በአገሩ ጉዳይ የሚያገባው ትውልድ ፍለጋ

‹‹የአሁን እኛ?››

በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ምሽቶችን የሚያደምቁ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጫወታዎን የሚታደሙ፣ ከዚያም አልፈው ጎራ ለይተው የሚሰዳደቡና የሚወቃቀሱ፣ የባሰ ዕለት ደግሞ በትልልቅ ጫወታዎች መልክ ጎራ ለይተው የሚቧቀሱ ወጣቶችን ማየት የከረመ አገራዊ ትዕይንት ሆኗል፡፡ ቅጥ ባጣ የፈረንጅ እግር ኳስ ፍቅር፣ ‹‹ከብርሃን ፍጥነት›› በላይ እየተስፋፉ ባሉ ‹‹የሱስ መሰረተ ልማቶች›› ውስጥ በመጥፋትና በቸልተኝነት የሚታማው ይህ ትውልድ ከላይ በተጠቀሱ ‹‹አደንዛዥ›› ጉዳዮች ተጠልፎ ካልወደቀም በጥልቅ ‹‹ራስን የማዳን›› ስሜት በመዋጥ አገሩን የረሳ፣ ፖለቲካ የማይገደው፣ ምርጫ የማያሳስበው ትውልድ ነው ተብሎ ይታማል፤ አለፍ ሲልም ደግሞ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስደት ወደተገኘው አገር ለመጓዝ ልቡ የቆመ፣ በአገሩ ተስፋ የቆረጠ፣ በየትኛውም አጋጣሚ አገር ጥሎ ለመሄድ ጓዙን ጠቅልሎ የተሰናዳ ወጣት እንዴት አገርን ይረከባል? ሊረከብስ ቢዘጋጅ ከማን እና እንዴት ይረከባል? ይህችን አገር ከእኛ የሚወስዳት ማነው የሚሉ ‹‹አባቶችም›› መኖር ሌላው ነባራዊ ሐቅ ነው፡፡ 

ለዚህ ዓይነቱን ትውልድ መፈጠር (ዓይነቱ ይሄ አይደለም ብለው የሚከራከሩ ባይጠፉም) ኃላፊነት የማይወስዱበት ‹‹የጎረቤት ልጅ›› ይመስል እዚህ ለመድረሱ ኃላፊነትን አንወስድም ዓይነት አንድምታ ያላቸውን ሐሳቦች መስማት አዲስ ነገር አይደለም፡፡ እንደውም አልፈው፣ ተርፈው ‹‹በእኛ ዘመን ቀረ!››ን ልክ እንደ አንድ የታሪክ ኩራት መገለጫ ያደረጉና ትውልዳዊ ኃላፊነታቸውን የረሱ ፖለቲከኞች ስለምክንያቱ ከማውራት ይልቅ ውጤቱን መውቀስ ይቀናቸዋል፡፡

 

ለምን? ለምን? ለምን?

‹ዛሬ ያለው እውነታ ለምን እንዲህ ሆነ? ትውልዱ ተግዳሮቶቹ ምንድን ናቸው? እውነትስ ጉዳዩ ‹‹የእሳት ልጅ አመድ›› ብቻ ተብሎ የሚታለፍ ነውን?› የሚሉ ጥያቄዎችን ለማንሳት የደፈረ፣ ለመመለስ የሞከረ ‹‹የእሳትም ሆነ የአመድ ትውልድ›› ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ በመሰረቱ ትውልዶች የሚያልፉበት መንገድ እና ሁኔታ ከዘመን ዘመን በብዙ የተለያዩ መንስኤዎችና ምክንያቶች የተሞላ በመሆኑ የእያንዳንዱ ትውልድ መንገድ ከሌላው በእጅጉ ይለያል፡፡ ሆኖም ሙሉ ለሙሉ ለመወራረስ ባንችል እንኳን የቀደመው ትውልድ በቀደደው መንገድ እያሰፉና እያጠበቡ፣ አቋራጭና ቅርንጫፍ እየጨመሩ መጓዝ የተከታይ ትውልድ ኃላፊነት ሲሆን መንገድን ማሳየትና መምራት ደግሞ የቀደመው ሥራ ነው፡፡ በአገራችን ነባራዊ የፖለቲካ፣ ማሕበራዊና ዓለምአቀፋዊ ሁኔታ ውስጥ የተደናበረ፣ መንገድ የጠፋው መስሎ የሚታየው ወጣት ራሱ በቀየሰው አዲስ መንገድ ሳይሆን፥ ባሳዩት ጎዳና ላይ የሚጓዝ መሆኑን መካድ ኃላፊነትን ለመውሰድ ያለመፈለግ ስሜት ካልሆነ ሌላ ትርጉም ሊሰጠው አይችልም፡፡

 

የከሰረው ትውልድና የተቆራረጠው የትወልድ ትይይዝ

አንድ ትውልድ በዕድልም ሆነ በስርዓት አገርን ተረክቦ ከማስተዳደር (ከመግዛት)፣ ለአገር ከመጋደል፣ ከመወቃቀስና ለዓመታት ከመኮራረፍ በተጨማሪ የሚጠበቅበት ትልቁ የቤት ሥራ ተተኪና ያገባኛል የሚል ትውልድ መፍጠር ነበር፡፡ የቀድሞው (ከሠላሳ ዓመት በላይ በፖለቲካው ተሳታፊ የነበሩት) ትውልድ ዘመን ሰዎች ከከሰሩባቸው የተለያዩ ጉዳዮች በተጨማሪ ትልቁ ኪሳራ ‹‹የሚያገባው ትውልድን›› መፍጠር ያለመቻላቸው ጉዳይ ነው፡፡ በዘንድሮዋ ኢትዮጵያ ገዢውም ሆነ ተቃዋሚው የአንድ ትውልድ ቡድን ለስልጣን ቁምነገር የሚሰጡትን ትኩረት ያህል እነርሱ በቅርቡ ትተዋት ለሚሄዷት ኢትዮጵያ ተረካቢ ወጣት አንድም ቀን ተጨንቀው ሲያወሱ፣ ፕሮግራም ሲቀርፁና አዲስ መሪ ሲያበቁ አይስተዋሉም፡፡

አልፎ፣ አልፎ በሰሞንኛ ፋሽን መተካካት እና የወጣቶች ተሳትፎ ተብሎ ሲጠቀስ ወይ ስለ ስልጣን መረካከብ፣ ወይም ደግሞ የወጣት ፓርቲ አባላቶችን ቁጥር ስለማሳደግ ሆኖ ጉዳዩ ባጭሩ ይቀጫል፡፡ ትውልዱ ከታላላቅ ኪሳራዎቹ ‹‹ከቀይ ሽብር››፣ ‹‹ከኩርፊያው››፣ ‹‹ከደረቅ የማይለወጥ›› አቋም ባለቤትነቱ በተጨማሪ ‹እራሴ የጀመርኩትን የማስቀጥለው እኔ ነኝ› በሚል አቋሙ ሌላ ኪሳራ ላይ ወድቋል፡፡ ላለፉት አምስት አሥርት ዓመታት የአገሪቷ ፈላጭ ቆራጭ ትውልድ ከላይ በተጠቀሱት አገራዊ ቁስሎች እንጂ የትውልድ ቅብብሎሹን በመበጣጠሱ ብዙም ሲተች አይስተዋልም፡፡

 

‹‹ባለስልጣን›› ወይስ ‹‹ባለቤት››?

በገዢው ፓርቲ ጎራ ያሉ አካላት የአገር ባለቤትነት ጥያቄን ወደስልጣን ጥያቄ ለማሻገር በመካከሉ ለሰኮንዶች ማሰብ እንኳን አይጠይቃቸውም፡፡ ‹አገሬን ያለ ወንበሩን ያለ› እስኪመስል ድረስ ስለመተካካትም ቢሆን ሲወራ ስለስልጣን እንጂ ስለአገር ተነስቶ አያውቅም፡፡ የተቃዋሚ ጎራም በበኩሉ የወጣቱን የአገር ባለቤትነት ጥያቄ ‹‹እኛስ መች ገና ባለቤት ሆንን?›› በሚል ስሜት ችላ ሲለው ይታያል፡፡ ከአገሪቱ የሕዝብ ቁጥር አንፃር ከፍተኛ ድርሻ ያለውን ወጣት ገለል ያደረገ ስርዓት ዘርግቶ ‹‹መተካካት›› በሚል መሰላል ግለሰቦችን ወደላይ ማውጣት ‹‹ነባሩን ፊት በአዲስ›› ከመቀየር ውጪ የኢትዮጵያን ወጣት ምን ገዶኝ ከሚል ስሜት ለማላቀቅ ምንም ዓይነት አስተዋጽዖ አያደርግም፡፡

በመተካካት ‹‹የተስፋ›› መሰላሉ ላይ ይወጡ ዘንድ፣ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ጀምሮ በአባልነት እያሰለፈ ያለው ገዢው ፓርቲ የመንግስታዊ ሚናውን ተጠቅሞ የተሻለ አቅም ያላቸውን ወጣቶች ‹የእኔ ናቸው› በሚል ፈሊጥ አገሪቷ ለሚቀጥሉት 40 ዓመታት ‹‹ያለምንም ችግር›› በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ጎዳና እንደምትጓዝ በእርግጠኝነት ይናገራል፡፡ ስልጣን በአንድ አገር መዋቅር ውስጥ የሚገኝ የመዋቅሩ አስተዳደራዊ አካል አንድ ቅርጽ ብቻ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ግን መሰረታዊ ስርዓቶችን አስተካክሎ፣ ያለፖለቲካዊ አመለካከት ልዩነት ለሁሉም ወጣቶች ‹‹አገራዊ ቦታ›› የማይሰጥ ስርዓት በየትኛውም አቅጣጫ ቢሆን የጠፋውን የአገር ባለቤትነት ስሜት መፍጠር ይሣነዋል፡፡ የሁሉም የሆነ ስርዓት መፍጠር ደግሞ የአገር ባለቤትነት ጥያቄን ከስልጣን ባለቤትነት ጥያቄ ለይቶ ማየት ይጠይቃል፡፡ የአገር ባለቤት መሆን የስልጣን ባለቤት መሆን ብቻ አይደለምና! ይህንን ለመፍጠር ያልቻለ ባለስልጣን፣ ትውልድ እና የአገር መሪ የአገሪቷ ባለቤትነት ስሜት ላጡ ወጣቶች መፈጠር መውቀስም ሆነ መፋዘዝን ለመተቸት የሞራል የበላይነትን እንደሚያጣ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

 

የእኛ (የወጣቶች) ተግዳሮቶች

ይሄ ትውልድ አንድን ትውልድ በአንፃራዊ መልኩ በተሻለ ሁኔታ የሚገነቡ መሰረታዊ ግብአቶችን ያጣ ትውልድ ነው፡፡ ጠንካራ እና አቅምን የሚገነባ፣ ንባብን እና ማወቅን የሚያበረታታ ስርዓተ-ትምህርት የተነፈገው፣ ዓለም ወደፊት በምትገሰግስበት በዚህ ፈጣን ዘመን የሚያወራበት፣ የሚነጋገርበት ‹‹ቦታ›› ያጣ፣ መረጃ የሚሰጡ፣ ዕውቀትን የሚያጎለብቱ፣ የሚሰጡና የሚናገሩለት የሚዲያ ተቋማት የሌሉት (በስህተት ቢያገኝ እንኳን በቀላሉ የሚነጥቁት)፣ ዘመኑና አካባቢው ያልተገጣጠሙለት ትውልድ ነው፡፡

አንድን ትውልድ ለመቅረጽ ወሳኝ ተፅዕኖ ያላቸው ሚዲያ፣ ስርዓተ-ትምህርት፣ ስነጥበብ እና ወዘተ በዚህ ዘመን ‹‹ባዶ›› በሆኑበት ሁኔታ ታግለው ‹‹የይገባኛልን ስሜት›› ወደራሳቸው የሚያመጡ፣ የተነጠቁትን (ያልተሰጣቸውን) አገራዊነት የሚፈልጉ ለዚህም የሚተጋገዙ ወጣቶች ያስፈልጉናል፡፡ በከፍተኛ የወጣት ምሁራን ፍልሰት የምትጠቃው ኢትዮጵያ፣ በድንዛዜ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶቿን ለማዳን ወጣቶቿን መጠቀም ይኖርባታል፡፡ ጩኸቱን (ብሶቱን) የሚሰማው ያጣው ትውልድ እርስበርሱ መነጋገር መጀመር ይኖርበታል፡፡

 

ዞን ዘጠኝ፤ እንደ አንድ መፍትሄ

ዞን ዘጠኝ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ የመነጋገሪያ (public discoursing) ዞን ነው፡፡ የዞን ዘጠኝ አባላት ከላይ በተነሱት ሐሳቦች ላይ ተመስርተን መነጋገር ባለመቻል፣ ሐሳብን በነፃነት ለመግለፅ ዕድልና ምቹ መድረክ በማጣት ወደዳር የተገፋውን ወጣት በጋራ መወያያ መድረክ ወደመሃል ማምጣት ይቻላል ብለን በማመን ይህንን ጦማር ከፍተናል፡፡ ለዚህም ራሳችን ወደመሃል መጥተን እና ሐሳብ ሰጥተን፣ ሐሳብ ተቀብለን የጋራ የመወያያ መድረክ እንዲፈጠር የቻልነውን አስተዋፅዖ እናደርጋለን፤ ለዚህ ዓላማ ግብ መምታትም ይህንን ፅሁፍ አሃዱ ብለን አቅርበናል፡፡

ሕዝባዊ ውይይት ለተሻለች ኢትዮጵያ፤ እንኳን ወደዞን ዘጠኝ በደህና መጡ!!!

About Zone Nine

Zone Nine is a team of writers on Ethiopian social, economical and political situations.

Posted on June 4, 2012, in Sociopolitics. Bookmark the permalink. 7 Comments.

  1. it is a very intesting & important idea.i have a great appriciation raise such idea that builds this generation in a good manner.so p/s go a head with full strength!!! God bless ETHIOPIA!!

  2. I honestly believe that the debate and dialogue that we initiate will help us to crystallize the real and lived reality of our society from every angle. Both in relation to the past and in connection to the future. Looking forward to the illuminating ideas we’ll be sharing. I sincerely appreciate the initiative and would love to contribute my part …mikiniytum yagebagnalina!!

  3. በፈቃዱ አንዳርጌ
    የእኛ ትዉልድ እሮሮ…..ዛሬም ለ አቶ መለስ ጉልቻ ቢቀየር ወጥ አያሳምርም
    ለዚያ ትዉልድ ፍሬ አምባገነኖችና ጨቋኞች ትዉልድን የማኮላሸት ርዮታቸዉ፣አፋኝ ለሆነዉ የትምህርት ፖሊሲያቸዉ፣የአንድ ለ አምስት አደረጃጀታቸዉ፣ለጎሳ ከፋፍለህ ግዛ ፖለቲካቸዉና ፣ለሃይማኖት፣ለወጣት ማህበሩ፣ለመምህራን ማህበሩ፣ለሰራተኛዉ ማህበሩ ጣልቃ ገብነታቸዉ የእኛ የአዲሱ ትዉልድ ትዉልዳዊ ምላሽ ለመስጠት ስለምን አፈረ? ስለምንስ ቸልተዉና አያገባኝም ማለቱ በዛ? ማን ይሆንስ የትዉልድ ኪራይ ሰብሳቢ? መጨረሻችንስ ምንስ ይሆን ? ምላሽ የሚሹ ትዉልዳዊ ጥያቄወች
    እናቴ እንደምትልኝ ከሆነ አይ የዚህ ዘመን ልጆች ምን ፍሬ አላችሁ ለምትለዉ እናታዊ ስላቅ ምንንነት ስጠይቃት እንዲህ ነበር ያለችዉ “ ዉልደትህ የሚጀምረዉ እዚህ አሁን በሃገሪቱ ሰልጥኖ ባለዉ ስርዓት ስለተወለድክ ነዉ ” የሚል ከመደበኛ ጊዜ አቆጣጠር ወጣ ባለ መልኩ የዚህ ዘመን “ ወያኔያዊ ዘመን ” ፍሬ ስለሆንኩ ነዉ አይ የዚህ ዘመን ልጆች ስትል አንዳንዴም ምሬቷን አንዳንዴም ገረሜታዋን የምትገልፅልኝ፡፡
    እኔም ለዚህ ፅሁፍ የእኛ ዘመን እያልኩ የሰየምኩት ከገዥዉ ቡድን ስልጣን ላይ መቆናጠጥ ይጀምራል፤ በተጨማሪም ዉልደታቸዉ ከገዥዉ ፓርቲ መምጣት በፊት ሆኖ ከዚያ ከ60ዎቹ ትዉልድ የፖለቲካ ማዕቀፍ ዉጭ የሆኑትን ይጨምራል ፡፡ ልማታዊ ገዥዎቻችንም የዚያ ትዉልድ ፍሬ አምባገነኖች እያልኩ እገልፃችኋለዉ፡፡ አንዳንዴ ሳስበዉ የእኛ ትዉልድ እዉነት ትዉልዳዊ ተጋድሎ አድርጓል? ትዉልዳዊ ርዮትስ አለዉ ?ነዉ አንዳንዶቹ እንደሚሉት እዉነትም ትዉልዱ ተኮላሽቷል? ያኔ በአፓርታይድ ዘረኛ አገዛዝ ስትናጥ የነበረችዉን ሀገራቸዉን ከአፓርታይድ መንጋጋ ያወጧት እነ ኔልሰን ማንዴላ፣ዋልተር ሲሲሉ እና ጓደቹ የኢትዮጵያዉያን አልገዛም ባይነት እንደ አርያ በመዉሰድ ነበር እኛዉ ደጃፋችን ድረስ ዘልቀዉ በመግባት የትዉልድ ግዴታቸዉን ለመወጣት የአርበኝነት ተሞክሮዋቸዉን የቀሰሙት፤ የእኛስ ትዉልድ ከነማንዴላ የትዉልድ ሃላፊነት ከፊሉ እንኳ እየተሰማን ይሆን?
    ለእኔ ለሃያ አራት ዓመቱ ፍሬ ልጅ የታየኝ ግን የእኛ ትዉልድ እየመከነ በመጥፋት ላይ ነዉ ባይ ነኝ፡፡እናት ሃገርም የወላድ መካን እየሆነች ነዉ፡፡ ለዚህ ትዉልድ ፖለቲካ ማለት ማስፈራሪያ ሆኖል፤ የአያገባኝም መንፈስ በትዉልዱ ላይ እየሰፈፈ የገዥዎቻችን ልብ እያደነደነዉ ዉሎ ካደረ ይሄዉ ሁለት አስርት ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ መብትን ከማስከበር ይልቅ በዉዴታ ግዴታ መርህ እጁን ለገዡ አሳልፎ ይሰጣል፣የስርዓቱ ምርኮኛም ይሆናል፤ያኔም የባርነት ኑሮዉን ይገፋል፣ባርነትን አምኖ በመቀበል አፈጣጠሩ ለባርነት እንደሆነ እራሱን አሳምኖ “ቀን እሰኪያልፍ የአባትህ ባሪያ ይግዛህ” በሚል አጉል ፈሊጥ የባሪያ ተዋረድ በመፍጠር ለጌቶቹ ባሪያ አዳሪ ይሆናል፤ያኔም ሞቱ የጀምራል እንደ እቃ እንደ አንዱም ይቆጠራል፡፡እዚህ ላይ የፕሮፌሰር መስፍንን “መዝሙረ ባሪያ” እንዲህ ያስታዉሰናል “ባሪያ ምን መብት አለዉ ግዴታ እንጅ” ሁሌም በግዴታ ብቻ መኖር ደግሞ ሰዋዊ አይደለም፤ እንሰሳዊም አይደልም እንሰሳትም መብት አላቸዉ፤ እንግዲህ ከእንስሳ በታች እንጅ ይሄ ድግሞ ያማል፡፡
    የእኛ ትዉልድ ቅድሚያ ምን መሰጠት እንዳለበት ሁሉ ግራ የተጋባ ይመስላል፤ ቆይ በድህነት፣በዲሞክራሲ ማጣት፣በኑሮ ዉድነት፣ በብሄርተኝነት ቋፍ ላይ ላለች ሃገሩ ትዉልዱ የሃገሩን ነባራዊ ሁኔታ ነዉ በቅድሚያ መከታተል ያለበት የአዉሮፓን ሊግን? አዉሮፓዎች እኮ በዲሞክራሲ ስርዓት ተቀኝተዉ፣ በእድገት ልቀዉ፣ በእዉቀት መጥቀዉ ነዉ ለዚህ ዓለምአቀፋዊነት የበቁት፡፡ የሃገሩ የኑሮ ደረጃ መዉጣት መዉረድ፣የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መዉጣት መዉረድ፣ የባህሉ የታሪኩ መበረዝ፣ የወላጆቹ ተስፋ ማጣት ነዉ ማስቀደም ያለበት የሆሊዉድ የፊልም ደረጃ መዉጣት መዉረድ? ብቻ ምን እንደምንፈልግ፣ ወዴት እንደምንሄድ፤ለምንስ ወደዚች ዓለም እንደመጣን ግራ የገባን የትዉልድ ነፋሶች ሆነናል፤ወዴት እንኳ መንፈስ እንዳለብን የማናዉቅ ቅብዝብዞች፡፡ የሃገሪቱ ጥሩ ዜጋ ማፍሪያ እና ትዉልድን መቅረጫ እየተባለ የሚነገርለት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የጥሩ ዜጋ ማፍሪያ ሳይሆን ማፈሪያ እየሆኑ ከመጡ ሰነበቱ፡፡ የከፍተኛ ትምህርት መምህሮችም ሆነ ተማሪዎች ከዕለት ወደ ዕለት አለመተማመናቸዉ ጨምሮ፣ በብሄር ተኮር ስብስብ አንጃ ለይተዉ፣ በሃይማኖት ጥላ ስር ተደራጅተዉ የከፋፍለህ ግዛ ሴራ ሰለባ በመሆን ሃሳባቸዉን እነኳ በፍርሃት ተሸብበዉ በግልፅ መግለፅ ከማይችሉበት ደረጃ እየደረሱ ይገኛሉ፡፡ እኔ እነኳ በቅርብ የታዘብኩትን ላንሳ በሃገሪቱ ካሉ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ከአንዱ ነበር በህግ የትምህርት ክፍል የተማርኩት አንድ ቀን የመማር መስተማሩ ሂደት ላይ ነዉ ክፍል ዉስጥ አንድ ተማሪ ጥያቄ ያነሳል፤ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ጥያቄዉ ፖለቲካዊ ይዘት ያለዉ ነበር ግን የህግ ጥያቄ ለህጉ መምህር ሲቀርብለት የዚህ ትዉልድ ፍሬ የሆነዉ ወኔ ቢሱ የህግ መምህር ጥያቄዉን እንዲህ ሲል ነበር ያለፈዉ “ ይሄ ፖለቲካ ነዉ እንለፈዉ” አስቡት የህጉ መምህር ፖለቲካዊ ይዘት ስላለዉ የህግ ጥያቄ ፖለቲካ ነዉ ብሎ ማለፍ ምን ይባላል? እንደነዚህ ያሉ ወኔ ቢስ መምህሮች ብዛታቸዉን እንግዲህ የትምህርት ሚኒሰቴር ይቁጠራቸዉ፡፡ እንግዲህ እነዚ እራሳቸዉ መብታቸዉን ያለስከበሩ መምህራን ናቸዉ የእኛን ትዉልድ እየቀረፁት ያሉት፤ ጥሩ ቀራጮች አይደሉም? ማን ነበር “ልጅህን ወደ ሚሄድበት መንገድ ምረዉ በሸመገለ ጊዜ ከእርሱ ፈቀቅ አይልም” ያለዉ ? ነፃነት ካስተማርከዉ የነፃነት ሰባኪ ሆኖታገኘዋለህ፣ ባርነት ካስተማርከዉ ባሪያ ሆኖ ታገኘዋለህ ፣ድፍረት ካስተማርከዉ ደፋር ሆኖ ታገኘዋለህ፣ፍርሃት ካስተማርከዉ ፈሪ፣ለነፃነቱ የማይሞት ልፍስፍስ ሆኖ ታገኘዋለህ፤ የእኛስ መምህሮች ወዴት መርተዉንና እየመሩን ይሆን?
    ወደ ዩኒቨርሲቲ ከመምጣቴ በፊት ለእኔ የከፍተኛ ተቋም መምህራንን የምስላቸዉ በእዉቀት የበለፀጉ፣ከሚያስተምሩት ኮርስ የዘለለ እዉቀት የታጨቁ፣ ለሃገራቸዉ የሚቆረቆሩ ሃገራቸዉን የሚዎዱ፣ አንድን ትዉልድ የራስ መተማመኑን ገንብተዉ ለሃገር ሃላፊነት ብቁ የሚያደርጉ ሃገራዊ ወኔ ያላቸዉ ይመስሉኝ ነበር፡፡ ያየሁት ግን ሌላ ፍዬል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲ ሆኖ ነገሩ ከሚያስተምሩት ኮርስ ዉጭ የሰፋ ነገር የሌላቸዉ፣ፈርተዉ የሚያስፈሩ፣ ስለሃገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ምን እዬተሰራ እንዳለ እያዩ እንዳላዩ ሆነዉ “ክፉ ቀንና ቅዝምዝምን ዝቅ ብለዉ ነዉ” እነዲሉ አንገታቸዉን ደፍተዉ ነገን እየጠበቁ ነገ መጥቶ ሌላ ነገን የሚጠብቁ ወኔ ቢሶች ሆነዉ አገኘኋቸዉ፡፡ ይህን ስል ለሃገር የሚያስቡ ልበ ሙሉዎች እና በእዉቀት የተሞሉ የሉም ማለት አይደለም፤ የወኔ ቢሶቹ ሚዛን ይደፋል ለማለት እንጅ፡፡ ይታያችሁ እንግዲህ የእኛን የትዉልድ አናፂዎች እና ይህ ትዉልድ መምከን ይነሰዉ?
    አሁንም የዚህ ትዉልድ ገድል አላበቃም በየመስሪያቤቱ ብትዘዋወሩ የዚህ ትዉልድ መፃጉዎችን ታያላችሁ፡፡ መቸም ይሄ ገዥዉ ደርጅት በዉዴታ ግዴታ ያልተበተበዉ አካል አታገኙም ነጋዴዉ፣መንግስት ሰራተኛዉ፣ተማሪዉ፣ሸኩ፣ቄሱ፣ፓስተሩ በዉዴታ ግዴታ አቢዮታዊ ዲሞክራሲን በግድ አሳምኖ አጥምቋቸዋል፤ ባያምኑም አስፈራርቶ ያኖራቸዋል፡፡አንድ የመንግስት ሰራተኛ ዉሳኔ ለመስጠት እንኳ መጀመሪያ ግምት ዉስጥ የሚያስገባዉ ምክንያት፣ሞራልን፣አግባብነትን ሳይሆን የአቢዮታዊ ዲሞክራሲን ካድሬዎች ፊት ነዉ፤ በዉሳኔዉ ፊታቸዉ የማይጠቁር ከሆነ ዉሳኔዉ ይሰጣል ካልሆነ ግን በልማታዊ ቄሶች የመዝጊያዉን ብረት የሚቃወም በሱ ይብስበታል የሚል ቅዱስ ቃል ይነገረዋል ከዛም መወሰን ይተዋል፡፡ ልብ በሉ ዉሳኔ እነኳ መወሰን የማይችል መፃጉ ትዉልድ የዚያ ትዉልድ ምርቃት፤ ያለ ነገር አይደለም የዚያ ትዉልድ ምርቃት ያልኩት እንደሚታዎቀዉ በሃገሪቱ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ከፍተኛ ሚና አለዉ የሚባለዉ የ1960ዎቹ ትዉልድ ነዉ በአሁኑ ሰዓት በአምባገነንነትም ሆነ በተቃዋሚ ጎራ ያለዉ፡፡ እዚህ ላይ የእኛ ትዉልድ ሚና ሲገመገም ምንም ነዉ ማለት ይቻላል ምክንያቱም የትዉልድን ቅጥር ለማፍረስ ያልተኛዉ የዚያ ትዉልድ አምባገነኖች በእኛ ትዉልድ መካከል አለመተማመን እንዲነግስ አድርገዉ በከፋፍለህ ግዛ ሴራቸዉ ትዉልዳዊ ሚናችን አሳነሱት፡፡ አቢዮታዊና ልማታዊ መሪዎች ነን ባዮችም መተካካት በሚሉት ያለፈበትና የተበላበት ከእነ አክሊሉ ሃብተወልድና ልጅ እንዳልካቸዉ መተካከት ኪሳራ ያልተማሩ የዚያን ትዉልድ በአዲሱ ፖሊሲ እየተካነዉ ነዉ በሚል የአሮጊቶች ሴቶች ጨዋታና የሽማግሌዎች ተረት ሊያታልሉን ይሞክራሉ፡፡በራሳቸዉ አምሳል የተቀረፀ የትዉልዳቸዉን ርዮት አጥምቀዉት፤ በእጅ አዙር ማዘዛቸዉ ላይቀር በእድሜዉ ከእኛ ዘመን በተግባሩ እነሱ ወገን የሆነ ልማታዊ ተተኪiii ስልጣን ላይ ቢወጣ ምኑ ነዉ ለዉጡ? እነዚህንም የትዉልድ ባንዳዎች እራሳቸዉን ለአምባገነኖች አሳልፈዉ ያሳደሩ፣ከአምባገነኖች በሚቸራቸዉ ፍርፋሪ የትዉልዳችን ቅጥር ለማፈራረስ ለሚተባበሩ፣ክብራቸዉን እንደ ይስሃቅ ልጅ ኤሳዉ በምስር ወጥ፣በኮንዶሚኒየም፣በሹመት የለወጡ ኤሳዉያን “በእኛ ዘመን ጊዜ በዚያ ትዉልድ አምባገነኖች ጭንቅላት የሚኖሩ፣ የከፋፍለህ ግዛ ርዮት የሚያራምዱ” የትዉልድ ባንዳዎች እንላችኋለን፡፡ ዛሬም ለ አቶ መለስ እነሆ ያኔ በዘመናችሁ አክሊሉ ሃብተወልድ በልጅ እንዳልካቸዉ ሲተኩ የተባለዉን መፈክር መቸም አትረሱትም ዛሬም ለ አቶ መለስ “ጉልቻ ቢቀየር ወጥ አያሳምርም” ቅመሙን ማስተካከል እንጅ፤ እናም በመተካካት ጠብ የሚል ነገር የለም ባለስልጣኖችዎም የእርሰዎ ጉልቻ እንደሆኑ የታወቃል ይልቅስ የሚበጀዉ ሁላችሁም ዉረዱና ትዉልዳዊ ሚናችን እንወጣበት!
    የአሁኑ ገዥ መደቦች የእኛን ትዉልድ ትዉልዳዊ ሚና ዝቅ በማድረግ አልፎም በማጥፋት የእነሱ ምርቃት እንደሆንን አስገድደዉም ሆነ አሳምነዉ በማንበርከክ እንደ አንድ የተሳካለት ትዉልድ የራሳችን ርዮት ዓለም እንዳናራምድ፣ ተደራጅተን አቤት እንዳንል በአቢዮታዊ ዲሞክራሲ ፀበል ካልተፀበላችሁ ከምኩራብ እየተገፋችሁ ትወጣላችሁ በሚል መርዛማ መርህ ትዉልደዊ ሚናችን አቀጨጩት፤እኛም የቀጨጨዉ ትዉልድ በማለት ትዉልዳዊ ምክነት በእኛ ላይ ሲፈፀም አይተን ዝም አልን፡፡ ግን ዝም ያላልን የራሳችን ሃገራዊ ሚና መወጣት የምንፈለግ፣የሃገር ፍቅር፣የሃገር አንድነት የሚያሳስበን፣የእናንተ ትዉልድ ምርቃት መሆናችን አምነን የማንቀበል፣ ከአባቶቻችን የወረስነዉ አልገዛም ባይነት በዉስጣችን የሚንቀለቀል፣ ለ አምባገነኖች ጀርባችን የሰጠን ሃገራዊ ግዴታ ብቻ ሳይሆን ትዉልዳዊ ግዴታ ያለብን የዚህ ዘመን ፍሬዎች እንዳለን እንዳትዘነጉ!! በቅዱስ መፅሀፍ ነህምያ የኢሩሳሌምን ቅጥር ለመገንባት፣ከብሯን ለመመለስ አቻወቹን ሰብስቦ እንዳከናወወነዉ ሁሉ እኛም የትዉልዳችን ቅጥር ለመገንባት፣የሃገራችን ክብር ለማስመለስ ለአሮጊቶች ጨዋታ ለሽማግሌዎች ተረታችሁ እና መሰሪ የብሄር ከፋፍለህ ግዛ እስተምህሯችዉ ሳንበረዝ፣ሳንበረከክ እልፍ ሆነን ከያለንበት ተጠራርተን ትዉልዳዊ ቅጥራችን እንገነባለን፤የሃገራችንንም ክብር እናስመልሳለን!!
    ነፃ ትዉልድ ይፈጠር!!

  4. Fitsum T.Berhan

    I believe on the very role and importance of public discourse as well as public reasoning.It is when ideas are expressed freely among the public,freedom and development becomes fostering.Hope, it is a good platform to share ideas and pursue that way…!

  5. ውድ በፍቃዱ አንዳርጌ፤ መጀመሪያ ለአስታትህ ያለኝን አክብሮት ከምጋና ጋር ልግለፅ፡፡

    1. ‹የእኛ ዘመን› ብለህ የገለጽከው ትውልድ ላይ ትንሽ ጫን ያልክ መሰለኝ፡፡ እርግጥ ነው ፖለቲካ ማስፈራሪያ ሆኗል፤ የአያገባኝም ስሜት በትውልዱ ላይ ሰፍኗል፡፡ የኔ ጥያቄ፣ እነዚህ እውነታዎች ችግሮች ናቸው ወይስ የሌላ ስር ሰደድ ችግር መገለጫዎች (symptom)? እውነት ትውልዱ በነፃነት የመምረጥ እድል አግኝቶ ነው ስለሀገሩ ጉዳይ ቸል/አያገባኝም ብሎ ጀርባውን የሰጠው? ፖለቲካውስ ለትውልዱ ማስፈራሪያ፣ አይነኬ እና ስልጣን ላይ ላሉ እና ስልጣን መያዝ ለሚፈልጉ ሌላ ጉዳይ (ኳስ፣ ፍቅር…) የሌላቸው ሰዎች ብቻ አድርጎ ማሰቡ ‹የእኛ ትውልድ› እንደው ዝም ብሎ ብርጉግ እና ዝንጉ ስለሆነ ነው ወይስ ሆን ብሎ ታቅዶበት በሀገሩ ጉዳይ ተሳታፊ መሆኑ የሚያስከፍለው ዋጋ መሸከም እንደማይችል በስልት ስለተነገረውና እንዲያይ ስለተደረገ?

    አስታየትህ መጨረሻ ላይ እንዳልከው ቀዳሚው ትውልድ ተረካቢውን የመቅረፅ የቤት ስራውን ከምር ወስዶ የሰራው አይመስልም፡፡

    2. ‹ልማታዊ› ያልካቸው ተተኪዎች ምን ያህል የጉልቻ ለውጥ ብቻ ስለመሆናቸው እርግጠኛ መሆን ይቻላል? የምንመኘውን አይነት የትውልድ ርክክብ ባይሆንም እዛ ለመድረስ ለሚደረግ የማራቶን ጉዞ ቢያንስ እንደመጀመሪያ እርምጃ መቁጠር አይቻልም? ከፊደል ካትሮ የራውል ካትሮ ኩባ ትንሽም ቢሆን አትሻልም?

    ከአክብሮት ጋር!!

  6. አወ ወዳጀ እኔም እልሃለዉ ይሄ ትዉልድ በተፈጥሮዉ ዝንጉና ገለልተኛ ሆኖ ስለተፈጠረ ሳይሆን ስርዓቱ የፈጠረዉ ትዉልዳዊ ምከነት እንጅ….ለዚህ ደግሞ ተጠያቂ ስርዓቱ ብቻ ሳይሆን እራሱ ትዉልዱ የተጫነበትን የፍርሃት ቀንበር ሰባብሮ ባለመዉጣቱ ሊወቀስ ይገበዋል፡፡ እርግጥ ነዉ ይሄን ለማድረግ መስዋትነት ግድ ይላል ለዚህ ድግሞ ሁለት አማራጩች አሉ፤ አንደኛዉ አማራጭ በባርነት፣በፍርሃት፣ በደመነፍስ ከመኖር ወደ ነፃነት በመሄድ እንደገና ትዉልዳዊ ቅጥርን መገንባት …..ሁለተኛዉ አማራጭ ደግሞ ታቅቦ በመኖር ነገን መጠበቅ፡፡ እስኪ ሁላችን እራሳችን እንፈትሽ እራሳችን ለምን ተገዥ አድርገን እየኖርን ነዉ? እራሳችን ለማንቃት፣ ማንነታችን ለመጠበቅ እንተጋለን? አየህ ወዳጀ ችግሩ ሁሉ የተያያዘ ሰንሰለታማ ነዉ፤ ከምንጩ ካደረቅነዉ ግን ታሪክ መስራት ይቻላል፡፡
    ሰለመተካካቱ ግን አሁንም ቢሆን እኔ ዉሃ አይቋጠርም ባይ ነኝ…እስኪ በመተካካት ወደ ስልጣን የመጡትን እንደ ዋቢ እንዉሰድ የኋላ ታሪካቸዉ ሲታይ አንድም ህዝባዊ መሰረት የሌላቸዉ ሲሆን በሌላ ጎን ደግሞ እስካሁን ለስርዓቱ ባሳዩት ድርጅታዊ ታማኝነት ጉርሻ ነዉ ባይ ነኝ፡፡ እነዚህ ልማታዊ ተተኪወች እንደ (መንግስት አባባል) በራሳቸዉ ርዮተ ዓለም ተመርተዉ ሳሆን ለስልጣን የበቁትና የሚበቁት በነባር ታጋዮች አምሳል የተቀረፁ ምስለኔዎች ናቸዉ፡፡ ይሄ ደግሞ ጉልቻዉን እንደመቀያየር ነዉ የምቆጥረዉ ምክንያቱም የዉሰት ርዮታቸዉ ምንም ሊያራምድ ስለማይችል ነዉ፡፡ እርግጥ ነዉ ነባር ፊት ከማየት አዲስ ፊት ማየት ተስፋ ሊፈነጥቅ ይችላል፤ አዲስ የለዉጥ ስርዓት ሊተኩ ግን አይችሉም፡፡ ለዛ ነዉ ስልጣን ይልቀቁና እንደ አንድ ወሳኝ ትዉልድ አዲስ ትዉልዳዊ ቅጥራችን እንገንባበት የምለዉ፡፡

  7. zone 9
    bertu bertu Tiru jimrr new. Yaltedefere yaltemokere hasab new. egziabher yrdachihuu!!

Leave a comment