦስተኛ የአገር ውስጥ እውነታዎችን በተዛባ ሁኔታ አይረዱም፣ ወይም ለግል ጥቅማቸው መጠቀሚያነት ሲረባረቡበት አልታዩም፣ አራተኛ እነዚሁ ሰዎች የስርዓት ለውጥ ከመጣ ተመልሰው መጥተው እኛኑ ነውና ‹‹ጽንፈኛ›› በሚለው አብረን ልንፈርጃቸው አይገባም፡፡
የዳያስፖራ ተቃዋሚ ፓርቲ/ቡድን አመራሮችና እና አባላት
በርካታ የቀድሞ ተቃዋሚ ፓርቲ አመራር አባላት ተሰድደዋል፡፡ በተለይም የፈረሰው የቅንጅት አባላት ከነበሩት ውስጥ ጥቂት የማይባሉት በስደት የየራሳቸውን ቡድን እና ፓርቲ መስርተዋል፤ ከነዚህ ውስጥ እንደምሳሌ የዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ግንቦት ሰባት አንዱ ነው፡፡ በሌላ በኩል የኦባንግ ሜቶ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ፣ የዶ/ር ፍስሐ እሸቴ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሽግግር ምክር ቤትም ሳይጠቀሱ የማይታለፉ ናቸው፡፡ እዚያው ለረዥም ዓመታት ነዋሪ የነበሩ፣ በተለይም በደርግ ዘመን የተሰደዱ በርካታ የኢሕአፓ ሰዎችም ፖለቲካው ውስጥ በግልም በቡድንም አይጠፉም፡፡
እነዚህንም በተመለከተ ሁለት አመለካከቶች አሉ፤ ምንም አልሠሩም/አይሠሩም እና ያቅማቸውን እየሠሩ ነው የሚሉ፡፡ ነገሮችን በምሳሌ መመልከቱ እየሠሩ ያሉትን እና ያላግባብ ስም እየፈሱ ያሉትን ለመለየት እና ወደፊትም እየጠየቅን ምስጋናችንን/ድጋፋችንን እንድንችር ያደርገናል፡፡ እነሆ ምሳሌዎቹ፡-

 • በገዢው ፓርቲ በአሸባሪነት የተፈረጀው እና ግዝፈቱ እና አስፈሪነቱ በቴሌቪዥን የሚደሰኮርለት ግንቦት ሰባት እስከአሁን ድረስ የሠራው ሥራም ሆነ ያሸበረው ሽብር ምን እንደሆነ ቢጠየቅ፣ ተቃውሟቸውን በይፋ ለሚገልፁ ሰዎች ‹‹ባጅ›› በመሆን ለመንግስት ከማገልገል ውጪ ይሄ ነው የሚል መልስ  ለማግኘት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሽግግር ምክር ቤት መነሻዬ ያለውን ለኢትዮጵያ የስርዓት ለውጥ የተዘጋጀ የሽግግር መንግስት የማዋቀር ሥራውን ትቶ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የሞት ቀን ላይ (እንደ መረጃ ሰጪ ሚዲያ) የጦፈ ክርክር በማድረግ የትኩረት አቅጣጫውን ስቶ ታይቷል፡፡ ሲመሠረት በሁለት ወራት ውስጥ፣ የአቶ መለስ ኅልፈት ከተሰማ ወዲህ ደግሞ በሁለት ሳምንት ውስጥ የኢትዮጵያን ሕዝብ ነጻ አወጣለሁ ብሎ ቃል የገባው ይሄው የሽግግር መንግስት ቃሉ ከተግባሩ የፈጠነ መሆኑ ሌሎች የዳያስፖራ ቡድኖችንም ሆነ እራሱን ከተኣማኒነት ዝርዝር ውስጥ በዚህ መንገድ እንዳያወጣ ያሰጋል፡፡
 • EAC (Ethiopian Americans Council) በመባል የሚታወቀው ቡድን በተቃራኒው፣ በተቃራኒው ለኦባማ ደብዳቤ ከመጻፍ አንስቶ፣ በልማት ሰበብ የሚገኙ የእርዳታ ገንዘቦች ነጻነትን ማፈኛ እንዳይወሉ የማንቂያ ደውል ለአሜሪካ መንግስት በመደወል እየሰሩ ያሉት የሚበረታታ ነው፡፡ የጋራ ንቅናቄ የተባለውም ቡድን በተለይ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የአቋም መግለጫ ጽሑፎችን በማውጣት ይታወቃል፤ አሁንም እንኳን በቅርቡ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ለውጥን የሚጠይቅ ግልጽ ደብዳቤ አሰራጭቷል፡፡ የHR2003 (የሰብኣዊ መብት ጉዳይን ያስቀደመ መመሪያ) የአሜሪካ መንግስት የኢትዮጵያ መንግስት ላይ እንዲጥል አሊያም እርዳታ እንዲያግድ የሚያደርገውን ዶሴ በማርቀቅ እና እንዲፀድቅ እና አገር ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ ጫፍ ደርሶ የነበረ ትግል የታገሉትም የዳያስፖራ ቡድኖች ናቸው፡፡ ይህንን በምክንያት ከመሟገት እና ለውጥን ከመወትወት ወይም የ‹‹አራማጅነት›› ሚና የተሻለ የሚሠሩ እና ሊበረታቱ የሚገባቸው አሉ፡፡

በተለያየ የፓለቲካ ግብ ውስጥ የሚንቃቀሱ የፓለቲካ ቡድኖች ምንም እንኳን የፓለቲካ አቋማቸውን በሚደግፍ መልኩ መረጃዎችን መተንተናቸው የሚያስቀወቅሳቸው ባይሆንም፣ ቡድኖቹ ግልጽ ባልሆነ የፖለቲካ ዓላማ እና የሕዝቡን ነባራዊ ፍላጎት እና ሁኔታ ከግምት ውስጥ ባላስገባ እንቅስቃሴ የሚሰጡት ትንታኔ አቅጣጫ ወይም መረጃ አምታች እና አወናባጅ መሆን የለበትም፡፡ ይህ ዓይነቱ ችግር አገር ውስጥ ያሉትም የፖለቲካ ቡድኖች ቢሆንም በዳያስፖራዎቹ ይጋነናል የሚል እምነት አለን፡፡ ውሸት ይነግሩናል ባንልም ከነርሱ ጋር የሚያሟግተንን እውነት ሊደብቁን፣ ወይም ለነሱ ፍላጎት የሚያመዝነውን ብቻ ሊያስተጋቡልን ይችላሉ የሚለው ስጋት አገር ውስጥ ባለው ወገን ዘንድ የሚፈጠረውም ይሄን ጊዜ ነው፡፡
ለመኖሪያ ፈቃድ ሲባል…?
ለትምህርት፣ ለስልጠና፣ ለወርክሾፕ፣ ለስብሰባ፣ ለጉብኝት እና በመሳሰሉ ምክንያቶች ከአገር ወጥተው በዚያው ቀልጠው የሚቀሩ ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ እነዚህ ሰዎች አሁን አሁን እንደፋሽን የሚጠቀሙበት የፖለቲካ ጥገኝነት መጠየቅን ነው፡፡ የፖለቲካ ጥገኝነት ጠያቂዎቹን በሁለት ከፍለን ልናያቸው እንችላለን፡፡ የመጀመሪያዎቹ፤ በሚሄዱበት አገር የፖለቲካ ጥገኝነት ሊያሰጣቸው የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት አገር ውስጥ በነበሩበት ወቅት የሚያደርጉ ናቸው፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ መታወቂያ ለማግኘት መጣር፣ መንግስትን በመተቸት ከሚታወቁ ሰዎች ጋር ፎቶ መነሳት እና መንግስትን የሚቃወሙ ጽሑፎችን በግል የሕትመት ሚዲያዎች በስማቸው ማውጣትን በምሳሌ ማንሳት እንችላለን፡፡ አጋጣሚውን አግኝተው ከዚህ አገር በሚወጡበት ወቅት ቀድመው ያዘጋጇቸውን ምክንያቶች እንደማስረጃ በማቅረብ የፖለቲካ ጥገኝነት ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡ በሁለተኛው ክፍል የምናገኛቸው ደግሞ ከላይ በጠቀስናቸው ባንዱ ምክንያት ከአገር የመውጣቱን አጋጣሚ ድንገት ያገኙና  ምንም ዓይነት ቅድመ ዝግጅት ሳያደርጉ የሚወጡ ናቸው፡፡ ካገር ሲወጡ እዛው የመቅረትን ጉዳይ በአዕምሮአቸው የነበራቸው ቢኖሩም የመመለስ ዕቅድ የነበራቸው እና እዛው ባሉበት ሐሳባቸውን ቀይረው ለመቅረት የወሰኑም ይገኙበታል፡፡ 
ሁለቱንም ቡድኖች የሚያመሳስላቸው በሄዱበት ለመቅረት ያላቸው ፍላጎት፣ መኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት የፖለቲካ ጥገኝነት መጠየቃቸውና የሐሰት መረጃዎችን ለሚመለከተው ክፍል ማቅረባቸው ነው፡፡ በመጀመሪያው ቡድን ያሉት ቀደም ብለው በጉዳዩ ላይ ተዘጋጅተውበት በመውጣታቸው እንደሄዱ ማመልከቻቸውን በማስገባት  ባጭር ጊዜ ውስጥም ሊሳካላቸው የሚችል ሲሆን በሁለተኛው ቡድን ያሉት ግን የሐሰት መረጃዎችን ማሰባሰብ የሚጀምሩትና የሚያገኙት ከጥቂት ቆይታ በኋላ አንዳንድ ጊዜም የቪዛቸው ጊዜ ወደማለቁ አካባቢ ወይም ካለቀ በኋላ ስለሚሆን ለብዙ መጨናነቅ፣ ወጪና እንግልት ይዳረጋሉ፡፡ እንዲህም ሆኖ መኖሪያ ፈቃድ የማግኘታቸውና ያለማግኘታቸው ጉዳይ እኩል፣ እኩል ነው፡፡
እንደነዚህ ዓይነት “ዳያስፖራዎች” (በትዕምርተ ጥቅስ) ብዙዎቹ ስለአገራቸው የፖለቲካ ታሪክ እና ወቅታዊ ፖለቲካና ማኅበራዊ ጉዳዮች ጠለቅ ያለ መረጃ ባይኖራቸውም፣ መንግስትን የሚቃወም የማንኛውንም ግለሰብም ሆነ ድርጅት ሐሳብ ያስተጋባሉ፡፡ ለዚህም በዋነኝነት ፌስቡክ እና ትዊተርን ጨምሮ የተለያዩ ማኅበራዊ አውታሮች፣ ጦማሮችን እና ድረገጾችን እንደመሳሪያነት ይጠቀሙበታል፡፡ ባለስልጣናት ለሥራም ሆነ ለስብሰባ እነሱ ወዳሉበት ቦታ በሚመጡበት ጊዜም – ነባር፣ በእውነተኛ ተቃውሞ ጦስ ተሰድደው የወጡ የዳያስፖራ አራማጆች በሚያስባብሯቸው – ተቃውሞዎች ላይ መታደም እና በቦታው መገኘታቸውን የሚያሳይ መረጃ መያዝ ተቀዳሚ ሥራቸው ነው፡፡
በተጨማሪም በአገራችን የሚካሄዱ ኢ-ፍትሐዊ ድርጊቶችን በመቃወም የሚደረጉ ሰልፎችና አላግባብ የታሰሩ ዜጎችን ለማስታወስ የሚዘጋጁ ፕሮግራሞች ላይም ቁጥር አንድ ተሳታፊ ናቸው፡፡ ምናልባትም ከፕሮግራሙ ርዕስ በዘለለ የተዘጋጀበትን ምክንያት እና ዓላማ ላያውቁ ይችላሉ፡፡ ባጭሩ በዚህ ምድብ የሚገኙ “ዳያስፖራዎች” አብዛኛዎቹ ማለት ይቻላል የኔ የሚሉት ፖለቲካዊ አቋምም ሆነ አመለካከት የሌላቸው ሲሆን ዋነኛ ሥራቸው በመንግስት ላይ የሚሰነዘርን ማንኛውም ዓይነት ተቃውሞ ባገኙት አጋጣሚ ሲያስተጋቡ መታየት ወይም መሰማት ነው፡፡ እነዚህ ጠቅላላውን የ‹ዳያስፖራ ፖለቲካ› ውጤታማነት እንዴት እንደሚያውኩት በሚከተሉት ምሳሌዎች መረዳት ይቻላል፡-

 • የተቃውሞ ሰልፎች እና ስብሰባዎች ላይ የሚሳተፉ እነዚህ ለፖለቲካው ጤንኝነት ደንታ የማይሰጣቸው ሰዎች ‹‹ጥገኝነት›› ፈላጊዎች ግንባር ቀደም እና አርማ ተሸካሚ ሆነው በፎቶ እና ቪዲዮ ማኅበራዊ አውታሮች ላይ በአጋጣሚ የሚመለከቱ እና ግለሰቦቹን የሚያውቋቸው የአገር ቤት ሰዎች ጠቅላላ የዳያስፖራውን እንቅስቃሴ በግለሰቦቹ ዓይን የመዳኘት እና በኢቴቪ ፕሮፓጋንዳ ‹‹ጥገኝነት ለመጠየቅ ሲሉ›› የሚለውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ስለሚሆን፣
 • ግለሰቦቹ የጥገኝነት ወረቀታቸውን ካገኙ በኋላ ተመልሰው ትግሉን ስለማይቀጥሉበት፣ መጣ ቅርት የሚሉ አራማጆችን መመልከቱ/መከታተሉ ተስፋ ስለሚያስቆርጥ፣
 • ግለሰቦቹ ወረቀቱን እስከሚያገኙ ድረስ ፖለቲካዊ ተሳትፏቸውን ለማጉላት እና ተቃዋሚነታቸውን ለማሳመን ጽንፍ ድረስ ስለሚጓዙ የጠቅላላውን ዳያስፖራ መልክ በአንድ ላይ የማጉደፍ ኃይል አላቸው፡፡

እነዚህን ግለሰቦች በጥንቃቄ መጠቀም ያልቻለ የዳያስፖራ ማኅበረሰብ ወይም ዝግጅት አስተባባሪ፣ ወይም በጥንቃቄ መከታተል ያልቻለ የአገር ውስጥ ነዋሪ መስመሩን የሳተ ግንዛቤ ስለዳያስፖራዎቻችንም ሆነ ስለአጠቃላይ እንቅስቃሴያቸው ያኖራል፡፡
የዳያስፖራ ሚዲያዎች
በተለይም በፖለቲካው ዙሪያ መረጃ እና ትንታኔዎችን የሚያቀርቡ በርካታ፣ ባብዛኛው ኢንተርኔት ላይ ጥገኛ የሆኑ መገናኛ ብዙሐን አሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ በድረገጽ የሚሰሩት እነኢትዮሚዲያ፣ ዘሐበሻ፣ ኢትዮጵያንሪቪው፣… እና አሁን እየጎሉ ከመጡት ውስጥ ደግሞ ጎልጉል ሳይጠቀሱ አይታለፉም፡፡ እነዚህ መገናኛ ብዙሐን በተለይ ገዢው ፓርቲን በሚቃወሙ መጣጥፎች ላይ ምንም መመዘኛ የሌላቸው እስኪመስል ድረስ፣በአገራዊ ስነምግባራዊ እሴቶች የሚያስገምቱ ስድቦችን በማስተናገድ ጭምር ይታወቃሉ፡፡ ከነርሱ በተቃራኒው የቆሙት እና የገዢው ፓርቲን በማንቆለጳጰስ ሥራ ተጠምደው፣ ዓላማቸው ‹‹አማራጭ ሚዲያ›› መሆን ይሁን ወይም ካድሬነት የማይለዩት እነአይጋፎረም፣ ኢትዮጵያፈርስት እና ትግራይኦንላይን የመሳሰሉት ድረገጾች ደግሞ ተቃዋሚውን እስካዋረደላቸው ድረስ የሚያሰራጩት መረጃ እውነት ይሁን ሐሰት እንኳን ለማጣራት አይጨነቁም፡፡
በዚህ መሐል የሚዲያዎቹን ማንነት እና እሴት የማያውቀው አንባቢ በከፍተኛ ደረጃ ይጎዳል፡፡ አሁን በተቃዋሚ ወገን የምንመድባቸው በሙሉ በኢትዮጵያ እንዳይነበቡ በመታገዳቸው በፊት በኢትዮጵያ ከፍተኛ ጎብኚ የነበራቸው እነናዝሬት እና ኢትዮጵያንሪቪው ከዝርዝሩ ወጥተው፣ ከፍተኛ ተነባቢነት ያላቸው እነትግራይኦንላይን መሆናቸውን የአሌክሳ ዌብ ትራፊኪንግ መረጃ ያመለክታል፡፡ ይሁን እንጂ የታገዱትን ገጾች ዜናዎች በዚህም ሆነ በዚያ እያሉ (በተለይ በማኅበራዊ አውታሮች) በኩል የሚያገኙት ብዙሐን ናቸው፡፡
ከዚህ በፊት የአገር ውስጥ ጋዜጦች መለስ በመልካም ጤንነት ላይ ናቸው ብለው በማለታቸው ይቅርታ እንዲጠይቁን ወትውተን እንደነበር ይታወሳል፡፡ ከዳያስፖራ መገናኛ ብዙሐን መካከልም፣ በተለይ ኢትዮጵያንሪቪው ብዙ ባለስልጣናትን እና ባለሀብቶች ሳይቀር ሞተዋል፣ ተሰደዋል የሚሉ ዜናዎችን ጽፎ አንብበን ከጥቂት ጊዜ በኋላ ስህተት መሆኑን ሰምተናል፡፡ በተመሳሳይ እነርሱም ይቅርታቸው ይገባን ነበር፡፡ ምንም እንኳን ይህ ጽሑፍ ይህንን ርእስ ለማንሳት ባያስብም የተአማኒታቸውን ነገር ግን ችላ ማለት አይገባም፡፡፡ 
የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥንም እዚህ ምድብ ውስጥ ይካተታል፡፡ የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የዳያስፖራ እኩያው ነው መባል ከጀመረ ሰንብቷል፡፡ በፅንፈኛነት ስሙ መነሳት ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ለዚህ እንደምክንያት የሚጠቀሱት፣ ሙያዊ ስነምግባር (professional ethics) ላይ እምብዛም አለመጠንቀቃቸው፣ ከዜና እና ዜና ነክ ትንታኔዎች በላይ አንጀት አርስ ፕሮግራሞችን አለመሥራታቸው፣ ከአገር ቤት ጋር የሚገናኙ ጥቃቅን የሁከት ዜናዎችን ማጋነናቸው ሳይጠቀሱ የማይታለፉ ድክመቶች ናቸው፡፡ አማራጭ መገናኛ ብዙሐን በሌለበት ኢሳትን አለማመን ቢከብድም፣ ኢሳት ይህንን ግዳጁን በሙሉ ኃላፊነት እንዲወጣ እና በሙሉ ልብ እንዲታመን ገና ብዙ ይጠበቅበታል፡፡
እርግጥ ነው፣ እነዚህ መገናኛ ብዙሐን እዚህ አገር የታፈኑ (የተነወሩ) በርካታ እውነታዎችን ለሕዝቡ በቻሉት መንገድ ሁሉ ለማድረስ በስደት ሕይወታቸው መፍጨርጨራቸው ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ቢሆንም ጥረታቸው ዋጋ እንዲኖረው ተአማኒነት ያላቸውን መረጃዎች ለማቅረብ መድከም አለባቸው፡፡ አለበለዚያ ስናነባቸው በጥርጣሬ እንዲሆን ልንገደድ እንችላለን፡፡
የዳያስፖራ ምሁራን እና አራማጆች
በኢትዮጵያ ያሉ ምሁራን ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚያስደፍር ሁኔታ ዝምታን በመረጡበት በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ ምሁራዊ እይታ እንዳያጣ ትንሽ የረዱት የዳያስፖራ ምሁራን እና ሌሎችም ለነፃነት ተቆርቋሪ ስደተኛ አራማጆች ናቸው፡፡ እነአለማየሁ ኃይለማርያም፣ እነመሳይ ከበደ፣ ጃዋር መሐመድ እና ሌሎችም ሳይጠቀሱ አይታለፉም፡፡
የዳያስፖራ ምሁራን በተለያዩ ከላይ በጠቀስናቸው እና ሌሎችም መገናኛ ብዙሐን የሚያቀርቧቸው ትንታኔዎች ምንም እንኳን በአብዛኛው ወደሚደግፉት ቡድን ርዕዮት ያመዝናሉ የሚል ሐሜት ቢያጋጥማቸውም በዳያስፖራው ማኅበረሰብ ተአማኒነት ያለው መረጃ በመስጠት የተሻሉ ናቸው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት፣ ብዙ ጊዜ መከራከሪያ ነጥቦቻቸው እውነታዎች እና ሳይንሳዊ ርዕዮተ ዓለሞች መሆናቸው ነው፡፡ በተጨማሪም እነዚህ ምሁራን የሚያቀርቧቸው ጽሑፎች እንደሌሎቹ አጫጭር መጣጥፎች ከስድብ ይልቅ አመክንዮ ይበዛባቸዋል፡፡ ስለዚህ የምሁራኑን ትንታኔ እያነበቡ የራስን ውሳኔ መውሰዱ ጠቃሚ እንደሚሆን መደምደም ይቻላል፡፡
በጥቅሉ፣ ፖለቲካ ቀመስ የሆኑ ጽሑፎችን የምናነበው ወይም የምንጽፈው መረጃ ለመለዋወጥ ያክል ብቻ ሳይሆን ለብሔራዊ ለውጥ ጉጉት ስላለን ነው፡፡ ቢሆንም ግን በአገር ውስጥም ሆነ በዳያስፖራው ውስጥ ብሔራዊ ብቻ ሳይሆን ግለሰባዊ አጀንዳ ያላቸውም ሰዎች አሉ፡፡ ይህ በተለይ በኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች ላይ ያተኮረው ጽሑፋችን ዓላማም፣ የዳያስፖራ ፖለቲካ ውስጥ ‹‹ማን፣ ምን እና ለምን›› የሚለውን በማገናዘብ ሁሉንም በጽንፈኝነት ወይም በተቃራኒው የዋሕነት ብቻ ሳይቀበል እንዲመረምር በማድረግ ማኅበራዊ ተዋስኦን ማበረታት ነው፡፡

በተለይ በጉዳዩ ላይ ከዚህ በፊት በተነሱ አስተያየቶች ዳያስፖራው ለሚታማበት ጽንፈኝነት የራሳቸውን ምክንያት የሚዘረዝሩ አሉ፡፡ ከነዚህ ምክንያቶች ውስጥ እኛ (በአገር ውስጥ ነዋሪዎች) በባሕላዊ አስተሳሰቦች እና በዴሞክራሲ መብት እጦት የታፈነ ማኅበረሰብ ውስጥ የነጻነትን ትክክለኛ ትርጉም እና ጣዕም በአግባቡ ማጣጣም ባለመቻላችን የመጣ ክፍተት እንደሆነ የሚናገሩ አሉ፡፡ በተጨማሪም፣ አንዳንዴ የነጻነትን ትክክለኛ ጣዕም ያጣጣሙ ስደተኞች ያን ዓይነቱ ለውጥ ወደአገር ቤት በተቻለ ፍጥነት እንዲመጣ ማሰባቸውም ለአንዳንድ ስህተቶች እንደሚዳርጋቸው ይታመናል፡፡ ዞሮ፣ ዞሮ እዚህም ያለነው ወይም እዚያ ያሉት የምንታገለው ለጋራ ለውጥ ስለሆነ እነርሱም እኛን፣ እኛም እነርሱን የምናደምጥበት መድረክ እና ቋንቋ ያስፈልገናል፡፡

የኢሕአዴግ ስርዓት፤ ፍጹም የበላይነት ወይስ የሕግ የበላይነት?

ይህ ጽሑፍ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ባካሄደው ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ ካቀረብኩት ንግግር የተወሰደ ነው፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ በስብሰባው ላይ ተገኝቼ ንግግር እንዳደርግ ዕድል ለሰጠኝ ፓርቲ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡
በቃል የቀረበውን በጽሑፍ ለማሰናዳት የፈለግኩበት ምክንያት በመጀመሪያ በጽሑፍ ሲቀርብ ሰፋ ላለ አንባቢ ተዳራሽ ስለሚሆንና በሁለተኛ ደረጃ ይህን መጽሔት [አዲስጉዳይ] ጨምሮ በሌሎች የሕትመት ውጤቶች ላይ ሲስተናገድ ትክክለኛው የሐሳብ ምስል ስላልቀረበ ምናልባት በዚህ ጽሑፍ የተሟላ መልዕክቱን ማስተላለፍ ይቻላል በሚል እምነት ነው፡፡…
ታሪክና ፍልስፍና
የሰው ልጅ በብዙ መልኩ ከታሪክ ሊማር ይገባዋል፡፡ ሆም ግን የረዥም ጊዜ የታሪክ ሒደት የሚያሳየው ሰው ከታሪክ መማር እንደሚያዳግተው ነው፡፡ ይህንንም ትዝብት ታላቁ የጀርመን የ19ኛው ክፍለዘመን ፈላስፋ ሄግል ‹‹ታሪክ የሚያስተምረን ነገር ቢኖር የሰው ልጅ ከታሪክ አለመማሩን ነው›› ሲል ገልጾታል፡፡
ኢሕአዴግም ሆነ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለያዩ ጥያቄዎች ላይ ኢ-ታሪካዊ አቀራረብ እንዳላቸው ለማየት አያዳግትም፡፡ ኢሕአዴግን በተመለከተ የድርጅቱ ምሁራን ታሪክን የሚጠቅሱት አንድም ካለፈው የተሻሉ መሆናቸውን ለማስረዳት አሊያም በፍፁም ከዚህ በፊት ያልነበረ አዲስ ነገር የፈጠሩ አድርገው ለማቅረብ ነው፡፡
የዚህ ዓይነት የታሪክ ዕይታ ችግሩ አንደኛ ‹‹የታሪክን ቀጣይነትና ተከታታይነት›› (continuity and discontinuity) በመሠረቱ የሚድንና ላለንበት ወቅት የታሪክ አሻራ ዕውቅና የማይሰጥ ነው፡፡ በመሆኑም ኢሕአዴግ አብዛኛውን ጊዜ ትኩረት የሚሰጥ የታሪክ ቀጣይ አለመሆን ላይ ነው፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ለፖለቲካችን ይበጀናል ከሚሉት የታሪክ ዕሳቤ ውጭ በትረካቸው ውስጥ ስለማያካትቱና አሁን ባለንበት ዘመን በተገኘ መስፈርት ታሪክን ከአውድ ውጪ እያዩ ስለሚፈርጁ የተዛባ ታሪክ አቀራረብ ይይዛሉ፡፡
ከአንዳንድ ተቃዋሚዎችም ወገን ቢሆን አልፎ አልፎ የታሪክ መዛባት ይስተዋላል፡፡ እንደማሳያ ለማንሳት የደርግን ስርዓት በሚያነሱበት ጊዜ የሚሰጡት አስተያየት አንድም እኩይ ድርጊቱን ያድበሰበሰ አሊያም ለስርዓቱ ይቅርባይነት ያደላ (Apologetic) ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
ፍልስፍናም አንድን ጉዳይ ለማብራራትና ለመረዳት ብዙ ጊዜ ቀጥተኛ መንገድ ይዛ አትጓዝም፡፡ ግልገል ያየች ንስር አደኗ ላይ ተምዘግዝጋ ከማረፏ በፊት ዙሪያውን እንደምታንዣብብ ሁሉ ፍልስፍናም የጉዳዩን ፍሬ ነገር የምታስረዳው ዳር ዳሩን ከዞረች በኋላ ነው፡፡ እኛም በቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ከመግባታችን በፊት ግላዊ ኃላፊነት (Equality of Responsibility)፣ የሕዝብ መልካም ፈቃድ (Individual of consent)፣ እንዲሁም የሕሊና ነጻነት (Idea Conscious) የሚባሉት የዴሞክራሲያ መርሆዎች በአውሮፓ እንዴት እንደፈለቁ አጠር ባለ መልኩ እመለከታለን፡፡
የክላርክ ታሪካዊ ማህደር
ጊዜው 1647 ዓ.ም. ነው፡፡ የእንግሊዝ አብዮት ንጉሡን ከዙፋን በማውረድ በድል ተጠናቋል፡፡ የአብዮቱ መሪ ተዋንያ የአገሪቱ የፖለቲካ ስርዓት ምን ዓይነት መልክ መያዝ እንዳለበት ለመወሰን ትልቅ ስብሰባ ይዘዋል፡፡ ከተሰብሳቢዎቹ ውስጥም አንደኛ የአብዮቱ ዋ መሪ ሰር ኦሊቨር ክሮምዌል፣ ሁለተኛ የወግ አጥባቂው ፓርቲ መሪ ሚስተር አየርተን፣ ሦስተኛ የሰራዊቱ መሪ ኮሎኔል ሬይንቦ፣ አራተኛ በቃለ ጉባኤ ያዥነት የተመደቡት ሚስተር ክላርክ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
ሀ – ግላዊ ኃላፊነት
በስብሰባው ላይ የተነሳው የመጀመሪያው ርዕሰ ጉዳይ በስልጣን ባቤትና በምርጫ ዙሪያ ነበር፡፡ ተሰብሳቢዎቹ ከእንግዲህ ወዲያ ስልጣን የሚገኘው በምርጫ መሆኑን ከተቀበሉና ዕውቅና ከሰጡ በኋላ አከራካሪ ሆኖ ያገኙት ‹‹ለመምረጥ ሕጋዊ መብት ሊያገኝ የሚገባው ዜጋ የትኛው ነው?›› የሚለው ነበር፡፡
ለዚህም የመጀመሪያው ሐሳብ አቅራቢ የወግ አጥባቂው መሪ ሚ/ር አየርተን ነበሩ፡፡ በእርሳቸው አቀራረብ የመምረት መብት ሊሰጠው የሚገባው ዜጋ ንብረት ያካበተ መሆን አለበት፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ንብረት የሌለው ሰው ለጉዳዩ ብዙ አትኩሮት ሳይሰጥ አገሪቱን ሊጠቅምና ሊጎዳ የሚችለው ፖለቲከኛም ሳያስበው እንዲሁም በተጨማሪ በቀላሉ እየተደለለ ድምፁን ሊያስረክብ የሚችል በመሆኑ ነው፡፡
በአንጻሩ ኮሎኔል ሬይንቦው ይህን ሐሳብ በመቃወም አስተያየታቸውን እንደሚከተለው አቅርበዋል፡፡ ‹‹ለመምረጥ የንብረት ባለቤትነት እንደመስፈርት መቅረቡ በሰው ል ላይ የመብት ጥሰት መፈፀም ይቆጠራል፡፡›› ካሉ በኋላ ይኸውም አንድ ደሀ እንግሊዛዊ እነቶኔ ከአንድ ሀብታም እንግሊዛዊ እነቶኔ እኩል በሆነ መልኩ ሕይወቱን የመምራትና የመወሰን መብት ስላለው የመምረጥ መብት ተጎናፃፊነቱ መነካት እንደሌለበት አስረድተዋል፡፡
በእንግሊዝኛ የተናገሩትን ብንጠቅሰው ‹‹The poorest he that is in England has a life to live as the richest he›› ነበር ያሉት፡፡
ይሄ ሐሳብ በመሠረቱ የምርጫ ጉዳይ ቢሆንም ይዘቱ ግን ሰፋ ብሎ እያንዳንዱ ዜጋ ሕይወቱን ለመምራት ብቸኛው ወሳኝ እርሱ መሆኑንም የሚያስገነዝብ ነው፡፡ ከዚያም አኳያ ስለ ነጻነት ምንነት በ20ኛው ክ/ዘመን መባቻ ላይ ‹‹what is liberity?›› ወይም ‹‹ነጻነት ምንድን ነው?›› የሚለውን ወሳኝ ድርሳን የጻፈውን ጆን ስትዋርት ሚል (John Stwart Mill) የኮሎኔል ሬይንቦውን ሐሳብ በማጠናከር እንደሚከተለው ያስረዳል፡፡ ‹‹አንድ ሰው በመሠረቱ ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሕይወቱን የመምራት መብት አለው፡፡ ይህም ማለት መብቱን በሚተገብርበት ጊዜ የሌላውን ሰው መብት ባልነካና ጉዳት በማያስከትል መልኩ ሊሆን ይገባል፡፡››
በታላቁ ስብሰባ ላይ እየተሳተፉ ያሉት ሰዎች፣ የኮሎኔል ሬይነቦው ሐሳብ ተቀባይነት ካገኘ በኋላ ወደ ሁለተኛው ርዕሰ ጉዳይ ተሸጋገሩ፡፡
ለ – ሕዝባዊ ስምምነት/ የሕዝብ መልካም ፈቃድ (consent)
መንግስት በመሠረቱ ሄዶ ሄዶ በሕዝብ መልካም ፈቃድ ላይ ማረፍ አለበት፡፡ በሌላ አነጋገር ከስዩመ እግዚአብሔርነት ወደ ስዩመ ሕዝብነት መሸጋገር ማለት ነው፡፡ ይህም የዘመናዊነት አንድ መገለጫ ነው፡፡
አሜሪካውያን ከእንግሊዝ በነፍጥ ነጻነታቸውን ከተቀዳጁ በኋላ ባስፋፉት የነጻነት ስልጣን የሚያገኘው ተገዢዎች ከሚሰጡት መልካም ፈቃድ ነው፡፡ (Governments derive their power from the consent of the governed) ማለታቸው ይህንን ያጠናክረዋል፡፡
የእንግሊዝን አብዮት በግንባር ቀደም የመሩት ተዋንያን ባካሄዱት ስብሰባ ላይ የነበረው አስተሳሰብ ማንም ሰው ወደስልጣን የሚመጣው የሕዝብን በጎ ፈቃድ ከተጎናፀፈ ብቻ ነው የሚል ብሒል ነበር፡፡
ይህንን የሕዝብ መልካም ፈቃድ ዕሳቤ በሚመለከት ከስብሰባው ታዳሚዎች አሁንም እንደገና ሁለት ተቃራኒ ሐሳቦች ቀርበው ነበር፡፡ በመጀመሪያ ሚስተር አየርተን ‹‹በመሠረቱ የሕዝብ መልካም ፈቃድና መንግስት እንደ ፅንሰ ሐሳብ አብረው መሄድ የማይችሉ ናቸው›› (Consent and government are not compatible) አሉ፡፡
ይህንን ሐሳባቸውንም ሲያብራሩት በሁሉም ነገር ላይ የሕዝቡ መልካም ፈቃድ የሚጠየቅ ከሆነ ስርዓት አልበኝነትእንደሚሰፍን በመግለጽ ነው፡፡
ኮሎኔል ሬይንቦው በተራቸው ለሚስተር አየርተን ስጋት የሚከተለውን መፍትሔ አቅርበዋል፡፡ በኮሎኔሉ አባባል የሕዝብ መልካም ፈቃድ ሲባል ለሁሉም ጉዳይና ለሚደነገገው ሕግጋት በመላ ሕዝቡ የግድ መልካም ፈቃዱን መስጠት አለበት ማለት አይደለም፡፡ የሕዝብ መለካም ፈቃድ ማለት ለሕግ አውጪዎች የውክልና ፈቃድ በመስጠት መሆን ማለት ነው፡፡ እዚህጋ ልብ ማለት የሚገባን የውክልና መንግስት ፅንሰ ሐሳብ የሚመነጨው ከዚህ ሐሳብ መሆኑን ነው፡፡
የውክልና መንግስትና የተደራጀ ተቃዋሚ በፅንሰ ሐሳብ ደረጃ ሊነጣጠሉ የማይችሉ ናቸው፡፡ በመሆኑም የዴሞክራሲያ መሠረታዊ ዕሳቤ የሐሳቡን አንድነት ማስተጋባት ብቻ ሳይሆን በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ አስተያየቶችን እንዲያንሸራሽሩ በመፍቀድና በመጨረሻም በብዙሐን ተቀባይነት ያገኘውን ማጽደቅ ነው፡፡
ዴሞክራሲ ማለት የታይታ ስምምነት (Unanimity) የሚፈጠርበት መስክ አይደለም፡፡ እዚህጋ የሕዝብ እንደራሴዎች ወይም ወኪሎች ወደፓርላማ ድምጹን ሰጥቶ የላካቸው ሕዝብ ወኪል ብቻ ናቸው ወይስ የራሳቸው የአስተሳሰብ ልዕልና ኖሯቸው ለአገር ይበጃል ብለው ባመኑት ነገር ላይ የግል አቋም ይወስዳሉ? የሚሉ ጥያቄዎችን ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ እንዲሁም ‹አንድ የፓርላማ አባል አላስፈላጊ ሆኖ ስታገኘው/ሲያገኘው ከፓርቲያቸው መርሕ የሚጻረር አቋም ሊወስዱ ይችላሉ ወይ?› ብሎ መጠየቅም ያስፈልጋል፡፡
በነዚህ ጥያቄዎች ዙሪያ ማለትም ከወከሉት ማኅበረሰብ (Constituency) ወይም ከፓቲ መርሕ ውጪመንቀሳቀስ ይቻላል ብለው ወሳኝ ድርሳናት የጻፉት የ18ኛው ክ/ዘመን የእንግዙ ፈላስፋ ኤድመንድ በርክ (Edmund Burke) እና የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ናቸው፡፡
ኤድመንድ በርክ ‹‹Letter to the sheriff of Bristol›› በሚለው መጣጥፍ ላይ ‹‹እኔን መርጣችሁ የላካችሁን የበሪስቶል ነዋሪዎች ብትሆኑም ባለኝ አዕምሯዊ ብቃት አምናችሁ ከመረጣችሁኝ በኋላ ፓርላማው ውስጥ በሚነሳው ክርክር እናንተ የምትፈልጉትን ብቻ ሳይሆን እኔ በግሌ ለአገር ይበጃል ብዬ የማምንበትን አቋም ከማንፀባረቅ ወደ ኋላ አልልም፡፡›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ጆን ኤፍ ኬኔዲ ደግሞ በበኩላቸው ‹‹profiles in courage›› (የጀግንነት አርኣያዎች ብለው አቶ ተሻገር ውቤ በተረጎሙት) መጽሐፋቸው ላይ የአሜሪካንን የ200 ዓመት የምክርቤት ታሪክ አጥንተው በተለያየ ጊዜ ከፓርቲያቸው ወይም ከወካዮቻቸው ፍላጎት ውጪ የአጠቃላይ አገርን ጥቅም በማስቀደም በግል የደረሰባቸውን ጫናና ጉዳት ተቋቁመው የጀግንነት ተግባር ፈፅመዋል ብለው ስለመረጧቸው የም/ቤት አባላት አትተዋል፡፡
ከሁለቱ ሰዎች አስተምህሮ የምንገነዘበው ነገር ቢኖር ተወካዮች አልፎ አልፎም ቢሆን በራሳቸው እምነት ሊጓዙ እንደሚገባ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ፓርላማ ከውክልናው ጋር አብሮ የሚሄድ የውይይት አጀንዳ የማፍለቅ ሚናም አለው፡፡ በፓርላማ የሚነሳው ሐሳብ በተለያዩ ሕዝባዊ አጀንዳ ይሆናል፡፡ ከዚህም የተነሳ ሰዎች የድጋፍና የተቃውሞ አቋም ይይዙበታል፡፡
የሞቀ ውይይት የሌለበት ፓርላማ እንደሞተ ባሕር በውስጡ ምንም ሕይወት አይኖረውም (ሕይወት አልባ ነው)፡፡
ሐ- ግላዊ ሕሊና ወይም የሕሊና ነጻነት
የእንግሊዝ አብዮት በተካሔደበት ወቅት የሃይማኖት ድባብ በጣም ጠንካራ የነበረበት ጊዜ ነበር፡፡ በተለይ አብዮቱን የመሩት ሰር ኦሊቨር ክሮምዌል በእጅጉ መንፈሳዊና የሃይማኖት ሰው ነበሩ፡፡ የተቀሩት የስብሰባው ተሳታፊዎችም ቢሆኑ ለሕሊና ነጻነት ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጡ ነበሩ፡፡
ቃሉ እንደሚያመለከተው ‹‹የሕሊና ነጻነት›› ማለት የፈለግነውን ማመን፣ የፈለግነውን መርሕ መከተል፣ የፈለግነውን ሃይማኖት መቀበልና በፈለግነው ወግ የመተዳደር መብትን የሚያጎናፅፍ ነው፡፡
እዚህ ላይ ማስታወስ የሚገባን ከብዙ ዓመታት የሃይማኖት ጦርነት በኋላ አውሮፓውያን ወደሰላምና መቻቻል እንዲመጡ ያደረገው ይኸው የሕሊና ነጻነት (Liberty of conscious) ዕሳቤ ተቀባይነት በማግኘቱ መሆኑን ነው፡፡
ከዚህ ዕሳቤ በመነሳትም ኦሊቨር ክሮምዌል ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን አስመልክቶ ‹‹እግዚአብሔር በማን አንደበት አንደሚናገር ስለማይታወቅ ለሁሉም ዜጋ የመናገር መብት ሊሰጥ ይገባል›› የሚል አስተያየት አቀረቡ፡፡ ነገር ግን አየርተን ይህን ሐሳብ በጥርጣሬ በመመልከት ‹‹ማንም እየተነሳ እግዚአብሔር አናገረኝ እያለ የሚሆንና የማይሆን ወግ ቢያቀርብ ምን ልናደርግ ነው?›› ሲሉ ሞገቱ፡፡
ለዚህም ጥያቄ ኦሊቨር ክሮምዌል ‹‹መቼም ሁላችንም እንደምናውቀው እግዚአብሔር የምክንያታዊነት አባት ነው፡፡ ስለዚህም የማይበጅና ኢ-ሞራላዊ መልዕክት በማንም አንደበት አያስተላልፍም፡፡ አንድ ሰው እግዚአብሔር ገልጾልኛል ወይም አናግሮኛል ብሎ ሲነሳ የነገሩን ጭብጥ መርምረን በእርግጥም እግዚአብሔር እንዳናገረው እና እንዳላናገረው ማወቅ ይቻላል፡፡ ይህንንም ማድረግ የሚቻለው ለሁሉም ሰው መብት ሰጥቶ ሐሳቡን በነጻነት የመግለጽ መብትን በማክበር ነው የሚል ምላሽ ሰጡ፡፡
ስለዚህ ከዚህ የምንረዳው የመናገር ነጻነት ዕሳቤ መሠረት ያገኘው ‹‹እግዚአብሔር በማንም አንደበት ሊናገር ይችላል›› ከሚል ሃይማኖታዊ አመለካከት መሆኑን ነው፡፡
የኢሕአዴግን የፖለቲካ ስርዓት በጥቂቱ
የኢሕአዴግ የፖለቲካ ስርዓት በጥቂቱም ቢሆን ለመተንፈሻ ስንነሳ አልክዛንደር ኸርዝን የተባለ የ19ኛ ው ክ/ዘመን ዕውቅ የራሺያ የስነጽሑፍ ሰው በአንድ ወቅት የሰነዘረውን ንፅፅሮሻዊ ንግግር እንደመንደርደሪያ እንውሰድ፤ እንደ ኸርዝን አቀራረብ፣ ‹‹አንድ እንግሊዛዊ ወይም አሜሪካዊ ‹እኔ እንግሊዛዊ ነኝ› ወይም ‹እኔ አሜሪካዊ ነኝ› ብሎ ሲል፣ አንድምታው ዜግነቱን ብቻ ሳይሆን ነጻ ሰው መሆኑንም እየነገረን ነው፡፡ በአንጻሩ አንድ የጀርመን ተወላጅ ‹እኔ ጀርመናዊ ነኝ› ሲል ‹እኔ በግሌ ነጻ ሰው አይደለሁም፡፡ የአገሬ ንጉሥ ግን ታላቅና ከሌሎችነገሥታት የሚበልጡ ናቸው› ማለቱ ነው፡፡››
ሰሞኑን ‹‹ታላቁ መሪ›› እየተባለ የሚቀርበውን ስሰማ አሌክዛንደርን ኸርዝን ከመቶ ዓመታት በፊ የተናገረውን እንዳስታውስ ያደርገኛል፡፡
ወደስርዓቱ ትንተና ስንገባ ካለፉት ሁለት ስርዓቶች ስያሜዎች አኳያ በአሁኑ ስርዓት ላይ መሠረታዊ ጥያቄ እናነሳለን፡፡ እነደ ፖለቲካ ፈላስፋዎች አስተምህሮ የፖለቲካ ስርዓት ስያሜዎች በየራሳቸው መፍትሔዎቻቸውን ይጠቁማሉ፡፡ ለምሳሌ ‹‹ፍፁማዊ የዘውድ አገዛዝ›› ስንል መፍትሔው መንግስታዊ የዘውድ አገዛዝ ይሆናል፡፡ ‹‹ወታደራዊ አምባገነንነት›› ስንል ቃሉ ራሱ እንደመፍትሔ ሕገመንግስታዊ ስርዓትን ይጠቁማል፡፡ ወደኢሕአዴግ ስንመጣ ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ›› የሚለው ስያሜ እንደመፍትሔ ምን ያስቀምጥልናል?
የኢሕአደግ ጉዳይ ከፖለቲካ አኳያ ውስብስብ የሚያደርገው ስርዓቱ የፖለቲካ ሕይወቱን የጀመረው ሕገመንግስት አዘጋጅቶ በማቅረብ ነው፡፡ በመሆኑም ኢሕአዴግ ከሕገመንግስቱ ጋር ያለው ግንኙነት ምን ይመስላል ብሎ መፈተሸ ተገቢ ይሆናል፡፡ ከዚህም በመነሳት የኢሕአዴግን ስርዓት ከሕገመንግስቱ አኳያ ስንፈትሸው ሙሉ በሙሉ ሕገ መንግስቱን ጥሎ አውሮፓውያን ቄሳራዊ (Ceaserism) እንደሚሉት ፈላጭ ቆራጭ ስርዓት ሙሉ በሙሉ አልመሠረተም፡፡ ከዚህ ይልቅ የኢሕአዴግ አካሔድ ሕገ መንግስቱን በከፊል እየሻረ ሲያሻው ደግሞ እያከበረ የሚንቀሳቀስ ስልጣን በጥቂት ሰዎች እጅ ያከማቸና እንዲሁም መሪዎች የሕግ ማዕቀፍ ሳይጣልባቸው የፈለጉትን የሚያደርጉበት ስርዓት (Authourianism) ነው፡፡
የኢሕአዴግ ፍፁማዊ የበላይነት በከፊል የሚመነጨው ስለ ‹‹ፖለቲካል›› ፅንሰ ሐሳብ ካለው አመለካከት ነው፡፡ ለመሆኑ ለኢሕአዴግ ‹‹ፖለቲካል›› ማለት ምን ማለት ነው? በሌላ በኩል ‹‹ፖለቲካል›› የሚለው ፅንሰ ሐሳብስ በድርጅቱ በኩል እንዴት ነው የሚገለፀው ብለን ስንነሳ እነርሱ በጽሑፍ ላይ ያሰፈሩት ሐሳብ ባይኖርም በተግባር እንደታዘብነው ለኢሕአዴግ ፖለቲካል ማት ወዳጅና ጠላት የሚለይበት መስክ ነው፡፡
ይኸው ፖለቲካን የወዳጅና የጠላት መለያ አድርጎ የመጠቀሙ አካሔድ በ20ኛው ክ/ዘመን አጋማሽ የጀርመን ቀኝ ክንፍ አቀንቃኝና የሕገ መንግስት ምሁር የነበረው ካርል ሽሚት ቀርቦ ነበር፡፡
ወዳጅና ጠላት እየለዩ መንቀሳቀስ የሚለው ብሒል ለዴሞክራሲና አብት ለሚመጣው ብዝሐነት በእጅጉ ተፃራሪ ነው፡፡ ይኸውም የሚሆንበት ምክንያት ወዳጅ ሲባል የማቅረብ፣ ጠላት ሲባል የመደምሰስ አካሔድን እንጂ በውይይትና ሰጥቶ በመቀበል መርሕ ላይ የተመሠረተ ባለመሆኑ ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ ለኢሕአዴግ ፖለቲካ የሁለት አፅናፍ ተፋላሚዎች መድረክ ስለሚሆን ዕርቅና ድርድር ለይስሙላ ቢቀርቡም ኢሕአዴግ ከደደቢት እስከ አዲስ አበባ የገጠማቸውን ኃይሎች አንድም አካቶ የራሱ አድርጓል አሊያም ደምስሷል፡፡ በሌላ አነጋገር የፓርቲው ታሪክ፣ ከተላያዩ ተቀናቃኞቹ ጋር የገጠመውን ችግሮች በዴሞክራቲክ ውይይት ለዘለቄታው የፈታ ስለመሆኑ አያሳይም፡፡
ኢሕአዴግ ስልጣን በጥቂት ሰዎች እጅ ሲከማችና መሪዎች የሕግ ማዕቀፍ ሳይጣልባቸው የፈለጉትን የሚያደርጉበት ስርዓት ነው ስንል የሐሳብ የበላይነት እንዲኖረው የሚያደርገውን እንቅስቃሰና ስለሕግ የበላይነት መጥቀስ አስፈላጊ ነው፡፡
የሐሳብ የበላይነት
ማንኛውም መንግስት (ፓርቲ) የሐሳብ የበላይነት እንዲኖረው ይጥራል፡፡ ኢሕአዴግም የሐሳብ የበላይነቱን ለማረጋገጥና ለመጎናፀፍ መከጀሉ የሚያስተቸው አይደለም፡፡ ጥያቄ የሚያስነሳበትና ትችት የሚጋብዝበት ማግኘት አለብኝ ብሎ የሚያስበውን የሐሳብ የበላይነት ለመቀዳጀት የተሠማራበት መንገድ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ሁለት ነገሮችን ማንሳት እንፈልጋለን፡፡ አንደኛ ኢሕአዴግ የመገናኛ ብዙሐን ሙሉ ለሙሉ በመቆጣጠር ለራሱ ፍፁማዊ ጥቅም ለማግኘት ይገለገልበታል፡፡ ይሄ ሙሉ በሙሉ የመቆጣጠር ፍላጎት የፖሊሲ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የስርዓቱ ወሳኝ አካል ነው፡፡
ሁለተኛ የዚህ ሙሉ በሙሉ መገናኛ ብዙሐንን የመቆጣጠር ዓላማ የሕዝብን በጎ ፈቃድ ለመፈብረክ ነው፡፡ ይህን በሚያደርግበት ጊዜ የፖለቲካና የርዕዮተ ዓለም ፉክክር እንዲኖር አይፈቅድም፡፡ ይህንንም የአዕምሮ ውጤት ማምረቻ (Means of Mental production) መቆጣጠር ለምን እንዳስፈለገ ለመረዳት የስዕልና የሙዚቃ አቀራረብን እንደምሳሌ እንውሰድ፡፡
ሙዚቃም ሆነ ስዕል እሙን ከመሆናቸው በፊት የምንም ነገር አለመኖርን (nothingness) ቅድመሁኔታቸው ያደርጋሉ፡፡ አንድ የሙዚቃ ኮንሰርት ከመቅረቡ በፊት አዳራሹ ሰጥ ረጭ ማለት አለበት፡፡ ከሙዚቃው ውጪ ያሉ ድምፆች በሙሉ የመደመጥ ፉክክርን እንዳይፈጥሩ ይወገዳሉ፡፡ በስዕል በኩልም አንድ ሰዓሊ የሚስልበት ወይም የምትስልበትን ሸራ ከስዕሉ ውጪ ያሉ ተፎካካሪ ቀለማትን ለማጥፋት በነጭ ቀለም ይቀቡታል፡፡ ልክ እንደሙዚቃው እና ስዕል ኢሕአዴግም ተፎካካሪ የሚላቸውን የሐሳብ ድምፆችና የአመለካከት ምስሎች አስወግዶ ያለውድድር የራሱን ብቸኛ የአመለካከት ውጤት እንዲንሰራፋ ያደርጋል፡፡
የሕግ የበላይነት
የኢሕአዴግ ስልጣን በጥቂት ሰዎች እጅ ሲከማችና መሪዎች የሕግ ማዕቀፍ ሳይጣልባቸው የፈለጉትን የሚያደርጉበት ስርዓት ዋናው መሠረቱ ከሕግ ልጓም የተላቀቀና ያሻውን ያለገደብ ስልጣንን መጠቀም ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት የተወሰኑ ነጥቦችን እናያለን፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ በሕግ የበላይነት (rule of law) እና በሕግ የመገዛት (rule by law) መካከል ልዩነት እንዳለ ማስታወስ የግድ ይላል፡፡ ይህ ሲባል ሕጋዊነት፣ የሕግ የበላይነት አካል ነው እንጂ የሕግ የበላይነት አጠቃላይ ገላጭ አይደለም፡፡
በመሆኑም ሕጉ ለመንግስት የፈለገውን ለማድረግ ገደብ የለሽ ስልጣን ቢሰጠው ድርጊቱ ሕጋዊ ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ግን በሕግ የበላይነት ማዕቀፍ ስር ሊወድቅ ይችላል፡፡ የሕግ የበላይነት የመንግስትን ማንአለብኝነት ስለሚገታው ለዴሞክራሲ ማበብ ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡
ሌላው የauthoritarianism (ስልጣን በጥቂት ሰዎች እጅ ሲከማችና መሪዎች የሕግ ማዕቀፍ ሳይጣልባቸው የፈለጉትን የሚያደርጉበት ስርዓት) መገለጫ የራሳቸው ልዕልና ያላቸው መንግስታዊ ያልሆኑ ማኅበራት እንዲኖሩ አይፈቅድም፡፡
መደምደሚያ
በዚህ ጽሑፍ መግቢያ ላይ ሦስት የዴሞክራሲ መርሖችን አንስተን ነበር፡፡ ሀ. ግላዊ ኃላፊነት፣ ለ. በሕዝብ በጎ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ መንግስት እንዲሁም ሐ. የሕሊና ነጻነት ናቸው፡፡
እነኚህ ሦስት የዴሞክራሲ ብሒሎች ሰፋ ያሉና የተወሳሰቡ ሐሳቦችን ያቀፉ በመሆናቸው በአንድ የመጽሔት አምድ ላይ አጠቃላይ ይዘታቸውን እና የያዙትን እንደምታ ማቅረብ ያስቸግራል፡፡ ሆኖምግን በነዚህ ሐሳቦች ዙሪያ ከአገራችን ጋ በቀጥታ በተያያዘ ጉዳይ አንድ ሁለት ነጥቦቸን አንስተን ጽሑፋችንን እናጠቃልላለን፡፡
እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱን ሕይወት የመምራት መብት አለው ሲባል፣ መንግስት ሕጋዊ ካልሆነ በቀር ጣልቃ የመግባት መብት እንደሌለው መታወቅ አለበት፡፡ ሆኖም ግን በኢትዮጵያ ገዢው ፓርቲ ገበሬውን ‹‹በዓመት ይህን ያክል ቀን በነጻ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ላይ መሳተፍ አለባችሁ፡፡ እምቢ ካላችሁ የገንዘብ ቅጣት ይከተላል፡፡›› እየተባለ ገበሬው በግዴታው የግል እርሻ ሥራውን በመተው ተራራ ሲቆፍር እንዲውል ተደርጓል፡፡
እንዲህ ዓይነት ድርጊት ላይ የሕግና የሞራል ጥያቄዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ አንደኛ ገበሬው ለሚመጣው ትውልድ ጠቀሜታ ሲባል የተወሰነ ጊዜውን መስዋዕት አድርጎ ተከፋይ ባልሆነበት የጉልበት ሥራ ላይ እንዲሰማራ ማስገደዱ ችግር የሚሆነው አገሪቱ የገበሬዎች ብቻ ሳትሆን የሁላችንም ስለሆነች መስዋዕትነት መክፈል ካስፈለገ ሁላችንም መክፈል አለብን እንጂ ገበሬው ብቻ ተመርጦ ሳይከፈለው መሥራት አለበት የሚል እምነት የለኝም፡፡ እንደመንግስት ሪፖርት ከሆነ 26 ሚሊየን ገበሬ በዚህ የጉልበት ሥራ ላይ ተሰማርቶ ከ8 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያለው ገቢ በጉልበት መልክ መንግስት አግኝቷል፡፡
ምናልባት እዚህ ላይ ቆም ብለን ነገሩን ስናገናዝብ በአብዮት ጊዜ ‹‹መሬት ላራሹ›› የሚለው ጥሪ ያስተጋባው ገበሬው አርሶ የላቡን ዋጋ አላገኘም በሚል ነበር፡፡ አሁንም እንደትላንቱ ‹‹መሬት ላራሹ›› እንደተባለ ‹‹ሒሳብ ለላቡ›› ብለን የምንጠይቅበት ጊዜ ላይ የደረስን ይመስለኛል፡፡
በሕዝብ በጎ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ መንግስት ጽንሰ-ሐሳብን በተመለከተ ኢሕአዴግ የርዕዮተ ዓለም ውድድር እንዳይኖር ከማድረጉም ባሻገር መሬትን እና የከተማ ቤትን እንደፖለቲካ መሳሪያ በመጠቀም የሕዝብን መልካም ፈቃድ ለማግኘት የሚያደርገው የማያልቅ እንቅስቃሴ ነው፡፡ በመሠረቱ ‹ሕዝባዊ ፈቃድ› ወይም ስምምነት የሚባለው ቃል እንደ አንድ ዴሞክራቲክ መርሕ ሲታይ ‹‹ዜጎች የፈለጉትን እንዲመርጡ ልዕልና አላቸው›› ከሚል መሠረተ ሐሳብ የፈለቀ ነው፡፡
ሆኖም ግን በአገራችን የገጠር መሬትን እና የከተማ ቤትና ቦታን ይዞታን ተቆጣጥሮ የዜጎችን የፍላጎቶቻቸውን የመወሰንና የመበየን አቅማቸውን በእጅጉ አዳክሞታል፡፡ በመሆኑም ይህ ሁኔታ ምርጫ ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ያሳርፋል፡፡
ለማጠቃለልም በእኔ እምነት ኢሕአዴግ ሕገ መንግስት አርቅቆ ሕገመንግስታዊነትን ሳይሆን በሁሉም መስክ ፍፁማዊ የበላይነትን የተጎናፀፈ ስርዓት ነው፡፡
—–
ይህ ጽሑፍ በአዲስጉዳይ መጽሔት ቅጽ 6 ቁጥር 134 የተስተናገደ ነው፡፡

አፋዊነት… (Sweet Talk)


በብርካን ፋንታ

ሁላችን ከሆንን የቋንቋ ፈላስፋ
በተግባር መስካሪ አንድም እንዳይጠፋ

ይህ የእዮብ መኮንን ዘፈን ግጥም የዚህን ጽሑፍ ገዢ ሐሳብ ይገልፃል፡፡ ሲነገር ከንፈር የማያደናቅፍ፣ ሲደመጥ ጆሮ የማይኮረኩር፣ በአዕምሮ ሲሰላሰል የማይጎረብጥ በተግባር መሬት ላይ የማይተገብሩት የአፍ ፈሊጥ /leap service/ በከተማችን በርክቷል፡፡ በጊዜ ብዙ ሰዎችን ታዝበናል፡፡ድሮም ትልቅ ነበርክየሚል የግጥም ፉካሬ በጌትነት እንየው ከመስማት በላይ፣ በፍትህ ጋዜጣመንግስት መዶሻ ነው፤ ሕዝብ ደግሞ ምስማርሲለን ከነበረ አምደኛግድቡ በአቶ መለስ ይሰይምምስላቸው በብር ይታተምየሚል ጭብጥ የያዘን ተውኔት ድርሰት ከማየት በላይ፤ ወደ መልካምም ወደ ክፉም አገራችንን በሚመራው በዛች ቀውጢ ሰዐት ፍፁም ከሚያምኑት “Meles Zenawi is back in town” የሚል ዘገባ ከማንበብ በላይ፤አገር ማለት የኔ ልጅየሚል ውብና ጥልቅ መልዕክት ያለው ግጥም ገጣሚ / በድሉ ዋቅጅራ በፍትህ ጋዜጣ አምደኛ በሆኑ ማግስት ለጠ/ሚሩ መታሰብያ ግጥም መድረክ ላይ ሲያነበንቡ ከማየት በላይ ሌላ የመከዳት ስሜት የሚፈጥር ምን ነገር አለ?! ምንም የለም!

ይህ ጽሑፍ የአቶ መለስ ዜናዊን መልካም ያልሆነ አስተዳደር ለመተችት የተነሳ አይደለም፡፡ ወትሮም አቶ መለስ በሕይወት በነበሩበት ጊዜ የሚበጀንን ነው የሚያደርጉት ብለው ሲሞግቱ ለነበሩትም አይደለም፡፡ ክፉ ናቸው፤ በደለኛ ናቸው የሚል ወንጀል ሲያቀርቡ የነበሩት ሲሞቱ ደግሞ በተቃራኒው መላዕክትነታቸውን ሲሰብኩ ለከረሙት ታዝበናል፣ አይተናል ለማለት ነው፡፡ የቀድሞ / ተፈጥሯዊ ሞት የአንዳንድ ግለሰቦች ጭንብል አስወለቀ እንጂ ይህ ችግር በአደባባይ መታየት ከጀመረ ሰንበቷል፡፡ አቶ መለስ ዜናዊ ራሳቸው የተሳተፉበትእንደገናየተሰኝ ዘጋቢ ፊልም ላይ እንዲህም የሚል የአፍ ፈሊጦችን አድምጠን ነበረ፡፡

ዋናው ሕሊና ነውሕሊና ደግሞ ከሁሉም በላይ ነው መሆን ያለበት! ፍትሕ፣ ስርዓት ሁል ጊዜ ፐርፌክት አካሄድ ከሄደ በዚች ምድር፣ በዚች አገር ምንም አይከሰትም፡፡
(
አትሌት ኃይሌ /ሥላሴ)

ይህን የተናገረው 1997 ምርጫ ምክንያት በታሰሩ የፓለቲካ እስረኞች እና መንግስት መሐል በሽምግልና የተሰየመው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ /ሥላሴ ነው፡፡ ወዳጄ እንደሚለው ኃይሌ እግረ ብርሃን እንጂ ልበ ብርሃን እንዳልሆነ አልዘነጋሁም፡፡ ሆኖም ግን በአፈጠጠ እውነት ላይ ተደራድሮ እስረኞቹን 12 ዓመት ሕፃን ባንክ እንዲዘርፍ ልከን አሳስተን ነው ያስገደልነው የሚል የይቅርታ ሰነድ ሕሊናው እየተመለከተ ፈርመዋል፡፡ ያን ጊዜ ሕሊናውን ከወዴት ሰውሮት እንደነበረ አላውቅም፡፡ በየትኛው የሞራል እርከን ላይ ቆሞ ሰለሕሊና እንደሚሰብክም አይገባኝም፡፡ ዛሬ የስፖርት ጋዜጠኛ ፍስሐ ተገኝና የመሳሰሉት ሕሊና እያለን ያልተፈፀመውን 11 ዓመት ታዳጊ ባንክ ሊዘርፍ ነበር የሚል ዜና አላነብም ሲሉ ከአገር ተሰደው እየኖሩ ነው፤ እነኃይሌ በአንፃሩ ዋናው ነገር ሕሊና ነው እያሉን ነው፡፡ ታዲይ ይህ ምንድን ነውይህ የአፍ ፈሊጥ ነው፡፡


ዋናው ነገር አባይን እገድባለሁ ብሎ ማሰቡ ነው ትልቅ የሚያደርገንለእኔ አባይን እንገድባለን ብለንማሰባችነው ዋናው ቁም ነገሩ!…አገራዊ ጉዳዮችን መለየት አለብን፤ ያለንበት 21ኛው መቶ ክፈለ ዘመን የተለያዩ ፓርቲዎች፤ የተለያዩ ርዕዮት ዓለሞች፣ የተለያዩ የአሠራር መንገዶች የተለያዩ ነገሮች ያለበት ነው፡፡ እብርነት ውበትነት የሆነበት ዘመን ላይ ነው ያለነው፤ ከዚህ ውጭ መሆንም አንችልም፡፡ ግን እንደገና ደግሞ እነዚህን ሁሉ የሚያስተባብር አንድ ነገረ አለ፤ እርሱም ኢትዮጵያ የሚባል ነገር አለየፖለቲካ ፓርቲዎች ልንመሠርት የምንችለው፣ ልንከራከር የምንችለው፣ አሸንፈን ፓርላማ ልንገባ የምንችለው፣ ተሸነፈን ልንወርድ የምንችለው፣ ኢትዮጵያ የምትባል አገር ስትኖር ነው፡፡
(
ዳንኤል ክብረት)

ጤናማ ሞራል እንዲኖረን በጽሑፉ የሚተጋው፣ታሪኩን የዘነጋ ትውልድ እንደተፈጠረ በበሰለ ጽሑፍ ሸንቆጥ የሚያደርገው፣ ወጋችንን ተረታችንን መዘንጋት እንደሌለብን የሚያስታውሰው፣ ከድንጋዩ ይልቅ ሰዉ ክቡር እንደሆነ የሚመክረው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በቀረበው ዘጋቢ ፊልም ከተናገረው የተቀነጨበ ነው፡፡ ከአፄ ልብነድንግል ጀምሮ አባይን ለመገደብ ሐሳብ የነበራቸውን ነገሥታት ታሪክ ዋጋ በማሳጣት ዛሬ እንገድባለን ብለንማሰባችንብቻትልቅእንደሚያደረገን ሰብኮናል፡፡ ኢትዮጵያ የምትባል ነገር ያለ ሕዝብ ነጻነት በፍትሕ ላይ ባልተመሰረተ የፖለቲካ አስተዳደር ልትፀና እንደምትችል ከታሪክ አስታዋሻችን ምክር እየተለገሰን ነው፡፡ ይህ የዳንኤል ንግግር ከአፍ ፈሊጥነት እና ገዢው ፓርቲ ላዘጋጀው ፕሮፓጋንዳ ማጣፈጫነት የዘለለ ምን ውሃ የሚያነሳ ነገር አለው?ምንም! ይሄም የአፍ ፈሊጥ ነው!

እነዚህ ለአስረጅነት ቀረቡ እንጂ በፖለቲከኛው፣ በኪነ ጥበበኛው፣ በጋዜጠኛው፣ በነጋዴው፣ በሐኪሙ እና በሌሎችም በቀላሉ ማንም ሊያስተውለው የሚችል አገራችንን ወግቶ የያዘ ችግር ነው፡፡ ይህ አፋዊነት በዚሁ ከቀጠለ በአገራዊ ደረጃ የሚያመጣው ልክ ያልሆነ የትውልድ አስተሳሳብ ብዙ ዋጋ ያስከፍላል፡፡

አሲምባ ተራራላይ ውረዱ!

በእውቀቱ ስዩም “ኗሪ አልባ ጎጆዎች” ባሰኘው ግጥሙ ውስጥ አያቶች የወጠኑትን፣ አባቶች የገነቡትን ቤት ልጆች ምን እንደሚሉት በቅኔ ወርዶት ሲያበቃ እንዲህ ዘግቶታል፡-
የአያቶቻችን ቤት፥ ይሁን ባዶ፣ ይሁን ኦና
በኛ ቁመት፣ በኛ መጠን አልተቀለሰምና፡፡ (ግጥሙን በቃሌ ስለወጣሁት ቃላት ልገድፍ እችላለሁ!)

ከአሁን በፊት የነበረው ትውልድአሲምባ ተራራላይ ያስወጣው ድንጋይና ሳሩ አይመስለኝም፡፡ ወጣት ግምባር ላይ ጥይት የሚያሰድድ፣ የሴት ልጅን ጡት የሚያስቆርጥ፣ ከአንድ ማሕፀን የወጡ ሁለት ወንድማማቾችን ጎራ አስለይቶ የሚያታኩስ አስተሳሰባቸው ነው ወደ አሲምባ ተራራ ላይ ያስወጣቸው፡፡ ትውልድ› ዘመኑ ያፈራውን አስተሳሰብ አላምጦ ለአገሬ የሚበጃት ይህኛው ሕሳቤ ነው የሚል ስሌት ላይ ጽኑ እምነት ጨምሮ ውድ የሆነውን ሕይወቱን ያለምንም ፍርሐት ከፍሏል፡፡ ከፋም ለማም ትውልድ› ይበጃል ያለውን አድርጓል፡፡ አሁን የ‹ያ ትውልድ› ክሽፈት ታሪክ መዝገብ ወይም ትውልዱ አብሰልስሎ አገሪቱ ያስመለሳትን ሐሳብ የምንወቅጥበት ጊዜ ላይ አይደለንም፡፡ ኢሕአፓ፣መኢሶን፣ ሰደድን እያጣቀሱ፤ ፋኖ ተሰማራን እየፎከሩ ሕዝቡ ከተጨበጠበት የፍርሐት ቆፈን ለማላቀቅ መሞከር ዘመንን ያለማገናዘብ በጥልቅ ያለማሰብ ችግር ነው፡፡ ገዢው ፓርቲን የሚሞግት የሚያሳጣ ፓሊሲ፣ ተቋም፣ መዋቅር እና የፖለቲካ ርዕዮት ዓለሙ ላይ ከመመራመር ይልቅ እገሌ ደርግ ነበር፣ ኢሕአዴግ ጣኦት ነው፣ ሰውዬው ኤርትራዊ ነው፣ አራማጅ ነኝ፣ ሕዝብ ፈሪ ነው፣ መብራት ተቆረጠ፣ መብራት ተቀጠለ ሐሳቦች እኛን አያነቁም፡፡ ሕዝቡ ከተከናነበው የፍርሐት ጃኖም አያላቅቅም፡፡ ዛሬ እንደ በፊቱ ኧረ ጎራውን ብቻ ፎክሮ፣ ቀረርቶ አቅራርቶ፣ እንደው በደፈናው በሽላላ የምትነቃ ኢትዮጵያ አይደለም ያለችው፡፡ ይህን መሳይ ችግር በብዛት በጋዜጣ ጸሐፊዎቻችን የሚስተዋል ነው፡፡ ይሄን ዘመን ያገናዘበ የዚህን ትውልድ ጥያቄ መመለስ የሚችል አስተሳሰብ ያነገበ አገርን ወደፊት ሊያራምድ የሚችል ጽሑፍ ብናገኝ ነው የራሳችንን አሲምባ መፍጠር የምንችለው፡፡ እንደው በደፈናው ኢሕአዴግ ክፉ ነውና ደረታችሁን አቀብሉ ሐሳብ አሁን ያለውን አምባገነናዊ ስርዓት ያጸና እንደሆነ እንጂ ለአገር አይበጅም፡፡ 1997 .. ባልተመረመረ ፖለቲካ ደረታችንን አቀብለን የከፈልነው ዋጋ የሚዘነጋም አይደለም፡፡

መድኀኒቱን ስጡን
ቃልን መርጠን ከየቤቱ
ለመናገር መጎምዥቱ
ለእኛስ ነው ወይ መዳኃኒቱ?”

ችግራችንን በተለያዩ ተረቶችና ምሳሌዎች መዘርዘር የአዋቂነት ልኬት የመሆን አዝማሚያ ይስተዋላል፡፡ ፔዳል፣ ብስክሌት፣መዶሻ፣ ምስማር፣ድስትና ክዳን፣ የግሪክ አፈ ታሪኮች፣ የአበው ተረቶችን እያጣቀሱ በሽታችንን ማብራራት አሳቢነት (Thinker) አይደለም፡፡ ሲታከክልን ዝም ብለን እንጂ ቁስሉን አዝለን ከምንዞረው ከኛ በላይ በሽታውን የሚያውቅ የለም፡፡ አሁን ያለው ስርዓት ለአገራችን ፈፅሞ እንደማይበጃ ከኑሮ በላይ የሚያስረዳ ነገር የለም፡፡

ደራሲዎች፣ ገጣሚዎች፣ ጋዜጠኞች እና ሌሎች ጸሐፊዎች በመንደር ከሚወራው በተሻለ ለአደባባይ የሚበቃ ሐሳብ አለኝ እና ወደ ጋዜጣ መጥቻለሁ ስትሉ የበሽታውን መድኀኒት ጠቁሙን፤ አብዮታዊ ዲሞክራሲ የሚለው መርሕ አይበጀንም ስትሉ የሚበጀንን ርዕዮተ ዓለም አሳዩን፡፡ ይሄ መንግስት መውረድ አለበት ስትሉ፣ እንዴት መውረድ እንዳለበት መንገዱን ስጡን፡፡ በደፈናው ስለተበደልን ብቻ ሕይወታችሁን ማግዱ አትበሉን፡፡ እንደው ብድግ ብሎ ሕዝብ ቄጤማ ነው የሚል ፈሊጥ አንስቶ የቄጤማን ልፍስፍሰነት እየተነተኑ ሕዝቡ ፈሪ እንደሆነ መተንተን ተራማጅነት አይደለም፡፡ ይሄ ፈፅሞ ለአገርም አይረዳም፡፡

ማቅ ልበስ፤ ውደቅ በንስሐ
እንደ ቶን ፍም እሳት ይፋጃል ይልሳል
መንገዱ ከሲኦል ያደርሳል፤
የደበቅከው እውነት ሳይጮህ በበረሃ
ማቅ ልበስ ውደቅ በንስሐ
(አቤል ሙሉጌታ)

ዛሬ ይርጋለም ዱባለንና ሰለሞን ተካለኝን እየኮነኑ በደላቸውን ሊያጥቡ እየሞከሩ ነው፤ ዛሬ የራሳቸውን ጉድፍ ሳይነቅሉ ሌላው ንስሐ እንዲገባ እየሞገቱ ነው፡፡ በሁለት በኩል ተስላችሁ፣ እምነት አጉድላችሁ፣ ለስጋችሁ አድልታችሁ፣ ንዋይ አሳውሯችሁ፣ ዝና ባርቆባችሁ፣ እውቀት ስንክሎባችሁ፣ ሌላም ሌላም ምክንያት ኖሯችሁ በደል ስለፈፀማችሁ ወግዱ ሂዱ ለማለት ተፈልጎ አይደለም፡፡ የአፍ ፈሊጣችሁ በእምነት ከሆነ እንሞግታችሀለን፤ በስህትት ከሆነም ይቅር እንላችኋለን፡፡ ሁለት አሥርትመታት በስቃይ ለመሩን መሪ ለአንድ ቀንም ቢሆን ከልብ አዝነናል፤ ለይቅርታ ፍፁም ቅርብ መሆናችንን ያመላክታል፡፡ እኔ ስለአቶ መለስ ዜናዊ አንባቢነት ነው የጻፍኩት፣ የኔ ተቋም ይቅርታ ጠይቋል፣ የሰው እንጂ የራሴን ግጥም አላነበብኩም ዓይነት ሰንካላ ሰበብ ክደቱን አያክምም፡፡ ሁሉም ለፈፀመው በደል የራሱ የሆነ ምክንያት አለው፡፡ በቀጣይነት አምነናችሁ ብርሃናችሁን እንድንቀበል፣ ያለጥርጣሬ ፍሬያችሁን እንድናጣጥም አጥጋቢ የሆነ ማብራሪያ አሊያም ከልብ የሆነ ይቅርታ ይገባናል፡፡ ይሄ በደላችሁን ያጥባል፤ነጥቆ እንዳልነጠቀ ማባበልሕሊናችሁን አይበጀውም፡፡

ከአፍ ፈሊጥ በዘለለ ጥረት አድርጋ በነበረችው ዳኛ ብርቱካን ሚደቅሳ በአሜሪካ ለሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ባደረገችው ንግግር ሐሳቤን እቋጫለሁ፡፡

“…የዚህ ፕሮግራም ዋና ዓላማ እንደሚመስለኝ ኢትዮጵያን ማወደስ ነው፡፡ እያሰብኩት ነበረእውን ኢትዮጵያ የምትወደስ ናት ወይ እያልኩኝይሄን በሐቀኝነት ስንመልስ ብዙ ቅር የሚያሰኙ ነገሮች አሉ፡፡ ከቅሬታም በላይ የሆኑ፤ ምክንያቱም ኢትዮጵያ የነጻነት አገር አይደለችም፡፡ ኢትዮጵያ የፍትሕ አገር አይደለችም፡፡ ኢትዮጵያ ዛሬም ዜጎቿ በድህነት የሚኖሩባት በሐፈረት የሚያቀረቅሩባት፣ ብዙ ዜጎቸ የሚሰደዱባት ነች፡፡ ስለዚህ እናወድሳት ውይ ብለን እንጠይቅ፡፡አይ መወደስማ አለባት የሚል አቅም ነው ያለኝ፡፡ ስናወድሳት ግን ምን አስበን ነው? ኢትዮጵያ ታላቅ አገር ነበረች፤ ይህን እኔ አይደለሁም የምናገረው ታሪክ ነው የሚመሰክረው መልዕክቴ ይሄው ነው:: ኢትዮጵያ ልትወደስ የሚገባት ታላቅ አገር ነች! ታለቅነትን ለማየት ግን ሁሌም በአንድነት እንቁምአንድነታችን ሁላችንንም የሚያቅፍሁላችንንም የሚያሰባስብና የኢትዮጵያ የጋራ መኖሪያነት በሚያውቁት ይሁን፡፡
(
ብርቱካን ሚደቅሳ)

አሜን ይሁን! … “አንድነታችን ሁላችንንም የሚያቅፍ፤ሁላችንንም የሚያሰባስብና የኢትዮጵያ የጋራ መኖሪያነት በሚያውቁት ይሁን”… ይሁን!

የዓለም ሃይማኖቶች እና ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት

አቤል ዋበላ

መግቢያ
አንቀጽ ፲፰
እያንዳንዱ ሰው የሐሳብ የህሊናና የሃይማኖት ነጻነት መብት አለው፤ ይህም መብት ሃይማኖቱን ወይም እምነቱን የመለወጥ ነጻነትንና ብቻውን ወይንም ከሌሎች ጋር በኀብረት በይፋ ወይም በግል ሁኖ ሃይማኖቱን ወይም እምነቱን የማስተማተር በተግባር የመግለጽ የማምለክና የማክበር ነጻነትን ይጨምራል፡፡
አንቀጽ ፲፱
እያንዳንዱ ሰው የሐሳብና ሐሳቡን የመግለጽ መብት አለው፤  ይህም መብት ያለጣልቃ ገብነት በሐሳብ የመጽናትንና ዜናን ወይም ሐሳቦችን ያላንዳች የድንበር ገደብ የማግኘትን፣ የመቀበልን ወይም የማካፈልን ነጻነትን ይጨምራል፡፡
እንዲህ ጎን ለጎን አጠጋግቶ ያሰፈራቸው ዓለም አቀፉ የሰብኣዊ መብቶች ድንጋጌ (UDHR) ነው፡፡ ይሁንና በድንጋጌው በቅደም ተከተል እንደመስፈራቸው ሲስማሙ አይሰተዋልም፡፡ በአንድ ያለማችን ክፍል ያለ የማመን መብቴ ተደፈረ የሚል ግለሰብም ሆነ ቡድን በሌላው የዓለማችን ክፍል የሚገኙ ሰዎችን የመናገር ነጻነት ሲደፈጥጥ ይሰተዋላል፡፡ ሌላው የመናገር መብቴ ገደብ የለውም የሚል ደግሞ የሌላውን ሰው የማመን መብት ሲጥስ እና በአማኒው እሴቶች ሲያፌዝ ተመልክተናል፡፡ ይህ እሰጥ አገባ በተለያዩ እምነቶች፣ በአማኞች እና እምነት የለሾች፣ ባስ ሲል ደግሞ አንድ እምነት አለን ብለው በሚናገሩ ቡድኖች መካከልም ይስተዋላል፡፡ በቅርቡ በሀገረ አሜሪካ በ‹ዩቲዩብ› የተለቀቀ አንድ ቪድዮን ተከትሎ በተነሳው ብጥብጥ ምክንያት ይህ ርዕሰ ጉዳይ  በዓለም ዙርያ መነጋገገሪያ ሆኗል፡፡ ዐሳብን በነጻነት መግለጽ እስከምን ድረስ ነው? እስከመቼ እምነቶች የነውጥ እና ሁከት መነሾ ምክንያት ሆነው ይቀጥላሉ? የሚሉ ጥያቄዎች በብዙዎች በሕሊናቸው እንዲያመላለሱ አድርጓል፡፡
በሀገራችን ዓለም አቀፉን ወጀብ የተከተለ ትርምስ ባይፈጠርም አንዳንድ ብልጭታዎች መታየታቸው አልቀረም፡፡ በተለይ ሁለቱ የየሀገራችን ሰፊ ተከታይ ያላቸው እምነቶች (እስልምናና ክርስትና) ‹‹ያለመሪ›› የሃይማኖት አባት በተቀመጡበት በዚህ ወቅት ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢና የሰከነ ውይይትን የሚጠይቅ ነው፡፡ የኢሕአዴግ መንግስት በተለመደ ስልቱ እኔ ብቻ ላውራ ስለሚል ቄሱም ሼኩም የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ካህናት እንዲሆኑ ይፈለጋል፡፡በዚህም ምክንያት እንኳን በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ጉልህ ተጽዕኖ ያላቸው እምነቶች ይቅርና ሌላው ግለሰብም ይናገር፣ የተለየ አስተሳስብ ይኑረው፣ ያን ይገልጽ፣ ያንፀባርቅ ዘንድ አልተፈቀደለትም፡፡ ለዚህ ማሳያ እሩቅ ሳንሄድ ይህች ጦማር በኢትዮጵያ እንዳትነበብ የደረሰባት ተደጋጋሚ እገዳ ማሳያ ነው፡፡ ይህ ጽሑፍ ከሰው ልጅ መሠረታዊ እሱነቱ ጋር የተያያዙት እምነት እንዲሁም ዐሳብ መግለጽን እንዴት ማየት አለብን የሚለውን በመዳሰስ ለውይይት መነሻ የሚሆን ዐሳብን ለማቅረብ ይሞክራል፣ ለማብራራት የሚሞክረው ‘ይህ እምነት ልክ ነው፣ ያኛው ጸብ አጫሪ  ነው ወይም እምነቶች ሁሉ ልክ ናቸው የሚለውን ሳይሆን የተለያየ እምነቶች ያሉበት ሀገር (በተለይ ኢትዮጵያ) እንዴት ትኑር የሚለውን ይሆናል፡፡የውይይታችን ማጠንጠኛም ከዚህ ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩርም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

መቻቻል እና የተዛባ ትርጉሙ
አብዮታዊ ዴሞክራሲ ካመጣብን ቃላትና የተዛቡ ዐሳቦች አንዱ  ‘መቻቻል’ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የእምነት ጉዳዮች ሲነሱ የመንግስት ሚዲያዎች ይህንን ቃል ደጋግመው በመጥራት ግጭቱን የሚያበርዱ ይመስላቸዋል፡፡ መቻቻል መቻቻል፣ መቻቻል፣. . . . ይህ ግን ከእምነቶቹ ዶግማ አንጻር ከተመለከትነው እጅጉን የተንሸዋረረ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በመሠረቱ ሁለት የተለያዩ የእምነት አስተምህሮዎች ሊቻቻሉ አይችሉም፤ ተቻቻሉ ከተባለም አንዱ አንዱን ካልጨቆነ በስተቀር ሌላ ሁለቱንም ያልሆነ ሦስተኛ አዲስ እምነት ነው የሚሆኑት፡፡ ይህ ለሌሎች ጉዳዮች ሊሠራ እንደሚችል የተለያዩ ንደፈ-ሐሳቦች ሰፊ ማብራሪያን ይሰጣሉ፡፡ ነገር ግን ብዙ አዝማናትን ለተሻገሩት በብዙ ክርክር ላለፉት እንደ ክርስትና እና እስልምና ካሉ እምነቶች ጋር ግን አይገጥምም፡፡ አንድ በሀልዎተ እግዚአብሔር በሚያምን እና ይህች ዓለም አስገኝ፣ ፈጣሪ የላትም ብሎ በሚያምን መካከል የተቀመጠ ዐሳብ ካለ ሌላ አዲስ አስተሳሰብ ነው፡፡ ለምሳሌ ፈጣሪ ሊኖርም ላይኖርም ይችላል ብሎ እንደ መጠርጠር ያለ፡፡ በክርስትና “እግዚአብሔር አንድ ልጁን ለሁሉ ቤዛ አድርጎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶታል” ሲል በእስልምና ደግሞ  በግልጥ “አላህ አይወልድም፣ አይወለድም” ይላል፡፡ ታዲያ የመንግስት ባለስልጣናት እንዴት ነው መውለድ እና አለመወለድን ለማቻቻል ጥረት የሚያደርጉት???
ይህንን እንደ ጥቁር ከሰልና እንደ ነጭ ወተት ያለ ልዩነት በማድበስበስ፣ ለእምነት ተቋማት ተቋማዊ ነጻነታቸውን በመስጠት በቡድን አሊያም በግል የፈለጉት እምነት እንዲከተሉ ከመፍቀድ ይልቅ የቄሳራዊ ጳጳስነት (Caesario papal) መንገድን መከተል ይዟል፡፡ ይህም እምነት ተቋማቱን በቀሚስ ለባሽ ካድሬዎች በእጅ አዙር ለመምራት የሚደረግ ጥረት ነው፡፡ በአደባባይ ለሚዲያ ቀለብ ይሆን ዘንድ የካህናትቱን መስቀል ሲሳለሙ እና በየመስኪዱ ሲሰግዱ በማሳየት እኛም በእምነት ጥላ ስር ነን (ምእመን ነን)  ለማለት ይሞከራል፡፡ ይህም በየእምነቱ፣ በአማንያን አለመመራት፣ ተቋማቱን በተገቢው መንገድ ለማስተዳደር ባለመቻላቸው  ምክንያት ብሶት፣ ቁጭትና ጥያቄዎች እንደፈጠሩ አድርጓል፡፡ ለዚህ እንደምሳሌ የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን ጥያቄዎች ማንሳት ይቻላል፡፡
መንግስት አብዮታዊ ዴሞክራሲ ነው የምከተለው (አብዮታዊ ዴሞክራሲ በራሱ ከእምነቶች ጋር ብዙ የሚያላትም ገጾች ቢኖሩትም ዛሬ ከተነሳንበት ዐሳብ ጋር የሚሄደውን ብቻ ይዘን እንሄዳለን፡፡) ቢልም እምነቶችን በተመለከተ በሕገ መንግስቱ ላይ እንደሰፈረው “መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፤ ሃይማኖት በመንግስት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም” ማለቱ በእምነቶች ላይ ያለው አመለካከት ኢ-ሃይማኖታዊ ሴኩላሪዝም (irreligion or secularism) መሆኑን በግልጽ ያሳያል፡፡ በዚህም ምክንያት ሃይማኖቶች ከብዙ መንግስታዊ አካላት (መንግስት ከሕዝብ ተነጥሎ እንደተለየ አካል ተቆጥሮ) ከአገልግሎት ሰጪ፣  ከትምህርት ተቋማት፣ ከመንግስት ሚዲያ ከመሳሰሉት. . .  ሲገለሉ በተግባር አይተናል፡፡ ብዙዎቻችንም የሁከት፣ የብጥብጥ ስጋት ስላለብን ጉዳዩን በዝምታ ይሁንታን አጎናጽፈነዋል፡፡ ይህም ለችግሮች መፍትሔ የመሆን አቅም ያላቸው የእምነት በጎ እሴቶች እንደአማራጭነት እንኳን እንዳይታዩ አስገድዷቸዋል፡፡
በመሠረቱ ሴኩላሪዝም እንደመድህን መቀበል ተገቢ አይደለም፡፡ በየትኛውም መስፈርት የኢ-ሃይማኖታዊነት (ሴኩላሪዝም) ሕይወት መርህ ሳይንሳዊ አይደለም፤ ሃይማኖታዊ የሕይወት ዘዬም እንዲሁ ሳይንሳዊ አይደለም፡፡ ሳይንስ;- ሴኩላሪዝም ከአማኒነት እንደሚሻል ማሳየት አይችልም ምክንያቱም ጉዳዩ ከሳይንስ በላይ (beyond science ) ነውና፡፡ የሃይማኖት ኀልዮት በአመክንዮ ጥያቄ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል የታመነ ነው፡፡ ይህንንም ማድረግ፣ መጠየቅ የቅኖች መንገድ ነው፡፡   በሴኩላሪዝም እውነት እና በሃይማኖት እውነት መካከል ያለው ውዝግብ ግን በመደበኛ ሎጂክ ሊፈታ አይችልም፡፡ ይህ እውነታ በሁለት እምነቶች መካከልም ለሚካሄድ ክርክርም አይሰራም፡፡ የእስልምናን ስህተት ለማሳየት መጽሐፍ ቅዱስ (Christian scriptures) መጥቀስ እንደማለት ነው፡፡ለክርስቲያን መጽሐፍት ከቅዱስ ቁራን እና ሌሎች የበለጠ ስልጣን መስጠት ኢ-ምክንያታዊነት ነው፤ ከመጽሐፈ ሞርሞንም ቢሆንም የበለጠ የስልጣን የበላይነት የለውም፡፡
ይህ ሴኩላሪዝምን እንደገለልተኛ የማየት አካሄድ የተዛባ ነው፡፡ ምክንያም ሴኩላሪዝም ይህ ዓለም ከየት እንደመጣ እና ወዴት እንደሚሄድ የራሱ ትንታኔ አለው፡፡ ይህንን ካደረገ ከሌሎች ሃይማኖቶች ምን ለየው? ከጸበኞች መሀል አንዱን መርጦ ዳኛ አደርጎ መሾም ሲከፋ ደግሞ “እነዚህን አመጸኞች ግረፋቸው” ብሎ ልምጭ እንደመስጠት ያለ ነው፡፡ ሴኩላሪዝም የተውኔቱ አካል (entity) ነው እንጂ አዘጋጅ፣ አጋፋሪ ወይም ጸሐፌ ተውኔት ሊሆን አይገባውም፡፡ መንግስት ሴኩላሪዝምን እንደ ኀልዮት የማበረታታት መብት የለውም፤ በጉልበት ታንክ  ተደግፎ  ግን ተችሏል፡፡ ይህ ግን አላዋጣንም፡፡ ታሪካችንም ይህንን አያስተምረንም፡፡ ሀገሪቷ ጠንካራ ማኅበራዊ ጅማት ስላላት እንደሀገር መቀጠል ችላለች፤ ነገን ግን መተንበይ አንችልም፡፡
ከሴኩላሪዝም ባሻገር
ታዲያ ሴኩላሪዝም መፍትሔ ካልሆነ መፍትሔው ምንድን ነው የሚለውን ማጥናት ይገባል፡፡ በመሰረቱ ወደድንም ጠላንም አምልኮ ከሰው ልጅ ጋር የተሳሰረ፣ ከስሜት በላይ የሆነ አቅም ያለው ኃያል እንደሆነም ተረድተናል፡፡ብዙዎች ፍልስፍናን እና ሐሰሳን ለሕሊና ሰጥተው ለሃይማኖት ደግሞ ተረትን ይሰጣሉ፤ ከቀደሙት እጅግ የበዙት ደግሞ ሃይማኖት ፀረ-ሕሊና ወይም ህየንተ ሕሊና ሆኖ የሚቆም ነገር አይደለም፤ መልዕልተ ሕሊና ነው እንጂ ነው ይላሉ፡፡ ከሕሊና በላይ ነው እንደማለት፡፡ በዚህም ምክንያት ሃይማኖት እንደ ተበላ ዕቁብ የምንዘነጋው እንደ አረጀ አፈጀ ልማድ አሽቀንጥረን የምንጥለው ነገር አይደለም፡፡ ከዚህ ይልቅ የእምነትን መሠረታዊ ባሕርያት በማጥናት መፍትሔ መፈለግ ይበጃል፡፡
የትኛውም እምነት ሁለት መልኮች አሉት፤ የመጀመሪያው ይህች ዓለም ከየት እንደመጣች፣ ሰዎች በምድር ላይ እንዴት መኖር እንዳለባውቸውና ከሞት በኋላ ደግሞ ተስፋቸው ምን እንሆነ የሚያትት ነው፡፡ ይህም በየእምነቱ ሊቃውንት የሚተነተን ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ የተለየ መብት (privilege) የሚሰጥ ሌሎችን የሚያገልል (exclusivist) የተንኳሽነት ባህርይ ያለው ነው፡፡ ይህም ሕዝብ  አሕዛብ፣ አማኒ ኢ-አማኒ፣ የተጠመቀ ያልተጠመቀ ብሎ የአዳምን ዘር የሚከፋፍል ነው፡፡ ይህ ልዩነት በመቀጠሉ በማኀበረሰቡ ውስጥ ከፍ ያለ ቦታ የሚያገኙ እና የገንዘብ ጥቅም የሚያገኙ የእንጀራ ገመዳቸው ከእነዚህ የእምነት ተቋማት ጋር የተሳሰረ ሰዎች ደግሞ ልዩነቱን የበለጠ እንዲሰፋ ተግተው ይሰራሉ፡፡እውቁ  ጸሐፊ ሰልማን ሩሽዲ  የቁጣ መፈልፈያ (outrage industry) የሚላቸው ዓይነት ነገር ናቸው፡፡ እነዚህ ኃይላት እምነትን የወግ አጥባቂዎች ማጎሪያ፣ የቁጡዎች መነሐሪያ፣  ኋላቀር፣  ማኅበረሰባዊነትን የሚንድ፣ ከሕሊና ውጪ ያለ (anti-rationale) ያደርጉታል፡፡
ሁለተኛው የእምነት ገጽ ደግሞ በተቃራኒው ሁሉን ሰብስቦ የሚያቅፍ፣ ስለሰብዓዊነት የሚሰብክ፣ የሰው ልጆችን የሚያስተሳስር ነው፡፡ ለበጎ ምግባር ሰውን የሚቆሰቁስ፣ ያጣው እንዲያገኝ፣ ያለው የበለጠ እንዲኖረው፣ የወደቀ እንዲነሳ፣ የታመመ እንዲድን፣ ለፍጹምነት ናፍቆት ያለው (nostalgic) ነው፡፡ በአጠቃላይ በነገረ መለኮት ዕውቀት ከመራቀቅ ይልቅ ስለፍቅር አብዝቶ የሚጨነቅ ነው፡፡  በእኛ ማኅበረሰብ ይህ መልክ የመጉላት አዝማማሚያ አለው፡፡ አቡነ ዘበሰማያት አንዴ መዝለቅ የማይችሉ ወይም “ያላህ ያረቢ አትበለን እምቢ” ብለው በእምነት ከማይመስላቸው ጋር ሳይቀር በፍቅር የሚኖሩ፤  ከአሕዛብ ጋር አትብላ! ከካፊር ጋር አትወዳጅ! የሚለውን ስብከት አልፈው (transcendence) ተካፍለው የሚበሉ ኢትዮጵያውያን ተቆጥረው አያልቁም፡፡ ሐዘኔታን የተላበሰ፣ ለድሆች የሚራራ፣ በደልን የሚጠየፍ ድሀ ሲበድል፣ ፍርድ ሲጓደል የሚቆጠቁጠው ነው፡፡ እንደማሕተመ ጋንዲ እና እማሆይ ትሬዛ ያሉ ታላላቆች ካልሆነ ብዙዎቹ የሃይማኖት መሪዎች ያልኖሩበት ነው፡፡
የእምነት ሰው ሁለቱንም መልኮቹን ይዞ የሚዞር ነው፡፡ አንደኛ ሲጎላ አንደኛው ደግሞ ሲደበዝዝ የሚኖር፡፡ በዚህም ምክንያት ዓለማችን ታንክና መድፍ በመስቀል የሚባርኩ ጳጳሳት፣ የጀሐድ ጦርነት የሚያውጁ ዑላማዎችን አስተናግዳለች፤ ብዙ ደም ፈሷል ብዙ ንብረትም ጠፍቷል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ሙሉ ሕይወታቸውን ለድሆች የሰጡ፣ ለፍትሕ እና ለእኩልነት የቆሙ፣ ድምፅ ለሌላቸው ምፃቸውን የሰጡ ደጋጎችንም አይተናል፡፡
ይህ መልክ እንዲለዋወጥ ምክንያት የሆኑ ብዙ የእምነቶቹ የውስጥ ጉዳዮችና ከሌላው ጋር (በሌላ የእምነት ጥላ ስር ካለው፣ ከኢ-አማኒው እንዲሁም ግራ ከገባው) የሚጋሯቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንዱና ዋነኛው ዐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ነው፡፡
ዐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ግንባር ቀደሙ እና የእምነቶቹን ሰላማዊነትን የሚቃኝ መልክ የሚያሲዝ ነው፡፡የመጀመሪያው እምነቶቹ በሕዝቡ ዘንድ በግልጽ እንዲነገሩ ዕድል ስለሚሰጥ የስማ በለው ደጋፊ አይኖራቸውም፡፡ሁሉም አውቆ እና ጠይቆ ስለሚረዳ እንደከብት የሚነዳውን ቁጥር ባያጠፋውም ይቀንሰዋል፡፡ ሁለተኛው ተገፋን እንዳናስተምር፣ እምነታችንን እንዳንመሰክር ተለከለን የሚል የእምነት ክፍል አይኖርም፡፡ ሐሳቡን በነጻነት የሚገልጽ እምነት፣ ነጻ የሆነ ህዝባዊ ምህዳሩን(public space) አቅሙ እንደፈቀደ ያለ አድሎ የሚጠቀም እምነት፣ ተቋማዊ ነጻነቱ የተጠበቀለት እምነት ለእኩይ ምግባራት ቦታ አይኖረውም፡፡ በዚህ ሂደት የእምነቶች መልካም ገጽ እያበበ ጸብ አጫሪነት እየከሰመ ይሄዳል፤ ፉክክር ካለም ለጽድቅ(ለእውነት) ይሆንና ማኀበረሰቡን የከበበው የቁስም ሆነ የመንፈስ  ድህነት ይወገዳል፡፡
ከሴኩላሪዝም ጋር ያለው ትልቁ ግጭት እዚህ ጋር ያለ ይመስለኛል፡፡ ሴኩላሪዝምን የአውሮጳ ስልጣኔ ምንጭ እምነትን ደግሞ የኋላቀርነት ምልክት የማደረግ አባዜ በመኖሩ ከላይ እንዳየነው ካለምንም ፍልስፍናዊ ዳራ (philosophical background) ሴኩላሪዝም ተቀባይነትን አግኝቷል፡፡ የአውሮጳ ስልጣኔ በመሠረቱ ከሴኩላሪዝም ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡ የአውሮጳ የስልጣኔ መንፈስ ምን እንደ ሆነ ለማሰረዳት ዶ/ር እጓለ ገብረዮሐንስ በፍልስፍና ካነሆለላቸው ሀይድልበርግ (Martin Heidegger) የኒቨርሲቲ እንደተመለሱ የጻፉትን መግለጹ ተገቢ ይመስለኛል፡፡
“በስነ ምግባር ረገድ የሰውን ጠባይና ችሎታ በመመርመር ከከፍተኛ የሞራል ሐሳብ ጽርየት ደርሰዋል፡፡ በማኀበራዊ ኑሮ ረገድ የእያንዳንዱ መብት እና ተግባር ተጠብቆ ሰው በንጹሕ ተምኔቱ መሠረት በሰላም ተደስቶ የሚኖርበትን የሕግ ውሳኔ አስገኝተዋል፡፡ በሀብት በንብረት በኩል ባነሰ ድካም ብዙ የሥራ ፍሬ በማስገኘታቸው ከራሳቸው አልፈው ለመላው ዓለም የሚተርፉ ሆነዋል፡፡ በሥነ ፍጥረት ዕውቀትና የእርሱ ዘርፍ በሆነው በቴክኖሎጂ ረገድ ከላይ እንደጠቀስነው የሰውን ሕሊና በጣም በማበልጸጋቸው ሰው ከሰውነት ድንበር ለማለፍ ምንም አልቀረው፡፡ በውበት ጥበባት ረገድ እነ ራፉኤልን ዳቢንቺን ሞዛርትን ቤቶሆቨንን ስመ ስማቸው ብቻ ብዙ ይናገራል፡፡ የአውሮጳ ስልጣኔ በአጭሩ ይሄ ነው፡፡ ባጭር ለመናገር ስንል ሳንበድለው አልቀረንም፡፡ ግን በሌላ ዕድል እንክሰዋለን፡፡
. . . .እሊህን የሕሊና ሕግጋት ወይም የስልጣኔ ፍሬዎች ያስገኙት አውሮጳውያን ናቸው፡፡ ግን እስያውያንም አፍሪካውያንም የራሳቸው ለማድረግ ይችላሉ፡፡ ዕውቀት ሲባል በጠቅላላ በማናቸውም ሰው ዘንድ በአምሳለ ዘርዕ ያለ ነገር ነው፡፡ ያንተም የኔም አይደለም፡፡ የሁላችንም ነው፡፡”
እውነታው ይሀ ሆኖ ሳለ የምዕራብ ክርስትና መምህራን ሴኩላሪዝም የእነርሱን ብዙ እሴቶች ገንዘብ በማድረጉ በቀጥታ እምነታችነን ተቀበል ከማለት ይልቅ ወደ ሴኩላሪዝም በማስጠጋት ቀስ በቀስ ወደራሳቸው የእምነት ጎራ ለማስገባት (በሰፈሩት ቁና መሰፈር አይቀርም እንዲሉ ወዳጅ ያደረጉት ሴኩላሪዝም እነርሱ ካበጁለት መስመር በማፈንገጥ ብዙ የምግባር እሴቶቻቸውን እንዲያጡ ሆኗል) ሙከራ ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ይህም ሌሎች እምነቶች የከሸፈውን ሚሺነሪ በዘዴ ቀይረው መጡ እንዴ ብለው እንዲጠይቁም አስገድዷቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የመጠቃት ስሜት ሳለለ ከምዕራብ የመጣን ነገር ሁሉ እንደ ርኩስ የማየት ዘይቤ አለ፡፡ ይህ በልማት እና በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ላይ አሻራው ጥሏል፡፡ ይህንን የመጠቃት ሰሜት በመላው ዓለም በሚገኙ ሙስሊሞች እና ምስራቃውያን ክርስቲያኖች (ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስያናትም ከዚህ ይመደባሉ) ይጋሩታል፡፡ ይህም እምነቶቹን ለመጠቀሚያነት ለሚያውሉ ሰዎች ምእመናንን ለእኩይ ዓላማ ለማሰለፍ እንዲችሉ ይረዳቸዋል፡፡ በመላው ዓለም የሚገኝ የትኛውም ሙስሊም አሜሪካ እና ምራባውያንን እንዲጠላ ተቀርጿል፡፡ ይህ አል ቃይዳን እና መሰል አሸባሪ (ይቅርታ አሸባሪ በኢትዮጵያ ሳይሆን በምዕራባውን ትርጉሙ ነው የተጠቀምኩበት) አባላትን ለም መሬት እንዲያገኝ ረድቶታል፡፡
የመላው ዓለምን ችግር የመፍታት አቅም ላይኖረን ይችላል፡፡ ሀገሪቱን ሴኩላር ማድረግ በእምነቶች መካከል ያለን ችግርንም ሆነ እምነቶች አመጡት የሚባለው ችግር ማስቀረት አይቻልም፡፡ ነገር ግን ሀገር በቀል የሆኑ መልካም እሴቶችን በመንከባከብ የብዙሐን ሀገር (pluralistic state) መገንባት እችላለን፡፡ በብዙሐን ሀገር የትኛውም እምነት ሆነ እምነት የለሽ በእኩል የሚታይበት ለጋራ እሴት ሰብኣዊነት በማስቀደም በኅብረት የሚሠራበት ነው፡፡ የተገፋ የእምነት ክፍል ስሌለ (ሁሉንም እምነት ከሚገፋው ሴኩላሪዝም በተቃርኖ) ለአክራሪነት ቦታ አይኖርም፡፡
የኢሕአዴግ መንግስት ግን በጀመረው የጥፋት ጎዳና መቀጠል  መምረጡን የምንረዳው እምነቶችን ከህዝባዊው ምህዳር ማግለሉ አንሶት ተቋማዊ ነጻነታቸውንም ለመስጠት ፍቃደኛ ባለመሆኑ ነው፡፡ Jo¨ rg Hausteina* and Terje Østebø  EPRDF’s revolutionary democracy and religious plurality: Islam and Christianity in post-Derg Ethiopia” የሚል ርዕስ በሰጡት ጥናታቸው ኢሕአዴግ በሃይማኖት ጉዳዮች ጣልቃ በመግባት ሕዝባዊውን ምሕዳር በማወኩ ምክንያት፣ በእምነቶች መካከል ሀገራዊ መግባባት በማራቁ ምክንያት እምነቶቹ የየራሳቸው የተለያየ የታሪክ ትርክት እንዲኖራቸው ማድረጉን ይገልጻሉ፡፡ ይህ ለሃይማኖት ጽንፈኝነት መምህራን ለመጽሐፋቸው ርዕስ ለሁከታው መቀስቀሻ እንደ የተቀበረ ድማሚት ያገለግላቸዋል፡፡  
ሌላው ሕሊችንን  ከፍ ከፍ ማድረግ የሚጠበቅብን ጉዳይ የእምነቶችን እሴቶች በተለመለከተ ነው፡፡ ሃይማኖቶች በጊዜ ሒደት ያበለጸጓቸው የራሳቸው እሴቶች አሏቸው፡፡ እነዚህ እሴቶች በዚያ በእነርሱ ወረዳ ለሌለ ሰው ትርጉም ባይሰጡም ለምእመናን ግን ትልቅ ዋጋ አላቸው፡፡ ብዙ ጊዜ ግን እምነትን የሚያሄሱ ሰዎች ይህንን ግምት ውስጥ አያስገቡም፡፡ ለሌሎች ተነጻጻሪ እሴቶች የሚያደርጉትን ጥንቃቄ ለእምነቶች እሴት ሲያደርጉ አይታይም፡፡ ለምሳሌ የአንድ ሕዝብ በዳሌ መጨፈር፣ ትከሻን ማውረግረግ፣ የአንዳንድ ድምጾች መደጋገም፣ ከትናጋ ጋር የሚጋጩ ድምጾች መብዛት የመሳሰሉ ነገሮች ያን ጎጥ ያስከፋሉ ተብሎ ስለሚታሰብ በእርሱ ላይ ላለመቀለድ ይሞከራል፡፡ ይህ ግን እምነቶች ላይ ሲደረግ አይስተዋልም፡፡ የሀገሪቱ መንግስትም ሴኩላር በመሆኑ ለእነዚህ የሰላም እሴቶች ድጋፍ እና ጥበቃን አያደርግም ይህም ለምንጓጓለት ሐሳብን በመግለጽ የሚያምንም ማኀበረሰብ ግንባታ እንቅፋት ሆኗል፡፡

ይህን ስናደርግ በእኔ እምነት “የክርስቲያን ደሴት” ወይም “ኢስላማዊት በሸሪአ የምትመራ ኢትየጵያን” ከመስበክ ይልቅ የጋራ ቅኝቶችን የሚደግፉና ለአዳዲስ አስተሳሰቦች በር የሚከፍቱ ቤተ እምነቶች ይኖሩናል፡፡ ነገር ግን እኛን የሚወክል ሀገራዊ ሁኔታዎችን ያገናዘበ ስርዓትን ተባብረን በሰላማዊ መንገድ ካልጠየቅን ምን አልባት በፈጣሪ ለማመን ፍቃድ መጠየቅ ሊኖርብንም ይችላል፡፡ በፈጣሪ መኖር አላምንም ብንል ደግሞ በፓርቲችን ማመን ግዴታህ ነው የሚባልበት ዘመን ሩቅ አይሆንም፡፡ጽሑፌን ሁሉን በሚያስማማው እና ‹‹በአንተ ላይ ሊደረግ የማትፈልገውን በሌላው አታደርግ›› በሚለው ድንቅ ዓረፍተ ነገር ስዘጋ ልቤን ደስ እያለው ነው፡፡

የታክሲ ሰልፍ መጀመሪያውና መጨረሻው


ጠዋት ሁለት ሰዓት አካባቢ ወደቦሌ ለመሄድ አራት ኪሎ የተገኘ ሰው እጅግ ረዥም ሰልፍ ለመሰለፍ ይገደዳል (የጥቅምት 6/2005 ሰልፍን በፎቶው እና ቪዲዮው ይመልከቱ!) የቦሌ ታክሲ ለመጠቀበቅ ከተሰለፉት ሰዎች ፊት ለፊት ስምሪታቸው በፈረንሳይ ለጋሲዮን ወደጉራራ የሆኑ ታክሲዎችም ተሰልፈው የሚቀድሟቸው ታክሲዎች እስኪሞሉ ድረስ ይጠብቃሉ፡፡ ይህ የአዲስ አበባ ታክሲ የሰሞኑ አጀንዳ ነው፤ እንኳን ደህና መጣችሁ፡፡

የታክሲ ስምሪት ጉዳዮች
የታክሲ ስምሪቱ በ2004 መባቻ እንደወጣ የተደሰቱም የተበሳጩም ነበሩ፡፡ የስምሪቱ ጉዳይ ሁለት ዓመት ተጠንቶበታል ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ ስድስት ያክል መስመሮች ስምሪት ሳይመደብላቸው መቅረታቸው የሚታወስ ክስተት ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ የታክሲ ስምሪቱ ወዲያው እንደተተገበረ የተዘበራረቁ ነገሮችን ለማስተካከል በሚል በሁለት ወር ውስጥ ማሻሻያዎች ወጥተው ተተግብረዋል፡፡
የታክሲ ስምሪቱ ክፍያን በልምድ ሳይሆን በኪሎ ሜትር እንዲሆን አድርጎ የነበረ ሲሆን፣ ማሻሻያው ደግሞ ታክሲዎች የተሰማሩበትን ቦታ ታሪፍ ፊትለፊት እንዲለጥፉ የሚያስገድድ ነበር፡፡ ሁሉም አልተተገበሩም፤ እንዲያውም አንዳንድ ተሳፋሪዎች ታሪፎቻቸውን (እስከ መደባደብ በሚደርስ ትግል) ለማስከበር ቢሞክሩም ቀስበቀስ ሁሉም ተስፋ እየቆረጠ ወደበፊቱ የልምድ አሠራር ተመልሷል፡፡ ሌላው እያቆራረጡ መጫን በስምሪቱ ወቅት የተከለከለ ቢሆንም አስፈጻሚ ባለመኖሩ እሱም በድሮው አሠራር ቀጥሏል፡፡

እነዚህ የስምሪቱ ቅጥያ አገልግሎቶች አልተተገበሩም፡፡ ለመሆኑ ስምሪቱስ ማምጣት የነበረበትን የትራንስፖርት እጥረት ቀርፏል፤ ወይም ለመቅረፍ የተወሰነ አስተዋፅዖ አድርጓል? – ጥያቄያችን ነው፡፡
ሲሳይ ፋንታዬ ለአምስት ዓመታት የታክሲ ሾፌር ሆኖ ሠርቷል፡፡ የታክሲ ስምሪት የታክሲ እጥረቱን አባብሶታል ብሎ ያምናል፡፡ ባነጋገርኩት ወቅት በምሳሌ የነገረኝ እንዲህ በሚል ነበር፤ ‹‹ታፔላ ቢኖርም ባይኖርም ለውጥ የለውም፤ እንዲያውም… ከቦሌ ተነስቼ ወደሜክሲኮ እሄዳለሁ እንበል፣ ሜክሲኮ ስደርስ ስምሪት ከሌለብኝ ወደጦር ኃይሎች ሊሄዱ የተሰበሰቡ ሰዎች ከገጠሙኝ እነርሱን እዚያ አደርሳለሁ፡፡ በዚህ መንገድ ሰው የበዛበትን ቦታ ያማከለ አሠራር መሥራት ይቻላል፡፡››
ሲሳይ የተናገረው እውነት ነበር፤ በፎቶው ላይ የሚታዩት እና ታክሲ ጥበቃ ከተሰለፉት ሰዎች ፊትለፊት የተሰለፉት ታክሲዎች በየጎደለበት አቅጣጫ ቢንቀሳቀሱ ኖሮ ይህ አይከሰትም ነበር፡፡ እነዚህ አራት ኪሎ ላይ የተሰለፉት ታክሲዎች በበፊቱ አሠራር ቢሆን አጭርም፣ ረዥምም እየጫኑ ፈረንሳይ ደርሰው እጅግ ተሰብስቦ የሚጠብቃቸውን ሰው ትንሽ መፍትሔ ይሰጡት ነበር፤ የስምሪት ጣጣ ባይኖርባቸው፡፡
የስምሪቱ ሌላው ችግር ለብልሹ አሠራር የተጋለጠ መሆኑ ነው፡፡ የስምሪቱን አቅጣጫ የሚያወጡት የታክሲ ማኅበራቱ ናቸው፡፡ እያንዳንዱ የታክሲ ማኅበር የራሱ አቅጣጫ/ዞን ውስጥ ያሰማራል፡፡ ለምሳሌ ፀሐይ እና አዲስ ሕይወት ከሽሮሜዳ እስከ ሜክሲኮ፣ ከአራት ኪሎ በፈረንሳይ እስከ ጉራራ ድረስ አቅጣጫቸው ነው፡፡ ሆኖም እዚህ አቅጣጫ ላይ (እንደዕለታዊ ሁኔታዎች ሊለያይ ቢችልም) በጥቅሉ ከሽሮሜዳ እስከሜክሲኮ የሚሰማራ ታክሲ ከአራት ኪሎ ወደፈረንሳይ ከሚሰማራ ታክሲ ይልቅ ያተርፋል፤ ወይም ብዙ ገቢ ያገኛል፡፡
ስለዚህ ታክሲዎች የማኅበራቱ አስተባባሪዎችን በገንዘብ በመደለል የሚፈልጉት መስመር ላይ ብቻ ለረዥም ጊዜ ወይም ለሁል ጊዜ እንዲመደቡ ያደርጋሉ፡፡ ከላይ ባነሳነው ምሳሌ፣ ሁሌም ከሽሮሜዳ ሜክሲኮ የሚሰማራ ታክሲ የበለጠ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ ይህንን ታክሲ ለመጥቀም ደግሞ ሌሎቹ በፈረንሳይ መሰማራት ስለሚኖርባቸው (ወይም በሜክሲኮ ለመሰማራት ከሚፈጅባቸው ጊዜ የላቀ ርዝመት በመፍጀት) ተጎጂ ይሆናሉ፡፡
የታክሲ ሥራ ያዋጣል?
በቅርቡ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በወጣ ዜና ብዙ የታክሲ ባለንብረቶች ታክሲዎቻቸውን እየሸጡ መሆኑን ያትታል፡፡ ለምን የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የመጀመሪያው ጉዳይ የሚሆነው ሥራው ‹ያዋጣል ወይስ አያዋጣም?› የሚለው ነው፡፡
ቀደም ሲል የጠቀስነው ሾፌር ‹‹አያዋጣም›› ባይ ነው፡፡ ‹‹እንዲያውም፤ የታክሲ ሥራ ከባለንብረቱ ይልቅ ለሾፌሩ ያዋጣዋል›› ይላል፡፡
የታክሲ ባለንብረት በየቀኑ ከሾፌሩ የሚቀበለው 120 (አሁን 150 ሆኗል) ብር ነው፡፡ ይሄ 120 ብር በወሩ ቀናት ሲባዛ 3,600 ብር ይሆናል፡፡ ከዚህ ውስጥ በየወሩ ለውጥ የሚያስፈልጋቸውን እነ‹ቴስቲኒ› (በባለሙያው አጠራር) በ2000 ብር፣ ባትሪ በ400ብር – ስድስት ወር ያገለግላል፣ ጎማ እስከ2000 ብር አውጥቶ መቀየር እና ብልሽትም ከገጠመው ማሠራት የባለንብረቱ ኃላፊነት ነው፡፡ ይህንን ሁሉ ወጪ መሸፈኑ እንኳን ሊያተርፍ እንዲያውም የሚያከስር እየሆነ እንደሆነ ባለንብረቶችም እየተናገሩ ነው፡፡
ከ5 ዓመት በፊት ‹ቴስቲኒ› በ250 ብር ማስቀየር ይቻል ነበር፣ ባትሪ በ400 ብር እና ጎማ እስከ 500 ብር ማስቀየር ይቻል ነበር፤ አሁን ግን የታክሲ ሥራን የመለዋወጫዎቹ ዋጋ የማይቀመስ ስላደረገው፣ ከሥራው የሚወጡ እንጂ ወደሥራው የሚገቡ ባለንብረቶችን ማግኘት እያከበደ መጥቷል፡፡
የታክሲ ሾፌሮች ከ350 ብር እስከ 400 ብር የወር ደሞዝ ይኖራቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ታፔላ ከተጀመረ ወዲህ ከዕለት ገቢያቸው ላይ በአማካይ እስከ 50 ብር እየያዙ ይወርዳሉ፡፡ ይህ መጠን በፊት በአማካይ 150 ብር እንደነበረ ይናገራሉ፡፡ የቀነሰው ገቢያቸው እንጂ ቅጣቱ እንዳልሆነ እና በጣም እንዳማረራቸው ያነጋገርኳቸው የታክሲ ሾፌሮች በሙሉ ተናግረዋል፡፡ የመንግስት መሥሪያ ቤቶች ለሾፌር የሚከፍሉት ከ900 እስከ 1100 ብር ነው፣ ብዙ ጫና የለውም፣ አልፎ አልፎ ጥቅማ ጥቅሞችም አይጠፉትም… ይህንን አስመልክተው የመንግስት መሥሪያ ቤት ውስጥ ለመቀጠር እየተፍጨረጨሩ ያሉ ሾፌሮችም ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ ይህ የሚያሳየን የታክሲ ሥራ ለሾፌሩም፣ ለባለንብረቱም ከዕለት ዕለት መክበዱን ነው፡፡
የተሳፋሪው ቁጥር እየጨመረ በመጣ ቁጥር የታክሲዎች የማስተናገድ አቅም እጅግ እያጠረ መጥቷል፡፡ በፊት በግፊያ ታክሲ ውስጥ ለመግባት ይደረግ የነበረው ትንቅንቅ አሁን የማይሞከርበት ደረጃ እየደረሰ ስለመጣ ተጠቃሚው ሰልፍን እንደመፍትሔ ወስዶታል፡፡ ሜክሲኮ /ቡናና ሻይ አካባቢ/ የተጀመረው የታክሲ ጥበቃ ሰልፍ በየአካባቢው እየተስፋፋ ነው፡፡ ሰልፉ የተጠቃሚውን ጨዋነት ያሳያል፣ ነፍሰጡሮች እና አዛውንትን ከሌሎች እኩል እንዳመጣጣቸው እንዲስተናገዱ ያደርጋል፤ በጣም የሚበረታታ ነው፡፡ ነገር ግን ጊዜያዊ ችግርን የመቀበያ መንገድ እንጂ መፍትሔ ሊባል ፈፅሞ አይችልም፡፡

አሁን ሰልፉም ቢሆን መጀመሪያውና መጨረሻው (ጫፍ ለጫፍ) መተያየት የማይችልበት ደረጃ እየደረሰ ስለሆነ ጠዋት ሥራ ለመግባት ያሰበ ሰው ተራው እስኪደርሰው ሲጠብቅ አይውልም፡፡ ስለዚህ የሚመለከተው ክፍል /መንገዶች እና ትራንስፖርት ባለስልጣን/ ዘላቂ እርምጃ ዛሬውኑ /ሳይቃጠል በቅጠል/ መተግበር ካልጀመረ ወደማይወጣበት አዘቅት እኛንም ራሱንም መውሰዱ ነው፡፡

አንድ ለመንገድ፡- ከካምፖሎጆው ፍጥጫ ማግስት


በታምራት ተስፋዬ
እኛ ኢትዮጵያውያን ጥሎብን በብዕር ለመግለጽ ከምንችለውም በላይ በእግር ኳስ አቅላችንን እስከምንስት ድረስ ልክፍት ውስጥ ገብተን በራሳችን የሚያረካን ጠፍቶ የሌሎችን ማድነቅ ከጀመርን ይኸው ሦስት አሥርት ዓመታቶች ተቆጠሩ፡፡ ይበል ነው፤ ይኸው ጊዜ ተለውጦ ለረዥም ጊዜ አልጎመራ ያለው ፍሬ ሊበስል ከጫፍ ላይ ደርሷል፡፡ ኢትዮጵያ ሱዳንን አሸንፋ ለአፍሪካ ዋንጫ አልፋለች፡፡ ታዲያ ለምን እግረመንገዳችንን የኢትዮ-ሱዳን ጂኦ ፖለቲካዊ ግንኙነት ላለፉት 20 ዓመታቶች ምን ዓይነት ገጽታ እነደነበረው በትንሹ ለመዳሰስ አንሞክርም፡፡
ደርግና ሱዳን
የደርግ መንግስት ከሱዳን ጋር ኦፊሻላዊ ግጭት ባይኖርበትም እባብ ለእባብ እንደሚባለው የሁለቱም መንግስታዊ አስተዳደሮች እርስ በእርስ ሲጠባበቁ እነደነበር የታሪክ ድርሳናት ያትታሉ፡፡ ሱዳን ሕወሓትንና ሻዕቢያን በክልሏ ላይ እንደልብ እንዲፈነጩና የራሳቸውን ቢሮ እንዲከፍቱ ስታደራጅ ደርግ የመልስ ምት በሚመስል መልኩ የደቡብ ሱዳን ነጻ አውጪዎችን በማስታጠቅና በፋይናንስ በመደጎም የበቀል ዱላውን ይሰነዝር ነበር፡፡ በዚህ ወቅት የሱዳን ሕዝብ በሁለት ጎን ተጠቃሚ ነበር፡፡ ሕወሓት በእርሻና በትራንስፖርት ዘርፍ ተሰማርቶ ሀገራቸውን ሲረዳ በሌላ አቅጣጫ ደርግ ነጻነት ለሚፈልጉ ሕዝቦች ያለውን በመስጠት ሕዝቡ በሁለቱም ወገን ተጠቃሚ እንዲሆን አድርጎ ነበር፡፡
የገደለው ባልሽ…
ኢሕአዴግ ስልጣን በያዘ በአንደኛ ዓመቱ ወርሃ ሰኔ ላይ ዱብ ዕዳ ወረደ፡፡ ሀገራችንን ለመጎብኘት ወደ አዲስ አበባ የመጡት የግብጹ ፕሬዝዳንት ቦሌ አየር ማረፊያ ሲደርሱ አቀባበሉ በፖሊስ ኦኬስትራ ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ ነገሮች ተገላብጠው በክላሽ እና በቦንብ ሆነ፡፡ ስድስት የሚሆኑ የአረብ ሀገር ተወላጆች ሙባረክን በክላሽ እንኳን ደህና መጣህ ቢሉትም የግድያው ዕቅድ ሳይሳካ ቀርቶ አራቱ አዲስ አበባ ላይ ሲመቱ አንዱ ሸሽቶ ሱዳን ገባ፡፡ ግጭቱ ኢትዮጵያና ሱዳን ላይ በመሆን ክርክሩ አሳልፈሽ ስጪኝ አልሰጥም ሆነ በመሰረቱ በወቅቱ ሙባረክ ከኢትዮጵያ ይልቅ ለሱዳን ቅርብ ነበሩ፡፡ እንደውም በአንድ ወቅት በአንድ እንትን የሚባለው ደረጃ ላይ ደርሰው ነበር፡፡ መኖር መልካም ነው ብዙ ያሳያል፤ ይኸው በክላሽና በቦንብ ያልተፈቱት ሙባረክ በHeዝብ ጩኸት ተረቱ፡፡ እኛም በርእስነት የተጠቀምኩትን ተረት ሳንተርት ኢትዮጵያና ሱዳን ሰላም አወረዱ፡፡

የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት
ሱዳን በዚህ ወቅት የጆከርነት ሚናዋን ስትጫወት ሰነበተች፤ ከወደብ አከራይነት እስከ መሳሪያ አስተላላፊነት በመሳተፍ በአንድ ድንጋይ እንደሚባለው ከሁለቱም ሀገር ጋር በመሰለፍ ኢኮኖሚዋን አፈረጠመች፡፡ ጦርነቱ የሁለቱንም ሀገሮች ኢኮኖሚ ያሽመደመደ ሲሆን በተቃራኒው የሱዳን ሕዝብ በጦርነቱ ተጠቃሚ ለመሆን በቃ፡፡
የሚሊኒየም ዋዜማ
በበርበሬ ገበያ ላይ በታየው ቅጥ ያጣ የዋጋ ጭማሪ ‹‹አልጫው ሚሊኒየም›› የተባለው ሀገራዊ በዓል የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የሱዳንም በዓል እስከሚመስል ድረስ መዲናችን በሱዳን ዘፈን ‹‹እልል በቅምጤ›› ስትል አመሸች፡፡ በዕለቱ ነፍሳቸውን ይማረውና የቀድሞው ጠ/ሚኒስትራችን ከአልበሽር እና ከባለቤታቸው ጋር በሱዳን ሙዚቃ ሲደንሱ አመሹ፡፡ በወቅቱም ጥላሁን ገሠሠ እያለ እንዴት በሱዳንኛ የሚሉ ድምጾች ከየአካባቢው መሰማት ጀመሩ፡፡ መቼም ይህቺ ነገር ለተራ ፖለቲከኛም አትጠፋም፤ ይህ ጸሐፊ ሆን ተብሎ የተደረገ ነው ብሎ ያምናል፡፡ በወቅቱ መለስ ግንኙነታችን በሙዚቃችሁ ከመጨፈርም በላይ ጥርጣሬ የሌለበት መልካም ጉርብትና እንዲኖረን እንፈልጋለን የሚል መልዕክት ለአልበሽር ለማስተላለፍ አስበው ይመስለኛል፡፡ አልበሽርም መልዕክቱን በመረዳት በሚመስል መልኩ ግንኙነቱን ማጠንከር ላይ መሥራት ጀመሩ፡፡
ጥላሁን ገሠሠና አልበሽር
ሄግ የሚገኘው ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ዳርፉር ላይ በደረሰው ቀውስና በተያያዥ ጉዳዮች አልበሽር ላይ የበረራ እገዳና በማንኛውም ጊዜ ተይዘው ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ዋራንት ቆረጠባቸው፤ ምድር ቀውጢ ሆነች፡፡ ሰውየው በነጻነትና በመታሰር መሀል ላይ ወደቁ፡፡ እንቅስቃሴያቸው ሁላ ድጋፍ ለማገኘት ደፋ ቀና ሆነ፡፡ በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ታላቁን የሙዚቃ ሰው አጣች፡፡ እንደተለመደውም አጀንዳው በኢትዮጵያ ወደ አንድ አቅጣጫ ዞረ፤ ጨዋታው ሁላ ጥላሁን ጥላሁን ሆነ፤ በዚህ ወቅት አልበሽር ወደ አዲስ አበባ ድምጻቸውን አጥፍተው ከተፍ አሉ፡፡ የዋሆች ለቀብር ይሆን ብለው ያስባሉ፤ አልበሽር ግን ዋራንቱ ምንም ተጽእኖ እንዳላሳደረባቸው እና ፉርሽ እነደሆነ በኢትዮጵያ ጉብኝት አስመሰከሩ፡፡ በወቅቱ ሚዲያው ሁላ ከአልበሽር ይልቅ ጆሮዋቸውን ለሙዚቃ ተንታኙ ሠርጸ ፍሬስብሓት አዋሱት፡፡ ጨዋታው ሁላ ሞናሊዛዬ ነሽ ሆነ፤ አልበሽርም ድምፃቸውን እንዳጠፉ በአረብኛ ሞናሊዛዬ ነሽን እያንጎራጎሩ ጉብኝታቸውን ጨርሰው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ፡፡ ዓለም አቀፉ ሚድያም የሄግ ሕግ አልተከበረም በማለት ለአንድ ሰሞን ተንጫጫ፤ ኢትዮጵያም (አልበሽርን ያለምንም ኮሽታ በማስተናገድ) ግንኙነቷ ለችግር ጌዜም እነደሆነ ለፕሬዚደንቱ ስታሳይ ጥላሁን በበኩሉ በሕይወት እያለ ሚሊኒየም አዳራሽ ባለመገኘት ለሱዳን ያደረገውን ውለታ በመሞቱ ደግሞ ሚዲያውን ይዞ አጀንዳውን በማዞር ውለታውን ዳግም አረጋገጠላቸው፡፡ ነፍስ ይማር ሌላ ምን ይባላል፡፡
ኢትዮጵያ እነደ ጆከር
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ለሁለት ለተከፈሉት ሱዳኖች እንደ ጆከር በመሆን  በሁለቱም መሀል ላይ ድልደይ በመሆን እያገለገለች ትገኛለች፡፡ በዚህ ወቅት ለሁለቱም ሱዳኖች ከኢትዮጵያ ውጭ የጋራ ፍላጎታቸውን የሚስከብር እንደሌለ የተረዱ ይመስላል፡፡ እናም ኢትዮጵያ በዚህ ቀውጢ ሰዓት ከሱዳን ሕዝብ ጋር በመቆም አለኝታነቷን አረጋግጣለች፡፡
ያልተነካው አጀንዳ
ነፍሳቸውን ይማርና የደቡብ ሱዳን የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት የነበሩት ጆን ጋራንግ የደቡብ ሱዳንን ወሰን (border) እስከ ባሮ መነሻ ድረስ መሆኑን በለሆሳስ ይናገሩ ነበር፡፡ ይህ መቼም ለኢትዮጵያ አስደንጋጭ ነው፤ በእርግጥም ደቡብ ሱዳን በዚህ ወቅት ድክ ድክ እያለች ስለሆነ ይህን ጥያቄ ማንሳት ባትችልም አጀንዳው ግን ጠረጴዛ ላይ እንዳለና ከጊዜዎች በኋላ መነሳቱ እነደማይቀር ግልጽ ነው፡፡ በእውነቱ የጋምቤላ ኢትዮጵያዊነት ላይ ምንም ድርድር አያስፈልግም፤ ነገር ግን ነገሮች ጥሩ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ በአንድ ወቅት ለሥራ ጋምቤላ በሄድኩበት ወቅት ብዙውን ቁጥር የሚወክለው የኑዌር ኽዝብ ከስልጣኑ እራሱን አግሎ ባሮን  ይዞ እየተመመ መሆኑን ለመገንዘብ ችያለሁ፡፡ የቤት ስራውን በጊዜ መጀመር መልካም ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በኅብረ-ትርኢት ሙዚቃን ከመልቀቅና የቁንጅናን አክሊል ለክልሉ ከመስጠትም በላይ ጋምቤላ ላይ ትልቅ ሥራ መሰራት ያለበት ይመስለኛል፡፡ ሕዝቡን የስልጣን ተጋሪ ማድረግና መሠረተ ልማቶችን ማስፋፋት ችግሩን በዘላቂነት ይቀርፈዋል ተብሎ ታሰባል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ነገሮች ከሆኑ በኋላ መቱ እና ቴፒ ላይ ቆሞ ዘራፍ ከማለት ውጪ አማራጮች ላይኖሩ ይችላሉ፡፡
ለትዝታ እና ለማንቂያ ያክል ይህንን ካልኳችሁ አሁን ደግሞ ወዳቋረጥኳችሁ የድል ማግስት ጭፈራ ልመልሳችሁ ‹‹…የእርግብ አሞራ……የእርግብ……የእርግብ አሞራ…›› (የእርግብ አሞራ  ማለት ግን ምን ማለት ይሆን?)
—-

ጸሐፊውን ለማግኘት በኢሜይል አድራሻቸው tamrattesfaye39@yahoo.comይጻፉላቸው፡፡

የኛ ኃይል


“ፒያሳ፤ መሐሙድጋ ጠብቂኝ” በመሐመድ ሰልማን የተጻፈ እና ከፍተኛ ተወዳጅነትን ያተረፈ ኢ-ልቦለዳዊ መጣጥፎች ስብስብ ነው፡፡ የዛሬ ዓመት ገደማ ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ በተባለ መንግስታዊ ባልሆነ ድርጅት  አማካይነትመጽሐፉን የመገምገሚያ ዝግጅት አምስት ኪሎ በሚገኘው ብሔራዊ ሙዚዬም ቀርቦ ነበር፡፡ በውይይቱ መሐል የመጽሐፉ ዝነኝነት ምንጮች ምን ምን ናቸው የሚል ውይይት የነበረ ሲሆን ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ‹‹ደራሲው የአዲስ ነገር ጋዜጣ ጸሐፊ የነበረ›› መሆኑን እና ‹‹ጽሑፎቹም በአዲስ ነገር ጋዜጣ እና ድረገጽ ላይ ወጥተው የነበሩ›› መሆናቸውን ጠቀሰ፡፡ ውይይቱ የአዲስ ነገር ጋዜጣ መታሰቢያ ይመስል፣ የትዝታ ጫወታው ተጧጧፈ እናም ከውይይቱ ተሳታፊዎች አንዱ የሚከተለውን ሲናገር ረዥም ጭብጨባ አዳራሹን አደመቀው ወጣቱ አስተያየት ሰጪ በንግግሩ መሃል የተጠቀመው እና ጢም ብሎ የሞላውን አዳራሽ በጭብጨባ ያናጋው ንግግር የሚከተለው ነበር፡፡
‹‹ይህ ትውልድ በአዲስ ነገር ጋዜጣ የሚደራደር ትውልድ አይደለም፡፡››
ጉዳዩን አስገራሚ የሚደርገው ወጣቱ ይህንን የተናገረው አዲስ ነገር ጋዜጣ መታተም ካቆመች ከሁለት ዓመታት በኋላ መሆኑ ሲሆን፣ አጋጣሚው የጋዜጣዋ መንፈስ በበርካቶች ልብ ውስጥ በትኩስነት መኖሩን የሚናገር ነበር፡፡
ዛሬ፣ ጥቅምት 5/2005 የዓለም የጡመራ የተግባር ቀን (Blog Action Day 2012) “የኛ ኃይል” በሚል መሪ ቃል ይከበራል፡፡ የጡመራ የተግባር ቀን በየዓመቱ የሚከበር፣ በዓለም ዙሪያ ያሉ ጦማሪዎች በሙሉ በአንድ ሐሳብ ዙሪያ የሚጽፉበት ቀን ነው፡፡ የተጀመረው እ.ኤ.አ. በ2007 ሲሆን በተመሳሳይ  ዓመት ‹‹አካባቢ››፣ በ2008 ‹‹ድህነት››፣ በ2009 ‹‹አየር ለውጥ››፣ በ2010 ‹‹ውሃ››፣ በ2011 ‹‹ምግብ›› በሚል ሲካሄድ ዘንድሮ ደግሞ በ2012 ‹‹የእኛ ኃይል›› በሚል እየተካሄደ ይገኛል፡፡
የዘንድሮው መሪ ቃል፣ ማኅበረሰብ፣ እኩልነት፣ ፀረ-ሙስና እና ነጻነትን በተመለከተ የኛ ኃይል ምን እንደሆነ በመስበክ እንዲከበር ታስቦ የተመረጠ ነው፡፡ አከባበሩ ቀላል ነው፤ አስተባባሪዎቹ እንዳስቀመጡት ‹‹profile someone or a group who inspires you by the way they made a positive influence… (ባመጡት አዎንታዊ ተጽዕኖ ያነቃቃችሁን የሆነ ሰው ወይም ቡድን በመምረጥ ጻፉ…)›› የሚል ነው፡፡

እኛም ጮክ ብለን ስናስብበት እና በጭንቅላታችን ያቃጨለችው አዲስ ነገር ጋዜጣ ብቻ ሆነች፡፡ አዲስ ነገር ጋዜጣ ለሁለት ዓመታት (ከጥቅምት 2000 እስከ ታሕሳስ 2002) ብቻ በስርጭት የቆየች ነገር ግን መራኄ አዘጋጇ መስፍን ነጋሽ የጋዜጣዋን ሁለተኛ ዓመት አስመልክቶ እንደገለፀው ‹‹አጭር ግን ረዥም ዓመት›› የኖረች ያክል የማትረሳ ጋዜጣ ናት፡፡
አዲስ ነገር ጋዜጣ በሌጣ ግለሰብ ተፅዕኖ እና ባለቤትነት የማትመራ፣ በስድስት መሥራች አባላት የተቋቋመች እና በሕፀፅ አታች (critical analysis) ጽሁፎቿ ከፍተኛ ተወዳጅነትን እና ተነባቢነትን ለማትረፍ የበቃች፣ የአንባቢውን ቁጥር ያሳደገች፣ የጸሐፍትን ችሎታ የፈተነች (standard ያኖረች)፣ በየጊዜው በማደግ እና ተፅዕኖ በመፍጠር ላይ የነበረች ጋዜጣ ነበረች፡፡ ጋዜጣዋ በቅንጅት መፍረክረክ ሰሞን ተመስርታ በተለይም ኢሕአዴግን በሚነቅፈው ማኅበረሰብ ውስጥ የነበረው የስሜት ስብራት በመጠገን ከፍተኛ መነቃቃትን ለመፍጠር የቻለች እና በማንኛውም መለኪያ አማራጭ መገናኛ ብዙሐን የሚለውን ማዕረግ ለመቀበል የምትመጥን ናት ለማለት ያስደፍራል፡፡፡
ሃሌሉያ እና Terje S Skjerda የተባሉ የጥናት ባለሞያዎችበግል ጋዜጦች ብቃት ላይ እ.ኤ.አ. በ2009 ባደረጉት እና ሁሉንም የግል ጋዜጦች ሊባል በሚችል መልኩ በነቀፉበት ጥናታቸው ውስጥ አዲስ ነገር ጋዜጣን እንዲህ ሲሉ ነበር የጠቀሷት፡-
[To be fair,…] There are newspapers which have steered away from extremist reporting and instead try to give space for different voices. Late 2007 saw the launch of Addis Neger, a private newspaper which by 2009 has grown to become one of the two largest Amharic weeklies with a weekly circulation of 25,000-30,000 copies. Its profile is serious,balanced and critical journalism with emphasis on commentaries and in-depth stories. Within the professional limitations that exist, Addis Neger and other publications have produced valuable reporting which has challenged the government in the public sphere.
([ሚዛናዊ ለመሆን…] ከፅንፈኛ ሪፖርቶች አፈንግጠው ለተለያዩ ድምፆች ቦታ የሰጡም ጋዜጦች ነበሩ፡፡ በ2002 ከአገሪቱ ሁለት ከፍተኛ ስርጭት ያላቸው (ከ25,000-30,000 ቅጂ) ጋዜጦች መካከል አንዱ ለመሆን የበቃው የአዲስ ነገር ጋዜጣ መመስረት በ2000 አጥቢያ ታየ፡፡ ይዘቱ በአስተያየቶች እና ጥልቅ ታሪኮች ላይ ያተኮረ፣ ቁምነገር አዘል፣ ሚዛናዊ እና ሂስ አዘል ጋዜጠኝነትን የተከተለ ነበር፡፡ በነባራዊው የሙያተኞች እጥረት አዲስ ነገር እና ሌሎችም መንግስትን በሕዝባዊ ክበብ ውስጥ የሚገዳደር እሴት ፈጥረዋል፡፡)
አዲስ ነገር ጋዜጣ፣ መስራቾቿ እና ጋዜጠኞቿ በመሰደዳቸው አሁን መታተም ካቆመች ሦስት ዓመታት እየተጠጋት ነው፡፡ ሁለቱ ጋዜጠኞቿ ዐብይ ተክለማርያም እና መስፍን ነጋሽም በቅርቡ ሽብርተኝነትን በመተባበር የ8 ዓመት እስር ተፈርዶባቸው በስደት ላይ ይገኛሉ፡፡ አዲስ ነገር ጋዜጣ ላይ ይወጡ የነበሩት ጽሑፎች ግን እስካሁንም ተፅዕኗቸው አልበረደም፡፡ ዳንኤል ክብረት፣በእውቀቱ ስዩም እና መሐመድ ሰልማን የአዲስ ነገር ላይ ጽሑፋቸውን መጽሐፍ አድርገዋቸው እንደአዲስ በብዙ ሺህ ኮፒዎች ተሸጠዋል፡፡ እነሠርጸ ፍሬስብሓት በሙዚቃ ላይ፣ እነማስረሻ ማሞ በፊልም ላይ የሚጽፏቸው ሂሶች የአልበሙን እና የፊልሙን ገበያ ከመወሰንም በላይ፣ ባለሙያዎቹ ለሥራቸው እንዲጠነቀቁ፣ ለአድማጭ ተደራሹም እንዲመርጥ የሚያደርጉ ነበሩ፡፡ ዶ/ር ብርሃኔ ረዳኢ በአስቂኝ የአጻጻፍ ስልቱ የሚያቀርባቸው የሕክምና ነክ ጉዳዮች የብዙዎችን ቀልብ እንደገዙ እስከዛሬም ይታወሳሉ፡፡
የአዲስ ነገር በኢትዮጵያ ፕሬስ ላይ የፈጠረችው ተጽእኖ በቀላሉ የሚታይ አልነበረም፡፡ እንደ አማራጭ፣ ተወዳጅ እና ተመራጭ ሚዲያ ሆኖ ከመቆየትም፣ በተጨማሪ የንባብ ባሕልን ወደ ፋሽንነት ለማምጣት እንዲሁም የወጣቱን ትውልድ ድምጽ የማሰማትም ሚና ነበራት፡፡ አዲስ ነገር ወደ ንባብ እና ወደ ቁም ነገር ያመጣቻቸው አያሌ ወጣቶች ዛሬም ከአዲስ ነገር አለመኖር በኋላም ሐሳብን በነጻነት ስለ መግለጽ ሲጨነቁ እና ሲጠበቡ ይታያሉ፡፡ በአዲስ ነገር መነሳሳት የተነሳም ወደ ጡመራ እና ውይይት የመጡ፣ ተስፋ ማድረግ የጀመሩም ቀላል አይደሉም፡፡

ከሚዲያው የሚመነጭ ጤናማ የአደባባይ ተዋስኦ በጠፋበት በፕሬሱ የጨለማ ዘመን ማግስት አዲስ ነገርን ማግኘት ለጤናማ ሕዝባዊ ውይይቶች መከፈት አስተዋጽዖ የነበረው ከመሆኑም በላይ ጋዜጣዋ መንግስትን በጠንካራ መልኩ በመተቸት ብትታማም የገዥውን ፓርቲ አቋም የሚያንጸባርቁ ቋሚ አምደኞች ነበሯት፡፡ አሁን በሥራ ላይ የሚገኙ እና ታዋቂ የሆኑ የሚዲያ ተቋማትም ቢሆኑ ራሳቸውን ሲገልጹ አዲስ ነገርን ማነጻጸሪያ ሲያደርጓት ተስተውሏል፡፡

በኢትዮጵያ የፕሬስ /ሐሳብን በነጻ የመግለጽ/ ነጻነት እያሽቆለቆለ ለመምጣቱ የአዲስ ነገር ጋዜጠኞችን እንኳን የሚያሠራ ክበብ አለመፈጠሩ ዐብይ ምስክር ነው፡፡ ዛሬ በዓለም የጡመራ ተግባር ቀን ጋዜጣዋን እና ጋዜጠኞቹን ማስታወስ ያስፈለገንም ለዚሁ ነው፡፡ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት፣ የሕዝብ ድምጽ /የሕዝብን ብሶት/ የሚያስተጋባ፣ የሕዝብን መንፈስ የሚያነቃቃ ጋዜጣ ያስፈልገናል፡፡ አዲስ ነገር ጋዜጣ የፈጠረችው እና ለመግደል የሚያስቸግር መንፈስ ቢኖር ይኸው መንፈስ ነው፡፡ ዓመታት አልፈውም “ዛሬም በአዲስ ነገር የማይደራደር ትውልድ” ለመፍጠር በቅታለችና!!!

ሁለት ዓይን፣ ሁለት ዕይታ


ጊዜው ለውጡ ከተካሄደ አምስት ዓመት በኋላ ነበር፡፡ በወቅቱ የነበረው መንግስት ባጎናፀፈው የመወዳጀትና የመተባባር ባህል መሠረት ሃይማኖቶች ሕብረ ዝማሬ ያስተጋባሉ፡፡ የዱቤዎች ፈጣን ምቶችና የከበሮዎች ቀሰስተኛ ድለቃዎች ተደማምረው የራሳቸው የሆነ ሜሎዲ ፈጥረዋል፡፡ ዘማርያን በአንድ በኩል በሚያስረቀርቀው ድምፃቸው ዓለማቸውን ይቀጫሉ፡፡ መንዙማዎች በሌላ በኩል ያስተጋባሉ፡፡ ትላልቅ እንጨቶች የተጣለባቸው እሳቶች ይርመሰመሳሉ፡፡ ግቢው ጭስ በጭስ ሆኗል፡፡ ቄስና ሼህ አራጆች ሰንጋዎቻቸው ጥለው በትልቁ ጎራዴ ይበርካሉ፡፡ ደሞች በየአቅጣጫው ቦይ ፈጥረው ግቢውን ደም በደም አድርገውታል፡፡ የስጋ ዘለላዎች በተዘረጉት ቀጫጭን አጠናዎች ላይ ተዘርግተዋል፡፡ በሌላ አቅጣጫ ደግሞ የሀገሬውን የባህል ጭፈራና ዝማሬ በጋራ ሆነው ያቀልጡታል፡፡ ከግቢው ውጪ የፈረስ ውድድር እየተካሄደ ነው፡፡ ጎረምሶች የገና ዱላቸውን ይዘው የገና ኳሳን ይጠልዛሉ፡፡ ሰዎች በእያንዳንዱ ነገር የመሳተፍ ውዴታ ውስጥ ተጠምደዋል፡፡ ይህ ሁሉ ግርግር በአካባቢው ማኅበረሰብ ትብብር ተሰርቶ የተጠናቀቀው በደቡብ ሸዋ በሐይቆችና ቡታጀራ አውራጃ የሚገኘው መስጊድ ለማስመረቅ ነበር፡፡
አባቴ በዛን ወቅት በብሔራዊ ስሜት ነህሉሎ ነበር፡፡ ከፍተኛ የብሔራዊ ስሜት ጡዘት ውስጥ ገብቶ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ‹የአሞራ አገር ዋርካ፣ የእስላም አገር መካ› እንዳልተባለ አሁን ደግሞ ሙስሊሞች እንደክርስቲያን ወንድሞቻቸው እንደአንድ ዜጋ ተቆጥረዋል፡፡ እንደሌላው ጊዜ በተለየ ሁኔታ የመታየቱ፣ የማሽሟጠጡና በጎሪጥ የመመልከቱ ብሎም የመፀየፉ ስርዓት ካከተመ አምስት ዓመት ደፍኗል፡፡ አባቴ ለውጡ ባስከተለው የማኅበረሰብ ግንኙነት ምክንያት ተደስቶ ሴት ልጁን ‹ኢትዮጵያ› አላት፡፡ ባያውቀው ነው እንጂ ለልጁ ትልቅ የዕድሜ ልክ የቤት ሥራ ነበር የሰጣት – ነፍሱን ይማረውና፡፡ የሙስሊሞች እንደኢትዮጵያዊ በእኩል ዓይን የመታየት የቤት ሥራ፡፡ ይሄው የቤት ሥራው ሳይሠራ ፈተና ሆኖብን ምንም ለውጥ ሳይካሄድ እንዳለን አለን፡፡ በሁለት አቅጣጫ የተወጠረ ስስ ገመድ ይዘን አንዳች የአንዳችንን ከኢትዮጵያዊነት መዝገብ ለመፋቅ ጥረት አያደረግን፡፡ ይገርማል አባቴ በአፄዎቹ ጊዜ የነበረው ስርዓት ዳግመኛ ይከሰታል ብሎ ቢያምን ኖሮ ይህንን የዕድሜ ልክ የቤት ሥራ ከልጁ ዘንድ ባላስቀመጠ ነበር፡፡
ሙስሊሞች በኢትዮጵያውነታቸው ላይ የመለየት ሥራ የሚሰሩት መንግስታት ብቻ አይደሉም፡፡ የባለፉት መንግስታት ሰበካ ያጀሉ አንዳንድ የአፄው ዘመን አመለካከት ያላቸው በማኅበረሰቡ ውስጥ ተሰግስገው የጥላቻ አመለካከታቸውን በማኅበረሰቡ ላይ ያሰራጫሉ፡፡ እስቲ አንድ ታሪክ ላጫውታችሁ፡፡ ለታሪክ ሁሉ ነገር ታሪክ ነው፤ እዚህ አገር ከመወለዳችን በፊት ታሪክ፣ ከተወለድን በኋላ ታሪክ፣ አፈርም ስንለብስም ታሪክ፣ ሌላ የለንም ታሪክ፣ ታሪክ…፡፡ እዚህ ላይ ግን ኢትዮጵያ በድሮ ማንነቷ አንቱ ከሚባሉት ሀገራት ውስጥ አንዷ መሆኗን አልክድም ችግሩ ግን የድሮ ማንነት አሁን ባለንበት ሁኔታ ላይ ለመመንዘር ስንሞክር ነው፡፡

ወደ ታሪኬ ልግባ… በአንድ ወቅት እህቴ ‹ኢትዮጵያ› ትምህርቷን ለመማር አንድ ስሙን በማልጠቅሰው የትምህርት ተቋም ውስጥ የመመዝገብ ሂደት እያከናወነች ነበር፡፡ መዝጋቢው ዕድሜያቸው ጠና ያሉ ባጠቃላይ እምቢ አላረጅም ብለው እዛ ተቋም ውስጥ የቀሩ አዛውንት ናቸው፡፡ ለምዝገባ ስሟን ጠየቋት፡፡ መለሰችላቸው ‹‹ኢትዮጵያ አህመድ…›› ያደፈውን መነፅራቸውን ወደ ግንባራቸው ከፍ አድርገው የጥላቻ ንግግራቸውን አወረዱት ‹‹… ቆይ ቆይ አባትሽ ምን እየሰራ ነው?! ሁለት የማይቀላቀል ነገር ያቀላቅላሉ፡፡ ኢትዮጵያ ብሎ አሕመድ የማይሆን ነገር! ሰው እንዴት ዘይትና ውሃን ለማቀላቀል ይሞክራል?! ኤዲያ! ዛሬ ደግሞ ምንድነው የምታሰማኝ…›› ይህን ሁሉ ተብትበው ኢትዮጵያ ከአሕመድ ጋር ደብለው መመዝገቡን ግን አልተዉትም፡፡ ሥራቸው ነውና፡፡ ቆይ እስቲ ሰዎች ኢትዮጵያ ከአሕመድ ጋር ወዳጅነት መፍጠር አይችሉም እንዴ? መቼም ይህ ስያሜ የሚያስገርመው ክርስቲያኑን ብቻ አይደለም ሙስሊሙንም ጭምር እንጂ! አንዳንዱ አገሩን ከዚህ ውጪ አድርጎ የሚስል ‹‹ይቺ በምኗም ተምሳሌት የማትሆን አገር¡… እንዴት አባትሽ ይህንን ማንንም የማይወክል ገዳይ ስያሜ ያወጣልሻል?›› የሚለውን ጨረር ይለቃል፡፡ አንዳንዱ ደግሞ አፉን እያጣመመ ‹‹ተሃድሶ ተካሂዷል ማለት ነው!›› ይላል፡፡ አንድ ሰው ተወልዶ እትብቱ የተቀበረበት ያደገበትና ስንት ውጣ ወረድ ያሳለፈበት አካባቢ ብሎም አገር የመውደድ ተፈጥሮአዊ ግዴታ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ሰው መቼም የተወለደበት አካባቢ ነውና የሚመስለው፡፡
የኢትዮጵያዊነት ስፌት
ሙስሊሞች በኢትዮጵያ ውስጥ በሌላ ዓይን መታየት ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ በትንሹ አበበና አሕመድ ትምህርት ቤት ውስጥ ያላቸውን ቦታ ብንመለከት ለየቅል ነው፡፡ ያው አበበ በየመጽሐፍቱ ‹‹በሶ በላ!›› እንደተባለ ይዘከራል፡፡ አሕመድ ደግሞ በመማሪያ መጽሐፍት ውስጥ ምሳሌያዊ ቦታም የለውም፡፡ ስለዚህ አበበና አሕመድ ኢትዮጵያ ውስጥ ያላቸው እንድምታ የተለያየ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊና አረባዊ፡፡ በአንድ አገር ውስጥ ሁለት የተለያዩ ዜጎች አንዱ የእናት ልጅ ሌላው የእንጀራ እናት ልጅ ሆነው የሚታዩ መምሰል ከጀመሩ ቆይተዋል፡፡
በዚች እኛን ዜጎችዋን በምታስደምም አገር ሙስሊሞችን እንደመጤ የማየቱ እንድምታ ታውቆም ይሆን ሳይታወቅም በቀጥተኛ ወይም ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ሲገለፅ ይስተዋላል፡፡ ቴዎድሮስ እንደአገር ገንቢ፣ አሕመድ ግራኝ እንደአገር አፍራሽ፡፡ ቴዎድሮስ ከቱባው የኢትዮጵያ አንድነት ጋር ሲገኛኝ በአንፃሩ ደግሞ አህመድ ግራኝ ወራሪና በታኝ የሚለውን የታሪክ ስያሜ ይለጠፍበታል፡፡ እነዚህንና የመሳሰሉትን እንድምታዎች ከቅርብ ክርስቲያን ዘመዶቻችን ሳይቀር ሲገለፅ ይታያል፡፡ እስቲ በአንድ ወቅት ከአንድ ወዳጄጋ ስለኢትዮጵያዊነት ስንጨዋወት የነገረኝን ላውሳላችሁ፡፡ በክርክራችን መሃል ወዳጄ ምርር ብሎ ማውራቱን ቀጠለ፡፡ ‹‹እኛ (ክርስቲያኖች) ከሳውዲ ስትሰደዱ ተቀብለን ስላስጠለልን ነው እንዲህ የምትሆኑት፤ የዛን ጊዜ በእንግድነት ባንቀበላችሁ እና ባናስተናግዳችሁ ኖሮ ኢትዮጵያዊ አትሆኑም ነበር›› አለኝ፤ በጣም ተናደድኩ ኢትዮጵያዊ ደም እያለኝ እንደ መጤ በመቁጠሬ በጣም ስሜታዊ ሆንኩ፡፡ ‹‹ቆይ ቆይ ወዳጄ! አንተ እያልከኝ ያለኸው መጤ ነህ ነው፡፡ በዛን ጊዜ ከአሁኗ ሳውዲ የመጡትን እንግዶች ተቀብለው በእንግድነት ያስተናገዱትኮ ያንተውም የእኔም አያቶች ነበሩ፡፡ ክርስትናም እስልምናም የመጡት ከውጭ ነው፤ ያንተም የእኔም አያቶች እዚህ ነው እትብታቸውን የቀበሩት! ማንም አረባዊ ማንም እስራኤላዊ አይደለም፡፡ እምነቱ ይለያይ እንጂ…›› አልኩት፡፡ ዕድሜ ለETV! በእኛ የኢድ በዓል እቺን የማትቀየር ኢትዮጵያዊና እስላማዊ ግኑኙነት ሁሌ እንደደሰኮረ ነው፡፡ ከዓመት ዓመት እንደዲሪቶ እየቀጣጠሉ አንዲት ሃባ የማይለወጥ የጃጀ ድስኮራ!! ይህ ድስኮራ በደንብ ስርዓት ባለው መልኩ በትክክለኛ መልዕክት ተላልፎ ሁሉንም ባኮራ ነበር፡፡ ነገር ግን የእያንዳንዱ ነገር ላይ ላዩ የሚያውቁት የETV ጋዜጠኞች በግልብ እያሉት እንደተለመደው ያልሆነ እንድምታ በማኅበረሰቡ ላይ ይፈጥራሉ፡፡
ኢትዮጵያዊነት በአፄዎቹ ጊዜ ሲሰፋ ሁሉን የኢትዮጵያ ቀለማት እንዳያካትት ተደርጎ ነው፡፡ ሕብረ-ቀለማዊነትን በማያስተናግድ በአንዲት ትንሽ ማንገቻ የታሰረ ትንሽዬ የሕፃን ቁምጣ፡፡ በአሁን ጊዜ ሁሉም ዜጎች እዛ ቁምጣ ውስጥ እራሳቸውን ሲከቱ ማንነታቸው በዜሮ የሚባዛበት የተንሸዋረረ ዜግነት ነበር፡፡ አንዳንዶቹ ይህን ትንሽዬ ኢትዮጵያዊነት እንደማያካትታቸው ሲያውቁ ሌላ ተቃራኒ ፅንፍ በመፍጠር ማንነታቸውን ያስከብራሉ፡፡ የተለያዩ የማንነት ፅንፎች መፈጠራቸው ለሀገሪቷ ዕድገት ማነቆ ነው የሚሆነው፡፡ “የተከበሩ ሟች  አባታችን” ‹‹የአክሱም ሃውልት ለወላይታ ምኑ ነው?!›› ነበር ያሉት፡፡ ይገርማል! ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከሰሜን እስከ ደቡብ ባለው የማንነት መገለጫ እንዲኮራ አባታዊ ምክር መስጠት ነበር ከመሪ የሚጠበቀው ፡፡ የአክሱም ሃውልት ለወላይታው የማንነት መገለጫ ካልሆነ፣ የላሊበላ አብያተ ክርስታኒያት ለሙስሊሞች እንደራስ ቅርስነት ካልታየ፣ የገዳ ስርዓት ለአማራው መኩሪያ ካልሆነ፣ የሐረር ግንቦችና  የነጃሺ መስጊዶች ለክርስቲያኑ እንደራሱ ቅርስ ካልተቆጠረ ኢትዮጵያ ምኗን አገር ሆነች፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያዊነት ሁሉኑም የሚያካትትና ኢትዮጵያውያን ደግሞ ሆደ ሰፊ ሊሆኑ ይገባል ባይ ነኝ፡፡
ወቅቱ በጃንሆይ ገዜ ነበር፡፡ ከጉራጌ ቀቤና የተገኙት የቃጥባሬ ሼህ ጥልቅ የሆነ ኢትዮጵያዊ ስሜት ነበራቸው፡፡ ይህንን ብሔራዊ ስሜት እምነቱ ውስጥ የተለያዩ እስላማዊ እንዲሁም ኢትዮጵያዊ የሆነ ማንነትና ባህል እንዲፈጥሩ አድርጓቸዋል፡፡ የቃጥባሬ ሼህ ኮፍያ ተመልክታችሁ ታውቃላችሁ? ኮፍያው ላይ ከሦስት የተለያዩ ቀለሞች ማለትም አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ የተዋቀሩ ሲሆን አምስት ክቦች ይታያሉ፡፡ አምስቱ ክቦች አምስቱን የእስምልና ማዕዘናት ሲያመለክቱ ሶስቱ ቀለማት ደግሞ ኢትዮጵያነት ያመለክታሉ፡፡ ይሄ ነው ኢትዮጵያዊነት በእምነት ውስጥ! ሁሉንም የሚያካትት! አሁንማ ሁሉም ጥግጥጉን ይዞ ሌላውን የማያካትትና ሌላውን ከአገራዊ አንድነት የሚፍቅ ተግባራት እያከናወነ በቃ የሚለው ጠፍቷል፡፡ አርቆ አሳቢ ድሮ ቀረ፡፡ ሁሉን ነገር ማጦዝ ነው በተንሸዋረረና ሁሉን በማያካትት እይታ….
ጊዜው ቴዎድሮስ ‹‹እምቢ ለአገሬ!›› ብሎ ራሱን የሰዋበትና አጤ ዮሐንስ በተገኘው አጋጣሚ ስልጣኑን ተረክቦ ሙስሊሞች ሃይማኖታቸውን በሀይል እንዲቀይሩ ከፍ ሲልም ያለ ርህራሄ የሚቀላበት ወቅት ነበር፡፡ በዛን ወቅት በጎጃም ሀገረ ገዢ የነበረው ይህንን አስገድዶ ክርስቲያን የማድረግ ዘመቻ በሚገርም ጥበብ ተወጣው፡፡ የሃይማኖት ቅየራው ሂደት የሚካሄደው በዋነኝነት ስጋ በማብላት ነበር፡፡ ሕዝበ ሙስሊም በተሰበሰበበት ቄሱ ከመጋረጃ ፊት ሼኩ ከመጋረጃ በስተኋላ ሆነው ሰንጋውን አጋደሙት፡፡ ከዛማ ከመጋረጃ በስተጀርባ የሚገኙት የሃይማኖት አባት በሬውን ሸልተው ከበጋረጃው ፊትለፊት ለሚገኙት የሃይማኖት አባት ማረጃውን አቀበሉት፡፡ ቄሱ ማረጃውን ወደ ላይ ከፍ አደርገውት ‹‹ይሄው በስመ አብ ብለን ባርከነዋል›› አሉ፡፡ ይህንን ሚስጥር የሚያውቁት ጥቂት የሃይማኖት አባቶችና ባለስለጣናት እንዲሁም የዛ አካባቢ የሙስሊም ማኅበረሰብ ነበር፡፡ ይሄ ነው ጥበብ፣ መተባበሩ በአካባቢው ማኅበረሰብ ለዘላለም ሲወሳ ይኖራል፡፡ ምንም አንኳን ከዛሬ 100 ዓመት በፊት ሙስሊሞችን ሃይማኖት የማስቀየር ስርዓት በቀጥተኛ መንገድ ቢገባደድም አሁንም ሙስሊሙን ሽባ የማድረግ፣ ሽባ አድርጎም ከሃይማኖቱም የማራቅ ሂደት እንደቀጠለ ነው፡፡ ቀጥሎ አንመልከተው፡-
ጭንቅላቱን በለው
እንደሚታወቀው እንደኢትዮጵያ ባሉ አገራት በአንድ ቤተሰብ ውስጥ አባት ያለው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ለቤተሰቡ የመሪነት ሚና ይጫወታል፣ የገቢ ምንጭም ነው፣ ቤተሰቡን ከአደጋ ይከላከላል፣ ባጠቃላይ የቤተሰቡ ራስና ምሰሶ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በአሁን ጊዜ በተለያዩ ምክንያቶች ሙስሊሙ የራሴ የሚለውን መሪ እንዳይኖረው ተደርጓል፡፡ መሪ ለመሆን ከፍ ከፍ የሚሉት ታዳጊ መሪዎች ጭንቅላቻቸው እየተመቱ ቤታቸው ይቀመጣሉ፡፡ ሌላው ደግሞ እንኳን አንድ ማኅበረሰብ ለመምራት ይቅርና አህያዎችን በሰልፍ መምራት የሚያቅተው ሰው የሸህና ሐጂ ካባ ይከናነብና የዚህ ከአፍሪካ በብዛቱ ሦስተኛ የሆነ ሕዝብ ባልፈለገው መልኩ ‹‹መሪ›› ተብሎ ይቀመጣል፡፡ በሌላ ወገን ከሃይማኖቱ አልፎ በሀገሪቱ ጉዳዮች ላይ የሁሉም አገር የሆነችን ኢትዮጵያ ወክሎ አገራዊ ሚና ይጫወታል፡፡ ይሄ ነው ሁለት የተለያየ ዕይታ… በሙስሊሞች በኩል የመሪነት ሚና እንዳይጫወቱ ተቋማቸው ሽባ ሆኗል፡፡ ይህ ተቋም ሕጋዊ ዕይታው ከአንድ ኩባንያ የማይተናነስ በየዓመቱ ፍቃዱን የሚያድስ ተቋም ነው፡፡ ከግዴታዎቹ ውስጥ በዋነኝነት በዓመት ሦስቴ ለበዓላት ራሱን ማሳየትና የማያውቁትን ፖለቲካ መዶስከር ነው፡፡ በሙስሊሞች ዘንድ አንድ ነገር ጠብ ማድረግ የተሳነው ተቋም፡፡ ከባለሙያዎች ይልቅ ባህላውያን የሚበዙበት ተቋም፡፡ ካለመሪ አንድን የአገሪቷ እኩሌታ የሚሆን ማኅበረሰብ ለመምራት ይቅርና አንድን ቤተሰብ መምራት አይቻልም፡፡ በአሁኑ ጊዜ የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ሙስሊሙ አውራው እንደተመታበት የንብ ቀፎ ተበታትኖ ይገኛል፡፡ ስለዚህ ሙስሊሞች ያለመሪ እንዳይቀሳቀሱ ተብትቦ የያዛቸው ገመድ ሊፈታ ይገባል፡፡
ወደ አንድ ጎን ያዘመሙ የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት
እንደሚታወቀው አገራችን ኢትዮጵያ ሃይማኖትና መንግስትን መለያየት እንደመፍትሄ ተመለክታ ትግበራውን ከጀመረች እነሆ ግማሽ ምዕተ አመት ሊሞላን ጥቂት ነው የሚቀረን ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት አንድ የመንግስት ተቋም ተሂዶ ስለአንድ ሃይማኖት የሚያመለክቱ ጥቅሶችንና ፎቶዎችን መመልከት የተለመደ ነው፡፡ አንዳንዴ የሰቀላ ፉክክር በግልፅ የሚካሄድ ከፍ ሲልም የሰቀሉት የሃይማኖት ጎራ ለማገልገል የተቆረጠ ነው የሚመስለው፡፡ አገሪቷ የምትመራው በዓለማዊ ሕግ ሆኖ ተቋማቱ ግን ሲወርድ ሲዋረግ የመጣውን ሃይማዎታዊ ማንነቱ እንደተጠበቀ ነው፡፡ ባጠቃላይ መለስተኛ የሃይማኖት ተወካዮች ይመስላሉ፡፡ ይህ ነው እንግዲ መገለጫው ወደ አንድ ጎን ያዘመሙ ነገር ግን ሁሉንም እናስተናግዳለን የሚሉ የመንግስት ዓለማዊ ተቋሞች፡፡ አንዳንዴ እንዲሁም የራሳቸውን የሚያቀነቅን ሲመጣ ነገሮች በሚያስገርም ፍጥነት ይጠናቀቃሉ፡፡ አመለካከታቸውን የማይደግፍ ሲመጣ ግን ጉዳዩን መጎተት፣ ማመናጨቅ ሲበዛም መሳደብ የራሳቸው ነው፡፡ ምንም እንኳን ባብዛኛው ኢትዮጵያዊ ፈሪሃ አምላክ መሆኑን ባልክድም አለማዊነት ሁላችንም የሚያግባባ መስሎ ይታየኛል፡፡
ተቋም የለሽ ማድረግ
ሙስሊሞች ተቋም የለሽ ማድረግ ከትልቁ መጅሊስ እስከ ትናንሽ መድረሳዎች ድረስ የዘለቀ ነው፡፡ እስላማዊ የሆኑ ተቋማት ሲቋቋሙ በጥርጣሬ ዓይን ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ ለሙስሊሙ ስለየማይገሰሰው ሕገመንግስት ይሰበካል በሌላው ወገን ደግሞ የራሱን የሃይማኖት አጀንዳ እንዲያከናውን ባለሙሉ መብት ይሆናል፡፡ በቅርቡ በመቋቋም ሂደት ላይ እያለ ባልታወቀ ምክንያት የተቋረጠው የዘምዘም ባንክ በዐብይነት የሚጠቀስ ነው፡፡
መሠረተ ልማት ማሳጣት
ይህ ጉዳይ ለአንዳንዶቹ ላይዋጥ ይችላል ነገር ግን ሕዝበ ሙስሊሙን ከአፄዎቹ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ከመሠረተ ልማት ማራቅ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ እስላማዊ ግብረሰናይ ድርጅቶች እንዳይገቡ በሩን መከርቸም የሌላው ዓለምአቀፍ የሚሽነሪዎች ተቋም እንዲገቡ የጥሪ ደውሉን በተደጋጋሚ መምታት የተለመደ ሆኗል፡፡ ባጠቃላይ ሙስሊሞች በመሠረተ ልማት አመካኝቶ የሚሽነሪዎች ሰለባ ማድረግ በግልፅ የሚታይ ጉዳይ ነው፡፡ ታዲያ ምን ይደረግ በንፁህ መጠጥ ውሃ እየተመጣ!
በሩን መከርቸም
እንደሚታወቀው እስልምና ዓለም አቀፋዊ ሃይማኖት ነው፡፡ በየትኛው የዓለም ቦታዎች እስልምና አይገኝም ማለት ይከብዳል፡፡ ሙስሊሞች ደግሞ የጋራ የሆነውን ችግሮቻቸውን በዓለም አቀፍ ስብሰባዎችና አጀንዳዎች ላይ ይፈታሉ፡፡ ይህ ዓለም አቀፋ እስላማዊ ግኑኙነት ከትንሽዋ ጅቡቲ እስከ ብዙ ሙስሊም ሕዝብ የሚገኝባት ኢንዶኔዥያ ያካትታል፡፡ ኢትዮጵያ ግን በብዛቱ ከአፍሪካ ሦስተኛ የሆነ የሙስሊም ሕዝብ እያላት በዓለም አቀፋዊ መገናኛ ብዙሐን ‹‹የክርስቲያን ደሴት ነኝ!›› ብላ በሩን ከዘጋች ሰነባብታለች፡፡ ሌላው ደግሞ ከግኑኙነቱ አልፎ የዓለም አቀፍ የግኑኙነቱ ኃላፊ ሲሆኑ ሙስሊሙ ግን ምንም ዓይነት ምልከታ እንዳያሳይ በማዕቀብ ታጭቋል፡፡ ማዕቀቡ መቼ ያበቃል? ዋናው ነገር ሠላም፣ ዋናው ነገር ጤና፣ ዕድሜ መስታወት ነው እናያለን ገና! ተብሎ የለ…
በመጨረሻም
እምነቶች ጌታቸውን የሚጠሩበት ስያሜ ወይም ቋንቋ ቢለያይም መሠረታቸው ግን አንድ ነው፤ እሱም በመልካም ፀባይ ያዛሉ፣ ከክፉ ምግባር ይከለክላሉ እንዲሁም ለራስህ የምትወደን ለወንድምህ እንድትወድ ያዛሉ፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ የሦስቱ አብርሃማዊ ሃይማኖች ቤት ናት ብዬ ብገልፀው ማጋነን አይሆንም፡፡ ሦስቱም በሰላማዊ መንገድ የራሳቸውን አሻራ የጣሉባት አገር ናት ኢትዮጵያ፡፡
የኢትዮጵያና የኢስላም ግንኙነት ከሌላው ሀገር በተለየ መልኩ የቆየ ነው፡፡ ኢስላም ለዓለም ከመሰበኩ በፊት ኢትዮጵያ ነው የከተመው፡፡ የሰላት ጥሪ አዛን ለመጀመሪያ ጊዜ ያስረቀረቀው የሐበሻ ልጅ የሆነው ቢላል ነው፡፡ እናትና አባታቸውን ያጡት ነቢዩ መሀመድ በኢትዮጵያዊው እናት እንደ እናት ክብካቤ ተደርጎላቸው አድገዋል፡፡ ነቢዩ መሐመድ መካና መዲና አልመች ሲላቸው ሙሉ እምነታቸው ኢትዮጵያ ላይ ጥለው ባልደረቦቻቸውንና ልጆቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ ሰደዋል፡፡ እንግዳ ተቀባይ የሆነው የሀገራችን ሕዝብ ብቸኝነት እንዳይሰማቸው መልካም እንክብካቤና እምነታቸውን በነፃነት እንዲያከናውኑ ፈቅደዋል፡፡
እንደሚታወቀው ውጭ ያሉ አካላት የራሳቸውን ኢ-ኢትዮጵያዊ አመለካከት ለማስረፅ እስከ አሁን ያልተቀረፈው ድህነትና ድንቁርና መፍትሄ ዘየድን በማለት እየሰረጉ ይገኛሉ፡፡ ስለሆነም አንድነት ከሀይልም በላይ መሆኑንና ድህነትና ድንቁርናን ደግሞ በራሳችን ቀናኢ መፍትሄ አሻሽለን ልናሳያቸው ይገባል፡፡ ምክንያቱም ከውጭ የሚመጣ ‹‹መፍትሄ›› የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ አለውና፡፡ በአንድነት ስንሠራ ነው ለውጥና ልማት የሚያመጣው ነገርግን ሁሉንም ያላማከለ ወደ አንድ ጎን የተንጋደደ ተግባር እንደ ግመሏ ጀርባ በአንድ ጎን ያበጠ ይሆናል፡፡ አንዱ አድጎ ሌላው ቢተኮስ ምንም ለውጥ ባያስከትልም እንኳን ያደገው ዕድገት ይገታል፡፡
በጽሑፌ ማገባደጃ ላይ በወሎ ክፍለ ጠቅላይ ግዛት ጎጃም በሚባለው አካባቢ በ1897 እ.ኤ.አ የተወለዱተ የታላቁን አሊም ሸህ ሰዒድ መሐመድ ሳዲቅ ድንቅ ንግግር ልጥቀስና ልሰናበት፡፡

‹‹ … እኛም የአንድ አገር ሕዝብ የሆነው ኢትዮጵያኖች፣ ያንድ ቤት ሰው ስለሆነ ደካሞች በኃይለኞች እንዳይደመሰሱ፡፡ ….የሰው ልጆች በአዕምሮ ተመስርተው እንዲኖሩ የተመሰረተውን ሀይማኖት ለመለያያ መሳሪያ ማድረጋችን ቀርቶ እንዲሁ እንደተጀመረው መተሳሰራችን እየበረታ እንዲሄድና ለራስህ የምትወደውን ለወንድምህ አድርግ በተባለው መሠረት እርስ በርሳችን ተፋቅረን ያለው ለሌለው አካፍሎ… ያልተማረው ተምሮ ሕግን አክባሪ እንድንሆን እንመኛለን…›› ~ (ደሴ ከኢድ አልፈጥር ሰላት በኋላ በ3/6/1954)
—–
ጸሐፊውን ለማግኘት የኢሜይል አድራሻቸው የሆነውን ezunaa@facebook.com ይጠቀሙ::

‹‹ሕዝብ›› ምንድን ነው?


በክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ ብሉይ ኪዳን ውስጥ የሙሴ ታሪክ ትልቅ ሥፍራ ይሰጠዋል፡፡ ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ ከግብፆች ቅኝ ተገዢነት ነፃ ያወጣ መሲህ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሕዝቡ በሙሴ ላይ ያፈነግጥ እንደነበር ዘጸአት፣ ምዕራፍ 32 (ቁጥር 1 – 4) ይተርክልናል፡-
“ሕዝቡም ሙሴ ከተራራው ሳይወርድ እንደ ዘገየ ባዩ ጊዜ፥ ወደ አሮን ተሰብስበው ይህ ከግብፅ ምድር ያወጣን ሰው ሙሴ ምን እንደ ሆነ አናውቅምና ተነሥተህ በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን አሉት። አሮንም፣ በሚስቶቻችሁ በወንዶችና በሴቶች ልጆቻችሁም ጆሮ ያሉትን የወርቅ ቀለበቶች ሰብራችሁ አምጡልኝ አላቸው። ሕዝቡም ሁሉ በጆሮቻቸው ያሉትን የወርቅ ቀለበቶች ሰብረው ወደ አሮን አመጡለት። ከእጃቸውም ተቀብሎ በመቅረጫ ቀረጸው፥ ቀልጦ የተሠራ ጥጃም አደረገው፤ እርሱም። እስራኤል ሆይ፥ እነዚህ ከግብፅ ምድር ያወጡህ አማልክትህ ናቸው አላቸው።”
በ1997 ተቃዋሚዎችን የመረጠ ሕዝብ በ2002 ገዢውን ፓርቲ ይመርጣል፣ በ2008 ለኦባማ ራሱን የሳተ ሕዝብ በ2012 ለራምኒ ይዘምራል፡፡ ይህ ሕዝብ ምን ዓይነት ፍቺ ይገኝለታል? በዚያው በምርጫ 97 ሚያዝያ 29 ኢሕአዴግን በመደገፍ ‹‹ማዕበል›› ለመሰኘት የበቃ ሕዝብ መስቀል አደባባይ ወጣ፤ በማግስቱ ሚያዝያ 30 ከዋዜማው እጥፍ የበዛ (‹‹ሱናሚ›› የተሰኘ) ሕዝብ ወጣ፤ የቱ ነው ሕዝብን በትክክል የሚገልፀው?
ዘርጋው የአማርኛ መዝገበ ቃላት ‹‹ሕዝብ›› የሚለውን ቃል ሲፈታው ‹‹በአንድ አገር፣ ከተማ፣ ክልል፣ ገጠር ውስጥ የሚኖር ጠቅላላ የሰዎች ቁጥር፣ ብዛት›› ይለዋል፡፡ በርግጥ ይህ መዝገበ ቃላት እንደሚለው ‹‹ሕዝብ›› ቁጥር ብቻ ነው ወይስ ሌላ ትርጉም ይኖረው ይሆን? በየፈርጁ እንመለከተዋለን፡፡

ሕዝብ ሕገመንግስቱ ውስጥ
የኢፌዲሪ ሕገመንግስት (1987) በመግቢያው ላይ ‹‹እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች፡-›› ብሎ ይጀምራል፡፡ አካሔዱ ከላይ – ሁሉንም ብሐሮች ካቀፈው ስብስብ (set) ወደታች – ነጠላ ብሔር/ብሔረሰብ (subset) ስለሚወርድ ‹‹ሕዝቦች›› የሚለውን ‹‹የተለያየ የዘር ሐረግ ያላቸው ሰዎች ስብስብ›› ብለን ልንፈታው እንድንዳዳ ያደርገናል፡፡ ግን ደግሞ የአገር ውስጥ ፖለቲካ ዕውቀታችንን ስናስታውስ ሕዝቦች የሚባሉት የብሔር ዕውቅና ያላገኙ፣ የአንድ ቋንቋ እና ባሕል ባለቤቶች ናቸው፡፡ ይሄ ትርጉም የትም ስለማያደርሰን ሌላ የ‹‹ሕዝብ›› ትርጓሜ ፍለጋ እንጓዛለን፡፡
የሕገመንግስቱ ፈጣሪ ኢሕአዴግ ነውና፣ በግንባሩ ስያሜ ውስጥ ያለው ሕዝቦች ማንን እንደሚወክል እንጠይቅ፡፡ ግንባሩ የብሔር ፓርቲዎች ስብስብ ስለሆነ ብዙ ብሔሮችን በአንድነት ‹‹ሕዝቦች›› ብሏል ስንል ደግሞ እላይ ከደረስንበት ድምዳሜ የተለየ ትርጉም እናገኛለን፡፡
ሕዝብ በቁጥር
ነገሩን በምሳሌ እንጀምረው፤ ‹‹የአዲስ አበባ ሕዝብ ኢሕአዴግን መረጠ›› ሲባል ምን ማለት ነው? በ2000ው የሕዝብ ቆጠራ መሰረት ከ1.88 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ፖለቲካዊ ምርጫ ለመምረጥ ዕድሜያቸው ይፈቅድላቸዋል፡፡ ነገር ግን ድምጻቸውን የሰጡት 1.04 ሚሊዮን ያክሉ ብቻ ናቸው፡፡ ከነዚህ ውስጥ ደግሞ 0.56 ሚሊዮኖቹ ብቻ ናቸው ለኢሕአዴግ ድምጻቸውን የሰጡት (ማለትም ዕድሜያቸው ከደረሱ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች አንፃር 30% ያክሉ ብቻ)፡፡ ነገር ግን የአዲስ አበባ ሕዝብ ኢሕአዴግን መረጠ ይባላል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት መሪር ሐዘን አዘነ፣ መተኪያ እንደሌላቸውም ተናገረ›› ሲባልስ የትኛውን ሕዝብ ነው? ስንት ያክሉን ሕዝብ ነው?
ሕዝብ በአስተያየት እና ፍርድ አሰጣጥ
‹‹ሕዝብ ይፈርዳል፤›› እርግጥ ነው ሕዝብ ብዙ ነገሮችን አንድ ላይ አመሳክሮ ይፈርዳል፣ የፍርድ ባለቤትም ስለሆነ ፍርዱ ቢወደድም ቢጠላም ይፀድቃል፡፡ ሕዝቦች ሶቅራጠስን፣ እየሱስን እና ሌሎችንም ያለዘመናቸው የተፈጠሩ ነብዮችን እንደተሳሳቱ ፈርዶ አይቀጡ ቅጣት አስቀጥቷቸዋል፡፡ ስለዚህ የሕዝብ ፍርድ ሁሌም ፍትሐዊ ነው ማለት ይቻል ይሆን?
ሀ). ሕዝብ for dummies
ሕዝብን እና ፍርድ አሰጣጡን፣ ወይም ውሳኔ አስተላለፉን በገደምዳሜው ከተቋረ ውሃ ጋር ማመሳሰል ይቻላል፡፡ አንድ የውሃ ኩሬ ቦይ ከተቀደደለት፣ መጨረሻው ገደልም ይሁን ግድብ፣ በየትም በኩል ይቀደድለት በየትም ዝም ብሎ ይፈሳል፡፡ አንድ ኩሬ ውስጥ የተቋረ ውሃ የኬሚካል ጠብታ ብናፈስበት፣ ኬሚካሉ መርዝም ይሁን መድሃኒት ወዲያው ይቀላቀላል፡፡ ቅልቅሉም እንደኬሚካሉ ብዛት በውሃው ውስጥ ሰርፆ ይቀራል፡፡
ሕዝብም እንዲሁ ነው፡፡ የመገቡትን ሐሳብ አዳኝም ይሁን አጥፊ ይቀበላል፡፡ የከፈቱለትን መንገድ መጨረሻው ይመርም አይመር ይከተላል፡፡
ግለሰቦች የተሰጣቸውን ሐሳብ መመርመር ሲጀምሩ፣ ወይም ‹‹ለምን?›› ብለው መጠየቅ ሲጀምሩ ከ‹‹ሕዝብ›› ተራ ይወጣሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ጠያቂ ግለሰቦች በተቀደደላቸው በመፍሰስ ፈንታ ቦይ ቀዳጅ፣ ፈር ቀዳጅ ወይም መሪ ይሆናሉ፡፡ ስለዚህ ከሕዝብ የጋርዮሽ ሐሳብ አራማጅነት ያፈነገጡትን ግለሰቦች እንበላቸው እና ስለሕዝብ ምንነት እናስረዳቸው፡፡
ለ) ሕዝብ ለግለሰቦች
ሕዝብ ባገኘው ሁሉ መንገድ የሚማር ከዘመን ዘመን እያደገ፣ እየተሻሻለ የሚሄድ በአንድ አካባቢ ወይም አገር ለረዥም ዘመናት አብረው የሚኖሩ ትውልዶች ስብስብ ነው፡፡ ሕዝብ ካገኘው ነገር ሁሉ ትምህርት እየቀሰመ፣ በቀሰመው ነገር ላይ ተመስርቶ ባሕሉን እና እሴቱን የሚገነባ፣ በገነባው እሴት ላይ ተመስርቶ ፍርድ የሚሰጥ፣ ግለሰቦችንም ሆነ ሁነቶችን ገዢ/ከሳች አካል ነው፡፡
በዘመናችን ሕዝባዊ አስተሳሰብን ከሚፈጥሩ ነገሮች ውስጥ
(1) ትምህርት፣
(2) መገናኛ ብዙሐን እና
(3) ስርዓተ አምልኮ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
እነዚህን ሦስት የሕዝባዊ አስተሳሰብ ምንጮች የሚገብሩት ዕውቀት የሕዝቡን ትውፊት፣ ባሕል፣ እሴት ይቀርጻሉ፡፡ ስርዓተ አምልኮን በተመለከተ ወደፊት አዳዲስ ሃይማኖቶች እና አማልክቶች የመፈጠር ዕድላቸው ጠባብ ነው፤ ቢፈጠሩም አማኝ/አምላኪ የማግኘት ዕድል የላቸውም፡፡ መገናኛ ብዙሐን እና ትምህርት ግን መቆሚያ የላቸውም፡፡
መንግስታት ስርዓተ ትምህርትን እና መገናኛ ብዙሐንን የሚቀርፁበት መንገድ ምን ዓይነት ሕዝብ ማፍራት እንደሚፈልጉ ያሳብቃል፡፡ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ለትምህርት በጣም ጉጉ ከመሆናቸው የተነሳ አቅማቸው የፈቀደውን ያህል ጥረት ትምህርትን ለማስፋፋት አድርገዋል፡፡ ሚኒስትሮቻቸውም ጥሩ የትምህርት ደረጃ የነበራቸው እንጂ እንደአሁኑ ዘመን በፓርቲ ታማኝነት ብቻ የሚሾሙ አልነበሩም፡፡ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ሕዝብ እንዲያውቅ እና እንዲነቃ ያደረጉት ሙከራ በራሳቸው/በአስተዳደራቸው ላይ የሚያምፅ ትውልድ እንዲያፈራ ሆኗል፡፡
አሁን የእርሳቸውን ተቃራኒ እየተከተሉ ያሉት መሪዎች የፈጠሩት የትምህርት እና መገናኛ ብዙሐን ስርዓት ግን በአሁኑ ሰዓት ለሚስተዋሉት አምባገነን ገዢን የመቀበል (እና ‹‹መተኪያ አይገኝላቸውም›› ብሎ የመስጋት) እውነታዎች መንስኤ ነው፡፡

ሕዝብ የስርዓት ውጤት ነው፤ ጠያቂን ሕዝብ መፍጠር የመንግስት ግዴታ እንጂ መብት አይደለም፤ ጠያቂ መሆን ደግሞ የሕዝብ መብት ነው፡፡