Opportunism (ዝንደዳ?)

ጥንት

ከሰው ልጆች የስልጣኔ ታሪክ ጋር እኩል የሚጠቀስ ረጅም ታሪክ አለው፡፡ ከክርስቶስ ልደት አምስት መቶ አመታት በፊት አቴና የብዙ ሰዎች መመላለሻ በመሆኗ የከተማው ኑሮ የበረታ ወድድርን ፈጠረ፡፡ በዚህም ምክንያት ከተለመደው የተመጠነ ጤናማ አካልና መንፈስን የሚያጎለብት ትምህርት በላይ የሆነ ነገር ያስፈልግ ነበር፡፡ በዘመኑ የነበሩ (sophist)  ሶፊስት የተሰኙ ሊቃውንት  ሰባት የትምህርት ስልቶች (grammar, dialectics, Rhetoric, mathematics, geometry, astronomy and music) በደንብ አቀናብረው የከተማውን መላ ወጣቶች በተለይ የሀብታሞቹን ልጆች ደሞዝ እየተቀበሉ በመዘዋወር (አንድ ቦታ ሳይረጉ) ያሰተምሩ ነበር፡፡ ዋናው ዓላማቸውም እንዴት የወቅቱን ሁኔታ ተጠቅሞ መክበር እንደሚቻል ማሳየት ወይም አላግባብ ለመበልጸግ የሚረዳ ዕውቀት ማቀበል ነበር፡፡ ፖለቲከኛውን ለስልጣን፣ ነጋዴውን ወደሀብት በሌላም የኑሮ ዘርፍ ለተሰለፈው ለሥራው አስፈላጊውን ነገር ብቻ ይሰጡ ነበር፡፡

ይህ ነገርን ሁሉ ለግል ጥቀም ማበጃጀት ለዓለማችን ስልጣኔ እንደምሶሶ የሚቆጠሩት ቀደምት ፈላስፎች  (ሶቅራጠስ፣ ፕላቶና አሪስጣጣሊስ) በአጽንኦት የተቃወሙት ዐሳብ ነው፡፡ ትምህርት መታሰብ ያለበት ከጥቅም ባሻገር ነው፤ ከፍ ያሉ በሰውነት (ሰው በመሆን) በሚገኙ የስነምግባር ሕግጋትን በማስቀደም ነው፡፡ በተለይ ትልቁ የአውሮጳ መምህር ሶቅራጠስ ሰው እያንዳንዱን አጋጣሚ ለመመዝበር (to exploit) ወደወጭ ከማየቱ በፊት ‘ራስን ማወቅ’ን ፣ ወደውስጥ ማየትን ማስቀደም እንዳለበት አስተምሯል፡፡ ከእርሱ በወጉ የተማረው ፕላቶ ደግሞ ጉዳዩን አስፋፍቶ አስተምሯል፡፡ ይህ የትምህርት መሰረታዊ የአቅጣጫ ለውጥ በዘመናችን በምዕራባውያን መሪነት ዓለማችን ለደረሰችበት ቁሳዊም ሆነ ሌሎች ከፍታዎች እንደ መሰረትነት አገልግሏል፡፡የሶፊስቶችን ህጸጽ በቅጡ የተረዳው  ጀርመናዊ ባለቅኔ  “ዕውቀት ለአንዱ ለሁልጊዜ የሚያከብራት ወደላይ ወደአርያም የምትመራው ሰማያዊት ነብይት ናት፡፡ ለሌላው ግን በወተትና በቅቤ የምታገለግለው አንድ ወፍራም ላም ናት” ሲል የተናገረው ምነኛ! ድንቅ ነው፡፡

በጣልያን ጊዜ

የሀገራችንን የኋላ ታሪክ ስንፈትሽ ከላይ ካነሰነው ዐሳብ ጋር መሳ ለመሳ የሚጠቀስ ታሪክ እናገኛለን፡፡ያ ትዕቢተኛ ሞሶሎኒ ባነገበው ነፍጥ ተማምኖ ኢትዮጵን ለሁለተኛ ጊዜ ሲወር ኢትዮጵያውን በከፍተኛ ተጋድሎ መጀመሪያ የመንግስታቱን ህብረት (league of nations) “አንዱ አባል ሀገር በሌላው ላይ ጥቃት እና ወረራ አይፈፀምም” የሚለውን መርህ በማክበር በመከላከል በኋላም ጣሊያን ብዙ የጦር አውሮፕላኖች፣ የመርዝ ጋዝ በመጠቀም ህዝብን በዘር፣ በሀይማኖት የሚከፋፍል የፕሮፓጋንዳ ወረቀት እየበተነ ሲያሸንፍ ደግሞ እንደሌሎች ቅኝ ገዢዎች ተዝናንቶ እንዳይገዛ:- በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ ጫካዎች ዓለምን ባስደነቀ አርበኝነት ሀገራቸውን መጠበቃቸውን ታሪክ አይረሳውም፡፡

ይኼ ጦርነት አንድ የተወሰነ ግንባር ብቻ አልነበረውም፡፡ ወይም ደግሞ ሁለቱ ጦሮች በአንድ መስመር ገብተው አይዋጉም ነበር፡፡ በራስ ካሣ የሚመራው ጦር (ወደኋላ የራስ ስዩም እና የራስ ሙሉጌታ ጦር ተቀላቅለውታል) አቢ አዲ ላይ መሽጎ ወደ ተንቤን በማጥቃት በብዙ መስዋዕትነት የፋስሽትን ጦር ድል አድርጎ ነበር፡፡ እንደውም በጊዜው በስፍራው የነበረው የቼኮዝሎቫኪያ ተወላጁ አዶልፍ ፓርለሳክ እንደሚለው የአድዋ ድል ሊደገም ምንም አልቀረውም ነበር፡፡

ከተንቤን ተዋሳኝ በሆነችው ሰሆላ የሚኖሩ በሰላሙ ጊዜ በእርሻ፣ ሲገኝ ደግሞ በቀበሌያቸው የሚያልፍ ሲራራ ነጋዴ በመዝረፍ ከህግ ውጭ የሚኖሩ፣ በወቅቱ የትግራይ አስተዳዳሪ ለነበሩት ለራስ ስዩምም ሆነ ለደጅ አዝማች ኃይለ ሥላሴ ጉግሳ የማይገብሩ ሰዎች ነበሩ፡፡ እንዲሁ ወደ ጦር ሜዳ ሳይወርዱ እነርሱ በሌሉበት በተገኘው ድል ሊደሰቱ አልቻሉም፡፡ ምክንያታቸው ከመላው ኢትዮጵያ የመጣው ወዶ ገብ ወታደር ከጦር ሜዳ ባገኘው ምርኮና ሀብት ሲፎክር እና ሲሸልል እነርሱ ግን በአዋሳኝ ቀበሌ ተቀምጠው ባዶ እጃቸውን መቅረታቸው አሳዝኗቸው ነው፡፡ ይህ ሀዘን እና ቁጭት በመንደራቸው እንዲሰበሰቡ አስገደዳቸው፡፡ ይህ የመበልጸግ ሐሳባቸውን ለማሳካት ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር ጣልያንን ወግተው ከግዳዩ ሊካፈሉ ወሰኑ፡፡ የኋላ የኋላ ዘራፊነታቸውን የራስ ስዩም ጦር እንደማይዘነጋላቸው ሲረዱ የሚያዋጣው መልዕክተኞችን ወደራሶቹ መላክ እንደሆነ ተስማሙ፡፡ መልዕከተኞቹ በደረሱ ጊዜ በአካል በስፍራው የነበረው ካፒቴን ፓርለሳክ ‘የሀበሻ ጀብዱ’ በተሰኘው መጽሐፉ ያሰፈረውን ተጫነ ጆብሬ እንዲህ ሲል ተርጉሞታል፡፡

የሰሆላ ሰዎች ባለፈው የምርት ዘመን እምብዛም እንዳልቀናቸው፣ ለሁለት ሺህ እና ሦስት ሺህ የጣሊያን ጦር የሚበቃ ኃይል እንዳላቸው አሳስበው፤ የተከበሩት ጌታ ራስ ስዩም መንገሻ የጣልያኑን ጦር በጦራቸው አግደው ይዘው አላሳልፍም በማለታቸው ቢያንስ የጣሊያንን ወታደሮች ገድለው እንዳይዘርፉና ኑሯቸውን እንዳይደግፉ እንዳደረጋቸው፤ በዚህም ምክንያት ክፉኛ የተቸገሩ መሆናቸውን ገልጸው ከዚህ ጦርነት ምንም ጥቅም ሳያገኙ ባዶ እጃቸውን መቅረታቸውን አስረዱ፡፡ ቀጥለውም ራስ ስዩም መንገሻ ፈቃዳቸው ሆኖ አንድ ሦስት ሺ ያህል የጣልያን ጦር ቆርሰው ወደ ግዛታቸው ቢያሳልፉላቸው ውለታውን ከእግዚአብሔር ሁሉ እንደሚያገኙት ተናገሩ፡፡”
‘ቅኝ ግዛት ምንድን ነው?’፣ ‘የጣልያን ጦር እንዲህ በቀላሉ ተቆርሶ የሚሰጥ ነው?’፣ ‘ሐሳባቸው ከእነርሱ በኋላ በተነሳው ትውልድ ላይ ያሳደረው ተጽእኖ ምንድን ነው?’፣ ‘መንግስታችንስ ከእነዚህ ሕዝቦች ጋር ምን የሚጋራው ነገር አለ? የሚሉትን ጥያቄዎች ወደጎን ትተን የታሪኩን ሌላ ገጽ ስናሰተውል ሶፊስቶች  ትምህርትን እንደመዘበሩት የሰሆላ ሰዎችም  ጦርነቱን ለተመሳሳይ አላማ የማዋል ሀሳብ እንደነበራቸው እንረዳለን፡፡

ትላንት

ብዙውን የቅርብ ጊዜ ታሪካችንን ብንፈትሽ ብዙ ጉዳዮች ተጠምዝዘው ለግለሰቦች ወይም በቡድን በተደራጁ ወንበዴዎች ተዘርፈዋል፡፡   የዘውዳዊን ስርዓት አርሞ ወደፊት ያራምደናል የተባለለት አብዮት አቅጣጫውን የለወጠው በጥቅመኞች  ነው፡፡ ማንበብ እና መጻፍን ዋና ቁም ነገር አድርጎ የተነሳው የእድገት ህብረት ዘመቻም የጨነገፈው እንዲሁ የገበሬውን ልጆች ለመድፈር፣ ሀብት ንብረቱን ለመዝረፍ ባላፈሩ ሰዎች ነው፡፡ ሶሻሊዝምም በጥራዝ ነጠቅ ምሁራን እንዳይሆን እንዳይሆን መደረጉ የሚገባን  ሁሉም አንድ ርዕዮት እየተከተሉ ነገር ግን  የአልቤኒያ ፣ የቬትናም እያሉ በየጎጥ ተከፋፍለው  መራኮታቸውን ከታሪክ ስናነብ  ነው፡፡በእርስ በርስ ጦርነት ልጆቻቸውን ያጡ የትግራይ እናቶችን “በጨው ደንደስ በርበሬ ተወደስ” እንጉርጉሮ ስናደምጥ ደግሞ አሁንም እዚያው እንዳለን እንረዳለን፡፡ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነትን እንደ ጥሩ አጋጣሚ  ተጠቅመው የከበሩ ድርጅቶችም የትየለሌ ናቸው፡፡የቅንጅት መሪዎች በወህኒ ሳሉ የቅንጅትን ምኞት እና ተስፋ የማይጋሩ ሰዎች ስሙን እና ጣቷን ለመዝረፍ ያደረጉት ትግል የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡

ዛሬ

ዛሬ ዛሬ ሀገራችን ከኋላ ታሪካችን በገዘፈ መልኩ  ለቅርጫ እንደቀረበ ሠንጋ በሆዳሞች ተከባ ትገኛለች፡፡ ትምህርት ከአጸደ ህጻናት እስከ ከፍተኛ ተቋማት ፣ ከገዢ እሰከ ተቃዋሚ ፓርቲ ፣ ህክምና፣ የግል ጋዜጣ ፣ ኤፍ ኤም ራዲዮ ፣ የመንግስት ሚዲያ ፣  ከሀይማኖት ሰባኪነት እሰከ አባትነት ፣ ከግል ድርጀቶች  እሰከ መንግስት ሥራ፣ ተዋናይ ፣ አዝማሪ ፣ ከሱቅ በደረቴ እስከ አስመጪና ላኪ … መዝባሪና የምዝበራ  መድረክ ያልሆነ ምን አለ? ለምዝበራ የተጋለጠውን ከመዘርዘር ያልተጋለጠውን መናገር ይቀላል፡፡በማኀበራዊ ህይወት ጓደኝነት እንኳን ስንት ያወጣል እየተባለ እየተገመተ ነው የሚኖረው፡፡(በሌላ ጦማር እንመለስበታለን) የታሪክ አጋጣሚዎችን ሁሉ እንደ ወፍራም የወተት ላም የማየት  አባዜ ትልቅ ትንሹን የሚያመሳስል ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ትውልድ ከፍ ያለ ዐሳብ እንዳይኖረው ዙሪያውን ጋርደውት ይገኛሉ፡፡

የሀገራችን መጻኢ ጊዜ ያገባናል የምንል ሰዎች ይህን ሰፊ ችግር ለማስወገድ ግልጽ ውይይት ማድረግ ይገባናል፡፡ወይይት ለመጀመር አንዱ መነሻ ደግሞ የምንነጋገርበት ንድፈ ዐሳብን የሚወክል ቃል ከማግኘት ይጀምራል፡፡በቋንቋችን  Opportunismን የሚተካ አቻ   ትርጉም አለመኖሩ ደግሞ ጉዳዩን የበለጠ ያከብደዋል፡፡በመጠኑ የቀረበ ትርጉም ያገኘኹት  አዳም ረታ በ ‘እቴሜቴ የሎሚ ሽታ’ በተሰኘው የአጭር ልብወለድ መድብል ያሰፈረው ነው፡፡

አዳም በማራኪ ብዕሩ እንዲህ ይላል፡፡

መዘንደድ ማለት ዘንዶ መሆን ማለት ነው፡፡ በልቶ ጠጥቶ የሚተኛ፡፡ ዝንደዳ ጭራሽ አገርን መርሳት፣ ለአገር የሚችሉትን አለማድረግ ነገር ግን የአገሪቷን ምግብ እያሳደዱ በመብላት ብቻ ዜግነትን ለማሳየት መጣር ማለት ነው፡፡ የምናደርገው ነገር ቢኖር የልኳንዳ ስጋ በርካሽ ገዝተን እምብርታችን እስኪፈርስ በልተን በየአልጋችን መውደቅ ነው፤ ጠላት መጥቶ በር አንኳክቶ አገራችንን ቢወስድም አንሰማም፡ ይህንንዝንደዳእለዋለው፡፡

እስቲ ምን ይመስላችኋል? በዚህ መግባባት ላይ ከደረስን ወደመፍትሔው  ለማምራት ዘንዶውን በጉልህ ለመለየት አተያይ እናዋጣለን፡፡ ዝንደዳ ፣ መዘንደድ ፣ …እንዴት አያችኋት?

About abel wabella

Mechanical Engineer, Aircraft Technician, Blogger , Independent Researcher and Criti­cal Conflict Agent …abelpoly

Posted on June 19, 2012, in Sociopolitics. Bookmark the permalink. Leave a comment.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: