“የቃሊቲው መንግስት” እኔ እንዳነበብኩት

ባህር ማዶ ካለች አንዲት  ወዳጄ ጋር ስለአንዳንድ  ጉዳዮች (ስለሀገር ፣ ስለቤተክርስቲያን ፣ ስለወገን ወዘተ…) በምናወራበት የአዘቦት ወጋችን መሐል የፓስታ ሳጥን ቁጥሬን እንድነገራት ጠየቀችኝ፡፡ በሆዴ ‘ለዲያስፖራዎች የወገብ እና የጫማ ቁጥርን መስጠት ፋሽን ካለፈበት ሰንብቷል፤ ለምን ጠየቀችኝ? ያውም ጶስጣዬን ሆሆ!!’ እያልኩኝ አቀበልኳት፡፡ ከቀናት በኃላ ሳጥኔን ከፍቼ አዲስ የመጣ ነገር እንዳለ እንዳረጋግጥ ነገረችኝ፡፡ በፖስታዬ ምንም ነገር አለማግኘቴን ነግሬያት ጉዳዩን በዚሁ ልቋጨው ስንደረደር የኖረችበት የዲያስፖራ ዴሞክራሲያዊ ባህል ፣ መብትን የመጠየቅ ልማድ ግድ ብሏት በዚያው ካለው ከአገልግሎት ሰጪ ተቋም የመልዕክቱን ልዩ ቁጥር (tracking number) ጠይቃ  ሰጠችኝና በአንድ የፖስታ ቤቱ ሰራተኛ ርዳታ ዳጎስ ያለው መጽሐፍ በእጄ ገባ፡፡ እኔም በከፊል ለኪሴ ሳስቼ በከፊል ደግሞ ለሙስናው መስፋፋት የግሌን አስተዋጽኦ ላለማበርከት ብዬ  እርዳታ   የለገሱኝን ሰው  በእግዚአብሔር ይስጥልኝ ተሰናብቼ ከታላቅ የንባብ ዐራራ ጋር ወደጎጆዬ አመራሁ፡፡

ርዕስ – የቃሊቲው መንግስት

 ዝግጅት ፣ጥንቅር ፣ ጸሐፊ  – ሲሳይ አጌና

 የገጽ ብዛት – 443

 አሳታሚ – Netsanet publishing and distributing agency

 ዋጋውና  እና የት እንደታተመ አይገልጽም

ከምርጫ 97 በኃላ የቅንጅት መሪዎች ፣ ጋዜጠኞች ፣ የማኀበረሰባዊ እና ሙያዊ ማኀበራት ሰራተኞች እንዲሁም ከአርባ ሺህ በላይ ዜጎች በጅምላ መታሰራቸው ይታወቃል፡፡ በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያን የሚጎበኙ የውጭ መንግስታት  እና አለምአቀፍ ተቋማት ተወካዮች አራት ኪሎ ከደረሱ በኃላ ወደቃሊቲ መውረድን አስለመዱ፡፡ በዚህም ምክንያት በሸገር ሁለት መንግስታት እንዳሉ ይተረት ጀመር፤ የአቶ መለስ ዜናዊው ‘የአራት ኪሎው መንግስት’ እና በቅንጅት መሪዎች በቡድን የሚመራው ‘የቃሊቲው መንግስት’፡፡ወደኃላ እንደምናነሳው የመጽሐፉ ይዘት ስለዚህ ቃሊቲ ስለወረደው መንግስት ስለሚያትት ጸሐፊው ጥሩ ርዕስን መርጧል፡፡የሽፋን ስዕሉ ደግሞ የቤተ መንግስቱን የቃሊቲ ወህኒ ቤት አጥርና ሚያዝያ 30 1997 ዓ.ም. መስቀል አዳባባይን ያጥለቀለቀው ፣ ከሰው መሀል መርጦ ያነገሳቸውን ህዝብ ማስፈሩ ደግሞ እጅግ ገላጭ ሆኖ አግኝቼዋለው፡፡

የመጽሐፉ ይዘት መንግስት እሰረኞቹን መያዝ ከተጀመረበት ከጥቅምት 22 1998 ዓ.ም. ጀምሮ የመሰረተ ዐሳቡ ክቡድነት ያህል ለሀገሪቱ መጻዒ ጊዜ አንዳች ነገር ባላበረከተ  ይቅርታ ከእስር  እስከተፈቱበት ሐምሌ 13 1999 ዓ.ም. ድረስ ጥቃቅን ነገሮች ሳይቀር እየዘረዘረ ያስቃኘናል፡፡ጥቅምት 22 ከምሽቱ ሶስት ሰዓት አከባቢ ይጀምርና ራሱ በተባራሪ  የሚያገኛቸውን መረጃዎች ሲጠቃቅስ ይቆይና በቁጥጥር ስር ሲውል ደግሞ  ወደ ወህኒ ቤት ይዞን ወርዶ በትዝታዎቹ ተመስጦ ውስጥ ይከተናል፡፡ በተደደጋጋሚ በመታሰሩ፣ ብዙ ጊዜ ቃሉን ስለሰጠና በሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶች በሸገር ያሉ ወህኒ ቤቶችን ከነመንገዶቻቸውን ፣ ከነመርማሪዎቻቸው እና ዘቦቻቸው ጥንቅቆ ያውቃቸዋል፡፡ከቃሊቲ በተጨማሪ እንደ ዓለም በቃኝ እና ማዕከላዊ ያሉ ዝነኛ እስር ቤቶችን በነዋሪነት ስለሚያውቃቸው እያንዳንዷን ኮሽታ በጥንቃቄ እንዲያስተውል ረድተውታል፡፡ስለወንጀል ምርመራ ቆይታው ካሰፈረውና ፈገግ ያሰኘኝን ተረክ ላቀብላችኹ፡፡

       …አዲስ እስረኛ በገባ የመጀመሪያው ቅዳሜ ምሽት 2 ሠዓት ከእራት በኋላ አንድ ዘፈን ፣ አንድ ገጠመኝ ፣ አንድ ቀልድ ማቅረብ አለበት ፡፡ ቀልድ እና ገጠመኝ መናገር ግዴታ አይደለም፡፡ሆኖም መዝፈን ግን ለማንም የማይቀር ነው ፡፡እንኳን  ሕዝብ በተሰበሰበበት ሊዘፍን ለብቻው እንኳን ሆኖ አንጎራጉሮ የማያውቅ የእኔ አይነቱ ጋግርታም ግን ሌላ አማራጭ ይሰጠዋል፡፡ይህም ኦሪጅናል ካሴት ገዝቶ ለቤቱ ማጫወት ነው፡፡ኦርጂናል ካሴት ግዛ የሚባለው እና ግዴታ የሚጥልበት እስረኛ ቴፕ በሌለበት ክፍል ወስጥ ኦሪጅናል ካሴቱ ተገዝቶ ምን ላይ እንደሚጫወት ግራ እየተጋባ 13ቱን ብር ሲከፍል ፣ ኦሪጅናሉ ካሴትም ቴፑም በአንድነት ከዚያው ከእስረኛው መሐል ብቅ ይላል፤ ኦሪጅናል ካሴት የሚባለው ከእሰረኛው መሐል  ጥሩ ድምጽ ያለው ስለአዲሱ እስረኛ ሆኖ (በእርሱ ተገብቶ)  የሚያንቆረቁረው ዜማ ነው ፤  ከ13ቱ ብር ካልተሳሳትኩ ሦስቱ ብር ለዘፋኙ ይሰጠውና ቀሪው 10 ብር ለቤቱ ገቢ ይሆናል፡፡…

ወንጀል ምርመራ ፣ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ ፣ ማዕከላዊ  እያለ ወደዋናው መዲና ቃሊቲ ይወስደናል፡፡በዚያ ደግሞ ያስገረሙት ሁነቶችና ተዋንያንን ምስል ከሳች በሆነ መልክ ያስቃኘናል፡፡ “መነኩሴው” ፣ ሽማግሌዎቹና ወፈፌዎቹ ፣ደቦቃና አስመራ ድርደር (በወህኒ ቤቶች የቦታ ጥበት ምክንያት የተፈጠሩ የመኝታ ዘይቤዎች)… ይነግረንና ወደጠነከረው ርዕሰ ጉዳይ የክስ ቻርጅ ያመራል፡፡ ስለ ዳኞች እና ዓቃቤ ሕግ የኋላ ታሪክ  በማስቀደም እያንዳንዷን የፍርድ ቤት ውሎ በዝርዘር ይተነትናል፡፡

የየዕለቱ ፍርድ ቤት ውሎችን ሲጀምር ከፍርድ ሂደቱ ተዋንያን ንግግር መካከል  የሚመዛት እምቅ ኃይለ ቃል ለመጽሐፉ ውበት ለአንባቢያን ደግሞ ወደችሎቱ የምትወስድ ምትሀት ናት፡፡ “ምን እምነት ክህደት ትጠይቁናላችኹ ጠ/ሚ/ሩ ሞት ፈርደውብን የለ! የጠ/ሚ/ሩን ውሳኔ በፖስታ አድርጋችኹ ቃሊቲ ላኩልን ፣ አታመላልሱን” የሚለውን የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን ንግግር ስናነብ ፍርድ ቤቱ ምን ያህል ከደረጃ በታች ይጫወት እንደ ነበር እንረዳለን፡፡የሲቪክ ደርጅት አባላት የሆኑት ዳንኤል በቀለ /ከአክሽን ኤይድ/ ፣ ነጻነት ደምሴ /ከ ኦርጋናይዜሽን ፎር ሶሻል ጀስቲስ ኢን ኢትዮጵያ/ እና ካሣሁን ከበደ / የአዲስ አበባ መምሀራን ማኀበር ሊቀመንበር / በቀር ሌሎቹ ተከሳሾች በዚህ ፍርድ ቤት እምነት ስለሌለን  አንከራከርም የሚል አቋም በመያዛቸው መድረኩን ዓቃቤ ህግ ብቻ የሚናገርበት አድርጎታል፡፡

ዓቃቤ ህግ መጀመሪያ ካቀረበው 25 ገጽ የክስ ቻርጅ በተጨማሪ  24 የቪዲዮ ካሴቶች ፣ በጣት የሚቆጠሩ የድምጽ ማሰረጃዎችና ተጨማሪ የሰነድ ማሰረጃዎች በአይነት 94 በገጽ ብዛት 900 ሲሆን ይህም ጸሐፊው ጠ/ሚ/ሩ በቶን የሚመዘኑ መረጃዎች እንዳላቸው የተናገሩት ውሸት መሆኑንና ግራም እንኳን የሚሞላ እንዳልሆነ በመግለጽ አንባቢን እስኪደክመው በመዘረዝር እንዲያስረዳ ረድቶታል፡፡ (ዓቃቤ ከዚህ ሁሉ እንቶ ፈንቶ ማስረጃ በኃላ 382 ምሰክር መጥራቱ ደግሞ የጠ/ሚ/ሩ በቶን የሚመዘን ማስረጃ አለን ዲስኩር በአየር ላይ እንዳይቀር መጨነቁን ያሳብቅበታል፡፡) የፀሐፊው ጥቂት  ማብራሪያዎች ጠንካራ አለመሆን  እርሱንም እንደዐቃቤ ህጉ አሰስ ገሠሡን የሚጎትት አስመስሎታል፡፡ እዚህ ጋር የህግ ባለሙያን ዕውቀት የሚጠይቁ ጉዳዮች ላይ የወሰደው ጥንቃቄን ሳላደንቅ አላለፍም፡፡ነገር ግን ከአቀረባቸው ተደጋጋሚ ማስረጃዎች ይልቅ ለማሳያ አንድ አንድ እየጠቀሰ ቢያልፍ ትዕግስት የለሽ አንባቢን መጽሐፉን ሳይጨርስ አንዳያስቀምጠው ይረዳው ነበር፡፡ከዚህ በተጨማሪም ሰነዶቹን በሙሉ  ወጥ በሆነ መንገድ አባሪ ላይ ቢያካትታቸው ኖሮ የፈለገ እያመሳከረ ፣ ያልወደደ ደግሞ ሳይጎረብጠው ባልተቆራረጠ የንባብ ጡዘት እንዲያነብ እድል ይሰጥ ነበር፡፡

ከፍርድ ሂደቱ በተጨማሪ ጋዜጠኛው የዳሠሳቸው የመጽሐፉን ዋጋ ከፍ የሚያደርጉት  የአጣሪ ኮሚሽኑ እንቅስቃሴና ስለተቀለደበት ይቅርታ በማስረጃ ያቀረባቸው ትንታኔዎች ናቸው፡፡በተለይ አጣሪ ኮሚሽኑ አባላት በምርመራው ያገኙትን ውጤት ለማዳን ሀገርን ጥሎ እስከመሰደድ መድረሳቸው አንጀትን ያኝካል፡፡ለኮሚሽኑ የተሰጠው ሀላፊነት ቀጭን ነበር ‘መንግስት በሰኔ 1 1997 እና በጥቅምት 22 1998 ዓ.ም. የወሰደው እርምጃ ተመጣጣኝ  ነበር / አይደለም’  የሚል ፡፡ መንግስት  ውጤት ለመቀየር የአጣሪ ኮሚሽኑ አባላት ላይ ጫና በማሳደሩ ምክንያት በቪዲዮ የተደገፈ ማስረጃ ይዘው መሰደዳቸውን የምናገኘው ከሲሳይ አጌና መጽሐፍ ነው፡፡ ኢትዮጵያ “ሁላችንም የጠበቅነው ከ10 እስከ 16ሺ ነበር የሞተው ግን 1 ሺህ አይሞላም ስለዚህ ተመጣጣኝ ነው ፡፡”  ያሉት የእነ ሼህ ኤልያስ ሬድማን ብቻ ሳይሆን ለእውነት መስዋዕትነት የከፈሉት የነአቶ ፍሬህይወት ሳሙኤል ፣ የአቶ ወ/ሚካኤል መሸሻ  ሀገር መሆኗን ለትውልድ ጽፎ ማስቀመረትን የመሰለ ታላቅ ገድል የለም፡፡በተለመደው ድፈረት በረከት ስምኦን ስለተሰደዱት የአጣሪ ኮሚሽኑ አባላት ሲጠየቅ “ለጥገኝነት ማግኛ የሚደረግ ሙከራ ነው” ማለቱን ተከትሎ   አቶ ወ/ሚካኤል መሸሻ  የሰጡት መልስ የእውነት ወዳጆችን ያጽናናል፡፡ “እኛ የየትኛውም ፓርቲ አባል አይደለንም እንዲያውም የመንግስት ሹመኞች ነን… አሁን እድሜዬ 55 ደርሷል ፤ በምክትል  ሚኒስቴር ደረጃ ደሞዝ አገኛለው ፤ መንግስት መኪና መድቦልኛል ፤ በዚህ እድሜዬ ከዚህ በላይ ምን እፈልጋለው? “

በቅርቡ አዲስ አበባ ላይ በተደረገው ዎርልድ ኢኮኖሚክ ፎረም ኦን አፈሪካ ላይ የደሞክራሲ መርሆች በራሳቸው የሚቆሙ መሆናቸውን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የምር ግን ለነዚህ መርሆች ታማኝ አለመሆናቸውን እንዲያውም በደረሱበት ላይደርሱ መሐላ ከፈጸሙ እንደሰነበቱ የምነረዳው  የፍትሕ ስርዓቱ ላይ የፈጸሙትን ማፈራረስ ይህ መጽሀፍ  አጋልጦ ሲያሳየን ነው፡፡

በመጨረሻም በመጽሐፉ የኋላ ሽፋን አርቲስት ታማኝ በየነ ፣ጋዜጠኛ ደረጀ ደስታ እና ጋዜጠኛ  አበበ ገላው አጭር አስተያታቸውን አስፍረዋል፡፡ በአንድ አይነት የቦለቲካ ሜዳ የሚጫወቱ ሰዎችን አስተያየት ከመደርደር ይልቅ እንደኔ እንደኔ  ጉዳያዊ እውቀት(subject authority)  ያላቸውን  ቢያካትት  መልካም ነበር፡፡  የታሪክ ምሁራን ፣ የህግ ባለሙያዎች ወይም ከሂደቱ ተሳታፊ የፓሊተካ መሪዎች አንዳቸውን እንደምሰክርነት ቢያቀርብ የተሻለ ይሆን ነበር እላለው፡፡

በቅርቡ ታትሞ ካነበብናቸውና በዚህ የቅርብ ጊዜ ታሪክ  ዙሪያ የተጻፉ ሽያጭን ብቻ ማዕከል ካደረጉት አንስቶ  ጲላጦሳዊ ከደሙ ንጹህ ነኝ የምትል የእጅ እድፍ ድረስ ያሉትን  መጽሐፍት ስንናጤን የሲሳይ አጌና ይበል የሚያሰኝና ትውልድ ለታሪክ እና ለምርምር ሲያጣቅሰው የሚኖር  ነው፡፡  በወቅቱ ዋና ተዋናይ የነበሩ የፓለቲካ መሪዎች አቶ በረከት ስምኦንን ጨምሮ ከያሉበት የአስተሳሰብ ምህዳር የተቃኘ መጽሐፍ አስቃኘተውናል፡፡አንድ የታሪክ ተማሪ የሆነ ወዳጄ “ወቅቱን ለታሪክ መዝግቦ ለማስቀረት የተሻለ ሚዛናዊ ትርክት ያካፍሉናል ብዬ የምጠብቀው ያን የህሊና(የዐሳብ) እስረኛ እስክንድር ነጋና ሲሳይ አጌና ነው” ሲል የነገረኝ ትክክል መሆኑን የተገነዘብኩት የዚህን መጽሐፍ የመጨረሻ ገጾች በስስት እየቆጠርኩኝ ሳነብ ነው፡፡

About abel wabella

Mechanical Engineer, Aircraft Technician, Blogger , Independent Researcher and Criti­cal Conflict Agent …abelpoly

Posted on June 9, 2012, in የመጽሃፍ ቅኝት. Bookmark the permalink. 3 Comments.

  1. well reviewed, Abe!

  2. The author in his narratives tried, with intent or out of a ‘brave stance to be a truth teller’, to slander and defame the politicians, who at the time were being tried for treason, forgetting that place is the matter. The personality traits and character of individuals differs from place to place. It is true that when people live together, they tend to show their real personality. The author seems to forget that these people whom he vehemently accuses of being divided, shameful and unbecoming are in prison. Whatever a person who is in prison does and says could be at times deluding and it may not be a real personality. Given the fact that these people were waiting for their life time sentence or some kind of consequences, presumably they would get nuts at things. When they saw that they failed because of internal and external causes, they would get nutty. Even if what was narrated was true and provided that the people should know who is who in the oppositions camp, the author who is also a journalist did not calculate the political peril it (the book) would incur on the people. If it would reach to the wider population, I presume, it would have a devastating effect in mounting the people’s suspicion on the already existed oppositions and the opposition to come.

  1. Pingback: በዚህ ሳምንት(ከ June 2-9) የኢትዮጵያ ብሎጎች ምን ጻፉ? | Endalk's Blog

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: