Category Archives: መዝናኛ

የሴቶች ወጪ <=> የወንዶች ገቢ


ሴቶች በዝግመተ ለውጥ ካለመቆጠር ወደ መቆጠር ከመቆጠርም አልፈን ‹ከስኬታማ ወንድ ጀርባ አንዲት ጠንካራ ሴት አለች› የሚባልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ ተፈጥሮና ባህላችን ተደማምረው አሳማኝ ምክንያት ሳይኖር የሴትና የወንድ የሆኑ ነገሮች እንዲለዩ ሆነዋል፡፡ የሥራ ዘርፍ፣ የትምህርት ዘርፍ፣ አለባበስ፣ አነጋገር፣ አካሄድ፣ አጻጻፍ፣ ባሕሪ፣ አመለካከት… ሁሉም የሴት እና የወንድ የሚባሉ አሏቸው፡፡ ጥልቅ የመመራመር ክህሎትን በሚጠይቁ ዘርፎች ተሰማርተው የሚገኙ አንዳንድ ሴቶች የተቀረነውን ወክለው የተቀመጡ እንጂ እንደወንዶቹ እራሳቸውን ብቻ ወክለው አይደለም፡፡ ለምሳሌ ‹የመጀመሪያው የወንድ ጄኔራል› የሚባል ነገር ሰምተን አናውቅም፡፡ ‹በመጀመሪያ ወደጠፈር የተጓዘው ወንድ› ሲባል ልንሰማም አንችልም፡፡ ምክንያቱም መጀመሪያውኑ ወደ ጠፈር የመጓዝ ተግባር እና የጦር አዛዥነት ሥራ የወንድ ብቻ ተደርጎ ስለሚቆጠር እና በዘርፉም የሴቶች ተሳትፎ ከወንዶቹ ጋር ሊነፃፀር የሚችል ስላልሆነ ነው፡፡
በአገራችን ከተለመዱና የወንዱ ተግባር ተደርገው ከሚቆጠሩ ነገሮች አንዱ ወጪዎችን የመሸፈን ኃላፊነት ነው፡፡ እስካሁን ድረስ ‹ሴትማ አትከፍልም› እየተባለ የከፋይነት ሥራ የወንድ እንደሆነ ቀጥሏል፡፡ ማኅበረሰባችን ለወንድ የወጪ ሸፋኝነት ኃላፊነት ሲሰጥ በውስጥ ታዋቂነት ጥሮ ግሮ በሚያፈራው ኃብት የሚመሰርተውን ቤተሰብ የማስተዳደር ሥራ ከሱ እንደሚጠበቅ ይረዳዋል፡፡ ስለዚህም በተሰማራበት ዘርፍ ጠንክሮ በመሥራት ገቢውን ማሻሻል የሕይወት ዘመኑ መመሪያው ይሆናል፡፡ ከሴት የሚጠበቀው ጥሩ ሚስት እና እናት እንድትሆን ነው፡፡ የራሷ ገቢ የምታገኝበት መተዳደሪያ ወይም ሥራ ያላት ብትሆንም እሰየው ነው፤ ባይኖራትም ግን ችግር የለውም፡፡ እንዲኖራት አትገደድም፡፡
ወንድየው ወደፊት ለሚያገባት ሚስቱና በጋራ ለሚያፈሯቸው ልጆች ማስተዳደር እንዲችል ገቢውን ለማሳደግ እና ኃብት ለማፍራት ተግቶ ይሠራል፡፡ ‹ቤት ሳይኖረኝ› ‹ቋሚ ሥራ ሳልይዝ› ‹ጥሩ ደሞዝ ሳይኖረኝ› የሚሉ ወንዶች እንጂ ሴቶች እምብዛም አይደሉም፡፡ ባጭሩ ማኅበረሰባችን ለሴቶችና ለወንዶች ብሎ ሁለት የተለያየ የተግባር መንገድ አስቀምጦልናል፡፡ በሴቷ መንገድ የሚገኙ ወንዶች  እንዲሁም በወንዱ መንገድ የሚገኙ ሴቶች ቢኖሩም በአብዛኛው ሴቱም ወንዱም በተመደበለት መንገድ ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡ ይህ አመዳደብ ወንዶችን የሴቶች የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር ሆነው በበላይነት እንዲመሩን ያደርጋቸዋል፡፡ እኛ ሴቶችም በአብላጫ ድምፅ ያፀደቅንላቸው ይመስላል፡፡

የዩንቨርስቲ ተማሪ በነበርኩበት ወቅት ከሴት ጓደኞቼ ጋር እራት እንብላ ብለን የካፌ ምግብ ትተን በከተማው ወደሚገኝ ሬስቶራንት ከሄድንባቸው ጊዜያቶች በአብዛኛው ለማለት ባልደፍርም ሒሳባችን በማናውቀው ሰው ተከፍሏል እንባል እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ግብዣው ሲደጋገምብን ነገሩ ጣመንና እራሳችን ስንከፍል መበሳጨት ደረጃ ደረሰን ነበር፡፡ የሚከፍልልን እንደማናጣ በመተማመን ምንም ሳይኖረንም ወጥተን እራት እስከማዘዝ የደረስንበት አጋጣሚም እንዲሁ ትንሽ አልነበረም፡፡
በሥራ ዓለም ያለች አንድ ወዳጄ ስታጫውተኝ ከጓደኞቿ ጋር በእረፍት ቀናቸው የሚጋብዛቸው ወንድ ለማግኘት ፕሮግራም እንዳለበት ሰው ዘንጠው፣ ረፈድፈድ ሲል ተያይዘው ይወጡና መጋበዝ የሚፈልጉበት ሬስቶራንት ወይም ሆቴል አካባቢ ያለ ካፍቴሪያ ይቀመጣሉ፡፡ መቼም  ከሦስት ወይም ከአራት ሴት ቢያንስ አንዷ በእረፍት ቀን ደውሎ ‹ምሳ ልጋብዝሽ› የሚል አድናቂ አታጣምና  የተደወለላት ሴት ያለችበትን ቦታና ከጓደኞቿ ጋር እንደሆነች በማሳወቅ መምጣት እንደሚችል ትነግረዋለች፡፡ ይመጣና እዛው ሻይ ቤት ቆይተው ምሳ ሰዓት ሲደርስ ‹የት እንብላ?› ሲባል ያው በቅርብ የሚገኘው ሬስቶራንት ወይም ሆቴል ይመረጥና  ያሻቸውን ይበላሉ ያማራቸውን ይጠጣሉ፡፡ ከፋዩ የታወቀ ነው፡፡ ጋባዡን ያመጣችው ሴት ከጎኑ ከሌሎቹ በተለየ ቀረብ ብላ የመቀመጥ የውዴታ ግዴታ አለባት፡፡ ሊጋብዝም አይደል! ይህ ሰው በድጋሜ ላግኝሽ ብሎ ላይደውልላት ቢችልም ግድ አይሰጣትም፡፡ ወላድ በድባብ ትሂድ አይደል የሚባለው ለሚቀጥለው ሳምንት ደግሞ የሌላ ጓደኛቸው አድናቂ ወይም አዲስ የሚገኝ ስፖ (ስፖንሰር ተቆላምጦ ሲጠራ) አይጠፋም፡፡ ይህ ሁኔታ በጠንካራ ግንኙነት ላይ የተመሠረተ የፍቅር ሕይወት ስትጀምር ወይም ትዳር እስክትይዝ ድረስ ሊቀጥል ይችላል፡፡
ከወዳጄ የሰማሁትን በምሳሌነት ጠቀስኩ እንጂ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ሌሎች በቁጥርና በዓይነት የበዙ ታሪኮች ያደባባይ ሚስጥር መሆናቸው የማይካድ ሐቅ ነው፡፡ እንዲያውም አንባቢ ቢያንስ አንድ ከዚህ ጋር የተያያዘ እውነተኛ ገጠመኝ ይኖረዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በአስተያየት ቢያሰፍረውም ደስ ይለኛል፡፡
ሴቶች ፍቅረኛ ከመያዛቸው በፊት ‹በስፖንሰር የመዝናናት እና ወጪን መሸፈን› መርሕ ላይ የተመሰረተ ኑሮ ለምደው፥ ፍቅረኛቸውን ወይም የትዳር አጋራቸውን በሚመርጡበት ወቅት ምርጫ ውስጥ የሚያስገቡት ወንድ ከስፖዎች ያልተናነሰ ወጪያቸውን ሊሸፍን የሚችለውን ነው፡፡ ከጓደኛቸው ያልተናነሰ ኑሮ ለመኖር ከመሻት ወይም የተሻለ ከመመኘት እና ቤተሰብን ለማስደሰት ያላቸውን ፍላጎት ለሟሟላት በዕድሜ በጣም ከሚበልጧቸው፣ ከውጭ አገር ዜጎች እና ባለትዳር ከሆኑ ጋር የፍቅር ግንኙነት ይጀምራሉ፡፡ ‹ሴቶች ፍቅረኛቸውን የሚመርጡበት ዋነኛው መስፈርት የኃብት መጠን ነው› የሚል ትችት ከወንዶች በተደጋጋሚ የሚሰነዘረውም ለዚህ ይመስላል፡፡ በዚህ መልኩ የሚመሰርቱት የፍቅር ጓደኝነት ወይም ትዳር ሴቶችን በቀጥታ የወንዶች የኢኮኖሚ ጥገኛ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ሴቶቹ ወጪያቸውን በራሳቸው ችለው ለመኖር ስለማይችሉ ባያምኑበትም ለወንዱ ትእዛዝ እና ፍላጎት ተገዝተው እንዲኖሩ ይገደዳሉ፡፡
በርግጥ ለሴቶች እንዲህ ዓይነት ባሕሪ ማሳየት ማኅበረሰባችን ከፍተኛውን ሚና ቢጫወትም በተለይ በጉዳዩ ላይ ተዋናይ የሆኑት ወንዶችና ሴቶች ተጠያቂ ከመሆን አይድኑም፡፡ በዋነኝነት ግን ከወንዱና ከሴቱ ተጠያቂው ማነው ለሚለው ጥያቄ መልስ ማግኘት ጉዳዩን እንደማውራት ቀላል አይደለም፡፡ ከዶሮና ከእንቁላል ማን ቀድሞ ተፈጠረ ዓይነት ነገር ነው፡፡ ወንዶች ጊዜያቸውን፣ ዕውቀታቸውን እና ጉልበታቸውን ተጠቅመው በሚያገኙት ገቢና ኃብት በመጠቀም አብራቸው የፍቅር ጊዜ ለማሳለፍ የምትፈቅድ ሴት እስክትገኝ ድረስ ያለመሰልቸት ሴቶችን ለማዝናናት ሲያውሉት ምንም አይመስላቸውም፡፡ ገቢያቸው እራሳቸውን ለማዝናናት የማይፈቅድላቸው ሴቶችም ወጪያቸውን ሸፍነው ሊያዝናኗቸው ፈቃደኛ በሆኑ ወንዶች ይደለሉና በስፖንሰር የመዝናናት መስመር ውስጥ ይገባሉ፡፡ ገንዘቡን ለዚህ ተግባር የሚያውል ወንድ ባይኖር ሴቷ በዚህ መስመር አትገኝም፤ እንዲሁም ገንዘብ የማያማልላት ሴት ብትኖር ኖሮ  ወንዱ የፈለጋትን ሴት ለማግኘት ገንዘቡንና ሃብቱን ባልተማመነ ነበር፡፡ ለዚህም ነው የችግሩ መንስኤ ‹ሴት ናት›፣ ‹ወንድ ነው› ብሎ ለመፍረድ የሚከብድ የሚሆነው፡፡ እንዲያውም በመሀል ቤት የሴትና የወንድ የፍቅር ግንኙነት ወደ ‹ነፃ ገበያ›ነት እንዳይጠጋ ስጋት አለኝ፡፡
ስለዚህም ወንዶች ገንዘባቸውንና ኃብታቸውን ተማምነው ሴቶችን ለማጥመድ የሚያደርጉትን ጥረት እና ወጪዎችን መሸፈናቸውን በመተው እኛ ሴቶች የራሳችንን ወጪ መቻል እንዳለብን እንድናስብ ቢያደርጉ፤ ሴቶች ደግሞ ‹እቤት ከመዋል› ብለን ብቻ መሥራታችንን ትተን ገቢያችን ወጪያችንን እንዲችልልን የተቻለንን ሁሉ ጥረት ብናደርግ፣ ፍላጎታችንን ከገቢያችን ጋር ብናመጣጥነው እና ዓላማ ኖሮን ለምንመሠርተው/ለመሠረትነው ኑሮ በኢኮኖሚ ረገድ ጉልህ አስተዋፅኦ ማድረግ ብንጀምር እንዲሁም የራሳችን የሆነ አቋም ቢኖረን ወደፊት ብዙ ለውጦችን እናያለን ብዬ አምናለሁ፡፡ የአሁን ዘመን ወጣት ሴትና ወንዶች የመጪው ትውልድ ወሳኝ የማኅበረሰብ ክፍሎች ነንና፡፡

በመጨረሻም፣ ይህ ጽሑፍ የማይወክላቸው ጥቂቶች እንዳሉ ሳላስታውስ አላልፍም፡፡

ሎሚ ሽታ… መጽሐፍ አንደ ፊልም

ሶሊያ ሽመልስ

መጀመሪያ ይህንን ጽሁፍ ለመጻፍ ስነሳ ሙሉ ለሙሉ የፊልም ተመልካች አስተያየት ብቻ እንሆነ ይቆጠርልኝ፡፡ ባለሞያነት ሲያልፍም አይነካካኝ! ባይሆን የጥበብ አፍቃሪ ዕይታ ነገር ነው በሉና ውሰዱልኝ፡፡
የአማርኛ ፊልሞች ላይ ተስፋ ከቆረጥኩ ከራርሜለሁ፡፡ ታዲያ አንድ ከሃገር ገባ ወጣ የሚል ጥበብን በምንም ሁኔታ የሚያደንቅ ወዳጄ (እየተበሳጨም ቢሆን) እግሩ ወጥቶ በገባ ቁጥር የአገርኛ ፊልሞችን አብሬው እንዳይ ይጋብዘኛል፡፡ የእርሱን ጨዋታ ፍለጋም የፊልሞቻችንን ለውጥ ለማየትም ያህል በርሱ ግብዣ ክፍተት ልክ ነው አማርኛ ፊልሞችን የማየው፡፡ ታዲያ እነርሱም አይቀየሩም፣ እኔም አልቀየርም፤ እበሳጫለሁ፣ ያበሳጩኛል፤ ጓደኛዬን ተነጫንጬበት ቆይታችን ያበቃል፡፡ ተመሳሳይ ሁነቶችን በተመሳሳይ ስሜቶች እያስተናገድን እንደጋግማለን፡፡ እርሱ ፊልሙ ጥሩ ጎን ባይኖረው እንኳን ፈልጎ (ምንም ጥሩ ጎን የሌለው ፊልም የሚሰራባቸው አገራት መካከል መቼም ዋነኞቹ ነን፡፡ ይህንንም እንግዲህ እንደለመድነው፤ ከዓለም አንደኛ ምናምን ብለን ገጽታ ለምን አንገነባበትም?)  ይሔንን እንደዛ ቢያደርጉት እኮ ጥሩ ፊልም ይሆን ነበር፣ ትንሽ አክቲንጉን እያለ… ማጽናኛ ቢጤ ሊነግረኝ ይሞክራል፡፡ በዚህ የአገርኛ ፊልሞች ብስጭቴ ነበር ከወራት በፊት የአዳም ረታ እቴሜቴ ልቦለድ ወደ ፊልም እየተቀየረ እንደሆነ የሰማሁት፡፡ እውነቱን ልናገርና ከፋኝ! አዳም ምን ነክቶት ነው ለፊልም አሳልፎ የሚሰጠን ያውም እቴሜቴን ብዬ ለጥቂቶች ነግሬያለሁ፡፡ ኧረ እንደውም በፊስቡክ ላይ ራሱ ስጋቴን አስቀምጬ ነበር!
(ስለ አዳም ሌላ ቀን እናወራ ይሆናል ስለ እቴሜቴ ግን ዝም ብዬ አላልፍም፡፡ ከኢ-ፓለቲካዊ ንባብ ከራቅኩ ቆይቻለሁ፡፡ እንደውም ትቼዋለሁ ማለት ይቀላል፡፡ አዳም ረታ ሲሆን ግን ሁሉም ነገር ሌላ ይሆናል፡፡ በጽሑፉ፣ በፊልሙ፣ በመጽሐፉ፣ በቲያትሩ በሁሉም ቦታ የሚታየውን አገራዊ ዝቅጠት ለማረሳሳት የቀረልኝ ብቸኛ ማጽናኛ ነው፡፡ እቴሜቴ ደሞ የብዙዎቻችን (በተለይ የሴቶቹ) ታሪክ በዘመን፣ በዓይነት እና በሰፈር ተከፋፍሎ የተቀመጠበት ምርጥ ሥራው ነው፡፡ ሆ…… ስለእኔ ነው እንዴ የሚያወራው አስብሎኛል፡፡ ያውም ብዙ ጊዜ! ይህንን የምንጊዜም ምርጥ መጽሐፍ ነው አዳም ለሐበሻ ፊልም ሠሪ የሰጠብኝ ብዬ ነበር የተከፋሁት!)


ምሳጤ 1-ፓስተሩ

በዚያው የፊልሙን መሰራት በሰማሁ ሰሞን ፖስተሩን አየሁት፡፡ በእኔ ህይወት ቀዳዳ ብትገባ አገርህን ታያታለህ -የምስራቅ ንግግር የፊልሙ ፖስተር ላይ ይታያል፤ ረጋ አልኩኝ፡፡ ተመስገን! ቢያንስ ቢያንስ ቁም ነገር እንዲሆን ታስቧል ማለት ነው የሚል መረጋጋት ተሰማኝ፡፡ የፖስተሩ ገፅታ በሚገባ የተሰራ እና የመጽሐፉን መንፈስ ያልለቀቀ መሆኑ አረጋጋኝ፡፡ ሌላው የምርቃቱ ዜና ባለፉት ሳምንታት እስኪመጣ ድረስ ‹ምን አድርሰውት ይሆን፣ ምስራቅን እንዴት አደረጓት ይሆን? ወይ ጉድ እንዴት ነው አሁኑን እና ጥንቱን የሚያገናኙት?› አልፎ አልፎ የሚመጡብኝ ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ እውነቱን ለመናገር የሚቆረጡ እና ከታሪኩ የሚወጡ ገጸ ባህሪያት እንደሚኖሩ ሁሉ ጠርጥሬ ነበር፡፡

ምሳጤ 2- ምርቃቱ
ባለሞያዎቹ አስበውበት ይሁን ሳይችሉ ቀርተው (በምረቃው ወቅት የቲያትር ቤቶችን ትብብር አለማሳየት የማርቪክ ፊልም ፕሮዳክሽን ማናጀር ወ/ት ፊቨን ጠቅሳው አልፋለች) ምረቃው የተጋነነለት እና የአሰልቺው “በመላው ኢትዮጵያ በሁሉም ቲያትር ቤቶች በተመሳሳይ ሰዐት” በሚሉ ከፊልሙ ስኬት በላይ የምርቃቱ ስኬት የሚያሳስባቸው ፊልሞች ዓይነት አልነበረም፡፡ ተመስገን ነው! ለቧልት ፊልሞች ምርቃት የምናባክነውን ረዥም ሰዐት በዚህ ፊልም ምረቃ ወቅት አልነበረም፡፡ በእርግጥ ጥቂት ቸልተኝነት እና የማስተባበር ችግሮች ይታዩበት የነበረው ይህ የብሔራዊ ቲያትሩ የመጀመሪያ ቀን የምረቃ ሥነ ስርአት እንደ ሌሎቹ ፊልሞች ዓይነት ፊልም መጠበቅ እንደማይገባ ከሚናገሩ ማሳያዎች አንዱ ነበር፡፡

በስነ-ስርአቱ ላይ ደረጀ ኃይሌ መድረኩን የመራ ሲሆን የፊልሙን መነሻ ልቦለድ ጸሐፊ የአዳም ረታን ስራዎች ዝርዝር በንባብ ለተመልካቹ አሰምቷል፡፡ የፊልሙ ዳይሬክተር እና ስክሪፕት ጸሐፊ እንዲሁም የፕሮዳክሽን ካምፓኒው ማናጀር ምስጋናቸውን ለማቅረብ ወደ መድረኩ ብቅ ብለው ነበር፡፡ ማስተባበር የጎደለውን መድረክ ይበልጥ አጋልጠውት ተሰናበቱን እንጂ፡፡ ማናጀር ፊቨን በጽሁፍ እና በንግግር መሃል ባለ በፍርሃት በተሞላ የንግግር ሙከራዋ የቲያተር ቤቶችን ወቀሳ ጀምራ አቋርጣዋለች፡፡ የገንዘብ እጥረት እንዳላጋጠማቸው እና ከ700 ሺኅ  ብር በላይ ለፊልሙ ማዋላቸውን ነግራን ከመድረክ ስትሰናበት ደረጀ ኃይሌ ታታሪ ሠራተኛ ስለሆነች ነው ንግግር ያልቻለችው ብሎ አስተባብሎላታል፤ (ምክንያቱ እና ንጽጽሩ ባይጥምም)፡፡ አብርሃም (የፊልሙ ዳይሬክተር እና ስክሪፕት ጸሐፊ) ድጋፍ ያደረጉ ሰዎችን እና  አዳም ረታን በስክሪፕት ሥራው ወቅት ላደረገለት ትብብር አመስግኗል፡፡ የፊልም አስመራቂ በማይመስል ቸልተኛ የአለባበስ ስነ ስርአት መድረክ ላይ የተገኘውን የአብሃምን አለባበስ ሳይ ምናለበት እስቲ ታዳሚውን ማክበሩን እና ማስታወሱን ለማሳየት ያህል በስነ ስርዓት ቢለብስ አስብሎኛል፡፡ እንግዳ ክቡር ነው፤ የእኛ ጥሩ ሆኖ መታየት የአክብሮታችን መገለጫ እንጂ ራሳችንን ከፍ ከፍ ማድረጊያ ተደርጎ ሊቆጠር አይገባም፡፡ (እንደዚያ ተብሎ ከታሰበ!)
ከሞላ ጎደል ባልተጋነነ የምረቃ ስነ ስርዓት እና በአዳም ረታ መልዕክት ፊልሙ ተጀመረ፡፡ አዳም በመልክቱ ሥራችን መማሪያችን ይሁን ብሎ ለባለሞያዎቹ እንኳን ደስ ያላችሁ መልእክቱን አስተላፏል፡፡
ምሳጤ 3 -የፊልም ስክሪፕቱ
አብሃም እጁ ይባረክ እና መጽሐፉን ወደ ስክሪፕት ለመቀየር የሚነሳ ማንኛውም ሰው ከዚህ በተሻለ መልኩ ሊያደርገው አይችልም ነበር እስክል ድረስ በአሳማኝ ሁኔታ ነው ከመጽሐፉ ወደ ፊልም ያሻገረን፡፡ ድሮ እና ዘንድሮን እያፈራረቀ ባሳየበት ትረካ የታደሰን ውልደት እና ዕድገትን እና የታደሰን ትዳር በተራ በተራ በምርጥ የስክሪፕት አጻጻፍ አሳይቶናል፡፡ እውነቱን ለመናገር በመጽሐፉ የነበረችው የታደሰ የረዥም ጊዜ ፍቅረኛ ሴተኛ አዳሪዋ (ጸሐይ) ካለ መኖርዋ ውጪ ላላየው እችል ይሆን ብላችሁ የምትሰጉለት የመጽሐፉ ክፍል የለም፡፡

ሎሚ ሽታ ከነአጃቢዋ ሁላገርሽ፣ ታደሰ ከነዝምታው፤ እናቱ ምስራቅ ከነምሬቷ፤ አስናቀ ከነማጭበርበሩ ሁሉም ነፍስ ዘርተው የፊልም ገጸ ባሕሪይ ሆነው አሉ፡፡ የፊል መቼት ያለምንም ማምታታት በጥራት ተሰራ ሲሆን በተራዎቹ ፊልሞቻችን ላይ እንደተለመደው ዓይነት የታሪክ ወጥነት ማጣት (ታሪክ አለን ስላሉን እንጂ ትልቁ ችግራችንማ ታሪክ ያለው ፊልም ማጣት ነው) በዚህ ፊልም ይህ ችግር ፈጽሞ አይታይም፡፡
ትወና እና ዳይሬክቲንግ
ሎሚ ሽታ የተዋናዮች ምርጫው ብዙም የሚያስከፋ አይደለም፡፡ሁሉም ፊልም ላይ የሚታዩትን እና እነሱ ከሌሉበት ፊልም የለም ብለው ከሚያስቡ የተራ ፊልሞቻችን ከዋክብት ሎሚሽታ ነጻ ነው፡፡ ተመሳሳይ እና አለመቻሉን የማያውቅ ተዋናይ የሰለቻችሁ ሎሚ ሽታን እዩት ግልግል ነው! አልፎ አልፎ ከሚያጋጥሙ የትወና ብቃት ችግሮች ውጪ በተለይ የመጽሐፉን ገጸ ባሕሪያት በሕያውነት ለማረጋገጥ እና አንባቢ ተመልካችን ላለማሳዘን እንደተጨነቁ መናገር ይቻላል፡፡ በተለይ የምስራቅን (የታደሰን እናት) እና የሁላገርሽን ገጸ ባህሪይ የተጫወቱት ተዋንያን እንደሚችሉ አሳምነውኛል፡፡ የጥንቱን የቀይ ሽብር ነጭ ሽብር ዘመን ወደ ፊልሙ የተቀላቀሉበት መንገድ የተገነጠለ (ያልተዋሀደ) ቢመስልም ያን ያህል ተመልካችን አያስቀይምም፡፡
የአስናቀ ቤት ከላይ የታደሰ ቤት ከታች የታደሰ አሮጌ መኪና የሎሚሽታ ጠይምነት ቤቱ እና የታደሰ እሳት ወይ አበባ… ሁሉም እንደሳላችሁት አሉ፡፡ ዕድሜ ለጠንካራው ፕሮዳክሽን ይሁንና  ከቤቴ በላይ ቁራ ሰፍሮም… ሳይቀር በታደሰ ቤት ጣራ ላይ ቁራው ቆሞ ይገኛል፡፡

ኮስታራው ሎሚ ሽታ

ፊልሙ ኮስታራ ነው፡፡ ኮስታራ ፊልም በናፈቀን በዚህ የቧልት ዘመን የተገኘ ጠንካራ ፊልም ሆኖ እንዲወጣ መፍቀዳቸው ባለሞያዎቹን ያስመሰግናቸዋል፡፡ ለነገሩ ሎሚ ሽታን ሲመርጡ ጉዳዩን አስበውበት እንደሆነ ያስታውቃል፡፡ ቢሆንም ተመልካችን ሳይንቁ ገበያን ሳያሳድዱ ፊልሙን በይዘቱ ብቻ እንዲታይ መፍቀዳቸው ከዘመኑ የፊልም መንፈስ የራቀ ነውና ዘመኑን ለተጋፈጣችሁ የፊልሙ አባላት ሙገሳዩ በዚሁ አጋጣሚ ይድረሳችሁ፡፡ ሎሚ ሽታ በተለያዩ የፊልም ባለሞያዊ ምዘና ቢለካ ሙሉ ፊልም ላይሆን ይችላል፡፡ ከመጽሐፍ እንደመምጣቱ ግን በዚህ ገበያን በቧልት ብቻ ለማግኘት በሚሮጥበት ዘመን እንደ መምጣቱ ግን ተሳክቶለታል፡፡ ዘመኑን ተጋፍቶ አዲስ ነገርን ሞክሮ ለዚያውም በጥሩ አፈጻጸም ለዓይናችን በቅቷልና ተሳክቶለታል፡፡ ከጥበብ ከዚህ በላይ ምን ይፈለጋል? እነ አብርሃም ከበረቱ ወይም ለሌሎች አርአያ ከሆኑ እነከአድማስ ባሻገርን፣ እነሰመመንን፣ እነሰንሰለትን… በፊልሞቻችን እናይ ይሆናል፡፡ ሎሚሽታም የቧልት ፊልምና  የስኬት ማማ ተደርጎ መቆጠር የሚያቆምበት ዘመን መጀመሪያ ሆኖ ሊቆጠር ይችል ይሆናል! ማን ያውቃል?